ኦህዴድ በተሃድሶ እና በአመራሮች ሹም ሽር ኦፌኮ በአመራሮች እስር የተጠመዱበት የኦሮሚያ ፖለቲካ

 

በይርጋ አበበ 

ከ80 በላይ ብሔረሰቦች እና ብሔሮችን የያዘው የኢትዮጵያ ግዛት ላለፉት 25 ዓመታት በኢህአዴግ እየተመራ ሲሆን 547 መቀመጫዎች ያሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ ላለፉት 14 ወራት በኢህአዴግ አባሎች ብቻ ተይዟል። በአገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በህግ ደረጃ የጸደቀ እና እውቅና የተሰጠው ቢሆንም ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የአገሪቱን ሁሉንም ክፍሎች በትጥቅ ትግል የደርግን መንግስት አስወግዶ ስልጣን ከያዘው ከኢህአዴግ እና አጋር እያለ ከሚጠራቸው የአምስቱ ታዳጊ ክልሎች (ሶማሊያ፣ ሀረሪ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር እና ጋምቤላ) ገዥ ፓርቲዎች ውጭ የፖለቲካ ስልጣን የተረከበ ሀይል አልታየም። ይህ ክስተትም ኢህአዴግን “ስልጣኑን ለማካፈል የማይሻ እና የፖለቲካ አመለካከት ብዝሃነትን መቀበል የሚከብደው” እየተባለ እንዲተች አድርጎታል። የመድረክ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ አቶ ጥሩነህ ገምታ “የፓርቲ ፖለቲካ በኢትዮጵያ” በሚለው መጽሃፋቸው “ህወሓት/ኢህአዴግ የሚከተለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ አውራ ፓርቲነት የተለያየ አመለካከት ያላቸውን የኢትዮጵያ ህዝቦች በአገር ስሜት ማስተባበርና ማሳተፍ የማይችል ከቻይናው አዲሱ ዴሞክራሲ የተቋጬ ዲቃላ ርዕዮተ ዓለም የሚከተል ድርጅት ነው” ሲሉ ይገልጹታል። አቶ ጥሩነህ አያይዘውም “ኢህአዴግ በባህሪው የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን (የፖለቲካ አመለካከት ብዝሃነትን) ለመቀበል የሚከብደው ነው” ይላሉ።

በ2008 ዓ.ም ኅዳር ወር ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ቁጣ እና በኋላም በአማራ ክልል ከተፈጠረው ተመሳሳይ ሁነት በኋላ ገዥው ፓርቲ ወደ ውስጡ ተመልክቶ ችግሮቹን ለይቶ በማውጣት ከህዝብ ጋር በመወያየት በጥልቀት ተሃድሶ እንደሚያደርግ ቃል መገባቱ የሚታወቅ ነው። እንደተባለውም በአቶ ኃይለማሪያመ ደሳለኝ አማካኝነት በ2008 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ የተሾሙት የገዥው ፓርቲ ጎምቱ ካቢኔዎች (የፌዴራል መንግስቱ ባለስልጣናት) ለአንድ ዓመት ስልጣን ላይ ከቆዩ በኋላ በሌላ ጓዶቻቸው ተተክተው እነሱ ደግሞ ወደ ሌላ ቦታ ተዘዋውረው እንዲሰሩ ሹመት ተሰጥቷቸዋል። ይህ የፌዴራል መንግስቱ ተሞክሮም የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች በሚያሰተዳድሯቸው ክልሎች ተፈጻሚ በመሆን በርካታ የክልል፣ የከተማ አስተዳደር፣ የዞን፣ የክፍለ ከተሞች እና የወረዳዎች ካቢኔ ሹም ሽሮች ተካሂደዋል። በዚህ ዝግጅታችን በአገራችን ሰፊ የቆዳ ሰፋት እና ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የያዘውን የኦሮሚያን ክልል ፖለቲካዊ ብዝሃነት (Political Diversity) ሁኔታ ለመመልከት እንሞክራለን።

 

የኦሮሞ ፖለቲካ በ25 ዓመታት ውስጥ

በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ተሳተፎ እያደረጉ ከሚገኙ ዘውጌ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኦሮሚያን ክልል የሚያስተዳድረው የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) እና በክልሉ የኦህዴድ ተቀናቃኝ የሆነው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ይገኙበታል። እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች በተለያዩ የፖለቲካ ግለቶች እና ውዝግቦች ታጅበው በክልሉ እየተንቀሳቀሱ ሲሆን በተለይ የአራት ኪሎውን ቤተ መንግስትም ሆነ የፍላሚንጎውን የኦሮሚያን ጬፌ (የኦሮሚያ ክልል መንግስት) ወንበር መጨበጥ ያልቻለው ኦፌኮ ከሚያቀርባቸው ፖለቲካዊ አቤቱታዎች መካከል ኦህዴድ እንዳልንቀሳቀስ ቀፍድዶ ይዞኛል የሚለው ክሱ ቀዳሚው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉም ሆነ በብሄረሰቡ ተመራጭ “እኔ ነኝ” ሲል በድፍረት ይናገራል። ለዚህም አንዱ ማሳያው አድርጎ ኦፌኮ የሚያቀርበው “ላለፉት 25 ዓመታት በኦሮሚያ ክልል የተረጋጋ ሁኔታ አለመኖሩን በተለይም በተደጋጋሚ ጊዜ በክልሉ የሚነሳው ህዝባዊ አመጽ እና ባለፈው አንድ ዓመት ሙሉ በክልሉ የነገሰው ውጥረት ምክንያቱ ኦህአዴድ በክልሉ ህዝብ ያለመፈለጉ ምክንያት የፈጠረው ነው። ለዚህ ደግሞ ኦህዴድ ለክልሉ ህዝብ መስራት ከሚገባው በታች መስራቱ ነው” ኦፌኮ አያይዞም ኦሀዴድን በሙስና እና በኪራይ ሰብሳቢነት ይከሰዋል።

የክልሉ ገዥ ፓርቲ ኦህዴድ በበኩሉ “ኦፌኮ ለኦሮሞ ህዝብ ሰላምና ልማት የሚያበረክተው አንዳች ረብ ያለው ፓርቲ እንዳልሆነ ደጋግሞ ይገልጻል። የራሱን ፕሮግራም ተመልክቶ ለክልሉ ህዝብ የሚበጀውን አጀንዳ ከመቅረጽ ይልቅ የተሰሩ ልማቶችን በመንቀፍ ጊዜውን ያጦፋል” በማለት ይተቸዋል። በኪራይ ሰብሳቢነትና በሙስና ላይ ያለውን አቋም በተመለከተም የቀድሞው የፓርቲው ሊቀመንበርና የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሙክታር ከድር የኦህዴድን 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ ለመንግስታዊ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ “በፓርቲያችን ውስጥ ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት መኖሩን በግምገማችን ለማወቅ ችለናል። በዚህ ላይ በወሰድናቸው ተከታታይ እርምጃዎችም ኪራይ ሰብሳቢነትን በገጠሩ ክፍል ሙሉ ለሙሉ በሚያስችል መልኩ ማጥፋት ብንችልም በከተማዎች ግን ችግሩ ስር የሰደደ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ገና ብዙ ይቀረናል።” ሲሉ ተናግረው ነበር።

የኦህዴድ ተሃድሶ

ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ኦህዴድ በተደጋጋሚ ጊዜ የአመራር እና አባላት ግምገማ በማካሄድ ተስተካካይ የለውም። የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶከተር ነጋሶ ጊዳዳ “ዳንዲ የነጋሶ መንገድ” በሚለው መጽሃፋቸው በአንድ ወቅት “3000 የፓርቲው አባላት መባረራቸውን” አስታውቀዋል። ከዚያ ጊዜ በኋላም ቢሆን ኦህዴድ ከቀድሞው የክልሉ ፕሬዝዳንት ጁነዲን ሳዶ እና የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አልማዝ መኮ ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ አመራሮቹ በግምገማ ከመሰናበታቸውም በላይ በፖለቲካ አመለካከታቸው ልዩነት ምክንያት ከአገር ሲኮበልሉ እና አገር ውስጥ ሆነው ሲቃወሙ ይታያሉ።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ አሁንም በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነገግ ያደረገው በገዥው ፓርቲ ላይ የተነሳው ህዝባዊ ቁጣ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው በኦሮሚያ ክልል ያለው ተቃውሞ መሆኑን ተከትሎ ኦህዴድም ራሱን ገምግሞ የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ቀደም ባሉት ሳምንታት አስታውቋል። ከዚህ የፓርቲው እርምጃዎች መካከል ደግሞ አንዱ የሆነው ከፓርቲ አመራሮቹ እና ከክልሉ የመንግስት ኃላፊዎች ላይ የካቢኔ ሹም ሽር ማድረጉ ይገኝበታል። በዚህ የካቢኔ ሹም ሽሩ መሰረትም የክልሉን ፕሬዝዳንት ሙክታር ከድርን በቀድሞው የክልሉ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ በአቶ ለማ መገርሳ የተካ ሲሆን የፓርቲውን ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ አስቴር ማሞን ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተክቷል።

በወቅቱም አዲሱ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ “በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት በህዝብ አገልጋይነት ለመተካት ልዩ ትኩረት እንሰጠዋለን። ወጣቱን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ፣ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ማረጋጋት እና ከህዝቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይኖርብናል” ሲሉ ተናግረው ነበር።

የክልሉ መንግስት የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ፈቃዱ ተሰማ በበኩላቸው ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “በክልላችን ለሚገኙ ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ከኢኮኖሚው ተጠቃሚ ማደረግ፣ ለህዝብ የሚቀርቡ አገልግሎቶችን ማሻሻል፣ ህዝቡ ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎችን መመለስ፣ ከድንበሮች ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶችን መፍታት፣ በኢንቨስትመንት ስም የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን ማቋቋም እና ተገቢውን የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እና የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ማረጋጋት” ሲሉ የአዲሱን ካቢኔ የመጀመሪያ የቤት ስራዎች መናገራቸው ይታወሳል።

ኦህዴድ ከክልሉ የመንግስት መዋቅር እና ከከፍተኛ የፓርቲ አመራሮች ሹም ሽር ማግስት ደግሞ ሰሞኑን (ባሳለፍነው ሰኞ) በምዕራብ አርሲ እና በጅማ ዞኖች እንዲሁም በጅማ እና ሻሸመኔ ከተሞች የካቢኔ ሹም ሽር አካሂዷል። ይህ እርምጃም ከህዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ መልስ ለመስጠትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚረዳ ኦህዴድ ገልጿል። በሌላ በኩል ደግሞ የካቢኔ ሹም ሽሮችና የፓርቲው የተሃድሶ ስራ በክልሉ ለሚነሱ የህዝብ ጥያዎችና አለፍ ሲልም ህዝባዊ ተቃውሞዎች የሚሰጡት ምላሽ ሊኖር አይችልም ሲሉ የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ተናግረዋል።

 

 

የኦፌኮ አቤቱታ

ኦፌኮ ሊቀመንበሩ ዶከተር መረራ ጉዲና “ከሽብርተኛ ድርጅት አመራር (የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ)” ጋር ተገናኝቶ በመወያየት የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁን ተላልፈዋል ተብለው ታስረው ክስ ተመስርቶባቸዋል። ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የውጭ ቋንቋዎች አስተማሪ የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ወደ አሜሪካ ሂደው “ከአሸባሪው” ኦነግ ጋር በመገናኘት የሽብር ተልዕኮ ለመፈጸም ተነጋግረው መጥተዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸው እስር ቤት ከገቡ ዓመት አልፏቸዋል። የፓርቲው ዋና ጸሃፊ አቶ በቀለ ነጋ ደግሞ ከማንኛውም የፖለቲካ ተሳትፎ እና ማንኛውንም ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጡ በቤታቸው በቁም እስር ከዋሉ ዓመት አልፏቸዋል፤ የእሳቸው ምክትል አቶ ደጀኔ ጣፋም እስር ላይ ናቸው። ከዚህ በተረፈ ደግሞ ሌሎች በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ለእስር መዳረጋቸውን ፓርቲው ይናገራል።

የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ “ፓርቲያችን ኦፌኮም ሆነ ሊቀመንበራችን ዶክተር መረራ እንደሚታወቀው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን የምንመኝ ነን። በጠብመንጃ ስልጣን ይዞ የአገሩን ዜጋ ከሚጠራጠር የአገዛዝ ስርዓት ተላቀን የምንፈልገው ሰላምና ዴሞክራሲ የሁላችንም በሆነችዋ አገራችን ላይ እንዲሰፍን የምንታገል ሰዎች ነን” ብለዋል። በቅርቡ የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) በአመራሮቹ ላይ ሹም ሽር አካሂዷል ተሃድሶ እያደረገም ይገኛል። ይህ የክልሉ ገዥ ፓርቲ እንቅስቃሴ በእናንተ እና በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚኖረው ጠቀሜታ አይኖርም ወይ? ለሚለው የሰንደቅ ጋዜጣ ጥያቄ መልስ የሰጡት አቶ ሙላቱ “አዲሶቹ አመራሮች እኮ የሚሰሩት የቀድሞዎቹን እንጂ የስርዓት ለውጥ ወይም የሲስተም ለውጥ የሚያመጡ አይደሉም። የህዝቡ ጥያቄ እኮ እርቅ ይውረድ፣ ከአለአግባብ የታሰሩ ሰዎች ይፈቱ፣ የስርዓት ለውጥ ይምጣ እንጂ እናንተ እርስ በራሳችሁ እየተለዋወጣችሁ ታድሰናል አትበሉን አላልንም ነው። ስለዚህ የዚህ ፓርቲ ተሃድሶም አልኮው መለዋወጥ ይበልጥ አፈናውን እና እስሩን ያባብሰዋል እንጂ የተሻለ ዴሞክራሲ እና መረጋጋትን ሊያመጣ አይችልም” ሲሉ ገልጸዋል።

በቅርቡ ለእስር የተዳረጉትን የፓርቲውን ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲናን የእስር ቤት ሁኔታ በተመለከተ ደግሞ “ዶክተር መረራ ተጠርጥሮ ቢታሰርም በወዳጆቹ እንዳይጠየቅ ተደርጓል። ይህ ደግሞ የግለሰቡን ሰብአዊና ህገ መንግስታዊ መብት መጣስ ነው። በሌላ በኩል ጠበቆቹ አቶ ወንድሙ ኢብሳ እና ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማሪያም እንዲጠይቁት የተደረገውም እጆቹን በካቴና ታስሮ እና በፖሊስ ታጅቦ ሲሆን ለተወሰነ ደቂቃ ብቻ (30 ደቂቃ) ነው እንዲያነጋግሩት የተፈቀደው። ከዚህ በተረፈ ደግሞ ምንም እንኳ ሰውየው የጤና ችግር ቢኖርበትም በአሁኑ ወቅት ግን ጤንነቱ ደህና መሆኑን ጠበቆቹ ነግረውናል” ብለዋል።

ምንጭ፦- ሰንደቅ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s