ርዕዮተ ዓለም የተጫነው ፌደራሊዝማችን [ደረጀ ይመር]

ethnic-federalism-in-ethiopiaየ1987 ሕገ መንግሥት ይዞት ከመጣው ሥር-ነቀል ለውጥ አንዱ በአሃዳዊ አገዛዝ ሥር ስትባትት ለኖረችው ሃገራችን፣ ፀጉረ ልውጥ አስተዳደራዊ መዋቅርን ማስተዋወቅ ነበር፡፡ ይህ ዘርን ማዕከል ያደረገ ፌደራላዊ አወቃቀር /Ethnic federalism/ የታነጸበት ሕገ-መንግስት፣ ከምዕራባውያን ባለ ብዝሃ ባህል ዲሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም ይልቅ ለቀድሞው ሶቭየት ኅብረት የሶሻሊስት ሕገ-መንግሥት በእጅጉ የቀረበ ነው፡፡ ለዚህም ዋቢ ማጣቀሻ ይሆን ዘንድ ሕገ-መንግሥቱ በተደላደለባቸው አንጓ ጭብጦች ላይ የትኩረት አቅጣጫን ማሳረፍ በቂ ይሆናል፡፡

ፌደራላዊ አወቃቀር በአንዲት ሉአላዊ ሀገር ላይ ሲዘረጋ፣ ሁለት ተጻራሪ ጽንፎችን ከቁጥር ጥፎ ነው፡፡ አንደኛው የሕዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነትን የበለጠ የተሳለጠ ለማድረግ በሚል እሳቤ /coming together/ ቅቡልነትን የሚያገኝ ሲሆን ሌላኛው ሀገርን ከመበታተን ለማትረፍና የሕዝቦችን የእርስ በእርስ ትስስር በአዲስ አተያይ ለመቀየድ ታሳቢ ተደርጎ የሚተገበር /holding together/ ፌደራላዊ አወቃቀር ነው፡፡ ቀዳሚው ለምዕራባውያን፣ የኋለኛው ደግሞ የሀገራችንን ፌደራላዊ አወቃቀር በግብር እንደሚመስል በዘርፉ የተሰማሩ ልሂቃን ያስረዳሉ፡፡
የፌደራል ስርዓቱ መሬት ወርዶ በተግባር ላይ ከዋለበት ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ብሥራትም ሆነ ፈተናን ይዞ መምጣቱ አልቀረም፡፡ በታሪክ ሂደት ውስጥ ማንነታቸው በፈጠረባቸው ልዩነት የተነሳ ወደ ዳር ተገፍተው የኖሩ ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት የቋንቋ ነፃነት/lingustic Autonomy/ ማጎናጸፉ እንደ ብሥራት የሚቆጠር ቢሆንም፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ፌደራላዊ አወቃቀሩ ላይ ታሳቢ መደረግ የሚገባቸው ነባራዊ ኹነቶች ቸል በመባላቸው የተነሳ ህልውናችንን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ተግዳሮቶች ጋር ፊት ለፊት እየተላተምን እንገኛለን፡፡
በፌደራላዊው ሥርዓት ዝርጋታ ወቅት መልከአ ምድራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነልቦናዊ ዝምድናዎች ፊት ተነስተው ቋንቋ  ብቻ ነው እንደ ዋንኛ አማራጭ የተወሰደው፡፡ በእዚህም የተነሳ  በሀገራዊ ብሔርተኝነት ኪሳራ ክልላዊ ማንነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎመራ ሊሄድ ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም መለያ ጠባዮች
አወዛጋቢው የብሔር ብሔረሰብ ጉዳይ
በስታሊን አፍላቂነት ለፍሬ በቅቶ የነበረው የቀድሞ ሶቪየት ኅብረት ሕገ-መንግሥት የታነጸበት ስነልቦናዊ ቅኝት የእኛው ሕገ-መንግሥት ተጋርቶታል ከሚያስብለው አንዱ የብሔር ብሔረሰቦችን የአርስ በእርስ ግንኙት የሚመረምርበት የታሪክ መነጽር በአንድነት መግጠሙ ነው፡፡ ሕገ-መንግስታችን እንደ ስታሊኑ የሶቪዬት ኅብረት ሕገ-መንግስት የሚንደረደርበት ታሪካዊ ዳራ ሀገራችን ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች እስር ቤት እንደነበረች በማብሰር ነው፡፡ ይህም መንደርደሪያ ሉዓላዊ ስልጣንን ለብሔረሰቦች ጠቅልሎ  በማሸከም ይደመደማል፡፡ አንቀጽ ስምንት፣ ንኡስ አንቀጽ አንድ ላይ፣ ይህንን ስልጣን በግልጽ ሰፍሮ እናገኘዋለን፡-
“የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች  የኢትዮጵያ ሉአላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡”
ከግል መብት ይልቅ ለቡድን መብት የይለፍ ፍቃድ የሚሰጡ አንቀጾች በሕገ-መንግስቱ ውስጥ መመልከት ብርቅ አይደለም፡፡ የቡድን መብት በግል መብት መቃብር ላይ አበባ ያኖራል፡፡ “እንኳን የበቀልኩበት ዘር ጦቢያም ትጠበኛለች” ለሚል ተሟጓች ዜጋ፣ ሕገ-መንግስቱ ፊት አይሰጥም፡፡ ከእዚህም በተጨማሪ በሜትሮፖሊቲያን ከተሞች ውስጥ ለሚኖሩ ሁለትና ሶስት ብሔር ላላቸው ዜጎች የሚተወው ኩርማን ሥፍራ ማግኘት የሚታሰብ አይሆንም፡፡ የብሔር ማንነት ከሁሉም ማንነት ልቆ ሕገ-መንግሥቱን ተዋርሶታል፡፡
ለመሆኑ ብሔር ማለት ምን ማለት ነው?
በሀገራችን የብሔረሰብ ነፃነት ጥያቄ ገዥ ሆኖ ብቅ ያለው በ 1960ዎች የተማሪዎች እንቅስቃሴ እንደነበር ከታሪክ ድርሳናት እንረዳለን፡፡ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የፈጠረው መነቃቃት ብረት አንስተው ወደሚታገሉ ሽምቅ ተዋጊዎች ተጋብቶ፣ በሒደት አጠቃላይ ፖለቲካዊ ቁመናቸው በእዚሁ ረግረግ ውስጥ ተውጦ ሊቀር ችሏል፡፡ ገዢውን የፖለቲካ ፓርቲ ጨምሮ በተቃዋሚነት የሚሰለፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀድመው የሚያነሱት አጀንዳ ከብሔር ማንነት ጋር የተቆራኙ ርዕሰ ጉዳዮችን እንደሆነ ከአደባባይ የተሰወረ ሀቅ አይደለም፡፡
ብሔርን የማርክሲዝም ሌኒንዝም መዝገበ ቃላት በእንዲህ መልኩ ነው የሚያብራራው፡
በታሪክ ሂደት ውስጥ የተከሰተ የሰዎች ማኅበረሰብ ነው፡፡ አንድ ብሔር በመጀመሪያ ደረጃ የሚለየው ባሉት የወል ቁሳዊ የኑሮ ሁኔታዎች ነው፡፡ በአንድ መልክ አምድራዊ ክልል ውስጥ መኖር፣ በኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች መተሳሰር፣ በአንድ ቋንቋ መጠቀም፣ በጋራ ታሪካዊ ሒደት ውስጥ የወል ሥነ-ልቦናዊ ገጽታዎችና ባህላዊ አመለካከቶች መከሰት የብሔር መሠረቶች ናቸው፡፡
በአሁኗ ኢትዮጵያ በአንድ ክልል ውስጥ የተሰባሰቡትን ሕዝቦች በታሪክ፣ በስነ-ልቦና፣ በመልከአ ምድራዊ ኩታ-ገጠምነትና በኢኮኖሚያዊ ትስስር መለኪያ ከገመገምናቸው ከላይ ከሰፈረው የብሔር መለኪያ ምንአልባትም አንዱን ብቻ ነው ሊያሟሉልን የሚችሉት፡፡ ለአብነት ያህል በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪነቱ፣ በአማራ ክልል ሥር የተቀነበበው ሕዝብን እንመልከት፡- ታሪክ እንደሚነግረን ከሆነ የሸዋ አማራ ከወሎ አማራ ወይም ከጎንደር አማራ  ይልቅ ከሸዋ ኦሮሞ ጋር የተሳሰረ ስነ-ልቦና ነበረው፡፡ አጤ ምኒሊክ ሀገር ለማቅናት ወደ ደቡብ ሲዘምቱ፣ የጎንደርና የወሎ ባላባቶች አጤው እንደወጡ እንዲቀሩ የሚመኙትን ያህል፣ ሀገር በማቅናቱ ሂደት ላይ ከአጤው ጎን በመሰለፍ ግምባር ቀደም ተሳታፊዎቹ የሸዋ ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡
የሸዋ አማራና የሸዋ ኦሮሞ በስነ-ልቦና፣ በታሪክ፣ በመልክአ ምድራዊ ኩታ-ገጠምነትና በኢኮኖሚዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ሲመዘኑ እጅግ የተዋሀዱ ሕዝቦች ናቸው፡፡ የሸዋ አማርኛ ተናጋሪ ከጎንደር አማርኛ ተናጋሪ ጋር በአንድ ክልል ውስጥ ሊካተት የቻለው ከመለኪያዎቹ መካከል በቋንቋ ማንነት ብቻ ነው፡፡ የቋንቋ ማንነት ደግሞ መገለጫው ዘውግ /ethnicity/ አንጂ ብሔር እንዳልሆነ የስነ-ማኅበረሰብና ፖለቲካ ልሂቃን ያብራራሉ፡፡
አብዮታዊ ዲሞክራሲ
የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም የእኛ የእትዮጵያዊያን መገለጫ ከሆነ ግማሽ ክፍል ዘመን ደፈነ፡፡ ከ1960 መባቻ እስከ ቆምንበት ዘመን የርዕዮተ ዓለሙ ተጽእኖው በተለያየ ቅርጽ ሲደባብሰን ኖሯል። አምባገነናዊው የደርግ አገዛዝ አፈር ከለበሰበት 1983 ዓም አንስቶ የርዕዮተ ዓለሙ ቅርጽና ይዘት መልኩን እየቀያየረ፣ የፖለቲካ አገዛዙን እንደተጣባው ቀጥሏል። ለእዚህም ማሳያ  አንዱ ገዢው ፓርቲ የሚመራበት  ከማርክሲዝም ሌኒንዝም የተዋሰው አብዮታዊ ዲሞክራሲ መርህ ዋቢ ምስክር ይሆናል፡፡
አብዮታዊ ዲሞክራሲ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ሕዝብ የተበሰረው በ1917 በራሺያ ቦልሺቪክ አብዮት ወቅት  ኢቪስቲያ በሚባል ተነባቢ ጋዜጣ  ላይ ነበር። ይህ ርዕዮተ ዓለማዊ ቅኝት ከካፒታሊዝም ወደ እውነተኛ ሶሻሊዝማዊ ስርዓት ለመሸጋገር በእነ ሌኒን አታጋይ ፓርቲ /ቫንጋርድ ፓርቲ/ አማካኝነት እንደ ብቸኛ አማራጭ የተወሰደ  መርህ ነበር። ርዕዮተ ዓለማዊው ቅኝቱ፣ ከ1983 መንግሥት ለውጥ በኋላ በሀገራችን ፖለቲካዊ ምህዳር ላይ የፊት አውራሪነት ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
ከ1983 የመንግሥት ለውጥ ማግስት ዋንኛ ጥያቄ ሆኖ ብቅ ያለው፣ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ምን አይነት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ይመጥናታል የሚል አጀንዳ ነበር፡፡ ከ 80% በላይ በግብርና በሚተዳደር ሕዝብ ላይ የምዕራባውያንን የሊብራል ዲሞክራሲ የሚሸከም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ንጣፍ ማግኘት የሚታሰብ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ስለዚህ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ያካተተ፣ ኢትዮጵያዊ ዲሞክራሲ ይዘርጋ የሚል ውይይት  ለሥርዓቱ ቅርበት ካላቸው ምሁራን ጋር ይደረግ ጀመረ፡፡
ይህም ውይይት ውሎ አድሮ በሶስተኛው ሞገድ /ሰርድ ዌቭ/ መጽሐፍ የሚታወቁት ጉምቱ ልሂቅ ፕሮፌሰር ሀንቲንገተን አማካሪነት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከኢትዮጵያ ምድር ላይ ሊተከል ችሏል። የኢትዮጵያ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከራሽያው አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚለይበት ዋንኛ ጠባይ አንዱ መድብለ ፓርቲን በሕገ-መንግሥት ላይ በይፋ መፍቀዱ ነው፡፡ ይህ አይነት አንቀጽ በቀድሞ ሶቪየት ኅብረት ሕገ-መንግሥት ላይ አልተካተተም ፡፡
የአብዮታዊ ዲሞክራሲው ዋንኛ አስኳል መርህ የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ነው። በመርሁ መሠረት የፓርቲው ላዕላይ ምክር ቤት የሚያወጣው ማንኛውም ውሳኔ እስከ ታች ቀበሌ አመራር ድረስ ተፈጻሚ ሊሆን ይገባል። እዚህ ጋ ነው የክልሎች ሥልጣንና የፓርቲ ስልጣን መደበላለቅ የሚመጣው።
ሕገ-መንግሥቱ የሰጣቸውን ሥልጣን ለሚሻማ ፖለቲካዊ አሰራር ተገዢ እንዲሆኑ የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ ግድ ይላል። በእዚህም ምክንያት የፓርቲ ርዕዮት ዓለምና ሕገ-መንግሥታዊ አሠራር የሚለይበት ቀጭን ድንበር ውሉ እየጠፋ፣ የክልሎችን ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን ከፈተና ላይ ሲጥለው በተለያዩ አጋጣሚዎች ይስተዋላል፡፡
የፌደሬሽን ምክር ቤት ሚና
የ1987 ሕገ መንግሥት የወለዳቸው የተወካዮች  እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ሕግ የማውጣት ሥልጣን ለየቅል ነው፡፡ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት፣ የሕግ አውጪነት ሥልጣንን በበላይነት ጠቅልሎ የያዘው የተወካዮች ምክር ቤት ብቻ ሲሆን የፌደሬሽን ምክር ቤት በሕግ አውጪነት ሥራ ውስጥ የሚሳተፍበት አሠራር የለም፡፡ ይህ አሰራር ፌደራላዊ ሥርዓትን በሚከተሉ ምዕራባውያን ሀገራት ላይ ልዩ ገጽታ ነው ያለው፡፡ ለአብነት ያህል የአሜሪካን ሕገ-መንግሥት ብንወስድ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤቱ /ሴኔቱ/ ከተወካዮች ምክር ቤት/ኮንግረስ/ ጋር በሕግ አውጪነት ረገድ ያለው ሚና እኩል ነው።  የፕሬዝዳንቱን ቪቶ ፓወር/ውሳኔን የማጠፍ ስልጣን/ እንዳይጠቀም ሁለቱም ምክር ቤቶች ከ 2/3 ድምጽ በላይ ወስነው ካሳለፉት ፕሬዝዳንቱ ውሳኔውን የመሻር ስልጣኑ ያከትማል። ስለዚህ ሴኔቱ የአግድሞሽ የቁጥጥር ሥልጣን/checks and balance/ ላይ ያለው ተሳትፎ ልክ እንደ ኮንግረሱ መሳ ለመሳ በሆነ ረድፍ ነው የሚቀመጠው፡፡
የእኛ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ግን ሕገ-መንግስትን ከመተርጎምና በክልሎች መካከል የሚፈጠር ግጭትን ከመፍታት በዘለለ ልክ እንደ አሜሪካው ሴኔት የቁጥጥር  ሥልጣን ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አይችልም፡፡ አንቀጽ 48 እንዲህ ይላል፡-
The constitution provides that where the concerned states fail to reach an agreement on border related issues, the House of Federations shall decide such disputess on the basis of settlement patterns and the wishes of the peoples concerned
በአጠቃላይ ፌደራላዊው ሥርዓት በመርህ ደረጃ ሊከልሳቸው የሚገቡ በርካታ ኹነቶች እንዳሉት እሙን ነው፡፡ በተለይ የርእዮተ ዓለምን ጣልቃ ገብነት የሚሸብቡ አንቀጾችን በሕገ-መንግስቱ ላይ በሪፈረንደም ወይም ከዜሮ ድምር የፖለቲካ ስሌት ነጻ በሆነ ውይይት አማካኝነት በማካተት፣ ራስን በራስ የማስተዳደሩ ሥልጣን የበለጠ ጥርስ እንዲኖረው ማድረግ ከገዢው ሥርዓት የሚጠበቅ ቁርጠኝነት ይሆናል፡፡

ምንጭ   _   አዲስ አድማስ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s