የዶ/ር መረራ መታሰር ሰላማዊው ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተደረገ ጥሪ ነው!!! – መላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)

መላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)

መረራ ጉዲና ገና ከለጋ ወጣትነት ህይወቱ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ባልተቋረጠ ወኔና ጥራት ለአንዲት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ሲታገል የኖረ ዜጋ ነው፡፡ በዚህ ያልተቋረጠ ተጋድሎው በንገሱ ዘመን አምቦ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኖ በተማሪው ንቅናቄ በነበረው ንቁ ተሳትፎ ለአጭር ጊዜም ቢሆን እስር ቤት ተወርውሯል፡፡ በደርጉ ዘመን ደግሞ በመኢሶን ታጋይነቱ ለሰባት አመታት በእስር ተንገላቷል፡፡ ለአለፉት 25 አመታት ደግሞ የወያኔ ኢህአዴግን ግፈኛ አገዛዝ በመቃወም በሰላማዊና ህጋዊ የትግል ስልት ተሰማርቶ ከነዚህ የጥፋት ሃይሎች አንጻር እነሱ ከፋፍለህ ግዛን ሲያራመዱ የህዝቦች ወንድማማችነትን እየሰበከ፣ እነሱ ለስልጣናቸው ሲሉ በለየለት የአፋኝና የአመጽ ጎዳና ሲሰማሩ ዴሞክራሲን፣ ሰላምንና ህጋዊነትን እያነገበ ሲሞግታቸውና ሲታገላቸው በህዝባችን ፊት ተአማኒነትንና ተወዳጅነትን ያተረፈ ብርቅየ የኢትዮጵያ ልጅ ነው፡፡

Dr. Merera Gudina

መረራ ጉዲና በዚህ ረጅም የታግል ታሪኩ የሚታወቀው በወያኔ ኢህአዴግ ተቃዋሚነት ብቻ አይደለም፡፡ ለተቃዋሚዎች ጎራም ባለፉት 25 አመታት ያለመታከት የሚያስተላልፋቸው መልእክቶች የዚያኑ ያህል ግልጽና ያልተቋረጡ አንዳንዴም ከዚሁ ሰፈር ተቃውሞ የሚሰነዘርባቸው አቋሞች ናቸው፡፡ የኦሮሞን ህዝብ ኢትዮጵያዊነት አብስሮ በህዝቦች ወንድማማችነትና እኩልነት ላይ ለተገነባች ለአንዲት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ሲታገል በአንድ ወቅት ‘የዘመኑ ጎበና’ የሚል ቅጽል ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ ሰላማዊና ህጋዊ ትግል በማለቱና ይህን ሰሞን እንኳን በውጭ እያለ በተደጋጋሚ የሃገሪቱን ችግር በሰላማዊ መንገድ ከኢህአዴግም ጋር ተወየይተን እንፍታ እያለ በሚያስተጋባው አቋሙ በአንዳንዶች በ’ታማኝ ተቃዋሚነት’ ተፈርጆ ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ ከምንም ሳይቆጥር ሚልዮኖችን የሚያንቀሳቅስ ህዝባዊ ትግል መልክ እንዲይዝ ላለፉት 25 አመታት በግንባር ቀደምነት ታግሏል፡፡

በዚህ አዋጅ ምክንያት ትግሉ አይቆምም፡፡ ላለፉት 25 አመታት በተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች፣ በማስ ሚድያው በነጻ ጋዜጠኞች፣ በፖለቲካ መሪዎች ለዴሞክራሲ የሚደረገው ትግል ይካሄድ የነበረው፣ ባለፉት ሁለት አመታትም በተለይ በአማራና በኦሮሞ ክልሎች የተጧጧፈው ህዝባዊ ትግል የሚደረገው ታጋይ ዜጎች በጠራራ ጸሃይ እየተተኮሰባቸው፣ በገፍ እስርቤት እየተወረወሩና በገፍ እየተደበደቡ አንጅ ይህ የጥፋት ሃይል እነዚህን ትግሎች በሰላምና በጸጋ እያስተናገዳቸው አልነበረም፡፡ ዛሬ በዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰላማዊው ትግል መከልከሉ እስከዚህም የሚቀይረው ነገር አይኖርም፡፡ ባለፈው ሰሞን በአምስተርዳም ባደረገው ንግግር ዶ/ር መረራ ይህንን እውነታ ሲያስረግጥ ‘’ በይፋ አልተነገረም እንጂ ኮማንድ ፖስቱ ከአዋጁ በፊትም የነበረ የኢህአዴግ አሰራር ነው’’ በማለት በግልጽ አስቀምጦታለል፡፡ የሰላማዊና ህጋዊ ትግል ተምሳሌት የሆነው የዶ/ር መረራ በዚህ አዋጅ ሳቢያ መታሰር ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን ይህ ዜጋ የቆመለት ህዝባዊና ሃገራዊ ትግል ሚልዮኖችን በሚያካትት መልኩ ተፋፍሞ እንዲቀጥል በኢህአዴግ የተላለፈን ጥሪ አድርገን መቁጠር ይኖርብናል፡፡

ትግሉ ይቀጥል ሲባል ስለ ፍሬያማነቱም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዛሬ በዶ/ር መረራ መታሰር የሚቆጩና የሚቆጡ ሚለዮኖቸ ከሁሉም በላይ የዚህን ታጋይና የሌሎች በግፍ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎቻችን መፈታት እየጠየቁ ይህ ውድ ዜጋችን ‘ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ’ ብሎ ያስተላለፈውን መልእክት ተከትለው በአንድነት፣ እንዲሁም ከድሮ ጀምሮና አሁንም በአምስተርዳም ቆይታው ከፋፋይ የሆነውን ‘‘የታሪካ ሂሳብ ማወራረድ አቁሙ’’ ብሎ የሰነዘረውን ምክር አጢነው በብሄር፣ በሃይማኖትና በአካባቢ ሳይከፋፈሉ ወንድማማችነት፣ እርቅና ሰላም ወርዶ ለሁላችንም የሆነች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን ትግል ‘በመረራ መንፈስ’ እየተመሩ ማፋፋም ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡ እኛም ዛሬ በዚህ ራእይ እየተመራን ይህንን በጎና አገራዊ ራእይ እውን ለማድረግ ትግላችንን ማቀነባበርና ማፋፋም ይጠበቅብናል ፡፡

መላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)
ታህሳስ 2009

– See more at: http://ecadforum.com/Amharic/archives/17293/#sthash.5nGFCkoi.dpuf

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s