በጎሳ ትግል ወያኔ አይወድቅም፤ ቢወድቅም ውጤቱ አያምርም (ከመሳፍንት ዘፈረንሳይ ለጋሲዮን)

ከመሳፍንት ዘፈረንሳይ ለጋሲዮን
tmesafint@gmail.com

በኦሮሚያ ተቀጣጥሎ ወደተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ለተዛመተው ሰላማዊ የፍትህ ይገባኛል ጥያቄ የግድያና የእስራት ምላሽ እየሰጠ ያለውና በቅርቡም ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የእምነት ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙሃንና ዲፕሎማቶች ሳይቀሩ የመብት እንጥፍጣፊ እንዳይኖራቸው “በባርነት አዋጁ” የደነገገው የወያኔ ስርዐት ለሩብ ምዕተ ዓመት ሲሰራ የቆያውንና አሁንም እየሰራ ያለውን ሁሉ ያስተዋለ በሀገራችን የተከሰተውን ስር የሰደደ የፖለቲካ ቀውስ መረዳት አያዳግተውም።The Green, Yellow and Red Ethiopian flag in Gondar

ይህ የጥቂት ሽፍቶች ስርዐት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ በሚዳክርበትና ሀገራችንን ወደለየለት የጥፋት ጎዳና በፍጥነት እየጋለበ ባለበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት ኢትዩዽያችን ከልጆቿ የምትጠብቀው አስተውሎት የተሞላበት እርምጃ ብቻ ነው። ሀላፊነት የሚሰማውና ለሀገር ተቆርቋሪ የሆነ ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዞ በፅናት በገዢው ቡድን ላይ የሚደረገውን ጫና ማጠናከርና ለወደፊቷ ኢትዩዽያ የሚበጀውን በማሰናዳት ስራ ላይ መጠመድ አለበት። በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች እየሆነ የምናያውም ይህንኑ ነው።

ይሁን እንጂ ምስኪኑ ኢትዩዽያዊ ሀገሩን ከሰው በላው መንጋጋ ለማላቀቅ ክቡር ህይወቱን እየከፈለና ከወገኑ ጋር ወንድማማችነቱን በደሙ ማህተም እያረጋገጠ ባለበት በዚህ ወቅት ከየአቅጣጫው በመሰማት ላይ ያሉ ጎሳ ተኮር የአደረጃጀትና የትግል ቅስቀሳዎች እጅግ አሳሳቢና አስፈሪ ናቸው። ኢትዩዽያ ውስጥ በወያኔ የግፍ በትር ያልተገረፈ፤ ሰብዐዊ መብቱ ያልተደፈጠጠ፤ ወንድም፣ እህት፣ ወላጅ፣ ዘመድ አልያም ጓደኛው በግፍ ያልታሰረበትና ያልተገደለበት እንዲሁም ሀብት ንብረቱን ያልተዘረፈ የህብረተሰብ ክፍል ፈልጎ ማግኘት ከቶ አይታሰብም። ይህንን ወደር የለሽ ግፍና በደል ጎሳ ተኮር አድርጎ መቀስቀስና ማራገብ ከባድ አደጋ ያጭራል። ይህን ዓይነት ኋላቀር፣ ጠባብ፣ ኃይልን የሚበታትን፣ የጊዜዉን ነባራዊ ሁኔታ ፈፅሞ ያላገናዘበና የሀገራችንን ችግር የማይፈታ የትግል ስልት ገዢው ቡድን ሕዝብን በመጨፍጨፉ እንዲተጋና ስልጣኑንም እንዲያራዝም ይሁንታ ከመስጠት አልፎ የሀገርንና የሕዝብን አንድነትና ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ነው።

ሰፊው ኢትዩዽያዊ የሚያሰማው ጩኸትና የሚያካሂደው ትግል አንዳንድ የፖለቲካ ልሂቃን በሚያራግቧቸው ሸውራራ መልዕክቶች ሊቀለበሱ አይገባም። ጎሳ ጎሳ የምትለውን ጨዋታ ብቻ መጫወት የሚመርጡ ልሂቃን ለሩብ ምዕተ ዓመት በወያኔ ጥላቻንና መለያየትን ሲሰበክ የኖረው ህዝብ ከሚያሳየው የአንድነት መንፈስና ትግል ለመማር ቢሞክሩ መልካም ነበር።

አሁን ላይ ሆነን ሊያሳስበንና ሊያወያየን የሚገባው ጉዳይ የእንጀራ ገመዱ በፍጥነት እያጠረ የሚገኘው ይህ ስርዐት ከተወገደ በኋላ ስለምንረከባት ኢትዩዽያ እጣ ፈንታ እንጂ ተለያይተን ስለምንበታትናት ሀገር መሆን የለበትም። ሀገራችንንና ሕዝቧን ሊመጣ ከሚችለው ጥፋት ለማዳን የጎሳ ተኮሩ አስተሳሰብ በኢትዮጵያዊነት መንፈስና በጋራ ዓላማ መተካት አለበት። በጎሳ አሰላለፍ ወያኔን ታግሎ መጣልና ኢትዩዽያን ከጥፋት ማዳን ፈፅሞ አይቻልም። ይህ ወቅት የተጣመሩትን ኢትዩዽያውያን እጆች ይዘን ሩቅ ለመጓዝ የምናልምበት ነው። ወያኔ የዘመተው በኢትዩዽያውያን ሁሉ ላይ እንደመሆኑ ልንዘምትበት የሚገባው ኢትዩዽያውያን ሆነን ነው። ዘረኛው ስርዐት የተከለብንን የዘረኝነት መርዝ ነቅለን እስካልጣልን ድረስ ይህ አገዛዝ በጭራሽ አይወድቅም፤ ቢወድቅም ውጤቱ አያምርም።

አምላክ ኢትዩጵያችንን ይጠብቅ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s