የዐማራ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች የቤት ሥራ!

ከሙሉቀን ተስፋው

በየቀኑ በርካታ መልዕክቶችን ከተለያዩ ሰዎች እቀበላለሁ፤ በቅርብ የደረሱኝን ሁለት መልዕክቶች ግን መቼም የምረሳቸው አይመስለኝም፡፡ የዐማራ ሕዝብ ነጻነቱን እስኪጎናጸፍ አርፌ እንዳልቀመጥ ያስገድዱኛል፡፡ የዐማራን ሕዝብ ትግል በምችለው አቅም ሁልጊዜም እንድደግፍ የምጠቀምበት ዘዴ የተለያየ ነው፡፡

debremarkos-university-satenaw-news

ለምሳሌ አንደኛውን ልንገራችሁ፤ በ2008 ዓ.ም. በዓመያ የዐማሮች አገር እንዳለ ወድሞ በዐይኔ በብሌኑ ያየሁት ዕለት የተሰማኝ ስሜት እስከመቃብር አብሮኝ እንደሚዘልቅ ጥርጥር የለውም፡፡ ቤቶችና የእህል ማስቀመጫ ጎተራዎች በእሳት ወድመው ቦሎቄው ተደፍቶ አየሁት፡፡ ከተደፋው ቦሎቄ ዘገንኩና በቦርሳየ ውስጥ ከተትኩት፡፡ ያን ቦሎቄ ከልብስ ሻንጣየ ጋር አደረግኩት፡፡ የትም አገር ስሄድ ከልብሴ በስር ከዓመያ ያመጣሁት ቦሎቄ አለ፡፡ አውሮፓ ያላችሁ ሰዎች ብትጠይቁኝ በማንኛውም ሰዐት ያን ቦሎቄ አሳያችኋለሁ፡፡ ሁልጊዜ ልብስ ስለብስ ሻንጣየን ስከፍት ያን ቦሎቄ አገኛለሁ፤ ወዲያውኑ እነኚያ ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው የዓመያ ዐማሮች ከፊቴ ላይ ይሳላሉ፡፡ ስለዚህ የዓመያ ዐማሮችን ሁናቴ ልርሳ ብል እንኳ አልችልም፤ ያለኝ አማራጭ የዐማራ ሕዝብ ስቃይ የማያስደስታት አገር እስክትገነባ በምችለው ሁሉ ተግቼ መታገል ነው፡፡

ወደ ቀደመው ነገር ልመልሳችሁ፡፡ አንዲት ልጅ ከሳውድ አረቢያ ደወለችልኝ፡፡ ከማውራቷ በፊት ታለቅሳች፡፡ አታውቀኝ አላውቃት፤ እንዳላረጋጋት የምታለቅስበትን ጉዳይ ማወቅ አልቻልኩም፡፡ እንደምንም በእንባ እየተናነቀች ‹‹ዐማራ ግን ምንድን ነው ወንጀሉ? ለምንድን ነው እንዲህ በየቦታው እንድንገደል የተፈረደው? ዕውነት ፈጣሪ አለ?›› ከምትናገረው ይልቅ ልቅሦዋ የበለጠ ልብ ይሰብራል፡፡ የማደርገው ነገር ቢኖር ማድመጥ ብቻ ነበር፡፡

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ከባሕር ዳር ዩንቨርሲቲ አንድ ጦማር ደረሰኝ፤ መልዕክቱ ባጭሩ ‹‹ተመራቂ ተማሪ ነኝ፡፡ በነሐሴ በነበረው የዐማራ ተጋድሎ ከፊቴ ብዙ እንቡጥ ሕጻናት ሲቀጠፉ አይቻለሁ፤ ጓደኞቼ እና አብሮ አደጎቼ ተገድለውብኛል፤ በዚህ ዓመት የሚመረቁ የዲፓርትመንት ጓደኞቼ በወያኔ ጥይት ተገድለው ከእኔ ጋር ክፍል አልገቡም፡፡ የኔ ቤተሰቦች በወታደር ተከበው በየቀኑ በመታገል ላይ ናቸው፤ በርካታ ወጣቶች በእስር ቤት እየተሰቃዩ ነው፡፡ መመረቄን የሚጠብቁ ድሃ ቤተሰቦች እንዳሉኝ አውቃለሁ፤ ግን የታሠሩ፣ የተገደሉና እየተሰቃዩ ያሉ ወንድሞቼን ሳስብ የመማር ፍላጎቴ ተዘጋ፤ ምን እንደማደርግ ብቻ ነው ቀንና ሌሊት የማስበው…›› የሚል ነው፡፡

 

የዚህ ወንድማችን ጥያቄ የሁሉም የዐማራ ተማሪዎች ጥያቄ ነው፡፡ የዐማራ ተማሪዎች ጥያቄ እንደ 66ቱ ‹‹መሬት ላራሹ›› የሚል እንዳልሆነ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ በሕግ፣ በፖለቲካል ሳይንስ፣ በአስተዳደርና በመሳሰሉት ትምህርቶች ‹‹ሁሉም ሰዎች ከሕግ ፊት እኩል ናቸው›› እያለ መምህሩ ሲያስተምር ‹‹ዐማራው ግን በትግሬ መረገጡን›› አይታችኋል፡፡ በሕይወት መኖር የተፈጥሮ መብት መሆኑን ለሚነግራችሁ መምህር ‹‹በአጋዚ ወታደር የተገደለውን ወንድምህን ሕልሟ በአጪር ስለተቀጨችው እህትህ›› ማሰብ አለብህ፤ ቡሬ በአንድ የትግሬ ሆቴል ውስጥ አስከሬናቸው ተጠራቅሞ ስለተገኙት ወጣቶች፣ በድፍን ጎንደርና ጎጃም የአጋዚ ጥይት ግንባራቸውን የተባሉ ዐማሮች በዐይነ ኅሊናህ ይምጣ፡፡ ‹‹ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማንም ሰው አይታሰርም›› ሲልህ እናቷን መቅበር ያልተፈቀደላት ልጇን የትም የጣሉባትን ቀለብ ስዩም፣ ስለእነ ንግሥት ይርጋ፣ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፣ አታላይ ዛፌ፣ ጌታቸው አደመ፣ አንዷለም አራጌ፣ አንገው ሰጠኝ፣ እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ጌታቸው ሽፈራው… በብር ሸለቆ ስለታጎሩት የዐማራ ወጣቶች አስብ፡፡ ስለ ሰብዐዊ መብትህ ሲነገርህ ዲሑማናይዝ የሆነውን አባትህን አስታውስ፡፡ በበርሃ እየተዋደቁ ያሉት ወንድሞቻችን ለምን እንደሆነ ሊገባን ይገባል፡፡

ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት አለ ሲሉህ ከመቶ ሺህ በላይ በየአገሩ የተፈናቀሉ ዐማሮችን ጉዳይ አንሳ፡፡ ማንነት የሚወሰነው በራስ መሆኑን በቀቀኑ መምህር ሲያነብ በወልቃይትና በራያ ‹‹ትግሬነት በግዴታ የተለጠፈባቸውን›› ዐማሮች ሥቃይ ትዝ ይበልህ፡፡

ስለፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ስትነገር በሕወሓት የተሸጠችው አገርህን እስብ፡፡ ያኔ ዐማራነት ያለበትን ትክክለኛ ምስል ታያለህ፡፡ የእኔ የቤት ሥራ ምንድን ነው? ብለህ ራስህን ጠይቅ፡፡ ያኔ መማር ለዐማራ ወጣቶች ምንም እንደማይፈይድ ትገነዘባለች፡፡

ባለፈው ዓመት የተመረቁ የዐማራ ወጣቶች የትኛው ፋብሪካ ተቀጠሩ? ሰንቶች ሥራ ያዙ? ትምህርት ቤት የተመረቁ ዐማሮች ምንድን ነው ተስፋቸው? የትኛው የሥራ እድል ተመቻችቷል? ስንቶች ዩንቨርሲቲ ተመርቀው በአርብ አገር የማዕድ ቤት ሠራተኛና የግመል ጠበቂ ሆኑ? ስንቶቹ ሲሰደዱ በግብጽና በሊቪያ በርሃዎች ቀሩ? ስንቶቹ በሜድትራኒያንና ቀይ ባሕሮች የዓሣ ነባሪ ቀለቭ ሆኑ? ስንቶች ዐማራ በመሆናቸው ምክንያት በወያኔ ተገደሉ? የዐማራ ሕዝብ ስቃይ ምን ያክል ነው? መጨረሻውስ መቼ ነው? ይህን ይስቃይ ማን ያስወግደዋል?
እነዚህ ጥያቄዎች ደጋግመን ማሰብ አለብን፤ የቤት ሥራችን ይህ ነው፡፡ በወረቀት የሚሠራ አይደለም፡፡ በብዕር ሳይሆን በደም የሚጻፍ ነው የእኛ የቤት ሥራ፡፡ ጀግና ይወለዳል፤ ጀግና ይፈጠራል፡፡ የዐማራን ሕዝብ ነጻነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማረጋገጥ የዚህ ትውልድ የቤት ሥራ ነው፡፡ ሁሉም የዐማራ ወጣት፣ በዩንቨርሲቲም በኮሌጅም፣ በመሰናዶም፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ያሉ ተማሪዎች የቤት ሥራ ይህ ነው፡፡ የቤት ሥራ በአንድ ሳምንት አያልቅም፡፡ የጊዜው እርዝመት በትውልዱ ቁርጠኛነት ይወሰናል፡፡ 42 ኪሎ ሜትርን የፈጠነ በ2፡00 ሲጨርሰው የዘገየ ደግሞ ሳምንት ሊፈጅነት ይችላል፡፡ እጣ ፈንታችን በጠላቶቻችን የሚወሰንና እነሱ ሲፈልጉ የሚያስሩን፣ ሲፈልጉ የሚገድሉን፣ ሲፈልጉ የሚያሳድዱንና በሉ ያሉንን የሚያናግሩን ከሆነ እንዳለን አንቆጠርም፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ ይህ ነው፡፡ ከዚህ የሰው በታች (ዲሂውማናይዚንግ) ከሚያደርግ አስከፊ ሕይወት ነጻ መውጣት አለብን፤ ሌላ ምርጫ የለንም፡፡

የእኛ አባቶች ማንን ወለዱ? እሳት እሳትን ወይም አመድን ይወልዳል፡፡ እኛስ? የእሳት ልጅ እሳት ወይስ አመድ? የዐማራ ነበልባል ወጣት እንደብረት ቀልጦም የሚጠነክር ወይስ እንደ እንጨት ነዶ የሚያምድ? የቤት ሥራ ነው፡፡ በግል ከተሠራ ሁሉም ተማሪ እኩል ማርክ አያገኝም፡፡ እኩል ማርክ የምናገኘው በቡድን የቤት ሥራውን ስንሠራ ብቻ ነው፡፡ የቤት ሥራው የቡድን ነው፡፡ ቡድኑ ደግሞ ለሁለት ወይም ለሦስት ሰዎች አይደለም፤ 40 ሚሊዮኑ የዐማራ ሕዝብ የጋራ የቤት ሥራ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s