የጎንደሮች ትግል በብዙ መልኩ ከፍልስጤሞች ትግል ጋር ተመሳሳይነት አለው

አብርሃም በየነ

 • እንደ ፍልስጤሞችና አፍጋኖችም ጎንደሮች ለህዝባቸው መብት ሰማዕት ሆነዋል። እየሆኑም ነው። ገናም ይሆናሉ።
 • የፍልስጤማዊያን ትግል በዕድሜ እርዝመቱ ልቅና ይኑረው እንጂ በባህሪይው ግን ከጎንደሮች ትግል ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት            ገጽታ ያለው ትግል ነው።
 • እስራኤላዊያንና ፍልስጤማዊያን ወንድማማቾች ናቸው።
 • ትግራዊያንና ጎንደሮችም እንዲሁ። እስራኤሎችንና ፍልስጤሞችን ያጣላው የመሪት ጥያቄ ነው።
 • የትግራዊያንና የጎንደሮች ጥልም መነሾው የመሬት ጥያቄ ነው።
 • የፍልስጤሞች የዕምነት መሬት ምስራቅ ኢየሩሳሌም ስትሆን፣ የጎንደሮች የዕምነት መሬት ደግሞ ዋልድባ ነው።
 • የፍልስጤሞች የውኃ ጥያቄ የጆርዳን ወንዝ ሲሆን፣ የጎንደሮች የውኃ ጥያቄም የተከዜ ወንዝ ነው።
 • በፍልስጤምና በእስራኤል ጦርነት ጠብ አጫሪዋና ጉልበታሟ እስራኤል ስትሆን፤ በጎንደሮችና በትግራዊያን ጦርነትም ጉልበታሟና ጠብ አጫሪዋ ትግራይ ነች።
 • በፍልስጤምና በእስራኤል ጠብ አልሞት ባይ ተጋዳዮቹ ፍልስጤሞች ሲሆኑ፤ በጎንደሮችና በትግራዊያን ጠብም አልሞት ባይ ተጋዳዮቹ ጎንደሮች ናቸው።
 • የፍልስጤሞች ጥያቄ መፍትሄ ለማግኘት ዘመናት እንዳስቆጠረው የጎንደሮችም ጥያቄ እልባት እስኪያገኝ ዘመናት ማስቆጠሩ አይቀሬ ነው።
 • ስለሆነም ጎንደሮች ፍልስጤሞችን ሆነዋል። እንዴት? ቢሉ የሁለቱም ህዝቦች ጥያቄ ማጠንጠኛው የማን መሬት? ሆኗልና!

ሞት ለሰው ልጆች ፀጋም ዕዳም የሚሆንበት ጊዜ አለው። ዜጎች መብታቸው ሲደፈር፣ ነፃነታቸው ሲገፈፍ፤ማንነታቸው ሲፋቅና የመኖራቸው ህልውና በሞት ጥላ ስር ሲወድቅ ሞት ዕዳውን ያከብድባቸዋል። የክፍያውንም ዋጋ በህይዎት ይመነዝረውና መተኪያ የሌለውን ህይዎት በሞት ወለድ አገድ ያስይዘዋል። ህዝብም የታገቱትን መብቶቹን ለማስፈታት ሞትን ይኖሩታል እንጂ አይሞቱትም ብሎ ይንቀሳቀሳል። ሰው የተፈጠረው ለመሞት ነውና ሞትን ሙቶ ሊያቸንፈው ዕምቢኝ ለሀገሬ ሲል በሞት ላይ ያምፃል። ብሎም ጅግና ይፀነሳል። ሰማዕት ይወለዳል።

ህዝብም ከመቃብር በላይ የሚውል ስም በደሙ ጽፎ ለማለፍ ሆ ብሎ ይነሳል። የተቀሰቀሰው አመጽም መተኪያ የሌለውን ህይዎት ለመብትና ለሀገር ቤዛ በማድረግ ፀጋነቱን በህዝብ ስነ ልቦና ውስጥ ስርፀት እንዲያገኝ ያደርገዋል። ብሎም የሞት አስፈሪነት የጧት ጤዛ ወደ መሆን ይሸጋገርና ሞትን መሞት ሳይሆን ሞትን እየሞቱ መኖር የህዝብ ባህል ሆኖ ነጥሮ ይወጣል። ሞትን ይኖሩታል እንጂ አይሞቱትም እንዲሉም እንደ ፍልስጤሞች፣ እንደ አፍጋኖችና እንደ ጎንደሮች ሞትን ንቆ መኖር ይለመዳል። እናም የታገተው መብት እስኪፈታ፤ የተነጠቀው ነጻነት እስኪመለስ ህይዎት የሞት ማገዶ መሆኑ ይቀጥላል።

የወላድ ማህፀን በድባቡ ይኑርና የዕናቶችም ዛሬ ቤዛ የሆነውን ጀግና የሚተካ ሌላ ጅግና ለነገው ትግል ይፀንሳሉ። በዚህ መልክ የተቀጣጠለው የትግል እሳት እንዳይዳፈን እናቶች የጦርነት ማገዶ አቅራቢነታቸውን ሙያየ ብለው እንዲወስዱት ይገደዳሉ። በመሆኑም ትግሉ ያለማቋረጥ ህይዎት እየበላ የቀጣይነት እድሜ ይኖረዋል። የትግሉ ቀጣይነት ዕድሜም እየረዘመ ሲሄድ ህዝቡ ሞትን እየሞተ መኖሩን ይለማመደዋል። ይልቁንም ሞት አስፈሪነቱ ቀርቶ የጅግነነት አርማ ይሆንና ልጆች አድገው እንደ ትልልቅ ወንድሞቻቸው ጀብዱ ሰርተው ለመሞት ጉጉት እንዲያድርባቸው ያደርጋቸዋል። በዚህ መልክ ብዙዎቹ ታዳጊ ወጣቶች እድሜ ዳ ሲልባቸው ገና በጧቱ የእሳት እራት እየሆኑ ማለቅን ይመርጣሉ። ለምን? ቢባል መኖር በራሱ ተስፋውን አጨልሞባቸዋልና! የህይዎት ችቦም እንዲህ እንዲህ እያለ የነጻነት ቀንዲል ሆኖ ይኖራል።

የፍልስጤም ጀግኖችና የነ ላይላ ካሊድ አርማ መሬት ነክቶ የማያውቀው በዚህ ምክኒያት ነው። የወላዶች ማህፀን ጀግና መፀነሱን በቀጣይነት ስለያዘው በፍልስጤም የትግል ታሪክ ጀግና ይወለዳል እንጂ አይሞትም። ሺህ ጀግኖች ለፍልስጤም መብት ሰማዕት ሆነዋል። እንደ ትናንቱ ዛሬም…….. ነገም… . . . መስዋዕት ይሆናሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአፍጋን ጀግኖችም ለቅኝ ገዥ አንንበረከክም ብለው ለአፍጋን ህዝብ ነፃነት ህይዎት ገብረዋል። እንደ ፍልስጤሞችና አፍጋኖችም ጎንደሮች ለህዝባቸው መብት ሰማዕት ሆነዋል። እየሆኑም ነው። ገናም ይሆናሉ። ያልተቋረጠው የፍልስጤሞች ትግል በብዙ መልኩ ከጎንደሮች ትግል ጋር ተመሳሳይነት አለው። የፍልስጤማዊያን ትግል በዕድሜ እርዝመቱ ልቅና ይኑረው እንጂ በባህሪይው ግን ከጎንደሮች ትግል ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ያለው ትግል ነው።

እስራኤላዊያንና ፍልስጤማዊያን ወንድማማቾች ናቸው። ትግራዊያንና ጎንደሮችም እንዲሁ። እስራኤሎችንና ፍልስጤሞችን ያጣላው የመሪት ጥያቄ ነው። የትግራዊያንና የጎንደሮች ጥልም መነሾው የመሬት ጥያቄ ነው። የፍልስጤሞች የዕምነት መሬት ምስራቅ ኢየሩሳሌም ስትሆን፣ የጎንደሮች የዕምነት መሬትም ዋልድባ ነው። የፍልስጤሞች የውኃ ጥያቄ የጆርዳን ወንዝ ሲሆን፣ የጎንደሮች የውኃ ጥያቄም የተከዜ ወንዝ ነው። በፍልስጤምና በእስራኤል ጦርነት ጠብ አጫሪዋና ጉልበታሟ እስራኤል ስትሆን፤ በጎንደሮችና በትግራዊያን ጦርነትም ጉልበታሟና ጠብ አጫሪዋ ትግራይ ነች። በፍልስጤምና በእስራኤል ጠብ አልሞት ባይ ተጋዳዮቹ ፍልስጤሞች ሲሆኑ፤ በጎንደሮችና በትግራዊያን ጠብም አልሞት ባይ ተጋዳዮቹ ጎንደሮች ናቸው። የፍልስጤሞች ጥያቄ መፍትሄ ለማግኘት ዘመናት እንዳስቆጠረው የጎንደሮችም ጥያቄ እልባት እስኪያገኝ ዘመናት ማስቆጠሩ አይቀሬ ነው። ስለሆነም ጎንደሮች ፍልስጤሞችን ሆነዋል። እንዴት? ቢሉ የሁለቱም ህዝቦች ጥያቄ ማጠንጠኛው የማን መሬት? ሆኗልና!

እንደ ቀደምቱ ፍልስጤማውያን ጅግኖች የኛም አባቶቻች ክቡር ህይውታቸውን ሰውተው ነው ባላገር አድርገውን የኖሩት። እንደ ህዝብ እንድንኖር፤ እንደ ሰውም ባላገር እንድንሆን አባቶቻችን የህይዎት ዋጋ ከፍለውልናል። እንደ ህዝብም እንድንኮራ ነፃነት አጎናጽፈውናል። ህዝብ ያለ አገር ህዝብ ሆኖ መኖር እንደማይችል፤ መሬትም ያለ ህዝብ አገር እንደማይባል ክቡር የህይዎት ዋጋ ከፍለው ታሪክ አስተምረውናል። አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ተንበርክኮ መገዛትን ሳይሆን ዕምቢኝ ለክብሬ፤ ዕምቢኝ ለመብቴ፤ እምቢኝ ለነጻነቴ ብሎ ማመጽንና ገድሎ መሞትን በደም ቀለም ፅፈው የጀግነንት ታሪክ አውርሰውናል።

ሰሜን ጃናሞራንና ጠለምትን ጎንደሬ አድርጎት የኖረው የነደጃች ውቤና የነአጥናፉ መሸሻ ጅግንነት ነበር። ወልቃይትን፤ ፀገዴን፤ አርማጭሆንና አዳኝ አገርን ጎንደሬ አድርጎት የኖረው የነቢትወደድ አዳነ መኮነን ጀብዱ፤ የነቀኛዝማች ገብሩ ገበረ መስቀል አይበገሬነት፣ የነራስ ውብነህ ነፍጠኝነት፤ የነደጃዝማች ታከለ ወልደ ሐዋሪያት አርቆ አስተዋይነት፣ የነደጃች ብሬ ዘገየ ጀብዱ፣ የነደጃዝማች አስፋው ተሰማ፣ የነዳኘው ተሰማ፣የነባላንባራስ አላባሽ በሪሁን፣ የነፊታውራሪ በረደድ አስፋው፣የነገሪማ ታፈረ፣ የነፊታውራሪ አየለ አባ ጓዴ፤ የነረዳ ተሰማ ለጠላት አይበገሬነት ነበር።

የቀደምቱን አርማ አንስተው እነ ነጋ ነወጠ፤ እነ ሻለቃ አጣናው ዋሴ፤እነ አባ ታከለ፤ እነ ኪዳነ ማርያምና ሌሎቹም . . . ነጻነት ሲገፈፍ ሞትን ይኖሩታል እንጂ አይሞቱትም በማለት ሞትን አቸንፈው የኖሩ ስማዕታት ነበሩ። ዛሬም የጎንደር እናቶች ማህፀናቸው አልደረቀም። ጀግና ይወለዳል እንጂ አይሞትም እንዲሉ እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ወልዷል። አዳዲስ አጣናው ዋሴዎች፤ አዳዲስ ኪዳነ ማርያሞች፤ አዳዲስ ነጋ ነወጠዎች፤ አዳዲስ አየለ አባ ጓዴዎች ተወልደዋል። እየተወለዱም ነው። የወላድ ማህፀን በድባቡ ይኑርና ገናም የላቁ ደመቀ ዘውዱዎች በሺህ ይወለዳሉ።አገሬ አርማጭሆ ጀግና እንጂ ቡከን አያበቅልም። የወልቃይት ምድር ከጀግናም ጀግና መውለዱን ያውቅበታል። አገሬ ጋይንትና ደብረ ታቦር ዳግማዊ አድማሱ በላይን ፀንሷል። ስለሆነም ሞት ጎንደሮችን ይፈራል እንጂ ጎንደሮች ሞትን ከቶ ሊፈሩት አይችሉም።

ጎንደሮች ሞትን መኖር ከጀመሩ አርባ ሁለተኛውን ዓመት (1966-2008) ባለፈው ወርሃ ሚይዚያ አክብረዋል። ይህም በኢትዮጵያ የዕርስ በርስ ጦርነት ታሪክ ጎንደር ቀዳሚውን ስፍራ እንድትይዝ አድርጓታል። የጎንደሩ ረዥም የትግል ጉዞ የኤርትራውን ትግል “አጭር” አስመስሎታል። ዛሬ የዘመናችን አፋዓ ቤት የጎንደር ከተማ ሆናለች። የዘመናችን ናቅፋና ቃሮራም ወልቃይትና አርማጭሆ ሆነዋል። ትናንት በኤርትራ መሬት እንደ ተመረተው ዛሬም በጎንደር መሬት የሚመረተው የሞት ሰብል ሆኗል።የሞት መኸር ከዋኝ የሆኑት ጎንደሮች ግን እንደ ኤርትራዊያን ወንድሞቻቸው ከሰላሳ አምስት ዓመት መራር ትግል በኋላ የጦርነት አውድማቸውን ጠራርገው ወደ ቤት የመመለስ እድል አልገጠማቸውም። ለምን? ቢባል ወያኔዎቹ የትግሬዎችንና የጎንደሮችን አበቃቀል የአጋምና የቁልቋል አበቃቀል መልክ እንዲይዝ ስላደረጉት አጋሙም መውጋቱን፤ ቁልቋሉም መድማቱን አላቆመም።

ወያኔዎች ትግሬዎችንና ጎንድሮችን አጋምና ቁልቋል ማድረግ የጀመሩት ከአስራ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያዎቹ መባቻ ጀምሮ ነበር። ሀ ሲሉ 81 አዛውንት ጎንደሮችን ከወልቃይትና ፀገዴ ብሎም ድንበር ዘለው ከአምራኩባ (ሱዳን) እነ ፊታውራሪ አዲሱን አፍነው መዳረሻቸውን አጥፉ። በነርሱ ቤት አዛውንት ጎንደሮችን በማጥፋት ታሪክን ያጠፉ መስሏቸው ነበር። አዛውንቱ ሲታፈኑና መዳረሻቸው ሲጠፋ ግን የወልቃይት ህዝብ አልተንበረከከም። ይልቁንም ወጣቱ ወልቃይቴ የታፈኑ አባቶቹን አርማ አንስቶ የማን መሬት? ብሎ ጠየቀ። ከሶስት ሺህ በላይ ወጣቶችም በጥያቄው ሳቢያ ወደ ትግራይ ተወስደው መዳረሻቸው ጠፍቶ ቀረ። ቀሪው ወልቃይቴም በገዛ አገሩ ስደተኛ እንዲሆን ተፈረደበት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉም የጎንደር ካህናት የወያኔ የፖለቲካ ሰለባ እንዲሆኑ አዲስ የድራማ መድረክ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ተጀመረ። ድርጊቱ ካህናቱን እንቅልፍ ነሳ። ቄስ በስቀሉ ምእመን በቃሉ የወያኔን እብሪት አወገዘ። ለምን ተደፈርን ያሉት ወያኔዎችም ጳጉሜ አንድ 1984 ዓ.ም “ወጣቶችን ለአመፅ እያዘጋጀህ ነው በሚል ሰበብ ባህታዊ አምሃየስን ለማሰር ጎንደር ከተማ ውስጥ በቀሰቀሱት ግርግር ከሰላሳ ያላነሱ መዕመናን አደባባይ ኢየሱስ ላይ ተጨፈጨፉ። ባህታዊ አምሃየስን ጨምሮ ከአምስት መቶ በላይ ምዕመናን እየተደበደቡ እስር ቤት ተጎደጎዱ። ባህታዊውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከዲስ አበባ እንዳይወጡ ተከልክለው የቁም ዕስረኛ በመሆን አስራ ሶስተኛ ዓመታቸውን አስቆጠሩ።

በግርግሩ ሰሞን አደባባይ ኢየሱስ ላይ በተካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ መምህር መንክር “ደግሞ እንደ መሬቱ ዕምነቴንስ አላስወርስም” ሲሉ በዕምነታቸው ፀንተው ስለቆሙ ከዕስር እንደ ተፈቱ በመዳህኒት ተገደሉ። ሞታቸውን ተከትሎም፦

ቀና ብየ ሳየው ሰማዩ ቀለለኝ

ደግሞ እንደ ሁመራ ደግሞ እንደ ጠገዴ

የዕምነት መስቀሉንም ወሰዱት መሰለኝ፣

ስትል አንዲት አስለቃሽ ሙሾ ደረደረች። በደሉ ግን በዚህ ሙሾ አልተቋጨም። በቀጣዩ ዓመት መስከረም/ጥቅምት ወር ላይ የሱዳን ተወላጆች በወታደር ታጅበው ቋራ ድረስ ዘልቀው የቅርቅሃውን ደን ሲጨፈጭፉ ድንበሩን ለመታደግ የወጣው ገበሬ በሱዳን ወታደር ከፍተኛ ጥቃት ደረሰበት። የወያኔ ወታደር ግን ይበላችሁ ለማለት ይመስላል በቅርብ እርቀት ቆሞ ጥቃቱን ይመለከት ነበር። ይህን ሀገራዊ ክህደት አስመልክተው ገበሬዎቹ አገዛዙን ስለተቹ በጥይት ተደብድበው አለቁ።

ያ እልቂት ከ13 ዓመት ቆይታ በኋላ ሰሞኑን ተደገመ። ለ13 ዓመት ደመና አርግዞ የኖረው የጎንደር ሰማይ የደም ዝናቡን ሰሞኑን ጣለ። በዚህ የበደል ዳፋም የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ጎንደሮች ፍልስጤምን ሲሆኑ እንደገና ጎልተው ታዩ። የትግሬዎች ፂዎናዊነትም ነጥሮ ወጣ ። የጎንደሮች የማን መሬት? ጥያቄ ግን አየር ላይ ተንጠልጥሎ ስለቀረ ትግሉ ይቀጥላል።

aderaj3106@gmail.com

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s