ከእጅ አይሻል ዶማ!

 

ዶማ አባጣ ጎባጣ የሆነውን መሬት ለመደልደልና ለማስተካከል፣ መንገድና የእርሻ መስኖ ለመቅደድ፣ለተለያዩ ግንባታ ስራዎች ለማመቻቸት የሚረዳ፣ ስር የሰደደን አረም ከሥሩ ነቅሎ ለመጣል፣በእጅ ሊያሶግዱት የማይችሉትን እሾህ አሜኬላ ጎልጉለው ሊያሶግዱበት የሚችሉበት አጋዥ መሳሪያ ነው።ታዲያ ዶማ ብዙ አዳጋች ስራ ለመስራት የሚጠበቅበት ሲሆን ፣ያንን ለማሟላት ደግሞ የተዘጋጀ፣ስለት ያለው፣ችግሩን ከመሰረቱ ተነቅሎ እንዲጠፋና ዳግመኛ እንዳይከሰት ለማድረግ ብቃት ያለው መሆን ይገባዋል።ብቃት በሌለው ዶማ የሚፈለገውን አከናውናለሁ ቢሉ በባዶ እጅ ከሚሰሩት የተሻለ ውጤት ስለማይመጣ ልፋት ብቻ ይሆናል፤ዶማውም ከእጅ የተሻለ ስራ አይሰራም።

26-2699-rxrud00z
እንደዚያ ያለው ዋጋቢስ ዶማ ከሸክም በስተቀር የሚሰጠው ጥቅም የለም።ከእጅ የማይሻል ዶማ ነው። በዚህም አኳያ የሚታይ ብዙ ስራዎችና ተግባሮችን ለማከናወን የሚረዱ መሳሪያዎችና ዘዴዎች አሉ።የእነሱም ለተገቢው ስራ ብቃት አለመኖር እንደ ዶማው ውጤተቢስ ሆነው ይቀራሉ። በዶማው ቦታ የቤተሰብን፣የህብረተሰብን፣የአገርን፣ችግርና እንቅፋት፣እንዲሁም ቅራኔ ለማሶገድ የምንገለገልባቸው ዘዴና መሳሪያዎች አሉ።ሽማግሌና ድርጅት ዋናዎቹ ናቸው። እርቅ ለማውረድ የተሰየመ ሽማግሌ ችሎታና ብቃት ከሌለው ልዩነቱን ይበልጥ ያከረውና ፣በተለኮሰው ጠብ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ ከባሰ ቀውስና አለመግባባት ውስጥ ይከታል።በተመሳሳይም በአገር ደረጃ በህብረተሰቡ መካከል ለሚነሳ የፖለቲካም ሆነ ማህበራዊ ችግርና ጥያቄ መልስና መፍትሄ ለማምጣት ታስቦ የሚቋቋም ድርጅት፣አሰራሩና አደረጃጀቱ ከችግር ፈጣሪው አካል የማይለይ ከሆነ ያለውን ችግር በተመሳሳይ መልክ የሚያስቀጥል፣ አስቸጋሪውን አካል ተክቶ በተራው የሚያስቸግር ይሆናል።የዚህ አይነቱ አደረጃጀትና አሰራር ከላይ እንደታየው ጥቅመ ቢስ ዶማ የሚመሳሰል ነው።ለማህበረሰቡ፣ለአገር ጥያቄና ችግር መፍትሔ የማያመጣ ከንቱና የጥፋት ዓላማ ተከታይ ይሆናል። በአገራችን በኢትዮጵያ ያለው ችግር መንስኤው በጎሳ የተደራጁ ዘረኞች ያሰፈኑት ስርዓት ነው።ስርዓቱን ለማስፈን ከዚያና ከዚህ ተጠራርተው በመሰባሰብ ጦር ገጥመው የነበረውን የወታደር አምባገነን በሃይል አሸንፈው በፈረንጆች እርዳታና አቀነባባሪነት ስልጣኑን የጨበጡ ቡድኖች ናቸው።በሕዝቡ ፍላጎትና ምርጫ የተመረጡ ባለመሆናቸው የሕዝቡን ፍላጎት ለመመለስ አልቻሉም።ይበልጥ አገሪቱንና ሕዝቡን እስረኛና የግል ንብረት አድርገው የፈለጉትን እየፈጸሙ ለሃያ አምስት ዓመት የኖሩ ወንጀለኞች ናቸው።የነሱ ውጤት አሁን አገሪቱን ከመበታተንና ሕዝቡን እርስ በርስ ከመተላለቅ አደጋ ጠርዝ ላይ አድርሷል። በስልጣን ላይ ያለውን ቡድን በመቃወም በተመሳሳይ መልክ ና ለተመሳሳይ ዓላማ የቆመ የተሻለና ለአገሪቱና ለሕዝቡ የተለዬ ፍቅርና አክብሮት አለው ማለት አይደለም።የእሱም ዓላማና ፍላጎቱ ተመሳሳይ የዘር ፖለቲካ ማራመድ ነው።የዘር ፖለቲካ ደግሞ ውጤቱ ያው ተመልሶ ሕዝቡን ማተራመስና አገሪቱን መገነጣጠል ይሆናል። ሰሞኑን በአሜሪካ ዋና ከተማ በዋሽንግተን ሜሪላንድ በተባለው ቦታ አገር ወዳድና፣መሰረታዊ የዴሞክራሲ ለውጥ የሚሹ ኢትዮጵያንን በማግለል በተወሰኑ የጎሳ ድርጅቶች መካከል የተደረገው ስምምነት ወያኔ ከሃያአምስት ዓመት በፊት ካካሄደው አይለይም። የኦሮሞ፣የአፋር፣የሲዳማ በማለት የተደራጁት የጎሳ ድርጅቶች ድንኳን ውስጥ ግንቦት ሰባት የሚባለው ድርጅት መሰግሰጉና እንደመሪ መቀመጡ ሂደቱንና ውጤቱን የተለዬ አያደርገውም።እንደውም የጎሰኞች መሳሪያና በአዲስ አቀራረብ አገሪቱንና ሕዝቡን ለባሰ አደጋ የሚዳርግ ነው። በአገሪቱ ውስጥና ውጭ ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ስርዓት መስፈን የሚንቀሳቀሱና የሚታገሉ ድርጅቶች ባልተሳተፉበትና በተለይም በአገራችን በኢትዮጵያ የልዩነትና የግጭት ምክንያት የሆነውን የዘር አጀንዳ ይዞ መነሳት ወያኔና አበሮቹ ቡድን ከሚከተለው የተለዬ አያደርገውም። ስለሆነም ከእጅ እንደማይሻለው እንደ እርባና ቢሱ ዶማ ከወያኔ የማይሻል ስብስብ ነው።የጎሰኞቹ ዓላማ እንደሚታወቀው የወያኔ ሕገመንግሥት ያጸደቀውን በተግባር ለመተርጎም ነው።ተቃውሟቸውም ለምን በተግባር አልተተረጎመም ነው።የግንቦት ሰባት ዓላማ ግን በግልጽ ባይታወቅም በተግባር ግን አቋሜ ከምሰበስባቸው አይለይም ያለ ይመስላል።ከብሔር አቀፍ ድርጅቶች ይልቅ የጎሳ ድርጅቶችን መምረጥ
2 ሌላ ምን ትርጉም አለው?የጎሳ ፖለቲካ አገር ሲንድ እየታዬ ለተመሳሳይ ጉዞ አብሮ መሰለፍ ከቶ ለምን ጥቅም ይሆን? የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል እንዲሉ ይህ የተጀመረው አካሄድ ካለው ችግር የሚያወጣን አይሆንም።እውነት ለዴሞክራቲክ ስርዓት ለውጥና ለኢትዮጵያ አንድነት የተነሱ ቢሆን ኖሮ በተለያዬ ባንዲራ ስርና በተለያዬ የጎሳ ድርጅት ስም በጠረጴዛ ላይ ተደርድረው ከመፈራረም ይልቅ ሌሎችንም ባካተተ መልኩ በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ስር በኢትዮጵያዊነት የኩራት መንፈስ የጋራ መግለጫ ባወጡና ባወጁ ነበር።ያንን ለማስተካከልና ሕዝቡ የሚሻውን ነገር ለማድረግ አሁንም ጊዜው አልመሸም። በጣም የሚያስገርመው ደግሞ ስብስቡን አቀነባበርን የሚሉት ጥላ ካቢኔ(shadow cabinet)አባላት ቀደም ሲል ለአሜሪካ መንግሥት ባቀረቡት የእወቁልን የሽግግር ሰነድ አንቀጽ 39 የተባለውን አፍራሽ አንቀጽ ያካተተ የወያኔ ሕገመንግሥት ሳይለወጥ እንደሚያገለግል የሚገልጽ ነበር።አሁን በስብስቡ እንደተነገረው ከሆነ ግን አዲስ ሕገመንግሥት እንደሚረቅ ተደርጎ ነው። ግን በአገር አፍራሹ አንቀጽ 39 ላይ ያላቸውን አቋም ይፋ አላደረጉም።ለአገር አንድነት የሚያስቡ ቢሆን ኖሮ ይህንን አደገኛ አንቀጽ በይፋ አውግዘው መግለጫ ባወጡ ነበር። ወጣም ወረደ በጎሳ የሚነደፍ ሕገመንግሥት የጎሰኞችን ጥቅምና ፍላጎት የሚያስከብር ይሆናል እንጂ ለተባበረች፣ አንድነቷ ለተጠበቀ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሊሆን እንደማይችል ካየነው መማር እንችላለን። አሁን ደግሞ በፌስቡክና በሌሎቹም የዜና አውታሮች የሚሰራጨው በሚመጣው ሳምንት በኖቬምበር 10 2016 በቤልጅዬም ዋና ከተማ ብራሰልስ ውስጥ በሚገኘው የአውሮፓ ፓርላማ (በአና ጎሜዝ አዘጋጅነት ሊሆን ይችላል) በብራዚል ኦሎምፒክስ የማራቶኑ ውድድር የብር መዳሊያ ባለቤት የሆነው ፈይሳ ለሊሳ፣ የኦሮሞ ፍዴራል ፓርቲ ሊቀመንበር መረራ ጉዴናና የግንቦት ሰባቱ ብርሃኑ ነጋ እንደተጋበዙ የሚገልጽ ነው።ተጋባዦቹ የፖለቲካ ድርጅቶች እስከ አሁን ድረስ በተደጋጋሚ በየቦታው ተመርጠው በመጋበዛቸው ከመፈንደቅ ውጭ ኢትዮጵያን የምንወክለው እኛ ብቻ አይደለንም፣ሌሎችም ስላሉ ይጋበዙ ብለው አያውቁም።እንዲህ አይነቱ የአውሮፓውያኑና የአሜሪካኖች የመከፋፈል ስልት ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ታይቷል።አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር ተነስቶ በሚፋለምበትና ብዙ የሕይወት ዋጋ በሚከፍልበት ወቅት ነጥሎ ማቅረብና ማራቅ ለምን አስፈለገ ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው።ይህ የሚያሳየው አሁንም አውሮፓውያን ከፋፍለው አገራችንን በመዳፋቸው ስር ለማድረግ እንደማይቦዝኑ ነው። ይበልጥ ትኩረት የሰጡት ለኦሮሞው ጥያቄ ነው። ሌላው ቀርቶ በስደተኛ ጥያቄ ላይ እንኳን ፈጣን የመኖሪያ ፈቃድና እርዳታ የሚሰጡት በኢትዮጵያዊነቱ ለሚቀርበው ሳይሆን በኦሮሞነትና በኤርትራዊነት ለሚቀርበው ስደተኛ ነው።እዚህ ላይ ወገኖቻችን ለምን አገኙ የሚል አሳብ እንደሌለል ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ።ማንኛውም ሰው በአገሩ መቀመጥ ሳይችል ቀርቶ ቢሰደድ ክብሩና መብቱ መጠበቅ አለበት ባይ ነኝ።የምቃወመው እየነጠሉ ማስተናገዱን ብቻ ነው።ለምን እንደሚያደርጉትም እናውቀዋለን። ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ በነጮች የቅኝ አገዛዝ ስርዓት ላይ ያደረሰችው ጥቃት ላለሙት ዘረፋ አመቺ ባለመሆኑ የታሪክ ቂም በመቋጠራቸው በመከፋፈል በቀል ለመወጣት የሚሸርቡት ተንኮል ነው።በአሁኑም ጊዜ በወያኔ ፈቃድ በብዛት የንግድና የምርት እንቅስቃሴ የሚካሄደው በኦሮሞው አካባቢ በመሆኑ ሲሆን የተፈጥሮ ሃብትና ማእድንም በሰፊው ይገኝበታል ከሚለው የዝርፊያ ስትራቴጂ አንጻር በመነሳት ነው።ለዚህም ወጣቱ በአገሩ ላይ እየኖረ ስለአገሩ እንዳይታገል ሃይሉን ለማመንመን ከማሰብ የሩቅ ጊዜ ስሌትም እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። አዛኝ ቅቤ አንጓች እንዲሉ! ይህ ምኞታቸው ግን በተባበረ ኢትዮጵያዊ አገር ወዳድ አንድነት ይከሽፋል፣ምኞታቸውም ላም አለኝ በሰማይ ሆኖ ይቀራል። አገር ወዳዱ፣የአንድነትና የዴሞክራሲ ሃይሉ ከጎሰኞች ጠብ የሚልለት መልካም ውጤት እንደማይኖር ተረድቶ በውስጡ ያለውን ጥቃቅን ልዩነት አሶግዶ አገሩንና ሕዝቡን ከተመሳሳይ አደጋ ለማዳን አንድ ሆኖ መሰባሰብ አለበት።ተለያይቶ እየተነታረኩ መኖር ወይም እኔ ካልመራሁት እያሉ መፎካከር የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል ሆኖ ለተደራጀ ዘራፊ ዕድል መስጠት ነው።ወይም በሰሞኑ የብልጣ ብልጦች ድራማ ተጃጅሎ መቀመጥ በአንገት ላይ ማነቆ ማጥለቅ ነው።የአንድነት ሃይሉ “አገርህን አድን” በሚለው የጋራ መርሆ በአዲስ መልክ ተደራጅቶ በአንድ የጋራ አመራር ስር መታገል ይኖርበታል።በተለመደው አካሄድ መቀጠል ድካም ብቻ ነው፤ከእጅ አይሻል ዶማ!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
አገሬ አዲስ

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s