ድሮም ሆነ ዘንድሮ ሄኖክ የሺጥላ

ድሮም ሆነ ዘንድሮ የ አማራ ጥፋቱ ኢትዮጵያዊነቱ ነው። ስለ አማራ ሳስብ ሁል ጊዜም በዕዝነ ህሊናዬ የሚመላለሰው የሄነሪ ፥ ፋን ፥ ዳይኬ የተጣፈው « አራተኛው ሰብዓ ሰገል » የሚለው አጭር ታሪክ ነው ። በዚህ ታሪኩ ሄነሪ ከሶስቱ ሰባ ሰገሎች በተጨማሪ አንድ በታሪክ ያልተገለፀ ፥ በራዕይ ያልተሰበዘ ፥ ኅሣሢ አራተኛ ሰባሰገል ታሪክ ነው። ይህ አራተኛ ሰባሰገል የፍቅሩን ለህፃኑ እየሱስ ለማበርከት እንዴት እንዳልተሳካለት ባለመሳካቱም እንዴት እንደተሳካለት ይተርክልናል።

ጠሃፊው ሲገልጠው « የሀሳቡን ለማድረግ አሰበ ፥ ያሰበውም አልተሳካለትም ፥ ባለመሳካቱ ግን ሃሳቡ ተሳካ » ይለናል ።

ፀሃፊው « ይኽ ሰው አውግስጦስ ቄሳር ንጉሰ ነገስት በነበረበት ፥ ሄሮድስ በእየሩሳሌም በነገሰባቸው ዘመናት ፥ በፋርስ ተራሮች በምትገኘው ኤቅባጣና ይኖር የነበረ ሰው ነበር ። ስሙም አርጣባን ይባላል ይላል ። »

ጠሃፊው ስለ አርጣባን ሃብት እና ክብር ሲናገር እንዲህ ነበር የገለጠው

« ቤቱ የመንግስት ግምዣ ቤት በከበበው በባለ ሰባቱ ቅጥር አውድ በውጭኛው አድሞ አጠገብ ነበር። ከቤቱ ባጥ ላይ ሆኖ ማዶውን አሻግሮ የጥቁርና የነጭ ፥ የሐምራዊ እና የሰማያዊ የቀይ የብርና የወርቅ የቅኝ ማዘዣዎችን ይዞ ዘውድ ላይ እንደተጎብጎበ ፈርጥ የሚንቆጠቆተው የጳርጢያን ነገስታት የበጋ ቤተ መንግስት እስካለበት ድረስ ማማተር ይቻለው ነበር » ይላል ።

አርጣባን እንደ ሶስቱ ሰባሰገሎች ( ቃስጳር ፥ ሚልሾር እና ባልጣፃር ( ወይም ብልጣሶር ወይም ባልተዛር) ጋር በመሆን ለህፃኑ እየሱስ እሱን እንደ ባልዠሮቹ ስጦታ ሊቸር በኮከብ ብርሃን ተመርቶ ወደ እየሩሳሌም ተጓዘ። ቤት ንብረቱንም ሽጦ ለህፃኑ እየሱስ የሚያበረክተውን ስጦታዎች ገዛ ( ሶስት እንቁዎች ፥ ሰንፔር ፥ ከርከንድ እና ሉል ) ። ጓደኞቹ ( ሰባሰገሎቹ አይደሉም ) ባንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ከሱ ጋር አብረው ላለመሄድ ወሰኑ ። አርጣባን ጉዞውን ብቻውን ተያያዘው ። በጉዞው ላይ ግን ለእመቤታችን ልጅ ሊሰጥ ያዘጋጃቸውን ስጦታዎች ሁሉ በችግር ውስጥ ላሉ ሰዎች ሰጥቶ ጨረሰ ። ልቡ በሃዘን እየተመታ ከቆመለት አላማ ውጭ መልካም ነገርን ለማድረግ ሲል ስጦታውን ለሌሎች ሰጠ ፥ ስለ ፍቅር እና ሰዋዊ ምክንያት ሲል ችሮታው ለህፃኑ ክርስቶስ ሳይሆን በመንገዱ ላይ ላገኛቸው ነዳያን አዋለው ። ያሰበውን ባያደርግም እና ባይሳካለትም ፥ ባለሰው ጉዳይ ያሰበው ተሳካ ። መልካምም ሆኖ ተቆጠረለት ።

ይህ የአርጣባን ታሪክ ያለ ነገር አልመጣም! ተጎንደር ህዝብ ሰልፍ የ አርጣባንን ታሪክ አስታወሰኝ ። የወልቃይትን አማራነት እንደ መሪ መፈክር አድርጎ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ የጠራው የጎንደር ህዝብ ፥ መሃል ላይ በኦሮሞ ወንድሞቹ ሞቱ ልቡ ተነካ ፥ ስለዚህም ሰንፔሩን ለኦሮሞ ህዝብ አውጥቶ ሰጠ ፥ ቶፓዙን ለጋንቤላ ህዝብ አበረከተ ፥ ስለ ፍቅር የራሱን ህመም ችሎ ፥ ከአድማስ ማዶ ባለው ሰዋዊ ልቦና ተረታ።
ከርከንዱ የወልቃይት አማራነት ቢሆንም ቅሉ ፥ ውሉ ግን የሰው ልጆች ሰብአዊ መብት መከበር መሆኑን ተናገረ ። ልጆቹን የገበረበት ፥ የታረደበት እና የተገደለበት ዋነኛ ምክንያቱ አማራ መሆኑ ቢሆንም ፥ ደሙን ፥ ሞቱን ፥ ስቃዩን እና ህልፈቱን ከራሱ ባለፈ የሌሎእን ስቃይ ለማስታገስ ተጠቀመበት ።

አርጣባን መጉዞ ላይ ያገኘው እና በህይወት እና በሞት መሃከል የነበረው ሰው « ማነኽ አንተ እስቲ ሒወቴን እንደገና ለመመለስ ‘ኔን እዚህ ድረስ ለምን አሻኸኝ» ሲለው

አርጣባን « የኤቅባጣና ከተማው ሰባሰገሉ አርጣባን ነኝ የይሁድን ንጉስ ፥ ታላቁን ልዑል ፥ የሰው ልጅ ሁሉ ታዳጊውን ለመፈለግ ወደየሩሳሌም ነው የምሄደው » በማለት መለሰለት ።

አዎ የሰው ልጅን አዳኝ የሆነውን ክርስቶስን በመፈለግ ላይ ያለው አርጣባን ፥ ታሞ ፥ ደክሞ ፥ ዝሎ ፥ ደቆ ፥ ወድቆ ያገኘውን ሰው አንዳላየ ሆኖ ሊያልፈው አልቻለም ። ከጉዞ ራሱን ገትቶ ፥ የወደቀውን አንስቶ ፥ ከሸከፈው ፈቶ አብልቶ ፥ ከንፈሩን በውሃ አርሶ ፥ ህይወቱ ላይ ዳግም ነፍስ ዘርቶ ነው ጉዞውን የቀጠለው ።

ክርስቶስን መፈለግ ማለት በመንገድህ ላይ የምታየውን መከራ መታደግ ነው ። የጎንደር ህዝብ ለኔ አርጣባን ነው ። ለወልቃይት የማንነት ጥያቄ ሊታገል ወጥቶ መንገድ ላይ በወያኔ ጥይት ተመትቶ የወደቀውን የሃገሩን ልጅ ፥ ወንድሙን ፥ ደሙን የኦሮሞ ልጅ ትቶ ማለፍ ስላልቻለ ፥ « ሞታችሁ ሞቴ ነው !» ብሎ ያለው ።
ስቃያችሁ ስቃዬ ነው ብሎ የተናገረው ! ይህ ሰውነት ነው ! ይህ አርጣባንነት ነው! ይህ ክርስቶስን የሚፈልግ ሰው ሁነኛ መገለጫ ነው ። አው ክርስቶስን በአዳኝነቱ ስናመልከው ፥ እኛ ራሳችን ደራሽ ፥ ቋሚ ፥ ጠበቃ እና አዳኝ መሆናችንን እንዴት ዘነጋነው ?

አርጣባን በየደረሰበት የወደቀ ሲያነሳ ፥ የደከመ ሲደግፍ ፥ ቤተልሄም ሊደርስ አደልቦ ፥ እና አጠንክሮ ያደረሰው ፈረሱ ደከመበት ስለዚህም ለክርስቶስ ሊሰጥ ካሰበው ስጦታ ውስጥ አንዱን ( ሰንጴሩን ) ሽጦ የግመል ጠያሮች እና ስንቅ ለመግዛት ወሰነ ።

በደግነቱ ከጉዞው ቢስተጓገልም ፥ የሚጓዝበት እና ማየት የሚፈልገውን የፍቅር አምላክ እሱ ራሱ በተግባር ኖሮት ስለነበር ፥ ባያደርግም እንዳደረገ ሆኖ ተቆጠረለት ። የጎንደር ህዝን ሰላማዊ ሰልፍም ይህንን የሆነ እንደነበረ ይሰማኛል ።

እናመሰግናለን ! እናከብራችኋለን! እናፈቅራችኋለን ። አማራ ከጥንትም ለጉራጌ ለመሞት ፥ ለጉራጌ ለማገዝ እና ለመቆም ጉራጌ መሆን የሚያስፈልገው ህዝብ አልነበረም ፥ ወደፊትም አይሆንም ! ስለ አማራ ለመናገር ግን አማራ መሆን ግዴታ የሆነ ይመስላል ። መማር ከቻላችሁ ፥ ይህ ህዝብ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው ! ተማሩት!

ሄኖክ የሺጥላ

Henoke Yeshetlla's photo.
Henoke Yeshetlla's photo.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s