ነጭ በሬ ሆኜ ቆሜልሃለሁ እና ጨፉጭፈኝ! – ደመቀ ገሰሰ የኔአየሁ (PhD)

 

Ethiopiaእንደሚታወቀው ህወዓት ፋሺስት ጣሊያን አያቱ ሊፈፅም አቅዶ ያልተሳካለትን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ፕሮጀክት በ1983ዓም ይዞ ብቅ በማለት ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ከፋፉሎ ለመግዛት በብሄር ተከፋፉሎ የተሰራውን የፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያ ካርታ ከወዳደቀበት ፉርስራሽ አቧራውን አራግፎ አያቱ ጀምሮ ያልተሳካለትን ኢትዮጵያን የማፉረስ አጀንዳውን ይዞ ብቅ በማለት አንቀፅ 39 የሚባል እስከመገንጠል መብት በህገ-መንግስቱ ውስጥ በማስቀመጥ የአያቱን ፋሺስት ጣሊያን ፕሮጀክት ከዳር ለማድረስ አልሞ እና አቅዶ መነሳቱ ይታወሳል።

ፉሺስት ጣሊያን ለከፋፉለህ ግዛው ፕሮጀክቱ ትልቅ ደንቀራ ሆኖ የገጠመው ሃይል ቢኖር በአገሩ እና በሃይማኖቱ ድርድር የማያውቀው የአማራው ነገድ ነበር። ፋሺስት ጣሊያን እኛ የመጣነው የአውሮፓን ስልጣኔ እና ጥበብ ልናስተምራቹህ ነው እያሉ በመደስኮር ነበር። ይህ ዲስኩር ገና ምእራባውያን እራቁታቸውን በጢሻ ሲኖሩ የአለም ስልጣኔ ቀንዲል የሆነ ህዝብ መሆኑን እና ይህን ዲስኩርህን አይገባኝም ብሎ አሻፈረኝ ያለው የአማራው ነገድ በጣሊያኖች እይታ “ይህ የማይገባው መንቻካ ህዝብ አህያ ነገር ነው” ሲሉ ማጥላላታቸውን ተያያዙት። በተቃራኒ ከፋሺስት ጣሊያን ጋር የወገኑ እና በባርነታቸው ውስጥ የገባውን ባንዳ ወይም አስካሪ ደግሞ “እናንተ ትምህርት ቶሎ የሚገባቹህ ስልጡን ህዝብ ናቹህ” እያሉ የሰሜን ዘመዶቻችንን ማቆላመጡን ተያያዙት።

“ስልጣኔ አልገባው ያለው” የአማራ ችኮ ህዝብ ግን በአገሩ እና በማተቡ ቀልድ የለም ብሎ በሚያመልከው አምላኩ ምሎ እና ተገዝቶ ወራሪው ፋሺስት ጣሊያንን አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ሊያደባያቸው መላው የኢትዮጵያን ህዝብ ከዳር እስከዳር በማስተባበር ባርነትን ሊጭኑብን የመጡትን ባእዳን በአድዋ ተራሮች ስር አጥንቱን ከስክሶ እና ደሙን አፉስሶ አፈርድሜ በማስጋጥ ሃያልነቱን እና አልበገር ባይነቱን አሳያቸው።

የአማራው ህዝብ ኢትዮጵያ ሃገራችንን ባህር አቋርጠው የመጡትን ባእዳን ሁሉ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ እያስተባበረ እና ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር እየተባበረ ይቺን አገር ለዚህ ትውልድ ዋጋ ከፉሎ ያቆየ ህዝብ ነው። የአማራው ህዝብ በታሪኩ አንድም ቀን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ተለይቶ ብቻውን በመቆም የተዋጋው የውጭ ወራሪ ሃይል አልነበረም። የልቁንም እኒህ አርቀው የነገውን ያስቡ የነበሩት ቅደመ-አያቶቻችን በተናጠል የሚደረግ ትግል ውጤታማ እና ዘላቂ ትብብርን የማያመጣ እንደሆነ በመረዳታቸው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እያስተባበሩ ነበር ዳርድንበራቸውን ሲቆጣጠሩ የኖሩት።

በርካታ ጊዜ አገራችንን ቅኝ ለመያዝ የቋመጡት ፋሺስት ጣሊያንን በመመከት ዛሬ ላይ በአለም ህዝብ ዘንድ አንገታችንን ቀና ብለን እንድንሄድ አኩሪ ታሪክ ሰርተውልን አልፈዋል። በአደዋ ላይ አይቀጡ ቅጣት ቀምሶ የተመለሰው ጣሊያን ተመልሶ በሁለተኛው የአለም ጦርነት መባቻ ላይ አገራችንን ሲወር ከአደዋው ጦርነት እጅግ በተሻለ ዘምነው በሰማይ እየበረሩ እኛ ግን አሁንም የነበረንን እንደያዝን በመውዜር እና በአጋሰስ ብቻ ገጠምናቸው። ይህ የነበረው የትጥቅ አለመመጣጠን እንደማያዋጣን አብዝተው የተገነዘቡት አያቶቻችን ትልቁን ዲፕሎማሲ በመስራት እንግሊዝ ከጎናችን እንድትሰልፉ እና ለዳግም ድል እንድንበቃ አድርገውናል።

ይህን ታሪክ ወደኋላ ሂደን እንድናስታውስ አስፈላጊ የሆነበትም ምክንያት ዛሬ ላይ አማራው ምን ማድረግ እንዳለበት ለማስታወስ ነው። ህወዓት የትግራይን ሪፕብሊክ ለመመስረት አቅዶ ትግሉን ቢጀምርም እድል ቀንቶት የደርግን መንግስት ከሻብያ ጋር ተባብሮ እንደሚጥለው ሲገባው መገንጠሉ እንደማይጠቅመው በመረዳት ኢህዴግ የሚባል የድርጅቶች ስብስብ በመፉጠር ኢትዮጵያዊ መስሎ ከች አለ። ወያኔ ያኔ በለሱ እንደቀናው ትግራይን ገንጥሎ ቢሄድ ኖሮ ምን ሊደርስበት ይችል እንደነበር ለማወቅ ነብይ መሆን አያስፈልግም። የልቁንም ይህ ችግር የገባቸው ህወዓቶች ኢትዮጵያን ጌታቸው ፋሺስት ጣሊያን ለከፋፍለህ ግዛው አላማ ፈጥሮት የነበረውን የብሄር ካርታ አቧራውን አራግፎ አገሪቱን በብሄር ከፋፉሎ እየው እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያዊ ካባ ለብሶ ሁሉንም ብሄሮች ለራሳቸው የውስጥ ባንዳ የሚሆኗቸውን የየብሄሩ ተወላጆች በፓርቲ ስም በማዋቀር እየገዙ ይገኛሉ። እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ህወዓት 25ዓመት ሲገዛ ብቻውን በህወዓት ስም አይደለም። የልቁንም ብሄር ብሄረሰባችን መብት አስከብሬአለሁ በማለት የሁሉንም ዘውጎች ተወካዮች በመያዝ ነው። ብአዴን፣ደህዴን፣ኦህዴድ እና መሰል የብሄር ተቀፅላ ፓርቲወችን ከጎኑ በማሰለፉ ነው።

ህወዓት አሁን የሚደረገውን የነፃነት ትግል ለማፈን የቀረበው ህወዓት ብቻ ሆኖ አይደለም። የልቁንም አብዛኛው የመከላከያ እና ፓሊስ ሰራዊት ከትግራይ ውጭ በሆኑ ሌሎች ኢትዮጵውያን አደራጅቶ የመሪነቱን ቦታ ደግሞ ለሚያምናቸው የትግራይ ሰወች በመስጠት ነው እየወጋን ያለው። ህወዓት ብቻውን ከኢትዮጵያውያን ጋር የሚዋጋ ቢሆን ኖሮ ይህን ያህል ዋጋ ባልተከፈለ ነበር። እውነታው ግን ይህ አይደለም። ይህ ማለት ወያኔ ኢትዮጵያውያንን ይዞ ሲወጋን ወያኔን ልናሸንፉ የምንችለው እንደ ኦነግ ወይም የብሄር ድርጅቶችን በማዋቀር በብሄርህ ብቻ ስትደራጅ ሊሆን አይችልም። ከ25 ዓመት በላይ የአገሪቱን ጠቅላላ ሃብት በበላይነት በመቆጣጠር እና በስመ ፀረ-ሽብር አጋርነት ከምእራባውያን በሚደረግለት ልገሳ እና ስልጠና የፈረጠመን ሃይል እና ሌላውን ኢዮዬጵያውያን ይዞ በኢትዮጵያ ደረጃ ሲገጥመን እኛ አማራ ነፃ አውጪ ድርጅት፣ ኦሮሞ ነፃ አውጭ ድርጅት፣ወዘት እያልን በብሄር ጠበን ስንወርድለት የበለጠ ነጭ በሬ ሆነን ህዝባችንን ኑና ጨፉጭፉልን ከማለት ያለፈ ትርፉ ሊኖረው አይችልም። ትላንት ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር የአገራችንን ዳር ድንበር ከጠላት ሲከላከል የነበረው ትልቁ የአማራ ነገድ ወያኔ በፈጠረለት የብሄር ቋት እንሶ በመደራጀት አማራውን ነፃ ሊያወጣ የሚችልበት ምድር ላይ ያለ እውነታ አይደለም። ይህ ዝም ብሎ ሳያሰላስሉ እና ኢትዮጵያ የተሰራችበትን የታሪክ ምህዳር ሳያገናዝቡ፣የቀጠናውን ጂኦ ፓለቲካል አሰላለፉ ምን እንደሆነ ሳያስተውሉ እና ወያኔ አሁንም በኢትዮጵያ ካባ ስር ሌላውን ኢትዮጵያዊ አስተባብሮ እየወጋህ እያለ አንተ ከነበረህ የታሪክ ደረጃ ወርደህ በአማራነት ስትደራጅለት ለወያኔ ድግስ እና ምላሽ ሆንክለት ማለት ነው። እንዲያውም ይኽውልህ እያለ የበለጠ ከሌላው ጋር ያላትምህ ይሰራል እንጂ እንዲህ በቀላሉ ሽር የሚባልበት መንገድ አይመስልም።

በአማራ ብሄርተኝነት ስም እንደራጅ ብለው የሚያስቡ ቡድኖች ሃሳባቸው ትክክል ሃኖ ሳለ አሁን ላለንበት እውነታ ውጤታማነቱ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ወያኔ እና ሻብያ ብሄር ተኮር አጀንዳ ይዘው ሲታገሉ ድል የቀናቸው ትልቁ ምክንያት በዘመኑ የነበረው የቀዝቃዛው ጦርነት ትልቅ አስተዋዖ ነበረው። ዛሬ ላይ የጎረቢት አገሮች ሳይቀር በወያኔ ቀኝ እጅ ውሥጥ ባሉበት በአሁኑ ወቅት፣ በፀረ-ሽብር ምክንያት ህወዓት-ኢህዴግ ከምእራባውያን ሃያላን ጋር እጅ እና ጓንት ሆኖ እየሰራ ባለበት ወቅት፣ እራሱ ወያኔ ኢትዮጵያዊ ካባ ለብሶ እየታገለን ባልንበት በዚህ ሰዓት እንደ አማራ ነፃ አውጭነት፣እንደ ኦሮሞ ነፃ አውጭነት ወዘተ ሆነን ዳር ልንደርስ አንችልም። እያየነው ያለውም ሃቅ ይህ ነው። በብሄር ተደራጅቶ ሊሳካ የሚችል ቢሆን ኖሮ ኦነግ ከ40ዓመት በላይ ሚሊዮን ኣሮሞወችን ነጭ በሬ ሆኖ በመቆም ለእልቂት ዳረገ እንጂ ያተረፈው ትርፉ የለም። አማራውም የተለየ ሊሆን አይችልም ።ቅደመ አያቶቻችን ጠላትን በህብረት ተፋልመው አሸነፉት እንጂ በተናጠል አልሄዱም።

ዛሬ ላይ የተለየ እውነታ የለም። የልቁንም ዛሬ ላይ ወያኔ ያልገደልው እና ያላሰቃየው ህዝብ የለም። ሁሉም ህዝቦች የወያኔ ጭካኔ ደርሶባቸዋል። የኦሮሞው ወጣቶች አብዬት እና የአማራ ህዝብ ተጋድሎ እያሳየን ያለው ነገር ቢኖር ወያኔን ዘረኛ ቡድን አድርጎ በያሉበት እየተፋለሙት ይገኛሉ። ወያኔ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያዊ ካባ የተጀቦነበት ካብ እየተናደ ተነጥሎ እየተመታ ነው። ይህ ሃቅ ሆኖ ሳለ ልክ እንደ ቅድመ-አያቶቻችን ተባብረን በአንድ ላይ ለፉትህ እና እኩልነት መታገል በእኔ እይታ ብቸኛ አዋጪ መንገድ ይመስለኛል። ነገር ግን የአለምን የፓለቲካ ሚዛን ሳይመረምሩ፣ምድር ላይ ያለውን ሃቅ ሳይመለከቱ በኢሞሽን ብቻ በመነዳት የአማራ ብሄርተኝነት የአማራውን ችግር ይፈታል የሚል እምነት የለኝም። የልቁንም በወያኔ ክፉ በትር የተጎዱ እና እየተጎዱ ያሉትን ሌሎች ወገኖቻችን ጋር በመተባበር ፉትህ የሰፈነባት ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት መታገል አውጭው መንገድ ነው።

እስኪ አስቡት ወያኔወች ኢትዮጵያ ሆነው ሲገጥሙን በምን መስፈርት ነው አማራ በአማራነት ሆነን ልንገጥማቸው ያሰብን? እናም እናስተውል! የአንድ ድርጅት ስኬት የሚለካው ይዞት የተነሳው አላማው አዋጪነቱ(feasibility) ሲኖረው ነው። ለሚደረገው ትግል የአለም አቀፉ የትብብር ድጋፉ ሊያገኝ መቻል አለበት። የጎረቢት አገሮች ሚና ተለይቶ መታየት አለበት። የአማራው ስነ-ልቦና መታወቅ አለበት። እውነት ለመናገር ይህ በአማራነት ብቻ ተደራጅቶ የአማራንም ህዝብ ሆነ ኢትዮጵያን ነፃ ማውጣት የሚቻል እንኳ ቢሆን እጅግ እረጅም አመታትን የሚፈጅ እና ኪሳራውም የከፋ ነው የሚሆነው።

ይህን ስል አማራው መደራጀት የለበትም እያልኩ አለመሆኔ ሊሰመርበት ይገባል። አማራው አሁን እያደረገ ያለውን ተጋድሎ ተቀናጅቶ መቀጠል ይኖርበታል። ነገር ግን የአማራ ነፃ አውጭ ብሎ እራስን ነጭ በሬ አድርጎ ለጥቃት ማጋለጥ ሳይሆን እንደ ቅድመ አያቶቻችን ሌሎችን ብሄሮች ተባብሮ እና አስተባብሮ ወያኔ ነጥሎ ለመምታት ሲቻል ብቻ ነው። ወያኔ በህብረ-ብሄራዊ ጭንብል ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሲገጥመን እኛ ወርደን አማራ ሆነን ልንገጥመው ማሰብ ለወያኔ የሞራል ልእልና ካርድን መሸጥ ብቻ ሳይሆን በራሳችን ወገን ሳይቀር ወያኔ አስተባብሮ ልክ በኦነግ እና ኦብነግ ላይ ያደረሰውን የጭካኔ በትር በእኛ ላይ እንዲዘምትብን ነጭ በሬ መሆን ነው።

አንድ አማራውን የሚወክል ፓለቲካል ፓርቲም ቢኖር መላክም እንጂ ችግሩ አይታየኝም። አንድ ጠንካራ የአማራ ፓለቲካ ፓርቲ ካለ ለሽግግር መንግስትም ሆነ በዘላቂነት የአማራውን ፉላጎት እና ጥቅም የሚያስከብር ፓርቲ ሊኖር ይገባል። በእኔ እይታ የአማራውን ህዝብ ችግር እና ትግል የሚዘክር እና የአድቮኬሲ ስራ የሚሰሩ እንደ ሞረሽ-ወገኔ አይነት ድርጅቶችን ማጠናከር፣ ህዝባችን ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ጋር ሆኖ የሚያደርገውን ተጋድሎ መርዳት እና ማገዝ ወቅቱ የሚፈልገው አዋጪ መንገድ እንደሆነ አስባለሁ።

ቸር ይግጠመን!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ከህዝቦቿ ጋር በክብር ትኑር!

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s