ደም ሳይፈስ ስርየት የለም! – ያሬድ በላይነህ ከ ብራሰልስ

 

Bale Robe 3

በእምነት ፍርሃት አንገቴን ቀብሬ እሰማው ከነበረው የሰንበት ስብከት ውስጥ አንድ ሃይለ ቃል ጎንትላ አነቃችኝ።”ደም ካልፈሰሰ ስርየት የለም” የምትል ጠጣር ቃል።ይህች ቃል እንደጥቅምት ብርድ ውስጤ ገብታ ልታንዘፈዝፈኝ ቃጣት።በመንፈሳዊው ምኩራብ ስር ቁጭ ብዬ ስጋዬ ተጎልቶ መንፈሴ ጸጥ ያለውን አዳራሽ ለቆ ወጣ።ቼበለው የሃሙሱ ፈረስ ነው ያለችው ዘፋኟ? ቼ ብዬ ሄድኩኝ ወደ ሰሜኑ የሃገራችን ክፍል የወልቃይትን የማንነት ጥያቄ ተቆናጦ የሩብ ዘመን የዝምታ እልፍኝን ሰብሮ ከወጣ የህዝቤ መንፈስ ጋር ልገናኝ።በእነ ወልቃይት ጠገዴ፣ጸለምት አርማጭሆ የጥንቱ የበጌምድር ጎንደር መንደር የጥንቶቹ ጀግኖች አናብስት መንፈስ በዚህ ትውልድ ደም ውስጥ ሲሯሯጥ ታየኝ።የዘረኞችን፣የጎጠኞችን ድንኳን ከስሩ ነቅሎ ሊጥል እንቢኝ ለሃገሬ እንቢኝ ለነጻነቴ ብሎ ሲወጣ ታየኝ።የዛ የቋራው አንበሳ የመይሳው ካሳ መንፈስ ቀስቅሶት የመከራውን ቀንበር ከጫንቃው አውርዶ ሊጥል ተማምሎ የወጣ ህዝብ ድምጽ በጎንደር አደባባዮች ላይ ሲያስገመግም ተሰማኝ።

በረጅሙ ተነፈስኩ የጎንደሩ የህዝብ ማእበል የጨቋኞችን አንገት አስደፍቶ አፈሙዛቸውን እንደሽመል አንከርፈው ሊውጣቸው የቀረበውን አይቀሬውን የህዝብ ቁጣ የሚጋፈጡበት የምጥ ቀን መድረሱን ሲመለከቱ ታየኝ።ሰልፍ ባዩ ቁጥር ንጹሃንን ለመቅጥፍ ቃታ ለመሳብ ይፈጥን የነበረ የገዳዮች ጣት አርፎ መቀመጡ ደነቀኝ።እነዛ ያለርህራሄ ቆመጥና ጥይትን ያዘንቡ የነበሩ እጆች ምን አዚም አግኝቷቸው ይሆን እንዲህ ደርቀው የቀሩት ስል ራሴን ጠየኩ።ላለፉት ሃያ አምስት አመታት በግድ ሊያጠልቁልን የሞከሩት የዘር ቡልኮ ተቀዳዶ በጎንደር አደባባዮች ላይ ነትቦ ተበጣጥሶ ሲወድቅ ታየኝ።”አረ ጥራኝ ጫካው አረ ጥራኝ ዱሩ ላንተም ይሻልሃል ብቻ ከማደሩ” እያለ ድንበር ተሻግረው ደጁን የረገጡትን ወራሪዎች ሲያርበደብድ የነበረ ያ የፋኖዎች የአልገዛም ባዮች መንፈስ በጎንደር ሰማይ ስር ዳግም ነግሶ ሳየው ኩራት ነገር ተሰማኝ።

ከፋፍለው ለመግዛት እንዲያመቻቸው ከኢትዮጲያዊነት ማማ አውርደው የጎጥ ስርቻ ስር የወተፉንን እኝህን የእፉኝት ልጆችን እስከመጨረሻው ሊጋፈጣቸው የወጣውን ህዝብ በምናቤ መልሼ አየሁት።ዘረኝነት በቃኝ፣ስደት በቃኝ፣ድህነት በቃኝ ብሄራዊ ውርደት መሸከም በቃኝ የሚል የብዙሃን የሃገሬ ህዝቦች ድምጽ ከየፈፋው ሲሰማ በብሄራዊ እንቢተኝነት የእብሪተኞችን ቅጥር ሲነቀንቅ ታየኝ።በኦሮሚያ የተለኮሰው የመብት ትግል አድማሱን አስፍቶ ወደሰሜን ተራሮች አናት ሲንጠራራ በጨቋኞቹ የእብሪት ልሳን አከርካሪውን ሰብረን ቀብረነዋል የተባለው አማራ ማንነቴን መልሱ፣የወገኖቼ የኦሮሞዎች ሞት የኔም ሞት ነው፣የፈሰሰው ደማቸው የኔም ደም ነው በማለት የዘረኝነት እርሿቸውን መልሶ የጨቋኞቹ አይን ላይ ሲደፋ ታየኝ።ከወደምስራቅ ኢትዮጵያም በአወዳይ አመጹ ሲቀጣጠል አሁንም በመሰዊያው ላይ የንጹሃን ፍትህን ጠያቂ ኢትዮጵያውያን ደም ሲፈስ ታየኝ።

የመብት ጩኸት፣ህዝባዊ እንቢተኝነት በቃኝ የሚል የተጨቋኞች የጋራ ድምጽ፣በግፈኞች አረር የሚፈስ የእንቢ ባዮች ደም ድምጽ ወደጸባኦት ሲጮህ ተሰማኝ።እውነት ነው “ደም ካልፈሰሰ ስርየት የለም” ነጻነት ካለመስዋእትነት አትገኝም።ካለትግል ድል የለም።ማንም ነጻነትን በወርቅ ዋንጫ ከጨቋኞች እጅ በስጦታ ተችሮ አያውቅም ከጨቋኞቹ የብረት መዳፍ በሃይል ፈልቅቆ ይወስዳታል እንጂ።መንፈሴ አላረፈም ይህ እንቢታ የእሩብ ዘመንን ቀንበር ሲሰብር፣የግፈኞችን የእብሪት ግንብ ሲነቀንቅ፣ለነጻነት ሲሉ በግፍ የታሰሩትን እግረሙቅ ሲፈታ ታየኝ።እስከመቼ የጥቂቶች የበላይነት፣እስከመቼ በሃገር ባይተዋርነት፣እስከመቼ ስደትና ጉስቁልና እስከመቼ የዘረኞች የእብሪት አገዛዝ ተጭኖብን መንፈሴና ነፍሴ አላረፉም ዳግም በኦሮምያ እንቢተኝነት፣በአማራ፣በደቡብ፣በጋምቤላ… ይህ ትግል አይቆምም አልኩ ለራሴ የጭቆና ቀንበር ሳይሰበር፣እብሪተኞች ሳይንበረከኩ፣የህግ የበላይነት በሃገሬ ምድር ሳይሰፍን የለም…አይሆንም…አልኩ ለራሴ።መንፈሴ የትግሉን ጎራ አዳርሶ በድን ስጋዬ ወደተወዘፈበት የሰንበት ምኩራብ ስመለስ ካህኑ”ደሙ ስርየትን ሞቱም ትንሳኤን ያመጣል እስቲ ተመልከቱ ዛሬ በቀራንዮ ተራራ ላይ የመስዋእቱ የድል ታሪክ እንጂ ሽንፈት አይታወጅም በጎልጎታ ትንሳኤ እንጂ ሞት አይነገርም”ሲሉ እውነት ነው አባ አልኩኝ እውነት ነው ዛሬ ህዝቤ የግፍ አገዛዝ በቃኝ ብሎ ከመሰዊያው ላይ ቆሟል ጨቋኞችን ሊፋለም፣የግፍ ቀንበሩ አሽቀንጥሮ ሊጥል፣ረሃቡን፣ስደቱን የዘመናት ጉስቁልናውን ጥሎ በትግሉ ነጻ ሊወጣ አሻፈረኝ ብሏል።አዎ ዛሬ ትንሳኤ ቀርቧል የፈሰሰው የብዙሃን የሃገሬ ልጆች ደም ስርየትን ሊያመጣ ቀርቧል።ሁሉም ተባብሮ የሚቆምበት የጎጠኞችን እግረሙቅ ሰብሮ የሚወጣበት የድል ቀን ቀርቧል።ሃገር ውስጥ ያለው ሰላማዊ ትግሉን በእንቢተኝነት ገፍቶ የዚህን አጥፊ ስርአት ግብአት ሊያፋጥን፣በውጭ ያለውም ስደተኛ የዚህ ትግል አጋርነቱን በተግባር የሚያረጋግጥበት፣ስደቱ የሚቆምበትን ቀን እውን ለማድረግ ሳይከፋፈል በጋራ የሚቆምበት የድል አጥቢያ ላይ ነው ያለነው።

በጥቃቅን አጀንዳዎች ተለያይቶ ለስርአቱ የመከፋፈል ሴራ እጅ ሰጥቶ የሃገሩን ጉዳይ ችላ የሚልበት ሁኔታ መቆም አለበት።ካለበለዚያ የዲያስፖራው የስደት በሰው ሃገር የባይተዋርነት ህይወት ማብቂያ አይኖረውም።ጭቆና የወለደው ድህነት፣ረሃብና ስደት በቃ ሊባል ይገባል በጋራ በመቆም። የካህኑ ስብከት አብቅቶ የትንሳኤ መዝሙር ሲያስተጋባ መንፈሴ ከመነነበት የሃሳብ አለም ነቃ።ደም ሳይፈስ ስርየት ወይም ፈውስ የለም በሚለው የስብከት ጀልባ ተሳፍሬ ከቀዘፍኩበት የሃሳብ አለም የመለሰኝ የትንሳኤው የድል መዝሙር የሃገሬ ትንሳኤ መቅረቡን አሳየኝ ልቤ የሃሴት ድቤውን እየደለቀ እግሬ የቤተክርስትያኑን አጸድ ለቆ ወጣ።መንፈሴ ግን እንደ ግብጹ ታህሪር አደባባይ በመጥለቅለቅ ላይ ያሉትን የሃገሬ የብሶት አንባዎችን ሊቀላቀል ነጎደ።የብዙሃንን ህዝብ አመጽ ሊገቱ ያልቻሉት የሙባረክ ታማኞች ግመላቸውን እየጋለቡ ህዝቡን በጅራፍ እየገረፉ ሊበትኑ ሲባክኑ ህዝቡ ከግመላቸው ላይ እየገለበጠ ሲረመርማቸው በሩቁ ታየኝ።የኛዎቹም ከተቀመጡበት የእብሪት ማማ ላይ የሚገለበጡበት ቀን መቅረቡን እያየሁ እግሬ ወደመራኝ ተጓዝኩ።መንገዶች ሁሉ ወደ ሃገሬ የብሶት አደባባዮች፣የእንቢታ የአልገዛም ባይነት አንባዎች ያመራሉና ካለጥርጥር ጉዞዬ ወደ ድል ጎዳና ነው።የታሉ እኒያ ተርብ የሃገሬ ልጆች የታሉ እኒያ የጠባቦችን የዘር ጥብቆ ለባለቤቶቹ ወርውረው የሙስሊም ኮሚቴዎች ነጻ ይውጡ፣እነበቀለ ገርባ የነጻነት ድምጽ የሆኑን ነጻ ይውጡ በማለት የከፋፋዮችን ወገብ በድንጋጤ ከፍለው የጣሉ አንበሶች?የታሉ እኒያ ሞት እና እስራት ያልፈታቸው ሌንጫ ኦሮሚያ የኦሮምያ አንበሶች የገዳዮችን የእብሪት ክንድ የሰበሩ በሞታቸው የሃገር ትንሳኤን እያቀረቡ ያሉ ወገኖቼ፣የታሉ እነዛስ ከባህር ማዶ ሆነው የውጩ አለም ምቾትና የሩጫ ህይወት ሳይገታቸው ለታፈነው ድምጽ የሆኑት ስደተኛ ወገኖቼ፣በዚ ወሳኝ የቁርጥ ቀን ላይ የተገፊዎች የድረሱልን ጩኸት ሊቀሰቅሳቸው ይገባል።ጥሩልኝ የሃገሬን ልጆች እስከመቼ የመከራን ቀንበር ሸሽተን ተሰደን እናመልጠዋለን።ጭቆናን በተባበረ ክንድ ታግሎ የመጣያው የድል ቀን ቀርቧል እኔ መንፈሴም እግሬም ወደ ሃገሬ አደባባዮች ነው እንደህዝቤ እናንተም ተከተሉኝ በውጭም በውስጥም ያላችሁ የሃገሬ ልጆች።

06/8/2016
ያሬድ በላይነህ ከ ብራሰልስ

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s