ኢሬቻ – ህዝብ ለዋቃ ምስጋና ፣ ለወያኔ የጦር ቀጠና [ታሪኩ አባዳማ]

ታሪኩ አባዳማ መስከረም 2009

erecha-satenaw-newsኢሬቻ የታላቁን ኢትዮጵያዊ የኦሮሞ ህዝብ ማንነት በደማቅ ቀለም የሚያንፀባርቅ ባህላዊ የምስጋና ቀን ነው። የወያኔ ካድሬዎች ዛሬ ደርሶ እንደሚሰብኩት ሳይሆን ኢሬቻ በየትኛውም ያለፉት መንግስታት ተስተጓጉሎ አያውቅም። ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሳታፊው ብዛት እየጨመረ መምጣቱ የማይካድ ቢሆንም ኢሬቻ ግን ወያኔ ከመጣ ወዲህ መከበር የጀመረ በአል አይደለም። በቋንቋችሁ እንድትናገሩ ያበቃናችሁ እኛ ነን እያሉ አፌን የፈታሁበትን የኦረምኛ ቋንቋ እነሱ የፈጠሩትን ያህል ሲመፃደቁበት አፍረት የማይሰማቸው ወራዶች ናቸው።

ኢሬቻ እኛ ስልጣን ከያዝን ወዲህ መከበር ጀመረ ብሎ መመፃደቅ አንድም የለየለት ድንቁርና አለበለዚያም ጭልጥ ብሎ ያንድን ህዝብ ታሪክ እና ማንነት እንደማንቋሸሽ ይቆጠራል። የኦሮሞ ህዝብ ኢሬቻን እንዴት ፣ መቼ እና የት እንደሚያከብር ከሌላ ወገን መመሪያም ፈቃድም ጠይቆ አያውቅም። ኢሬቻ ከኦሮሞ ህልውና ጋር የተቆራኘ ፣ የነበረ ፣ ያለ እና የሚኖር የሰከነ የማንነት መግለጫ ባህል ነው።

ፈጣሪ ላደረገለት በጎ ነገር ሁሉ ምስጋና ሊያቀርብ የተሰበሰበ ዜጋ ባህሉ እና ወጉ በሚፈቅደው ረገድ ስርአቱን ካለማንም ጣልቃገብነት ያከናውናል። ፈጣሪን ሲያመሰግን የደረሰበትን በደል ጨምሮ ድምፁን ከፍ አድርጎ በብሶት እንባውን በመርጨት ይገልፃል። ዘንድሮ ምስጋና ለፈጣሪ ለማቅረብ የተሰበሰበው ህዝብ አሁን አገሪቱን ተቆጣጥሮ በሚገኘው ታጣቂ ዘረኛ መንግስት የሚደርስበትን ግፍ እና በዚህ ቅጥ ያጣ በደል የተነሳ ህይወታቸውን የሰዉ ፣ ንብረታቸውን የተዘረፉ እና ወህኒ የተወረወሩ ወገኖቹን ለማሰብ አንድ አፍታ ከምስጋናው መድረክ ጊዜ ቢሻማ ማንንም ሊገርም አይገባም። እነኛ ለእኩልነት ፣ ለሰብአዊ መብት መረጋገጥ እና ለህግ የበላይነት መስፈን ሲሉ መስዋዕት የሆኑ ኦረሞዎች እንዲህ ባለው ታላቅ የምስጋና ቀን ያልተዘከሩ መቼ ሊዘከሩ ነው?

በምስጋና ሰአት እስከ ዛሬ ህዝቡ የተቀበለውን ፍዳ እና ግፍ ከፈጣሪ ፊት ማቅረብ ፣ ፍትህ ፣ ሰላም እና ደህንነት አውርድልን ብሎ መጮህ የተለመደ ጉዳይ ነው። ከዚህ ግፍ ታደገን ፣ ስማዕቶቻችንን ባርክ ፣ የተጎዱትን ፅናት ስጣቸው ብሎ ድምፁን ማሰማት የምስጋናው አካል ነው። የሮሮው እና ጩኸቱ ድምፀት እንደ ብሶቱ ጥልቀት መራራ ሊሆን ይችላል። Down down woyane ብሎ የሚሊየኖች ድምፅ ሲያስተጋባ ይህ ህዝብ እየደረሰበት ባለው ግፍ እና በደል ምን ያህል መማረሩን እና በቁርጠኝነት ግፉን ለማቆም መነሳቱን  ያረጋግጣል። ይኼ ጩኸት የግፍ ክምችት ገንፍሎ ላጥለቀለቀው ህዝብ ፀሎት ጭምር ነው።

ያለንበት ዘመን እጅጉን ተለውጧል – ይህ ትውልድ አባቶቹ ያቆዩለትን በጎ ባህል ሲጠብቅ እና ሲያከብር ዘመኑ በፈቀደለት መንገድ ባህሉን እና ማንነቱን በማስተጋባት ላይ ነው። ለግፈኛ መንግስት አልንበረከክም ብሎ ፅናቱን ለሁሉም ወገን የሚያረጋግጠበት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ማረጋገጥ ይሻል።

 

ኢሬቻ በቅርብ ያለፈውን ዘመን በጥልቅ የሚያስቡበት ፣ አሁን ያሉበትን የሚመረምሩበት እና መጪው ዘመን የተሻለ እንዲሆን የሚመኙበት ብሎም ቃል የሚገቡበት እና ፀሎት የሚያደርሱበት አውደ አመት ነው። በሚሊየን የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጅ ዜጎች አገር አቋርጠው ባንዲት ቢሾፍቱ የተሰበሰቡት በምልአተ ህዝቡ መሰረታዊ ህይወት እና ህልውና ላይ ወያኔ እያደረሰ ያለውን በደል እርግፍ አድርጎ ዘንግቶ አስረሽ ምቺው ለማለት ነው ብሎ የጠበቀ ካለ እራስን ከማታለል የተለየ አይሆንም። በዚህ ረገድ የወያኔ መሪዎች ለህዝብ ያላቸው ግንዛቤ ምን ያህል የተኮላሸ መሆኑን የሚያመለክት ነው ማለት ይቻላል። ተጨባጭ ሁኔታው ከምናባዊ ምኞት እጅጉን ይለያያል። ህዝብ እውነት ነው ፣ ህዝብ ግልፅ ነው ፣ ህዝብ ሀያል ነው ፣ ኢሬቻ የህዝብ ነው።

የዚህ ህዝብ ብሶት እጅግ መራራ ነው። ሰብአዊ ክብሬ ይረጋጋጥ ብሎ በመነሳት ከወያኔ ጋር ግብግብ ከገጠመ አመታት እና ወራት አልፈዋል። ለዚህም ይመስለኛል በዘንድሮው ኢሬቻ በአል ላይ አባ ገዳ የቡራኬ ቃላቸውን አሰምተው ሲያበቁ መድረኩን ለመቆጣጠር ያሰፈሰፈው የወያኔ ባንዳ ተላላኪ ይውረድ ብሎ ህዝቡ የገነፈለው። ለመሆኑ የወያኔ ባንዲራ እና የወያኔ ተላላኪዎች ኢሬቻ መድረክ ላይ ምን አመጣቸው? ከተሰበሰበው ህዝብ ጀርባ ያሰለፉት የአጋዚ ጦር እና ታንክ ፣ አየር ላይ ያንጋጉት የተዋጊ ሄሊኮፕተር ጫጫታ በኢሬቻ ስነ ስርአት ላይ ምን ፍለጋ መጡ? ፀሎት ለማድረስ ቄጠማ ይዞ በተሰበሰበው ምእመን ላይ ‘ተመጣጣኝ እርምጃ’ ለመውሰድ?

ብዙውን ጊዜ እንደምንለው ወያኔ ወራሪ ሀይል ነው ፣ ወያኔ ከጠመንጃ በስተቀር ቅንጣት ህዝባዊ ሽታ የሌለው አረመኔአዊ ድርጅት ነው። የህዝብ ወገን ላለመሆኑ ትልቁ ማስረጃ ደግሞ ኢሬቻ ላይ የወረራ ጦር መሳሪያውን እና ጨፍጫፊ ሰራዊቱን ለግድያ አሰልፎ መገኘቱ ብቻ ነው። ኢሬቻ ቄጠማ እንጂ ታንክ የሚያሰልፉበት ቦታ አይደለም። ወያኔ ሁልጊዜም ቢሆን ለኢሬቻ ባዕድ ነው ፣ ኢሬቻ ሰላም ነው ፤ ወያኔ ገዳይ ነው እናም ከቶውንም አብረው አንድ መድረክ ላይ ሊቆሙ አይችሉም።

ወያኔ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊ እሴቶች ክብር ሰጥቶ አያውቅም። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ህዝቦች የሚኮሩበትን ማንነት ማንቋሸሸ እና ማጥቃት ተግባሩ ነው። እንደ ኢሬቻ አይነት ባንድ መድረክ ላይ ሚሊየኖችን የሚየስተናግድ ባህላዊ ስርአት ብዙም የለም ብል ማጋነን አይመስለኝም። ይኼ ባህላዊ መድረክ ለወያኔ ተፈጥሮ ተስማሚ አይደለም። በጥምቀት እና ደመራ ወይንም ቁልቢ ገብርኤል ምዕመኑ በየአጥቢያው ደጀሰላም ስለሚሳተፍ እንዲህ እንደ ኢሬቻ በላቀ ብዛት በሚሊየን ተሰባስቦ አንድ ቦታ አያከብርም።

ኢሬቻ በምስጋና መንፈስን አድሰው የሚመለሱበት እንጂ በአፋኝ ስርዓት ወጥመድ ውስጥ ወድቀው ህይወትን የሚያጡበት ቦታ አልነበረም። እንደ ወጡ የሚቀሩበት ቦታም አይደለም። ቄጠማ የታቀፈ ምእመን እንጂ ታንክ እና ሄሊኮፕተር የታጠቀ ወራሪ ጦር የሚታደምበት ቦታም አልበረም። ወያኔ ምን ያህል ደመኛ ጠላታችን እንደሆነ ሌላ ተጨማሪ አስረጂ የምንሻ አይመስለኝም።

ወያኔ ባጠመደው እና ባመቻቸው የወረራ ጥቃት ለፀሎት መጥተው ህይወታቸውን ለተነጠቁት ፣ አካል ጉዳት ለደረሰባቸው እና የመንፈስ መረበሽ ሰለባ ለሆኑ ወገኖቼ ሁሉ መፅናናትን እመኛለሁ – ሁላችንም አልቅሰናል።

 

እኛም Down down woyane እንላለን!!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s