እይታ “የጎንደር ሰልፍ” ከሰልፉ በኋላስ…? (ከአርሴማ መድህኑ)

ከአርሴማ መድህኑ

ኢህአዴግ እመራበታለሁ በሚለው ህገ መንግስት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን እንደ ዴሞክራሲያዊ መብት በመውሰድ የትኛውም ወገን በሚፈልገው ጉዳይ አቋሙን ለመግለጽ ሰልፍ ለማድረግ ‹‹ማሳወቅ››ብቻ እንደሚጠበቅበት ቢደነግግም መሬት ላይ ያለው እውነታ ከዚህ እጅጉን ያፈነገጠ በመሆኑ የጎንደሩ ደማቅ ሰልፍ የተከናወነው ከእውቅናው ውጪ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡The Gondar protest July 31, 2016

‹‹እውቅናውን ››ባልቸረው ሰላማዊ ሰልፍ የታየውን የህዝብ ጨዋ ድርጊት በመንተራስ ‹‹ሰልፍ ማድረግ ህገ መንግስታዊ መብት ነው››ወዘተ በማለት ሰልፉን ‹‹እውቅና በመስጠቱ የተደረገ ››ለማስመሰል ካድሬዎቹ በሶሻል ሚዲያዎች የሚያደርጉትን መንፈራገጥ እውነታውን በመግለጽ ማስቆም ይገባናል፡፡

ሰልፉ ከኢህአዴግ እውቅና ውጪ መደረጉ በራሱ በአገር ውስጥ ለሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቅ ትምህርት ሊሰጥ እንደሚገባው ይሰማኛል፡፡ህዝብን ከጀርባው ማሳተፍ የቻለ ማንኛውም አይነት ንቅናቄ በየትኛውም መንገድ ሊታፈን እንደማይችል ጎንደር ምስክር ተደርጋ ልትጠቀስ ትችላለች፡፡

ሰልፉ ጾታ፣ሐይማኖትና ዕድሜ ሳይለይ ህዝብን ወደአደባባይ ለማውጣት በሚያስችል መልኩ የተቀሰቀሰበት በመሆኑ ሰልፉን ለማፈን ተሰማርተው የነበሩ ኃይሎችን ለማሳፈር ችሏል፡፡ተቃዋሚዎች በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች እንዲህ አይነት መነሳሳት በህዝቡ ውስጥ በመፍጠር የስርዓቱን ዕድሜ ለማሳጠር ለታይታ ከሚሆኑ የለብ ለብ አጀንዳዎች በመጠበቅ ውስጥ ውስጡን ከህዝብ ጋር ሊያገናኛቸው በሚችሉ አጀንዳዎች ዙሪያ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡

ተቃዋሚዎች ህዝብ ጋር ደርሰው ወይም ህዝብን ሊያነሳሳ የሚችል የፖለቲካ አጀንዳ ፈጥረው አደባባዩን ለመሙላት ምን መስራት እንደሚገባቸው ጊዜ ወስደው ሊሰሩበት ይገባል፡፡እነርሱ ጋር ያለውን የሰው ኃይል ሳያጣሩና ለአደባባይ ህዝብን የጠሩበት አጀንዳ ምን ያል ህዝብን በአጋርነት ሊያቆመው እንደሚችል ሳያጣሩ በሚጠሯቸው ሰልፎች አመራሮቻቸውን ለእስራትና አባላቶቻቸውን ለፖሊስ ቆመጥ ሲዳርጉ ደጋግመን ታዝበናል፡፡Gondar protest rally

የጎንደሩ የአደባባይ ሰልፍ ለዘረኝነት እጅ ያልሰጠ፣ስልጣኔ የተስተዋለበት፣ኢትዮጵያዊነት ምናልባትም ከ1997 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወደሰበትና አጋርነት የታየበት ነበር፡፡ዛሬም ኢትዮጵያዊነትን ገዢዎቻችን ቆፍረው መቅበር አለመቻላቸውን፣ላለፉት 25 ዓመታት የደከሙበት የጎጥ ፖለቲካ የእንቧይ ካብ መሆኑ የተረጋገጠበትና አማራው በኦሮሚያ ክልል በጠራራ ጸሐይ በጥይት እየተቀጠፈ የሚገኘውን የኦሮሞ ህዝብ ወንድሙና እህቱ በማድረግ እንደሚቆጥር ያሳየበት በመሆን አልፏል፡፡

ህዝቡን ለአደባባይ የገፉት ምክንያቶች ወልቃይትን በግዴታ በትግራዋይነት መጥመቅ፣የኮሚቴ አባላቱን ማሰርና ለሁለት አሰርት ዓመታት በህዝቡ ላይ የደረሱ ግፎች ናቸው፡፡እነዚህ ጥያቄዎች፣ብሶቶችና መገፋቶች ተገቢውን ምላሽ በማግኘት ህዝቡ የጠየቀው ፍትህ እስካልተገኘ ድረስ የጎንደሩ ሰልፍ ምንም እርባና አይኖረውም፡፡
የሰልፉን ስኬት ከኢህአዴግ እውቅና ውጪ በመደረጉ ብቻ በመለካትም መኮፈስ አይገባም፡፡ሰልፉን እንደመንደርደሪያ በመውሰድ ግን ወደ ግቡ እንዲደርስ መስራት በኢትዮጵያ እውነተኛ ለውጥ ተፈጥሮ ለማየት ከሚፈልግ ዜጋ ሁሉ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡

አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከሁሉም አቅጣጫ እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ በሚገኝ የህዝብ ተቃውሞ እየተመታች ትገኛለች፡፡ይህንን የህዝብ መነሳሳት ለተሻለ ለውጥና አብዩት መምራት(shape) ደግሞ የወጣቶች፣የምሁራንና የፖለቲከኞች ድርሻ ነው፡፡

መንግስት በወሰዳቸው እርምጃዎች የተሰላቹ፣ለውጥ የሚናፍቁና ለዚህም የትኛውንም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጁ ቆራጦች በሞሉበት አገር ስትራቴጂስቶች ወደፊት እንዲመጡ ሁኔታዎች መመቻቸት ግድ ይላቸዋል፡፡

በቱኒዚያ፣በግብጽና በተለያዩ የአረብ አለማት በቅርቡ የተመለከትናቸው የለውጥ ማዕበሎች በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሱ በመሆናቸው አብዮቶቹ የሚፈጥሩት ማዕበል አገሪቱን (መርከቧን)ለማያባራ መናወጥ እንዳይዳርጋት ከወዲሁ ሁሉም ወገኖች የሚቀራረቡበትንና ለመነጋገር የሚያስችላቸውን ሁኔታዎች መፍጠርና ንቅናቄው የሚፈለገውን አይነት ለውጥ እንዲያመጣ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡

ስርዓቱ አይኑን አፍጥጦ መቶ በመቶ አሸንፊያለሁ ባለ ማግስት የተነሳበት ተቃውሞ እየለበለበው ከቁጥጥሩ ውጪ እየወጣ በመሆኑም የሚወስዳቸው እርምጃዎች እጅግ ሊከፉ እንደሚችሉ ግምት ውስጥ የሚከትና ይህ እንዳይፈጠር የሚሰራ አካል ከወዲሁ መፈጠር ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s