በደም እየተጠመቁ አዲስ ዓመት አይጠባም! [በላይነህ አባተ]

በላይነህ አባተ (abatebeai@yahoo.com)

14322757_1190219394369069_3853230140470559572_nበአዲስ ዓመት ልጃገረዶች በአደይ አበባ፣ በጠልስም፣ በመስቀል፣ በድሪ፣ በአንባርና በአልቦ ተውበው አበባየሁ ሆይን ይዘምሩ ነበር፡፡ እነዚህ ልጃገረዶች ዛሬ ክር አስረው፣ ፊታቸውን ልጠውና ራሳቸውን ተላጭተው ለታረዱት ወንድሞቻቸውና አባቶቻቸው ሚሾ ያወርዳሉ፡፡ ጎረምሶች በአዲስ ዓመት ችቧቸውን አብርተው “በቆላ በደጋ ያላችሁ እንዴት ከረማችሁ?” እያሉ ሆያ-ሆየን ይጨፍሩ ነበር፡፡ ዛሬ እነዚህ ጎረምሶች መብት ስለጠየቁና የቅድመ አያቶቻቸውን ሰንደቅ ስለሰቀሉ እንደ በግ ታርደው ያሞራ ሲሳይ ሆነዋል፤ ካሞራ ሲሳይነት የተረፉትም ከርቸሌ ተጠብሰዋል፡፡ እናቶችና አባቶች በጳጉሜ ውኃ ተጠምቀውና ልባሳቸውን አጥበው አዲስ ዓመትን ይቀበሉ ነበር፡፡ የዛሬ እናቶችና አባቶች የታረዱና የተቃጠሉ ልጆቻቸውን በላስቲክ እንደ አዲስ ዓመት ስጦታ ተቀብለዋል፡፡

የታረዱና የተቃጠሉት ልጆቿ ደም ኢትዮጵያን ከፋሽሽት ዘመን የባሰ ጃኖ አልብሷታል፡፡ ከተከዜ እስከ ዓባይ፤ ከዓባይ እስከ አዋሽ፤ ከአዋሽ እስከ ሸበሌ፣ ከሸበሌ እስከ ገናሌ፣ ከገናሌ እስከ ባሮ ያሉ ወንዞቿ ደም ጎርሰዋል፡፡ ከወልቃይት እስከ ጎንደር፤ ከጎንደር እስከ ደብረታቦር፣ ከደብረታቦር እስከ ባህርዳር፣ ከባህርዳር እስከ ደብረ ማርቆስ፤ ከደብረማርቆስ እስከ አምቦ፣ ከአምቦ እስከ ደንቢ ዶሎ፤ ከደንቢ ዶሎ እስከ ወሊሶ፤ ከወሊሶ እስከ ቂሊንጦ፤ ከቂሊንጦ እስከ ዶዶላ፣ ከዶዶላ እስከ ያቤሎ ያሉ ኩሬዎች ደም ቋጥረዋል፡፡ ደም ያልነካው ውኃ እንኳን ለመጠመቂያ ለጸበልም ጠፍቷል፡፡ ይህንን ደም የጎረሰ ውኃ የማትያስ ሲኖድ የልማት ውኃ እያለ ወደ ሕዝብ ይረጨዋል፡፡ በኢትዮጵያ እሚወርደው የግፍ ዶፍ በጥፋት ውኃ፣ በሰዶምና ገሞራ ከጎረፈው የግፍ ዶፍም ከፍቷል፡፡

ከጥፋት ውኃንና ከሰዶም ገሞራ በኋላ ክርስቶስ ለፍትህ በመስቀል ተሰቅሏል፡፡ ክርስቶስ ለፍትህ የተሰቀለበትን መስቀል “አባ” ማትያስና ጳጳጳሳቱ ሳህን ሰርተው ፍትፍት ይዝቁበታል፤ ቪላ ገንብተው ይዘንጡበታል፤ ሉመዚን ቀጥቅጠው ይንፈላሰሱበታል፡፡ ፍትፍት ዘክዛኪውና በሉመዚን ተንፈላሳሹ አባ ማትያስና ተቋዳሽ ጳጳሳቱ “እስተንፋስ ያለው ሁሉ ይተንፍስና አትግደል” የሚሉትን ቃላት ሽረው “አትተንፍስ፤ አለዚያ ትሞታለህ” እያሉ ሟቹን ሲያስጠነቅቁ ይታያል፡፡ እነዚህ ፍትፍት ዘክዛኪዎች በሐዘን የተጎዳውን ሲያጽናኑና የታሰረውን ሲጠይቁ ሳይሆን በነፍሰ-ገዳይ ሰይጣኖች “ለሽምግልና” ታዝዘው ከነካባቸው ሲግበሰበሱ ይታያል፡፡ በሰማእታት አስከሬን ከበሮ እየመቱ እሚጨፍሩትን ሲያሳልሙ ይስተዋላል፡፡ አናባቢ ሆይ! ቤተመንግስትን ሰይጣን ቤተክርስትያንን ይሁዳዎች ነጥቀዋታል፡፡ በዚህም ምክንያት የግፉ ዶፍ አላባራ ብሏል፡፡ የማያባራው የግፍ ዶፍም እንኳን ወተትን ውኃ በማስሸፈት ይገኛል፡፡

ወተት ቀርቶ ውኃ በሚሸፍትበት ወቅት “እንኳን አደረሰህ” የሚባልለት አዲስ ዓመት አይኖርም፡፡ የገዳይ ደጋፊዎች በሲዳሞና በወለጋ ወርቅ ተሽቆጥቁጠው ከበሯቸውን እየወቀሩና እየዘለሉ በሰማእታት አስከሬን ስለጨፈሩ ሰዶምና ገሞራ እንጅ አዲስ ዓመት መጣ አይባልም፡፡ እነ ተከዜ፣ እነ አንገርብ፣ እነ ዓባይ፣ እነ ጨሞጋ፣ እነ አዋሽ፣ እነ ደዴሳ፣ እነ ባሮና ገናሌ ደማቸው ሳይጠራ አዲስ ዓመት አይነጋም፡፡ እነ ራስ ዳሽን፣ እነ ቋራ፣ እነ በላያ፣ እነ አመዳሚት፣ እነ ዝቋላ፣ እነ ጭላሎ የጎረምሶችን ሆያ-ሆየና የልጃገርዶችን አበባየ-ሆይ ሳያስተጋቡ አዲስ ዓመት አይጠባም፡፡ የሊማሊሞ ዳገት፣ የጣራ ገዳም ጋራ፣ የጮጨ ግርግዳ፣ የየረር ተራራ፣ የዓባይ በረሃ፣ የዋልድባ ገዳም፣ የዘጌ አድባራት፤ የሰብስቤ ዋሻ፣ የጋንቤላ ጫካ የሰማእታትን ጩኸት እያስተጋቡ አዲስ ዓመት አይከበርም፡፡ የማእከላዊ፣ የቃሊቲ፣ የቂሊንጦ፣ የዝዋይ፣ የሰንዳፋ፣ የብርሸለቆ፣ የአንገርብና የአሶሳ እስር ቤቶች የጦቢያን ልጆች ስቃይና ጣረ ሞት እየተመለከቱ አዲስ ዓመት አይከበርም፡፡

የዲያብሎስ ብሮድካሽን ኮርፖሬሽን(EBC=DBC) የሰማእታት ዓይን ሳይፈርስ አስረሽ ምቺው ስለጨፈረ አዲስ ዓመት ገብቷል አይባልም፡፡ “አባ” ማትያስ የምድርን ችሎት አምልጦ ከእግዜር ችሎት እንደቀረበው ወንድሙ “አባ” ገብረመድህን የደም ውኃን የልማት ጸበል እያለ ስለረጨ አዲስ ዓመት ተከበረ አይባልም፡፡ የለም! የለም! አዲስ ዓመት የለም፡፡ በፍልሰታና በጳጉሜ በደም እየተጠመቁ አዲስ ዓመት አይጠባም፡፡

 

መስከረም አንድ ሁለት ሺ ዘጠኝ ዓ.ም.

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s