ራሱን እያደለበ ለዕርድ ተራውን የሚጠበቀው ፍሪዳ – በገ/ክርስቶስ ዓባይ

አዎ! ፍሪዳ ለተለያዩ ዝግጅቶች ያስፈልጋል። ለሠርግ፤ ለዓውደ ዓመት፤አንዳንዴም ለሐዘን እንዲሁም በአዘቦት ጊዜም ፍሪዳ በየ ሉካንዳ ቤቶች በየጊዜው በቄራ እየታረዱና እየተወራረዱ ለየባለጉዳዮች ይከፋፈላሉ። ነገር ግን ፍሪዳው በየማድለቢያ ቤቱ የሚቀርብለትን የማወፈሪያ መኖ እየተመገበና ውሀውን በገፍ እየሸመጠጠ እኖራለሁ በሚል ተስፋ ራሱን አዝናንቶ በምቾት ይቆያል። አንድ ቀን ጊዜው ሲደርስ ድንገት ባልታሰበ ወቅት የደለበው ፍሪዳ እንደገና ሳያፈስ (ተመልሶ ሳይከሳ) ከመንጋው ተለይቶ እየተነዳ ወደ ገበያ በመውጣት ቀድሞ ከነበረው ዋጋ በላይ ይሸጥና ቄራ ተወስዶ መጨረሻው ዕርድ ይሆናል። ይህ የማይቀር ሐቅ ነው። የደለበ ሠንጋ ሁሉ በምንም ሁኔታ መታረዱ አይቀርም። እንደሚታወቀው እንስሳትን የሚያደልቡት ሰዎች ናቸው። የሚያፋፋ መኖ በውድ ገንዘብ እየገዙ በማቅረብና ሰዓታቸውን ሳያጓድሉ አምቦ ውሀ እያጠጡ የሚንከባከቧቸው ለጽድቅ ሳይሆን ከፍተኛ ትርፍ ለማግኘት ብለው ነው። እዚህ ላይ መገንዘብ የሚገባን ጉዳይ የሚደልቡት እንስሳት ብቻ ሳይሆኑ አምባገነን መንግሥታትም እንዲሁ በደንብ እስኪሰቡ ድረስ እንክ እንክ እየተባሉ ይደልባሉ። በተለይ በዚህ አምባገነን መንግሥታትን በማድለብና በመጨረሻም በመሰርጀቱና በማወራረዱ በኩል የተካነው የአሜሪካው ሲአይኤ ነው።

በግልጽ እንደሚታወቀውና ከታሪክም እንደምንረዳው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዓለማችን ከቀሰመችው ዘግናኝ ኪሳራ የተነሳ መንግስታት እየተለሳለሱ ሰላምን በመስበክ፤ በአንጻሩም እስፖርትን በማበረታታት አገሮች የቀድሞ ቂማቸውን እንዲረሱና እንዲቀራረቡ በማድረግ የተጫወቱት ሚና ቀላል አልነበረም። ይህም በመሆኑ ዓለማችን ለጥቂት ዓመታትም ቢሆን አንጻራዊ ሰላም የሰፈነባት እንደነበረች አይዘነጋም። በተለይ ደግሞ መላውን ዓለም ያወደሙት አንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች አሜሪካንን በጨርፍታ እንኳ አልነኳትም። ምናልባት ጃፓን የተሳሳተ ቀመር በመከተል የአሜሪካዋን ፐርል ወደብን ለመውረር መሞከሯ የሚታወስ ቢሆንም ከዚያ አልፋ በመሔድ የአሜሪካንን ኢኮኖሚ የሚያናጋ ተግባር አልፈጸመችባትም። በመሆኑም፤ ዓለም በጦርነት እሳት እየነደደች በደም አበላ በምትታጠብበት ወቅት የአሜሪካ ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች ለአንድ ሰዓት እንኳ ሳይቆሙ ቀን ከሌት በመሥራት ዕድገቷን በማፋጠን ላይ ነበሩ።

ይህም ሁኔታ ለአሜሪካ በኃያልነት ጎልታ እንድትወጣና ዘመናዊ የጦር መሣሪያዋንም በሂሮሽማ እና ናጋሳኪ ላይ በተግባር እንድትሞክር ምክንያት ሆኖላታል። በተለይ ደግሞ በጦርነቱ ሳቢያ ኢኮኖሚያቸው የተንኮታኮተው የአውሮፓ ሀገሮች የአሜሪካንን ድጋፍ ይፈልጉ ስለነበር ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ ንዋይ ወደ እነዚህ አገሮች በማስገባት በእጅ አዙር ጥገኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ከፍተኛውን ድርሻ የተጫወተው ጄኔራል ሞተር ካር ኩባንያ በርካታ የመኪና ማምረቻዎችን በተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች በመትከል ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ሀብት ወደ አሜሪካ እንዲጎርፍ ምክንያት ሆኗል። አሜሪካ ሌላም ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሮላታል። አውሮፓ በጦርነት ማዕበል በወደቀችበት ወቅት የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲአይ ኤ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችና የምርምር ተቋማት ውስጥ ይሠሩ የነበሩትን ዕውቅ ሳይንቲስቶች በማነፍነፍና ቪዛ በማደል ወደ አሜሪካ እንዲሄዱ ታላቁን ተግባር ተጫውቷል። ነገሩ ዘግይቶ የተገለጸላቸው አውስትራሊያና ካናዳም ከዚሁ የልሂቃን አእምሮ ዘረፋ በጥቂቱም ቢሆን ለመጋራት ጥረት አድርገው ተሳክቶላቸዋል። ለምሳሌም ታዋቂው የፊዚክስ ጠበብት አልበርት አንስታይን፤ እንዲሁም የማኅበራዊ ጉዳይ ሊቁ ኖአም ቾምስኪ በዚሁ ወቅት የተገኙ መሆናቸው አይካድም።

ይህንን ለመንደርደሪያ ይሆነን ዘንድ ከጠቀስን ወደ ዋናው ጉዳያችን እንመለስ። እኤአ በሜይ 14 ቀን 1948 ዓ/ም የእሥራኤል መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ በ1960ዎቹ ዓመታት በዙሪያው የሚገኙ የዓረብ አገሮች እሥራኤልን ጥምድ አድርገው ያዟት። እሥራኤልም ይህ ጉዳይ እንደሚመጣ ቀደም ሲል የተዘጋጀችበት ስለነበር አልተበገረችም። ከዚህ በተጨማሪ እንግሊዝና አሜሪካ እሥራኤልን በገፍ መርዳት ያዙ። በተለይ አሜሪካ የአካባቢውን እስትራተጅክ አቀማመጥ በማጥናት ከኢትዮጵያ ጋር የነበራትን የጠበቀ ግንኙነት መሠረት በማድረግ ቃኘው ስቴሽን በመባል የሚታወቀውን ጣቢያ አሥመራ ላይ እንድትተክል ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ፈቃድ አገኘች። ቃኘው እስቴሽን እንዳሁኑ የሳተላይት መገናኛ ባልተስፋፋበት ወቅት በሄሊየም ጋዝ የተሞላ የላስቲክ ፊኛ ላይ ካሜራ አስሮ ወደ ሰማይ በማምጠቅና ፎቶግራፍ በማንሳት የዓረቦችን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር፤ መረጃውንም ለእሥራኤል መንግሥት በመመገብ እንደቆየ ይታወቃል። በመጨረሻም ጦርነቱ በእሥራኤል የበላይነት ሲጠናቀቅ እንደገና አሁንም በቀጠናው እስከመጨረሻው አስተማማኝ ስላምን ለማስፈን እንዲቻል በሚል ሽፋን በአሜሪካ አደራዳሪነት በእሥራኤልና በዋናዋ ጠላት ግብጽ መካከል የካምፕ ዴቪድ ስምምነት ተፈርሞ ተቋጨ።
በዚህ ጊዜ ጠቅላላው የዓረብ አገሮች ግብጽን እንደ ከሐዲ ሲቆጥሯት፤ አሜሪካንን ደግሞ ዓይንሽ ላፈር አሏት። አልፎ ተርፎም የነዳጅ ማዕቀብ ሁሉ ጣሉባት። ኦፔክ የተባለውን የነዳጅ አምራች አገሮች ማህበርም በማቋቋም የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር ተስማሙ።

ይህ ሁሉ ሲሆን በግልጽ የሚታወቀው በዓለም ከፍተኛው የነዳጅ ሀብት ክምችት ያላት ሀገር ሩሲያ እንደሆነች ነበር። ነገር ግን ሁኔታው ተለውጦ ከፍተኛው የነዳጅ ሀብት ክምችት የሚገኝባት ሀገር ሳውዲ አረቢያ መሆኗ ሲረጋገጥ አሜሪካ ከጨዋታ ውጭ እንደሆነች ተገነዘበች (ስለዚህ ጉዳይ የፍሬደሪክ ፎርሳይዝን “ዘ ዴቭልስ ኦልተርኔቲብ”ን ይመለከቷል)። ይህ አጋጣሚ ለአሜሪካ ታላቅ ራሥ ምታት ነበር። ይሁን እንጂ ዕድሜ ለሲአይኤ የተዘጋውን በር ለመክፈት የሚያስችለውን ቁልፍ ለመቀመር ሂሳቡን መሥራት ያዘ። በዚህም በርካታ ስሌቶችን በማዘጋጀት ሲሞክሩ ቆይተዋል። አንደኛው በ1970 ዎቹ ዓመታት በተከሰተው በኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት አሜሪካ ኢትዮጵያን በመካድና የዚያድ ባሬን ሶማሌ በመደገፍ በዚያ አድርጋ ከዓረቦች ጋር ግንኙነት ለመመሥረት ያቀደችው ሙከራ አልተሳካላትም። እንኳን በሶማሌ አድርጋ ወደ ዓረብ ለመግባት ይቅርና ሶማሌም በጀ ብላ የአሜሪካንን ሞግዚትነት አልተቀበለችውም። ከዚህ በኋላ በጦር መሣሪያና በተለያዩ የአሜሪካ ተራደኦ ስትንበሸበሽና ስትደልብ የቆየችው ሶማሊያ አሻፈርኝ ባለች ጊዜ በሲአይ ኤ የጠረጴዛ ዙሪያ በተወሰነባት ደባ ይኸው አስከአሁን ድረስ መንግሥት አልባ እንድትሆን ተፈርዶባታል።

ሁለተኛው አማራጭ የነበረው የኢራቁን ሳዳም ሁሴንን በስደት ከነበረበት ከግብጽ አውጥቶ ወደ አገሩ ኢራቅ እንዲመለስ በማመቻቸትና ሥልጣን ላይ እንዲወጣ በማድረግ እንደ ዓሣ መያዣ በመጠቀም ሳውዲ አረብያን ማጥመድ የሚሉት መላምቶችን ተግባራዊ ማድረግ ነበር። በዚሁ ዕቅድ መሠረት አሜሪካ ሳዳም ሁሴንን እኤአ ጁላይ 16 ቀን 1979 ዓ/ም ጀምሮ ሥልጣን ኮርቻ ላይ እንዲፈናጠጥ ከፍተኛ የሆነ የወታደራዊ ምስጢሮችን በማማከርና ስለኃያልነቱ የሜዲያ ሽፋን በመስጠት፤ የረቀቁ የምኅንድስና ንድፍና በዓለም የተከለከለውንና የተወገዘውን የባዮሎጅካል መሣሪያ ጨምሮ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ አቅርቦትን በማስታጠቅ ረገድ እኤአ እስከ ኦገስት 2 ቀን 1990 ዓ/ም ድረስ ከፍተኛ ትብብር በማድረግ ቆይታለች።

በነዚህ የአሥራ አንድ ዓመታት ጊዜ ውስጥ በተለይ ታላቁን የጤግሮስ ወንዝ የፍሰት አቅጣጫውን በማስቀየሩ ሂደት የአሜሪካ የምኅንድስና ተሳትፎ እጅግ የላቀ እንደነበር ይነገራል። የወንዙን የፍሰት አቅጣጫ ለማስቀየር ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ለልማት ታስቦ ሳይሆን የሺያ ሙስሊሞችና የኩርድ አማጺዎች ለውሃ ችግር እንዲጋለጡና ትግላቸው እንዲዳከም ለማድረግ ነበር። በቀጣይም እኒሁ የነፃነት ታጋዮች በአሜሪካ የጦር አማካሪዎች በታገዘ የባዮሎጅካልና የተላያዩ ዘመናዊ የናፓል ቦምብ መሣሪያዎች መፈተኛ እንዲሆኑ መደርጉም በሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች በሠፊው ሲወገዝ እንደነበር አይዘነጋም። ይህ ሁሉ ሲሆን ዋናው የአሜሪካ ዕቅድ ሳዳም ሁሴንን በቀጠናው በጣም ተወዳዳሪ የማይገኝለት ኃያል መሪ እንዲሆንና ገዝፎ እንዲታይ ማድረግ ነበር። በመሆኑም የሳዳም ሁሴኗ ኢራቅ የሺያ ሙስሊሞች አገርከሆነችው ከጎረቤቷ ኢራን ጋር በገጠመችው ጦርነት ከአሜሪካ በተደረገላት ድጋፍ ታግዛ ጦርነቱን በድል አድራጊነት እንድታጠናቅቅ ሆነ።

አሜሪካ ሳዳምን በዚህ መልኩ እንደ ሠንጋ በሬ ስታደልበው ቆየች። ሳዳምም የልብ ልብ ተሰማው በተለይ ደግሞ በተንኮሏ ተወዳዳሪ የማይገኝላት ኮሎኒያሊስት እንግሊዝ ከኢራቅ በመነጠል ኩየት በማለት የፈጠራቻትን ሌላዋ የነዳጅ ባለፀጋ ሀገር ወደ ቀድሞ ታሪካዊ እናት አገሯ ኢራቅ ለመጠቅለል እንደሚችል ከአሜሪካው አምባሳደር አፕሪል ግላስፒ ፍንጭ በማግኘቱ ሳዳም ሁሴን ቁሞም ተቀምጦም ህልሙ ይኸው ጉዳይ ሆነ። ይህ አጋጣሚ ለአሜሪካው ሲአይኤ ታላቅ ፈንጠዝያን ፈጠረ።

ፍሪዳው በደንብ እንደሰባ ጉልህ ማሳያ ነበር። ይህ በዚህ እንዳለ አሜሪካ ማደሊን ኦልብራይት የተባሉትን ከፍተኛ መላክተኛዋን ወደ ሳውዲ አረብያ በመላክ ጉዳዩ ለንጉሥ ፉአድ “ከፍተኛ ምስጢር” ተብሎ ተነገረ። ይኸውም የሳዳም ሁሴን ዕቅድ ጠቅላላ የአረብ አገሮችን በአንድ መንግሥት ጠቅሎ ለማስተዳደር እንደሚፈልግና በቅርቡም ኩየትን ሊወር እንደሚችል፤ ቀጥሎም አንድ ባንድ እያለ ሁሉንም የዓረብ መንግሥታት እንደሚያዳርስ የሚል ሲሆን፤ ንጉሠ መንግስታቸው እንዳይደፈር የሚፈልጉ ከሆነ ከኃያሏ አሜሪካ ጋር የስምምነት ውል በመፈራረም ዋስትና ማግኘት የሚችሉ መሆኑ ተገለጸላቸው።
ንጉስ ፉአድም ልዑላውያን መኳንንቶችን በመሰብሰብ ስለሁኔታው እንዲመከርበት አደረጉ። ይሁን እንጂ ተሰብሳቢዎቹ፤ “አይሆንም እንጂ ቢሆንም እንኳ አሜሪካንን ከመሰለ ጠላት ጋር ውል ከመዋዋል ይልቅ ወገናችን በሆነው በሳዳም ሁሴን እጅ መውደቅ ይሻለናል” የሚል አቋም ያዙ። ንጉሡም በዚሁ ውሳኔ መሠረት ውጤቱን ለአሚሪካዋ መልዕክተኛ አሳወቁ። ወዲያውኑ ለሳዳም ሁሴን ኩየትን መውረርየሚችልበት ወቅት ላይ መድረሱ ተነገረው። የዚያኑ ዕለት የሳዳም ሁሴን ወታደሮች ኩየትን ይዘዋት አደሩ።

እንደገና አሜሪካ ድፕሎማቷን ወደ ሳውዲ በመላክ ለንጉሥ ፉአድ ባለፈው ጊዜ የቀረበላችሁን ዕድል አልተጠቀማችሁበትም፤ ይሁን እንጂ አሜሪካ አካባቢው የሰላም ቀጠና እንዲሆን ፍላጎት ስላላት ይኸው ዕድል እንደገና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቀርቦላችኋል። አሁን ያላችሁ በቀናት ሳይሆን በሰዓታት ብቻ የሚቆጠር ጊዜ ሲሆን፤ ይኸውም የሳዳም ሁሴን ወታደሮች የሳውዲን መሬት እስኪረግጡ ድረስ ብቻ ነው። የሳዳም ሁሴን ወታደሮች የሳውዲን መሬት ከረገጡ በኋላ ግን አሜሪካ በምንም ተዓምር እጇን አታስገባም። ስለዚህ አሁኑኑ ውሳኔያችሁን አስውቁን ተብለው ንጉሡ ሲጠየቁ ሰውነታቸው በፍርሃት መርበትበት ያዘ። በዚህ ቀውጢ ሰዓት አማካሪዎችን የማወያየት ዕድል ቀርቶ ቀደም ሲል በአሜሪካ የተዘጋጀውን የስምምነት ሠነድ እንኳ የማንበብ ጊዜ አልገጠማቸውም። ዝም ብለው በነሲብ መፈረም ነበረባቸው።

የስምምነቱ ፊርማ መጠናቀቁ እንደተረጋገጠ፤ ለዘመናት እያደለበ ሲያሰባው ከነበረው የአሜሪካ መንግሥት፤ ሳዳም ሁሴን “ኩየትን በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ” ከጸጉር የቀጠነች ማስጠንቀቂያ ደረሰው። ሳዳም ሁሴን እስከዚያች ሰዓት ድረስ ለዕርድ እየተዘጋጀ መሆኑን አላወቀም፤ አልጠረጠረምም። ነገር ግን የሁኔታው እንቆቅልሽና ውስብስብነት ጉዳይ እጅግ በጣም ስላናደደው በእቢተኝነቱ በመጽናት የሚመጣውን ለመቀበል እስከመጨረሻው ራሱን አዘጋጀ። የጦር መሣሪያው ይቅርና በዓለም አቀፉ ሚዲያ የሳዳም ሁሴን መጥፎ ዝናው እየጎላ መሥራጨት ያዘ። እንዲያውም ቀደም ሲል ለክፉ ቀን ተብሎ የተያዘበት መጥፎ ተግባሩ ተራ በተረ እየተመዘዘ መውጣት ጀመረ።

ሳዳም ሁሴን ሥልጣን ከያዘበት ጌዜ ጀምሮ ከ 250 ሺ በላይ የሚሆኑ የራሱን ዜጎች እንዳስገደለ በይፋ ሲታወጅ፤ ዓለም በሙሉ ሳዳም ሁሴንን በጅምላ አወገዘ። በመጨረሻም ሲደልብ የቆየው ፍሪዳ ሳዳም ሁሴን ታረደ። በአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እየፈሰሰባቸው ሲገነቡ የቆዩት የመሠረተ ልማቶች ሳይቀሩ በአሜሪካ ሮኬቶች እንዳልነበሩ ሆኑ። ጦርነቱ ቀጣይነት እንዲኖረውና ሁሉም ነገር እስኪደመሰስ ደረስ ጊዜ ለመግዛት እንዲያመች ከአሜሪካ በኩል የተሰጠው ምክንያት ሳዳም ሁሴን አደገኛውን የኒውክሌር መሣሪያ እየገነባ ነው የሚል ሽፋን ነበር። እውነታው ግን ያ አልነበረም፤ ዋናው አሜሪካ ሳውዲ አረብያ እንድትገባ በር ለመክፈት ሲሆን ሁለተኛው ግን ኢራቅ በቀላሉ መልሳ አንዳታንሠራራ ሕንፃዎቹን ሁሉ በማፈራረስ ወደ አሻዋ ክምር መለወጥ ነበር።
ወደኛው አገርም ስንመለስ ተመሳሳይ ዕጣ ይጠብቀናል። በግልጽ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ብዙ ጠላቶች (ምቀኞች) አፍርታለች። ከእነዚህ ዓይነተኛ ጠላቶች መካከል እንግሊዝ ቀዳሚዋ ስትሆን እሷ በቀረጸችው የወደፊት ዕቅድ መሠረት ኢትዮጵያን ቢቻል የማጥፋት፤ ባይቻል ደግሞ የማሳነስ ፖሊሲ ተመርኩዞ የዓባይን ወንዝ የውሀ ፍሰት መጠን ለዘለቄታው በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀጠል እንዲቻል ግብጽ ሁለተኛዋ ጠላት እንድትሆን ተኮትኩታለች። ይህም ማለት ኢትዮጵያ በማንኛውም መንገድ የተረጋጋ መንግሥትና የፈጣን የመሠረተ ልማቶችን እንዳታካሂድ እንደ አንድ ሁነኛ አጀንዳ ተቀርጾ በተወሳሰበ የስላላ መረጃ በመከታተል ማክሸፍ ዋነኛ ተግባር ሆኖ ለዘመናት ሲሠራበት እንደቆየና አሁንም በዚሁ አቋሟ እንደጸናች መሆኑን የማይገነዘብ ምሁር ኢትዮጵያዊ አለ ለማለት ይቸግራል።

ይህ እንግዲህ እጅግ በጣም የረቀቁትን የባዮሎጅካል ጥቃቶችን ያካትታል። በዚህም የገበሬው ምርቱ እንዳያድግ በተለያዩ አቅጣጫዎች የአረም ዘሮችን አስርጎ በማስገባትና አዝመራን የሚበክሉና የሚያቀጭጩ የፈንገስ ተውሃስያንን በመላ ሀገሪቱ በማሠራጨት፤ የተለያዩ የሰውና የእንስሳት ተላላፊ በሽታዎችን በማዛመት፤የሕዝቡን ሞራል በመሥበርና የመንግሥትን ዕቅድ በማሰናከል ከፍተኛ ሚና የምትጫወተውን እንተወውና በግልጽ የሚታወቁትን ጣልቃ ገብነቶች መጥቀሱ ብቻ ለዚሁ ጥናት አስረጋጭ ማስረጃዎች እንደሆኑ እንገነዘባለን።

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የአፍሪካ አንድነት ማኅበርን ለማቋቋም ያደርጉት የነበረውን ጥረት በማጥላላትና ቀጥሎም ከሊቢያ ጎን በመሰለፍ መሥሪያ ቤቱ ከአዲስ አበባ ወጥቶ ወደሌላ ሀገር እንዲዛወር ግብጽ ስታድም መቆየቷ አይካድም። በደርግ ዘመነ መንግሥትም በመጀመሪያ የሶማሊያን መንግሥት፤ ቀጥሎም ጀብሀን ከዚያም ሻዕቢያንና ወያኔን በጦር መሣሪያና በገንዘብ ከፍተኛ ዕርዳታ እየሰጠች ኢትዮጵያ የተረጋጋ መንግሥት እንዳይኖራት የበኩሏን የመሰናክል አሽክላዋን ስትዘረጋ እንደቆየች ለማንም የተሠወረ አይደለም። በአሁኑም ሰዓት በተለይ የዓባይን ግድብ ተመርኩዞ ከፍተኛ የሆነ ሤራ በማውጠንጠን ላይ ትገኛለች። ስለሆነም ኢትዮጵያን ለማተራመስና ከውጭም ከውስጥም ለሚንቀሳቀሱ ማናቸውም ተቃዋሚ ኃይላት ግብጽ የታቻላትን ሁሉ ከማድረግ እንደማትቆጠብ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው። እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ግብጽ ዕርዳታ የምታደርገው ኢትዮጵያ የተረጋጋችና ሰላም የሰፈነባት ሀገር እንዳትሆን በማሰብ እንጂ ለተቃዋሚዎች የሚበጅ መሠረታዊ ዓላማ ስላላት አለመሆኑን ግን ማጤን ተገቢ ይሆናል።

ለምሳሌ ወያኔ ሥልጣን በያዘበት ወቅት የሽግግር መንግሥቱ የመጀምሪያው የመወያያ አጀንዳ ሆኖ የቀረበው ወደ ስድስት መቶ ገጽ የሚሆን የስምምነት ሠነድ በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ስላለው የዓባይ ወንዝ ጉዳይ ነበር። በዚህም ኢትዮጵያ ግብጽን ሳታማክር በዓባይ ወንዝም ሆነ በገባር ወንዞች ላይ ምንም ዓይነት የልማት ዕቅድ ማድረግ እንደሌለባት የሚከለክል እንደነበር በትዝብት የምናስታውሰው ጉዳይ ነው።

ወደ እንግሊዝ ስንመለስ ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ ባህልና ወግ ጠንቅቃ አጥንታዋለች። ምንም እንኳ ዙሪያውን በመውረር የኢትዮጵያን ግዛት ስታሳንስ ብትቆይም በሌሎች ሀገሮች እንዳደረገችው ሁሉ በኢትዮጵያ ለማድረግ ሳትችል ቀርታለች። ስለሆነም ድፍረቱም ሆነ ሙከራዋ ሁሉ ሊሠምር እንደማይችል በየጊዜው እያሰረገች ከምታስገባቸው ሰላዮች ሪፖርት የተረዳችው ሳይሆን እንዳልቀረ መገመት አይከብድም። ሰላዮቿ በግልጽ እንዳስቀመጡት “በሰላም ጊዜ ለሥልጣን እርስ በእርሱ የሚዋጋ ሕዝብ፤ የውጭ ጠላት አገሪቱን ለመውረር በቀረበ ጊዜ ግን የውስጥ ሽኩቻቸውንና ቂማቸውን ወደጎን አድርገው ጠላታቸውን ተባብረው እንደሚወጉ” ገልጸዋል። ይህ ብቻም አይደለም ሕዝቡ በቋንቋ እና በሃይማኖት የተለያየ እንኳ ቢሆን በሚደንቅ ሁኔታ ተከባብረውና ተፈቃቅረው ይኖራሉ። በተለይ ደግሞ ጥንታዊት ሀገር ከመሆኗ የተነሳ የራሷ ፊደል ያላት ሀገር በመሆኗ መሪዎቿ ሐሳባቸውንና ትዕዛዛቸውን ሳይዛባ ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላው ማስተላለፍ ይችላሉ በማለት ዘግበውታል።
እንግሊዝ ይህንን ሪፖርት በከፍተኛ ጥልቀት ከመረመረች በኋላ ኢትዮጵያን መውረር ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል በመረዳት አልደፈርችም። ነገር ግን ባንወራትም ማሳነስ የሚል ዕቅድ አውጥተዋል። በተለይ አፄ ተዎድሮስ አንድ መቶ ሃምሳ አራት የእንግሊዝ ሰላዮችን በግዞት ለስድስት ዓመታት ካቆዩአቸው በኋላ ጀኔራል ናፒየር እሥረኞችን እንዲያስለቅቅ ዘጠኝ ሚሊዮን ፓውንድ ተመድቦለት ከሕንድ ተነስቶ ከዘመተ በኋላ እንግሊዝ ምንጊዜም የማይቀለበስ አቋም ይዛ ቀጥላለች።

አንደኛው ኢትዮጵያን በቀጥታ ሳይሆን በእጅ አዙር ለመቆጣጠር እንዲያመቻት ጣሊያንን እየጎተጎተች ስታታልል ቆይታለች። በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ ከውጭው ዓለም አገሮች ጋር የንግድ ግንኙነት እንዳትፈጥር የቀይ ባሕርን ተከትሎ ካርታ በመንደፍ ወደብ አልባ እንድትሆን አድርጋለች። በሦስተኛ ደረጃ በተለይ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት የአገሪቱን አንድነት በመስበክና የሌላውን ሃይማኖትም አክብሮ በመቀበል የሚያደርገውን አስተዋጽዖ በመኮነን፤ የአማራውም ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራና ስደትን የሚጸየፍ በመሆኑ፤ በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ለትምህርት እንኳ ወደ ውጭ ሄደው በዚያው የማይቀሩ በመሆኑ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአገሪቱን ምስጢር ለመረዳት የማይቻል ሆኖ ቆይቷል።

ነገር ግን በደርግ ዘመን በተፈጠረው የአሜሪካ ክኅደት (በፕሬዚዳንት ካርተር) አገሪቱ ያለዕቅድና ሳትፈልግ ሉዓላዊንቷን ላለማስደፈር ስትል ወደ ሶሺያሊስት ጎራ እንድትቀላቀል በተገደደችበት ወቅት በተፈጠረ የአስተሳሰብ አለመግባባት አብዛኛው ምሁር ለመጀምሪያ ጌዜ ተሰደደ። ይህም ለጠላቶች ባልጠበቁት መንገድ ሲመኙት የኖሩት ሁሉ ተሳካላቸው። ነገር ግን በአንድ በኩል ቢሳካላቸውም በሌላው በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ከእጃቸው አፈትልካ ወጥታ በሶሺያሊስት ጎራ ተሰለፈች። ይህንን ደግሞ እንደገና ለማስመለስ በተቃዋሚነት የሚገኙ ወንበዴዎችን ማለትም ወያኔንና ሻቢያን በገንዘብ፤ በጦር መሣሪያና ዘመናዊ መገናኛና የታሸጉ ወታዳራዊ ምግቦችን በማቅረብ እስከመጨረሻው ደገፉ። በዚህም የሲአይኤ ዳይሬክተር፤ በሮናልድ ሬገን ጊዜ ምክትል ፕሬዚዳንት ቀጥሎም የአሜሪካ አርባ አንደኛ ፕሬዚዳንት የነበሩት ታላቁ ጅርጅ ቡሽ ግንባር ቀደም ተዋናኝ እንደነበሩ አይካድም።

ወያኔ ኢትዮጵያን በተቆጣጠረበት ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ በየመንገዱ ይቸረቸር የነበረው ወታደራዊ የታሸገ ምግብ ከዚሁ መርሃ ግብር የተገኘ መሆኑን ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል።
እንግዲህ የኦርቶዶክስን ሃይማኖትና አማራን እንዳያንሰራራ አድርገን አከርካሪውን ሰብረነዋል በማለት አቦይ

ስብኅት የተናገሩት የራሳቸው ዕቅድ ሳይሆን የተሰጣቸውን የቅጥረኝነት ዓላማ ማስፈጸማቸውን ለመግለጽ እንደተጠቀሙበት መረዳት ብልኅነት ነው።
የዓለምን ሕግ በጣሰ መልኩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የእንግሊዝ ፓስፖርት ይዘው እያለ ከየመን ሰንዓ በወያኔ ታፍነው መታሠርና እስካአሁንም ድረስ ላለመለቀቃቸው ምክንያት የእንግሊዝ የስላላ ድርጅት (የአስኮትላንድ ያርድ) እጅ የለበትም ለማለት ይከብዳል። እኒህ ሰው ለኢትዮጵያ አንድነትና ለሕዝቦቿ እኩልነት የሚታገሉ እንደመሆናቸው መጠን እንቅስቃሴያቸውም እንግሊዝ እየተከተለችው ላለው ፖሊሲ በተቃራኒነት ቆመው በመገኘታቸው ሳይሆን እንደማይቀር አለመጠርጠር ሞኝነት ነው።

በዚያም ሆነ በዚህ የምንረዳው ኢትዮጵያን የማተረማመስና ዕድገቷን የመግታት፤ ሕዝቦቿን በስበብ ባስባቡ እንዲጠራጠሩና እንዳይግባቡ በማድረግ ሰላምን በማደፍረስ የማወክ ተግባር መፈጸም ነው።
ስለዚህ ወያኔዎች የሆናችሁ ሁሉ ይህንን ሐቅ መገንዘብ ይገባችኋል። እርግጥ በአሁኑ ሰዓት የአሜሪካው ሲአይ ኤ መረጃ ይሰጣችኋል፤ እናንተም እንዲሁ ትሰጣላችሁ፤ ወንጀላችሁን እያወቀ ገመናችሁን ይሸፍናል፤ ይህ የማይታበል ሐቅ ነው። ለአውደ ዓመት እንደሚዘጋጅ ፍሪዳ እያደላባችሁ መሆኑን መረዳት ይገባችኋል። በአጋጣሚ ለገና ያልታረደ ፍሪዳ ፋሲካን ሊያመልጥ አይችልም። ወቅቱ ሲመቻች ያን ጊዜ ልክ እንደ ሠይጣን፤ ተንኮል ሲያሠራ ይቆይና በመጨረሻዋ ሰዓት ሰውየው ሲሞት ከሳሽ ሆኖ የሚገኘው ያው ሠይጣን እንደሆነ ሁሉ አሜሪካም ያላትን መረጃ ሁሉ እየመዘዘች ከናዚ ወንጀለኞች ባልተናነሰ ሁኔታ በዓለም ዙሪያ እየታደናችሁ እንድትያዙ በማድረጉ በኩል ግንባር ቀደም ሆና የምትሰለፍ አገር መሆኗን አለመገመት ጅልነት ነው።

የእናንተ ጉዳይ ጸሐፊውን ብዙም የሚያሳስብ አይደለም፤ ነገር ግን እንደ አንድ ንጹሕ ኢትዮጵያዊ ሁለት ጉዳዮች ያስጨንቃሉ። አንደኛው ይብላኝ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ፤ እናንተ በሠራችሁት ኃጢያት የዘለዓለም ተሸማቃቂና በርጋጊ ሆነው እንዲቀሩ ታደርጋላችሁና ነው። ሌላው ደግሞ በእናንተ ምክንያት እስካሁን የተገነባው መሠረት ልማት ሁሉ ሊወድም እንደሚችል የሚያጠራጥር አይሆንም። በእርግጥ አገር ወዳድ ነን የምትሉ ከሆነ ለእናንተም ሆነ ለቤተሰባችሁ በጥልቅ በማሰብ “አጥብቀህ በልተህ ወደ ቤተሰብህ ተመለስ” እንዲሉ፤ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ በሰላም የሽግግር መንግሥት በመመሥረት የኢትዮጵያን ውድቀት የሚፈልጉትን አገራት ሁሉ ቅስም በመስበር ሰላም ለማውረድ መወየየትና ከውሳኔ ላይ መድረስ ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ጀግንነት ማለት እንዲህ ያለ ውሳኔ ነው።

እዚህ ላይ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያምን ማሰቡ በጣም ጠቃሚ ይመስለኛል። ብዙ ሰዎች እርሳቸውን ይዘልፋሉ፤ አሳንሰውም ያወራሉ። ነገር ግን ታላቅ ጀግና እና አስተዋይም መሪ ነበሩ። በእርግጥ ብዙ ስኅተት ቢሠሩም ለአገራቸው አንድነትና ሉዓላዊነት ሲሉ እንደሆነ መሠመር አለበት። ያም ሆነ ይህ ግን የሠሩትን ስህተት ሁሉ የሚደመስስላቸው ታላቅ ውሳኔ ላይ በመድረስ አገራቸውን ከታላቅ ጥፋት ለመታደግ ሲሉ የአንድ ወያኔ ባለሥልጣን እንኳ የሚያህል ገንዘብ ሳይኖራቸው፤ ቤሳ ቤስቲን ሳይዘርፉ የራሳቸውን ሕይወት በስደት ላይ እንዲወድቅ አድርገዋል።
ጉዳዩን ጠለቅ አድርጎ ለተመራመረው ይህ ታላቅ መስዋዕትነት ነው። እንዲህ ያለ ድፍረትና ጀግንነት ወያኔ ይኖረዋል የሚል እምነት ባይኖርም የኢትዮጵያዊነቱ ደም እስካለ ድረስ አገርን ከጥፋት ለማዳን የኔ ይቅርብኝ የሚል ውሳኔ ላይ መድረስ ብልህነት እንጂ ዳካማነት አይሆንም። “ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች” ይባላል። የወያኔ ድልብ ፍሪዳዎች የማረጃው ቢላዋ ሳይሳል በክብር መልቀቁ አስተዋይነት መሆኑን መመርመር ተገቢ ነው። አይ የመጣው ይምጣ በማለት እስከመጨረሻው ሞችኮ መያዝ ግን ለማንም አይበጅም። ቢያንስ እንኳ በወያኔ ዘመን እንዲህ እንዲህ ተሠራ የሚያሰኙ ብጎ ተግባራትን ለታሪክ ማትረፉ ጥሩ ማስታዎሻ ሊሆን ይችላል።

ካልሆነ ግን የመጨረሻው ወቅት ሲደርስ ወያኔዎችም እንደ ናዚ የጦር ወንጀለኛ በገቡበት አገር ሁሉ እየታደኑ ከነቤተሰባቸው እንደዛር ተቅበዝባዥ ሆነው ይቀራሉ። መዝረፍ፤ ማሠር፤ መግረፍና መግደል ጀግንነት አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። ጀግና ማለት ለአገርና ለወገን ሲሉ የራስን ጥቅም፤ ክብርና ዝና አሳልፎ መስጠት ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱን ጀግንነት ወያኔ ካልተላበሰና ቆራጥ እርምጃ ካልወሰደ ፈሪ ነው ማለት ነው። ፈሪ ደግሞ የዝቅተኝነት መንፈስ የተጠናወተው በመሆኑ፤ ያዘው፤ እሠረው ግረፈው፤ገደለው እያለ ጊዜውን ሲገፋ ይቆይና በሰፈረበት ቁና መሠፈሩ አይቀሬ ነው።
ፖሊሲው የማይሠራ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ፤ ሕዝብም እንዳለፈው ሰጥ ለጥ ብሎ የማይገዛበት ደረጃ ላይ መድረሱ ሲታወቅ፤ ባለፈው ሁኔታ እንቀጥል ማለቱ የወፍጮ መጅ በአንገት ላይ አስሮ ወደ ባህር እንደመግባት ይቆጠራል። ስለዚህ ይህ ከመሆኑ በፊት ጀግና የሆኑ የወያኔ ኢንተለጀንስ ሰዎች የሁኔታውን አሳሳቢነት በመገምገም እንደ ሰባ ፍሪዳ ከመታረድ በፊት ራሳቸውን አድነው ሌላውን ወገናቸውንና

አገራቸውን ማዳን የሚገባቸው ይመስለኛል።
የእሥራኤል አምላክ ከመዓቱ ይሰውረን! ኢትዮጵያችን በክብር ለዘለዓለም ትኑር!
ገ/ክርስቶስ ዓባይ

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s