ከንቲባውን ጨምሮ የከተማዋ ባለስልጣናት በቆሻሻው ጉዳይ በስብሰባ ተወጥረዋል

ከንቲባውን ጨምሮ የከተማዋ ባለስልጣናት በቆሻሻው ጉዳይ በስብሰባ ተወጥረዋል

Addis Admass:   የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማን ጨምሮ ዋና ዋና የከተማዋ ባለስልጣናት፤ በተለያዩ አካባቢዎች ከሳምንት ባላይ ሳይነሱ ለቆዩት የደረቅ ቆሻሻ ክምችቶች መፍትሄ ለማግኘት በስብሰባ ተወጥረው መሰንበታቸው ተገለፀ፡፡
በጉዳዩ ላይ የአስተዳደሩን ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ከንቲባው ቢሮ በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም፤ “ኃላፊዎቹ ከቢሮ ውጪ በኦሮሚያ ክልል በስብሰባ ላይ ናቸው” በሚል ሙከራችን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ሰንደፋ ከተማ አካባቢ በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ የአዲስ አበባ ቆሻሻ እንዳይጣል በአካባቢው አርሶአደሮች መከልከሉን ተከትሎ ከሐምሌ 7 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ የከተማዋን ቆሻሻ ወደ ስፍራው ወስዶ መጣል አልተቻለም። ይሄን ተከትሎ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች (ዋና ዋና ጎዳናዎችና አደባባዮችን ጨምሮ) የቆሻሻ ክምር ተቆልሎ ሰንብቷል፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የከተማዋ አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ጋር ሲያደርግ የነበረው ውይይትና ድርድር ሳይሳካ መቅረቱ የተገለፀ ቢሆንም ባለስልጣናቱ ትላንት ድረስ በዚሁ ጉዳይ በስብሰባ ላይ እንደነበሩ ከንቲባው ፀሃፊ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከሳምንት በላይ በየአካባቢው ተጠራቅሞ የቆየው የደረቅ ቆሻሻ፤ ነዋሪውን ለከፍተኛ የጤና ችግር እየዳረገው መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በፒያሳ፣ በመርካቶ፣ በአትክልት ተራ፣ በካዛንቺስና ሳሪስ አካባቢዎች ተዘዋውረን ለመመልከት እንደቻልነው፤ የደረቅ ቆሻሻ ክምሩ በየአስፋልቱና በየ ጥጋጥጉ ከመጠን በላይ ተቆልሏል፡፡
ወቅቱ የክረምት ጊዜ በመሆኑም የቆሻሻው እጣቢ በፍሳሽ መልክ በየጎዳናው ሲፈስ ያስተዋልን ሲሆን ይሄም በከተማዋ ከተከሰተው የአተት በሽታ ጋር ተያይዞ ነዋሪውን ለከፍተኛ ስጋት እንደዳረገው ለማወቅ ተችሏል፡፡
‹‹የአገሪቱ ዋና ከተማና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እየተባለች የምትሞካሸው አዲስ አበባ፤ የቆሻሻ ማከማቻ ሆና መሰንበቷ አስደንጋጭ ነው” ያሉ አንድ ነዋሪ፤ ሁኔታው እንደ ኮሌራ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች እንዲስፋፉ ዕድል ይሰጣል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች የተዘጉበትና ህፃናት በየሰፈሩ የሚጫወቱበት ወቅት መሆኑ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል ያሉት ሌላ አስተያየት ሰጪ፤ በዚህ ከቀጠለ የህፃናቱ ህይወት ለአደጋ መጋለጡ አይቀርም ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s