መሬት ሳትበይኝ ልብላሽ (ከይገርማል)

 

ወያኔወች ከትግራይ ጋር የሚካለሉትን የአፋርና የአማራ ለም አካባቢወችን መቆጣጠራቸው ሳያንስ ረጅም ርቀት ተጉዘው የጋምቤላንና የቤንሻንጉልን ለም መሬት በኢንቨስትመንት ስም ሕዝቡን ሳይቀር እያፈናቀሉ እየሸጡ እንደሆነ ስሰማ በታሪክ የማውቃቸው አንድ አባት ትዝ ይሉኛል:: በርግጥ እኒህ አባት የማንንም ሳይሆን የራሳቸው የነበረውን ሰፊ መሬት ነው እየሸነሸኑ የሸጡት::

ቀኛዝማች ሰውነቴ እልምነህ ይባላሉ፥ አጭር ቀጭን ወደጥቁር ያደላ መልክ ያላቸው። ተወልደው ያደጉት በዱሮው አጠራር በጎጃም ክፍለሀገር በደብረማርቆስ አውራጃ በስናን ወረዳ አሽመን እየሱስ በሚባለው የገጠር ቀበሌ ነው። የአርባው ዘር ወይም የወንበዴው ዘር በሚል ከሚታወቅ የዘር ሐረግ የሚመዘዙት “እኔን እኔን” በሚለው አባባላቸው የሚታወቁት ቀኛዝማች ሰውነቴ በአንደበተ ርቱእነት፥ በጫወታ አዋቂነትና በመብት ተሟጋችነታቸው በጎጃም ውስጥ ከሚጠቀሱ ስመጥር ሰዎች ውስጥ አንዱ ነበሩ። ቀኛዝማች ከሚታወሱባቸው መሀል ጥቂቱን አነሆ!

መሬት ሳትበይኝ ልብላሽ

ቀኛዝማች ጉልበታቸው ሳይዝል፥ ኣይናቸው ሳይፈዝ፥ ነጣቂ ሳይመጣ ነበር ትርፍ የተባለ ቤትና ቦታ ሸጠው ያጠናቀቁት። አብማ ተብሎ በሚጠራው የከተማው አካባቢ የሚገኘውን ትርፍ ቦታና መሬት ሲሸጡ “መሬት ሳትበይኝ ልብላሽ” እያሉ ነበር።ደርግ ወደስልጣን መጥቶ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት በአዋጅ ሲወርስ ሰውነቴ የቀራቸው የሚኖሩበት ቤት ብቻ ነበር። ተበድሮም ተገድሮም ለመጦሪያ ይሆነኛል ብሎ ሰርቪስ ቤት ሰርቶ ያከራየ ሳይቀር በትርፍ ቤት ስም ሲነጠቅ ሰውነቴ ትርፍ የተባለ ቤትና ቦታቸውን ሙልጭ ኣድርገው ሸጠው ባጠራቀሙት ገንዘብ በሰላም እየተጦሩ ነበር። እኒህን አባት እንደነብይ ያያቸውና በአድራጎታቸው የተገረመ ቢኖር የሚፈረድ ኣይሆንም። ወያኔስ እንዲህ አገር ምድሩን እየሸነሸነ እየሸጠ ያለው ምን ቢታየው ይሆን!

ቢጨንቀኝ ነው

የ፩፱፻፪፰ ዓመተ ምህረቱን የጣሊያን ወረራን ተከትሎ የጣሊያን ጦር ደብረማርቆስ እንደገባ የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ ባላባቶችን እና ታዋቂ ሰዎችን ሰብስቦ መግደል ነበር:: በአንዲት የጭንቅ ዕለት በውሰታ ሜዳ ላይ ተሰብስበው ሞትን ሲጠብቁ ከነበሩት የጎጃም ታላላቅ ሰዎች አንዱ የሆኑት ቀኛዝማች ሰውነቴ አንድ ያልታሰበች ቃል ከሞት ልትታደጋቸው በቃች:: “እኔን” የምትለዋን ቃል ደጋግመው ሲናገሩ የሰማ አንድ የጣሊያን ወታደር “ይኸ ሰው ምንድን ነው የሚለው?” ሲል አንዱን አስተርጓሚ ይጠይቀዋል:: ምንም ቢሆን ታዋቂ ሰው ስለሆኑ አስተርጓሚው በክብር “ጌታየ ምንድን ነው የሚሉት እያለ ነው ነጩ እየጠየቀዎት ያለው” ሲላቸው ፈጠን ብለው መላ አካላታቸውን በአይኖቻቸው እየፈቀዱ  ” እኔን እኔን! አይ እጅ! አይ እግር! አሁን ይኸን ገላ አፈር ሊበላው!” ሲሉ ያጉተመትሙና ቀጥለው በቁጭት “ከሁሉ ሁሉ የሚቆጨኝ ያንን ዳኛቸው የሚባል ሽፍታ ሳላስይዝ መሞቴ ነው” በማለት ይናገራሉ::

ዳኛቸው ማለት በዕድሜ ከርሳቸው የሚያንስ የናታቸው ወንድም የሆነው የስናኑ ፋኖ ፊታውራሪ ዳኛቸው ተሰማ ነበር:: ይህ ሰው ደግሞ በጣሊያኖች ከሚፈለጉት የጎጃም አርበኞች ውስጥ አንዱ ነበር:: ቀኛዝማች የተናገሩትን ከአስተርጓሚው አንደበት የሰማው የጣሊያን ወታደር ብርሀን ይዞ የመጣውን የጣሊያን ጦር በመውጋት ችግር እየፈጠረ ያለው ዳኛቸው እንዲያዝ የሚረዱ ከሆነ እንደሚሾሙ እንደሚሸለሙ ደጋግሞ ቃል በመግባት ወደ ማባበል ይገባል::

ቢያንስ ለአንድ ቀን ነፍሳቸውን ለማቆየት እንዲችሉ የዕድል በር ስለተከፈተላቸው በውስጣቸው የአሽመኑን እየሱስ ሳያመሰግኑ አይቀሩም:: “ምንም ችግር የለም” አሉ ፈጠን: ቆፍጠን ብለው:: “ሰተት አድርጌ ወስጀ እጁን አስጨብጣችኋለሁ:: ከዚያ በኋላ ብሞትም አይቆጨኝ” አሉ በእልህ እየተንቆራጠጡ::

የሰውነቴን ንግግር የሰሙ አብረዋቸው ተቀምጠው ሞታቸውን ይጠብቁ የነበሩት ትላልቅ ሰዎች: አጎታቸውን ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት የቆረጡ ከሀዲ አድርገው ሳይታዘቧቸው: አይንህ ላፈር ሳይሏቸው አይቀርም:: እሳቸው ግን በውሳኔያቸው ጸንተው “በሉ ፍጠኑ እንሂድ!” በማለት ያን የሞት አውድማ ጥለው የጣሊያንን ጦር እየመሩ ወደካብ ጊዮርጊስ ገሰገሱ::

ከገደማላ ጀምሮ እስከመንክርባዶ ድረስ የተዘረጋው በረባዳ ቦታ ላይ የሚገኘው “ገማና” ተብሎ የሚጠራው ጥቅጥቅ ያለው ደን በመሀሉ የሽገዛ ወንዝ የሚፈስበት ሲሆን ለወስፋት መግደያ የሚሆን አጋሙ: ቀጋው: ኮሽሙ: እንጆሩ: አሽቃሞው የተትረፈረፈበት ነበር:: ለነገሩ ወፍ የበላውን ሁሉ ቢበሉትስ ምን ይላል! በዚህ ደን ውስጥ አውሬ ብቻ ሳይሆን በተለያየ ምክንያት የሸፈቱ ሰዎችም ተደብቀው ይኖሩበታል:: ገማና እየኖሩ ጦም ማደር የለም:: ሚዳቋው: ድኩላው: ቡኸሩ ሞልቷል:: ለአደን ተብሎ ሩቅ መሄድ ሳይስፈልግ ከአንድ ቦታ ድምጽን አጥፍቶ በአይን ማማተርና ጆሮ መቀሰር ብቻ በቂ ነው:: አንዳንድ ጊዜም ሁሉም በየራሱ ሀሳብ ሲጥደፈደፍ ሳይታሰብ መጋጨት ሊኖር ወይም ተጠላልፎ መውደቅም ሊያጋጥም ይችላል:: ያሁኑን አያድርገውና ገማና ለመዋያ ብቻ ሳይሆን ቢከርሙበትም ለሆድ የማይታሰብበት ምን እበላ! የማይባልበት ቦታ ነበር::  ዳኛቸው ይገኝበታል ተብሎ የተገመተው ቦታ ይኸው ገማና ነበር::

ጦሩ በቀኛዝማች ሰውነቴ እየተመራ ገማና ሲደርስ የአርበኞች ሰራዊት በአካባቢው አልነበረም:: ሽፍቶቹ ለቀውት ከሄዱት ቦታ ላይ የተለያየ ትዕይንት ይታያል:: በየቦታው ተቆፍሮ ከተሰራው ምድጃ ከሚነደው እሳትና በብረትምጣድ እየበሰለ ካለው ምግብ የሚወጣው ጭስ ይትጎለጎላል:: ተገፈው ያለቁ እና ገና በመገፈፍ ላይ የነበሩ ፍሪዳወች እዚያም እዚያም ይታያሉ:: አካባቢው ዝርክርክ ያለ በመሆኑ የአርበኞች ጦር በድንገት ተነስቶ ከአካባቢው ለመሰወሩ ተጨማሪ ማስረጃ የሚያስፈልግ አልነበረም:: ወደቦታው የተንቀሳቀሰውን የጣሊያን ጦር ያየ የአካባቢው ሰው ለአርበኞች እንደተናገረ በሁሉም ዘንድ የተገመተ ቢሆንም ይህንን ያደረጉት ራሳቸው ቀኛዝማች ሰውነቴ ይሆናሉ ብሎ ያሰበ ግን አልነበረም::

ወደገማና ጉዞ ሊደረግ ዝግጅት በሚደረግበት ጊዜ ቀኛዝማች ምን ማድረግ እንዳለባቸው እያውጠነጠኑ ነበር:: ነፍሳቸውን ለማዳን ብለው ለሀገሩና ለወገኑ እየተዋደቀ ያለውን የብዙ አመት ታናሻቸው የሆነውን የእናታቸውን ወንድም አንገቱን ለገመድ አሳልፈው ለመስጠት የሚታሰብ ነገር አልነበረም:: በድንገት አንድ የሚያውቁት ሰው ላይ አይናቸው ሲያርፍ ነፍሳቸው በደስታ እፎይ አለች:: ይህችን የጭንቅ ጊዜ አለፍኋት ማለት ነው ሲሉም አሰቡ:: አመች ጊዜ ጠብቀው ያን የሚያውቁትን ሰው በአይናቸው ይጠቅሱና “በፍጥነት ገስግሰህ ዳኛቸው ዘንድ ገማና ሂድና የሆነውን ሁሉ ንገረው:: ነፍሴ የተረፈችው አንተን ለማስያዝ እንደምፈልግ ስለነገርኋቸው ነው:: ወደአንተ ልንመጣ ዝግጅት ላይ ነን:: አብስላችሁ ልትበሉ ስትሉ ድንገት እንደደረስንብህ አድርገህ ጥፋ:: እየመጣ ያለው ጦር ከባድ መሳሪያ የታጠቀ ጦር ነው:: ለእኔ ስትል ምንም ነገር ሳታደርግ ከአካባቢው ተሰወር:: እሱን እንደሆነ ነግ ከነገ ወዲያ ታገኘዋለህ:: ለዛሬው እኔን አትርፈኝ:: ብለህ ንገረው” ብለው ሰውየውን ከላኩ በኋላ ነበር ተረጋግተው ጦሩን እየመሩ ጉዟቸውን በደስታ የጀመሩት::

ይህንን ተልዕኮ ለማስፈጸም ጦሩን በበላይነት የመሩት የጣሊያን ወታደራዊ መኮንኖች ገማና ላይ ባዩት ሁኔታ ቀኛዝማች ሰውነቴ ሀቀኛ ናቸው ብለው በማመናቸው በነጻ ለቀቋቸው::

ከ5 አመቱ የአርበኝነት ውጊያ በኋላ የጣሊያን ጦር በኢትዮጵያ አርበኞችና በእንግሊዝ ሰራዊት ጥምር ኃይል ተመትቶ ሲወጣ አጼ ኃ/ሥላሴ ወደአዲስ አበባ የተጓዙት ደብረማርቆስ ለአንድ ወር ያህል ከቆዩ በኋላ ነበር:: ቀኛዝማች ሰውነቴ ከንጉሱ ጋር ቀደም ሲል ጀምሮ ቀረቤታ ስለነበራቸው ንጉሡ ደ/ማርቆስ በቆዩበት ጊዜ ሁሉ አልተለይዋቸውም::

ጉልት ከልጅ ልጅ የሚተላለፍ በየደብሮች (የገበሬ ቀበሌወች) የባላባቶች የአካባቢ አስተዳደር አካል ነው:: ቀኛዝማችን የጣሊያን የጦር አዛዦች በምህረት ሲለቋቸው የጣሊያን መንግሥት ሽህ አመት ይግዛ ብለው መርቀዋል በሚል በጠላቶቻቸው የተቀናበረ ክስ ስለተመሰረተባቸው የወቅቱ የጠ/ግዛቱ ገዥ ከጉልታቸው ነቀሏቸው:: ይህን ውሳኔ ተቀብሎ እሽ ብሎ መኖር ለቀኛዝማች ፈጽሞ የማይሞከር ነበር:: ከአያት ቅድመአያት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣን እርስተጉልት አሳልፎ ሰጥቶ አርፎ መቀመጥ የሚታሰብ አልነበረም:: ሰውነቴ ካላግባብ ተወስዶብኛል ያሉትን እርስትና የተነካባቸውን ክብር ለማስመለስ አዘናግተውና አመች ጊዜ ጠብቀው ለአቤቱታ ወደሸዋ የተሻገሩት በዚህ ምክንያት ነበር::

በማንኛውም ጊዜ ቤተመንግሥት ለመግባት ፈቃድ ያላቸው ሰውነቴ ካላንዳች ችግር ከጃንሆይ ዘንድ ቀርበው እንደደንቡ ለጥ ብለው ሰግደው ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ ቁጭ ብለው ጨዋታ ይጀምራሉ:: ንጉሱ ቀኛዝማቹ የመጡበትን ጉዳይ ቢጠረጥሩም የሆዳቸውን በሆዳቸው አድርገው “ልትጠይቀን ነው የመጣህ ወይስ ችግር ገጥሞህ ነው?” ሲሉ ጥያቄ አቀረቡላቸው:: ቀኛዝማች ሲመልሱ “አንድም አይንዎን ልይ ብየ ነው: ሌላም ችግር ገጥሞኝ ነው” አሉ:: ጃንሆይ ምንም እንደማያውቁ መስለው “ምን ችግር ገጠመህ?” ሲሉ  ጠየቋቸው:: “ከአያት ከቅድመአያቶቼ ሲወርድ ሲዋረድ የተረከብሁትን ጉልቴን ብቀማ ነው አቤት ልል የመጣሁት” አሉ ቀኛዝማች አንገታቸውን ሰበር አድርገው:: ይኸኔ ንጉሡ “ጣሊያንን ሽህ አመት ግዛ አላልህም?” ሲሉ  ቆጣ ብለው ጠየቁ:: ሰውነቴ “እኔ አላልሁም” ብለው ክርክር ለመግጠም ፍላጎቱ አልነበራቸውም እና ምንም መረበሽ ሳያሳዩ ረጋ እንዳሉ “አዎ ብያለሁ” አሉ አንገታቸውን ቀና አድርገው ፊት ለፊት እያይዋቸው:: “እኮ ለምን?” አሉ ጃንሆይ ይበልጥ ተቆጥተው:: ቀኛዝማች ትንሽ ፈርጠም ካሉ በኋላ የሆነውን ሁሉ ነግረዋቸው ሲያበቁ “ጣሊያንን ሽህ አመት ግዛ ያልሁት ቢጨንቀኝ ነው:: እርስዎስ ቢጨንቅዎ አይደል ሀገር ጥለው የሄዱ” ሲሉ አከሉ:: ይኸኔ ንጉሡ ደፍረው ቀኛዝማችን የሚቆጡበት አንደበት አልነበራቸውም:: እንዲህ እንዳሁኑ የቅጥፍጥፍ ዘመን ስላልነበር ጃንሆይ የራሳቸውን ድክመት ሸፍነው ሌላውን ተጠያቂ የሚያደርጉበት መሰረታዊ ምክንያት አልነበራቸውም:: ለደቂቃወች ጸጥ ብለው ሲተክዙ ከቆዩ በኋላ ከአንደበታቸው የተደመጠው “እውነት ብለሀል ሰውነቴ:: ምነው ሌላውም እንዳንተ ዋሽቶም ቢሆን ነፍሱን ባቆየልኝ ኖሮ!” የሚለው ነበር::

ሰውነቴ የተወሰደባቸውን ጉልት አስመልሰው ደርግ በአዋጅ እስኪሽረው ድረስ በስራቸው የነበረውን ሕዝብ በሰላምና በፍቅር ሲያስተዳድሩ ኖረዋል::

የሕዝብ ጠበቃነት

ሰውነቴ የአካባቢ ዕድገትና የሕዝብ ሰላም የሚያሳስባቸው ነበሩ:: ጎጃም ተበድሏል ብለው ካሰቡ ግምባር ቀደም ተከራካሪ ሆነው ተሰልፈው ታግለው ለማታገል ወደኋላ ብለው አያውቁም:: ለዚህም እንደምሳሌ የሚጠቀሰው የሚፈለገውን ያህል ሥራ አልሰሩም በሚል ሕዝቡን በማስተባበር ደጃዝማች ጸሀይ ዕንቁሥላሴን ከጎጃም እንዲነሱ ማስደረጋቸው አንዱ ነው:: ተቃውሟቸውን ለመግለጽ የተጠቀሙባቸው ሰላማዊ መንገዶች ደግሞ በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው:: በረዶ የቀላቀለ ዝናብ በሚዘንብበት አንድ ቀን ብዙ ሕዝብ በሚያይበት ቦታ ላይ ከሜዳ ላይ ቆመው ዝናብ እየወረደባቸው ያሰሙት ተቃውሞ በጎጃሞች ዘንድ ሲታወስ ይኖራል:: “ኧረ እባክዎት ወደዚህ ይምጡና ይጠለሉ?” ብለው የለመኗቸውን ሰዎች “ጸሀዩ ነው እንጅ ዝናቡስ አልጎዳኝም” በማለት በደጃዝማች  ጸሀይ ላይ የነበራቸውን ተቃውሞ በሰላማዊ መንገድ አሰምተዋል:: በአንድ ወቅት ደግሞ ከበጅሮንድ ረታ ጋር በነበራቸው ክርክር በፍ/ቤት በመረታታቸው ተናደው የተናገሩት ነገር ነበር:: በክርክሩ የተረታሁት ደጃዝማች ጸሀዩ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ለበጅሮንድ ረታ ድጋፍ ስላደረጉ ነው በሚል ቀኜ ቂም ቋጥረው ቆይተው ኖሯል:: በጅሮንድ ረታ የቁምጥና በሽታ አለባቸው ተብለው ይታሙ ስለነበር የክርክሩን ውጤት ለማወቅ የጓጓ አንድ ሰው ከርቀት ላይ ሆኖ “እንዴት ሆነ?” ብሎ ሲጠይቃቸው ሌላውም እንዲሰማ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው “ስንሟገት ውለን ከጠዋት እስከማታ: ጸሀዩ በርትቶ ቆማጣው ረታ” ብለው ተባብረው በድለውኛል ያሏቸውን ሰዎች ስም ጠቅሰው ብሶታቸውን በመረሩ ቃላት ገልጸዋል::

የሰጠህን አመስግነህ አትቀበልም! አበድረኸዋል?

በያኔው የአጼ ኃይለሥላሴ ያስተዳደር ስርዐት ጉቦ መብላት የተለመደ ነበር። ጉዳዩን ለማስፈጸም ወይም አቤቱታ ለማቅረብ የፈለገ ሰው ለጉልተገዥው ትንሽም ቢሆን በጉቦ መልክ ሸጎጥ ማድረግ እንደነውር አይታይም ነበር። ቀኛዝማች በህዝቡ አንዲወደዱ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ በትንሽ በትልቁ እየተነሱ ሰውን ለመቅጣት የማይፈቅዱ: የሰውን መብት አክባሪና ፍትሀዊ ከመሆናቸው በተጨማሪ የተሰጠኝ ጉቦ አነሰ ብለው ስለማይሉ ነበር። ይህን በተመለከተ የሚነገርላቸው አንድ ነገር አለ። አንድ ባለጉዳይ ቀኛዝማች ዘንድ መቅረብ ይፈልግና ለእልፍኝ አስከልካዩ ሁለት ብር ይሰጣል። የልፍኝ አስከልካዩ በድፍረቱ ተናዶ ሰውየውን አያዳፋ ሲያባርረው ቀኛዝማች ይሰማሉ። ወዲያው የልፍኝ አስከልካያቸውን ያስጠሩና ሰውየውን ለምን አየገፈተረ አንዳባረረው ይጠይቁታል። የልፍኝ አስከልካዩ ንዴቱን መቆጣጠር አንዳቃተው ከላይ ከላይ እየተነፈሰ የሆነውን ይነግራቸዋል። ሁሉንም በጸጥታ ካዳመጡ በኋላ እንዲህ አሉ፥ “የሰጠህን አመስግነህ አትቀበልም! አበድረኸዋል? በል አሁን ባስቸኳይ ሂድና ጥራው” ብለው ሰውየውን አስጠርተው ጉዳዩን ሰሙለት::

ከቂጡ ቆርጨ በአፉ ስላጎረስሁት

ሌላው የሚወደዱበት ምክንያት ደግሞ በጉቦ ያገኙትን ገንዘብ አጠራቅመው ሕዝቡን ሰብስበው ግብር የሚያበሉ በመሆናቸው ነበር። ይህንን በሚመለከትም የሚታወስላቸው ነገር አለ። “እንዲያው ምን ቢያደርጉ ነው ሕዝቡ እንዲህ የሚወድዎ?” ተብለው ሲጠየቁ “ምን ኣደርግለታለሁ ብላችሁ ነው ከቂጡ ቆርጨ በአፉ ስላጎረስሁት ይሆናል እንጅ”።

 

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s