የኢህአዴግ መሰነጣጠቅ ወደ አደባባይ ይወጣ ይሆን? * ከአዜብ ቀሚስ ስር ያመለጠው ኦህዴድና የህወሓት ቀጣይ ሴራ * ለገዱ የተደገሰውና ዉዝግቡ

 

የኢህአዴግ መሰነጣጠቅ ወደ አደባባይ ይወጣ ይሆን? 

  • በጥልቀት መታደስ ወይስ በጥልቀት መበስበስ?
  • ከአዜብ ቀሚስ ስር ያመለጠው ኦህዴድና የህወሓት ቀጣይ ሴራ
  • ለገዱ የተደገሰውና ዉዝግቡ

ከመሃዲ ሂርጳሳ

ለ25 ዓመታት ኢትዮጵያን በኢህአዴግ ስም ቀጥቅጦ የገዛው የአውራው ፓርቲ ዘዋሪ ህወሓት ጭንቅ ጥብብ ያለው ይመስላል፡፡ ጭንቀቱ የፈጠረበት መንቆራጠጥ ደግሞ ከጓዳ ወጥቶ ሳሎን ደርሷል፡፡ በዙሪያቸው ሆኖ በንቃት ላስተዋላቸው ሁሉ በግልጽ የሚታይ ህመም ነው፡፡ አንደአካሄዱ በቅርቡ በረንዳ ላይ ቀጥሎም አደባባይ ይወጣል ወይስ ህወሐት እንደለመደችው በሴራዋ ታኮላሸዋለች የሚለው ግን ተራ ጥያቄ አይመስልም፡፡ ለማነኛውም ኢህአዴግ ከውስጥ መሰነጣጠቅ ስለመጀመሩ የታዘብኩትን፣ ከታማኝ ምንጮቼ ያገኘሁትን ጭምጭምታና መላምት ከሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ጋር እያይዤ ነጥብ በነጥብ እንደሚከተለው ላቅርብ፡፡

screen-shot-2016-10-24-at-5-12-52-am

ኦህዴድን ያልተሻገረው ጥልቅ ተሀድሶ

በታሪክ ከታዩ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ቀውሶች ውስጥ ከግንባር ቀደምቶቹ ተርታ የሚሰለፈው የአሁኑ ሀገራዊ ችግር በርካቶችን ስጋት ላይ የጣለና አሳሳቢ ነበር፡፡ ይህን እውነትም መንግስት በተደጋጋሚ በሚሰጣቸው መግለጫዎቹ ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሲገልጻቸው ይደመጣል፡፡ ስርዓቱ የችግሩን ጥልቀት ከማመኑ ጋር ተያይዞም ̎የማስተካከያ እርምጃዎችን እወስዳለው በጥልቅም እታደሳለው̎ ሲል ሙሉ እምነት ባይጣልበትም ሀገሪቱ ላይ ከተከሰተው ችግር አሳሳቢነት አንጻር ግን ተስፋ ያደረጉ ነበሩ፡፡ እውነት ነው ጅማሮው መልካም የሚባልና ፖለቲካውንና ኢህአዴግን በቅርብ ለሚከታተሉ ተስፋ ሰጪ ነበር፡፡ በቀደሙት ጊዜያት ብዙው ሰው ለፖለቲካው ቅርበትም ሆነ መሳብ ስላልነበረው የለውጡን ጅማሮ ሀያልነት መረዳት አይችልም፡፡ ነገር ግን አራቱ ፓርቲዎች በየራሳቸው የጀመሩት ግምገማ ከምንጊዜውም በተሻለ በአንጻራዊነት ከህወሓት ጥርነፋ ነጻ የነበረና ለሚወክሉት ህዝብ በመወገን የተጀመረ ነበር፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው የኦህዴድ እርምጃ ነው፡፡

ፖለቲካውን የሙጥኝ ብሎ ለሚከታተል ሰው በግልጽ እንደሚታወቀው እስካሁን ድረስ ኦህዴድን ሲዘውሩ የነበሩ ሰዎች በተዘዋዋሪ በህወሓት ስውር እጅ ኦሮሚያን ሲያስተዳድሩ ሳይሆን ሲያስመዘብሩ የቆዩ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜም የኦሮሚያን አመራሮች ለማንሳትም ሆነ ለመሾም በተዘዋዋሪም ቢሆን የህወሓት ውሳኔና ምክር በቀጥታ ይወርዳል፡፡ የአሁኑ አዲስ ሹመትም ሆነ የቀደሙትን የማውረድ ውሳኔ በራሱ በኦህዴድ ነጻ ግምገማ የተከናወነ ሲሆን ውሳኔውን አምኖ መቀበል ያቃተው ግን ኦህዴድን በጥርጣሬ የሚመለከተውና የሚተቸው ህዝብ ብቻ ሳይሆን በይበልጥ ህወሓትንና ሌሎች አጋር ፓርቲዎችንም ጭምር ያስደነገጠ ነበር፡፡ በአንድ በኩል በግልጽ የህወሐት ተላላኪ መሆኑ የሚታወቀው የኦህዴድ አንጃ መመታቱ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎችም ድርጅቶች የኦህዴድ አይነቱን ወይም የበለጠውን ውሳኔ እንዲያሳልፉ ጫና መፍጠሩ ነው፡፡

ዝርዝር ጉዳዮችን በቀጣይ ንኡስ ርዕሶች ስር የማነሳቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለአሁኑ የኢህአዴግ ውስጣዊ መሰነጣጠቅ ጅማሮ አንዱና ዋነኛው መንስኤ የኦህዴድ እርምጃና እሱን ተከትሎ የተፈጠሩት ዉዝግቦች ናቸው፡፡

የኦህዴድን ዉሳኔ የበለጠ ቦታ የምንሰጠው ደግሞ አንዳቸውም ይህንን ዉሳኔ የማስተላለፍ ሞራል ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ነው፡፡ የብአዴንና የገዱ አንዳርጋቸው ጉዳይ በተለየ የሚታይና በቀጣይ ርዕሶቼ የማነሳው ይሆናል፡፡ ያም ሆነ ይህ የተጀመረው ̎የተሀድሶ̎ መንገድ አለመቀጠሉ ዛሬም የስርአቱን አለመለወጥ ከመንገር አልፎ ኢህአዴግ በጥልቅ ከመታደስ ይልቅ በጥልቅ ወደመበስበስ ተሸጋግሯል የሚለው አስተሳሰብ ገዢ እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡

ገዱን ከስልጣን የማስወገድ ዱለታ

የኦህዴድ እርምጃ ሁለት ባላ ላይ የተንጠለጠለ ለመሆኑ ከየድርጅቶቹ የሚሰሙት ሹክሹክታዎች ይናገራሉ፡፡ አንዱና ቀደም ብዬ የጠቀስኩት የህወሓት ተናዳጁና የታማኝ ተላላኪዎቹ መመታት ያንገበገበው ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን የኦህዴድን ውሳኔ ፍጹም መቀበል የከበደውና ያልፈለገ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ግን ታማኝ አገልጋዮቹን በኦህዴድ ውስጥ የተነጠቀው ህወሓት በብአዴን ውስጥም ዳግም ላለመነጠቅና የቀድሞ አሰላለፉን መንሻፈፍ ለማስተካከል ሲል የጠላውንና ያስደነገጠውን የኦህዴድ መስመር መከተል የፈለገ ይመስላል፡፡ ነጥብ እስካስቆጠረለት ድረስ ህወሐት የትኛውም አሰላለፍ ውስጥ ለመቆየት የሚቸገር አይመስልም፡፡ እናም ብአዴንም የኦህዴድን መንገድ ተከተለች በሚል እሳቤ የእግር እሳት የሆነባቸውንና ከህዝቡ ጋር የወገኑትን አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ከስልጣናቸው ዘወር ማድረግ ስለመፈለጋቸው ከሹክሹክታ ከፍ ባለ ድምጽ እየተሰማ ነው፡፡

ሁለቱ የኦህዴድ አንጃዎች 

በኦህዴድ ውስጥ ብዙም ያልተሰወረና የኦሮሞ ፖለቲካን በቅርብ የሚከታተሉና የሚያጠኑት ጭምር ደጋግመው ሲሉ እንደሚደመጠው ሁለት አንጃዎች አሉ፡፡ አንደኛው ቡድን ተላላኪና ከመንገድ ላይ ድርጅቱን ተመልምሎ የተቀላቀለ ኦህዴድን በህወሐት ሰንሰለት ጠፍሮ ያከረመው የነአስቴር ማሞ አንጃ ነው፡፡ ሌላኛው ሁለተኛው ቡድን በኦህዴድ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የሚደርስበትን ስልታዊ ጫና ተቋቁሞ በውስጡ የሰነቀውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ብዙ መሰናክሎችን ያለፈውና አሁንም ለማለፍ የተዘጋጀው ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን አሁን ባለው ሁኔታ ሰልጣኑን ይዞታል፡፡ በዚህ ቡድን ላይ የኦህዴድ ካድሬዎችም ሆኑ ብዙ ቁጥር ያላቸው ኦሮሞዎች እምነት እንዳላቸው ከሹመቱ ማግስት ጀምሮ የተለያየ አቋም ያላቸው ጸሀፊዎችና የኦህዴድ ተቺዎች ጭምር ያሰፈሩትን ጽሁፍ አንብበናል፡፡

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በኦሮሚያ ላይ ለተፈጠሩ ማናቸውም ከፍተኛ ችግሮች መንግስትም አምኖ ሽምግልና የሚልካቸው፣ ህዝቡም የክልሉ ፕሬዝዳንቶች እያሉ ከዚህኛው ቡድን ካልሆነ ሌላ ሰው ድርሽ እንዳይልብን ማለታቸው በራሱ አንዳች የሚያስረዳን ሚስጥር አለው፡፡ እርግጥ ነው በዚህ ቡድን ውስጥ ያሉ አመራሮች ለህዝቡ ወገንተኝነት ያለውን አስተያየት በመንግስት መገናኛ ብዙሀንም ሆነ ለስርዓቱ በወገኑ ሚዲያዎች ላይ ጭምር ሲሰነዝሩ አስተውለናል፡፡ ለምሳሌ ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ የመጀመሪያውና ወዲያው ጋብ ብሎ የነበረው ተቃዉሞ ተቀስቅሶ ህዝቡና የጸጥታ ሀይሉ በተጋጨበት ወቅት ይሄኛው ወገን ነበር ብቅ ብሎ ህዝቡ ያነሳው ጥያቄ ተገቢና ተቃዉሞውን ማሰማት መብቱ እንደሆነ አስረግጠው የተናገሩት፡፡

የኢሬቻው ሀዘንና መላምቶቹ

እጅግ ልብ ሰባሪ አሳዛኝ ህልፈት የደረሰበት የመስከረም 22ቱ የኢሬቻ በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ በቦታው የተገኙ የዉጭ መገናኛ ብዙሀንን ጨምሮ መንግስትም የሞቱ መንስኤ መረጋገጥ ነው ሲሉ ሌላኛው ወገን ደግሞ የለም ከወታደሮች በተተኮሰ ጥይት ነው ግፍ የተፈፀመው ሲሉ አምርረው መንግስትን ይወነጅላሉ፡፡  ከዚህ በተለየ ግን እውነታው እስኪረጋገጥ ድረስ በመላምት ደረጃ የሚሰነዘር አንድ ነጥብ አለ፡፡ ይህ መላምት በኦህዴድ ውስጥ ከነበረው የጎራ መለያየት ጋር በተያያዘ የሚሰነዘርና ኦህዴድ እራሱ እስካሁንም የተገለጠለት የማይመስለው ጉዳይ ነው፡፡ ይኽውም  የቢሾፍቱው ሞት በመጨፈላለቅ ብቻ ያልደረሰና ይልቅም  የቀድሞው የኦህዴድ አመራሮች በህወኃት ፊትአውራሪነት አዲሱን አመራር ለማስወገዝ የተዶለተ ነው የሚል ነው፡፡ በዳያስፖራው ላይ ያነጣጠረና ለፖለቲካው ጡዘት ሲባል  ደም እንዲገበር የዳያስፖራው ክንፍ ከጥግ ቆሞና ሆን ብሎ ያራገበው ነው የሚለው የሌሎች ወገኖች መላምትም እንዳለ ሆኖ፡፡

opdo

ከአዜብ ቀሚስ ስር ያመለጠው ኦህዴድ

በኦህዴድ ሁለቱ አንጃዎች ላይ ያለን መረጃና መሬት ላይ ያለው እውነታ ፍጹም የተራራቁ ናቸው፡፡ በነአስቴር ጎራ ስላለው ሙሰኝነትና ዘረፋ ብዙ አንሰማም፡፡ ለፓርቲው አመራሮች ቅርብ ከሆኑ ሰዎች የሚሰማው ተጨባጭ እውነታ ግን ፍጹም ተቃራኒና የሚያስደነግጥ ነው፡፡ የነ አስቴር ጎራ በግሉ ብቻ አይደለም የሚዘርፈው፡፡በቡድንም ጭምር እንጂ የሚያዘርፈው፡፡ በአዜብ መስፍን ፊትአውራሪነት ኦሮሚያ ላይ በህወኃት ቡድኖች ለሚደረገው የሀብት ዝርፊያ ዋነኛዋ ተወካይና አመቻች አስቴር ማሞና ግብረአበሮቻቸው ነበሩ፡፡ በተዘዋዋሪም የመለስ ህወሓት ብቻ ሳይሆን ኦህዴድም እስካሁን ድረስ በአዜብ ቀሚስ ስር ነበር፡፡ አሁን ግን የአዜብና አስቴር ፍቅር መሞጃሞጃው መጨረሻው የደረሰ ይመስላል፡፡ ምንም እንኳን ከውስጥ ሰዎች ሾልኮ እንደሚሰማው አዜብ መስፍን በኦሮሚያ ላይ ለማካሂደው ዝርፊያና ግልቢያ ቀኝ እጄ የሆነችው አስቴር ተቆርጣለችና ቀጥሉልኝ በማለት ዳግም መፍጨርጨር ብትጀምርም፡፡

የሆነው ሆኖ ዋናው ጉዳይ በመግቢያዬ ላይ የነካካኋቸው ሁለት ጉዳዮች መሰረታዊ ናቸው፡፡ አንዱ በይፋ ኢህአዴግ ተሰነጣጥቆ ገመናው አደባባይ ላይ ይወጣል ወይስ በውስጣቸው ተጀምሮ የነበረውን ለውጥ አምነው ይቀበላሉ? ወይስ ደግሞ ህወሐት እንደለመደችው የትግሉን አቅጣጫ አስቀይሳ ለውጡን ታዳፍነዋለች? ይህንን ግን ጊዜው የሚፈቅድላቸው አይመሰልም፡፡ ይህ ከሆነ ምናልባትም የኢህአዴግን መሰነጣጠቅ አደባባይ አስጥቶት የፓርቲውን ግብዓተ መሬት ያፋጥነው ይሆናል፡፡

የብአዴን ምክትል ሊቀመንበርና የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

እመኑኝ አይለወጥም

አሁን ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት እዚህም እዛም ያለውን ከፍተኛ ቀውስ እንዲሁም በየድርጅቱ ውስጥ የሚደረገውን ለውጥና ጠንካራ ግምገማ ተከትሎ ኢህአዴግ ይለወጣል ወይ የሚለው ነው፡፡ ከሁነኛ የመረጃ ምንጮች እንደሚሰማው ከሆነ፣ ከኋላ ሆነው ስርዓቱን የሚዘውሩት የህወሕት ጉምቱ ባለስልጣናት በኦህዴድ አዲሱ አመራርና አጋሮቻቸው ላይ ጥርሳቸውን ነክሰዋል፡፡ በክልል ላይ አሽከሮቻቸው ለተወሰደባቸው የበላይነት እነሱ ደግሞ በተቃራኒው በፌዴራል ደረጃ ተጽዕኖ ለመፍጠርና ከሚኒስትርነት ጭምር ለማግለል ተግተው እየሰሩ ነው፡፡ ምናልባትም ከተሳካላቸው ጥቂት የማይባሉ የኦህዴድ ጠንካራ አመራሮችን ከሚኒስትርነት ያስወግዳሉ ማለት ነው፡፡ እርምጃውንም ጠንካራውንና ወጣቱን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በማንሳት ጀምረውታል፡፡

ሌላው ከብአዴን፣ በተለይም ደግሞ ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው፡፡ ህወሕት በአቶ ገዱ ላይ ተስፋ ከቆረጠች ቆየ፡፡ ነገር ግን እሳቸውን ከስልጣን ቆርጦ መጣሉ ቀላል የሆነላቸው አይመስልም፡፡ በኦህዴድ አመራሮች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ወደመስማማት የመድረሳቸውን ያህል በአቶ ገዱ ጉዳይ ግን ለሁለት ተከፍለዋል፡፡ አንደኛው ወገን አባረን ወይም አነስ ያለ ስልጣን በመስጠት የሚመጣውን እንይ ሲል፣ ሌላኛው ቡድን ግን ትንሽ ጊዜ ሰጥተን ዉሳኔውን በሂደት ብናየው ይሻላል የሚል ነው፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s