የተጋሩ ፈተናዎች እና የመፍትሔ ጥቆማዎች (በአቤል ዋበላ)

 

ወያኔ-ህወሓት ለትግራይ ህዝብ (ተጋሩ) በረከት ወይስ መርገም አመጣለት የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጥልቅ ጥናት የሚያሻው ይመስለኛል፡፡ ይህንን ጥናት ለማካሄድ ቁርጠኝነት ቢኖር እንኳን ጉዳዩ ተጨማሪ ገቢሮችን እያስተናገደ መሄዱ ጉዳዩን የበለጠ ውስብስብ ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ ባለአእምሮ የሆነን ሁሉ ያስጨንቃል፡፡ ምክንያቱም ዋጋው ከጥቂት የንጹሐን ደም እስከ ዘር ማጥፋት ድረስ የሚያስከተል አሳሳቢ እና አደገኛ ስለሆነ ነው፡፡ ከደደቢት አንስቶ እስከ አራት ኪሎ(1996-1983 ዓ.ም.) ያለውን ማስላት አጠቃላዩን የቡድኑን ጉዞ እና መጪውን ጊዜ እንደመተንተን አይከብድም ብዬ አስባለው፡፡ የነገው ግን ትልቅ ሸክም ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችለው ከስሜት የጸዳ እና አስተዋይ አእምሮ ያለው ሰው ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ ያንን ሚና የመወጣት ትዕቢት እንደሌለ ከወዲሁ መግለጽ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን የብዙ ወገኖቼ ስጋት የኔም ስጋት ነውና ዝም ከማለት አንዳንድ ሐሳቦችን ለመጠቆም ሰለመረጥኩኝ ይህንን ጻፍኩኝ፡፡
ከፈተናዎቹ ልጀምር፡፡ የተደበቀ ነገር ሳይሆን ሁላችንም ያስተዋልነው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ወያኔ አምባገነን የሚያስብሉ ሁሉንም አይነት ዕኩይ ተግባራት ፈጽሟል፡፡ ይህ ለትግራዋይም ሆነ ለሌላው ኢትዮጵያዊ የተሰወረ አይደለም፡፡ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት በኢትዮጵያ ያለው ስርዓት ጨቋኝ አይደለም ወይንም ቢያንስ የተወሰነው የትግራይ ተወላጅ የተለየ ጥቅም አላገኘም ብሎ የሚያምን ቢኖር ከዚህ በታች ያለውን በማንበብ እራሱን እንዳያደክም እመክራለው፡፡

ጦማሪ አቤል ዋበላ
ጭቆናን ለዘላለም ተሸክሞ የሚኖር ህዝብ ስለሌለ ጊዜው ሲደርስ በአብዛኛው ሀገሪቱ ክፍል ህዝባዊ እምቢተኝነት ተነስቷል፡፡ ይህንን እምቢተኝነት ለማፈን ስርዓቱ የጭካኔ እርምጃዎች እየወሰደ ደም እያፈሰሰ ነፍስ እየቀጠፈ ነው፡፡ ይህም ህዝቡን ወደ አልሞትባይ ተጋዳይነት እያመራው ነው፡፡ በሞት እና በህይወት መካከል ያለ ሰው ደግሞ የሚታገለው ጨቋኙ በመረጠለት መንገድ ብቻ ነው፡፡ ጨቋኙ የውሸት ዴሞክራሲን እና መከፋፈልን እንደተጠቀመው ሁሉ የትግራይ ህዝብንም እንደመሳሪያነት ተጠቅሟል፡፡ ለአንዳንዶች ደግሞ ጨቋኙ የትግራይ ህዝብ ጉያ ውስጥ የተሸሸገ በትግራይ ህዝብ የሚነግድ ሳይሆን እራሱ የትግራይ ህዝብ ነው፡፡
ወደዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረሳቸው ሁለት ዐብይ ምክንያቶችን ይጠቀሳሉ፡፡ አንደኛው የትግራይ ተወላጆች ለስርዓቱ ያላቸው ስስ ልብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በጉልህ የሚታየው በሁሉም ዘርፍ ያለ ተጠቃሚነት ነው፡፡ ተጋሩ ስለወያኔያዊው ስርዓት መቆርቆራቸው አንደኛው ምክንያት ተፈጥሮዊ የሆነና በሰውን ልጆች መካከል ያለ የቅርብ ወገንን አብልጦ የመውደድ ስሜት ነጸብራቅ ስለሆነ ጤነኛ እና የሚጠበቅ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ያዋለደው ነው፡፡ ‘እኛ ነን ከአውሬው የደርግ ስርዓት ነጻ ያወጣናችኹ’ ከሚለው አንስቶ ‘የኢትዮጵያ ህዝብ ከትግራይ ህዝብ ጋር ጠላትነት ውስጥ ገብቷል፤ ስለዚህ እኛን መደገፍ ያለባችኹ ለራሳችሁ ህልውና ስትሉ ነው’ እስከሚለው የሚደርስ ነው፡፡ የትግራይ ተወላጆች ተጠቃሚነት ሁሉንም ዘርፍ ያካለለ ነው፡፡ መደበኛ እና ኢ-መደበኛ የፖለቲካ ስልጣን የበላይነቶች፣ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ አብላጫዎች፣ በሠራዊቱ፣ በፖሊስ እና በደህንነቱ ውስጥ ያሉ ፍጹም የበላይነቶች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
እነዚህን ሁለት ጉዳዮች የሚመለከቱ ተጋሩ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ህወሓትን ከትግራይ ህዝብ ለመለየት ቢከብዳቸው አይፈረድባቸውም፡፡ ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ በሀሳብም በተግባርም የህወሓት አቻ ገጽ ሆኖ ስለተሳለ ነው፡፡ ማደናገሩ መደናገር ሆኖ ቢቀር መልካም ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ጨቋኙ ለተጨቋኙ የመታገያ መንገድ እየመረጠለት ነው፡፡
ከቀልባቸው ጋር የሆኑ ተጋሩዎች ፈተና ይሄ ነው፡፡ በጠራራ ጸሐይ የሚፈጸመውን በደል ይመለከታሉ፡፡ ይህንን ለማስወገድ የሚደረግ ትግል ተገቢ እና የተቀደሰ እንደሆነ ይገነዘባሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ትግል የገዛ ወገናቸውን ዒላማ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በሥራው ጥፋት ተመጣጣኝ ቅጣት ቢያገኝ ችግር አይኖረውም ነበር፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ስርዓቱ የፈጠረለትን ኢ-ፍትሓዊ ዕድል ተጠቅሞ አዲስ አበባ ላይ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ቢገነባ ወይም ጋምቤላ ሰፋፊ እርሻዎች ቢኖሩት አልያም ከኦሮሚያ ጫት እና ቡና ወደውጪ ቢልክ ደክሞ ያገኘውን በመተው በዘረፋ የወሰደውን ንብረት እንዲመልስ እና ለተላለፈው ህግ በፍርድ ቤት እንዲጠየቅ ይደረጋል እንጂ ህይወቱን እንዲያጣ መደረግ የለበትም፡፡ ይህ በግለሰብ ደረጃ ያለ ነው፤ ወደጅምላ ጭፍጨፋ ላለማደጉ ግን ምንም ዋስተና የለንም፡፡
ይህንን ያልተመጣጠነ ምላሽ እና የጅምላ ፍረጃ በመስጋት ተጨቋኙን በስርዓቱ ላይ ማመጽን ተው ማለት ተገቢ እንዳልሆነም ሁሉም ይረዳዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የትግራይ ተዋላጅ የሆነ ባለአእምሮ ኢትዮጵያዊ ‘የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ’ ሆኖበት ተጨንቆ ይገኛል፡፡ ይህም እጅና እግሩን አስሮ የበይ ተመልካች አድርጎታል፡፡ የችግሩን ስፋት ቢገነዘብም ምንም አይነት ሱታፌ አለማድረጉ ሁሉን ነገር ጊዜ እንዲፈታው የተወ ያስመስልበታል፡፡ ነገር ግን ችግር ሳይፈቱ እንዳለ ቢተውት የበለጠ ውስብስብ ሆኖ ለመፍታት አስቸጋሪ ይሆናል እንጂ ወደ ሰማይ አይተንም፡፡
ከላይ ያነሳነው ዝምታ ለሁላችንም አይበጅም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በትግራይ ተወላጆች ግምባር ቀደም ተነሳሽነት ያልተጀመረ ትግል ሀገርን እንዳማያድን ጽፈዋል፡፡ ስለዚህ ለሁላችንም ሲባል ይህን ዝምታ( እርግጥ ነው ይህ ዝምታ የማይመለከታቸው ከጥቂት ግለሰቦች መኖራቸውን አልክድም) መስበር አስፈላጊ መሆኑን በማመን አንዳንድ ሊደረጉ የሚችሉ ነገሮችን መጠቆም ወደድኩኝ፡፡ ጥቆማዎቹ መሰረት ያደረጉት ይህንን ስርዓት ለመለወጥ ወይም ተገዶ መሰረታዊ ማሻሻሎችን እንዲያደርግ የትግራይ ተወላጆች ሚና ምን ይሁን በሚለው እና ለውጥ ቢመጣ ደግሞ ለውጡ በሰላማዊ ሽግግር የሚጠናቀቅበትን የትኛውም የኢትዮጵያ ማኀበረሰብ የጥቃት ዒላማ እንዳይሆን ማድረግን ነው፡፡
1. የትግራይ ብሔርተኝነት ፈር ማስያዝ:- በስርዓቱ አፈቀላጤዎች ሆን ተብለው የሚቀናበሩ አጀንዳዎችን በጥንቃቄ ማስተዋል ይገባል፡፡ ለምሳሌ አጼ ዮሐንስ በኢትዮጵያ ታሪክ ያላቸውን ድርሻ ማጉላት እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ንጉሱ እንደሌሎቹ የሀገሪቱ ነገስታት የሚነቀፍ እና የሚያስመሰገን ታሪክ ሰርተው አልፈዋል፡፡ ይህንንም ሁሉም ኢትዮጵያው ይረዳዋል፡፡ ዝርዝሩ ለአካዳሚያዊ ስራዎች የሚተው ነው፡፡ ነገር ግን አጼው ከሌሎች ነገስታት ተነጥለው እንደሚወቀሱ እና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ህሊና ተገቢው ቦታ እንደሌላቸው አድርጎ የማቅረብ አባዜ ይስተዋላል፡፡ ይህ የትግራይ ተወላጅ የሆነ ኢትዮጵያዊን በጭፍን ለመንዳት ካልሆነ ምንም ረብ የለውም፡፡ በቅርቡ የሰማኹት ደግሞ “‘ትግሬ’ ብሎ መጥራት አስነዋሪ ነው የትግራይ ተወላጅ ትግሬ ሳይሆን ‘ተጋሩ’ የሚባለው ነው’ የሚል ክርክር ነው፡፡ ይህ ከቀድሞው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘…ወርቅ የሆነው…’ ከምትል ንግግር ጋር ሲደመር በናዚ ሰርዓት እንደነበሩት ጀርመናውያን የበላይነት ስሜትን በመቆስቆስ ከሌሎች ጋር በእኩልነት መኖርን አደጋ ውስጥ ይከታል፡፡
2. የኢትየጵያ ህዝብ በተለይ አማራው ጠላትህ ነው የሚለውን ስብከት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዳይሸጋገር መግታት:- ብዙ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ከሌላ ብሔር ተወላጆች በእጅጉ በሚሻል መልኩ ልጆች የወላጆቻቸውን ቋንቋ በቤት ውስጥ እንዲማሩ ያደርጋሉ፡፡ ይሄ የሚበረታታ ነው፡፡ ቋንቋ እና ሌሎች መገለጫዎችን ልጆች እንዲማሩ በትጋት መስራት ያስፈልጋል ጠላትነትን ግን በአዲስ ትውልድ አእምሮ ውስጥ አንዝራ፡፡
3. የህወሓት የተጋድሎ ታሪክ ድምጸት ማሰተካከል:- ከደርግ ጋር በተካሄደው ትግል በርካታ የትግራይ ተወላጆች መስዋዕት መሆናቸው ሀቅ ነው፡፡ ይህ ዋጋ ተከፍሎ ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ደግሞ በብዙዎች ዘንድ እነዚህ ሰዎች ያን ሁሉ ዋጋ የከፈሉት ለምንድን ነበር የሚለው እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል፡፡ ይህንን ተረክ አጉልቶ መናገር አሁን በስርዓቱ እየደማ ባለው ዜጋ ቁስል ላይ እንጨት እንደመስደድ ይቆጠራል፡፡ የትጥቅ ትግሉ መሪዎችንም ተጨቋኙ ህዝብ የሚመለከተው በተመሳሳይ መልኩ ነው፡፡ የእነርሱን ምስል ማግነን የጭቆናው ስርዓት ይቀጥል እንደማለት ይቆጠራል፡፡ በእርግጥ ቡድኑ እና የቡድኑ አውራ የነበሩ ግለሰቦች ለሀገር ያበረከቱት አስተዋጽኦ ካለ ታሪክ አይዘነጋቸውም፡፡ ነገር ግን እሬሳን ከመቃብር እያወጡ በእርሱ ተከልለው ዙፋን ላይ መቀመጥ የማያዋጣ የፖለቲካ ታክቲክ ነው፡፡
4. ልማቱን በዝርዝር መፈተሸ፡- ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በርካታ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ይህ ግን ግርድፍ መረጃ ስለሆነ በዝርዘር መታየት አለበት፡፡ እንደ አስረጅ ሲቀርብ እንደችሮታ መታየት የለበትም ምክንቱም መንግስት ያን ማደረግ ግዴታው ነውና፡፡ የተሰሩ የልማት ሥራዎች በደንብ የተጠኑ ነበሩ? ባለሙያዎች ስለእነዚህ የተሰሩ ፐሮጀክቶች ምን ይላሉ? ህዝቡስ በርግጥ በቂ ነገር አግኝቷል? የልማት ክፍፍሉ ፍትሓዊ ነበር? የህዝብ ሀብት በልማት ሰበብ አልተዘረፈም? ጥራቱስ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? ምን ያህል ብር ተበድረን? ለመጪው ትውልድ ምን ያህል ዕዳ አሸጋግረን? የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት እና ዕድል በአግባቡ ተጠቀምን? በአለም አቀፍ ደረጃስ ቦታችን የት ነው? የመንግስት ሰነዶች እና ቁጥሮች ምን ያህል ተዓማኒ ናቸው? አለም አቀፍ ተቋማት እና ልዕለ-ኃያል መንግስታት በምን ፍልስፍና ከአምባገነን መንግስት ጋር ያሰራሉ? ስለልማት ስናወራ እነዚህን እና ሌሎች ተገቢ ጥያቀዎች ለመመለስ መሞከራችንን አንርሳ፡፡
5. የትግራይ ተወላጆች ያገኙትን ኢ-ፍትሓዊ ጥቅሞች ማመን፡- በዚህ ስርዓት የትግራይ ተወላጆች ጨርሶ የተለየ ጥቅም አላገኙም ብሎ መካድ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያለንን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል፡፡ የትግራይ ተወላጆች በግልጽ የሚታይ አይን ያወጣ ዘረፋ እያካሄዱ ነው፡፡ ከመካድ ይልቅ የሚሻለው የእነዚህ መረጃዎች ምንጭ መሆን ነው፡፡ የትኞቹ የትግራይ ተወላጆች እንዴት በመንግስት ድጋፍ እንደበለጸጉ፣ የህዝብ ሀብት እንደዘረፉ፣ የትኞቹ ባለስልጣናት ምን ያህል የሀብት ክምችት እንዳላቸው እና ከሀገር እንዳሸሹ፣ የትኞቹ የልማት ስራዎች አለአግባብበ ትግራይ ክልል እንደተከናወኑ ማጋለጥ ሌላው ኢትዮጵያዊ በላባቸው ደክመው ሀብት ያደራጁ የትግራይ ተወላጆችን ከሌቦቹ ጋር እንዳይፈርጅ ይረዳዋል፡፡ የትግራይ ህዝብ የትኛው ባለስልጣን ምን እንደዘረፈ እና ማን ዘመዶቹን የሀገር ሀብት ሰርቆ እንዳናጠጠ ያውቃል፡፡ ይህንን በተጨባጭ መረጃ በማራጀት እና ይፋ በማድረግ በደፈናው ሙሉ ተጋሩ ዘርፎ እንደከበረ የሚነገረውን በማስተካከል ወደ እውነታው ማምጣት ያስፈልጋል፡፡
6. የትግራይ ህዝብ በዚህ ስርዓት የደረሰበትን በደል ማጋለጥ፡- በትግራይ ያለው ፖለቲካዊ አፈና ከሌላው የኢትዮጵያ ክልል ቢበረታ እንጂ አያንስም፡፡ ነገር ግን ይህ ለሌላው ኢትዮጵያዊ አስረጅ በሆነ መልኩ ሊገለፅ ይገባዋል፡፡ እርግጥ ነው ጥቂት የአረና ፓርቲ ወጣቶች የተወሰኑ ሙከራዎች እያደረጉ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን በቂ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ሶሻል ሚዲያ የዜጎችን ችግር እያንዳንዱ ዜጋ ወደአደባባይ ማውጣት እንዲችል አድርጓል፡፡ ስለዚህ የስርዓቱን አፈናዎች ለማውጣት በሌሎች የሀገሪቱ ክፍል እንዳለው መነሳሳት በትግራይም ሊኖር ይገባል፡፡
7. በትግራይ ያለውን ድህነት በመረጃ ማሳወቅ፡- ምን ያህል የትግራይ ተወላጆች የምግብ እህል ተረጂዎች ናቸው? ምን ያህሉ የትግራይ ገበሬ አርሶ ልጆቹን ማብላት ይችላል? ስንት ወንድም እህቶቻችን ከትግራይ ተሰደዱ? ከሦስት ዓመት በፊት ሳውዲ አረቢያ ካባረረቻቸው ኢትዮጵያውያን መካከል ምን ያህሉ ከትግራይ ናቸው? በትግራይ ከተሞች ጎዳና ተዳዳሪነት እና ልመና እየቀነሰ ነው ወይስ እየጨመረ? ወጣቶች ተምረው በቀላሉ ስራ ያገኛሉ ወይስ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ስራአጥ ይሆናሉ? ወይስ ለሆዳቸው ሲሉ በስርዓቱ መዋቅሮች ውስጥ በታማኝ ካድሬነት ያገለግላሉ? እነዚህ መረጃዎች ተዓማኒ ሊባል በሚችል መልኩ ከተደራጁ ትግራይ ተጠቅሟል ወይም አልተጠቀመም የሚል ክርክር ውስጥ ሳንገባ በሀገራችን ፍትሓዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የበኩላችንን ለማደረግ ያግዘናል፡፡
8. የሀይማኖት አባቶች ከብሔራቸው ይልቅ ለሃይማኖታዊ መመሪያቸው እንዲታመኑ ማድረግ፡- ትግራይ የእስልምናም የክርስትናም የሀይማኖት አባቶች መፍለቂያ ነች፡፡ በተለይ የዘር ሐረጋቸው ከትግራይ የሚመዘዝ ብዙ ካህናት እና መነኮሳት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ የሀይማኖት አባቶች መካከል ጥቂት የማይባሉት ከአምላካቸው ይልቅ ለመንግስት ባለስልጣናት ሲያጎበድዱ የሚስተዋሉ ናቸው፡፡ ለእነዚህ አባቶች ከቄሳር ይልቅ ለጌታ እንዲገዙ፣ ድሃ ሲበደል ፍርድ ሲጓደል የሚያዝኑ፣ የሚጸልዩ እና አጥፊውን የሚገስጹ እንዲሆኑ መንገር ይገባል፡፡ በተለይ እርስ በርስ የሚያጠፋፋ፣ ህዝብን በህዝብ ላይ የሚያነሳሳ ነገር ከመከሰቱ በፊት ግንባር ቀደም በመሆን ይህንን አደጋ መመከት የእነርሱ ድርሻ መሆኑን እናሳውቃቸው፡፡ የማይገባውን ለመውሰድ የሚሮጠውን፣ የንጸኀንን ደም ለማፍሰስ የሚቻኮለውን ሁሉ ከተግባሩ እንዲታቀብ እንዲያስጠነቅቁ፣ ህዝቡን ደግሞ የሌላ ሰውን ነጻነት ማክበር ሀይማኖታዊ ግዴታው እንደሆነ እንዲያስተምሩ መንገር ያስፈልጋል፡፡
9. ማኀበረሰባዊ ትስስርን በመጠቀም ግንዛቤ መፍጠር፡- በመኖሪያ ቤት ከቤተሰብ ጋር፣ በትምህርት ቤት ከጓደኞቻችን፣ በመስሪያ ቤት ከባልደረቦቻችን ጋር በመነጋገር እየመጣ ያለውን አደጋ ማስገንዘብ ይገባናል፡፡ በኢትዮጵያ የዘር ግጭት ሊነሳ የሚችልበት ዕድል ዜሮ እንዳልሆነ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በኮንሶ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ መንስኤዎች እና በትግራይ ህዝብ ስም እየተፈጸመ ያለውን ወንጀል የውይይት ርዕስ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በሠራዊቱ፣ በደህንነት መዋቅሩ እና በመንግስት ስልጣን ላይ ያሉ ዘመዶችን እባካችኹ የዚህ ዕኩይ ተግባር ተሳታፊ አትሁኑ ማለት ይገባል፡፡ የበታች ካድሬ ወገኖቻችን የገዛ ወጋናቸውን በሚጎዳ ተግባር እየተሳተፉ እንደሆነ ማስረዳት ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
10. የትግራይ ተቃውሞን(#TigrayProtests) ማደራጀት፡- ከላይ ባየናቸው ዝርዝር ጉዳዮች ላይ የሚኖረን ምላሽ ትግራይ ስለራሱ ሲል ማመጽ ወይም አለማመጽ እንዳለበት ይነግረናል፡፡ በደሉ በራሱ ላይ ባይደርስበት እንኳን ስለተጨቆኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ሲል ማመጽ ይገባዋል፡፡ እርግጥ ነው ከላይ እንዳነሳነው መታፈኑ ከሌላው ቢብስ እንጂ ስለማያንስ መሬት ላይ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ይከብድ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ቢያንስ በሶሻል ሚዲያ ያንን አመለካከት ማራመድ አያቅትም፡፡
አንዳንዶች አጠቃላይ ችግሮችን ለማስቀረት በኢትዮጵያ ታርጋ ብቻ ነው መቃወም ያለብን የሚል ክርክር ያነሳሉ፡፡ ይህንን ሲሉ ኢትዮጵያዊነት በስርዓቱ ተረጋግጦ እንደወደቀ አልተረዱም፡፡ ኢትዮጵያዊነት በመታገያ ስልትነት የማገልገል እድሉ አናሳ መሆኑን የኢትዮጵያን የፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉ ሁሉ ይገነዘባሉ፡፡ ከዚያ ይልቅ ኢትዮጵያዊነት መፍትሔ ነው፤ ሁላችንም የምናሸንፍበት፣ ከጥፋት የምንድንበት መፍትሔ፡፡ ብቸኛው መፍትሔ ግን አይደለም ሌሎች ሁላችንም የምንሸነፍባቸው ‘የመፍትሔ ሐሳቦች’ አይጠፉም፡፡ አሁን ግን አንድ የትግራይ ተወላጅ ተነስቶ “ኢትዮጵያ ኢትየጵያ፣ አንድነት አንድነት” ቢል ሌላው የሚረዳው ሊያታልለው እየሞከረ እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ተጋሩ ያለው አማራጭ ህዝቡ ከስርዓቱ እንደሚለይ ማሳየት ነው፡፡ ይህ ሁለት ዕድሎችን ይዞ ይመጣል፡፡ አንደኛው ተጨማሪ የህዝብ ሀይል ወደ ትግል መድረኩ አምጥቶ ስርዓቱን አዳክሞ የሚውደቅበት ጊዜ ያፋጥናል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ስርዓቱን ባያዳክም እንኳን በህዝቦች መካከል የጠላትነት መንፈስን አጥፍቶ የትግራይ ህዝብን ወደ ‘የኢትዮጵያ ጭቁን ህዝቦች ህብረት’ ያስገባል፡፡
ዝርዝሩ በዚህ ያበቃል ብዬ አላስብም፡፡ እስኪ ሌሎቻችንም ተጨማሪ መደረግ የሚችሉ ነገሮች ካሉ ጠቁሙን፡፡ ምናልባት አንዳንድ ሰው ከዚህ የተወሰኑ ሐሳቦች ወስዶ የስርዓቱ እድሜ ለማራዘም መጠቀሙ አይቀርም፡፡ ለእንደዚህ አይነቱ ሰው አጭር መልዕክት አለኝ፡፡ በእሳት አትጫወት! አበቃኹኝ፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s