የብአዴን የበታችነት ያክትም | ከያሬድ ጥበቡ

 

ከባህርዳር የሚወጡት መረጃዎች ሁሉ የሚጠቁሙት የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የሆነው አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሥልጣኑ እንደሚነሳ ነው ። ይህ በጣም የሚያሳዝን ፍፃሜና የክልሉን ህዝብ ፍላጎት የሚፃረር ተግባር ነው ። አቶ ገዱ የሚገለለው ምን ጥፋት ስለተገኘበት ነው? በሱ ምትክስ የሚመጣው ሰው ምን አይነት ሰው ይሆን? ይህስ ሹም ሽር ለህዛባዊ እምቢተኝነቱ የሚደነቅረው ችግርም ሆነ፣ የሚያደርገው አስተዋፅኦ ምን ሊሆን ይችላል?
Yared

ባለፉት 25 የወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ አመታት፣ ከዘጠኙ የክልል ፕሬዚደንቶች፣ እንደ አቶ ገዱ የህዝብ ይሁንታ ያገኘ ገዢ ነበር ማለት የሚቻል አይመስለኝም። ምናልባት ተቀራራቢ ሬከርድ የነበረው የትግራዩ ገብሩ አስራት ነበር ። አቶ ገዱም መልካም ስሙን አግኝቶ የነበረው፣ የአማራ ክልል ህዝብ የተለየ የልማት ተጠቃሚነት ስላገኘ ሳይሆን፣ የወያኔን ቀጥተኛ እዝ ለመቋቋም ፈቃደኛ መስሎ የሚታይ መሪ ሆኖ ስለተገኘ ነበር ። በተለይ የወያኔ ኮማንዶዎች በወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት ላይ ያልታሰበ ጥቃት በሰነዘሩበት ወቅት፣ ገዱ በእዙ ስር የነበረውን የክልሉን ልዩ ሀይል ለወያኔ ተባባሪ እንዳይሆኑ ከማድረጉም በላይ የጎንደር ህዝብ መሬት አንቀጥቅጥ ትእይንተ ህዝብ ባደረገበት ወቅት፣ ልዩ ሀይሉ ሰላማዊ ጥበቃ ከማድረግ ውጪ፣ ሰላማዊ ሰልፈኛውን እንዳይተነኩስ በማድረግ ጨዋ አመራርን ያሳየ ሰው ነበር ። እነዚህ መልካም ተግባሮቹና፣ የህዝብ ይሁንታ ያገኘ መሆኑ ግን ገዢውን ፓርቲ አላስደሰተውም ።

የሚፈለገው በሁሉም ክልሎች ከህዝብ የተነጠለና በነስዩምና አባይ ፀሀዬ የግል ፈቃድ ላይ የታጠረ ሎሌና ታዛዥ አመራር ብቻ በመሆኑ፣ አቶ ገዱ የሚገለልበት ወቅት ላይ ደርሰናል ። ይህ ግን መሆን አልነበረበትም ። የዞንና ወረዳ አመራሮችና ካድሬዎች “መሪያችንን በወያኔ ፈቃድ አናወርድም” የሚል ፅናት ቢኖራቸው ኖሮ፣ ወያኔ ወይ ተገዶ የብአዴንን አባላት ፍላጎት መቀበል ወይም የሲቪል አስተዳደሩን በትኖ ኦሮሚያ ክልል ላይ እንዳደረገው በወታደራዊ አገዛዝ መተካት ይገደድ ነበር ። ሆኖም ወያኔ የፈለገውን ማድረግ የሚችልበት አደጋ ከፊታችን ተደቅኗል ።

እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ከስልጣን መውረድ የነበረበት በጎንደር ከተማ ላይ ያልታሰበ ጥቃት ሰንዝሮ ለብዙ ዜጎች መቁሰልና ሞት ምክንያት የሆነው የትግራይ ክልሉ ፕሬዚዳንት አባይ ወልዱና ከማእከላዊ መንግስቱ የሚተባበሩት ዘረኞች ነበሩ ። አባይ እግሩን አንፈራጦ ተቀምጦ ወያኔ ጥልቅ ተሃድሶ አደረግኩ ብሎ ስብሰባውን ባጠናቀቀበት ሳምንት ብአዴን የህዝብ ይሁንታ ያገኘ መሪውን ለማሰናበት ቢገደድ፣ ሊያፍርበት የሚገባው ውሳኔ ነው ። አሁንም እድል ስላለ ከዚህ አይነት አሳፋሪ ውሳኔ ራሱን ማቀብ ይገባዋል ብዬ ማሳሰብ እወዳለሁ ።

እያንዳንዱ የዞንና የወረዳ ካድሬና አመራር አባል “አባይ በስልጣኑ ተቀምጦ ገዱን ብናወርድ የትግራይ ጠባብ ብሄርተኞችን እብሪትና መሳለቅ እንዴት ልንመክት ነው” ብሎ ሊጨነቅና ሊጠበብ ይገባው ይመስለኛል ። የምፅፈውን እንደምታነቡና፣ አጭር ፅሁፍ ለማንበብ የሚያሰችል ያህል የኔትወርክ ግንኙነት እንዳለ ስለማውቅ፣ “መካሪ አጥተን” ተሳሳትን እንዳትሉም በማሰብ ነው ። እባካችሁ ከዚህ አይነት አሳፋሪ ውሳኔ ታቀቡ ። የህዝባችሁንም ልብ በሃፍረትና በሃዘን አትስበሩ ። ጦርነት የቀሰቀሰውና፣ የድንበር ግፊት የሚያደርገው፣ ወልቃይቶችን የአማርኛ ዘፈን አደመጣችሁ ብሎ የሚያስደበድበው፣ አንዳችም ትንኮሳ ሳይደረግባቸው “በትግሬነታችን የተነሳ የዘር ማጥፋት ታቃጣብን” በሚል የሀሰት ክስ በጎንደርና በጎጃም የሚኖሩ ትግሬዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲሰደዱ በማበረታታት አሳፋሪ ተግባር የፈፀመው አባይ ወልዱና ተባባሪዎቹ የሆኑት ስዩም መስፍንና አባይ ፀሀዬ በስልጣን ተቀምጠው እንዴት በሰላማዊ ህዝብ ላይ አንተኩስም ያለ መሪያችሁን አሳልፋችሁ ለጠባብ ብሄርተኞች ትሰጣላችሁ ?
ቢያንስ በህገ መንግስት የተሰጣችሁንስ የክልል መሪውን ራሱ የክልሉ ህዝብ የመምረጥ መብቱንስ እንዴት ተላልፋችሁ፣ የክልሉ ሸንጎ፣ ፕሬዚዳንት አድርጎ የመረጠውን ሰው፣ በካድሬ ስብሰባ ትሽራላችሁ? ያወጣችሁትን ህግ ራሳችሁ እያፈረሳችሁ፣ ነገ ሲከፋችሁ ለናነተስ የሚደርስላችሁ የህግ ከለላ ከየት ሊገኝ ነው? እባካችሁ ተመከሩ ። የወያኔን እዝ የመፈፀም ምንም አስገዳጅ ሁኔታ የለባችሁም ። ይህ ምንጠራ በገዱ ይቆማል ብላችሁ ካሰባችሁም ሞኞች ናችሁ ። እንዲያውም ከገዱ ይልቅ ዋነኛዎቹ ኢላማዎች እናንተ ናችሁ ። ገዱስ ከፕሬዚደንትነት ቢነሳም ወይ አምባሳደር ወይም ምክትል ሚኒስትር ሹመት ለጊዜው ለመደለያ ይሰጠው ይሆናል ። ማወቅ ያለባችሁ ፣ ወያኔ “የዞንና ወረዳ ካድሬዎችና አመራሮች ናቸው ህዝቡን አይዞህ እያሉ ትምክህተኛ ያደረጉት” በሚል ጥርሱን የነከሰው በናንተ ላይ ነው ። በመቶዎች የምትመነጠሩትና መንገድ ዳር የምትወረወሩት እናንተው ናችሁ ። በዚያን ወቅት፣ አሁን ልትሰሩት በምትከጅሉት ገዱን የማባረር ውሳኔ የተነሳ፣ ዛሬ ፍቅር የሚያሳያችሁ ህዝብ ዓይናችሁን ላፈር ይላችኋል ። በረከት ስምኦንና ከበደ ጫኔ እያመሷችሁ እንደሆን እሰማለሁ ። ካስፈለገ “ዘወር በሉ ከፊታችን” ልትሏቸው ይገባል ። ደግሜ ላስጠንቅቃችሁ ፣ ዛሬ በገዱ ላይ እንድትወስኑ የምትጠየቁት ውሳኔ እውነተኛው ሰለባዎች ገዱ ሳይሆን እናንተ ናችሁ ። ጭክን አድርገው ነው የሚቀጠቅጧችሁ ። ለሌላው መማሪያ እንድትሆኑ አድርገው ነው የሚያደኸየሁዋችሁ ። ወሳኙን ትግል ዛሬ አድርጉ ።

የሰማሁት መረጃ እርግጠኛ ከሆነ፣ ወያኔ በገዱ ምትክ እንድትመርጡለት የሚፈልገው ብናልፍ አንዱአለምን ነው ። ይህ ሰው ለስራው ይመጥናልን? ባለፉት አመታት አፍቃሪ ወያኔ ተልእኮዎችን በማስፈፀም ስሙ የተበከለ ሰው አይደለምን? ከህዝቡ ፍላጎትና ስጋት ጋር የሚመጥን የተሻለ ሰው ከመሃላችሁ አይገኝምን? እንደኔ ግን ስለ ለውጥ ባታሰቡና፣ የወያኔ የጎማ ማህተም ባትሆኑና የክልላችሁን ህዝብ እንባ ብታደርቁ ይሻላችሁ ይመስለኛል ። በእኔ እምነት የተሻለው መንገድ በገዱ ዙሪያ ቆማችሁ፣ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፋችሁ “እምቢ ለወያኔ እዝ” ማለት ነው ። ለማንም ብላችሁ ሳይሆን ለራሳችሁ ስትሉ ። ልጆቻችሁን መንገድ ዳር ላለመወርወር ስትሉ ። ስራችሁን ላለማጣት ስትሉ ። ስደትና እስር እንዳያገኛችሁ ስትሉ ። ከሁሉም በላይ ግን ለሰብአዊ ክብራችሁ ስትሉ ።

በገዱ ላይ የምታደርጉት የወንጀል ትብብር፣ እውነተኛው ገፈት ቀማሾች ራሳችሁ መሆናችሁን ለሰከንድ እንኳን አትጠራጠሩ ። የናነተን ፈቃድ ሳይዝ ወያኔ ብቻውን ይህን ማድረግ አይቻለውም ። “የክልሉ ምክርቤት የመረጠውን መሪ እኛ ካድሬዎች ተሰብስበን ማውረድ አንችልም” ማለት መብታችሁ ነው ። ያንን መብታችሁን ተጠቀሙበት ። የክልሉ ምክርቤት ሲሰበሰብ ደግሞ፣ ከክልሉ ህዝብ ፍላጎትና የአስተሳሰብ እድገት ጋር የሚመጥን ውሳኔ ለማድረግ ታገሉ ። ገዱን አለማውረድ ብቻ ሳይሆን፣ ለወያኔ የተላላኪ ሚና ከመጫወት የማይመለሱትን ከሰልፋችሁ የማጥራት፣ በምትካቸው ህዝቡ ይወክሉኛል የሚላቸውን አዳዲስ የክልል ሸንጎ አባላትን በየአካባቢው እንዲመርጥ እስከማድረግ በትግሉ ግፉበት ። በመታገል የምታጡት ነገር የለም፣ ከወያኔ ጋር ከተሳሰራችሁበት የውርደት ካቴና ውጪ።
አዎን የውርደት ካቴና ይሰበር ። በክልላችሁ ይህን በማከናወን፣ ለኢትዮጵያም የተደላደለና የተረጋጋ የሰላማዊ ፖለቲካ ሽግግር እድል ታስጨብጣላችሁ ። ይህን ማድረግ አቅቷችሁ የወያኔን ፍላጎት ብታሰፈፅሙ ግን፣ የውርደት ሰንሰለታችሁ መጥበቅ ብቻ ሳይሆን፣ የመንገድ ተዳዳሪ ትደረጋላችሁ ። ትራባላችሁ፣ ትጠማላችሁ ። ያኔ የሚያዝንላችሁ ከንፈር መጣጭ ስንኳ አታገኙም ። እባካችሁ ለራሳችሁ ስትሉ ተመከሩ ። በገዱ ዙሪያ ቆማችሁ የወያኔን ጠባብ ብሄርተኛ እብሪትና የትንኮሳ ፓለቲካ አምክኑ ። ኢትዮጵያችንንም ከትርምስ ታደጓት ። ዛሬ በማወላወልና በፍርሃት ከወያኔ ጋር ብትቆሙ ግን እንደ ገና ዳቦ፣ ወያኔ ከላይ፣ ህዝባዊ እምቢተኝነቱም ከስር ይለበልቧችኋል ። በማንኛውም ሰው ውስጥ ያለው የፍትህ ብርሃን የናንተንም ውሳኔ እንዲመራው ጥልቅ ምኞቴ ነው ። ፈጣሪያችሁ ቀናውን መንገድ ያሳያችሁ።

ለብአዴን ካድሬዎችና አባላት ይህን መልእክት ማድረስ የምትችሉ ሁሉ ተባበሩ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s