ለእውነተኛ የትግራይ ልጆች የቀረበ ጥሪ (በዮሀንስ በርሄ ከኦታዋ ካናዳ)

በዮሀንስ በርሄ፡ ኦታዋ ካናዳ

ታላቁ ጸሀፊ ቪክተር ሁጎ “ወቅቱ ከሆነ ሀሳብ የጠነከረ ነገር የለም” በማለት ይህን በጊዜ ማለፍ የማያረጅ ሀሳብ የተናገረው ከመቶ አመት በፊት ነው። ዛሬ ኢትዮጵያን ያጋጠማትን ቀውስ አደገኛነትና ከችግሩም ለመውጣት ልዩነታችንን አጥብበን በስርአቱ ብልሹነት ጊዜያዊ አትራፊ የሆኑትም ጭምር በአንድነት ህዝቡን ከአደጋ ልንታደገው  ግድ ይላል። ። ሀገሪቱ የከፋ አደጋ ላይ መሆኗን እያወቀ እንደማይመለከተው ከዳር የሚቆመውና አጥፊውን ቡድን የሚደግፈው በርካታ የትግራይ ተወላጅ ለህብረት ትግሉ ጥሪ በፍጥነት ተግባራዊ ምላሽ ካልሰጠ ሀገሪቱ የሚበለፅግባትና በሰላም ወልዶ ከብዶ የሚኖርባት መሆኗ ቀርቶ ህዙብ የሚተራረድባት ቀውጢ ምድር ልትሆን ትችላለች። ስለዚህም ዛሬ ወቅቱ የሆነው ሀሳብም ሁላችንም በሰላም መኖር እንድንችል ከኛው መሀል የወጡ ሀገር አጥፊዎች በአልጠግብ ባይነትና በጭካኔ ወደ ጋራ መቃብር ሲገፉን “በእኛ ስም ሀገር አታጥፋ ሰው አትጨርሱ አታጫርሱ” የሚል በተግባር የተደገፈ መልዕክት ለሕወሀት በአንድ ድምጽ ማስተላለፍ ነው።map of tgray

ከጥቂት ወራት በፊት ሕወሀት የሚቆጣጠረውን መንግስት የሚቃወሙ በርካታ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያኖች የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች አናወጠውት ነበር። ይኸው ትግል አሁንም አገርሽቶ ከበፊቱ በሰፋ መንገድ በመኪያሄድ ላይ ነው። አሁን በቅርብ ደግሞ የጎንደር ተመሳሳይ እንቅስቃሴ የሕወሀትን ሹማምንቶች በፍርሀት እያራዳቸው ይገኛል። ሀገሪቱ ውስጥ ተንሰራፍቶ ያለውን ከፍተኛ አፋኝ የፖለቲካ ሁኔታና ለሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሁሉም በሮቹ ተከርችመው መዘጋታቸውን ለሚያውቅ ሰው አሁን ያለው አስፈሪ አመጽ ብዙም ያልተጠበቀ አይሆንበትም። በአንፃሩ ደግሞ ሕዝባዊ ተቃውሞውን በመኮነን “በዲሞክራሲያዊ መንገድ ወደ ስልጣን የመጣውን መንግስት በህገወጥ መንገድ ለመገልበጥ የተቃጣ ሴራ ነው” ብለው የሚከራከሩ አይናቸውን በጨው የታጠቡ ቀጣፊዎች አሉ። እርጥባን ሰጪ ፈረንጆችን ለማስደሰት ሲባል በየአምስት አመቱ የአንድን አናሳ ቡድን ስልጣን እድሜ ለማራዘም የሚደረገው ምርጫ በሌለበት ምርጫ የሚሉት እቃ እቃ ጨዋታ ኢትዮጵያውያንን  ቀርቶ ለመሞኘት ፈቃደኛ የሆኑትን ፈረንጅ ወዳጆቻቸውንም አላሳመነም። በምርጫ ያሸነፋቸውን አስረውና ገድለው ሲያበቁ ፓርላማ የሚኮፈሱት እነበረከት “መንግስት የሆነው ህዝቡ መርጦን ነው” ቢሉ ማን ይቀበላቸዋል?

እንደ መንግስት ህዝብን ማሰባሰብ ሲገባ ህዝብን በታተኖ፣ የሀገር ድንበር ማስከበር ሲገባው ግራና ቀኝ ሀገር ቆርሶ ለባእድ እያደለ፣ የኢትዮጵያውያንን መብትና ክብር በያሉበት ማስከበር ሲገባው በባእድ እስርቤት ሲሰቃዩና በማንም ባለጌ በአደባባይ ሲቀጠቀጡ “ህገወጥ ስለሆኑ ነው” “የኛ ዜጎች ለመሆናቸው እርግጠኞች አይደለንም” እያለ ለወገን ሳይሆን ለጠላት ጥብቅና መቆም ልማዱ የሆነው  ሕወሀት የሚያራመደው ከፋፋይ የጎሳ ፖለቲካ ሀገራችንን ወዳልታሰበና የማይታወቅ አዘቅት በመግፋት ላይ ይገኛል። የዚህ ጽሁፌም ትኩረት እየተራገበ ያለው የጎሳ ፖለቲካ በአጠቃላይ በሀገራችን ኢትዮጵያና በተለይም በትግራይ ተወላጆች ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋና እንዴትስ አደጋው ሊወገድ እንደሚችል ግልጽ ውይይት የማድረግ አስፈላጊነት ላይ ነው።

‘ከተለያየ ጎሳ የመጡ የኢሕዴግ አባልት እያሉ ትግሬዎቹ ላይ የተለየ ትኩረት ማድረግ ለምን አስፈለገ?’ ብለው የሚጠይቁ አንባቢዎች ይኖራሉ። እውነት ነው ሕዝቡ በድምፁ ውክልና ሳይሰጣቸው “ጎሳችንን እንወክላለን” የሚሉ ጨካኞችና በውሸት ትርፍ የሚያጋብሱ ሸቃጭች ኢሕአዴግ ውስጥ አሉ። እንደዚህ አይነቶቹን ለማይዘልቅ ጥቅም በራሳቸው ዘመዶችና  የአካባቢያቸው ሕዝብ ላይ “ግደል” እያሉ አጋዚን የሚያዘምቱ ህሊና ቢሶች በሌላ ጽፍ እንመለከታቸዋለን። አሁን ግን በተለይ ትግሬዎች ላይ አሳዛኝ የሆነና ማስወገድ የማይቻል ልዩ ትኩረት የሚስቡ በርካታ ምክንያቶች አሉና ትኩረቱ በዚህ የህብረተሰባችን ክፍል ላይ ይሆናል።

በመጀመሪይ ደረጃ ሕወሀት ለከፋፍለህ ግዛ ቁማሩ እንዲመቸው የጎሳ ፖለቲካ በስፋት በሚያራምድበት ሁኔታ ይቅርና የጎሳ ፖለቲካ በህግ በታገደበት ግን የተረጋጋ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ በሌለበት ስፍራ ሁሉ ከጎሳ ወይንም ከማንነት ጋር የተቆራኘ ውይይትን ማስወገድ አዳጋች ነው። ምክንያቱም ፍትህ ከሌለ የቡድን ወይንም የጎሳ አድልዎ ይኖራል። በሁለተኛ ደረጃ ፍትሀዊ ስርአት በሌለበት ህብረተሰብ ውስጥ ሀብት የፖለቲካ ስልጣን መቆናጠጫ ይሆናል። በዛሬይቱ ኢትዮጵያችን ደግሞ የጎሳ አባልነት የፖለቲካ ስልጣን ያስገኛል። የፖለቲካ ስልጣን ደግሞ ወደ ንብረትና ሀብትነት ይለወጣል። እንደምናየው የኢሕአዴግ ፖለቲከኞችና ወዳጅ ቤተሰቦቻቸው ከተቀረው ዜጋ የተለየና የተሻል እድል እየተሰጣቸው ያልደከሙበትን ሀብት ያጋብሳሉ። ለዚህም ነው ማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ የኢኮኖሚ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ፖለቲካዊና ማህበራዊ ግንኙነቶች ፍትሀዊ ባልሆነ መንገድ ሲዋቀሩ ማየት የሰዎችን ስሜት ከምንም በላይ የሚረብሸው። በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያችን ያሉ በአነስተኛ ኢኮኖሚ እድገት ደረጃ ላይ ያሉ ሀገሮች ያለውን ሀብት ፍትሀዊ ባልሆነ መንገድ ጥቂቶች ሲቀራመቱት አብዛኛውን ህዝብ ለአስከፊ ድህነት እየዳረጉት ስለሆነ የሚያስከትለው ቅሬታና ጥላቻ በጣም ከፍተኛ ነው።

በርካታ የትግራይ ተወላጆች በነጻነት እጦትና በድህነት እንደሚማቅቁ ስለማውቅ በሕወሀት ስልጣን ላይ መሆን ትግሬዎች በሙሉ ተጠቃሚ ሁነዋል እያልኩ አይደለም። ብዙም ባይሆኑ ከፋፋይ ፖለቲካውን አሻፈረኝ ያሉ ሀቀኛ የትግራይ ልጆች “ነጻ አውጪአችሁ ነኝ” በሚለው ሕወሀት በጭካኔ ተገድለዋል በህየውት ተቀብረዋል ታስረዋል ተዋርደዋል ከስራ ተፈናቅለዋል። ልንክደው የማንችለው አንድ ሀቅ ግን አለ። ይኸውም መንግስት በሚያመቻቻቸው የጥቅም እድሎች ትግሬዎች ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው በላይ ተጠቃሚ መሆናቸው ነው። ብዙ ጥናት ማድረግ ሳያስፈልግ ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የመንግስትና የግል ሥራ ዘርፍ እንቅስቃሴ ብንቃኝ አብዛኛውን ተቆጣጥረው የያዙት ትግሬዎች መሆናቸው ፍንትው ብሎ ይታያል። አንድ ምሳሌ ብቻ ብንጠቅስ አኙዋኩና ሱርማው ወገናችን ከቀዬው እየተፈናቀል መሬቱ ለሌሎች ሲታደል ከዘጠና ከመቶ በላይ የዚህ ግፍ ጊዜያዊ አትራፊ የሆኑት የትግራይ ሰዎች ናቸው። ከዚህም ባሻገር ትግራይን መልሶ ለማቋቋም በሚል ሽፋን ከብዙ አመታት በፊት የተመሰረተው ኤፈርት የሚሉት በሁሉም ዘርፍ ኢኮኖሚውን አንቆ የያዘው ድርጅት መረን ለለቀቀው የወያኔ ባለስልጣናት ሙሰኝነት በጣም አትራፊ በመሆን የህዝብን ንብረት በአናሳዎች ቡድን በግለኝነት እንዲዘረፍ አድርጓል።

በመጨረሻም በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛውን የማስገደድ (ወታደር፣ ፖሊስ፣ እስርቤት…) ሀይል ይዘው የሚገኙት የሕወሀት አባላት ናቸው። ሕወሀት እወክላዋለሁ የሚለው ደግሞ የትግራይ ክፍለሀገርን ህዝብ ነው። እርግጥ ነው ከአንድ ጎሳ መምጣት ብቻውን በጎሳው ስም ለተስራ ወንጀል በጅምላ ተጠያቂ አያደርግም።  የዘርና ጎሳ አባልነት ሰው መርጦ የሚወስደው ነገር ስላልሆነ  ሰው በተግባሩ እንጂ በጎሳ አባልነቱ ሊገመገም ሊሸለምና ሊፈረድበትም አይገባም። በአንጻሩ መዘንጋት የሌለብን ደግሞ የምንነጋገረው በህይወት ላይ ተጽእኖ ስለሌለው ፍልስፍና ሳይሆን በህዝብ የእለት ከእለት ህይወት ላይ ከፍተኛ ጫና ስለሚያደርግ ወሳኝ ጎሳን ማእከል ያደረገ ፖለቲካነው። ሰዎች በተፈጥሯችን የወገናዊነት ወይንም ቡድናዊነት ስሜት አለን። አሳዛኙ እውነታም የሕወሀት መንግስት ባህሪይ አንድ ጎሳ ተጠቃሚ ሲሆን ሌላውን ተጎጂ የሚያደርግ ስለሆነ ከባለስልጣናቱ ጋር ያለን የጎሳ ግንኙነት እንደተራ ነገር እንዲታይ አይፈቅድም። ይሄም በመሆኑ አንድ ሰው አባል በሆነበት ጎሳ ሥም ወንጀል ሲፈጸም ምን አይነት የሞራል እርምጃና አቋም መውሰድ አለበት የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

ከዚህም ባሻገር እንኳንስ የሕወሀት ያላሰለሰ በጎሳ የማስፈራራትና የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ባለበት ይህም ባይኖር በሀገሪቱ ውስጥ የሚታየው ጥቂቶች በቅጽበት በለጽገው አብዛኛው ህዝብ ለረሀብና እርዛት መዳረጉ ብቻ“እነሱና እኛ” የሚል ሕዝባችንን በተለያየ መስመር የሚፈርጅ አደገኛ ስሜት ሊፈጥር ይችላል። ይህም ነው አንደኛው ምክንያቴ ትግሬዎች ዲሞክራሲያው ስርአት ለማምጣት በሚደረገው ትግል ዋና አካል መሆን አለባቸው የሚያስብለኝ። በትግሬ ስም የተደራጀ ቡድን በህዝብ ላይ ለአመታት ወንጀል ሲፈጽም የትግራይ ተወላጆች ጥፋቱን ማውገዝ ካልፈለጉ የተቀረው ህዝብ ምን ሊያስብ እንደሚችል መገመት አዳጋች አይደለም። በተለይ ከአመት አመት እየባሰበት የመጣው የሕወሀት ጭካኔና ህገወጥነት ልክ ባጣበት ወቅት በዝምታ መመልከት ውጤቱ መከራው የዛሬን ጉልበተኞች ቤት ጭምር እንዲጎበኝ መጋበዝ ነው።

አባል በሆኑበት ህብረተሰብ ወይንም ጎሳ አሸናፊነት መኩራራትና አንድ ቅርስ የሚጋሩት ሰው ስልጣን ላይ በማየት መደሰት ቀላልና የተለመደ ነገር ነው። ነግርግን የዚህ አይነት የቡድን ስሜት እንደ ሰው የማሰብ አቅማችንን ከሸረሸረውና “አጥፊው የኛው ነው” በሚል ተልካሻ ስሜት ግፍ ሲፈፀም ዝም ካሰኘን የሞራል ሀላፊነታችንን መወጣት ተስኖናል ማለት ነው። ማንኛውም የማሰብ አቅም ያለው ሰው እራሱን ከዚህ አይንት ኋላ ቀር አስተሳሰብ ነጻ በማድረግ ለፍትህ መቆም መቻል አለበት። ከዚህ ጋር አብሮ የሚሄድ  አባባል ሳስብ በቤተሰብ መሀክል የሚኖርን መጎዳዳት ለመግለጽ ወላጆቻችን የሚጠቀሙበት “የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አለወጣ” የሚለው ትዝ አለኝ። ጭፍን የሕወሀት ደጋፊዎች ይህን አባባል ለወጥ አድርገው “የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ሟቹን እርሺውና ዝፈኝ ለገዳይሽ” የሚሉ ይመስላል።

የትግራይ ተወላጆች ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን ለመገንባት በሚደረገው ትግል ውስጥ ትክክለኛ ስፍራቸውን መልሰው ለመያዝ ምን ማድረግ ይችላሉ?

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት እርምጃዎች በምሳሌነት የቀረቡ ሲሆን ከዚህም በላይ ማድረግ እንደሚቻል አምናለሁ።

አንደኛ፡ እንደ አንድ የተደራጀ ቡድን በመሆን ኃይሉና ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን የተቃዋሚዎች ስብስብ በመቀላቀል ኢሕአዴግ ወይንም በሌላ ስሙ ሕወሀት በስማቸው እየፈጸመ ያለውን ወንጀል ግልጽና ጠንካራ በሆነ መንገድ ማውገዝ፣

ሁለተኛ፡ ስልጣን ላይ ላለው መንግስት ባልደረቦች የሚሰጡትን ማንኛውንም የሞራልም ይሁን ቁሳዊ ድጋፍ በመንፈግ ሁሉንም በሚያሳትፍና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚቀርበውን የኢትዮጵያን ህዝብ ጥያቄ እንዲቀበሉ ማስገደድ፣

ሶስተኛ፡ ባላቸው የጎሳ ተመሳሳይነት ብቻ መንግስት ለትግሬዎች የሚሰጠውን የተለይ ቅርበት በመጠቀም ግልጽና ስውር የሆኑ እርምጃዎችን በመውስድ የሕወሀት ባልደረቦችን ወንጀል ማጋለጥና የስልጣን አቅማቸውን ማዳከም፣

አራተኛ፡ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት የራሱን ከፋፋይ እቅድ ለማራመድና የውይይት ርእሶችን ለመቆጣጠር ሲል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሚደግፋቸው ስብስቦች አለመሳተፍ፣

አምስተኛ፡ ትግሬዎች መሀክለ ያሉ ከፋፋዮችና ዘረኛ የሆነ አባባል በሌሎች ላይ የሚረጩ ግለሰቦችንና ስብስቦችን ግልጽና ጠንካራ በሆነ መንገድ በማውገዝ ድርጊታቸው በአጠቃላይ ለኢትዮጵያም ይሁን በተለይ ለትግራይ ተወላጆች እንደማይበጅ ማሳየት፣

የትግራይ ተወላጆች ይህን ከላይ የተዘረዘሩትን እርምጃዎች ቢወሰዱም ድርጊታቸውንና ምክንያታቸውን በጥርጣሬ የሚመለክቱ እንደሚኖሩ እገምታለሁ። ለዚህም ዋናው ምክንያት ሕወሀት ከሀያ አምስት አመታት በላይ ሲነዛ የቆየው የውሸትና የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ በህዝባችን መሀከል የነበረውን መተማምን መናዱ ነው። ይህንን በተንኮል የተሸረሸረ መተማመን መልሶ መጠገን ቀላል ባይሆንም ዛሬ የምንስወስዳቸው እርምጃዎች ሁኔታውን ሊያሻሽሉት ወይንም ይብስ ሊያበላሹት እንደሚችሉ መገምት ይበጃል። የትግራይ ተወላጆች የሚወስዱት እርምጃ ትክክለኛና ፍትሀዊ ከሆነ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያላቸውን አጋርነት የሚጠቁምና እራሳቸውም የወያኔ ተጠቂ የሆኑትን ብዙሀን የትግራይ ተወላጆች ከጥቂት ዘረኛ ወንጀለኞች የሚለይ ይሆናል።

በሌላኛው በኩል ደግሞ የወያኔን መንግስት በጭፍን እስከመጨረሻው ድረስ ለመደገፍ የወሰኑት ወገኖች የአሸናፊነትና የስኬት ፕሮፖጋንዳ እየረጩ ሀገሪቱ ሀብት በሀብት መህኗንና ፍትህ መስፈኑን ያውጃሉ። በተለይ ደግሞ ለትግሬዎች ሁሉም ነገር የተሳካ እንደሆነ አድርገው በመንገር ይሄን እድል በሌሎች እንዳይቀማ ሕወሀትን ብቻ መደገፍ እንዳለብት ይሰብካሉ። ከዚህም ባሻገር ሁሉንም የማስፈራራትና አንዱን ጎሳ ከሌላው የማናከስ ዘመቻቸውን ያኪያሂዳሉ። ነገር ግን ምንም ቢያደርጉ ሀገሪቱ ውስጥ የሰፈነውን ኢፍትሀዊ የስልጣንና ሀብት ክፍፍል እንዲቀጥል ማድረግ  አይቻላቸውም። የአብዛኛውን ህዝብ ያመረረ ቁጣ እስከመጨረሻው ማፈን የተቻለው መንግስት በታሪክ አልታየም ወደፊትም ሊታይ አይችልም። ምንም አይነት ቅጥፈት፣ ጉልበት፣ መሳሪያ፣ ሚሊሺያ፣ ፖሊስና ወታደር መጠቀም ለነጻነት የተጀመረን እንቅስቃሴ ማስቆም አይችልም። ብቸኛ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ፍትሀዊ የሆን ህዝብ የፈቀደው ስርአት መመስረት ነው።

የተለያየና አንዳንዴም ተፎካካሪ ፍላጎት ያለውን በርካት ህዝብ ማስተዳደር ምንግዜም ቢሆን ውስብስብ ነው። መንግስት በህዝብ ዘንድ ታማኝነትና ተቀባይነት እንዲኖረው የተለያየ ፍላጎትና ባህል ያላቸውን ህዝቦች በሀገራቸው ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ከቁጥራቸው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ድርሻ  እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል። ማንኛውም የህብረተሰብ አካል ምንም ያክል መልካም አስተሳሰብ ቢኖረውና በአላማው የጸና ቢሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ ያሉባት ችግሮች ብዛትና ውስብስብ መሆን አብዛኛውን ህዝብ ያላሳተፈ ቡድን ብቻውን ሀገሪቱን የማስተዳደር ሀላፊነትን ሊወጣው አይችልም። በተለይም እንደ ሕወሀት/ኢሕአዴግ ያለ አናሳ ቡድን ይህን ሀላፊነት በጭራሽ መወጣት አይችልም። ስለዚህም ውጤታማና ሁሉንም በአግባቡ የሚያሳትፍ ቢያንስ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በህጋዊነቱ ተቀባይነት ያለው የፖለቲካ ስርአት መፍጠር አለብን።

ሕወሀት መቼ እንደሚወድቅ አይታወቅ እንጂ መውደቁ አይቀሬ ነው። ጠራርጎ ሊውስደው መቻሉ የማያጠራጥር  የተቃውሞ አውሎንፋስ በሁሉም አቅጣጫ ከቦት ይገኛል። ከሕወሀት ባህሪይ እንደሚጠበቀው ሹማምንቶቹና ደጋፊዎቹ በተልያየ የሀገሪቱ ክፍል ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበትን ህዝባዊ አመጽ “ጥቂት ግራ የታግቡ ወንጀለኞች የሚውስዱት እርምጃ” እያሉ ሲያጣጥሉት እናያለን። እንቅስቃሴውን በጉልበት ሊያፍኑትም ይሞክራሉ። ሕወሀትና ደጋፊዎቹ የለውጡን ማዕበል እያዩ አላየንም ማለታቸውና ጭንቅላቷን አሸዋ ውስጥ እንደ ቀበረችው ሰጎን መሆን እየተጋጋመ የመጣውን የለውጥ ማዕበል ሊያስቆመውና ህዝብ ለነጻነት ያልውን ጥማት ሊያፍነው አይችልም።

በመጨረሻ ለትግራይ ሀቀኛ ልጆች የማቀርበው ጥሪ የሚከተለው ነው። የትግራይ ተወላጆች ሆይ፡ ላለፉት ሀያ አምስት አመታት ሕወሀት/ኢሕአዴግ ስማችሁን በመጠቀም የጥላቻን እሳት ሲያራግብና ሀገራችንን ከአንድነት ወደልዩነት ሲገፋ መቆየቱ አይጠፋችሁም። ይህን በማድረጉም የናንተን ባህሪይና ስም በማጉደፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላችሁን ከፍተኛ ታሪካዊ ስፍራ አበላሽቶታል። በዚህ ቡድን ከፋፋይ ፖሊሲ ምክንያት እናንተን ከመንግስት ጋር አንድ አድርጎ የማየት አደጋም እየጨመረ ነው። በዚሁ መንግስት ከፋፋይና የሀገርና ህዝብ ጥቅም የሚጎዳ ፖሊሲ ምክንያት ኢትዮጵያችን ወደ ማይሆን አዘቅት ብትወርድ ትግሬዎችን ጨምሮ ማንም ኢትዮጵያዊ አይጠቀምም። ማንነታችሁ ላይ ከፍተኛ ስፍራ የሚኖረውን የታሪካችሁን ምእራፍ እናንተንም በተገኝው አጋጣሚ ከመሸጥ የማይመለሰው የዘረኞችና ሌባዎች ስብስብ የሆነው ጠባብ ቡድን እንዲጽፈው አትፍቀዱ። አንድ እግራቸውን አድዋ ሌላውን ሀማሴን አንድ እጃቸውን አሜሪካን ሌላውን ቻይና አንፈራጠው ቀን ስትዞርባቸው ጥለዋችሁ ሊሮጡ የተዘጋጁ ከሃዲዎች አቀንቃኝ አትሁኑ። “ታሪካችን አይጎድፍም። እንደቀድሞውም ጥቅማችንም ጉዳታችንም ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ይሁን” ብላችሁ ተነሱ። መንግስት ያልፋል። የምንኖረው ከሕዝብ እንጂ ከመንግስት ጋር አይደለምና ደህንነታችንም ይሁን ብልጽግናችን ዋስትና የሚያገኘው ሕዝብ ለኛ ካለው መልካም ስሜት መሆኑን መቼም ቢሆን አንዘንጋ።

ይህ ጽሁፍ ከእንግሊዝኛ ወደአማርኛ ስንተረጉመው ለእጥረትና ለግልጽነት በማሰብ ለውጥ ተደርጎበታል። በመተርጎም የተባበሩኝን ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ።  ሀሳባችሁን በዚህ ኢሜይል አድራሻ ልትልኩልኝ ትችላላችሁ: yohannesb23@gmail.com

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s