አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በመከላከያ ምስክርነት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ሰበር ችሎት አዘዘ

በሽብር ድርጊት ወንጀት ተጠርጥረው በተመሠረተባቸው ክስ እንዲከላከሉ ብይን በተሰጠባቸው በእነ ዘመኑ ካሴ መዝገብ አቶ አሸናፊ አካሉ፣ አቶ ደህናሁን ቤዛ፣ አቶ ምንዳዬ ጥላሁንና አቶ አንሙት የኔዋስ በመከላከያ ምስክርነት የቆጠሯቸው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ቀርበው እንዲመሰክሩ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት አዘዘ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን የመጨረሻ ትዕዛዝ መሠረት በማድረግ፣ ክሱን ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፌዴራል ማረሚያ ቤት ባስተላለፈው ትዕዛዝ፣ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ሐሙስ ሐምሌ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ያቅርብ ብሏል፡፡

የግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡላቸው አራቱ ተከሳሾች በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤት አመልክተው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግለሰቡ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቱና በማሳገዱ ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡

ተከሳሾቹ በዋናነት የተጠረጠሩበት ወንጀል አቶ አንዳርጋቸው የግንቦት ሰባት አመራር በነበሩበት ወቅት፣ ከተከሳሾቹ ጋር ኤርትራ ውስጥ በመገናኘት የተለያዩ ትዕዛዞችን ማስተላለፋቸው በክሱ በዋናነት በመጠቀሱ፣ ክሱን በሚመለከት ራሳቸው አቶ አንዳርጋቸው ቀርበው እንዲመሰክሩላቸው መሆኑ በተደጋጋሚ ተዘግቧል፡፡

የሥር ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ አቶ አንዳርጋቸው በመከላከያ ምስክርነት ቀርበው እንዲመሰክሩላቸው ሲያስመዘግቡ ዓቃቤ ሕግ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ያሳገደ ቢሆንም፣ መዝገቡን መርምሮ ይግባኙ እንደማያስቀርብ ብይን ሰጥቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ መሠረታዊ የሕግ ስህተት እንዳለበት በመጠቆም ለሰበር ሰሚ ችሎት በማቅረብ ለጊዜው መዝገቡ ታግዶ የከረመ ቢሆንም፣ ግንቦት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ሰበር ችሎቱ ትዕዛዝ ሰጥቶበታል፡፡

ፍርድ ቤት በሰጠው ትዕዛዝ ላይ ይግባኝ እንደማይባል ትርጉም እንደተሰጠበት አስታውሶ፣ የቀረበለትን የይግባኝ አቤቱታ ውድቅ በማድረግ በመከላከያ ምስክርነት የተቆጠሩት አቶ አንዳርጋቸው ቀርበው እንዲመሰክሩ የሥር ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲሰጥ በማለቱ፣ የሥር ፍርድ ቤትም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው ከዱባይ ወደ አስመራ ሲሄዱ የመን ሰንዓ ላይ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው፣ ከሁለት ዓመት በፊት ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ይታወሳል፡፡

የተለያየ አስተያየት ሲሰጡ በቴሌቪዥን መስኮት ከመታየታቸው በስተቀር አቶ አንዳርጋቸው የት እንዳሉ በግልጽ አይታወቅም፡፡ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር የነበሩት ሚስተር ግሬግ ዶሪ በተለያዩ ጊዜያት ስለደኅንነታቸው ሲገልጹ ነበር፡፡ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሀሞንድ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በአግባቡ እንደተያዙና በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s