ኤጲደቅስዮ (ዲ/ን ዳንኤል ክብረት )

ኤጲደቅስዮ

“ርትዕ ከሌለ ፍትህ ብቻውን ዋጋ አይኖረውም”

ፊሳልጎስ የተሰኘውና በ2ኛው መክዘ በእስክንድርያ ተጽፎ በ5ኛው መክዘ ወደ ግእዝ የተተረጎመው መጽሐፍ ‹ኤጲዲቅስዮ› ስለሚባል ዛፍ ይተርካል፡፡ ይኼ በሕንደኬ ሀገር የሚገኝ ዛፍ ሁለት ጠባይ አለዉ፡፡ አርጋብ የዛፉን ፍሬ ስለሚወዱት በእርሱ ላይ እየተሰበሰቡ ይመገቡታል ይላል መጽሐፉ፡፡ እንደ እባብ ላሉ እንስሳት ደግሞ ጥላዉ እንኳን ከነካቸው ይሞታሉ፡፡ ነገር ግን ለእባቦቹ ሌላ ዘዴ ለግሷቸዋል፡፡ ርግቦችን ለማጥመድ የሚመጡት እባቦች የፀሐይ ጥላ ባላረፈበት አቅጣጫ፣ ወይም ፀሐይ ስትጠፋ ወይም ደግሞ ደመና ሲጋርድ ወደ አካባቢዉ ይመጡና ያደፍጣሉ፡፡ ዛፉን ርግቦችም እባቦችም ይፈልጉታል፡፡
ይህ ዛፍ በላቲኑ አምቢዴክትረስ (ambidextrous) ይባላል፡፡ ‹አምቢ› ማለት ‹ሁለቱም› ማለት ሲሆን ‹ደክስተር› ማለት ደግሞ ‹ትክክል› ማለት ነዉ፡፡ ‹አምቢዴክትረስ› ማለትም ‹በሁለቱም በኩል ትክክል የሆነ› ማለት ነዉ፡፡ የእንግሊዝኛው ቃል መጀመሪያ ተግባር ላይ የዋለዉ በሕግ ሰዎች ዘንድ ነዉ፡፡ አንተም ልክ ነህ፣ አንተም ልክ ነህ ብሎ ከከሳሽም ከተከሳሽም ወገን ጉቦ ለሚቀበል ዳኛ ነበር ቃሉ ጥቅም ላይ የዋለዉ፡፡
ርግቦቹ ወደ ኤጲደቅስዮ ዛፍ ሲመጡ ሁለት ነገር ተስፋ አድርገዉ ነዉ፡፡ በአንድ በኩል የዛፉን ፍሬ ጣፋጭነት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የርግቦች ዋና ጠላት የሆነዉ እባብ የዛፉን ጥላ በመፍራት ወደ አካባቢዉ አይደርስም ብለዉ በማመን፡፡ ኤጲደቅስዮ ዛፍ ግን ለርግቦቹ ምግብ እንደሚሆነዉ ሁሉ ለእባቦቹም የምግብ ምንጭ ነዉ፡፡ እባቦቹ እንዴት ከዛፉ ጥላ ማምለጥ እንደሚችሉ ጠንቅቀው ያዉቃሉ፡፡ ፀሐይ በምሥራቅ ስትሆን በምዕራብ፣ በምዕራብ ስትሆንም በምሥራቅ በኩል ይመጣሉ፡፡ ያንንም ካልቻሉ እስክትገባ ጠብቀው ከች ይላሉ፡፡ ኤጲደቅስዮ ለርግብም ለእባብም የሚሠራ ዛፍ ነዉ፡፡
አሁን አሁን በሀገራችን አስቸጋሪዉ አሠራር እንደ ኤጲደክስዮ ዛፍ ለሁለቱም ወገን ለመሥራት የሚጥረዉ አሠራራችን ነው፡፡ ለሕጋዊዉም ለሕገ ወጡም፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ቤቶችን በማፍረስና ባለማስፈረስ በተፈጠረ ግብ ግብ የሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ እጅግ አሳዛኝ ነዉ፡፡ እነዚህ የፈረሱ ቤቶች እንደ ሜክሲኮ የድንበር መተላላፊያ ዋሻ ምድር ውስጥ፣ እንደ ንጉሥ ሕዝብ ናኝ የምኞት ቤተ መንግሥት አየር ላይ የተሠሩ ቤቶች አይደሉም፡፡ በዚሁ በከተማችን ምድር ላይ የተሠሩ ናቸዉ፡፡ እንደ ታዴዎስ እርሻ በአንድ ቀን አልበቀሉም፡፡ ሲቆፈሩ፣ ሲገነቡ የኖሩ ናቸዉ፡፡ አካባቢዉ እንደ አንታርክቲካ መስተዳድር አልባ አይደለም፡፡ ክፍለ ከተማና ወረዳ አለዉ፡፡ ታድያ ለመሆኑ እነዚህ ሁሉ ቤቶች እንዴት ሊሠሩ ቻሉ? ይህንን ያህል ዘመንስ እንዴት ሊቆዩ ቻሉ? እነዚህ ሰዎች በአካባቢው ስብሰባ ሲኖር ሲጠሩ፣ መዋጮ ሲኖር ሲያዋጡ፣ ምርጫ ሲኖር ሲመርጡ የኖሩ ናቸዉ፡፡ ችግሩ ያለዉ እንደ ኤጲደቅስዮ ዛፍ ለሁለቱም ከሚሠሩ አካላት ነዉ፡፡ ነዋሪዎቹ ቤቱን ሲሠሩ አይተዉ እንዳላዩ በማለፍ ጥቅሙን ሲጋሩ የነበሩ፤ ምናልባትም ደግሞ በድብቅ እየፈቀዱ ገንዘብ ሲቀበሉ የኖሩ፡፡ በጊዜው ሕጉን ከማስከበርና ‹ይሆናል ወይም አይሆንም› የሚል ዉሳኔ ከመስጠት ይልቅ ነገሮችን በማዘግየት ከገንቢዎቹ ጋር ሲስማሙ የኖሩ አካላት ናቸዉ የችግሩ መነሻዎች፡፡ እነዚህ አካላት በአንድ በኩል የመንግሥት አካላት ሆነዉ ሕግ ያስከብራሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከነዋሪዎቹ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ የነዋሪዎቹ ቤት ሕገወጥ ነው ተብሎ እንዲፈርስ ሲደረግ አብረዉ መጠየቅ የነበረባቸው አካላት ነበሩ፡፡ የነዋሪዎቹን የቤት ችግር በጊዜ መፍታት ያልቻሉ፣ ነዋሪዎቹ ቤት እንዲገነቡ ውስጥ ለውስጥ የፈቀዱ፣ ቤቶቹ እየተገነቡ መሆኑን አይተዉ ዝም ያሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ እኩል ተጠያቂ የማይሆኑ ከሆነ ግን አሠራሩ እንደ ኤጲደቅስዮ ዛፍ ለእባቦች የበለጠ ይጠቅማል ማለት ነው፡፡ ነዋሪዎቹ እንደ ርግቦቹ በአንድ በኩል በቀላሉ ቤት ለመሥራት መቻላቸዉን አይተዉ፤ በየዘመኑ የሚቀያየሩት ኃላፊዎች የሚሰጧቸዉን ቃል እያመኑ ምንም አንሆንም ብለዉ ዘመናትን አስቆጥረዋል፡፡ ያላቸዉን ጥሪት አውጥተው ቤት ገንብተዋል፡፡ ልጅ ወልደዉ አሳድገዋል፡፡ የሥራ ኃላፊዎቹ ነገሩ ነገ ሊያስጠይቅ እንደሚችል ቢረዱም እንደ እባቡ እንዴት ከችግሩ ማምለጥ እንደሚችሉ ያዉቁበታል፡፡ በመጨረሻ የሚጎዱት ዛፍና ፀሐይዋን አምነዉ የተጠጉት ርግብ ቤት ገንቢዎች ናቸዉ፡፡በየጊዜዉ የሚወሰኑ ውሳኔዎችም ቢሆኑ ፍናፍንት የሆኑ ውሳኔዎች ናቸው፡፡ ሕገ ወጥ ግንባታ ነዉ ተብሎ ቤታቸዉ የሚፈርስባቸዉ አካላት እንዳሉ ሁሉ ሕገወጥ ብትሆኑም ሕጋዊ እናደርጋችኋለን የሚባሉ አካላት አሉ፡፡ እንዴት ተደርጎ ነዉ ሁለቱ ነገሮች በአንድ ጊዜ ትክክል የሚሆኑት፡፡ ዉሳኔው ሁለት የሚቃረኑ ‹ትክክል› ነገሮችን ለመሥራት የሚሞክር ነዉ፡፡ አንድ ሕግ የጸና ሕግ የሚሆነዉ በመቼዉም ጊዜ፣ ለሁሉም ዓይነት ዜጎች በማንኛዉም ሁኔታ እኩል ተግባራዊ ሲሆን ነዉ፡፡
በጥንቱ የኢትዮጵያ የውትድርና ሥምሪት፣ ወታደር ደመወዝና ቀለብ ስላልነበረዉ በሄደበት ሀገር በመንደር ተመርቶ ጠይቆም ቀምቶም እየበላ ነበር የሚኖረዉ፡፡ በዚህ ዘመን ብዙ ግፍ ተፈጽሟል፡፡ ቤት ንብረት ይበረበራል፤ ከብት ይታረዳል፣ ሴት ልጆችና ሚስቶች ይደፈራሉ፡፡
ከሰዉ እኖር ብዬ፣ ልጀ አሳድግ ብዬ
ለባሻ ዳርኩለት ሚስቴን እቴ ብዬ
የተባለዉ በዚህ ዘመን ነበር፡፡ ታድያ በአንድ ወቅት በአንድ መንደር ወታደር ይሠራል፡፡ አንዱ ወታደር ወደ አንዱ ገበሬ ቤት ሲገባ ቆንጆ የሆነች ሚስቱን ያያል፡፡ ይዤ እሄዳለሁ ሲል ከባል ጋር ይጋጫል፡፡ ግርግሩን የሰሙ ሌሎች ወታደሮች  ይመጡና ገበሬዉን የፊጥኝ ያሥሩታል፡፡ ሌላው ወታደር ደግሞ ሌላ ቤት ሲገባ ባሏ የታሠረባትን ሴት ያገኛል፡፡ አብሮ ያድራል፡፡ ያቺም ሴት አስተዛዝና ባሏን እንዲፈታላት ትለምነዋለች፡፡ ሀገሩን ለቅቀው ሲሄዱ ፈትቶ ይሰድላታል፡፡ ታድያ ይህንን ሁለቱን ታሪክ ያየ የሠፈር እረኛ፡-
አይ ዉበት አይ ዉበት አይ ዉበት ቁንጅና
አንዱን ያሳሥራል አንዱን ያስፈታና
ብሎ ገጠመ ይባላል፡፡
መሬት ማግኘት ለአንዳንዶች ጠጠር እንደ ማግኘት ሲቀልል፤ ለአንዳንዶች ደግሞ ነዳጅ እንደ ማግኘት ይከብዳል፤ ሕጋዊ ያልሆነ መሬት ይዞ ሕጋዊ መሆን ለአንዳንዶች እንደ ቅል ቀላል፣ ለሌሎች እንደ ዱባ ከባድ ነዉ፡፡ ከጉምሩክ ዕቃ ማውጣት ለአንዳንዶች ከኤቲኤም ብር እንደማዉጣት ሲቀል፣ ለሌሎች ደግሞ ዶላር እንደማዉጣት የከበደ ነዉ፡፡ አንዳንዶች በጊዜ አልገነባችሁም ተብለዉ መሬት ሲነጠቁ፣ ሌሎች ደግሞ በዘመናት ውስጥ ባይሠሩም የሚመጣባቸዉ ነገር የለም፡፡ ለአንዳንዶች የውጭ ምንዛሪ ከማግኘት ዝርዝር ሳንቲም ማግኘት ይከብዳቸዋል፡፡ ለአንዳንዶች ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ከማግኘት ዉጭ ሀገር ሄዶ መሬት መግዛት ይቀላቸዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን በአንዲት ሀገር ይኖራሉ፡፡ በአንድ ሕግ ግን አይተዳደሩም፡፡
በኤጲዲክስዮ ዛፍ አሠራር እባቦች አይጎዱም፡፡ ‹እንደ እባብ ብልህ› የተባሉትም ለዚህ ነዉ፡፡ የዛፏን ጥላ አቅጣጫ ያውቁታል፡፡ የሚጎዱት ርግቦቹ ናቸዉ፡፡ አሁንም የመንግሥትን ስስ ልብ የሚያዉቁት አይጎዱም፡፡ ሕግ እንዴት እንደሚወጣ፣ አሠራር እንዴት እንደሚቀየር፣ መመሪያ ከየት እንደሚመነጭ፣ ችግር ቢፈጠር እንዴት ማምለጥ እንደሚቻል፣ መሥዋዕትነት ቢከሰት የትኛዉን ፍየል መሠዋት እንደሚቀል አቅጣጫዎቹን ያውቋቸዋል፡፡ ድሮ በሀገራችን የእግር መንገድ የሚያዉቅ ሰዉ ይፈለግ ነበር፡፡ አቋራጩን መንገድ መርቶ እንዲያደርስ፡፡ ዛሬ የሚፈለገዉ የእጅ መንገድ የሚያዉቅ ነዉ፡፡
በጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ዘመን አንድ የአካባቢ ሹም አንዱን ገበሬ ከስሶ ለንጉሡ ችሎት ያደርሰዋል፡፡ የተከሰሰበት ወንጀል ደመኛዉን ገድሏል ተብሎ ነዉ፡፡ ከሳሹ ነገሩን ሲያስረዳ ‹በየጊዜዉ ሲዝት ነበር፣ አንተን አያርገኝ ሲለዉ ነበር፣ መሣሪያ ጠይቆን ሰጥተነዋል› ብሎ ይናገራል፡፡ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትም ‹ሲዝት ካየኸው፣ ለምን መሣሪያ ሰጠኸዉ› ይሉታል፡፡ እርሱም ‹ሲለምነኝ እንዴት እምቢ ልበለዉ› አለ፡፡ ንጉሡም ‹ሰዉዬውን የገደለው እርሱ ቢሆንም ያስገደልከዉ ግን አንተ ነህ፡፡
ወይ ብትመክረዉ ወይ ያኔ ከስሰህ ብታሣሥረው ይህ ሁሉ አይመጣም ነበር› ብለው በከሳሹም በተከሳሹም ላይ ፈረዱ ይባላል፡፡ ርትዕ ማለት ይህ ነዉ፡፡ ፍትሕ ለሁሉም በትክክል ሲያገለግል፡፡ እያንዳንዱ የሥራዉን ሲያገኝ፡፡ ርትዕ ከሌለ ፍትሕ ብቻዉን ዋጋ አይኖረዉም፡፡ ፍትሕ ዳኝነት፣ የሕጉም ሥርዓት ነዉ፡፡ ርትዕ ግን ይህንን ሥርዓት ለሁሉም በሚዛናዊነት መፈጸም ነዉ፡፡ ፍትሕን ርትዕ ካልተከተላት የኃያላን ማጥቂያ መሣሪያ ትሆናለች፡፡
ደካሞች ተገቢዉን ፍትሕ እንዲያገኙ የሚያደርጋቸዉ ርትዕ ነዉ፡፡ በሀገራችን የሕግና የሕግ ማስከበር ሥርዓትም አንዱ ጉድለት ርትዕ መጥፋቱ ነዉ፡፡ ርትዕ በሌለበት ሕጎች፣ የሕግ ማስከበር ሂደቶችና አሠራሮች ኤጲደክስዮ ዛፍ ይሆናሉ፡፡ ከርግቦች ይልቅ ለእባቦች የተመቹ!!

Leave a comment