አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች ፈተናቸው ብዙ ነው – ቢሆንም ድጋፌ አይለያቸውም #ግርማ_ካሳ

አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች በአሁኑ ጊዜ እየተንቀሳቀሱ ነው ማለት አይቻልም። የአመራር አባላቶቻቸው አብዛኞቹ ታስረዋል። የሰማያዊ ፓርቲን ብንመለከት እንኳን የምክር ቤት ሰብሳቢው ይድነቃቸው ከበደ፣ በቅርቡ የተደረገዉን ጠቅላላ ጉብዬ ሲመርይ የነበሩት አቶ አበበ አካሉ እንዲሁም ሌሎች ብዙዎች ታስረዋል።

በአገዛዙ የሚደረሰው አፈናና እንግልት እንደተጠበቀ፣ ሌሎች እየታሰሩና ዋጋ እየከፈሉ ታጋይ ነን ባዮች ትግሉ የወያኔ መሳቂያ እያደረጉትም ነው። ወያኔዎች ካደረሱት ጉዳት የበለጠ ደግሞ የሚያመዉና የሚጎዳው ይሄ በፓርቲዎች ዉስጥ የሚታይ የፖለቲካ እንጭጭነት ነው።

አንድ አሳዛኝ ዜና ሪፖርተር ላይ አነበብኩኝ። ጥቂት የኢንጂነር ይልቃል ደጋፊዎች ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሄደው የረበሹበት ሁኔታ ነው ያለው። ቆይ ረብሻ የሚፈጥሩት እነዚህ የኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ደጋፊዎች ፣ ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተገኝቶ መረበሻቸው ለትግሉ ምን ፋይዳ ነው የሚሰጠው ? ይሄንን ቢመልሱልኝ ደስ ይለኛል።

የ2007 ምርጫ ከተደረገ በኋላ በኢንጂነር ይልቃል እና አቶ ይድነቃቸው ከበደን፣ የፓርቲው የምክር ቤት ሰብሳቢን (አሁን በወያኔዎች የታሰረ) ጨመሮ በሌሎች አመራር አባላቶች መካከል አለመግባባቶች ተከስተው ነበር። ከአንድ አመት በላይ ችግሮችን መፍታት ስላልቻሉ ጠቅላላ ጉብዬ ተጠራ። እነ ኢንጂነር ይልቃል ጠቅላላ ጉብዬው የተጠራው በትክክለኛ መንገድ አይደለም ብሎ ለምርጫ ቦርድ አመለከቱ። ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባዬው በድርጅቱ ደንብ መሰረት ስለመጠራቱ እስካጣራ ጉብዬው እንዳይደረግ ብሎ አዘዘ። ነገሮች ካጣራ በኋላ ተወካዮች ልኮ፣ ጉብዬው ተደረገ። በጉብዬው ኢንጂነር ይልቃል አልተገኙም ነበር። ሆኖም ጉባዬው በምትካቸው ለሁለት አመት ከነሃብታሙ አያሌው ጋር በወህኒ ሲሰቃይ የነበረውን የሺዋስ አሰፋን ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ።ኢንጂነር ይልቃል ያንን አልቀበልም ብለው አቤቱታ ለምርጫ ቦርድ አቀረቡ። በአሁኑ ወቅት ምርጫ ቢርድ ጉዳዩን እንደገና እየተመለከተው ነው። (መጀመሪያ ደረጃ ምርጫ ቦርድ ድረስ መካሰስ አሳፋሪ ነው።)

የተደረገው ጠቅላላ ጉብዬ በምርጫ ቦርድ ተወካይ ታዛቢነት ቢደረግም፣ ምርጫ ቦርድ የጉባዬውን ሪፖርት መርምሮ፣ ኮረም መሙላቱን አረጋግጦ፣ በደንቡ መሰረት ጉብዬው መደረጉ አይቶ፣ ለአዲሱ አመራር እውቅና ይሰጣል፤ ወይም እንደገና ሌላ ጠቅላላ ጉብዬ እንዲጠራ ያደርጋል። ያ ወደፊት የምናየው ይሆናል።

ነገሩ በዚህ ሁኔታ እንዳለ የኢንጂነር ይልቃል ደጋፊዎች በዚህ መልኩ ስብሰባዎችን እንደ ዱርዬ መረበሻቸው ግን አሳፋሪ ነው። አንደኛ ምርጫ ቦርድ እነርሱ የፈለጉትን ቢወስንና ኢንጂነር ይልቃል የሰማያዊ ፓርቲ መሪ እንደሆነ ቢገለጽም፣ ይህ አይነቱ ድርጉት ፓርቲው ክፉኛ የሚጎዳ ነው። ለምን አርቀው እንደማያስቡ አይገባኝም።

የሰማያዊ ፓርቲን ደንብ አንብቤዋለሁ። ማንም ከፈለገ ደንቡን ተመርኩዞ ልከራከር ካለ መከራከር እችላለሁ። በደንቡ መሰረት የኦዲት ኮሚሽኑ ጉብዬ መጥራት ይችላል። በመሆኑም አሁን ላለው አዲሱ አመራር በግሌ እውቅና እሰጣለሁ። በአቶ የሺዋስ አሰፋ የሚመራውም ይህ አዲስ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር፣ በሁኔታው ሳይደናገጥ መስራትና ማድረግ የሚችለው ፣ በጣም ዉስን በመሆኑ ( የአገዛዙ አፈና በመብዛቱ) ትንሿን ማድረጉን እንዲቀጥል አበረታታለሁ። ለዱርዬ ፖለቲካ ብዙ ቦታ መስጠት የለባቸውም። አለመስማማቶች፣ ልዩነቶች ይኖራሉ። ግን ልዩነቶች ደንብና ሕብ በሚፈቅደው መሰረት መፍታት ሲገባ መረበሽ ዘመናዊ ፖለቲካ አይደለምና፣ ብዙ ሊያስጨነቃቸው አይገባም።

ለኢንጂነር ይልቃል ደግሞ አጭር መልእክት አለኝ። ትግሉ ከርስዎም ሆነ ከማናችንም የበለጠ ነው። በመሆኑም እርስዎ ለችግር ምክንያት መሆን የለብዎትም። የእርስዎን ስም እየጠሩ የሚረብሹትን አደብ እንዲገዙ ያደርጉ ዘንድ በአክብሮት እጠይቃለሁ። በአዲሱ አመራር አካሄድ አለመስማማትዎት መብትዎት ነው። በዚያ ችግር ሊኖር አይችልም። ሆኖም ግን የድርጅቱን ደንብ አክብረው፣ እንደዉም በድርጅቱ ዉስጣዊ መድረክ የአሁኑ አመራር ቻልንጅ እንዲያደርጉ አበረታታዎታለሁ። እርስዎና አቶ የሺዋስአንድ ወቅት አንድነት ፓርቲ የነበራችሁ ጊዜ ጓደኛሞች ነበራችሁ። ታዲያ ምን ችግር አለው አሁን ለሰማያዊ ፓርቲ ዋጋ የከፈሉት አንገት ከሚደፉ ከቀድሞ ጓደኛዎ፣ ለትግሉ ዋጋ ከከፈለው፣ ከአሁኑ ሊቀመንበር ጋር ቁጭ ብለው ቢነጋገሩ ? ምን ችግር አለው ሊቀመንበርስ ባይሆኑ ? ለመታገል የግል መሪ መሆን ያስፈለጋል እንዴ ?

ለተቀረነው ደግሞ ይሄን እላለሁ። አገር ቤት ያሉ ደርጅቶች ብዙ ችግር አለባቸው። አዎን ደካሞች ናቸው። ዉጭ ካሉ ደርጅቶች የደከሙት እነርሱ ይሻላሉ። አዎን ፈተናቸው ብዙ ነው። ግን እነርሱን የበለጠ እንዲጠናከሩ ማድረጉን ነው የምመርጠው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s