የአራት ፖለቲካ ፓርቲዎችን ስብሰባና ስምምነት በሚመለከት ያቀርብኳቸው መሰረታዊ አስተያየቶች

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

አስተያየቶችና ጥያቄዎች

ይህን ስብሰባ ከሌሎች የሚለየው ምንድን ነው?

የመጀመሪያውና ዋናው ኢትዮጵያን እንደ ታሪካዊና ዘላቂ አገር መቀበሉና ይህች አገር እንዳትበታተንና ለጥቃት እንዳትጋለጥ ከስምምነት ላይ መደረሱ ነው። በስብሰባው ላይ ያሳሰብኩትና ያሰመርኩበት የማምነበትና የምመራበት አቋም “ኢትዮጵያ ለድርድር አትቀርብም” የሚል ነው። ይህች አገር ብዙ መስዋእት ተከፍሎባት በልጆቿ ቆራጥነትና ህብረት ነጻነቷን፤ ብሄራዊ ግዛቷን፤ ክብሯንና ሉዐልዊነቷን አስከብራ ቆይታለች። ይህ የሚያኮራ ታሪክ ስኬታማ ሊሆን የቻለው በቋንቋ፤ በባህል፤ በብሄር፤ በስነልቦና፤ በተፈጥሮ ኃብት፤ በታሪክና በሌሎች መለያዎች ሳይበከል ኢትዮጵያ ተብላ በምትጠራ እውቅና ባላት አገር የሚኖረው ሕዝብ ሁሉ የታገለላትና የሞተላት፤ የአውሮፓ አገሮች ከመመስረታቸው በፊት የራሷ ስልጣኔ እና መንግሥት የነበራት አገር መሆኗ ነው። ይህ አኩሪ ታሪክ የአንድ ብሄር ወይንም የአንድ ኃይማኖት ጥረት ወይንም መታወቂያ አይደለም። ህወሓቶችና አጋሮቻቸው እንደሚሉትም የመቶ ዓመት ታሪክ ብቻ ያላት አገርም አይደለችም። በስርዓት ልዩነት የተነሳ ይኼን የዓለም ጥቁር ሕዝብ ሁሉ የሚኮራበትን ታሪክ መካድ ራስን ወይንም እወክለዋለሁ የሚሉትን ሕዝብ ዝቅ ማድረግ ነው። ራስን ዝቅ ማድረግ ደሞ ለተጠቂነት ያጋልጣል። የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች የሚፈልጉትም ይኼን ነው። ጠባብ ብሄርተኞቹ ህወሓቶች ባጠመዱት ወጥመድ ገብቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጎጥ፤ በብሄር፤ በኃይማኖት፤ በጥቅም ወዘተርፈ ተከፋፍሎ አቅጣጫ መቀየስ የሚጠቅመው ለሁለት ኃይሎች ነው፤Dr. Aklog Birara

አንድ፤  ለህወሓቶችና ለሚቆጣጠሯቸው ልሂቃንና የጥቅም ነጋዴዎች፤

ሁለት፤ ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ ለሚመኙ የውጭ ኃይሎች።

ይህ ከሆነ ማንም በኢትዮጵያ የሚኖር ብሄር ሊጠቀም አይችልም። አገራችን የነገዋ ሶማሊያ ወይንም ሶሪያ ወይንም ደቡብ ሱዳን ትሆናለች። የእርስ በርስ እልቂት አይቀርም። ይኼን የሚመኝ ግለሰብ ወይንም ቡድን ጤናማ አይደለም ለማለት ያስደፍራል። በሎንዶን የተካሄደው የኦሮሞው ውይይት “አደገኛና ሃላፊነት የጎደለው ነው” የሚሉት የኦሮሞና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ትችት አግባብ የሚኖረው ለዚህ ነው። “በኢትዮጵያ መቃብር ወይንም መፈራረስ” ላይ አዲስ አገር እንመሰርታለን የሚሉ፤ በምሁራን ስም የጥላቻ መርዝ የሚረጩ ግለሰቦች ያሳዩት ነገር ቢኖር እውቀትንና ሞያን ሳይሆን፤ ድንቁርናን ነው ለማለት ይቻላል። ሊክ እንደሌላው አገር ወዳድ፤ ታላቁ የኦሮሞ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ነጻነት፤ ግዛታዊ አንድነንትና ሉዐላዊነት የከፈለው መስዋት ለኢትዮጵያ ዘላቂነት መሰረት መሆኑን አስመስክሯል። ይህ ታላቅ ሕዝብ፤ ልክ እንደ ጎንደሬውና ሌላው ኢትዮጵያዊ “ዋርካ” ነው ለማለት ያስደፍራል። የጎንደር ከተማ ዋርካ ዛፍነቱ ብቻ ሳይሆን ምሳሌነቱ በአአምሮየ ተቀርጾ ይኖራል። ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንካራ ነው። ዋርካ ቦታውን አይለቅም። ታላቅ ሕዝብም ከራሱ ሸሽቶ አይገነጠልም። መሰረታዊ የሆኑ የስርዓት ችግሮችን ከሌላው ጋር ተባብሮ አማራጮችና መፍትሄዎች የመስጠት ኃላፊነት አለበት። የተቃዋሚዎችን ህብረት እና አንድነት የማየው ከዚህ ዋርካን የመሰለ መሰረት ከመጣሉ አንጻር ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሸቀጥ የማንም ንብረት አይደለችም። ለድርድር አትቀርብም የምለው ለዚህ ነው። ስብስቡ በዚህ መርህ ዙሪያ ስምምነት ያሳየ ይመስለኛል። ይህ በኢትዮጵያ ዘላቂነት ለምናምን ሁሉ ተስፋ የሚሰጥ ሂደት ነው።

በስብሰባው ላይ ያቀርብኳቸውን መሰረተ ሃሳቦች በአጭሩ ለማቅረብ፤

“አንድ፤ ትግሉ የሚካሄደው በአገር ቤት ነው፤ በውጭ አይደለም። የአሁኑን ሕዝባዊ ዐመጽ ከበፊቱ የሚለየው ሕዝቡ በምሬት ተቀስቅሶ ተቃውሞውን ራሱ የሚመራው፤ የራሱ የጎበዝ አለቃዎች ያሉት፤ የራሱ ወጣት ትውልድ የሚሞትለት፤ የሚገረፍበት፤ የሚቆስልበት፤ የሚታሰርበት፤ የሚታገልለትና ስርዓቱ መለወጥ አለበት የሚልበት መሆኑ ነው። ይህ ለአድር ባዮች አያመችም። በእኔ ግምት እና እምነት ወጣቱ ትውልድ የሚፈልገውና የሚመኘው ጥገናዊ ለውጥ አይደለም፤ መሰረታዊ የስርዓት ለውጥ ነው። በዛሬው ስብሰባ ካስደሰቱኝ ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋናው የወጣቱ ተሳታፊ ብዛት ነው። ወጣቱ በገፍ መገኘቱን እናመስግን። ወደፊትም እንዲሳተፍና እንዲመራ ቅስቀሳ አናድርግ። ይህ ወጣት ትውልድ በአገር ቤት የሚታገለውን ወጣት ትውልድ ያንጸባርቃል።

ሁለት፤ ከልጅነቴ ጀምሮ የማስታውሰው ብሂል አለ። በኢትዮጵያ ችግሮች ሲከሰቱ “ጎንደር ምን አለ?” ይባል ነበር። አሁን “ጎንደር ምን አለ?” የሚለውን ጥያቄ በማያሻ መንገድ መልሶታል። “ግፍ በቃኝ አለ” የሚል ሰብሳቢ አባባል ይመልሰዋል። በአማራው ክልል (ጎንደር፤ ደብረ ታቦር፤ አርማጭሆ፤ ወልቃይት ጠገዴ፤ ባህር ዳር፤ ደብረማርቆስ፤ ወሎና ሌላ) የሚታገለውና መስዋእት የሚሆነው ወጣቱ ነው። እኛ አይደለንም። በኦሮሚያና በኮንሶ የሚታገለውና የሚሞተው ወጣቱ ትውልድ ነው። እኛ አይደለንም። “የኦሮሞው ደም ደማችን ነው፤ የጎደሬው/አማራው ደም ደማችን ነው” የሚለው የሁለቱ ታላቅ ብሄሮች ወጣት ትውልድ ብሂል ተመሳሳይና ተደጋጋፊ ነው። ወጣቱን ትውልድ “በዚህ ስብሰባ ላይ የተገኙት ሆኑ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች አያዙትም። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቋንቋውንም፤ ምኞቱንም፤ ፍላጎቱንም የሚያውቁት አይመስለኝም። እነሱ የኖሩትን ኑሮ፤ እነሱ የደረሰባቸውን በደል፤ ግፍ፤ አፈናና ሌላ እኛ አናውቀውም። በአብዛኛው፤ በፖለቲካ አመራር ውስጥ የሚገኙት በእኔ የእድሜ ክልል ውስጥ ናቸው። ወጣቱ ትውልድ ከእኔ ትውልድ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። በማህበራዊ መገናኛ (ትዊተር፤ ፌስ ቡክ፤ ዩቱብ ወዘተ) የሚያደርገው ትግል ከእኔ ትውልድ የተለየ ነው። ደፋር ነው። ፍርሃት የሚባል ነገር አያውቅም። የሚሰራው አካደሚክ አይደለም። እኛ የምናየው ከትንተና አንጻር ነው። ወጣቱ ትውልድ የሚያው በመሬት ላይ ካለ ብሶት፤ ጭንቀት፤ ትግል፤ ተስፋ አንጻር ነው።  ወጣቱ ትውልድ በመሬት ላይ ያለውን ግፍ የሚያንጸባርቅ ነው። የእኔ ትውልድ ስብሰባዎች ይህን ግዙፍ ኃይል አላሳተፉትም፤ ለማስተማር አልሞከርነም፤ ለመሪነት አላዘጋጀነውም። ስለሆነም፤ ከዚህ ትውልድ ብንማር ይሻላል። ምን እንደሚፈልግ፤ ምን እንደሚመኝ፤ ለምን እንደሚታገል፤ ለምን ራሱን መስዋእት እንደሚያደርግ እንጠይቀው። እናውቅልሃለን የሚለውን ቅዠት እንርሳው።

ሶስት፤ እኔ የምጠይቀው፤ እናንተ (በዚህ የተሰበሰባችሁት አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች) ከዚህ ሰባ በመቶ የሚገመት ግዙፍ ወጣት ትውልድ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ያህል ነው? ይህን ጥያቄ እንድታስቡበት አደራ እላለሁ። ወጣቱን ትውልድ ያልያዘ ድርድር የትም አይደርስም። ያላማከረ ራሱን ለጥያቄ ያጋልጣል። ከዚህ ጋር አጣምሬ የምጠይቀው በመሬት ላይ የሚሞተውና የሚታገለው ወጣት ትውልድ እናንተ ማንን ወክላችሁ ድርድር ታደርጋላችሁ ብሎ ቢጠይቅ ምን መልስ ትሰጡታላችሁ? አገር ቤት ያሉትስ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ሚና ምን ይሆናል?

አራት፤ በዚህ ስብሰባ ሌሎች እንደተናገሩት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት የእያንዳንዱ ኢትዮጵዊ ክብር፤ ነጻነት፤ ሰብአዊ መብት፤ እውነተኛ እኩልነት፤ የትም ቦታ የመኖር፤ የግል ኃብት የመያዝ፤ የመምረጥ፤ የመመረጥና ሌሎች መብቶች በሕግ ሲከበሩ ነው። አንዱ አዛዢ ሌላው ታዛዢ፤ አንዱ በልቶ አዳሪ ሌላው ረሃብተኛ ወዘተ የሆነችበት ኢትዮጵያ ለማንም አትበጅም። የስርዓት ለውጥ አስፈላጊ ነው የምለው ይኼን ነው።

አምስት፤ በእኔ ግምት ይህ ስብሰባ መልካም ጅምር መሆኑን ብቀበልም፤ ከጅምርነት በላይ አይሄድም። ሌሎችን አግባብ ያላቸውን፤ በኢትዮጵያ ዘላቂነት ዙሪያ የተሰበሰቡ ድርጅቶችን አላካተተም። ስለዚህ፤ ይህ ጅምር ሌሎችን ማካተት አለበት።፡ሁሉን አቀፍ የሆነ ጉባኤ መካሄድ አለበት። በየቦታው ለአማራጭ የሚደረገው የተናጠል እሩጫ ወደ አንድ መአከል መምጣት አለበት። በዚህ በኩል ሻለቃ ዳዊትና ፕሮፌሰር ጌታቸው ያደረጋችሁት ጥርት በጣም ጥሩ ነው። አስፋፉት፤ ማንንም አትተው፤ ሁላችንም እንተባበር። እያንዳንዳችን የመተባበር፤ አብሮ የመስራት አምባሳደሮች እንሁን!

ስድስት፤ በሕዝብ ላይ፤ በተለይ በወጣቱ ላይ የሚካሄደው ጭፍጨፋ ይዘገንናል። የአስቸኳዩ አዋጁ ኢላማያደረጋቸው ሁለት ግዙፍ ብሄሮች አሉ፤

  • አማራው በዐማራነቱ፤ በማንነቱ፤ በመሬቱ፤ በህልውናው፤
  • ኦሮሞው በማንነቱ፤ በመብቱና በመሬቱ።

የእነዚህ ብሄሮች ጠበቃ የሆነው ወጣት ትውልድ በገፍ እየተገደለና እየተሰቃየ ነው። እነዚህ ብሄሮች ኢላማ ከሆኑ የህወሓት አገዛዝ ከማንኛውም እርምጃ፤ የስልጣን ድርድርን ጨምሮ፤ በፊት ከሕዝቡ ጋር መታረቅ አለበት ማለት ነው። ምክንያቱም፤ ህወሓት የተጣላው ከእናንተ ጋር አይደለም። የተጣላው ከሕዝቡ ጋር ነው። ከእናነት ጋር ተጣላሁ፤ ከውጭ ጠላቶች ጋር ተጣላሁ፤ ከኢሳት ጋር ተጣላሁ፤ ከኦሮሞ መገናኛ መረብ ጋር ተጣላሁ ወዘተ፤ የሚለው የዓለምን ሕዝብ ለማሳሳት ነው። ሰላም እንዲወርድ ከፈለገ ግድያውንና አፈናውን ማቆም አለበት ማለት ነው።

እናንተን የምጠይቀው አንድ ነገር አለ። ይኼውም ይህን ፈቅዶ ያደርጋል የሚል ግምትና እምነት አላችሁ? ይህን አስተማማኝ በሆነ ደረጃ ለማወቅ ከተፈለገ መረጃውን ከወጣቱ ትውልድ ሰብስባችሁ እንደሆነ ብታስተምሩን ይጠቅማል።

ሰባት፤ እኔ የ1991 የስልጣን ሽግግር እንዳይደገም አስጠንቅቃለሁ። ይህ ሽግግር የዐማራውን ሕዝብ እና ሕብረ ብሄር የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አላሳተፈም።

ውጤቱ የህወሓት የበላይነት መሆኑን አይተናል። በዚህ ስብሰባም የዐማራው ሕዝብ አልተወከለም። በዐማራው ሕዝብ ስም የተናገረው ግለሰብ ዐማራውን አይወክለውም። “አልወክልም ማለቱ” አግባብ አለው። ካልወከለ በዚህ ስብሰባ ላይ እንደ ተናጋሪ መቅረቡ የተሳሳተ መልእክት እንዳይሰጥ እሰጋለሁ። አንሳሳት፤ በዚህ ስብሰባ ላይ የተገኙ ድርጅቶች ዐማራውን አይወክሉትም። በእኔ እምነት ይህ አደገኛ ሂደት ነው። ማንኛውም ሽግግር ዐማራውን ማሳተፍ ግዴታው ነው። የዐማራው አለመወከልና አለመሳተፍ በመሬት ላይ የሚካሄደውን እልቂትና ትግል አያንፀባርቅም። በጎንደር፤ በወልቃይት ጠገዴ፤ በአርማጭሆ፤ በመላው ጎጃም ወዘተ፤ የሚካሄደው ሕዝባዊ አመጽና እልቂት ሃቅ ነው። በተመሳሳይ በገፍ የሚገደለውና እየታሰረ የሚወሰድበት ቦታ የማይታወቀው ወጣት ትውልድ ብዛት ሃቅ ነው። በእናንተ ግምት ይሕ ችግር እንዴት ይፈታል ትላላችሁ?

ስምንት፤ በመጨረሻ ለማቅረብ የምፈልገው፤ የዛሬው ስብሰባና ስምምነት ጥሩ ቢሆንም በዚህ ድርድር ያልገቡት በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ ነጻነትና ሉዐላዊነት፤ በሕዝቧ እውነተኛ እኩልነትና ዲሞክራሳዊ መብት የሚያምኑት እንዴት ባለ ሂደት እንዲሳተፉ ታደርጋላችሁ?

በእኔ ግምት ሁሉን አቀፍ የሆነ የፖለቲካ፤ የማህበረሰብና የታወቁ ግለሰቦች ስብሰባና ወደ ብሄራዊ ቃል ኪዳን የሚያመራ ውይይትና ድርድር መካሄድ አለበት። ይህ ከሆነ ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ለመደራደር እድሉ ከፍ ይላል።

በዚህ ስብሰባ ሃሳቤን እንዳቀርብ ስለተጋበዝኩ ምስጋናየ ከፍ ያለ ነው። “የኢትዮጵያ አገራዊ (በእኔ እምነት ብሄራዊ ቢባል ይሻላል) ንቅናቄ” የሚል መርህ ይዞ መታገል እድሎችን ይከፍትልናል የሚል ግምት አለኝ።

በመጨረሻ ከላይ በመግቢያው እንደተናገርኩት ወዳጀ ዶር ዲማ ኦሮሞኛ ቢያስተምረኝ ኖሮ ደስ ባለኝ ነበር። ሁለቱን ቋንቋዎች የሚናገሩ ወገኖቸ ያስቀኑኛል። ቋንቋን ማወቅ ለመቀራረብ፤ ለመማር፤ ለመተማመን፤ ለመከባበር፤ ወዘተ ይጠቅማል። እኛ እንግሊዝኛ ስለምንችል ነው በአሜሪካ የተሳካ ኑሮ የምንኖረው።

አመሰግናለሁ”

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s