….በዚህም’ኮ መንገድ አለ! (አሰፋ ጫቦ )

….በዚህም’ኮ መንገድ አለ!

 Addis Admass

መንደርደሪያ
የዚህ ጽሁፍ ዋና አላማ በሚያዝያ ወር 2008 በዋሺንግቶን ዲሲ አካባቢ የትዝታ ፈለግ መጽሐፌን ለማስመረቅ በተዘጋጁት ሁለት መድረኮች የታዘብኩትን ለማካፈል ነው::
ከሚያዚያ 14 እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2008 በዋሺንግቶን ዲሲ አካባቢ በተለይም ሲልቨር ስፕሪንግ ሰነበትኩ። የጉዞዬ ዋና ምክንያት የትዝታ ፈለግ የተባለ የስብስብ ስራዬ ወደ መጽሐፍነት ስለተሸጋገረ አደባባይ ለማውጣት ነበር። ማስመርቅ ልንለውም እንችላለን፡፡ እዚህ አሜሪካ Book Signing Event ይሉታል።
ሁለት ወዳጆቼ መድረኩን አዘጋጁት። ሚያዝያ 16 ቀን 2008 አርታ አሌ ሆቴል ያሬድ ጥበቡ ወዳጆቹን ጋብዞ ያዘጋጀው አንዱ ነበር። ሌላዉ ሚያዝያ 21 ቀን 2008 ታዋቂዋና የማከብራት ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ያዘጋጀችው ነው። ያሬድ ያዘጋጀው መድረክ ላይ ብዙ ገጠመኞችም ነበሩ። የሆቴሉ ስም ራሱ፤አርታ አሌ ሆቴል፤  ለኔ ታሪካዊ ነው:: ከአፋር መሬት ከርሰ-ምድር የሚንተከተከው እሳተ ጎሞራ ስፍራ ስም ነው። የጓደኛዬ ልጅ፤ዶሊ፤ሀች-አምና ጎብኝታው ያነሳችውንና የተነሳችበትን ምስል Facebook ላይ ለጥፋ አየሁት:: ፈረንጅ ጎብኝዎች የለጠፉትን ከማየት በላይ አላጤንኩትም ነበር። ከኔ (ከኛ?) ይበልጥ ፈረንጅ ያውቀዋል እንደ ማለት ይመስለኛል። እዚህ አሜሪካ ታዲያ የሆቴል ስም ሆኖ ብቅ አለ::
አራት በር ያለው ዘመናይ ምግብ ቤት ነው። ይበልጥ የገረመኝ ባለቤቱ፤ዶክተር ሰለሞን፤ ሐኪም ነው። ስለደነቀኝም ምክንያት ፈልጌ ደጋግሜ አነጋገርኩት። አለባባሱ፣አነጋገሩ፤የቃላቶቹና ሐሳቦቹም ምርጫ፤አገላለጹ (Body Language) ጭምር የአሜሪካን ዘመናይ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አይነት ሆነብኝ። ለመሆኑ ስንቶቻችን እንሆን ተፈጥሮ በለገሰን ስጦታ ሳንሰማራ ቀርተን እንዲህ ጓደኛ ወይም የሰፈራችን ልጆች በሔዱበት ፈለግ የተከተልነው? አሰኘኝ። በኔና  በዶክተር ሰለሞን ዘመን፣ ዝንባሌህ/ተሰጥኦህ እንዲህ ነውና ይህንን ወይም ያኛውን ብታጠናው/ብትማረው ይሻላል የሚል አልነበረም። የአሁኑን አላውቀውምና የምለው ብዙም የለኝም።
አንድ ልረሳው የነበረው ነገር!! በስራ ምክንያት ከመሔዱ በስተቀር ዶክተር ሰለሞን አፋር አይደለም። ይህ ደሞ በመጠኑም ቢሆን ሰፋ ያለ ስዕል መሳል የመቻልን አዝማሚያ የሚጠቁም ይመስለኛል። በተለይም ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሆቴሉ፤የንግድ ድርጀቱ፤የመንግስት መስሪያ ቤት ስሞች፤በተለይም የኢትዮጵያ ፖሊስና ወታደር ማዕረግ ከኢትዮጵያ ተፋቶ፣ የእንግሊዝና የአሜሪካ ስም በሆነበት ዘመን መሆኑ የበለጠ ክብደት የሚሰጠው ይመስለኛል።

ትዝብቱ
መጽሐፉ ምረቃ ላይ ንግግር፣መግለጫ ሊባልም የሚችል ይመስለኛል፤አደረኩ። የመጽሐፉ ስብስብ 28 ምእራፎች አሉት። ዝርዝሩ ውስጥ አልገባሁም። አብነት ይኖራቸዋል ያልኩትን ጥቂቶች አነሳሁ። ከዚያ በፊት ግን መጽሐፉ የተዘረጋበትን ንፍቀ-ክበበ፤ትልቅ ምስል፤(Vista,Big Picture) ለማሳየት ሞከርኩ። መጽሐፉ ውስጥ ያሉት ምናልባት ከአንድ ሁለት በስተቀር መድረኳ ኢትዮጵያ ነች። ስለዚህ ከኢትዮጵያ፣ማለትም ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር አዛምጄ ለማቅረብ ሞከርኩ። በዚህ አጭር ጊዜ፤በዚች በአንድ መጽሐፍ ሰበብ የኢትዮጵያን ታሪክ መዳሰስ እኔም ሆንኩ ማንም ሊያደርገው የሚችል አይመስለኝም። የኢትዮጵያን ህዝቦች ታሪክ ትልቁን ምስል በዚህ በተነሳው ጉዳይ ዙሪያ ለመሳል ሙከራ ነበር። ቢቻል ታሪኳን የምናይበት ሰፋ ያለ ትልቅ መነጽር ለመስራት ሙከራ መሆኑ ነው።
እዚህ ላይ አንድ የግርጌ ማስታወሻ (footnote) የሚሉትን አይነት ነገር ማለት እፈልጋለሁ። የኢትዮጵያ ታሪክ ስል እኔ ታሪክ ነው የምለውን አይደለም። በተቻለ መጠን ተጽፎ፤ተመዝግቦ፤ዛሬ ምድሪቱ ላይ ባሉት ሕዝቦችዋ ላይ የሚንጸባረቀውን እውነት ነው። ሕዝቦችዋ ደግሞ የብዙ ዘመናት አነባበሮ ናቸው። ግምቴና ምኞቴን አይደለም። ለፖለቲካ ፋይዳ ተብሎ በግምት፣ተጣሞም፣ተንሸዋሮም ሲቀርብ አይና ወይ ይደንቀኛል፤አንዳንዴ ያስደነግጠኛል። መጽናኛዬ ግን “ይኸ ሀላፊና ረጋፊ ስለሆነ ትዕግስትና ጊዜም ስጠው!” የሚለው ነው። አጋጣሚው ሲገኝ ደግሞ አውራ ጎዳናው በዚህ በኩል ነው ብዬ ከመጠቆምም ወደ ኋላ አልልም። ወደ ኋላ አለማለት ነው!! ሆኖም  ያኛው ወገን የሚለው ውስጥም’ኮ አንዳንድ እውነት አይጠፋም ማለቱ ጥሩ ነው። በር አለመዝጋት! አለመቀርቀር! ለማለት ነው። የእውነቱ ብቸኛ ባለቤት (Monopoly) ያለው የለም!
ሁለቱም አውዶች ላይ በአካል ቋንቋ (Body Language) ሆነ በቃላት የተገለጠው ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ነበር ለማለት የምችል ይመስለኛል:: በጥሞናና በተመስጦ የማዳመጥ ነገር በእያንዳንዱ ፊት አያለሁ:: አነባለሁ! ቆሜ ስለምናገር፤ተቀምጠው ስለሚያዳምጡ፣ ለማስተዋል ከሁሉም የተሻለ እድል ነበረኝ። በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ ኦርቶዶክሶቹ “አልዕሉ አልባቢክሙ ሀበ እግዚአብሔር….” የሚሉት አለ። ልቡናችሁን አንቅታችሁ/አንግሳችሁ አድምጡ ለማለት ይመስለኛል። ያንን ያየሁ ይመስለኛል!
ጣይቱ ማእከል የማደርገውን ገለጻ ጨርሼ ቁጭ ስል አጠገቤ የነበረው አያሌው ከበደ፤“ጋሽ አሰፋ ሰው’ኮ ቆሞ ያጨብጭባል!” ሲለኝ አፍሬና ደንግጬ ተነሳሁ። ፈረንጆቹ Standing Oviation የሚሉት ነው። ከዚያም ወደ ጥያቄና መልስ ወይ፤ወደ አስተያየት መስጠት ተኬደ።
በጥያቄና መልሱ ወቅት ሁለት ነገሮች/ ነጥቦች ጎልተው የወጡ ይመስለኛል። አንደኛው፤ ከጥያቄ ይልቅ የአስተያየቱ አይነት ተቀራራቢነት ነበረ። ”…ዛሬ የነገርከኝ አዲስ ነገር የለውም! ያው የማውቀውን ወይም አውቃለሁ የምለውን የአገሬን ታሪክ ነው። አንተ፤እንዲህ አቀራርበህ፤ፈተህ፣አቃለህ ተርጉመህ ስትነገርኝ እንዴት አባቴ ሆኜ ነው እኔ እንዲህ ሳላይ የቀረሁት!” የሚል ነው። ቃል በቃልም ባይሆን መንፈሱ ይኸው ነበር። እንዲያ ተከፍቶ ሳይታይ በባከነ ጊዜ/ ዘመን መቆጨት ያለበት መስሎ ታየኝ። ሁለተኛው ክፍል ደግሞ “ነገም ይነጋል! መንገድም፣ አማራጭ መንገድም  ሞልቷል። ያንን የመፈለግ እንጅ አለቀ-ደቀቀ የሚያሰኝ ነገር የለም!” የሚል ነበር። በተስፋና በይቻላል መልክ መመልከት ልንለው የምንችል ይመስለኛል። Positive Thinking የሚሉት። “ጥሩ ተመኝ ጥሩ እንድታገኝ” እንዲሉ።
የሰዉ ስብጥር ራሱ ገረመኝ። በእድሜ ከ50 በላይ የምንሆነው እኔን ጨምሮ 10% ብንሆን ነው። በአብዛኛው ምሁር፤ሊቀ ሊቃውንት ሊባል የሚችለው ስብጥር መስለኝ። ይህን ያውቅሁት ያሬድ ጥበቡ ያዘጋጀው መድረክ ላይ ነበር:: መጽሐፉን ለገዙት ፊርማና ትንሽ አስተያየት በመጻፍ ላይ ሳለሁ፤ “ለአቶ—” ብዬ ስጀምር፣ ያሬድ አንድ ሁለቴ፤ “አሴ! ምን ነካህ? እሱኮ ዶከተር ነው!” ሲለኝ ነበር፣“ማእረግህን ምን ልበል?” ወደ ማለት የገባሁት፡፡ እንደገመትኩት አንድ አስሩ ያክል በየመስካቸው ዶክተሮች ነበሩ።
ሌላው የማውቀው የሚያውቀኝ ብዙ ሰው አገኘሁ። ማእከላዊ የማውቃቸውን ምስማኩ አስራትንና መስፍን ቡልቻን አገኘኋቸው፡፡ መስፍንን ረስቼው ኖሮ ደጋግሞ “ጋሽ አሰፋ ምን ነካህ ?! መስፍን ቡልቻኮ ነኝ!” አለኝ። ለካስ አንዴ በጻፍኩት መጣጥፍ ላይ መስፍን ቡልቻንና ሳምሶን ሙላትን አንስቼ ነበር። ቀና ብሩህ የመርካቶ ነጋዴ ልጆች ነበሩ። ሳምሶንን የዛሬ ስንት አመት  Cambridge, Massachussettes  አግኝቼዋለሁ፡፡ የኮከበ ጽባህ ልጆችን፣ ከኔ ቀደም ሲል የነበረውን ኢሳያስንም ጭምር አገኘኋቸው፡፡ አንድ የአርባ ምንጭ ልጅም አገኘሁና፤ “ስለ አርባ ምንጭ አልጻፍኩም ይቅርታ፤ስለ ጋሞና ስለ ጨንቻ ጽፌአለሁና በዚያ ተካካስ!” አልኩት።
ጣይቱ ማእከል ሌላው የደነቀኝ፤በተለምዶ በየወሩ የግጥም ንባብ አለና የዚያን ማታ የተነበበው ነበር። ገጣሚዎቹ ወጣት ልጆች ነበሩ። ግጥማቸው ምራቁን አጣጥሞ የዋጠ፤ክንፍ ያለው፤ወደ ላይ ወደ ሕዋው የነጠቀ ፤የመጎርጎር እግር ያለው፤ ሰንጥሮ ወደ እመቀ እመቃት ወርዶ ጉዳችንንና ልእልናችንን የሚያበስር ነበር።
ከሁሉም በላይ የጀነራል መርዕድ ንጉሴን ልጆች፡- አስተዋይንና እህቱን አገኘኋቸሁ፡፡ አስተዋይ መርዕድ ከኔ ጋር ማእከላዊ፣እታች ግቢ፣7 ቁጥር፤ ጨለማ ቤት አብሮኝ ታስሮ ነበር። የትዝታ ፈለግ ከተዘከረላቸው ሰዎች አንዱ ጀነራል መርዕድ ንጉሴ ነበሩ። ትንሽ ተላቀስን!! የልባችን ሳይደርስ በሰው ብዛት ተለያየን። የእለቱ ሙሽራ አይነትም ስለነበርኩ ያንንም ይሕንንም ሳነጋግር በቂ ጊዜ አልነበረኝም። ለዚያውም ከአዳራሹ ሰአት እላፊ ደርሷልና ውጡ ተብለን ነበር የተለያየነው።
ያን’ለት ማታ ኩኩ ሰብስቤንም አገኘኋት። በዝና እንጅ አንተዋወቅም። የመጣሁ ሰሞን ወንድምዋ DC ምን የመስለ ምሳ ፖቶማክ (Potomac) ወንዝ ዳርቻ ጋብዞኝ ነበር። ኩኩን በቅርበት የተዋወቅሁት ራት ላይ ነበር።
ራት-ምሳ ግብዣ እንደ ልብ ነበር። 10ሩን ቀን መኝታዬ ጋ የምደርሰው ሁሌም ከዘጠኝ ሰአት በኋላ ነበር። አንዱን ምሸት፤ በማላውቀው ከተማ፤ዝናብ እየጣለ፤በማላውቃት፤በማታውቀኝ ሴት መሪነት (GPS) ወደ ቤት ስሄድ ፖሊስ አስቆመኝ። መኪናዬ (የተከራየሁት) የተሰመረለትን ስቶ ሳይዋዥቅ የቀረ አይመስለኝም፡፡ እንደተለመደው መንጃ ፈቃድ ጠይቆኝ “ስትጠጣ ነበር?!” አለኝ። “አዎን!” አልኩት “ምን?!” ሲለኝ “ውሃ!” ስል መለስኩለት። እውነቴን ነበር። ያን ያህል የምውደው ዊስኪ Johny Walker ጭምር ጣእሙ ጠፍቶብኝ መጠጣት ካቆምኩ ዘመን የለውም። ፖሊሱ ታዲያ ጢም ብሎ ሰክሮ ይንገዳገዳል። ጨንቻ፤“ድንቄም! ዋሪቴም! ዋኬኔም!” የሚሉትን አስታወሰኝ። ዋሪቴ ማን እንደሆነች አላውቅም። ወደ ዶርዜ መሔጃው ላይ፤ከመሪ ጌታ ብቃለ ከበበው ቤት ዝቅ ብሎ፣ጋሽ ጣሴ ዋኬኔ እንደነበረ አውቃለሁ። “ድንቄም ሕግ ማስከበር!” ለማለት ነው።
ብቻ ራት ለመብላት ሔድንና ኩኩም መጣች። ”አንተ ለመሆኑ ከበዛወርቅ አስፋው በስተቀር ሌላ አርቲስት ታውቃለህ?” ብላ ጀመረች። የበዛወርቅን የትዝታ ዜማ “እስላም ክርስቲያኑን እንዲህ ያዋሐደው፤ማተቡ ነው፤ከጥንት አብሮ የገመደው!” የሚለውን ደጋግሜ አንስቼው ኖሯል።  “የአንቺንም ዘፈን በጣም እወደዋለሁ!” አልኳት። “መች በአደባባይ መሰከረክ!?” አለችኝ። “እንዲያውም ከአርቲስቶቹ ሁሉ የምትቀርቢኝ አንች ነሽ!” አልኳት። “ለምን?” ብትለኝ “አንቺም እኔም የጨንቻ ልጆች ነንና!” አልኳት። አባትዋ፤ደጃዝማች ሰብስቤ ሽብሩ፤እኔ ልጅ ሳለሁ የጋሞ ጉፋ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ነበሩና አንድ ክረምት ልጆቻቸው ጭምር መጥተው ማየቴን ነገርኳት። ተማመንና ሁለት የጨንቻ ልጆች ተባብለን ተዛመድን። ኩኩ ሰብስቤ፤የተዝናናች፣እንደ ልብዋ የምትናገር፣የምትጫወት፣የምትጫወተውን የምታውቅ (small Talk)፣ነጻ የሚሏት አይነት (Cosmopolitan) አርቲስት ሆና አገኘኋት። አንጎራጎረችልንም!
ቀኑ አርብ ምሽት፤የኦርቶዶክሶቹ ስቅለት ዕለት ነበር። የገረመኝ አንድ እኔ ያለሁበት ማእድ ሲቀር የተረፈው የጾም ራት ነበር። ያልጠበኩት ስለነበር ገረመኝ። ከዚህ እኔ ያገኘሁት ትምህርት፤ሌላውን በራሳችን መመዘኛ ብቻ አለመለካቱ ጥሩ መሆኑን ነበር።
ከእለቱ ቅኝት፤ማለትም ከመጽሐፉ ምረቃ ጋር የማይሔድ ነገርም ገጥሞኝ ነበር። ያንን የመጨረሻው ጠያቂ ሆኖ የመጣው በዕውቀቱ ሥዩም ነበር። “ኢ.ጭ.አ.ት (የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል) የሚባል የደርግ ዘመን የፖለቲካ ድርጅት ሊቀ መንበር ነበርክና ስለዚያ አስረዳን” አለ። አንድምታዉ “ጠባብ ብሔርተኛ ሆነህ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ታወራለህ!” እንደ ማለት መሰለኝ።
መጀመሪያ የመጣልኝ Non Sequitur ነው። Non Sequitur ማለት ”ይህ ከዚያኛው አይከተልም!” እንደ ማለት ነው። የህግ ባለሙያ ነኝ። በዚህም ላይ ዩንቨርስቲ የመጀመሪያ አመት ይሁን ሁለተኛ ተማሪ ሳለሁ  ፍልስፍና 101 የሚባለውንም ወስጃለሁ። ይህ 101 ደግሞ ሎጂክ (Logic) የሚሉት ነው።
በዕውቀቱም ዩኒቨርስቲ ተምሯል። ያ 101 አሁን መኖር አለመኖሩን አላውቅም። ብቻ ሰለ ኢ.ጭ.አ.ት አስረዳሁ! “ለመሆኑ ከዚህ ጋር እንዴት አገናኘኸው?” አላልኩም። ያ ተገቢው መልስ የነበረ ይመስለኛል ።በእውቀቱን አምና ዲሲ የሔድኩ ጊዜ ከሌሎች “ጋሽ አሰፋ ያንተን ጽሁፍ እያነበብን ነው ያደግነው!” ከሚሉት ብዙ ወጣት ምሁራን ጋር አግኝቼው ነበር። እንዲያውም ያንተ ጽሁፍ ስብስብ በሙሉ አለኝ ብሎኝ፣ ይህ መጽሐፍ የማድረጉ ሀሳብ የመነጨው ከበዕውቀቱ ነበር። ኢትዮጵያ ሲመለስ እንዲተባበሩት የልጄንና የእህቴንም ስልክ ቁጥር ሰጠሁት። ከዚያ በFacebookና በemail ብለው- ብለው  ጠፋ! ጠፋ! በሰጠኝ ስልክ አንዴ ስደውል፣ አንድ ሰው ጸያፍ መልስ ሰጠኝና ተውኩት። አሁን እንደገና አሜሪካ መጣ ሲሉ ጊዜ ስልክ ቁጥሩን ፈልጌ ስደውል ዘጋብኝ። ለካ መጽሀፍ ሊያሳትም ኖሯል።
አሁን ሳየው ለካ በዕውቀቱ እኔ “ማነው ነፍጠኛ?” በሚል የጻፍኩትንና በቃለ መጠይቅም የሰጠሁትን ቃል በቃል ጠቅሶ፣ለአጼ ምንሊክ መልሶ ማቋቋሚያ (Rehabilitation) በሚመስል ተጠቀመበት። መጀመርያ ነገር፤ የኔ “ማነው ነፍጠኛ?” መንፈስ ማንንም መልሶ ለማቋቋም ሳይሆን ታሪክ በተገቢ መልኩ እንዲታይ ነበር። ምንሊክም ሆነ ማንም እውነተኛና ታሪክ ነጋሪ እንጅ መልሶ ማቋቋምን የሚፈልጉ አይመስለኝም። በዚህ ላይ ከእገሌ ወሰድኩ ማለት ስነምግባር ብቻ ሳይሆን ሕግም ነው። እኔ ሕግ ትምህርት ቤት የዚህ ፕላጄሪሲም (Plagerisim) የሚባለው ለ4 አመት ዳኛ ነበርኩ። “ከእገሌ ወሰድኩ” ሳይል ፤የግርጌ ማስታወሻ (footnote) ሳይለጥፍ የሚጽፍ ተማሪ ለመቅጣት የተቋቋመ Honer Court ይባል ነበር።
ይህ ደግሞ ሌላ አስታውሰኝ። የትዝታ ፈለግ ውስጥ የኔይቱ ጀግና የሚል ስለ ዘውዲቱ አስማረ የተጻፈ አለ። አንድ ሌላ ሰው ደግሞ “የኔ ጀግና!” በሚል መጽሀፍ ጽፏል ተባልኩና ያ መጽሐፍ ሰሞኑን ሊመጣልኝ ነው። ”ከአሰፋ አገኘሁ” አይልም። ሕጉ ይቅርና ከእገሌ ወሰድኩ ነውርነት የለውም። ወጥ ሐሳብ ያለን ጥቂቶች ነን። አብዛኛዎቻችን ሌላው ከተናገረውና  ከጻፈው እያዳበርን ነው።
በዕውቀቱ ሥዩም የትና የት ሊደርስ የሚችል ጸሐፊ፤ከሁሉም በላይ ገጣሚ ነው። ግጥሞቹ፤ቢያንስ እኔ ያነበብኳቸው፣የመጠቁና ፍልስፍና የሚሞክራቸው ናቸው። በእውቀቱ እንዲባክንብን አልፈልግም። ተስፋዬ ገብረአብ ምን የመሰለ፤የትና የት ይደርሳል ያልኩት ደራሲ ባከነብን። አልባሌ፤አላፊ ጠፊ፤ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ የባከነብን ይመስለኛል። ለዚህ መድኅኒቱ ለጥበቡና ለራስ ታማኝ መሆን ነው። ለነዚህ ታማኝ የሆነ ዝንተ አለም ታማኝ ሆኖ ይኖራል።

ትምሕርቱ
እኔ ከዚህ መጽሐፍ ምረቃ ዘላቂ ትምህርት ያገኘሁ ይመስለኛል። ነገር ዓለሙ ሁሉ ሰበብ-አስባብ ይፈልጋል ልንልም የምንችል ይመስለኛል። በዚህ በሳይንሱ ክሪቲካል ማስ (Critical Mass) የሚሉት አይነት መሆኑ ነው። “ሰኔና ሰኞ!” ሲገናኝ እንደ ማለት ነው።
በክርቲካል ማስ ውሃ ሲፈላ ይተናል። ሲቀዘቅዝ ደግሞ ወደ በረዶነት ይለወጣል። ያንን ሲያሞቁት ወይም ሲያቀዘቅዙት ደግሞ ውሀ ይሆናል። የኔ አንዲት ስብስብ መጽሐፍ ያንን ያክል ”ሰኔና ሰኞ“ ሆናለች ለማለት አይደለም። አንዳች ነገር ሊሆን ወይም ላይሆን ሰበብ አስባብ ይፈልጋል ለማለት ነው። ከዚህም ተነስቼ የትዝታ ፈለግ ሰበብ አስባቡ ሆና፣ ያው ውስጣችን የታመቀንና ሊወጣ ምክንያት ሲሻ የነበረውን አወጣችው ወይም ለመውጣቱ ምክንያት ሆነች ለማለት ነው።
ለዚህ እስቲ ሁለት አባባሎችን እንውሰድ። አንደኛው “ጠርጥር ገንፎም ውስጥ አይጠፋም ስንጥር” እና  ሌላው “ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ!” የሚሉትን። ይህንን በዘመናይ ቋንቋ Negative versus Positive thinking ብለን ልናይ እንችላለን። ነገርን በቀና መንፈስና አጣሞ በመተርጎም ውስጥ ያለ ልዩነት መሆኑ ነው።በዚህ “ገንፎም ውስጥ አይጠፋም ስንጥር!” ላይ June 26,2016 አንድ በኔ ላይ  የደረሰ ምሳሌ ልስጥ። አንድ ሰው፤እዚህ ስሙን መጥራት የማልፈልገው፤ Facebook ላይ “ወዳጅ ልሁን “ብሎ ጠይቆኝ “እንኳን ደህና መጣህ!” ብዬ ተቀበልኩት። ቀጥሎ “ጤንነትህ?” ሲለኝ “እዚህ አሁን በጋና ወበቅም አለው” አልኩኝ። “ለመሆኑ የት ነው ያለኸው?” አለኝ.” Dallas Texas USA” አልኩት። “አሜሪካ ነው?” አለኝ::”.USA አሜሪካ ማለት ነው” አልኩኝ። “USA አሜሪካ መሆኑን ከአንተ በፊት አውቃለሁ!” አለኝ። በኔ ግምት ይህ “ገንፎ ውስጥ አይጠፋም ስንጥር” ሳይሆን ገንፎው ውስጥ ስንጥር ጨምሮ “ይኸው ስንጥር አለበት!” ብሎ ማስረጃ ለማቅረብ እንደ መሞከር ነው። አንዳንዱ የፖሊቲካ አስተያየት ሳዳምጠው፣ የዚህ ጣእም/ ምሬት/ሬት ያለው ስለሆነ ይሰውረን ነው። እኔ ይህንን ግለሰብ ከወዳጆች አንባ ሰርዠው ተገላገልኩ። ይሰውረን ማለት ነው የሚበጀው።

ገልጠን ብናየው
ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝን ለማስረዳት ገጽ 3 ላይ የግርጌ ማስታወሻ ብዬ የጠቀስኩትን በድጋሚ እንድትመለከቱት እጠይቃለሁ፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ንግግር፣ንትርክ፣ጭቅጭቅ፣ዉዝግብ ውስጥ በአብዛኛው ይህንን የማየው ይመስለኛል። ጤነኛውን በሽተኛ ነህ ብለው ነገሩት። ጉንፋን የያዘው፣በነጭ ሽንኩርት፤ በጦስኝ፤ግፋ ቢልም አስፕሪን ወስዶ እንዳይድን ካንሰር ይዞሃል አሉት። ካንሰር ደግሞ ቀዶ ጥገናን የሚጠይቅ በሽታ ነው። በአብዛኛው ቀሳፊ በሽታም ነው። ነገሩ ያለው መጀመሪያውን ታመሃል ያለው ሐኪም የህክምና፤የሕመም አይነት የመለየት፣የመቻል ባለሙያ አለመሆኑን የመረዳት ጉዳይ ነው። ግፋ ቢል የዚህ በዘር ከፋፍለህ ግዛው የቅርብ ምንጩ የሙሶሊኒ የጣሊያን የምስራቅ አፍሪቃ ግዛት (Africa Orientale Italiana) መሆኑ የመረዳትና የማስረዳት ጉዳይ ነው። ጉንፋንና ካንሰርን ለይቶ የመረዳት ጉዳይ ነው።
ታዲያ በዚህ በየድረገጹ በተለይም የአማራና ለኦሮሞ መብትና ግዴታ እንታገላለን የሚሉት የሚገርመው ክርክራቸውና አስተያየታቸው ከኢትዮጵያ የተፋታ መሆኑ ነው። ኦሮሞ ከራያና አዘቦ ጀምሮ የሌለበት ክፍለ ሐገር የለም። ኦሮሞ በኢትዮጵያ በሕዝብ ቁጥር አንደኛው ነው። በምርጫ እንኳን ቢኬድ አብላጫው ኦሮሞ ስለሆነ  የኦሮሞ መንግስት ነው የሚሆነው። ከዘመን መሣፍንት ጀምሮ፤ ልጅ እያሱን፣ንግስት ዘውዲቱን፤ኃይለ ሥላሴን፣ጀነራል ተፈሪ በንቲንና መንግስቱ ኃይለማርያምን ጨምሮ መሪዎቻችን ኦሮሞዎች ነበሩ። ከ108 የደርግ አባላቱ ውስጥ ግማሽ ያክሉ ኦሮሞዎች ነበሩ። ከኢህአዴግ ወዲህ ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንቶችና ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን የሚያስተዳድሩት ከንቲባዎቹ ኦሮሞች ናቸው። ያም ሆኖ በክርክራቸው፤ሙግታቸው፤ጭቅጭቃቸው ውስጥ የኢትዮጵያን ስም አይጠሩም። ይህ እንዲህ ከፍተው ሲያዩት ግራ የሚያጋባ ነው። ወይም አዲሱ የኢህአዴግ ክትባት፤ ካንሰር ታመሃል የሚለው እውነቱን ፍቆታል ማለት ነው። “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! የሚለውን የምሰማው የሸገርን 102.1 FM ራዲዮ ስከፍት ብቻ ነው። ስንጥር ገንፎ ውስጥ ጨምሮ “ይኸውና!” ማለት መስሎ ይታየኛል።
ሌላው የፖለቲካ ሊቃውንት ነን የሚሉ ሁሉ ሲናገሩም ሲጽፉም የሚክዱት የ17ቱን አመት የደርግ ታሪክ ነው። የማያከራክረው ግፉና ጭካኔው ላይ ያተኩሩና ሌላውን ይክዱታል። ብዙዎች ደግሞ የራሳቸውን ጉድ ለመሸፈን ደርግን መሽሎኪያ ቀዳዳ (Escape Goat) ሲያደርጉት ይታያሉ። ደርግ የሰራቸው ዘለዓአለማዊና ታሪካዊ ድርጊቶች አሉ። ኢትዮጵያን ሬፑብሊክ አድርጓል። በሐይማኖት እኩልነት የእስልምና ተከታዮችን በአላት ብሔራዊ በአል አድርጎታል። በየካቲት 25,1967 የገጠር መሬት አዋጅ ሕዝቡን ፤በተለይም የደቡብ ኢትዮጵያን ህዝብ ከዘመናት ጢሰኝነት፤ገባርነት ገላግሏል። የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ ማለት ደግሞ አብዛኛው ኦሮሞ ማለት ነው። የካቲት 25,1967 የምኒልክን የአስገባሪነት ቀንበር ደመሰሰ (Null and Void) ማለት ነው:: እርግጥ የሚቀጥል የመብት ፤የነፃነት የብሔረሰብ ጥያቄዎች አሉ።
ያንን የምንጀምረው ከባዶ፤ከዜሮ ሳይሆን ደርግ ባጎነጸፈን ድል ላይ ተመስርተን ነው። 17 አመት የኢትዮጵያን፤ያንድ ሀገርን ታሪክ መካድና “አላየሁም! አልሰማሁም!” ማለት ለፖለቲካ ንግድ ካልሆነ በስተቀር ፋይዳ ያለው አይመስለኝም። የጤናም አይመስለኝም!
ሕዝቡ ግን እውነቱን ያውቃል። ያለፈ ዘመን ቁስል፤ የሻረ ቁስል መርቁዟል ያሉ፤የአገራቸውን ስም በአደባባይ መጥራት ያልፈለጉ፤”የጋራ ቤታቸውን” የካዱ የት እንደደረሱ የትላንትናዋ ዩጎዝላቪያ፤የዛሬይቱ ብጥቅጣቂ ወይም ወደዚያ በማምራት ላይ ያለችውን ሶሪያን ልብ ይሏል። ትምህርቱ  ከታሪክ መጽሐፍት ሳይሆን ፊት ለፊታችን ተገትሯል! ተወጥሯል! ተሰትሯል!

ሲጠቃለል
የትዝታ ፈለግ ከጠበኩት በላይና ውጭ ሔዶብኛል። ምን ጠብቀህ ነበር ብባል መልስ የለኝም። መጀመሪያ በመጽሐፍ መልክ መታተሙ ራሱ የኔ ሐሳብ አልነበረም። “የአንተን ጽሁፍ እያነበብን ነው ያደግነው” በሚሉ ወጣቶች አነሳሽነት ነበር። እዚህ አሜሪካ በምረቃው ላይ የሆነውን ለመግለጽ ሞክሪያለሁ። በስልክ፤ በFacebook, በemail በMessenger የደረሰኝ መልዕክት ቁጥር ስፍር የለውም።
መልእከቱ ከመላው አለም ነው ለማለት እችላለሁ። ከኢትዮጵያ፣ከጨንቻ ጀምሮ ደሴ፤ባህር ዳር፣ ጎንደር፤መቀሌ ይገኙበታል።
የትዝታ ፈለግ ውስጥ  ሰዎች፤አንባቢዎቹ ምን አዩበት? ምን ታየበት? የሚል ጥያቄ ማንሳቱ ጥሩ ይመስለኛል። በኔ ግምት መጀመሪያ ነገር የትዝታ ፈለግ ውስጥ የተወሳሰበ ነገር የለበትም። ይህም ማለት ሰው፤አንባቢው፣ያልተወሳሰበ ነገር ይወዳል ማለት ነው። ቀላሉን ነገር አወሳስበው ለማቅረብ የሚሞክሩ ጸሐፊዎችም ተናጋሪዎችም አሉ። እርግጠኛ ምክንያታቸውም ባላውቀውም “ነገሩ እንዲህ እንደምታስቡት ቀላል እንዳይመስላችህ!” የሚል  አንድምታ ለማስተላለፍ ይመስለኛል። በዚያውም “እኔ ሆኜ ነው እንዲህ ያፍታታሁላችኁ እንጂ እንዲህ ቀላል እንዳይመስላችሁ!” ለማለትም ጭምር ይመስለኛል። አዋቂ ነኝም ለማለትና ከሌላው “ተራ ሰው” ተለይቶና ገንጠል ብሎ፣ጎልቶ፣ፈክቶ ለመታየትም ይመስለኛል።
በኔ አስተያየት የትዝታ ፈለግ እሽጉን ከፍቶ ለማየት መሞከሩ ይመስለኛል ተነባቢነት ያስገኘለት። ”ገልጠን ብናየው!” እንደ ማለት ነው። ወይም በአሉ ግርማ “መጋረጃው ተቀዶ መቅደሱ ታዬ!” እንዳለው መሆኑ ነው። በአጭሩ እሽጉን ከፍቶ፣ ሳጥኑ፣ፓኮው ውስጥ ምን ምን እንዳለ የመመርመር ጉዳይ ነው። መጀመሪያውኑ ሳጥኑን የቆለፈው፤እሽጉን ያሸገው አላዋቂም ሊሆን ይችላል ብሎ የመጠርጠር ጉዳይም ሊኖር ይችላል:: ይገባልም!! አብሮ መታሸግ፤መቆለፍ የሌለባቸው አብረው ከታሸጉ ”አጥፊና ጠፊም!”ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህም ላይ ለስንት ዘመንስ ይታሸጋል የሚሉትም አለ። ማንኛውም እሽግ ዘመኑ ያልፍበትና (Expire Date) ካልታደሰ ሊቃጠል ወይም ጎጅም ሊሆን ይችላል። ከሁሉም በላይ እሽጉ ውስጥ የተበላሸ፤የበሰበሰ ፤ጠረኑን የለወጠ፣ሊወገድ የሚገባውም ሊኖር ይችላል ብሎ መፈተሹ ጉዳት ያለበት አይመስለኝም።ከዚህ ጋር የሚያያዝ እሽጉ እንዳይከፈትና ውስጡ እንዳይታይ የሚፈልጉ “የፖለቲካ ድርጅቶችና “የፖለቲካ “ጠበብቶች” ብዛት እንደ አሸን የፈላ ይመስለኛል። የተገነቡት የጠና መሠረት ላይ ስለአልሆነ፣የእምቧይ ካብ ወይም የተልባ ክምርነትም ስለማይጡ፣ ነካ ሲያደርጉት መንሸራተቱ ስለማይቀር፣ይህንንም ስለሚያቁት “ዕውነት ለምኔ!” ይሆኑና “አትንገሩን! አትደርሱብን!”  የሚሉትም አላቸው። የፖለቲካ የንግድ ኩባንያ መሆኑ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ማናቸውም ህዝብ፣ እውነቱ ሲነገረው ያውቃል። ራሱ ከሚያውቀውም ጋር ያነጣጥርና “ይህ እውነት ነው!” ይላል። ያንን ካላለም “እውነት ይመስለኛል!” ይላል። ካልሆነ ደግሞ “አልገባኝም! ሆኖም አልጣመኝም!” ይላል። የትዝታ ፈለግ ይህንን መሠረታዊ ነገር የጫረ ይመስለኛል።ከሁሉም በላይ ግን ወዳጆቼ፤ዘመዶቼ፤ልጆቼ፤ከሁሉም በላይ የልጅ ልጆች ወደውታልና ከዚህ በላይ ጸጋ ያለ አይመስለኝም። እመቤት አስፋ እንደምትነገረኝ ልጆችዋ መጽሐፉን ታቀፈው ነው ያደሩት። የወንድሜ ልጅ፤ግርማ ሐብተ ገብርኤል ከአርባ ምንጭ “አሴ አለቀስኩ!” አለ። በኩራት መሆኑ ነው።በኦርቶዶክሶቹ ሕማማት ሔጄ በፋሲካ ማግስት ሰኞ ወደመጣሁበት ተመለስኩ። የመጀመሪያው መድረክ ሕማማት ዋዜማ፤ሁለተኛው አርብ የስቅለት ዕለት ነበር። ከሁለት ቀን በኋላ ትንሳዔ ሆነና ተፈሰከ! ፋሲካ ሆነ! “ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ!” እንዲሉ:: የፋሲካ ምን የመሰለ ምሳ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ጋዜጠኛው አሉላ ቤት ተጋበዝኩ።
ትንሳኤም ተከበረ!!
የኢትዮጵያን ትንሳኤ እመኛለሁ!!
ኢትዮጵያ በነፃነትዋ  ለዘለዐለም ትኑር!!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s