የሃረር ክልል፤ ሁሉም እኩል የሆኑባት ሳይሆን አማርኛ ተናጋሪዎች የተገፉበት ክልል #ግርማ_ካሳ

ሕዳር 29 ቀን 2009 የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በሚል በታሪካዊቷ የሃረር ከተማ በዓል ተዘጋጅቶ ነበር። በዝግጅቱ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ንግግር አድርገዋል። ይህ ዝግጅት ለአሥራ አንደኛ ጊዜ ሲሆን በሃረር የተከበረው፣ በአሉን የሕዝቢች እኩልነት, አብሮ የመኖር የመቻቻል እሴቶችን ለማጎልበት የታሰበ እንደሆነ የገለጹት፣ ጠ/ሚኒስትሩ አሁን ያለዉን ሕገ መንግስት የሕዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ ሲሉም አሞግሰዉታል።ቢሆን ደስ ባለን ነበር፤ ግን ሜዳ ላይ ያለው ሁኔታ ካሉት በጣም የተለየ ነው።

የሃረር ከልል በኢትዮጵያ ካሉ ዘጠኝ ክልሎች መካከል አንዷ ስትሆን፣ እንደሌሎች ክልሎች የራሷ ሕገ መንግስት የክልሉ ሕግ መንግስት ውስጥ በርካታ አንቀጾች ተቀምጠዋል። ከዚህ ከሃረር ክልል ሕግ መንግስት ሶስት ነጥቦችን ብቻ በማንሳት፣ አቶ ሃይለማሪያም እንዳሉት አሁን ያለው ፌዴራላ አወቃቀርና ፣ በሕዝቦች መካከል መቻቻል፣ መከባበና አብሮነት እንዲኖር ያደረገ ሳይሆን በአንድ “አማራ” በሚባለው እና አማራ ባይሆንም አማርኛ ተናጋሪው ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ለማሳየት እንሞክራለን።
በ1994 የሕዝብ ቆጠራ መሰረት የሃረሬ ክልል ህዝብ 131139 ነበር። በ2007 ቁጥሩ ወደ 183415 አድጓል። በ1994 ቆጠራ ዉጤት መሰረት አፋን ኦሮሞ አንደኛ ቋንቋቸው የሆኑ 49% ሲሆኑ አማርኛ ተናጋሪዎች 37% ነበሩ። አደሪኛ ተናጋሪዎች 7%፣ ጉራጌኛ ተናጋሪዎች እና ሶማሌኛ ተናጋሪዎች 1% ነበሩ። በ2007 የሕዝብ ቆጠራ ዉጤት ፣ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች ከ49% ወደ 56% ቁጥራቸው ሲያድግ፣ አማርኛ ተናጋሪዎች የሃረሬ ክልል ነዋሪዎች 27% ፣ አደሪኛ ተናጋሪዎች 8%፣ ሶማሌኛ ተናጋሪዎች ደግሞ 3% ሆኑ።
የሃረሬ ክልል ሕገ መንግስት በአንቀጽ 6 ላይ የክልሉ የሥራ ቋንቋ አደርኛና ኦሮምኛ ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል። በዚህም ምክንያት በሃረር ከአደሬዎች ብዛታቸው በሶስት እጥፍ የሚበለጡ፣ የክልሉ አንደ ሶስተኛ የሚሆኑ አማርኛ ተናጋሪዎች በአማርኛ ከክልሉ መንግስት አስተዳደር አገልግሎት እንዳያገኙ የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው። ይሄ በሞራል፣ በፍትህ ፣ በፍትህ አንጻር ትልቅ በደል ነው።

የ1994 እና የ2007 የሕዝብ ቆጠራን ብንመለከት የአማርኛ ተናጋሪዎች በመቶ እጅ ሲታሰብ ቁጥራቸው ቀንሷል። ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ከ49% ብዛታቸው ወደ 56% ብዛት ሲያድግ፣ አማርኛ ተናጋሪዎች ግን ከ37% ወደ 27% ወርደዋል።፡ይሄ የሆነበት የራሱ የሆነ ምክንያት አለው። ስርዓቱ፤ አገዛዙ ሲስተማቲክ በሆነ መንገድ ይሄንን ማህበረሰብ ታርጌት ስላደረገ ነው። ብዙ አማርኛ ተናጋሪዎች የሚወዷት፣ የተወለዱባት፣ ያደጉባት ሃረር፣ አመች ስላለሆነች ከተማዋን ጥለው ወደ አዲስ አበባ ፣ ድረዳዋና አዳማ እየተፈናቀሉ ነው።

የሃረሬ ክልል ሕገ መንግስት መግቢያው ላይ “የሐረሬ ህዝብ ምንም እንኳን በምእተ ዓመታት ለሚቆጠር ዘመን ራሱን በራሱ ያስተዳድር፣ በራሱ ታሪክ ወግና ባህል ይኮራ የነበረ ቢሆንም፣ በ1886 ዓ.ም በተደረገበት ወረራ በነፍጠኛው ስርዓት ሥር ከመዉደቁም በላይ ይሄን ስርዓት ለማስወገድ በተለያዩ ጊዜያት ባደረገው ንቅናቄና ትግል ምክንያት ለግርፋት ለእስራትና ብሎም ለስደት በመዳረጉ በራሱ ክልል በቁጥር አናሳ መሆኑ የተነሳ ልዩ አወካከል ማስፈለጉን በመረዳት “ የሚል ተጽፎ እናገኛለን።

የሐረሬ ብሄረሰብ አባላት የሐረሬ ክልል 7% ብቻ ለመሆናቸውና ቁጥራቸው ለማነሱ የክልሉ ሕገ መንግስት ተጠያቂ የሚያደርገው በ1886 የተደረገው እና በአጼ ሚኒሊክ አሸናፊነት የተጠናቀቀዉን የጨለንቆን ጦርነት ነው። የክልሉ ሕገ መንግስት፣ ሃረሬዎች የራሳችው አስተዳደር እንደነበራቸውና ከጨለንቆ ጦርነት በፊት በአካባቢው ብዛት እንደነበራቸው ነው ለመግለጽ የሞከረው። ሰነዱ ለይቶ ግን ነፍጠኛ የሚለዉን የአማርኛ ተናጋሪ ማህበረሰብን ይከሳል።

የፌዴራልም ሆነ ሃረሬ ክልል ሕገ መንግስትና ፌዴራል አወቃቀሩ፣ አቶ ሃይለማሪያም እንዳሉት የሕዝቦችን እኩልነት, አብሮ የመኖር የመቻቻል እሴቶችን ለማጎልበት የታሰበ ሳይሆን፣ አማራ የሚባለውን እና አማርኛ ተናጋሪዉን ማህበሰብ አዎንታ ያላገኘ ፣ ይሄን ማህበረሰብ ሆን ብሎ ለማጥቃትና ለማዳከም ተብሎ የተወጠነ ነው የሚመስለው።

አንዱ ግዛት እስቲ አንባቢያን ይረዱ ዘንድ ስለ ሃረር ታሪክ ትንሽ አንዳንድ ሐሳቦችን ለማስቀመጥን እንሞክር።

ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች አገር ናት። በተለያዩ ጊዜ በአገራችን የተለያዩ መንግስታት፣ ስልጣኔዎች ነበሩ። አጼ የኑኖ አምላክን በ1287 አካባቢ ስልጣነ ጨብጠው የነበረ ጊዜ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ግማሹን ጅቡቲ፣ ሃረርጌን ሶማሌላንድ የመሳሰሉትን ያካተተ ጠንካራው የሙስሊም መንግስት የይፋት ሱልጣኔት ነበር።( “Sultanate of Yifat”)። ዋና ከተማዉም ዘይላ (አሁን ሱማሌላንድ ያለችው ወደብ) ነበረች።

በዚህ ወቅት፣ የይፋት መንግስት ግዛት ስር በነበረችው በሃረር አባድር ኡመር አልሪዳ የተባሉ ሼክ ከበርካታ ሌሎች የሙስሊም አስተማሪዎች ጋር በመሆን፣ ከየመን መጡ። በአካባቢው ከሚኖሩ የአርጎባ፣ የሃራላና የጋቱሪ አናሳ ብሄረሰቦች ጋር በመሆኑ በዚያ አካባቢ መኖር ጀመሩ። እንግዲህ የሃረሬ ነዋሪዎች መሰረታቸው ይሄ ነው።

በይፋት ሱልጣኔትና በደጋማው ኢትዮጵያ ክርስቲያን ነገስታት መካከል በተለያዩ ጉዜያት የተለያዩ ጦርነቶች ተደርገዋል። በወቅቱ የይፋት መንግስት ዋና ከተማ ሆና ታገለግል የነበረችው አሁን በሶማሌናድ የምትገኘው የዘይላ ወደብ ነበረች። በ1332 አጼ አምደጽዩን የይፋትን ሱልጣን አሸንፈው፣ ጀማላዲን ሱልጣን አድርገው ሾመው ተመለሱ። የይፋት መንግስት ለአጼ አምደጽዩን ገበሩ። ጀማላዲንን ተክተው የጀማላድኒ ወንድም ናስራዲን ሱልጣን ሆኑ። ከናስራዲን በኋላ የተተኩ የይፋት ነገስታት በማመጻቸው ጦርነቶች ይባባሱ ጀመር። በ1403 አጼ ዳዊት አንደኛ ዜይላ ድረስ በመዝለቅ ሱልጣን ሳአዲን ሁለተኛን ማርከው ይገድሏቸዋል። የሱልጣኑ ልጆች አምልጠው ወደ የመን ይሻሻሉ።

በዚህ ሁሉ ወቅት ሃረር በይፋት ሱልጣኔት ስር ነበረች። በ1415 ሳብራዲን ሁለተኛ ከየመን ተመልሰው ከሃረር ከተማ በስተደቡብ በነበረች ዳካር ተብላ ትታወቅ በነበረው ከተማ ሰፈረ። በዚህ ሁኔታ የይፋትን እስላማዊ መንግስት ተክቶ የአዳል እስላማዊ መንግስት ጀመረ።
የአዳል መንግስት ራሱን በራሱ ማስተዳደሩ ቢቀጥልም፣ በሱልጣን ሞሐመድ ኢብን ባድሌ እና በአጼ በእደ ማሪያም መካከል በተደረገው ስምምነት መሰረት፣ የአዳል መንግስት አመታዊ ግብር ያስገባ ነበር። የግዛቱ የኢኮኖሚክ ማእከል የሆነችው የዜይላ ኤሚር፣ ላዴይ ኡስማን፣ ግብር አልከፍልም ብለው አመጹ። ሱልጣኑ ላይ ጦርነት ከፍተው የዳካርን ክከተማ ተቆጣጠሩ። ረገብ ብሎ የነበረው በክርስቲያን ነገስታት እና በሙስሊም ገዢዎች መካከል የሚደረገው ጦርነት እንደገና ቀጠለ። ኤሚር ማህፉዝ የተሰኑ ጦረኛ የሙስሊም መሪ በ1500 የአጼ ናኦድን ጦር አሸነፉ። አጼው በጦርንቱ ላይ ተገደሉ። ሆኖም ግን በሌላ ጦርነት በ1517 አጼ ዳዊት ሁለተኛ (ኣጼ ልብነ ድንግል) ኤሚር ማህፉዝን ገደሉ።አንዱ እያሸነፈ.፣ ሌላው እየተሸነፈ ድደም መፋሰሱ ቀጠለ።
በ1554 ሱልጣን አቡበከር ኢብን መሐመድ፣ የአዳል መንግስትን መሪ ሆኑ። ሱልጣኑ ከሶስት መቶ አመታት በፊት ከየመን የመጡ እነ ሼክ እነ ሼክ አባድር ኡመር አሪዳ የሰፈሩባትን ሃረር የአዳል መንግስት ዋና ከተማ አደረጓት። ከተማዋን ከተራ መንደርነት ወደ ተደራጀ ከተማነት ለወጧት።

የአቡበከርን ስልጣን የያዘው በትክክለኛ መንገድ አይደለም በሚል፣ ኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም አልጋዚ (ወይም በተለምዶ ግራኝ መሐመድ ተብለው የሚታወቁት)፣ ይቃወማሉ። ከሱልጣኑ ጋር በተደረገ ጦርነት ሱልጣን አቡበከር ይሞታሉ። ግራኝ መሐመድ ወንድማቸውን ኡመር ዲንን ሱልጣን አድርገው ይሾማሉ። የአዳል መንግስት ሱልጣን የሆኑት ኡመር ዲን ቢሆን፣ የአካባቢው የመስሊም ጦር መሪ ሆነው፣ ከአዳል ግዛት አልፈው በመሄድ፣ ከተወሰኑ ቦታዎች በቀር ድፍን ኢትዮጵያን ማለት ይቻላል፣ ግራኝ መሐመድ፣ ለመቆጣጠር ቻሉ። ግራኝ መሐመድ በጦርነት ላይ ይሞታሉ።ግራኝን ተክተው ኤሚር ኑረዲን ሙጃሂድ የሙስሊም ጦር መሪ ሆነው ይቀጥላሉ። እንግዲህ እኝሁ ኤሚር ናቸው ጀጎል ተብሎ የሚታወቀው የሃረር ግንብ የገነቡት።

ከግራኝ ጋር ይደረግ በነበረው ጦርነት፣ አጼ ገላውዲዮስ ወደ ጎንደር አካባቢ ይሸሻሉ። ግራኝ ከሞቱ በኋላ የክርስቲያን መንግስታት ማዓከል ከሸዋ ወደ ጎንደር ዞረ። ዋና ከተማዋ ሃረር በሆነችው በአዳል ግዛት እና በክርስቲያን ነገስታት መካከል ይደረጉ የነበሩ ጦርነቶች ቀንሰው በኦሮሞ ተስፋፊዎችና በአዳሎች መካከል ሆነ ችግሩ። በሃረር ይገዙ የነበሩት ኢማም ሙሐመድ ጃሳ ከኦሮሞዎች በሃረር አካባቢ ተከታታይ ጥቃትና ጦርነት ይደረግ ስለነበር፣ ወንድሙን የሃረር እንደራሴ አድርገው የመንግስታቸዉን ዋና ከተማ ከሃረር ወደ አዉሳ (ወደ ሰሜን ራቅ ብሎ ከአፋር ድንበር ጋር ወደ ሚገኝ ቢታ) አዞሩ።

ኦሮሞዎች የሃረርን አካባቢ በስፋት መቆጣጠር ጀመሩ። ሆኖም ግን በግምቡ መካከል ይኖሩ የነበሩ የቀድሞ ነዋሪዎች፣ በአዉሳ ሥር ሆነው ለተወሰኑ ጊዜ ከቂዩ በኋላ፣ በቱርኮች የበላይ ጠባቂነት የሃረር ኤሚሬት (መንግስት) አቋቋሙ። አሊ ኢብንዳዎድ በ1647 የሃረር የመጀመሪያው ኤሚር ሆኑ። እስከ 1875 ዓ.ም ድረስ የኤሚር አሊ ልጆች በሃረር፣ በኦሮሞዎች ተከበውና ከኦሮሞዎች ጋር ተስማምተው መግዛት ቀጠሉ። ኦሮሞዎች ሙስሊም በመሆናቸውም ከአካባቢው ህዝብ ጋር ተደባልቆ መኖር አልከበዳቸውም።

በ1870ዎቹ ግብጽ ከቱርክ ነጻ ወጣች። በቱርክ ሥር የነበረችው ሃረርም በግብጾች ቀጥተኛ አገዛዝ ሥር ወደቀች። በ1884 እንግሊዝ መልሳ ግብጽን በመያዟና እንግሊዞችም የሃረርን አካባቢ ስለተዉ ሃረር እንደገና በማንም ስር ያልሆነች ነጻ ኤሚር ሆነች። ከሁለት አመት በኋላ አጼ ሚኒሊክ የነ አጼ ዳዊት አንደኛ እና የነአጼ አምደጽዩንን ኩታ በመቀጠል ወደ ሃረር አመሩ። ከሃረር ወጣ ብላ በምትገኝ የጨለንቆ ከተማ በተደረገ ጦርነት የሃረሩ ኤሜር አብዱላሂ ሞቱ። ራስ መኮንን ስዩም የሃረር አገረ ገዢ ሆነው መቀመጫቸውን ሃረር አድርገው መግዛት ጀመሩ። አጼ ሃይለስላሰእም በሀረር የተወለዱት አባታቸው ራስ መኮንን በዚያ ስለነበሩ ነበር። የአጼ ሚኒሊክ ወታደርም ሆነው ብዙ አማሮችን ኦሮሞዎች ከሸዋ በመምጣት በሃረርጌ ሰፈሩ። ራሳቸው ራስ መኮንን በአባታቸው ኦሮሞም ነበሩ።

እንግዲህ ከዚህ የምንማራቸው መሰረታዊ ቁም ነገሮች አሉ፡

– ሃረር የብቻዋ አስተዳደር ቢኖራትም በታሪኳ መጀመሪያ በይፋት፣ ከዚያ በአዳል፣ ከዚያም በቱርክና በግብጽ ሥር የነበረች ከተማ ናት። አዳልና ይፋት ደግሞ ለሸዋ ነገስታት ይገብሩ የነበረበት ሁኔታ ነው የነበረው። እርግጥ ነው ግብጾች ከሄዱ በኋላ፣ አጼ ሚኒሊክ እስኪቆጣጠሯት ድረስ ፣ ራሷን የቻለች ነጻ አስተዳደር ነበራት። ሆኖም ጊዜው ከሶስት አመት የማይበልጥ ነበር።

– እነ አጼ አምደጽዩን፣ አጼ ዳዊት የይፋትና የአዳልም መንግስታት ሲያስገብሩ፣ ግብር እስከከፈሉ ድረስ ራሳቸው በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ነበር ያደረጉት። አንዱ ያመጸ ሱልጣን ሲገድሉ፣ ሌላ ሙስሊም ሱልጣን ነበር ተክተው የሚሄዱት።

– በይፋት ፣ በአዳል እና በሃረር መንግስታት ታሪክ ከክርስቲያን ነገስታት ጋር የተደረገው ጦርነት እንደተጠበቀ ፣ በሙስሊሞች መካከል የተለያዩ ከፍተኛ ጦርነቶች ተደርገዋል። በተለይም ከግራኝ አህመድ ሞት በኋላ ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ እስኪመጡ ድረስ በሃረር አካባቢ ከክርስቲያን ነገስታት ጋር ጦርነቶች የተደረጉበት ሁኔታ አልነበረም፡

– አሁን አደሬዎች ወይንም የሃረሬ ብሄረሰብ አባላት በሃረር ለመቶ አመታት የኖሩ ናቸው። ሆኖም ግን ሃረር፣ በተለይም ከጀጎል ዉጭ፣ በኦሮሞዎች ቁጥጥር ስር በመሆኗ፣ ከኦሮሞዎች ጋር ሲነጻጸር ቁጥራቸው በጣም ሊዋጥ ችሏል። የሃረሬዎች ብዛት የቀነሰው በዋናነት በኦሮሞዎች መስፋፋት ነው። ታሪኩ ሃቁ ይሄ ሆኖ እያለ፣ ለአደሬዎች ቁጥር ማነስ የጨለንቆውን ጦርነት እንደምክንያት ማቅረብ ታሪክን ማዛባት ነው።

– የሃረሩ ኤሚር አብዱላሂ ለአጼ ሚኒሊክ አልገብርም ስላሉ እንጂ የጨለንቆ ጢርነት የተደርገው፣ አጼ ሚኒሊክ ጸረ-ሙስሊም ስለሆኑ፣ ወይንም ጦርነትን ስለሚፈልጉ አልነበረም። በጂማ ሌላ ገዢ ጂማ አባጅፋር የአጼ ሚሊሊክ ቡራኬ አግኝተው ነበር ሲገዙ የነበሩት።በሰላምና በስምምነት።

የሃረሬ ክልል ሕግ መንግስት እና የ2007 ሕዝብ ቆጠራ ውጤት ለማወቅ የሚከተሉትን ሊንክ ይመልከቱ፡

https://chilot.files.wordpress.com/…/harari-regional-state-…
http://catalog.ihsn.org/index.php/catalog/3601

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s