ይድረስ ለሁሉም ቤተ እምነቶች አባቶች በሙሉ የድሀውን ልቅሶ ስለምን ቸል አላችሁት?

swe-satenaw-news-34ዛሬ ስለ እናንተ ኃላፊነት ለእናንተው ግልጽ ደብዳቤ ለመጻፍ ወደድኩኝ። ይህን ደብዳቤ እንድጽፍ ያስገደደኝ ነገር የእምነታችን መጽሐፍ የሆነውን ታላቁን መጽሐፍ ሳነብ መጽሐፉ የሚለውን እና የቤተ እምነቶቹ መሪዎች የሚያደርጉት ድርጊት መሳ ለመሳ አልሄድ ቢለኝ እና ባይገጥምልኝ ነው።
አሁን ያለንበት ዘመን መንግስት የተሰኘው የጥቂቶች ግለሰቦች ስብስብ የሕዝቡን የመኖር መብት በአደባባይ ሲደመስስ እና ሲረገጥ በገሃድ እያየን ያለንበት ነው። ታዲያ በዚህ ሁናቴ ውስጥ የእምነት አባቶች ሚና ምንድን ነው? የሁሉም ቤተ እምነቶች መሪዎች ዝምታን ስለምን መረጡ? ዝምታውስ ስለምንድን ነው? ንጹሐን እና አቅም የሌላቸው ሕጻን እና አረጋዊያን እንዲሁም ታዳጊዎችን በቀትር ፀሐይ ሕይወታቸውን በጠገቡ ወደል አጋሰሶች ( አጋዚ) እንደቅጠል በየቀኑ ሲረግፍ እያያችሁ ስለምን ዝምታን መረጣች?
ዘንድሮ መጽሐፉም ዝም…ቄሱም ዝም ሆነ እኮ። መጽሐፉስ ዝም ያለ አይመስለኝም፤ ቄሱ ግን ዝም ብሎዋል እና ስለ ምን ዝምታን መረጣችሁ? ላለመሞት ነውን? ብትሞቱስ ምን ልትጎዱ? ሐዋሪያው ለእኔ ሞት ጥቅሜ ነው አላለምን? ብኖርስ አለ ይኸው ሐዋሪያ…በሕይወት ብኖር ደግሞ እናንተ ነው አላለምን? ብትታሰሩ ምን ይገርማችሃል? የእምነታችሁ ሊቀ ካህን የሆነ እርሱስ አልታሰረምን? እንደ ወንበዴ አልተቆጠረምን? አልተገረፈምን? ይህ ሁሉ እኮ የሆነው ለሰው ልጆች ነው። መቼም ስለ እውነት መከራን መቀበል እምነታችን ነው። የተበደለን ማቀፍ መደገፍ የበደለን ደግሞ ተው ልክ አይደለክም ተመልስ ብሎ መምከር መገሰጽ እምነታችን ነው፤ ግጻፄን አልሰማም ብሎ አሻፈረኝ አልሰማም… አልመለስም ቢል ማውገዝም እምነታችን ነው። መጥምቁ ዮሐንስ አንገቱ የተቀላው እውነት ስለተናገረ እንጂ በ እውነት ላይ ስለሸፈጠ አይደለም፤ ይህ ዮሐንስ ግን በሚመጣው ዓለም የሁሉ ታላቅ እንጂ ታናሽ አይደለም።
ታዲያ እኛ የምናምነው እምነት ስለእውነት የሚቆም፣ ከእውነት ጋር የሚተባበር፣ ክፋትን፣ ነፍስ ማጥፋትን፣ ብዝበዛን የሚጸየፍ ከሆነ በየቤተ እምነቶቻችን ያላችሁ አስተማሪዎቻችን በአንድነት ስለ ምን ዝምታን መረጣችሁ? ዘወተር የምትጸልዮት ጸሎት፣ ምልጃ፣ ልቅሶ ስለማን ነው? ስለሰው አይደለምን? ሰው እኮ መብቱ እየተረገጠ ነው….ሰው እኮ እየሞተ ነው…መቼ ነው ስለጽድቅ እና ስለሰዎች እኩልነት ድምጻችሁን የምታሰሙት? የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ1983 ዓ.ም ግንቦት ወር ጀምሮ በታላቅ መከራ ውስጥ ይኖራል፤ ኢትዮጵያዊያን በቀትር በጠራራ ፀሐይ እንደ በግ ወደ መታረድ ሲሄዱ ይህንን በደል ለማቆም ስለምን ድምጻችሁን አላሰማችሁም? የኢትዮጵያዊያን ንብረት እንደ ጠላት ንብረት እየተዘረፈ ወደትግራይ እየተጋዘ ባለበት ሁኔታ፣ በደል እና ብዝብዛ በምድራችን ቅጡን ሲያጣ እናንተ ስለምን ፍርድ የሚያጓድሉትን ልትገስጹ ድምጽ አልባ ሆናችሁ?
አረ ለመሆኑ መጽሐፉስ ምን ብሎ ነበር? መጽሐፉ እማ፦
መጽሐፈ ምሳሌ2113 የድሀውን ጩኸት እንዳይሰማ ጆሮውን የሚደፍን ሰው፥ እርሱ ራሱ ይጮኻል አይሰማለትምም።
ትንቢተ ኢሳይያስ 101-2 መበለቶችም ቅሚያቸው እንዲሆኑ፥ ድሀ አደጎችንም ብዝበዛቸው እንዲያደርጉ፥ የድሀውን ፍርድ ያጣምሙ ዘንድ፥ የችግረኛውንም ሕዝቤን ፍርድ ያጐድሉ ዘንድ የግፍን ትእዛዛት ለሚያዝዙ፥ ክፉንም ጽሕፈት ለሚጽፉ ወዮላቸው!
ትንቢተ ኤርምያስ 223 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ የተበዘበዘውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ፤ መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም አትበድሉ፥ አታምፁባቸውም፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን አታፍስሱ።
*መጽሐፈ ምሳሌ 31 8-9 አፍህን ስለ ዲዳው ክፈት፥ ተስፋ ስለሌላቸውም ሁሉ ተፋረድ።አፍህን ክፍት፥ በእውነትም ፍረድ፤ ለድሀና ለምስኪን ፍረድ። ብሎዋል።
መጽሐፉ ያለው፦
  1. የድሀውን ጩኸት ስሙ
  2. ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ሁኑ
  3. የተበዘበዘውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ
  4. የግፍን ትእዛዛት ለሚያዝዙ፥ ክፉንም ለሚፈጽሙ …አገዛዛቸው ክፋትን ለሆኑ ሰዎች ጋር አትተባበሩ
  5. አፍህን ክፍት፥ በእውነትም ፍረድ… እንዲል መጽሐፉ ያለው ዝም በል ሳይሆን አፍህን ክፈት ነው…ጸልይ ብቻ ሳይሆን አፍህን ክፈት ነው።
ታዲያ ወዳጆቻችን የሆናችሁ አባት እና መምህሮቻችን ስለምን ግራ ትጋባላችሁ? ስለምንስ ዝም ትላላችሁ? አሁንም አልረፈደም ከተደበቃችሁበት ሰንጣቃማ የፍርሃት እና የሁለትዮሽ ሕይወት ወጥታችሁ ግፍን ልትቃወሙ ያስፈልጋል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s