ያቺ “ባነር”…! (በመስከረም አበራ)

በመስከረም አበራ
E-mail meskiduye99@gmail.com

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ መባቻ ከዘመነ መሳፍንት ማክተም ጋር የሚቆራኝ ነው፡፡የሃገራችንን የቀደመ ግርማ አኮስሶ፣ የጦር አለቆች የረብሻ ምድር አድሮጓት የኖረው፣ በታሪክ ዘመነ መሳፍንት ተብሎ የሚታወቀው ወቅት የቆየበት ጊዜ ዘለግ ያለ በመሆኑ ተክሎት ያለፈው ችግር ስርም ጠለቀ ያለ ነበር፡፡በተለይ ከዘመነ መሳፍንት በፊት የነበሩ የኢትዮጵያ ነገስታት በታላቅ ሃገር ላይ ታላቅ መሪ የመሆን አልፎም ቀይባህርን ተሻግሮ የማስገበር የታላቅነት ምኞት በትንንሽ መንደሮች ትንሽ አለቃ ለመሆን ወደ መቃተት የንዑስነት ምኞት አንሶ ነበር፡፡ ይህ የንዑስነት ዘመን መንደርተኛነት በሃገራዊነት ላይ የገነነበት፣ መነጣጠል አብሮነትን የረታበት፣የኢትዮጵያዊነት ስሜት የሰለለበት  ዘመን ነበር፡፡ ይህ የድቀት ዘመን ያከተመው ከወደ ጎንደር በተነሳ የቀደመ ታላቅነትን የመናፈቅ ሃሳብ ነበር፡፡ስር የሰደደው የዘመነ መሳፍንት ዘመን የንዑስነት ምኞት እና የመከፋፈል አባዜ በቋራው ካሣ ታላቅነት የመናፈቅ ከፍ ያለ እሳቦት ፍፃሜውን አገኘ፡፡የካሣን ውድ ህይወት ቢነጥቅም በዘመነ መሳፍንት የመንደርተኝነት ዝንባሌ  እልም ስልም ሲል የባጀው የኢትዮጵያዊነት ስሜት ወደ ህዝብ ልቦና ተመለሰ፡፡

ሆኖም ከዘመነ መሳፍነት ማክተም ብዙ ዘመን በኋላ ኢትዮጵያዊነት ሌላ ፈተና ገጠመው፡፡በተለይ ከኢህአዴግ ወደ ወንበር መምጣት በኋላ ኢትየጵያዊነትን የማቀንቀን ፖለቲካዊ አቋም፣ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ቱርፋቶች መስበክ፣ ስለኢትዮጵያዊ ወንድማማች/እህትማማችነት ማውራት  እንደ መርገም ጨርቅ ያለ ነገር ሆኖ ኖረ፡፡የመርገም ጨርቁ ስም ደግሞ “ትምክህተኛ አማራነት” ነው፡፡የኢትዮጵያ አንድነት የሚጠቅመው ለአማራው ብቻ ባለመሆኑ ኢህአዴግ አማራ ከሚላቸው ሰዎች ሌላም  በሁሉም የሃገራችን ጥግ ለኢትዮጵያዊነት የሚቃትቱ ኢትዮጵያዊያን በብዛት አሉ፡፡ኢህአዴግ ለእነዚህም ስም አለው – “የአማራ ተላላኪዎች” ሲል አንድ ሰው ስለ ሃገሩ ህልውና እና የሃገር ባለቤትነት ጥቅም በራሱ ጭንቅላት አስቦ ይረዳ ዘንድ የማይቻል አስመስሎት ቁጭ ይላል፡፡ እውነታው ኢትዮጵያዊነት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልቦና ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው ነው፡፡ አከራካሪው ነገር ኢትዮጵያ እንዴት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል የሆነች እናት ትሁን በሚለው ታሪክ ከማቃለል  ይልቅ እያከማቸው በመጣው የቤት ስራ ላይ ይመስለኛል፡፡ከእውነት ጋር ብዙ የማይስማማው ኢህአዴግ ታዲያ ይህን የታሪክ ክፍተት ለተፈጠረበት ኢትዮጵያዊነትን የማደብዘዝ እኩይ አላማ በደንብ ተጠቀመበት፡፡ አገዛዙ በቆይታው ስኬታማ የሆነበት ዋናው ጉዳይ ይህን አኩይ አላማ ከግብ ለማድረስ የሮጠው ሩጫ ይመስለኛል፡፡

ህወሃት አስራ ሰባት አመት ጭንጫ ገደሉን ረግጨ ቧጥጬ የታገልኩት ለብሄር ብሄረሰቦች መብት ስል ነው ባይ ነው፡፡ይህን ያስመሰክር የነበረው ደግሞ የአማራ ህዝብን ቅስም የሚሰብሩ ንግግሮች፣ ድርጊቶች በማድረግ ነው፡፡ ህወሃት ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊትም ሆነ ከመጣ በኋላ የፖለቲካ ግንዛቤው ጥግ የአማራን ህዝብ ማጥላላት፣ ያልሆነ ስም መለጠፍ፣ማሰር፣ ማፈናቀል፣መግደል፣ ሰድቦ ለተሳዳቢ መስጠት ይመስለው ነበር፡፡ ለሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች መብት መቆሙን የሚያስመሰክረውም የጠየቁትን፣ራሱም በህገመንግስቱ የፃፈውን እስከ መገንጠል የዘለቀውን መብት በመተግበር ሳይሆን የአማራን ህዝብ በአደባባይ በማበሻቀጥ፣ ‘የድሮ በዳያቸውን’ (አማራን መሆኑ ነው) የማጥፋቱን ታዳጊነት ገድል በመተረክ ነው፡፡ የድሮው ይቅርና በቅርቡ የአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝን ወደ ስልጣን መምጣት አስመልክቶ አዛውንትነታቸውን የሚመጥን የንግግር ጭዋነት የሚያጥራቸው አዛውንቱ ስብሃት ነጋ ‘ሰውየውን መሾማችን  አማራን እና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይን ከስልጣን አጥረገጥ የማጥፋታችን ምልክት ነው’ ሲሉ ጫካ የለከፋቸው የጥላቻ ክፉ ደዌ እያደር የሚብስ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ይህን ክፉ ጥላቻ ያረገዙት ህወሃትዎች የህዝብ መገናኛ ብዙሃንን ለብቻቸው አንቀው መያዛቸው፣በመገናኛ ብዙሃን ይህንኑ የጥላቻ ስብከት ለማጧጧፍ እፍረትም ሆነ ሃላፊነት የማይሞክራቸው መሆኑ ደግሞ የነገሩን ውጤት በተለይ በአማራው ህዝብ ላይ ክፉ አድርጎት ኖሯል፡፡ ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ከኢህአዴግ በኋላ ያለችውን ኢትዮጵያ እጣፋንታ አጨልመው የሚያቀርቡትም ከዚህ እውነታ ጋር በተያያዘ ነው፡፡የሰራውን የሚያውቀው ኢህአዴግ ደግሞ በዚህ ሃላፊነት በጎደለው ስራው ሊያፍር ሲገባው ይኩራራል፣ ‘ከሌለሁ ወዮላት ለኢትዮጵያ’ ሲል ያስፈራራል፡፡በሃገሪቱ ሌላ ፍጥረት ያልተፈጠረ ይመስል የእልቂቱ ተዋናዮች፣የሃገሪቱ እጣፋንታ ወሳኞች የአማራ አና የኦሮሞ ህዝብ እንደሚሆኑ ይተነብያል፡፡የአማራ እና የኦሮሞ ህዝብ ለመገዳደል ብቻ የሚፈላለጉ ታሪካዊ ባላንጣዎች አድርጎ ውሸትን እጅግ ደጋግሞ እውነት ሊያስመስል ምንም አልቀረውም ነበር፡፡

ከንቱው ልፋት

የስሌት አውዳችን ጎሳን ማዕከል ያደረገ ከሆነ ህወሃት ወጣሁበት የሚለው የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያ ንዑስ ቁጥር ካላቸው ጎሳዎች ወገን ነው፡፡ እንደ እውነቱ ቢሆን የጎሳ ፖለቲካ መሲህ ነኝ የሚለው ህወሃት  የሰፈሩን ልጆች ጠርቶ የወረረውን የፖለቲካ ስልጣን ለተላላቆቹ ኦሮሞ እና አማራ ጎሳዎች መልቀቅ ነበረበት፡፡ ይህን እንደማያደርግ ልቦናው የሚያውቀው ንዑሱ ህወሃት ታዲያ እንደ አማራጭ ያየው  ስልጣኑ ለሚገባቸው ጎሳዎች እርስበርስ የመናቆር፣አይን እና ናጫ የመሆን የቤት ስራ መስጠት ነው፡፡ ለኦሮሞዎች የተበዳይነት ሙዚቃ ከፍቶ ሲያስቆዝም ለአማራው እንደጉተና የከበደ የበዳይነት ሸክም ጫነው፡፡ አማራው በተነፈሰ ቁጥር በእብሪተኛነት፣በጭካኔ፣በትምክህተኛነት እየፈረጀ ሁለተኛ ወደ ስልጣን ዝር ማለት የሌለበት እኩይ አድርጎ ያቀርባል፡፡

በትዝታ እንዲቆዝም የተደረገው ኦሮሞ ታዲያ አሁን ሊቀመጥበት የሚችለውን የፖለቲካ ስልጣን ወንበር ጥያቄ ረስቶ ቀና ብለው “አቤት” የማይሉትን አፄ ምኒልክን በመርገም፣በመውቀስ እንዲጠመድ ተደርጓል፡፡አፄ ምኒልክም መላውን አማራ ወክለው የሞቱ ይመስል ለእርሳቸው በተነሳው የጭቃ ጅራፍ አማራ የተባለው ሁሉ ይገረፍ ያዘ፣ ለምኒልክ የተከፈተ የበደል ሙዚቃ ለአማራ ሁሉ የሚበቃ የጥላቻ ስንቅ አስቋጥሮ በጎሪጥ ሲያስተያይ፣ አፍንጫ ሲመታ አይን እንዳያለቅስ እንባ አድርቆ ኖሯል፡፡ አማራውም በፊናው በዋናነት በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በሌሎች ክልሎችም ለፍቶ ያፈራውን ንብረት ለቆ እንዲወጣ ሲደረግ ይህን ያደረገው ማን እንደሆነ ስለሚያውቅ በተዋለደው እና አብሮ በኖረው ህዝብ ላይ አፉን አላላቀቀም፡፡አማራነቱ ብቻ በደል ሆኖ ተቆጥሮ የሚገረፍበትን በትር ብርታት ስላወቀ አድርጎት የማያውቀውን አንገቱን መድፋት ተማረ፣ቅዝምዝምን ዝቅ ብሎ ማሳለፍ ተሽሎት ወገኖቹ ሲታሰሩ፣ሲገደሉ፣ ከምድር ዳርቻ ሲሳደዱ አዝኖ እንዳላዘነ ሆኖ አለፈው፡፡ሽሽት የማያውቀው ህዝብ ሽሽት ለመደ፡፡ይሄኔ ነው እነ ስብሃት ነጋ፣ሳሞራ የኑስ እና መለስ ዜናዊን የመሰሉ የጥላቻ ሰባኪዎች ‘አማራን እንዳይነሳ አድርገን ቀበርነው’ ያሉት፡፡

ሰፊውን የአማራ ህዝብ ብቻቸውን ገድሎ ለመቅበር የንዑስነት አቅማቸው እንደማይፈቅድ የተረዱት ህወሃቶች ባለግርማውን የኦሮሞ ህዝብ መጠለያ ማድረግን መረጡ፡፡ ‘ከየት አመጣችሁት?’ ተብለው የሚጠየቁበት መድረክ የለምና የኦሮሞ እና የአማራ ህዝብ አለም ከተፈጠረ ጀምሮ በኖረ የመረረ፣ የከረረ ጠላትነት እንዳላቸው ብቻቸውን በያዙት መገናኛ ብዙሃን ሲያላዝኑ ኖሩ፡፡ በሃሰት የተለወሰ የፈጠራ እና የጥላቻ  መርዛቸውን መድሃኒት አስመስለው የሚያቀርቡበትን ስብከት ስለሚያረክስባቸው በሳይንሳዊ መረጃ ላይ የቆሙ የታሪክ ድርሳናትን አጣጣሉ፡፡እውነትን ለመፈለግ በየዋሻው የተሻጡ ‘ኦርጅናል’ የታሪክ መዛግብትን የሚያስሱ ኢትዮጵያ-በቀል የታሪክ  ተመራማሪዎችን ፈተናቸውን አብዝተው ከሃገር አሰደዱ፡፡ ሰሞኑን በፕ/ሮ ፍቅሬ ቶሎሳ አዲስ መፅሃፍ ሽያጭ ላይ የተዘመተው ዘመቻ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡

የጎንደሩ ጥሎሽ …

ህወሃት ሁለቱን ህዝቦች እርቅ ሊጎበኘው በማይችል የጠላትነት አዘቅት ውስጥ ለመክተት የተጠቀመው መንገድ መገናኛ ብዙሃን፣የራሳቸውን ሃላፊነት አልቦ አንደበት እና ከሁለቱም ብሄር የወጡ ግዙ ባለስልጣን እና ካድሬዎችን ብቻ አይደለም፡፡ የነመለስ ዜናዊ የጥፋት መንገድ እጅግ ረቂቅ ነውና የተስፋየ ገብረአብን ውብ ብዕርም ለዚሁ እንቅልፋቸውን ለሚነሳቸው የሁለቱ ህዝቦች አብሮነት ማፍረሻ በደንብ አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡ ተስፋየም ሃፍረት እና ይሉኝታ ባለፈበት ያለፈ ሰው ስላልሆነ  ‘ነቅተንብሃል’ እየተባለም በልጅነቱ እንደማተብ የታሰረለትን የጥላቻ ክታብ ሊያወልቅ አልቻለም፤ ከቀድሞ አልባሽ አጉራሾቹ ጋር ከተጣላ በኋላም የጥላቻ ብዕሩ መርዝ መትፋቱን አላቆመም፡፡ ህወሃት ይህን ሁሉ ከንቱ ድካም ሲደክም የኖረው በአሽዋ ላይ የቆመ ቤት ለመስራት ነበርና የአንድ ቀን የህዝብ ድምፅ የሃያ አምስት አመት ድካሙን ገደል ከተተው፡፡ ከወደ ጎንደር በፍቅር ብዕር፣ በመተሳሰብ ሸማ ላይ የተከተበች አንድ ባነር ታሪክ ለወጠች፡፡ “በጎዳና ላይ የሚፈሰው የኦሮሞ ወንድምና እህቶቻችን ደም የእኛም ደም ነው” የምትል የአቶ በቀለ ገርባን ምስል የያዘችው ባነር ስንቱ ፊደል ጠገብ አጥብቆ የፈተለውን የጥላቻ ገመድ በጣጠሰች፤በምትኩ ሁለቱን ታላላቅ ህዝቦች በፍቅር እንባ አራጨች፤ ያች ባነር!!! መብቱን ከማስከበር ጎን ለጎን የጠፋ ወንድማማች/እህትማማችነትን ፍለጋ የወጣው የጎንደር ህዝብ በፍቅር ፊት መቆም የማይችለውን የህወሃት በአሸዋ ላይ የተገነባ የጥላቻ ቤት በፍቅር አውሎ ንፋስ ከስሩ ነቀነቀው፡፡የጥላቻ መንገድ አይቀናም፡፡ የሴራ ወንበር አይፀናምና ይህ የሚጠበቅ ነው፡፡የጥላቻ ሰባኪዎች ግን ይህን ይረዱ ዘንድ ብቁ አይደሉም፡፡ በወርቅ የማይገዛውን  የወንድማማችነት ፍቅር “ያልተቀደሰ ጋብቻ” ሲሉ ያልተቀደሰ ጭንቅላታቸው ያቀበላቸውን ዘባረቁ፤ ፍርሃት ያራደው ከንፈራቸው ላይ የሞላውን ስድብ ሁሉ በሰፊው ህዝብ ላይ አወረዱ፡፡

Gondar protest, Bekele Gerba's banner

ኢህአዴጎች ጥሩ የተናገሩ እየመሰላቸው ከአንደበታቸው የሚወረውሯቸው ቃላት እና ሃረጋት በመንግስት መንበር ላይ መሰየማቸውን አይመጥኑም፡፡ ሌሎቹ ቀርተው የአንደበታቸው ርቱዕነት ወፍ ያረግፋል ይባሉ የነበሩት የአቶ መለስ አንደበት እንኳን በግሌ ጨዋነት የጎደለው፣ማናለብኝነት ያሸነፈው፣ አንዳንዴም ግልብ  እንደነበረ ይሰማኝ ነበር፡፡በተከበረው ፓርላማ ፊት ‘ጣትህን እቆርጣለሁ፣ ምላስ እዘለዝላለሁ’ ይሉ ነበር፡፡ የሁለት አካላትን ሰላማዊ ግንኙነትም ከዕቁባታዊ ግንኙነት ጋር እየመሰሉ ማስረዳቱ ይቀናቸው ነበር፡፡ በ1997ዓም አላሰናዝር ብለው የነበሩትን አናጎሜዝን በተመለከተ ለአዲስ ዘመን እና ዘኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጦች ኤዲተር በፃፉት ማስታዎሻ “what love has to do with this” የሚለውን የታዋቂዋን ዘፋኝ የቲና ተርነርን ሙዚቃ ግጥም መንግስትነትን በማይመጥን አላስፈላጊ ሁኔታ አስገብተው ነበር፡፡

አሁን የመንግስት አንደበት ተደርገው የተሰየሙት አቶ ጌታቸው ረዳ መሆናቸው ደግሞ በኢህአዴግ መንደር ለአንደበት ጨዋነት ብዙ ቦታ እንደሌለ አሳባቂ ነው፡፡ ብሶት በጠበንጃ ፊት እንደቆመ እንኳን አስረስቶ የሚያጮኽውን የኦሮሞ ህዝብ ከጅኒ ጋር እያነፃፀሩ ሲያስረዱ ለአቶ ጌታቸው በአማርኛ መራቀቅ፤ በሃሳብ መምጠቃቸው ሊሆን ይችላል፡፡ለሰሚ ግን ትርጉሙ ሌላ ነው፡፡ አንድ ሰው በቤቱ የቀረ በማይመስል ሁኔታ ነቅሎ የወጣውን የአማራ ህዝብ ትቂት የሽፍታ ጠበቆች ሲሉ ዘለፉ፡፡ ሁለቱ ህዝቦች ከተገደሉ ልጆቻቸው እኩል የተሰደቡት ስድብ አስቆጥቷቸዋል፡፡ በዚህ የማያበቁት አቶ ጌታቸው ‘ሁለት ባላንጣዎች ያተቀደሰ ጋብቻ መስርተዋል’ ሲሉ አከሉ፡፡ እውነት ለመናገር ነገሩ በጋብቻ ሁኔታ ባይገለጽ ደግ ነበር:: ሆኖም ሰው በልቡ የሞላውን  በአንደበቱ ይናገራልና አቶ ጌታቸው በልባቸው የሞላውን ገለፁ፡፡ነገሩ የሚገባቸው በጋብቻ ሁኔታ መገለፅ ካለበት የኦሮሞ እና የአማራ ታላላቅ ህዝቦች ቅዱስ ጋብቻ ጎንደር ላይ በቀረበችው የፍቅር ጥሎሽ (ያቺ ባነር)ተጀምሮ ኦሮሚያ ላይ “አማራ የኛ” በሚል ሙዚቃ ታጅቦ ተፈፅሟል፡፡ይህ ቢመርም ሊቀበሉት የሚያስፈልግ ሃቅ ነው! በምድር ላይ የሚያስተዳድረው ህዝብ መተሳሰብ የሚያናድደው፣ክፉ የሚያናግረው መንግስት ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ “የአማራ እና የኦሮሞ ህዝብ ይህን አይነት መፈክር ይዘው መውጣታቸው የእኛን ስራ ለ,ያለመስራት ያመላክታል”  አሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ለፋና ሬዲዮ፡፡ ፋይሉ በድህረገፆች ስላለ ዝርዝሩን አንባቢዎቼ ቢያዳምጡ ሙሉ ስዕሉን ለማግኘት ይችላሉ፡፡ይህ ከአእምሮ በላይ ነው!

ቅዱሱ ጋብቻ!   

የኢህአዴግን እግር ተከትሎ በሃገራችን የተንሰራፋው እትብት እየተማዘዙ የጎሪጥ የመተያየት አባዜ አሁንም የሃገራችን ፖለቲካ ዋና ነቀርሳ ነው፡፡ ችግሩ የሚመነጨውም ሆነ የሚበረታው ተማርኩ በሚለው የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ መማሩ ስነልቦናውን ከታሪክ ጋር እያዋቃ ጥላቻን ብቻ እንዲሰብክ ያደረገው የትየለሌ ነው፡፡እንደ ደህና ነገር ስንት ገፅ መፅሃፍ አሳትሞ በየገፁ ጥላቻን ሳይረሳ የሚሰብክ ምሁር በበዛበት ሃገር፤ኢህአዴግም ይህን በደንብ ሲያሳልጥ ሃያ አምስት አመት ከንቱ ሲደክም ቢኖርም ሰሚው ሰፊ ህዝብ ጥላቻን የሚሰማበት የጆሮ መስኮቱን ዘግቶ ኖሯል፡፡ የጎንደር ህዝብ የጀመረውን የፍቅር ምልክት የኦሮሚያ ህዝብ ወዲያው ማስተጋባቱ ድሮም ኢህአዴግ በሚያራግበውን እና ፅንፈኛ የጎሳ ልሂቃን በሚያንፀባርቁት ደረጃ ህዝቦች በጠላትነት እንደማይፈላለጉ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ሳይውልሳያድር እናንተም የእኛ ናችሁ ሲል መልስ የሰጠው በፍቅር መበለጥን ስላልፈለገ ነው፡፡በፍቅር ላለመበላለጥ መሽቀዳደም ደግሞ የመልካም ልቦና ዝንባሌ ነው፡፡ይህ ብው በሚያደርግ ንዴት ውስጥ የሚከተው ደግሞ ራሱን መመርመር ግድ ይለዋል!

ጎንደር እና አዳማ አፋፍ ላይ ሆነው “ደምህ ደሜ፣አጥንትህ አጥንቴ” ሲባባሉ ሌሎች ከተሞችም ይህን ሲከተሉ የኮምፒውተር “በተን” በነኩ ቁጥር ህዝብን የመሩ የሚመስላቸው የጥላቻ ሰባኪዎች የወንጀለኝነት ስሜት እንደሚሰማቸው ጥርጥር የለኝም፡፡ ወትሮም ገታራነት የማይጫናቸው የኦሮሞ ምሁራን ይህ የህዝብ መተሳሰብ የኖሩበትን የፖለቲካ አቅጣጫ እንዳስቀየራቸው በአንደበታቸው ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ሁሉም የሚሉት ‘ህዝብ መራን፤ህዝብ በለጠን፤ ህዝብ ቀደመን’ ነው ! የትምህርት ደረጃን ቆጥሮ ብዙሃኑን ህዝብ ሳይንቁ፣ እኔ አውቅልሃለሁ ሳይሉ፣ይልቅ መበለጥን  አውቆ አካሄድን ማስተካልም የምሁራኑን ትህትና ያመለክታልና በተለይ የኦሮሞ ምሁራን ለዚህ ትህትናቸው  ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

ያመኑት ፈረስ …..

ከህወሃት የወቅቱ ዘዋሪዎች አንዱ አይተ ኣባይ ፀሃይየ የፓርቲያቸውን አርባኛ አመት ድል ባለ ድግስ ሲያከብሩ ‘እነ ኢህአፓ ሲንኮታኮቱ እኛ ድል የተቀዳጀነው ህዝብን ለማታገል ቀለል ያለውን የጎሳ ፖለቲካ የሙጥኝ ስላልን ነው’ አይነት ንግግር ሲናገሩ ተገርሜ ነበር ያዳመጥኳቸው፡፡ህዝብን የማታገያ ዘይቤ የሚመረጠው ስለቀለለ ነው ወይስ የህዝብ እውነተኛ ጥያቄ ስለሆነ? ቀላል የተባለው የጎሳ ፖለቲካ ከምክንያት ይልቅ ስሜትን ስለሚፈልግ ብልጣብልጦቹ የህወሃት መኳንንት በጎሳህ ምክንያት የፈረደበት አማራ ቆረጠህ ፈለጠህ እያሉ  የብረት ተሸካሚ፣ ወላፈን እሳት ላይ ተማጋጅ ነፍስ ለማግኘት  ስለማያስቸግር ነው፡፡ስልጣን ላይ ከተሳፈረ በኋላም ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ከላይ ለመጥቀስ በተሞከረው መልክ በሃገሪቱ የሚገኙ ወንድማማች ህዝቦችን  ከአንድነታቸው  ይልቅ ልነት ላይ እንዲያተኩሩ ማድረጉን በቀላሉ ስልጣን ላይ ተወዝቶ የመኖሪያ ሁነኛ ዘዴ አድርጎት እንደነበር ነገራ ነገሩ ያስታውቃል፡፡ በዚሁ በጎሳ እና በጥላቻ ፖለቲካ ተፀንሶ፣አድጎ ዙፋን ላይ የተሰየመው ህወሃት/ኢህአዴግ የሚወደውን ዙፋኑን እየነቀነቀው ያለው ከጎሳ ፖለቲካ ጋር በተዛመደ የመረረ ጥያቄ መሆኑ ትልቅ የፖለቲካ አያዎ ነው!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s