ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቄስ አይለቅም – ወያኔ እና የግንጠላ ነጋሪት (ታሪኩ አባዳማ)

ታሪኩ አባዳማ – ጳጉሚት 2008

“ልክ እናስገባለን” በሚል ድንፋታ ከሁለት ዓመታት በፊት የተጠነሰሰው የፍጅት ሴራ “እንመነጥራለን”፣ “እንጠራርጋለን”… በሚለው የባንዳዎች የክተት አዋጅ ተጠናክሮ የንፁሀን ዜጎችን ደም ማፍሰስ ቀጥሏል። መሬቴን ተቀማሁ ብሎ አቤቱታ በራሱ ቄየ ድምፁን ሊያሰማ የወጣን ዜጋ በጥይት ፣ ነጭ ካኒቴራ ለበስክ ተብሎ ጥይት ፣ ወህኒ ቤት እሳት ሲነድብህ ለምን ሸሸህ ብሎ ጥይት ፣ ልጄ ከሚጫወትበት ሜዳ ላይ በጥይት ተደብድቦ ላነሳ ብሔድ አደባባይ ላይ አረመኔአዊ ድብደባ ፣ መፅሀፍ ለመሸጥ አዙረሀል በሚል ድበደባ ወህኒ መታጎር እና ንብረት ዘረፋ ፣ ፌስቡክ ላይ እንዲህ አልክ ያንን አነበብክ ተብሎ ጥይት… በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ተሰምቶ ደርሶ የማያውቅ ግፍ እና ሰቆቃ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ነው።

የአባይ ፀሀዬ ‘ልክ እናስገባቹሀለን’ ትርጉሙ ያኔ ያልገባቸው ዛሬ በተግባር ሲፈፀም ሳይገለፅላቸው አልቀረም ብለን እናምናለን።

ሰሞኑን ደግሞ ሌላ የወያኔ/ኢህአዴግ አፈርሳታ ተጠርቶ ዳግማዊ አውጫጪኝ በዝግ ጉባኤ ሲካሄድ መሰንበቱን ሰምታቹዋል። የወያኔ ሁለተኛ ዙር አፈርሳታ በተለመደው እና ፀሀይ በሞቀው ‘አሳሳቢ’ ጉዳይ ዙርያ ተወያይቶ በመቋጫው ላይ “ይሄ አደባባይ እየወጣ ‘ሌባ ሌባ’ የሚለንን ሁሉ እንመነጥራለን” በሚል ቆራጥ ውሳኔ ተጠናቋል… የ‘ልክ እናስገባለን’ ደቀ መዛምርት ፉከራ መሆኑ ነው። ይኼ ነው በኦሮሞ እና አማራ ህዝቦች ላይ የወያኔ የወቅቱ ወታደራዊ ክተት ዘመቻ ትርጉም።

እናም የወያኔ ቱባ ሹማምንት ሁሉም “ሌቦች” ነን ሲሉ በድጋሚ አረጋግጠው ግን ከመካከላቸው አንድም ሌባ ስሙ ሳይጠራ ችግሩን ‘ከጥቅምት’ ጀምሮ እንፈታለን በሚል ‘ተስፋ’ ያዘለ መግለጫ አወጡ… አላገጡ ማለት ሳይሻል አይቀርም። ህዝብ የሚያውቀው ሌባው ሌባ ብቻ ሳይሆን ውሸታም መሆኑንም ነውና የጥቅምቷን ቀጠሮ እንኳ ‘ስንተዋወቅ አንተናነቅ’ በሚል የጨዋ ወግ ህዝቡ እየተሳለቀበት ይገኛል። ‘አይነጋ መስሏት…’  ምን አደረገች አሉ?

ያወጡትን መግለጫ ስንመረምረው ወያኔዎቹ ሌባ መሆናቸውን ሳይክዱ ነገር ግን በሚሊዮኖች ዜጎች አንደበት ሌባ መባላቸው ይበልጥ ያበሳጫቸው መሆኑን እንገነዘባለን። በቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው ከጥቅምት በፊት ሊመነጥሩ የተነሱትም ሌብነትን ሳይሆን ሌባ ሌባ የሚላቸውን ህዝብ መሆኑንም በማያሻማ ቋንቋ አረጋግጠው የጦርነት ክተት አውጀዋል። እነሱ እንደተመኙት የሚሊየን ህዝቦችን የነፃነት ጥያቄ በብረት ከደፈጠጡ ፣ እንደታቀደው ጥቅምት ላይ ሌባ ሌባ የሚል ህዝብ ሙሉ ለሙሉ መደምሰሱን ካረጋገጡ መፍትሔ ተገኘ ማለት ነው – ችግሩ ተፈታ ማለት ነው። ከዚያ ሌብነቱ ተጠናክሮ ሲቀጥል ሌባ ሌባ የሚለው ድምፅ በዘመቻ በርብርቦሽ ፀጥ አለ ይባላል – ያኔ ወያኔ የድል ሪቺት ይተኩሳል።

ጉልቻው ጠ/ሚኒስትር ‘ልክ እናስገባቸዋለን’ ሲል የጌቶቹን መፈክር አስተጋባ… በገዛ ራሱ ላይ የወንጀል ኤግዚቢት ፋይሉን እያከማቸ ንፀሀን ዜጎችን እየጨፈጨፈ የቀጠለ ስርአት እና ጠ/ሚኒስትር።

ባለፈው ዓመት በተጠራው የመጀመሪያው አፈርሳታ ‘ውስጣችን የተሰገሰገውን’ የሙስና ኔት ወርክ ለመበጣጠስ ‘በቁርጠኝነት’ ተነስተናል ብለው ወያኔዎቹ ያሰሙትን ቀረርቶ በተለይ ሎሌው ጠ/ሚኒስትር የደሰኮረውን የምትዘነጉት አይመስለኝም። ‘የተመታታ የወያኔ አፈርሳታ’ በሚል ርዕስ አጠር ያለ አስተያየት መዘንዘሬን ታስታውሱ ይሆን?

መለስ ዜናዊ ከሞተ በሁዋላ ‘ህወሃት ሊጠገን ይችላል’ ሲሉ አንዳንዶች ስለ ህወሃት የነበራቸውን አቋም ጠግነናል ብለውን በድረ ገፃቸውም ‘ሀይለማርያም ደሳለኝ ስር ነቀል ለውጥ ሊያመጡ በወያኔ ብልሹ አስተዳደር ላይ በቁርጠኝነት ተነሱ ሲሉ አምዳቸውን ማጣበባቸው አይዘነጋም። ያኔ እንዳሁኑ አካሄዱን በጥሞና ለሚያየው ሰው ሌቦች በነገሱበት አገር የሌቦች አፈርሳታ ጠርቶ ማንስ ማንን ሌባ ነህ ሊል ይችላል? ብለን መጠየቃችን የገዢዎቻችንን ርካሽ ተፈጥሮ ህዝቡ በጉልህ የተገነዘበው መሆኑን ለማንፀባረቅ ነበር። እነኛ አቋማቸውን የጠገኑ ወዳጆቻችንም የኔ አስተያየት አምዳቸው ላይ እንዳይወጣ አገዱኝ። በጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ትግሉን በፅናት እና አላንዳች ማወላወል መደገፉ አማራጭ የሌለው ግዴታችን መሆኑን በማሳሰብ ጉዳዩ አለፈ። ተንጋለው ቢተፉ ተመልሶ ባፉ ሆነና አሁን ህዝባዊው ትግል እየጎመራ ሲመጣ ያንን የጠገኑትን አቋም ዘንግተው ሌላ ጥገና እያካሄዱ ይመስላል… ህዝባዊ ትግል እንደ ጋቢ ተጠምዝዞ የሚያደርቁት ኩታ አይደለም።

ሃያ አምስት አመታት በጠራራ ፀሐይ መሬቱን ፣ ጥሬ ሀብቱን ፣ ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀስ ንብረቱን ሲዘርፉት ፣ ሲያፈናቅሉት እና መድረሻ ሲያሳጡት የቆየው ህዝቡ ነው። ታማኞቹን እየለየ ባንድ ጀምበር ሚሊየነር የሚያደርገው የወያኔ ታምራዊ ኢኮኖሚ አገራዊ ፋይዳው ቢከፍቱት ተልባ መሆኑ በተደጋጋሚ ታይቷል። ይህ በዘረፋ የተራቆተ ህዝብ ታዲያ ጣቱን ወደ አልጠግብ ባዩ ወያኔ ቀስሮ ‘ሌባ ሌባ’ አያለ መቆጣቱ ምን ጥፋት አለው። ያውም ሌባ መሆኑን ያልካደ መንግስት።

“እኛ ረሀቡን ችለን ብንገዛላቸው እነሱ ጥጋቡን ችለው መግዛት ተሳናቸው” ሲሉ አንድ አዛውንት የተናገሩትን ልብ ይሏል።

አሁን ችግሩ ያለው ጉዳዩ ሌባ ናችሁ በሚል የሚገታ አለመሆኑ ስለተከሰተላቸው መሰለኝ – ይልቁንም ‘በሌባ አልገዛም’ የሚለው ድምፅ በሚሊየኖች ቁጣ ታጅቦ አደባባይ መውጣቱ ከዚያም አልፎ አለም ትዝብቱን በይፋ መግለፁ ክፉ መዘዝ ከፊታቸው መጋረጡን እያሳበቀ ከመሆኑ ላይ ነው። በ‘ሌባ አንገዛም’ የሚለው ህዝባዊ ቁጣ እያየለ ዳር እስከ ዳር ማስተጋባቱ እና ወያኔ ያጠረውን የጎጥ ማንነት አፍርሶ ዜጎችን ባንድ አላማ ጥላ ስር ማሰለፉ ለወያኔ በርግጥም አሳሳቢ ነው።

ህግ የሚሉት ነገር በአገሪቱ ባይኖርም እንኳ እንደ ቆየው ወግ እና ስርአት ፣ እንደ ሀይማኖት እና ፈሪሀ እግዚአብሔር ባህል ቢሆን ኖሮ ሌባን በቅድሚያ ‘ሌባ’ ብሎ የሚጠራው የተዘረፈው ፣ የተጠቃው ፣ የተመዘበረው ወገን ነበር። ሌብነቱን እንደ ወያኔ ቀድሞ ያመነ ደግሞ ሌቦች ወደሚሰለፉበት ተራ ወደ ወህኒ ይቀላቀላል እንጂ አይን አውጥቶ ሌባ ብሆንም ግን ስለ ርኩስ ባህሪዬ ማብራሪያ ለማግኘት ካሻችሁ እስከ ጥቅምት ጠብቁኝ ሲል አያላግጥም። የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ ነው ነገሩ።

ተደረገ ስለሚሉት ስብሳባ እና አሁን በተከታታይ ስለሚያስተጋቡት ፕሮፓጋንዳ ስናነሳ ቆም ብለን የምናነሳው ጉዳይ አለ። ለመሆኑ እነኝህ ዛሬም ዘላቂ መፍትሔ አለን ፣ ዛሬም እንታደሳለን የሚሉ ተሰብሳቢዎች (ድርጅቶች) እነ አባዱላ (ምናሴ) ደግሞም እነ በረከት (መብረሀቱ) ምን እና ማን ናቸው። የአየር ፀባዩን ተከትሎ ቆዳውን የሚሸለቅቅ እና የሚታደስ እባብ ግን ሁለጊዜም እባብ ብቻ ይመስለኝ ነበር። ወያኔ እየታደስኩ ፣ ቆዳዬን እየሸለቀኩ እገዛለሁ ሲል መልሳችን ‘አዎ እባብ ቆዳውን ሸልቅቆ ሊታደስ ይችላል – እባብ መሆኑን ግን ከቶ አይቀይረውም’ እንላቸዋለን። ትግሉ የእባቡን አናት ቀጥቅጦ ከትቢያ ጋር የመቀላቀል ቁርጠኝነት የተላበሰ መሆኑንም አንዲያውቁት ማስገንዘቡ ደግ ነው።

ኢህአዴግ በሚል ስም አፈርሳታ የሚቀመጡት ከየት ወዴት የመጡ ናቸው ለማለት ያህል ነው — ጥያቄውን በአግባቡ መመለስ ደግሞ ባልተወለደ አንጀት ሲፈፀም ለቆየው ጭካኔ ፣ የዘረፋ ፣ የፍትህ እጦት ፣ አስተዳደር ብልሹነት ፣ የዘፈቀደ ግድያ… ቁልፍ የሆነ መልስ እናገኛለን።

እነ ምናሴ (አባዱላ) እና መብርሀቱ (በረከት ስምኦን) በረሀ ላይ በምርኮ ለወያኔ እጃቸውን የሰጡ እንደመሆናቸው ድርጅት የፈጠረላቸው ወያኔ ነው። አላማቸውን የዘረጋላቸው ፣ ተልእኳቸውን ያስተማራቸው ወያኔ ነው። መከተል የሚገባቸውን አደረጃጀት ስልት ፣ ሌላ ቀርቶ ምን ያህል ሀብት ለራሳቸው ዘርፈው ወያኔን ለላቀ ዘረፋ ሁኔታውን ማመቻቸት እንዳለባቸው የሚያስጠናቸው ያው ጌታ ሆኖ የፈጠራቸው ወያኔ ነው። በማናቸውም ጊዜ ጠፍጥፎ ከፈጠራቸው እና በሎሌነት ትእዛዙን ፍላጎቱን ሲያስፈፅምባቸው ከቆየው ወያኔ ውልፍት የማለት ብቃትም አቅምም የላቸውም። ህዝብ የሚያውቃቸውም በዚህ መልኩ ነው።

እንግዲህ አስቡት የኢትዮጵያ ህዘብ ስለ ፍትህ እጦት አደባባይ ቆሞ ሲጮህ መፍትሔ ልንሰጠህ ነው ብለው ከፈጣሪያቸው ከጌታቸው ጋር አንድ አዳራሽ ውስጥ የተሰበሰቡት እነኝህ የጦር ምርከኞች ናቸው። የወልቃይት ህዝብ ስለ ማንነት ከተባለማ እኔ ማን እንደሆንኩ እናንተ አትነግሩኝም ብሎ ሲነሳ ‘ጉዳዩን የትግራይ ክልል ተመልክቶ መፍትሔ ይሰጣል’ በሚል ተስማምተናል ያሉት እነ በረከት ስምኦን እና በነሱ የስለላ ሰንሰለት ተቀፍድዶ ለወያኔ የገበረው የጦር ምርከኞች ስብስብ ነው።

ለፍትሀዊው ህዝባዊ ጥያቄ ወያኔ እየሰጠ ያለው ምላሽ እጅጉን አሳፋሪ ቢሆንም የማይጠበቅ ግን አይደለም። ሌቦቹ ከህዝባዊ ፍርድ ጋር ቢጋፈጡ የሚሆነውን ጠንቅቀው ያውቃሉና ምርጫቸው እጃቸው ላይ ያለውን ማናቸውንም መሳሪያ ተጠቅመው ዕድሜያቸውን ማራዘም ነው። ይኼ ማንኛውም የመንደር ሌባ ሳይቀር የሚጠቀምበት ስልት በመሆኑ ሊገርመን አይገባም።

ዞሮ ዞሮ ግን ሰማይ ዝቅ መሬት ከፍ ቢል ነብሰ በላ ሌባ ከተጠያቂነት ማምለጥ አይችልም ብዬ ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልውሰዳችሁ።

ወያኔ ገና ሲጠነሰስ የድርጊት መርሀ ግብሩን ነድፏል ፣ አንደኛ ጠላት ፣ መለስተኛ ጠላት የሚላቸውንም ወገኖች በዝርዝር አስፍሯል ፣ መጨረሻ ግቡ ትግራይ የተሰኘውን የኢትዮጵያ አካል ገንጥሎ አዲስ መንግስት መመስረት መሆኑንም በመተማመኛ አፅድቋል። ጫካ የተረቀቀው እና የፀደቀው የግንጠላ ፣ የበታኝነት ፣ የመከፋፈል እና በዘር የመናቆር ባህል በህግ እና ህገ መንግስት ሰነድ ውስጥ ሁነኛ ምዕራፍ ተሰጥቶት ደደቢት የተረቀቀውን ‘በህገ መንግስቱ’ መሰረት እየተባለ ፍጅቱ ተባብሷል። ስለ ህግ እና ህገ መንግስት ሀ ሁ የሚያውቅ መንግስት እንበለ ህግ ጭፍጨፋ እያካሄደ በህገ መንግስት እየተገዘተ ህዝቡን አያሰለችም። ገና ያኔ ድሮ ደደቢት ላይ ወልቃይት ፣ ኮረም እና ሰቆጣን ሳይቀር የትግራይ ክልል ናቸው ሲል ካርታ ነድፎ የጨረሰውን ጉዳይ ዛሬ ደርሶ እንደ ህፃን የሚሸነገል አለ ይመስል ‘ክልሎች የተዋቀሩት በህገ መንግስቱ መሰረት ነው ይሉናል። ይህን የህወሃት ፕሮግራም እነሱው ሽግግር ብለው በጠሩት በስልጣን መያዣ ሰሞን እነሱ መልምለው እና ጋብዘው በጠሩት ጉባኤ ላይ ፀደቀ ‘ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ድንብር ተከለለ’ አሉ።

የክልሎች ዳር ድንበር በ’ህገ መንግስቱ መሰረት ተነድፎ ሲያበቃ የማያዳግም መፍትሔ አግኝቷል’ የሚሉን የደደቢቱን ካርታ በማስረጃነት እያጣቀሱ ነው።

ዛሬ በወያኔ አባላት እና ደጋፊዎቻቸው ጎላ ብሎ የምንሰማው አስቂኝ ሮሮ አለ። በትግራይ ተወላጆች ላይ እዚህ እና እዚያ ጥቃት ተሰነዘረ ፣ የትግራይ ንብረት የሆነ ተቋም ላይ ጥቃት ተፈፀመ… ወዘተ። በመሰረቱ ህዝቡ የጥቃቱ ኢላማ ያደረገው አይኑ እያየ እያወቀ ባንድ ጀምበር ሚሊየነር በሆኑ ዘራፊዎች ላይ ነው። ህግ እና ስርአት በአገሪቱ የሰፈነ ጊዜ የነኝህ ዘራፊዎች ተግባር ይበልጥ በዝርዝር ይወጣል – አሁን ግን ከህዝብ አይንና ጀሮ የተደበቀ አንዳችም ዘረፋ ሆነ ዘራፊ እንደሌለ ሁሉ ከቁጣው ማዕበል ሊያመልጥ የሚችል የተዘረፈ ንብረት ሆነ ዘራፊ የለም። ‘ወያኔ ሌባ’ የሚለው ጩኸት ከዳር እስከ ዳር እያስተጋባ ነው። በትግራይ ህዝብ ስም የማፊያ እና የዘረፋ ቡድን አቋቁመህ አገር ስታራቁት ህዝቡ አይቶሀል ፣ ደርሶብሀል እናም ያጋልጥሀል ብሎም አመቺ ሆኖ ባገኘው ዘዴ በገዛ ራሱ ውሳኔ እና መንገድ ይቀጣሀል።

ሌባው ትግራዊ ከሆነ ፣ ዘረፋው በትግራይ ወገናችን ስም የሚካሄድ ከሆነ ድርጊቱን የማውገዝ አና የመታገል ጉዳይ በትግራይ ህዝብ በራሱ ተሳትፎ ጭምር ሊፋፋም ይገበዋል። በስሜ አትነግዱ ፣ በስሜ ፀያፍ ፀረ አገር ተግባር አይፈፀም ብሎ ሊነሳ የሚገባው የትግራይ ህዝብ ነው።

እነኝህ የተነቃባቸው ዘራፊዎች ድሮ ደደቢት ላይ ትግራይን ገንጥለን ሪፐብሊክ እናቋቁማለን ባሉት መሰረት እነሆ ዛሬ ህዝቡ ከዳር እስከ ዳር አንቅሮ ሲተፋቸው ‘ይህ አመፅ ካልቆመ አገሪቱ የመገነጣጠል አደጋ ያሰጋታል’ ይሉናል ፣ ያስፈራሩናል። የዘረፍነውን ሀብት ብትነኩ ፣ የሾምነውን ሙሰኛ ምስለኔ ብታባርሩ ፣ ፍትህ እያላችሁ አደባባይ ብትወጡ ፣ የማንነት ጥያቄ እያነሳችሁ ብትሟገቱ ‘ትግራይን እንገነጥላለን’ አገሪቱም ትበታተናለች እያሉ በይፋ በየማህበራዊ መገናኛው እየተጋበዙ ነው። ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቄስ አይለቅም እንዲሉ ህወሀት እንደ ድርጅት የግንጠላውን አቋም ዛሬ ጥሎ ስለ አንድነት አጥብቆ ሰባኪ ይሆናል ብሎ የሚጠብቅ የለም። ያንን የደደቢት ረቂቅ የግንጠላ ማኒፌስቶ እስከ ወዲያኛው ቀብሮ ሁሉም ዜጎች በህግ ፊት እኩል የሚሆኑበት የፖለቲካ ስርዓት መምጣቱም አይቀሬ ነው።

ወያኔ ልክ እንደ ናዚ ጀርመን አዶልፍ ሂትለር ሁሉ ዜጎችን በትላልቅ የማሰቃያ እስር ቤቶች እያጎረ ነው። ባሰርት ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች አላንዳች የህግ አፈፃፀም ሂደት በየማጎሪያው በተዘጋጁ የማሰቃያ ዘዴዎች ፍዳቸውን እየቆጠሩ ይገኛሉ። በናዚ ትዕዛዝ የአይሁድ ዝርያ ያላቸው ዜጎች በጋለ የዳቦ ማብሰያ ውስጥ እንደ ከሰሉ ሁሉ ወያኔ በወህኒዎቹ ያጎራቸውን ዜጎች ሆነ ብሎ በሚለኩሰው እሳት እየቃጠለ ነው – ከእሳት አመልጥን ብለው ነብሴ አውጪኝ የሚሮጡትን በጥይት እየለቀመ በመጨፍጨፍ ዘዴ ይጠቀማል። ዛሬ ማርፈጃው ላይ ናዚ ናችሁ ሲል በለንደን ኤምበሲ ብዞቱን ያስተጋበው የኢትዮጵያውያን ድምፅ መላው አለም ይበልጥ ስለ ወያኔ ተፈጥሮ እንዲገነዘብ ያስቻለ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው።

እንገነጠላለን ብላችሁ መጋበዛችሁ አሁን የሚያሳስበው ኢትዮጵያዊ የለም። ግንጣላችሁን የምታረጋግጡበት ቀርቶ ለመስበክ የምትቆሙበት መሬት የሚኖራችሁም አይመስለኝም። በመላው ህዝባችን ህሊና ውስጥ ዛሬ የሚመላለሰው አንገብጋቢ ጥያቄ የመገንጠል አለመገነጠል ጉዳይ ሳይሆን ከሙሰኛ ፣ ከሌባ ፣ ከገዳይ ፣ ከጨካኝ እና ህሊና ቢስ ዘራፊ መንግስት እንዴት ልገላገል የሚለው ነው። በቁርጠኝነት እና በአንድነት የተሰለፈው ህዝብ እስከ ዛሬ ከከፈለው ውድ መስዋዕትነት በላይ የጠየቀውን ዋጋ ከፍሎ ትግሉን በድል ያጠናቅቃል።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s