“ያበራሽን ጠባሳ ያዬ በእሳት አይጫወትም” (ነፃነት ዘለቀ)

 » “ያበራሽን ጠባሳ ያዬ በእሳት አይጫወትም” (ነፃነት ዘለቀ)

ነፃነት ዘለቀ (nzeleke35@gmail.com)

የሀገራችን ዕጣ ፋንታ በሕወሓት እጅ ሥር ከገባ  በትንሹ ሩብ ምዕተ ዓመት ደፍነን ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት እየገሠገስንነው፡፡ የዕዝ ጉዳይ ሆኖ የቀን ጎደሎ ገጠመንና እኛም ሀገራችንም በመጥፎ ስኬቶች እየተንበሸበሽን ዛሬ ላይ ደረስን፡፡ መስያሚያ ጆሮና መመልከቻ ዐይን በሌላቸው ወንድሞቻችን እየተረገጥንና በከፋፍለህ ግዛው እንግሊዛዊ የአገዛዝ ሥልት እየታመስን ብዙ ባጀን፡፡ ሆኖም ግና ሁሉ ነገር እንደሚጀመር ማለቁም አይቀርምና ይህ ከፋፋይ የወያኔ ሥርዓት-አልባ ሥርዓት ወደማይቀርለት ታሪካዊ ግብኣተ-መሬት ሊወርድ እያኮበኮበ መገኘቱ ለወዳጆቹ ቀርቶ ውድቀቱን ለሚመኙና ለውድቀቱም ለሚሠሩ የነፃነት ፋኖዎች ግልጽ የሆነ ይመስላል፡፡

ነገር ግን ሟች ይዞ ይሞታል ይባላልና ከዚህ እንደነቀርሣ ውስጣችንን በልቶ ከጨረሰን ፋሽስታዊ ሥርዓት በቀላሉ መገላገል የምንችለው ተበዳዮች ነን የምንል ወገኖች በተለይ ልዩ ዘዴ ቀይሰን ስንታገልና ንጹሓን ወገኖቻችን እንዳይጠቁ ስንከላከል ነው፡፡ በገበያ ግርግር ሌባ ይበራከታል፤ ሌባ ደግሞ የማመዛዘን ችሎታና የኅሊና ጤናማነት የለውም፡፡ ስለሆነም በግርግር ወቅት ለጉዳት የሚዳርግን ማናቸውንም ዓይነት የሥጋት ምንጭ አስቀድሞ ማድረቅ ተገቢ ነው፡፡ አለበለዚያ ጸጸቱ ለማይበርድ ከፍተኛ አደጋ መጋለጥ ይኖራል፡፡

ከሥጋት ምንጮች አንዱ ከዚህ ቀጥዬ የምነግራችሁ ነው፡፡ በደንብ ተረዱልኝ!

በሩዋንዳ ጭፍጭፋ ጊዜ ሕዝቡ አለውድ  ጎሣውን የሚገልጽ የመታወቂያ ወረቀት በግዴታ ይሰጠው ነበር፡፡ የዚያ ዓይነት ከሩዋንዳ ይልቅ ለጠባብ ዘር ቅድሚያ የሰጠ አሠራር ያስከተለውን መዘዝ በወቅቱ ታዝበናል፡፡ ሁቱዎች ቱትሲዎችን እንደዐይጥ እየጨፈጨፉ ሲጨርሷቸው በአብዛኛውና ለመለየት የሚቸገሩትን ሰው መታወቂያ እንዲያሳይ በማስገደድ መታወቂያው ላይ “ቱትሲ” የሚል የዘውግ ስም ካዩ በያዙት ገጀራ  ባልተለመደ ጭካኔ ቀረጣጥፈው ይገድሉት ነበር፡፡ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንዲህ ያለ መታወቂያ ላይ ከዜግነት ባለፈ ዘርን የሚጠቁም መንግሥታዊ ሥርዓት ሲያጋጥም መረገም እንጂ የሥልጣኔ ምልክት አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻር እኛም ተረግመናል፡፡

የሀገራችን ጉግማንጉጎች በዚሁ የለዬለት አፓርታዳዊ አሠራር በየመታወቂያችን ላይ “ዐማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ሀረሪ….” እያሉ ጽፈውበታል፤ “የተለዬ ዘር የለኝም፤ ‹ኢትዮጵያዊ› ብለህ/ሽ ጻፈው/ፊው” የሚልን ሰው በነፍጠኛነትና(የፈረደበት ዐማራነት) በቀድሞዋ ኢትዮጵያ ናፋቂነት እየፈረጁ ለስቃይና እንግልት ዳርገውታል – እንዲህ የሚልን ሰው ትግሬም ይሁን ኦሮሞ መታወቂያው ላይ “ዐማራ” ተብሎ እንዲጻፍበት ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ጦስም ብዙዎች በተለይም በአገር አቋራጭ አውቶቡስ ተሣፍረው ሲሄዱ መንገድ ላይ በሚያጋጥሙ የተደራጁ ሽፍቶች አማካይነት አለርህራሄ ተጨፍጭፈዋል – መታወቂያን በዘርና በሃይማኖት መፈረጅ ጉዳቱ ከባድ ነው(የሃይማኖቱን ሰማዕትነት ነው ብንለውም እንኳን)፡፡ በግድያና በጭፍጨፋ ለሚያምን አይሲሳዊ ኃይል ዜጎችን በዚህ መልክ በጎሣ ፈርጆ በመታወቂያ ሞታቸውን ማወጁ ለጭራቆቹ ትልቅ እገዛ ማድረግ ነው፡፡ ዜጎችን በመታወቂያቸው ላይ በዘር መቦደን ለወፈፌ ጠላት ጭዳ ማድረግና የጥፋት ሥራቸውን በግማሽ እንደማቃለል ነው፤ ቋንቋቸውን የሚችል ሰው እንደምንም አሳምኖ ማምለጥ ሲችል በመታወቂያው ብቻ ይጠቃል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ በኢትዮጵያ ያላችሁ የቀበሌ መስተዳድሮችና የወያኔው ባለሥልጣናት በምታምኑት ይሁንባችሁ ይህን መታወቂያ ነገ ዛሬ ሳትሉ አሁኑኑ ለውጡት፡፡መታወቂያ ላይ ከተፈለገ የደም ዓይነት እንጂ የዘር ማንነት አይጻፍም፤ ነውርና ወንጀልም ነው፡፡ አንደኛ አንድ ሰው የጠራ ማንነት ላይኖረው ይችላል – በአባቱ ኦሮሞ በእናቱ ትግሬ በአያቱ ዐማራ ቢሆን ይህ ዓይነቱ ሰው አንድ የዘር ሐረግ መዝዞ እንዲጠራበት ወይም እንዲታወቅበት ማድረግ አይቻልም፤ እርሱም አይፈልግ ይሆናል – ያለመፈለግ መብቱንም መጣስ ሰብኣዊ መብትን መጨፍለቅ ነው፡፡ ሁለተኛ ዘውጋዊ ማንነት በባለቤቱ ዘንድ መቅረት ይገባዋል እንጂ ከሀገራዊ ዜግነት በዘለለ መታወቂያ ወረቀት ላይ አስቀምጦ በኩራት ሊኮፈሱበት የሚገባ ጀብድ አይደለም፤ ማንም በፍቃዱ መርጦ ዐማራ ወይ ትግሬ – ይህን ወይም ያን አይሆንምና፡፡ ስንት ጅልነት አለ!

ስለዚህ ይህን ዓይነቱን ከድንቁርና ወይም ከተለዬ ድብቅ ፍላጎት የመነጨ አሠራር በአስቸኳይ መለወጥና ዜግነት በሚል ቦታ ላይ “ኢትዮጵያዊ” ብቻ ብሎ መጻፍ ከፊት ለፊት የተጋረጠን አደጋ በእጅጉ መቀነስ እንደሚቻል መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ነገረ ካለፈ በኋላ መቆጨት አይጠቅምም፡፡ ከአሁኑ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ሁሉም ዜጋ ይህን ወቅታዊ ማሳሰቢያየን በየሄደበት በማስተጋባት መንግሥት ተብዬው በዐይን የማይታይ ረቂቅ ተቋማችን መታወቂያ እንዲለውጥልን ጫና ይደረግበት፡፡ ደግሞም ይቻላል፡፡ አንዳንዴ ዜጎችን ማዳመጥ ተገቢ ነው፡፡ በጥላቻ ታውሮ ምንም አስተያየት ላለመቀበል ጆሮን መጠቅጠቅ ጉዳቱ ከፍተኛ ነውና ወያኔዎች እባካችሁን በዚህ ነገር አስቡበትና አፋጣኝ እርምጃ ውሰዱ፡፡ በውጭ ሀገራት ያላችሁ ወገኖቻችንም ይህ ጉዳይ በቀጥታ ባይመለከታችም ወገኖቻችሁና ዘመድ አዝማዶቻችሁ የዚህ ሸውራራ ወያዊ ሤራ ሰለባ ይሆናሉና ለዓለም አሰሙልን፤ በሩዋንዳ ለተከሰተው ዕልቂት አንደኛው መራጃ ይሄው በመታወቂያ ላይ ዘውግን የመጻፍ አላስፈላጊ ጣጣ ነበር፡፡ እርግጥ ነው – ወያዎች ይህን ያደረጉት የሥራ ዕድሎችን ከማከፋፈል አኳያ የማይፈልጉትን ዘውግ ከማዕዱ ለማራቅና እንዳስፈላነቱም ከዚያ ለከፋ አደጋ በቀላሉ ለመዳረግ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ነገር በእንግሊዝኛው የቃል አጠቃቀም backfire  ሊያደርግና ካሰቡት ውጪ የጎንዮሸ ጉዳት እንደሚኖረው አልተረዱትም፡፡ ወያኔዎች በጥቅምና በሥልጣን ጥማት ያበዱ፣ በቂም በቀልና በጥላቻ የሰከሩ ደምባራዎች ስለሆኑ የፊት የፊቱን እንጂ የአህያን ያህል አንድ አሥር ሜትር ያህል እንኳን ወደፊት ራቅ አድርገው መመልከት የማይችሉ፣ ዕውቀትና ጥበብ በራቸውን የጠረቀሙባቸው የአስተሳሰብ ድሆች ናቸው፡፡ ለማንኛውም “ያበራሽን ጠባሳ ያዬ በእሳት አይጫወትም፡፡”ና ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ የእሳትን አስከፊ ጉዳት ለማየት በግድ እጅን ወደነበልባላዊ እቶን መክተት አይጠበቅብንም – ቀድሞ ከተቃጠለ ሰው መማር አስተዋይነት ነው – ሊያውም በነፃና እንደክፍያም ከታሰበ ከከንፈር መጠጣ ባልዘለለ የሀዘን ስሜት ብቻ፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s