ቅምቡርስ የት ትሄጃለሽ? መተማ፤ ትደርሻለሽ? ልብማ! [ሙሉቀን ተስፋው]

TPLF (1)ወታደራዊው መንግሥት በ1983 ዓ.ም. እንደእንቧይ ካብ ሲናድ፣ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ሕዝቡን ጸጥ ያሰኘ የፍርሃት መንፈስ ነግሶ ነበር፡፡ ፍርሃት መቼም የጥርጣሬ ልጁ ነው፡፡ በወቅቱ አዳሜ የደበተውም ተሰናባቹን ሳይሆን መጤውን ኃይል ባለማወቁ ነበር፡፡ በደርግ አምባገነንነትና ግፍ የተንገሸገሸው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ወያኔና ሻዕቢያ ወንበዴዎች፣ ጡት ነካሾች ናቸው ለሚል ውትወታው ጆሮ አልሰጠውም፡፡ “ደርግን የሚያህል የሰማይ ስባሪ ተንኮታኩቶ ይህቺ አገር ምን ይውጣታል?” ነበር ጭንቀቱ፡፡

ወያኔ አምሳያ በማይገኝለት የታሪክ ፍርደ ገምድልነት መሃል አገር ሲገባ፣ ከመሣሪያው በስተቀር ልክ የዘመነ መሣፍንት ጭፍራ ይመስል ነበር፡፡ በገጸ በረከትነት እጁ ላይ የወደቀችለት ዐሥራ ሰባት ዓመት በጠላትነት ያደማት ኢትዮጵያ ናት፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ቁመናም፣ መንፈስም ሆነ ርዕይ አልነበረውም፡፡ ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ጨቋኝ ገዥዎች ነበሯቸው፣ ቅኝ ገዥዎችንም ቀምሰዋል፣ ባንዶችንም አበጥረው ያውቃሉ፡፡ የወያኔ ሠይጣናዊ ተፈጥሮ ልክ ምን ያህል ከግንዛቤያቸው ውጭ እንደሆነ የተረዱት ውለው አድረው ነው፡፡
ኢትዮጵያን ለአሳር፣ ትግራይን ለሐሴት

ሕወሓት በአዲስ ገጽታ ሰላም፣ ፍትሕና እኩልነት እየዘመረ ተከዜን የተሻገረው የቂም መርዙን አርግዞ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ያለአንዳች መስዋዕትነት በራሷ ኪሳራ መቃብር ከትቶ፣ ዞሮ መግቢያውን ትግራይን አመቻችቶ ዓለሙን ለመቅጨት፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያዊነትን በአዋጅ አውግዞ ዘመተበት፡፡ ሕዝብን በጥላቻ ከፋፍሎ አናከሰ፡፡ ታሪክን፣ እሴቶችን፣ ተቋማትን አፈረሰ፡፡ የአገርና የሕዝብ ጥቅምን ናቀ፡፡ በቀነ ጎደሎ የተቀመጠበትን መንበር ክብር፣ በትዕቢትና ማናለብኝነት አረከሰው፡፡
የእኩይ ምኞቱ ማስፈጸሚያ እንደ ወሮበላ ጭፍራ የቻለውን በልቶ የቀረውን አጥፋፍቶ መሄድ ስለነበር፣ በራሱ ዳኝነት የደም ካሣ ቆርጦ የአገር አንጡራ ሀብት ዘረፈ አዘረፈ፡፡ የተረፈው በርካሽና ጊዜያዊ ነገሮች እንዲባክን፣ በዘፈቀደ እየሠራ በደስታ ማፍረሱን ሰለጠነበት፡፡ እያደር ሥልጣኑንም፣ ገንዘቡንም፣ መሬቱንም፣ ታሪኩንና ባህሉንም ሁሉንም ለብቻዬ ካልጠቀለልኩ አለ፡፡ ስግብግብነቱ ያነቃበት ስስት፣ እንኳን ‹ለደመኛው› የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርና፣ ለአንጋቾቹ የጎሳ ነጋዴዎች፣ ለዘረፋ ሽርኩ ሻዕቢያና ለሚምልበት የትግራይ ሕዝብም የማይራራ አደረገው፡፡

ወያኔ በተለይ በ1990 ዓ.ም ሻዕቢያን አባርሮ አዛዥ ናዛዥነቱን ካረጋገጠ በኋላ ልቡ በትዕቢት አበጠ፡፡ ለዚህ ማዕረግ ያበቃውን አሳረኛውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለፍቅሩ ጥላቻ፣ ለክብሩ ንቀት ከፈለው፡፡ ራሱ በጻፈው ስንኩል ገድል የትግሬን ‹አይበገሬነት›፣ “ዓላማ ጽናት”፣ “መለኮታዊነት” ወይም “ወርቅነት”፣ የሌላውን ኢትዮጵያዊ “ሆዳምነት”፣ “ልፍስፍስነት”፣ “እርኩስነት” ወይም “ጨርቅነት” አቀነቀነ፡፡ ከጎሰኝነት ወደለየለት ዘረኝነት ዘቀጠ፡፡

በዚህ የእብደት ትውፊት መሠረት “ምርጦች” ለገዥነት፣ “ውዳቂዎች” ለባርነት የተጣፉበት ዘመነ መሳፍንትን የሚያስንቅ የጡንቻ፣ የመድልዎ፣ የዝርፊያና የብልግና ሥርዓት ገነባ፡፡ አገሪቱን በጉልትነት ሸንሽኖ የጎሳ መኳንንት ሠራባት፡፡ ለትግሬ ሎሌነት እስከታመናችሁ ፍርፋሪያችሁን በየፊናችሁ ዝረፉ አለ፡፡ ወያኔ ዘላለማዊነትን አሻግሮ እያለመ፣ ልዕለ ኃያልነቱን ከልጅ ልጅ ለማሳለፍ ሽርጉድ ማለት ጀመረ፡፡ “ባለራዕዩ” መሪም ሳይቀባ አጅሬ ሞት ቀደመው እንጂ፣ የአፄ ዮሃንሐን ዘውድ እንዲደፋ “ንገሥለይ” ተደረፈለት፡፡
የሌብነት፣ የሽብርና ስናይፐር ሥርዓት

ወያኔ ከትግራይ ቢወጣም፣ ትግራይ ከነፍሱ አልወጣችም፡፡ ሆኖም እንደ ጥፋት ወንድሙ ሻዕቢያ በጊዜ ጨርቁን ጠቅልሎ ወደመጣበት እንዳይመለስ፣ ወሰን የሌለው ሥልጣን፣ ሀብትና ቅንጦት አሰረው፡፡ እያደር ልሒድ በሚለው ዘረኝነቱና አልጠገብኩም በሚል ስግብግብነቱ መካከል ልቡ ክፉኛ ተከፈለች፡፡ የአገር አባወራ ሲሉት ባይተዋር ሆኖ፣ ስንቁን ሰንቆና ሁለት ጉድጓድ ምሶ፣ ቆይ ነገ እያለ በቁጢጥ ኖረ፡፡

ይህ ጎሰኛ የአገር መሪነት፣ ኢትዮጵያን የጠላ ኢትዮጵያዊነትና በተቃርኖ የሚለመልም ተፈጥሮው እያደር ቢነቃበትም፣ መልኩን እንደ እስስት እየቀያየረ አዘገመ፡፡ በተግባር የሚያፈርሳትን አገር፣ ‹መድኅኗ ነኝ› አለ፡፡ እኔ ከሌለሁ አገር እንደቆሎ ትበተናለች፣ ሕዝብ ይፋጃል የምትል ማስፈራሪያ አዘል ምክር ለገሰ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በበኩሉ፣ ወርቃችንን ወስዶ ጨርቅ የሚመልስልን ጉድ ሄዶ ካላየነው በቀር ይህን ጉዳይ ማረጋገጥ አይቻልም ብሎ በ1997 ዓ.ም. በጨዋ ደንብ አሰናበተው፡፡

ከእንግዲህ ማንነቱን ሊደብቅ አልቻለም፡፡ ‹በደሜ ያገኘሁትን ሲሳይ ትቼ የትም አልሄድም› ሲል እቅጩን ተናገረ፡፡ ወደዳችሁም ጠላችሁም በብረት እየቀጠቀጥኩ እገዛለሁ፡፡ ካልሆነ ደግሞ በታትኛችሁ፣ አባልቻችሁ፣ አራግፊያችሁ ነው የምሄድ ሲል ዛተ፡፡ በገሃድ የንጹሐን ደም አፍስሶ፣ የስናይፐር መንግሥት ሆነ፡፡ ሽብርን የህልውናው ምሰሶ በማድረግ፣ በአዲስ ጉልበት ወደ ዝርፊያውና ውድመቱ ተሰማራ፡፡ በጎን ኢትዮጵያን እያለማኋት ነው፣ ሕዳሴዋን አስቀጥላለሁ በሚል ማጀቢያ ራሱን እያሞኘ ሌላ ዐሥር ዓመት ዘለቀ፡፡

ቦ ጊዜ ለኩሉ ነውና ዘንድሮ ዛቻም፣ ድለላም፣ ሴራም፣ ጉልበትም የማይመልሰው ማዕበል ገንፍሎ መጣ፡፡ ለሃያ አምስት ዓመታት የግፍ ጽዋ የተጋተው ሆደሰፊ ሕዝብ፣ በቁጣ ታጥቆ ተነሳ፡፡ እናት ኢትዮጵያ በድባብ ትሒድና፣ ሞት ቢደገስለት የማይፈራ ጀግና ትውልድ ተፈጠረ፡፡ ቀባሪው ሊቀበር ሆነ፡፡ ማጣፊያው ያጠረው ወያኔም ‹እኛ እንደሆን ወታደሮቻችንንና መድፋችንን ይዘን ትግራይ እንገባለን፤ በመብታችን እንጠቀማለን› የምትል መግደርደሪያ ሹክ አለን፡፡ በዚህም ተባለ በዚያ የስንብቱ ጉዳይ አያጠያይቅም፡፡ ስለዚህም ለጊዜው ጭንቀታችን ‹ወዴት እንዴት ነው አካሄዱ?› የሚለው ነው፡፡

በአንድ በኩል የትግራዋይ አጀንዳ በጥርዥ ብርዥም ቢሆን እንዳትዘነጋ አድርጓል፡፡ የምኞቱን ባያህልም፣ የታላቋን ትግራይ ግዛት አስፋፍቶ፣ ሀብት ንብረትና የጦር መሣሪያ አግዞ፣ በየባንኩ ገንዘብ አድልቦ፣ ወሳኝ መሠረተ ልማት ዘርግቶ፣ የትግራይን ሕዝብ በመንፈስ ነጥሎና አቆራርጦ፤ በዚህም ላይ በሕግ ከሆነ አንቀጽ 39ን፣ ካልሆነም የጦር ሠራዊቱንና ደኅንነቱን ሙጭጭ ብሎ ከርሟል፡፡
የትግራይ ሕዝብ እና ወያኔ አንድ ናቸው የሚለውን ‹‹ዕውነታነት›› ለጊዜው እንተወውና፣ ‹ትግራይ ማለት ወያነ፣ ወያነ ማለት ትግራይ› ሲል እንደፎከረውም ወደ ትግራይ ይሄዳል እንበል፡፡ የትግራዋይ እጣፈንታስ? እስካሁን እንዳመጣጡ ሠራዊቱን እንጂ የትግራይን ሕዝብ ይዤ እሄዳለሁ የሚል ወሬ ትንፍሽ አላለም፡፡

ምናልባት ወያኔ ቀንደኛ መሪዎቹና ካድሬዎቹን በአየር፣ ለዝርፊያ አምጥቶ የሰገሰጋቸውን ጋሻ ጃግሬዎቹንና፣ ታማኙን የሠራዊት ክፍል ከነጓዙ በምድር ይዞ ውልቅ ለማለት ቢያስብስ፡፡ ይህም ደግሞ በድርድር ካልሆነ ብዙ ፈተናዎች አሉት፡፡ መጀመሪያ መሃል አገር ያሉ ቁልፍ ሲቪልና ወታደራዊ ተቋማትን ማውደም፣ ቀሪውን ሰፊ ሠራዊት ትጥቅ ማስፈታት፣ በምርኮ ማገት ወይም መፍጀት ይፈልጋል፡፡ ከዚያም በየትኛውም አቅጣጫ ይሁን አበባ እየበተነ የሚሸኘው ሕዝብ ስለማይኖር፣ የግዱን እየተዋጋና እያጸዳ ጥሶ መውጣት ይኖርበታል፡፡

በሁለቱም ደረጃዎች ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎበት እንኳን ይህ ዕቅድ ቢሳካ፣ የወያኔ እጣ ፈንታው በመሃል አገርና በቀጠናው በሚኖረው ሰላምና መረጋጋት ይወሰናል፡፡ ለዚህም እስካሁን የለፋበትን አማራንና ኦሮሞን እንደገና ደም ለማቃባት መሞከሩ፣ በምሥጢር ያሰለጠናቸውን የሽብር ብርጌዶች ማሰለፉ፣ አልሸባብን ጨምሮ የትኛውንም የጸረ ኢትዮጵያ ቡድን ማስታጠቁና ማሰማራቱ አይቀሬ ነው፡፡ ኤርትራንም የከፈለውን ከፍሎ እርቅ መለመን ግዴታው ነው፡፡ በዚህ ላይ ሲወጣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በማስቆጣትና፣ ቀሪው ትግራዋይ ጦሱን እንዲቀበል ያደርጋል፡፡

የወያኔ ትልቁ ድንቁርናው የታሪክን፣ የባህልንና እምነትን ዋጋ አለማወቁ፣ በብዙ ሺሕ ዓመታት የተገነባን የሕዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት፣ በአንድ ትውልድ ሴራ ለማጥፋት መሞከሩ ነው፡፡ ይህ እስከዛሬ ተደግፎበት የነበረው ምስጥ የበላው ምሰሶ ዓይኑ እያየ መፈራረስ ጀምሯል፡፡ መልሶ ለማቆም እንደገና መፈጠር ይፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ወያኔ በምትሃት ካልደበቀው በቀር፣ ከላይ ለጠቀስነው ዓይነት መጠነ ሰፊ ሽሽት የረባ ዝግጅት አላደረገም፡፡ ጥቂት የሥርዓቱን ቁንጮዎች ነፍስ ላድን ቢልም፣ በድርድር ዋስትና ካላገኘ በቀር አይሆንለትም፡፡
እንዲህ ከሆነ ሥልጣኑን ሙጭጭ እንዳለ እስከ መጨረሻ ሕቅታው ይዋደቃል ማለት ነው? ቢሰምርለት መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በሆነ መዓት ፈጅቶ፣ ሌጣ መሬቷን ለዘርማንዘሩ ማውረስ መመኘቱን አያቆምም፡፡ ሆኖም አሁን ቆሌው የተገፈፈው ወያኔ፣ በስናይፐር መንግሥትነት መዝለቅ አይችልም፡፡ ምዕራባውያን የጡት አባቶቹን ማታለያ ዘዴ አያጣ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በሕዝብ ደም የጨቀየ እጁን ቢዘረጋም ተቀባይነት የማግኘት ዕድሉ እያመለጠ ነው፡፡ ከዕለት ዕለት ሆድ አደሮቹ እየከዱት፣ ሠራዊቱም ወደሕዝብ እየተናደበት፣ ተመልሶ ወደኮሳሳ ጭፍራነቱ መውረዱ አይቀርም፡፡

ይህ ገና ያልተገለጠለት ለራሱ ለወያኔ ብቻ ነው፡፡ ለጊዜው በተለመደው ዘረኝነቱ፣ ግብዝነቱና አፈናው ከመግፋት ውጭ፣ አዲስ ሐሳብና መፍትሔ ቀርቶ ያልተነቃ ሴራ እንኳን መፍጠር አልቻለም፡፡ ያው በተለመደ አፋናውና የሕዝብ ጭፍጨፋው፣ ያው በለመደበት የጥፋት መንገዱ ቀጥሏል፡፡ አንዳንዶች “ወያኔ አተት ይዞት ተኝቷል” ብለው የሚሳለቁት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ መባነን ከቻለ ከገባበት ከቅዥት ሲባንን ራሱን ከታሪክ ቆሻሻ ጋር ተጥሎ እንደሚያገኘው አይጠረጠርም፡፡

#የአማራ_ተጋድሎ ይቀጥላል!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s