የህልውና ልዕልና በእንቢተኝነት ልቅና የሥህናዊ – ታሪክ ገናና [ሥርጉተ ሥላሴ]

„ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም።“

( ወደ ቆረንቶስ ፩ኛቱ ምዕራፍ ፲ ከቁጥር  ፳፫ እስከ ፳፬)

ከሥርጉተ ሥላሴ  26.11.2016  (ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ)

sirgute
ከሥርጉተ ሥላሴ

ስታቀርበው ያቀርብኃል። ስታርቀው ያርቅኃል። ስታከብረው ያከብርኃል። ስታቃለው – ይነፍግኃል። መርህ ኑሮን ሲያስተዳድር፤ መኖርን ልብን  ይመራል። ህሊናን ደግሞ ሚዛን። ጤነኛ መንፈስን ደግሞ የመኖር ሉዑል – ፍቅራዊነት። በመኖር ውስጥ ሰብዕናን ማክበር የመሰለ ምራቁን የዋጠ የርትህ አመክንዮ የለም።

ጠራጠሮ

ያ …“ባዶ“ … ሳይመክን ዳግም መጣብኝ።ስለሆነም አጥንቴን ርህራሄ ባልሰራለት ፋስተርትሮት በምልሰት በቁስለት ሰቀቀን –በመጎዳትትህትና ልቃኘው ወደድኩኝ። ባይደገም ምንኛመልካም በሆነ ነበር። ግንስ ሆነ። እይተናነቀኝልሂድበት …

እንዲህም ሆነ …

ቀኑ ዕለተ ቅዳሜ ነበር ኢትዮዽውያን በወገናቸው የሰብዕዊ መብት አያያዝ ጉዳይ የሚመክሩበት ብሩክ ማዕልት። እኔም ወገኖቼ ስለ እኛነታችን በወልዮሽ ወደ እምንታደምበት ስብሰባ ለመገኘት ወስኜ ስለነበር ቀደም ብዬ ተገኘሁ። ከ 100  እስከ 120 የምንሆን ታዳሚዎች ነበርን። በአጋጣሚ ወንድሜ ስላልተመቸው እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ከወንድሜ ጋር ነበር ዘና እያልን ረጅሙን መንገድ መጪ የምንለው። ወይንም ከቤተሰብ ከአንዱ ጋር። እንደ ዛሬው ውርጭ ሳይደቃኝ። ያን ቀን ግን ጉዞው በተማላ ነበር። ሁሎችም አልቻሉም ነበር። የሆነ ሆኖ ክቡር እንግዳችን መጡ። ከመቀመጫችን ተነስተን በአክብሮት ተቀበልናቸው። ለእኔ በግሌ አጋይሥት- ዓለሙ ሥላሴ በአካል የተገኙ ነበር የመሰለኝ። ሳያቸው እጅግ ደስ አለኝ። የለበስኩት በነጭና በቡኒ የተሠራ የወላይታ ብሄረሰብ ባህላዊ ልብስ ሥለ-ነበር የሳቸውም ልብ እንዳአቀረበኝ አስተውዬበታለሁ። የነበርነው ሴቶች ጥቂቶች ከመሆናችን በላይ ኢትዮጵያዊነት ጠረን ያለው ባህላዊ ልብስ የለበስኩ እኔ ብቻ ነበርኩኝ።

የክብር እንግዳችን የተከበሩ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ነበሩ። ያን ጊዜ የኢሰመጉ ሊቀመንበር ነበሩ። የምናውቅ ቀደም ብለን ብናውቅም፤ እንደ አሁኑ የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት ገመናው አደባባይ ያልወጣ ስለነበር፤ በኢትዮጵያ የደረሰውን የሰባዕዊ መብት ረገጣ ሲገልጡ ታዳሚው በተመስጦ ያዳምጥ ነበር ። የነበረው ጸጥታ ወፍ ለቅማ ትወጣ ነበር። በዚህ ማህል ነው ደፍረስ የሚያደርግ ነገር ፕሮፌሰሩ የቀላቀሉት። አይቼ ሳልጠግባቸው፤ አዳምጬም ሳልጠግባቸው፤ ከአንድ ታላቅ ሙህርና የሀገር ሃብት፤ ለዛውም ሰውን ማዕከሉ አድርጎ መከራን ለመቀበል ከወሰነ፤ እኔ በግሌ እንደ ቅዱስ ሐዋርያ ከቆጠርኩት ዕውቀት – ጠገብ፤ ልምድ – ጠገብ የድርጊት አባወራ፤ ዱብ ዕዳ ነበር የሆነብኝ። እንዴት እንዳገናኙት አላውቅም። በኋላ ላይ ስንሰማ ሌላ ቦታ ሃሳቡን አንስተው የመይሳው ልጅ መልስ እንደሰጠችበት ሰማን። ከሰነዘሩት በትንሹ „አንድ ጠብራራ ጎንደሬ ተማሪ ነበረኝ። ጎንደሬዎችን ታውቋቸው ዬለ፤ ጉረኞች በሌላቸው ላይ የሚኮፈሱ … ባዶዎች፤ ቀጠሉ … ቀጠሉ … ትምህርቱን ለመቀጠል ከእኔ የሚፈልገው የምስክርነት መረጃ ነበር። መረጃውን ሰጠሁት። ካሰበው የትምህርት እርከንም ተሳክቶለት ደረሰ።“ ወዘተ … ዞር ብዬ ተመለከትኩ። አድማጬ ከስሜታቸው ጋር ምን ያህል እንደተጋባ ማረጋገጥ ነበረብኝ። የተናጋሪው የደም ትርታን አድማጩ አልሸመተውም ነበር። በተቀራኒው ከእኔ በባሰ ሁኔታ ገጻቸው ደምኗል። ያው ከስብሰባ ስንወጣ ዝም ብለን አንወጣም። በወገን ህዝባዊ ስብሰባ አይዋ ባይታዋርነት ስላልነበረ፤ የምርጥ ዜግነት ባለ ልዩ ባልድርሻነት ጭምምታውም ስላልነበር ቤተኝነታችን እኩል ነበርና የተለመደውን አድርሰን በፍቅር ተለያዬን።

ጉዞዬን በሙሉ ሲገልጡ የነበራቸው የሰውነታቸው እንቅስቃሴ፤ የድምጽ ምቱ፤ እዬተመላለሰ አወከኝ። የዕውነት ውስጤ ተቆርጦ እንደ ሰነበተ ጎመን ጥውልግ ነበር። በሳቸው ጻዕዳ መንፈስ ውስጥ እኔ ባይታዋር ነኝና። እንዳይደረስ የለም ቤት ስደርስ ወንድሜ ቡናው አፍልቶ እንዳስቀመጠው በረንዳ ላይ ለሽ ብሏል። የእንቅልፍ ዲታ ነው። የደላህ ብዬ ቀስቅሼ ትንሽ ከተጫወትን በኋላ እሱ ወደ ቤቱ በሰላም ሄደ። ድፍርስ ስሜት ይዞ ቢሾፍር ዕዳ ነበረው። የጎንደር ነገር አይሆንለትም። ጎንደር ለእሱ ሊቀ – ንግሥቱ ናትና። መልስ አለመስጠቴን ካወቀ ፍጥጫውን ማን ችሎት። ብቻ ዋጥ አደረኳት እንደ ካፌኖል። ምኔ ሞኝ …

በማግስቱ ስብሰባ ያልተገኙ ጎንደሬዎች በስልክ አጣደፋኝ። „ለምን ከዚያው ላይ መልስ አልሰጠሻቸውም ነበር?“ „ሪፖርቱን ልትሰሪው ነው?“ አዎን። „ምን ብለሽ?“ የአዳመጥኩትን ሳይሆን ያዬሁትን። ልንግባባ አልቻልነም። ምክንያቱም የተሳታፊዎችን ተሳትፎ መግለፁ ነፃነት ለራበው ምልዐት የወገን ተስፋ ነው፤ ሌላው ደግሞ የድርጅቴን ክብር መጠበቅ ነበረብኝ። ስለ እኔ ምሥክርነት የሰጡት አለቆቼንም በምንም ነገርና ሁኔታ አለማሳዘን፤ ከልጅነት እስከ እውቀት ስለ እኔ ምስክርነት ለሰጠ አካል አለማሰፈር እጅግ የማከብረው መርሄ ነው። ከሁሉ በላይ ጎንደር ለግራጫ ጸጉር ልዩ አክብሮት ስላለው „መንገድ ስታቋርጡ ታላቆችን አስቀድሙ“ እዬተባልን ነው ያደግነው፤ በተጨማሪም ልቤን የሸለምኩት ሙያዬ፤ ያደኩበትን ማህበረሰብ ጨዋ ሥነ – ምግባርና የኢትዮጵን ተስፋ መተላለፍን አልፈቀድኩትም ነበር። እንጂ የሳቸው ንግግር እዛው አዳራሽ የሚቀር፤ የእኔ ግን ዓለም የሚያዳምጠው ነበር። ዘገባዎቼ ደግሞ ጉልበታም ናቸው። መንፈስን የመግዛት አቅሙም እንዲሁ። አዬር ላይ ሞገዱ ስብርብር የማድረግ አቅም ነበረው። ግን እኔ ህመሜን ተጋፍቼ፤ ትእግስትን ከእዮብ ሸምቼ፤ የኢሰመጉን ዓላማ ያከበረ ዘገባ አቀረብኩ። ክቡርነታቸውንም የቀደሰ። እግዚአብሄር ይመስገን፤ እንዲሁም „በመርህ ይከበር“ የአንድነት ፓርቲ ችግር ውስጥ የፊት ለፊት ተሟጋች ነበርኩ። ከቂመኞች ማህበር ያልዘነቀኝ አምላክ አሁንም ይመስገን።

አሁን ወደ ቀደመው እንደ አቨው … አንድ ሰውን ማዕከሉ ያደረገ የሰብዕዊ መብት ተቋም መሥራችና ተሟጋች ከሀገሩ ልጆች ውስጥ በልቦናው የተፋቀ ማህበረሰብ መኖሩን ለሚያገናዝብ ማንኛውም ፍጡር፤ ይህን ወጣገብ ዕይታ ቢያደምጥ፤ ህዝበ ውሳኔው ከባድ ይሆን ነበር። ይህ የሃቅ ማህደር ጎንደሬ መሆን ሳይሆን እንደ ሰው ማሰብን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። የተከበሩት ፕሮፌሰር መስፍን  በደንበሩ ጉዳይ ላይ ያላቸው ዬተባደግ ዕይታም ጎንደርን በመንፈስ ከማግለል የመጣ ነው። ሚስጢሩ ይሄነው፤ የፋሲል ፈረሱ ስናር ሱዳን ላይ ይታሰር እንደነበር ሊቀ – ሊቃውንቱ ዝክረ ታሪካችን አስተምረውናል። አሁን ሰሞኑን በጻፋት ጹሑፍ ብስጭታቸውም የተፋቀው ዕውነት በድርጊት ከብሮ አደባባይ በመዋሉ ነው። በአጋጣሚ እዬጠበቀ የጎንደር ጥላቻ ዕምቅ ገመናን እንዲህ ይዘረግፋል። የእሚወራጬ መንፈሶች ፉጭትም ይሄው ነው።

ሆድ።

መረጃ አጉል ቦታና ጊዜ መፍሰስ ስላልነበረበት ጠብቄው ቆዬሁ። አሁን ግን የህልውና ህይወታዊ ታሪክ ስለሆነ ይገለጥ መዝገቡ – ይነበብ ተብሎ ተፈቀደለት። „ባዶ“ እራሱን አባዛቱ ክራሞትሽን ላግኘው ብሎ እንዲህ ከች ሲል፤ ከምሸከመው በላይ ነው።  የሆነ ሆኖ በሁለት ነገር መንፈሴ እረክቷል። የመጀመሪያው ለተከበሩ ፕ / መስፍን ወልደማርያም ወርኃ መስከረም ሲያብት በ2015 አሜሪካ አቀባበል ያደረገላቸው ጎንደሬ በመሆኑ፤ „የጎንደሬን ባዶነት፤ በባዶው መንጠባረሩን፤ በሌው መኮፈሱን“ ዕድሉን አግኝተው ማጣጣም ይችሉ ዘንድ እግዚአብሄር ስለፈቀደ ሁለተኛው ደግሞ በህይወት እያሉ ያ በያጋጣሚው ምክንያት እዬቆፈሩ ሥሙን እያነሱ ከሚያጣጥሉት፤ ከሚያብጠለጥሉት፤ መንፈሳቸው አብዝቶ ከሚጸዬፈው ቀዬ የአማራ ተጋድሎ ገኖና ደምቆ በብሌናቸው ማዬት እንዲችሉ መገደዳቸው። ከዚህ በላይ ለእኔ የመዳህኒተዓለም ታምር የለም። ልዑሌ ተመስገን።

„የእንግሊዝ ቪዛ የተከለከሉት ፕሮፌስር መስፍን ወ/ማርያም አሜሪካ ገቡ“

https://freedom4ethiopian.wordpress.com/2015/09/03/gtf-6/

የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ በቅንፍ ጎንደርን ያገለለ፤ ጎንደሬነትን የተጸዬፈ፤ ጎንደሬነትን ያጣጣለ። ከዓናቱ በተበላሸ ምናብ ውስጥ ጎንደር ላይ ይፈጸም የነበረው የሰባዕዊ መብት ረገጣ ሁነኛ መንፈስ አልነበረውም። „ዬኢትዮጵያ“ በሚለውም አስኳል ውስጥም ጎንደር ያልነበረበት ነበር። ይህ አግላይነት የተጠናወተው መንፈስ ውክልና በሚያገኝበት ቦታ ላይ ሁሉ፤ የእሳቸው መንፈስ ባረፈበት አዳዲስ ተቋማት፤ ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ጎንደር ስርዝ ነው። መንፈሳቸው በምንም ሁኔታ ከጎንደር ቅዱስ መንፈስ ጋር አይታረቅም። መቸውንም። ጎንደርን ሲያነሱ እንደምን እንዳገፈገፋቸው ላይ እኒህ ሰው መድፍ ከእጃቸው ቢገባ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ … ብቻ ከመራራ ያለፈ ጎምዛዛ ነው።

በኢትዮዽያ ሥም ለመሳተፍ መፍቅዴን ሳልመርምር ከሆነ ጎንደሬነቴን በሰረዘ መንፈስ ውስጥ መሆኑን ልብ ልለው ይገባል። ይህን ከተላለፍኩ እንኳንስ ለሌላው ለውስጤ የማልሆን ከንቱ ነኝ ማለት ነው፤ በውሸት መኖር ውስጥ ለመንፈሴ ግዞት የወሰንኩበት ግዑዝ። ከአማራ ማህበረሰብ ተውልጄ „አማራ የሚባል ማህበረሰብ የለም“ ስባል፤ አንቺ ኢትዮጵያ አይደለሽም መባሌ መሆኑን ሳይጎረብጠኝ ከቀረ ህይወቴን እንዲመራው የፈቀድኩለት ደመነፍሳዊ ዕሳቤ ነው ማለት ነው። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በሳሏት ኢትዮዽያ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ጎንደሬ ብቻ ነኝ ብልም፤ ወይንም ኢትዮዽያዊ አማራ ብልም በሁለቱም አማራጮች እኔ ሥርጉተ ሥላሴ ስሩዝ ነኝ። አውራውን የማንነቴን መግለጫ ኢትዮዽያዊ ዜግነቴን አልተቀበሉትም። ስለምን? ጎንደሬ ነኛ። „አማራነቴም የለም“ ከተባል የዜግነቴ ደግ መንፈስ በሳቸው መንፈስ የተፋቀ ወይንም የተፈገፈገ ነው። እና እኔ ዬት ነኝ? ምንድንስ ነኝ? ቅጠል ወይንስ ምን?  አዲሱ „የአደራ መንግስት“ የሚሉት ንድፈ ሃሳብ እኔን እንደ ጎንደሬነቴ ሆነ እኔን እንደ አማራነቴ የማያስተናግድ ነው። ነገር ግን ለመቆስቆሻነት ሆነ ለማገዶነት አሁንም ቅድምም ጎንደር ይታጫል። ቁስለት። የቅንጅት ጊዜ በአኃታዊ ዕድምታ „አሁን እንዲህ ትሉናላችሁ ነገ ባላችሁን መስመር አናገኛችሁም“ በማለት ገጥ – ለገጥ ልዑካኑን አፋጥጧል – መከረኛው። „ቃል የዕምነት ዕዳ“ ነውና በቃላችሁ ስለመገኘታችሁ ውል እሰሩ በማለት ሞግቷል – አሳረኛው። የእኔ መንፈስ መርኽ ይህ የቆሰለው የተገላይነት የወገኔ መንፈስ ነው።

ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ በክቡርነታቸው መንፈስ ውስጥ ጎንደሬነቴም ሆነ አማራነቴ በቁርሾ የተጠቀለለ መርዝ ነው። „በስማ በለው“ ሳይሆን ጠረናቸው እንዳይርቀኝ ከቅርባቸው ሆኜ „ባዶ“ ሲሉኝ አዳምጪ በተከበረው የሲያትሉ የአማራ ሆነ በአትላንታው የኦሮሞ ማህበረሰብ ህዝባዊ ስብሰባዎች የድጋፍ እንቅስቃሴዎች „ባዶን“ በብዕራቸው ደገሙት „ጎሠኛነት በባዶሜዳ“  ሲሉ። ለሁለተኛ ጊዜ ያን መንፈሴ ክፋኛ የተፀየፈውን የአንድ ክ/ሀገርን ህዝብ „ባዶ“ ባሉ በስንት አመቱ ሁለቱንም ታላላቅ ህዝቦች „ባዶ“ ሲሉ የአንድነት ኃይሉም ሊያመው፤ ሊጎዳው ይገባል። የፖለቲካ ወይንም የሲቢክስ ድርጅቶች ማኒፌስቶን ሳይሆን ሰውን ማዕከሉ ያደረገ ሚዲያም ቢሆን ቁስለቱ ሊሰማውና ሊያርመጠምጠው ይገባል።

እንደ ታቦት ክብካቡ ለሰው ልጅ ክብርና ልዕልና እንጂ ለተራጋጭ መንፈስ ሊሆን አይገባም። ማኒፌስቶ ወረቀት ነው። የሚቀደድ። የሰው ልጅ ግን ልዑል እግዚአብሄር በአምሳሉ የፈጠረው፤ ስለ ሰው ልጅ በደል መስቀል ላይ የተሰቀለበት፤ በችንካር የተቸነከረበት፤ መራራ ሃሞትና ከርቤ የጠጣበት፤ የሞተበት፤ ሞትን በሞቱ ድል ያደረገበት የቃሉ፤ የፍቅሩ ሚስጢር ትርጉሙ ሰው። ስለሆነም የርምጃችን አህዱ የሰው ልጅን ልዕልና፤ ልቅና መሆን ይገባዋል። „እግዚአብሄርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር።“ (ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ“ ፩ ቁጥር ፳፮)። ክቡር ፕ/ መስፍን ወልደማርያም በተለይ አሁን በዚህ ጉልበታም ዬጎንደር አብዮት የህልውና የአማራ ተጋድሎ ያሸተ ምዕራፍ ሊናደዱ ይገባል። በአንድ ፋሽስታዊ የጥቂቶች የጎሳ አንባገነን ግዛት „ለአማራ ማህበረሰብ የምን ውክልና?“ በማለት የፈለሰሙት „አማራ የለም ግዑዝ ዶክተሪን“ ግባዕተ መሬቱ የሚፈጸምበት ወቅት ነው። „የአማራ የለም ዶክተሪን“ ቀባሪ አልባ፤ ምሾ ወራጅም አልባ በደመ ነፍስ ኖሮ፤ እንዲህ ትቢያ ለብሶ፤ የፈለገውን ሳያገኝ እንደሻቀለ ላሽቆ ብን፣ ትን፣ ቅብር ሲል መበሳጨት የግድ ይሆናል። የአሳቻው ሽምቅ ተዋጊ „የአማራ ብሄር የለም ጠቀራ ዶክተሪን“ እንሆ ሁነኛ ጊዜ አግኝቶ ግባዕተ መሬቱ ተፈጸመ። በማን? በህልውና ልዕልና በእንቢተኝነት ልቅና በሥህናዊነት የታሪክ ገናና።

ስለምን „የአደራ መንግስት“ ፍልስፍና በስጋት ተናጠ?

የሁለቱ ማህበረሰብ ጉባኤዎችም „የአደራ መንግስት“ ፍልስፍን በእጅጉ የሚያሰገው ነው። እንደ በፊቱ በሚገለባበጡ ተለዋዋውጭ የፖለቲካ ምሥረታዊ ሥም ዛሬ መርፈስ የለምና። ወጣቱ ፍሬ ነገሩ ገብቶታል። መከራውንም – ኑሮበታል። እንደ ሀገር ተረካቢነቱም የወደፊቱ ዕጣ ፈንታው እሱን የበይ ተመልካች እንዳያደርገው የጠራውን መንገድ ጀምሮታል። የወረቀት ማንፊስቶ ሳይሆን ህልውናው ብቻ ሆኗል ማኒፊስቶ። ኑሮውን የሚወስነው በማኒፌስቶ በመቁንን በሚታደል ሽርፍራፊ ጥገኛ የመብት ልመና ሳይሆን፤ እሱ በፈቀደው፤ በቀዬሰው፤ የእኩልነት ፍትኃዊነት መሆን እንዲችል ወስኗል። በቃኝ ሲል ሁሉንምትብትብ በቃኝ ማለቱ ነው። አሻም ያለው ባለቤትነት በተነፈገው መኖር ውስጥ እንደማይቀጥል መቁረጡን ለወዳጅምለጠላትም ማሳወቁ ነበር። የመገፋት ክርፋትን ማስወገድ የሚቻለው ትግሉ የገማውን በድን ዕሳቤ ከአናቱ መናድ ሲችል ብቻ ነው። ለዚህ የደም ዋጋ እዬከፈለ ነው። በአዋጣው የደም ልክ ማንነቱን ያስከብራል። ወጣትነት ሁለመናነት ነው። ወጣቱ የራበው ፍትኃዊነት ብቻ ነው።

ወጣቱ ሁሉም ነገር አለው። ስለዚህ የፍላጎቱ የስኬት ቁልፍ በእጁ ነው። ደጅ ጥናት አያስፈልገውም። „የአደራ መንግስት“ ፍልስፍና (ለዛ ከተበቃ) ጤነኛ መንፈሱ በሃኪም ካልተረጋገጠ፤ ተገላብጦ ካልተመረመረ በስተቀር እንደ በፊቱ በዝንቅ ገጠመኝየወጣቶችን ሥነ – ህሊና መግዛት አይቻልም። ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ እንዳለ ዬተቀበልናቸው መንፈሶች ጦሶች ጊዚያቸውን ጠብቀው እያዬናቸው ነው። የግጭት ዓውድ። በአንድም በሌላም እዬተገለጡ ነው። ዕድሉን የተሰጣቸው መንፈሶች የአማራ ተጋድሎ ላይ ሲደረስ ወገቤን እያሉ ነው። ሽሽት እንጂ ድፍረት አላዬሁም እኔ። እኔ ነኝ ባሉ በሁሉም ዓይነት ሙያ በተሰማሩት ሊቀ – ሊቃውንታት በሁሉም ማለት እስከሚያስችል ድረስ። „ትዝብት ነው“ አሉ ፍሰኃ ለምለም። ቢያንስ ዕውነት ለሆኑ ጭብጦች አቅም አልተገኘም፤ አንዱ „ከፋኝ“ ይላል በታከተው ሥያሜ፤ ሌላው „የነፃነት ኃይሉ“ ይላል ባልጠራ አቋም፤ ሌላው ደግሞ „እራሳቸውን ያስታጠቁ“ ይላል በተቀረቀር ዕይታ። ወያኔ ደግሞ „ጥቂት ሰላም አዋኪዎች ምንትሶ ቅብጥርሶ“ ይላል። ዕውነት እንዲህ በግራ ቀኝ ተዘምቶባት ሱባኤ ገብታለች። ብሩህ ዳኛ ካልተገኜ ነገም ተንጠልጥሎ የሚታዬን ሰዎች አለን።

የሆነ ሆኖ ክቡር ፕ / መስፍን ወልደማርያ በህይወት እያሉ አማራ የአቅም ዓውራነቱ በበቃ ዕውቅና እና ውክልና የኢትዮጵያ ወሳኝ አካል ሆነው ከሚወጡት ጋር የደሙን ዋጋ በሥማ በለው፤ በተወካይ፤ በጥገኝነት፤ በፍርፋሪ ተጠማኝነት ሳይሆን እራሱን ሆኖ የተስፋ አካልነቱ ሲያረጋግጥ እንዲዩ አምላኬን አብዝቼ እለምነዋለሁ።

የአማራ ጉዳይ መወያያ አጀንዳ መሆኑ የግድ ነው። በሁለገብ ጠላትነት የተፈረጀበት፤ በሥሙ የተነገደበት ዘመን ማክተሚያ ዋዜማ ላይ ስለሚገኝ። በተረፈ „የፈሩት ይደርሳል“ ብሎ ማሰቡ፤ እራስን ለውጦ ተሰናድቶ መጠበቅ ይገባል። ወቅት ብልህ ነውና የራድ ቁራኛ ላለመሆን ውስጥን ማሰናዳት ይገባል። ይህ ገድለኛ ሞገድ አይመለስም። ዬቆረጡ ጀግኖች አሉበት።

ዕውን የሁለቱ ታላላቅ የማህበረሰብ ልጆች የዕንባ አለኝታነት ትጋት „ከባዶ“ የተነሳ ነውን?

በፍፁም።

  1. ውጪ ሀገር ያለው ወገን መሠረቱ የወገኑ የዕንባ ድምጽ ያሰባሰበው እንጂ፤ ሠርግ ላይ የተቀመጠ ሽሙንሙን፤ ኬክ የተቆረሰለት የቅልጣን ደቮ አይደለም። ይህ የበቃኝ ጉዞ እኮ እውነት ማህደሩ፤ የምልዐቱ ትንፋሸ መሰረቱ፤ መሪውም የጀግና ውሎ፤ ባለቤቱ ህዝብ ነው። ስለሆነም ቅብ ዕሳቤ ክፍሉ አይደለም። ወፊቱ ሹክ ያለችውም ይህንኑ ነው። የወገኔ ኑሮ በወፏ ዜና የተገነባ ነውና።
  2. ልጆቹ የበቃኝ ታሪካዊው ተጋድሎ ዕድምታ ባክኖ እንዳይቀር ሥራ ላይ ናቸው። የበቃኝ ታሪክ በመንፈስ አንድነት ውል ጅምር ነው። መተንፈሻ ያጡ የንፁህ አዬር መተንፈሻ ቯንቯዎች፤ የግዞት ስውር አፈናዎችና ዘመቻዎች፤ ባለቤት ያልነበራቸው የቀደሙ ሥልጡን የሃሳብ ማዕከሎች፤ ባለቤት ኑሯቸውም የትኩረት ስስነት የሚታይባቸው ቁም ነገሮች፤ አቅጣጫ ያልያዙ ተዛነፍ አስተሳሰቦች፤ የእኔ ባይ አግኝተው የፍላጎት ወጥነትን ለመውለድ መንገድ የወጠኑበት፤ ክፍተቱን በባለቤትነት ለመሙላት በስክነት ለመምከር የተሰናዱበት በጎ ጅምር ሲሆን፤ እርግጥ ነው „ዬሦስተኛ መንገድ ጥመኞች“ጥነት መንፈስን ነቅቶ በብቃት መመከት ከተቻለ፤ ለተስፋው አዝመራ ሰብሉን ከወዲሁ ማስላት ይቻላል። ይህም በተለይ ለአማራ የተጋድሎ ድጋፍ አምንጪ ኃይሎች የመወሰን አቅምን ብቻ ሳይሆን፤ የደም ዕንባን በቅጡ የመተርጎም ችሎታን፤ በሳል ተስጥዖን ይጠይቃል።

ተመስጦ

የአህዱ ጅማሬ ቆባ ላይ የሚገኘውን ፍላጎታችነን ብስል የማድረግ፤ የወጥ ፍላጎት ጣዕምን ከህዝብ ናፍቆት ጋር ለማገናኘት ብልህ ዕሳቤዎችን ዕውቅና ለመስጠት፤ የደጋፊ አባላትን የአያያዝ ድክመትን፤ ጤናማ ያልሆነውን መንገድ ሳይቀርም አቅርቦ የመንፈሱ ተጠቃሚም – ጠቃሚ ኃይልም የማድረግ አዲስ ፈር ነው። የለመድነው ከሊቃናት ብቻ ሲሆን፤ ይህ መንገድ ግን የተዘጉ አውራጎዳናዎችን ክፍት ለማድረግ ሞክሯል። በዚህ  ከቀጠለ ልብ ይሸለማል። የልቤ ይባላል፤ ምክንያቱም ዜግነታቸውን የተነፈጉ ምንዱባን መንፈሶች አሉና። በኢትዮዽያ የፖለቲካ አመራር ተፈጥሮ ባለቤት ካላቸው ማህበረሰቦች ይልቅ አቋጣሪ የሌላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ይበልጣሉ። ይህ ግንዛቤ እንደ መልካም ውርስ የተያዘ ነበር፤ አሁን የተጀመረው መንገድ ግን ፊት ተነስተው የነበሩ ወገኖች ጠያቂ እንዲኖራቸው ያነቃል – ያደራጃል። ትጉህ ት/ ቤት የመሆን አቅሙ ለነገ የዬምስራች ፍንጭ ነው። አውንታዊ የሆነ ፋክክር ይጸንሳል። አላችሁን? ይመጣል። ረጋ ብሎ ከተጀመረ የጦሮ ሰለባ አይሆንም። ሞቅ ሲል ሞቅ፤ ቀዝቀዝ ሲል ቀዝቀዝ የለም። የእኛ የፖለቲካ አያያዝ አደብ ያንሰዋል። ስለዚህም የኛ የፖለቲካ ክህሎት አድማጭነትን ጣዕሙ አድርጎ አያውቅም። ለዚህም ነው ህልሞቻችን መዋዋጥ የተሳናቸው። ፋሽስትም እንዳሻው ልዕልት ነፃነትን እንዳሻው ማረድ ዕለታዊ ተግባሩ የሆነው። አሁን የወያኔ መደበኛ ሥራ ህዝብ ማሰር፤ መግደል ብቻ እንጂ ኢትዮዽያን እያስተዳደረ አይደለም። ስለዚህም ባልታዩ ጉዳዮች ላይ መረባረብ ግድ የሚያደርገውም ይሄው ጭብጥ ነው። በእጃችን ላይ በወጥ ፍላጎት ላይ መዋዋጥአልተጀመረም። ቢያንስ ደፍረን እንጀምረው በሚሉት ላይ ጥርጣሬን አስወግዶ ቅንነትን ምራኝ ማለት ይገባል። ድጋፍ ማድረጉም ሆነ ማበረታቱ ቢቀር።

በጎ ዕንቡጥ።

እነኝ ሁለት ጉባኤዎች ማለትም የአትላንታውና የስያትሉ ማለቴ ነው፤ ዝንቅንቅ ፍላጎቶች መልክ ለማስያዝ ፊደል መቁጠር የተጀመረበት፤ የፖለቲካ መሪዎች ከወንበራቸው ወረድ ብለው ካለ ፕሮቶኮልና፤ ካለ ምንም ዓይነት ሲናሪዮ ከህዝብ መሃል ቁጭ ብለው ህዝብን ያደምጡ ዘንድ ፊደል የቆጠሩበት፤ ተማሪ መሆንን እንዲቀበሉ ያስተማረ የነገይቱ ኢትዮዽያ መቅድመ ብጡል ነበር።

ታላቁ የሥልጣን ምንጭ የህዝብ ፍላጎት እንጂ ቀና የሚያስቡ ወገኖች ስብስብ ፍልስፍና ብቻውን መሪ እንዳይሆን፣ ይልቁንም ከህዝብ ውስጥ መነሳትን መሪ አጀንዳና ሃሳብ መሆን እንዳለበት በድርጊቱ የሰበከ መልካም መንገድ ነበር። በሌላ በኩልም የችግር መፍቻው ቁልፍ የፖለቲካ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ህዝቡም መሆን እንዲችል መደረጉ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችን ጫና፤ የሥራ ብዛት የሚቀንስም በጎ ጅምር ነው። ከሁሉ በላይ ሕዝቡ መስመሩ ከተዘረጋለት በፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ያልታዩ፣ ያልተዳሰሱ፣ አዲስና ቀንበጥ ታታሪ ዕሳቤዎች ይፈልቃሉ። ይህ በህዝብ ፍላጎትና በፓለቲካ መሪዎች መካካል ቀጥተኛ የሆነ የጤናማ ፍላጎት ጥምረት መስመርን ይዘረጋል። በማህል አቅምን የሚበሉ የኢጎ ዕዳዎችም መቅኖ ያጣሉ። ጥላቻ ፈጣሪው አዋኪ ሃሳብን በጠራ መስመር ለመምራት ምቹ ይሆናል። የዘበጡ ሃሳቦችን ገርቶ የአቅም አካል በማድረግም እረገድ ይህ አዲስ መንገድ የሁሉንም የቤት ሥራ ያቃልላል። የተጣራ ምርት ለተጠቃሚው ለማቅረብ ገድ መንገድም ነው።

ዬዝግ ስብሰባ – ጠቀሜታው።

የአትላንታው ምልዓታዊ የምክክር መድረክ ዝግ መሆኑ አትራፊ መንገድ ነበር። እንዴት? የጠላት ፕሮፖጋንዳ ማዳበሪያ እንዳይሆን መደረጉ በራሱ አዲስ ቅጽ ነው። የተናጋሪዎችን ነፃነትንም ይጠብቃል። ተሳታፊዎች ነጻነት ከኖራቸው ውስጣቸውን የመግለጥ አቅም ይኖራቸዋል። ከሁሉ በላይ መሸከም የማይቻሉ፤ የውስጥ ሃዘን ፈጣሪ ዕሳቤዎች የአደባባይ ሲሳይ እንዳይሆኑ ክትር መሰራቱ፤ ለኢትዮዽያዊነት መንፈስ ብቁ ጥበቃ ያደረገ ቅዱስ ውሳኔ ነው። ከህሊና ጉስቁልና ሁላችነንም ታድጓል፤ ጤናችን ጠብቋል። የተዘመተበትን የአብሮነታችን ሩህ ብቁ ትንታግ በመሆን ለእያንዳዳችን መንፈስ የደህንነት ዘብ ቆሞለታል። ባላለቁ ዕይታዎች፤ ባልታሹ ጉዳዮች፤ ባልሰከኑ አጀንዳዎች መታመስን ከሥሩ ነቅሏል። ጊዜያችነን አልበላም። ስለሆነም ለዚህ ብልህና የቀደመ እርምጃ ታላቅ አክብሮት አለኝ፤ ዕውቀትም ገብይቸበታለሁ። ምክክሩ ዝግ መሆኑ የፖሮፖጋንዳን ቅንጥብጣቢ ክብር ነክ ምክንያቶች እንዳይጠጋው በእጅጉ ተጸይፎታል። እዩልኝም አላለም። እዩኝ … እዩኝ አላለም። ስለሆነም በሳል ምዕራፍ ነው። ተባረኩ።

ዝግነቱ … ሥልጡን ነው። ውስጥ ካለ ግርዶሽ ታዬ ማለት ነው። (X-ray) ስለዚህም ሸከር ያሉ ዕሳቤዎችን ልጎ ዉስጥን ከውስጥ ጋር ለማዛመድ ቀና መንገድ ነው። በዚህ መንገድ አድብተው የሚጠብቅ የግራ ፖለቲካ ጎታችና ቅንነት የፈለሰበት ሽምቅ ውጊያ ኪሳራ በኪሳራ ይሆናል። ይህ ደግሞ በስለት እንኳን የማይገኝ የመከራችን መፍቻ የሚስጢር ቁልፍ ነው። መጀመሩ በራሱ ነገን ቦግ ብሎ ይመጣልናል የሚል በጎ ምኞትና ተስፋ እንዲያድርብን ያደርጋል። የግብረ ኃይሉ አስተባባሪዎችም ባገኙት የውስጥ መንገድ ጠቃሚና ጠቃሚ ያልሆነውን በመለዬት በአገኙት መረጃ (feedback)፤ በጥበባዊ አስተዳደር ሁሉንም አቅም ቤተኛ ለማድረግ ይረዳቸዋል። የምልዕቱን የአቅም ጥሪት በአግባቡ ለማስተዳደር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በተጨማሪም እንደ ባህል እዬሆነ የመጣ አዳጊ ያልሆነ መንገድ ነበር። “ኑ ስብሰባ። … ግን ስትመጡ አንደበታችሁን አሽጋችሁ የሚዋጣውን አዋጥታችሁ በወሰንላችሁ ልክ ብቻ መቀጠል ግዴታችሁ ነው“ የሚለው ብልህነት የጎደለው መንገድ ሃዲዱ እንዲሰበር አድርጓል።

ስትመጣ „አፍህ እንደከረቸምክ ሰምተህ ብቻ መመለስ።“ ይህ በዚህ ግሎባላይዜሽን ዘመን፥ ዘመኑን ያላዳመጠ አካሄድ ነው። „ጨዋታን ጨዋታ“ ያነሳዋል ይላል የጎንደር ሰው። ስብሰባ ስሄድ በነበረበት ጊዜ ሁልጊዜ እማስታውሳት ወ/ሮ ነበረች። ወርቅ የሆነች። ብዙ የጎንደር ሰው የጠራ የገጽ ቀለም ነበረው። የዛሬን አያድርገውና። ከእነሱ ጋራ በአጥር ነበር የምንለያዬው። ያቺ ታይታ የማትጠገብ እመቤት ጎንደር ጡረታ ሰፈር በዘመናዊ ቢላ ነው የምትኖረው፤ የሰፈሩ እድር ማህበርተኛም ናት። ሃዘን ሲሆን እንጀራውንና ወጡን የምትልከው በቤት ሠራተኛ ነበር። የዕውነት ነው የምነግራችሁ። እሷ በቀብርም – በማስተዛዘንም ትውር አትልም። አቶ ሞት ከቤቷ ገባ። የአውራ ጎዳና ተወዳጅ ሠራተኛ የነበሩት ባለቤቷ አረፉ። ታዲያንላችሁ ማታ – ማታ ሠፈርተኛው ሰራተኛ ያለው በቤት ሰራተኛው፤ ልጅ ያለውም በልጅ እንጀራና ወጡን እዬላከ በመንፈስ ብቻ አስተዛዘነ። ጎንደር ዋዛ፤ እህ። መከራ በባዶ ድንኳን። እጅግ ከባድ ቅጣት ነበር። የጸደቀ እርምጃ ነበር። ስለዚህ ታሽጎ ውሎ ከመመለስ አቅሙ ያለው ሁሉ ገንዘብ በመላክ ስብሰባ ቢቀር ምን ይባል ይሆን? የሆነ ሁኖ ከዚህ ቅጣት በኋላ የእድሩ መሪ ሆነች። ስለዚህም የኦሮሞና የአማራ ማህበረሰብ ስብሰባዎች የገነገኑ ግትር መንገዶችን ሁሉ በሚገርም ሁኔታ ገርተዋል። በባይታወርነት የተገረፋ መንፈሶች ሁሉ አለንላችሁ ተብለዋል። ማለፊያ። ይሄ ዝንተዓለም ዬተኖረበት „እንዳያማም ጥራው እንዳይበላም ግፋው“ አቁሳይ ሂደትም በፈንታው ድንኳን ጥሎ እንዲቀመጥ ተገዷል። ለዚህም ነው ዘገባው ሁሉ አስተዛዛኝ የነበረው። ከዘገባ ውጪ የሆነ ታላቅ ማህበረሰብም አለ። አማራው። በውስጥ ለውስጥ መንገድ መሠረዙን አስተውሎበታል። እነዚህ የውስጥ ኃዘኖች ናቸው ለብሄርተኝነት ጥሎሽ የሚጥሉለት – ማጫም የሚያማቱለት። ለጎጆው ድምቀት ድርና ማግ የሚሆኑት። ነፍስ ታለች። ህሊና ታጥጣለች፤ አንደበት ትሞታለች። ብዕርና ብራን ለሌላው ለዕውነት እንዳደሩት ለዚህ ዓይን ላወጣ መገፋትም ዕውቅና ይሰጣሉ። እራስን ሰርዞ መኖር ስለማይቻል።

አውታር።

የፖለቲካ፤ የሲቢክስ፤ መሪዎችና አክቲቢስቶች እንደ ህዝብ – ከህዝብ ጋር ተቀምጠው እንዲያደምጡ መደረጉ የሥልጣን ሹም-ሽር ሲገጥም እንደ አንድ የእኔ ቢጤ ተራ ሰው ከሥር መኖርን እንዲለማመዱትም፤ ሰራዊታቸው ሕዝብን እንዲያደርጉ የልምምድ ት/ ቤት ተከፍቶላቸዋል። ይህ ፈጣሪ የገለጠው ሚስጢር እንጂ በሰው እጅ የተሠራም አይደለም። አመል ሆኖብን ከእኛ ብቻ ባለመሆኑ ለመግፋት ካላሰብን በስተቀር እንዲህ የምናቃልለው፤ የምናጣጥለው፤ ከዚህም አልፈን ተርፈን „በባዶነት“ የምንፈርጀው ሊሆን አይገባም። ለዘመኑ ጥልቅ፤ ምጡቅ ጅማሬ ነው። ክንውኑ ያደጉ መንገዶችን – የቀሩን ስልቶችን የሚሳዩ መስታውቶች ነበሩ። እንደ እኔ እንደ ሥርጉተ ሥላሴ አሰልቺ ወይንም አትራፊ ያልሆኑ መንገዶችን በቅጡ ገምግመን አቅማችን ለማፅናናት ቀበቷችን ሊሆን ይገባል ባይም ነኝ። በስተቀር በእጃችን ያለው ኃይል ሳይቀር መንፈሱ ይሸፍታል። ይተናልም። ትዕግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳልና። አንድ ሰው ምንም አያደርግም ማለት የሚቻል አይመስለኝም። አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስ ከቀረበው፤ ቅንነት ጥሪቱ ነውና ልዩ አቅም የመሆን ችሎት አለው።

አንድ የፖለቲካ ድርጅት ወይንም ሚዲያ፣ ወይንም ሙሁር፤ ወይንም የሲቢክስ ድርጅት ብቻውን ይህን የገዘፈ የፈተና ወንዝ መሻገር አይችልም – ዛሬ ባለው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ። ሁሉም የቤት ሥራውን ለመሥራት በተመቸው መንገድ ተደራጅቶ መሥራት አለበት። መብት ቦንዳ የጣቃ ጨርቅ አይደለም። በሜትር ተለክቶ የሚታደል ወይንም እንደ ሸቀጥ በጀምላና በችርቻሮ በገብያ ሥርአት የሚተዳደር። ክትር ተሰርቶል በተዘጋጀልህ እንደ አሸንዳ ፍሰስ የሚባልም አይደለም – መብት። ወይንም በሰዎች መልካም ፈቃድ ብቻ የሚቸር የቡፌ ግብዣ አይደለም -መብት። መብት በውስጥ ፈቃድ ብቻ ህልውናው የተረጋገጠለት የሥነ – መንፈስ ልዑል ነውየእኔ ብቻ ሊባል የሚችል የነፍስ ጥሪት ነው። መብት የህልውና ገዢ መሬት ነው። ይህ ንፁህ የሰው ልጆች መብት ለዘመናት እግር ከወርች ታስሮ የኖረበት ዘመን የሚከትመው የህልውና ልዕልና በእንቢተኝነት ልቅና የሥህነ – ታሪክ ገናና በሆነው የህዝብ ተጋድሎ ብቻ ይሆናል። መንገዱን ደግሞ ጀግኖቹ ጀምረውታል።

የተከበሩ ፕ / መስፍን ወልደማርያም ሆይ!! „ዝም በሉት¡ ምን ያመጣል¡ የት ይደርሳልማ!“ ከስሎ ቀረ። አይጠራጠሩ አማርኛም ሆኖ ኦሮምኛ ብሄራዊ ቋንቋ መሆኑ ብቻ የትውልዱን ጥያቄ አይመልስም ወይንም በመጠጋገን ፕሮፖጋንዳ መላሾ አይወራረድም። ከእንግዲህ አንቅረው የተፋት አማራም እንደወትሮው „የስማ በለው“ ውክልና መጠቃጠቂያ አይሆንም።

ክቡርነተዎት ዬቤተሰቦቼን የዘር ሐረግ አማራነቴን፣ እንዲሁም ናፍቆቴን የፋሲልን ከተማ ባይወዱትም በአመኑበት መሥመር የድርሻዎትን ለማበርከት  ከልጅነት እስከ እውቀት ልፋተዎትና ድካመዎትን፣ ላደረጉት የራስ መንገድ ተጋድሎ አክብራለሁ። እግዚአብሄር ዕድሜ ሰጥቶዎትም የተመኟትን ኢትዮጵያ ያዩ ዘንድ በቅን መንፈስ አልማለሁ። የዛን ግዜ ያን የመሰለ ሪፖርት የሠራችው ጎንደሬዋ ሥርጉተ ሥላሴ ነበረች፤ ለዛን ጊዜዋ ወጣቷ ሥርጉተ የሰጧት ሥጦታም ነበር። ከስጦታው ይልቅ ለቀንበጡ መንፈሴ ተጠንቅቀውለት ቢሆን ጥሩ ነበር። የማልሸሽገዎት  – ጎድተውኛል። እኔ ግን እስከዛሬ ድረስ አከብረዎታለሁ። ለወደፊቱም። እኛ ምን እንደምንፈልግ? ምን እንዳለን? ምን እንደምንችል? ጠንቅቀን እናውቃለን። ክቡርነተዎት እንደሚሉን „በሌለን ላይ የምንኮፈስ አይደለንም።“ „ባዶዎችም – አይደለነም።“ አቅማችን ወደ ተግባር ለማሸጋገር መንገዱ ዝግ ቢሆን እንጂ ያለንማ አለ። ለኢትዮዽያም ማገሮች ነን። ተስፋዎች። እኛን አልባ ኢትዮዽያ አንድ ጋት አትራመድም። „ጎንደር ምን አለ?“ ብሂሉም ይሄው ነው። ዕጣ ፈንታው ከመማገድ በቀር ዕልፈት አግኝቶ ባያውቅም። አሁንም ያሰፈሰፋ አይኖች ከእሱ ራስ ወርደው አያውቅም። ውጪ ያሉ ሊቃውንታት የአብዛኛው የአደራ ቤት ነው ጎንደር። አንድም ባለዕድል ህይወቱ ሲስተካከልለት አንድ የጎንደር ልጅ ወስዶ ለመስተማር ያሰበ የለም። ወጭት ያልሰበረ አላዬነም – አልሰማነም። ጎንደር የመከራ ጊዜየኢትዮጵያን እናቶች አደራ ያወጣ ታላቅ ህዝብ ነው። አማራ ማለት ሰባዕዊነት ማለት ነው

መርህ።

የማከብረዎት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም። ጥሪው የዕንባ ነው። የኃላፊነቱ ማሳ ዘርፈ – ብዙ ነው። ስለሆነም ለጥቂት ፓርቲዎች አቅም ብቻ የሚተው አይደለም። የሁለቱን የማህበረሰብ ልጆች ያሰባሰባቸው ወቅትን ያዳመጠ፤ ልቅናን ያጨው የብዙኃኑ የበቃኝ ገድል እንጂ፤ ውጪ ሀገር የሚኖሩ የሁለቱ ታላላቅ ማህበረሰቦች አምክኖዬ አይደለም። ወቅቱ ከቀደመው በተለዬ ሁኔታ በራሱ የጊዜ መስመር የፈነዳውን ማእበል የሚመጥን አቅም ይጠይቃል። ዬፖለቲካ ድርጅቶች ይህን የበቃኝ ገድል ምንጭ ይሆናል ብለው ስላላሰቡት በማኒፌስቷቸው ውስጥ አላካተቱትም ነበር። የማኒፌስቷቸው መንፈስ በዚህ የህዝብ ረመጥ ዝር አላለም ነበር። የዚህ ገድል ባለቤት ህዝብ ብቻ ነው። ከፖለቲካ መሪዎችና ማኒፌስቶ የዳታ ጉዞ አሻም ብሎ የተነሳው ህዝባዊ የበቃህኝ – የሂድልኝ ጥያቄን ለመምራት እውነትን ስንቁ ያደረገ፤ መነሻውም መድረሻውም ከህዝብ ፍላጎት ዉስጥነት የሚነሳ፤ እራሱን ዝቅ አድርጎ ለህዝብ የበላይነት ታዛዥ የሆነ መሪ ይሻል። የወቅቱ የእንቢተኝነትን ሞገድ ለመምራት ከታሰሩበት የማኒፌስቶ ፍቅር ራስን ማውጣት በእጅጉ ይጠይቃል። ምክንያቱም የወቅቱ የህዝብ „የማንነት ጥያቄና ተያያዥ ጉዳዮች“ በፖለቲካ ድርጅቶች አክብሮት ያልነበራቸው ስለነበሩ ማንፌስቶዎች ይህን የእውነት ጎዳና ለመምራት ከሽሽት በድፍረት የውስጥ ለውጥ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከተጋድሎ ስያሜዎች ጀምሮ እውቅና መስጠት ብቻ ሳይሆን ሙሉ አክብሮትም መሰጠት ይገባቸዋል። የተሻለ ክህሎትና ጥበብ የተሞላው መንገድ ወቅቱ ይጠይቃል። ስለሆነም አጋዢ ጥረቶችን ማበረታት ይጠይቃል። ነፃነት ከተፈለገ። በተለመደው መንገድ ከሆነ ግን ለወያኔ የገድ መንገዱ ይሆናል። የዕናቶች ዕንባ የወገን ደምም ባክኖ ይቀራል። ትዕግስትን ዋጥ አድርጎ እውነት ብቻ እንዲመራ ቢፈቀድ ኢትዮዽያ አላዛር ናት። እንደ ገና አዎን እንደ ገና ፈተናን አሸናፊው የተፈጥሮ ሚስጢርነቷ ዳግም ይጎመራል። ግን ወቅቱን በተደሞ ማድመጥ የሚችል ምራቃቸውን የዋጡ መሪዎች ጥሪዋን ሰምተው በሃቅ ማሳ አብሮነትን ማፍለቅ ከቻሉ ብቻ። እናት ሀገር ኢትዮዽያ ሁሉም አላት – ለሁሉም ትበቃለች። የምንም ነገር ደኃ አይደለችም። እኛ ታምሰን የምናምሳት እኛው ነን።

ወቅቱ በቢሮክራሲና በማዕከላዊነት ያልታሰረን መንገድ ይጠይቃል። ግልጽነትና አድሮ የሚገኝ ዕውነታዊነትን ብቻ ስንቅ በማድረግ፤ ጥርጣሬና ስጋትን በፍጹም ሁኔታ የሚታደግ ቀጥተኛና ያልተወሳሳበ፤ በፕሮፖጋንዳ ያልበከተ ቅልብጭ ያለ ቀላል መንገድን ይሻል – ባላንባራስ ዛሬ። ማዕበሉ ፈጣን፤ ፈተናዎቹ እጅግ የገዘፋ በመሆናቸው ፈጣን የጥያቄ ምላሽ ሰጪ አካልን መስመር መዘርጋትን ይጠይቃል። በዛሪይቱ ኢትዮዽያ የፋሽስቱ አስተዳደር ገዢ መሬት ላይ ሲሆን የህዝቡ የበቃኝ አብዮት ግን በከፋ ሁኔታ ሙት መሬት ላይ ስለሚገኝ። የነፃነት ትግሉ መሪዎች ሰብዐዊነታቸው ሚዛን የደፋ መሆን አለበት። ትንፋሹ ያጠረው መከረኛ ህዝብ ነው ያለን፤ ቀን በጨለማ የተዋጠበት፤ ፀሐይ የደም ካባ የለበሰችበት። መተንፈስ ፋታ ያጣበት። ስለሆነም የተጋድሎ አርበኛውን ደህንነት ለጠላት ጥቃት የሚያመቻቹ መረጃዎችና የፕሮፖጋንዳ ገብያዎች ባስቸኳይ መታረም ይገባቸዋል። ለእኔ የሚበልጥብኝ የፕሮፖጋንዳ ሰይፍ ሳይሆን የሰው ልጅ ለሚከፍለው መስእዋት በቂ ጥበቃ ሲደረግለት ማዬትን ነው።ለዚህ ነው ኃላፊነትትን መከፋፈል ግድ የሚሆነው። ባለቤትነት ከርህርህና ጋር መዋደድ አለበት። በዚህ ክፋ ጊዜ ያን መከረኛ ህዝብ ለበለኃሰብ እንይሰጥ ጋዜጠኞችም ቢሆኑ ለህሊናቸው ቢያድሩ ይሻላል። ህዝቡ በአውሮፕላን ቢጨፈጨፍ፤ ብርሸለቆ የታገቱት ቀንበጦች ቢረሸኑ የሚጎዳው ነው የሚጎዳው። ስለሆነም ኃላፊነት ከጎደለው የመረጃ ቅብብሎሽ በእጅጉ መቆጠብን በአጽህኖት ወቅቱ ዬጠይቃል። ስክነት የተጠናወታቸው ዕሳቤዎች ሁሉ ጥንቃቄ እርስታቸው ሊሆን ይገባል። ከዛ ማህበረሰብ የተፈጠሩትም ቢሆን ጠብተው ላደጉት ጡት ደጀን መሆን ይገባቸዋል። በግራ – ቀኝ ቋያ ላይ ለሚገኝ ማህረሰብ ተጨማሪ ውጋት መሆን አይገባም። ልብን፣ እትብትን፤ ማህፀን በማስተዋል ማድመጥ ይገባል። በሳት ጨዋታ የለም። የግል ክብርና ዝና አላፊ ነው። ትውልድና ታሪክ ግን ቀጣይ ነው። በዚህ ዙሪያ – ገባው ጨለማ በሆነበት ዘመን „ምሳሩ አልጠበቀም፤ ክፍተት አለበት፤ ደህና አድርገህ ቸንክርልን ብሎ ማወጅ“ ርህርህናን የመወጋት ያህል ነው። የህዝብን ተነቃቂነት በብርድ ምች ያሳቅቃል። የተሳትፎውንም አድማስ መንፈስ ያሸማቅቃል። ጎንደር መሬት ከተሆነ ታላቁን ብሂሉን „ሙያ በልብን“ ልብ ማለትን ይጠይቃል። „የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል“ እንዲሉ።

የብዕር መኸር ክወና።

ክቡር ፕ / መስፍን ወልደ ማርያም … የዋሽንግቱ ጉባኤም እኮ አንድ አውራ ህብረ ብሄራዊ ፖርቲ ከሦስት የዞግ ድርጅቶች ጋር በሚያስማማው ጉዳይ ብቻ አቅሙን በወልዮሽ ለመጠቀም ነበር ስምምነት ያደረገው። ችሎታው ከኖረ ስለምን እንደ አትላንታውና እንደ ሲያትሉ ጉባኤ አላብጠለጠሉትም? ለእርሰው መንፈስ የክትና የዘወትር ኢትዮዽያዊነት አለን ወይንስ ድፍረት እንደኛው ተሰደደ? ለነገሩ በፖለቲካ ወይንም የሲቢክሳ ድርጅቶት ያሉ የአማራ ልጆች በዬተደራጅበት የግል ነፃነታቸውን ማስከበር የቻሉም አይመስለኝም። ቅድመ አትላንታ ጉባኤ ምጥ እንደ ተያዘ ሰው ቃለ ምልልሱ ጥድፊያ ላይ ነበር። ለሲያትሉ ጉባኤ ግን ጭንቅ አልነበረም። ዬትም አይደርስም ነው። በለንደኑ ጉባኤም ሆነ በአትላንታው ጉባኤ ላይ አልተመቸንም ያሉ ወገኖች ብዙ ጽፈዋል። ግን በጸሐፊዎች የብራና ሰሌዳ ላይ የአንድም የኦሮሞ ማህበረሰብ የፖለቲካ ድርጅት አርማ ተለጥፎ አላዬሁም። „አማራ መደራጀት“ የለበትም በሚሉ ጸሐፍት ግን ልጅ – እግሩ የአማራ ድርጅት ቅስም በሚሰብር ሁኔታ የሁሉም አርማዎች ተለጥፈው አይቻለሁ። ዬጸሐፍት አለመሆኑን ግን አረጋግጫለሁ። ምክንዬቱም ሌላ ቦታ ሌጣውን ወይንም ብሄራዊነትን የሚያክበር ነገር ነበር ያዬሁት። እርግጥ በኋላ ላይ ተስተካክሎ አይቻለሁ። ሥህተትን ማረም መልካም ነገር ነው፣ ሊበረታታም ይገባዋል። ሰሞኑን ወያኔ አዲስ ካቢኔ ውስጥ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ የኦሮሞ ወገኖቼን ሲሾም አማራ ግን የለም።ስለምን? ዬት ይደርሳሉ ነው ነገሩ። „ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ።“ በጠላት ወረዳም ይሁን በወገን ወረዳ ያሉ የአማራ ልጆች እራሳቸውን ሸሽተው ስለሚኖሩ ንቀት እንዲነግስ ዕድሉን ሰጥተውታል። የወላጅ እናታቸውን ማህፀን ሆነ የአባታቸውን አብራክ ከሰው ሠራሹ ማንፌስቶ በታቻ አንገቱን እንዲደፈ በይነውበታል። የወላጅ እናታቸውን ጡት እረግጠውታል። የወላጅ እናት ዕንባ ደግሞ እዮርን ያንኳኳል። የኦሮሞ ልጆች ግን በሁሉም ቦታ ቁልፋን ይረከባሉ። እራሳቸውንም የእናታቸውንም ጡት የክብር ተክሊል በዬትኛውም ሁኔታ አሰርተውለታል። ማርከሻ ናቸው። ኩራት። (proud und Stolz) የሆነ ሆኖ እስከ ዛሬ ይታይ፣ ጅምር ነው እያልን እንደቆዬነው ለሁለቱ ታላላቅ ማህበረሰቦች ውጥንም ለሌላው የሰጠነው ዕድል ሊነፈግ አይገባም። ሽበቱ የዕውነት ሽበት ከሆነ።

ሌላው ግን በአብዛኛው ኢትዮዽያዊ የታቦትነት ማዕረግ የተሰጣቸው ታላቅ ሙሁር ያሉበት ህይወትን ከሳቸው በላይ የሚውቀው የለም። የፋሽስት ሥርዓቱ ለአንድ ሰውን ማዕከሉ ያደረገ (ጎንደርም አማራም ዬሌለበት ቢሆንም) ከተመቸዎት እሰዬው ነው። „ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው“ ይባል የለ።

ዬማከብረዎት፦ ዕውነት ቤቷ ህዝብ እንጂ ፕሮፖጋንዳ አይደለም። ዕውነት ዕልፍኟ ህሊና እንጂ ሰው ሠራሽ ማኒፌስቶ አይደለም።ህዝባዊ ማዕበሉ ከሰማይ የጠበቁት መና ሳይሆን መሬት የያዘ የሃቅ ዕንቁ ነው። ከዚህ በላይ አንገብጋቢ ጉዳይ የለም። ሊኖርም አይችልም። ስለዚህም ውስጣቸውን ያገኙት ልጆቹ ለዕንባው ዘብ እንዲቆሙ ግድ ይላቸዋል።

ክቡር ፕ/ መስፍን ወልደማርያም የውጬ የወገን ተቆርቋሪነት መሠረቱ ይህ የምልዐቱ ድምፅ ነው። „በባዶ ሜዳ“ አለመሆኑን  ምን አልባት ሥራ በዝቶቦዎት ካላዳመጡት እንሆ  — በአክብሮት። የዕውነት አሮጌ ሆነ ልዋጭም የለውም። ዕውነት ቅልብጭ ያለ ጉልህ አመክንዮ ነው። የሚታይ፣ የሚጨበጥና የሚዳሰስ። ዕውነት የምናብ ህልም ሰሌዳ ደንገጡር አይደለም። እውነት ብርኃን ነው። የአደባባይ ሚስጢርም።።

ምርኩዝ

የጎንደር አብዮት ዋዜማ – ሩህ። ጉልላት።

https://www.youtube.com/watch?v=DUWkqaWdj2w

„የፈራ ይመለስ ጎንደር ጥምቀት በአል አከበረች Gonder protest YEFERA YEMELES“

https://www.youtube.com/watch?v=tDA2amRLpxY

ገድለኛው የጎንደር አብዮት የአማራ ተጋድሎ የአልገዛም – ፀሐይ።

https://www.youtube.com/watch?v=ERwU7NNu7J4

ልጁን የገበረበት የአማራ ተጋድሎ ብረት ክንድ የበላይ መንፈስ ልዕልና። እጨጌ ።

ፍትህን ያለመ ድንቅ ቅኔ ዘ -ጉባኤ።

https://www.youtube.com/watch?v=5DRf6OBkxE0

„በጎንደሩ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተነበበ አስገራሚ ግጥም“

 ገድለኛው የግንጫ አብዮትና ህዝባዊ አዝመራው። ዕንቁ።

https://www.youtube.com/watch?v=NQEbZGps6Cc

“Oromo Students protest – As it happened in various parts of Oromia”

የብሩህ ተስፋ ማህደር። ርትህን —- https://www.youtube.com/watch?v=5DRf6OBkxE0

https://www.youtube.com/watch?v=5DRf6OBkxE0

ዬናፈቀ።

https://www.youtube.com/watch?v=kc1UT9SDoqk

“Oromo Protesters’ funeral processions turn into protest Satenaw Latest Ethiopian News & Br”

የበቃኝ ትንታግቀንዲል።

https://www.youtube.com/watch?v=nZFYlFqZryA

„Oromo Irecha Protest በኢሬቻ በአል ላይ የተገድሉትን ሰዎች ቁጥር መንግስት ለማቅረብ አልፈለገም። Oct 2016 Low, 360p”

….. ምን ያህል እንደተጓዝኩ አላውቀውም።

ምን ያህል እንደሚቀረኝም አላውቀውም።

አለማወቄን ስጠይቀው አለማወቁን ነገረኝ።

ተስፋን እጠብቃለሁ፤ የራዕዬ ሐሤት ነውና። ማዕዶቴ።

አምላኬ ሆይ! እምዬን ኢትዮጵያ ሀገሬን ጠብቅልኝ።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ። ደህና ሰንብቱ። መሸቢያ ጊዜ።

 

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s