„መንጠቆ“ን“ – ከሥርጉተ ሥላሴ

ከሥርጉተ ሥላሴ 15.01.2017 (ዙሪክ – ሲዊዘርላንድ።)

„እግዚአብሄርን ዬምትፈራ ሰውነት ዬተደነቀች ናት።“ (መጸሐፈ ሲራክ ምዕራፍ ፴፩ ቁጥር ፲፰)

ይድረስ ለአቦይ ስብኃት ነጋ – ካሉቡት። ካሉበት ያልኩበት ምክንያት አካለዎት እንጁ መንፈሰዎት በኢትዮዽያ ውስጥነት ሥህን – ስለሌለ። ለነገሩ አናውቃትም ብለዋል። ይበቃል ስሟን ካወቁ፤ ቀሪውን ደግሞ ለክቱ ዬመንጠቆ ተግባርዎት – ያውሉት። ከቶ አንጋፋ ዬፖለቲካነት ባለአቅምነት በሰባዕዊ መብት ጥሰትና በሰው ልጅ እርድ ይለካ ይሆን? መቼስ ይሆን አቦይ ስብኃት ከፈርኃ እግዚአብሄር ጋር ዬሚተዋወቁት?

እፍታ

አብዩን ዕርዕስ „መንጠቆ“ በትምህርተ ጥቅስ ያስገባሁት ለትውኔት ዬበቃ ስለነበር፤  ቃሉ ዬተውኔት ጸሐፊው ኃብት ስለሆነ ነው። ሌብነት ከአካል ቅጣትነቱ ዬመንፈስ ቅጣቱ ስለሚያል ለራሴ ስልም ነው። ህሊናዬ በሌብነት ጧት – ማታ እንዳይደበድበኝም ስለምሻ። ሁሉንም ሸሽቼ መኖር ይቻለኛል። ግን ህሊናዬን – አይቻለኝምና።

ዬዘር ጥፋት ባላንባራስ አቦይ ስብኃት

አቦይ ስብኃት… ግን ዬንጹኃን ዬደም ፍሰትና ዬልጆች ዬስጋት ለቅሶ ግብር ጥዋት – ቁርስ፤ ዬቀን – ምሳ፤ ዬጀንበር – መክሰስ፤ ዬምሽት ራትነት እንዴት ይዞዎታል? መቼ ይሆን ነፍሰዎት ከንጹኃን ደም ማፍሰስ ተዕቅቦ ያደረገች ማዕልት ዬምትናፍቀው? መቼስ ነው ዬድምጽ አልባዎቹ ዬኢትዮዽያ እናቶች ዬደም ዕንባ ለግራጫ ጸጉረዎት ዬርካታ ዳንኪራ ጭፈራ ማሟሻነቱ ዬሚያከትመው? መቼ ይሆን ዬህዝብ ሰቆቃና ስጋት ለርሰዎ ዬደስታ ምንጭነቱ ዬሚያከትመው? መቼ ይሆን ወጣቶች በተወለዱበት ሀገር መቀመጫ አጥተው በወመኔችዎት ቅጥቀጣው ዬሚቆምላቸው? እስኪ መቼና መቼቱን አቅል ከሚሸመትበት ሸምተው፤ ትዕግስትም ከሚቀናበት ማሳ ሽተው እንደ ባለሁለት ጸጉር አብቃይነትዎት ከራሰዎት ጋር ዬሚመክሩት፤ ዬሚዘክሩት መቼ ይሆን? ከገዳይነትና ከአስገዳይነት መንጠቋዊ ተግባርዎትስ መቼ ይሆን ዬሚቆጠቡት? ዬሚታቀቡት?

መቼ ይሆን ከዚህ ጭካኔ መኖው ካደረገዎ ሰብዕናዎት ጋር ዬሚፉቱት? መቼስ ይሆን እስከ ዘር ማንዝረዎት አጥንትን መጋጥን፤ አጋሰሳዊ ዬወልዮሽ ምዝበራ ሂደት ጋር ዬሚቆራረጡት? እኮ እስከ መቼ? ዬትኛውን ህዝብስ ይሆን ትዕግስቱን ዬሚጠይቁት? ዋስትናችን ነውስ ዬሚሉት ህዝብስ ዬኤርትራን ወይንስ ዬኢትዮዽያን?

ጣረሞት።

ዬትኛው ህዝብ ይሆን ለእናንተ ዬድልብ ከብትነት ቀጣይነት ዬሚፈቅደው? ያ … በዕምነቱ „ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን አርቀን እንዳይነሳ ቀበረነዋል“ ያሉት እናም አራባ ዓመት ሙሉ ከዶግማው በተጻራሪነት ቁማችሁ፤ በመሲህነት በካድሬዎቻችሁ ዬሰለላችሁት፣ ያሳደዳችሁት፣ ቅርሱን ያቃጠላችሁት፣ ዓውደ ምህረት ላይ መስሄዎቻችሁ በባሩድ ያቃጠሉት፤ ሃይማኖቱን ተዳፍራችሁ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዳይሄድ በስነልቦናው ዕቃ ዕቃ ዬተጫወታችሁበት ወይንስ ዬመንፈሱ ማረፊያ ዬሆኑትን ዬኃይማኖቱን ባዕላት ያስተጓጓላችሁበት ወይንስ ዬገዳማት ቅዱሳንን ያሰደዳችሁት ወይንስ ሊቀ – ሊቃውንት አባቶቹን አሰድዳችሁ ዬበረከት ተጠማኝያደረጋችሁትን ወይንስ ዬአባቶቹ ናፍቆት፤ ዓይንና ቡራኬ እንደ ናፈቀው ሥጋዊ እረፍታቸው በስደት እንደወጣ እንዲቀር ዬበዬናችሁበት እኮ ዬትኛው ዬኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት አማኝ ይሆን ከሃይማኖቱ ገዳዮች ጋር ከነጉዲት ጋር ዬሚቆመው? ህልመዎት ጣረሞት ላይ መሆኑን ይወቁት። አንድ ቀንጣ ነፍስ አያገኙም።

ከቶ ዬትኛው ዬነብዬ መሐመድ ዶግማ ተከታይ ይሆን ከእናንተ ጸረ እስልምና ዶክተሪን ጋር ዬሚቆም? ዬቱ? ያ ከአራጁ አይሲሳ ጋር መድባችሁ ከወገኖቹ ጋር ለማለያዬት ዬደባ ተውኔት ዬሰራችሁበት ወይንስ ዬሃይማኖት መሪውን በካቴና አስራችሁ ቃለ ምልስ ያደረጋችሁለት ወይንስ ለመቀጣጫ ዬዓለሙ ዬረመዳን ፍስክ በሰላምና በመልካም ሰባዕዊ ተግባር ሲከወን ዬኛዎቹ በጥይት ዬቆላችኋቸው – መግቢያ መውጫ ነስታችሁ „አሸባሪ“ እያላችሁ ለስደት፣ ለሞት፤ ለእስር፤ ለመደፈር – ለመደብደብ ያባቃችኋቸው ህዝበ ሙስሊሞች ይሆኑ ለእናንተ ዬደለበ ዬአልጠግብ ባይነት ቀጣይ ራዕይ አቤት ወዴት ብሎ ዬሚገዛው ወይንስ በገፍ በዬከተማው ሥርዓተ ሃይማኖቱን እንዳይፈጽም ዬቃጠሎ ዘመቻችሁ ተጠቂ ያደረጋችሁት እኮ ዬትኛው ይሆን ዬእናንተ ውስልትና ሴራ ጋር ግብረ – አበር ዬሚሆነው? ጣረሞት።

እኮ! በቀን ከ600 በላይ ሞት ከ400 በላይ ዬስቃይ ሰለባ ዬሆነው ዬኦሽትዚም መራራ ተውኔት እሬቻና ዕንባው ይሆን ዬእናንተ ዬማያባራው ስቃይ ቀጣይነት ተርቲመኛ ዬሚሆነውን? ምንም እንኳን ዬሥራ ዘመናቸውን ጨርሰው ቢሰናበቱም ከእኛ ጎን እንዲቆሙ ደጉ፤ ሴት አንጀቱና ሩህሩሁ አቶ ኪም ሙንን ዬዕንባችን ቤተኛ ያደረጋቸው ሰማያዊ ሚስጢር ዬዕሬቻ ዕንባ ይቅርታው ለአራጆቹ ደጅ ጠኝ እንደማይሆን በዕድምታ ሲያመሳጥር ነበር። ይህ ልዑቅ ታምር ዬገዳዮች፣ ዬአራጆች፣ ዬፋሽስቶች ይሆናል ብለው ማሰበዎት ዬራዕዬዎት ጣረሞትነትን ያመሳጥራል። አዩ አቮይ ስብኃት በዬትኛውም ሁኔታ ዕንባ ዋጋ አለው። ወኪልም አለው። አድማጭም አለው። ቀን ጠባቂ ዕንባ ዬድል ዓውራ!

ያ … ዬእስር ቤቱ ሁሉ ከተማ መስራች ዬካቴና ቤተኛ ዬሆነው ዬኦሮሞ ምልዕትስ ከቶ ዬእስር ቤት ዬከተማ መስራችነቱ በይሁንታ ቀራኒዎ ይቀጥልልኝ ብሎ መንፈሱን ለነፈርዖን ይሸልም ይመስለዎታልን? ዬገበሬው ውርሱ ቅርሱ ዬትውፊቱ አድባር መሬቱ ነው። ለነገ ለልጁ ዬሚያወርሰው መሬት እንዲህ በቁሙ ሲቸበቸብ ከትውልድ መነቀሉ ስለመሆኑ ዬሚስተው ይመስለዎታልን?

ገበሬ ቅርሱ፣ ነፍሱ፣ ህልውናው፥ ትዳሩ፥ ልጁ፤ ተስፋው መሬቱ ነው። ጎጆ ዬሚወጣው ልጁ ሽልማቱ፣ ማጫው መሬት ነው። ግን አስቻላችሁትን? ተስፋውን ቁርጥም አድርጋችሁ በልታችሁ፤ ዬኦሮሞ ገበሬን ህይወት በቁሙ እንዳወጣ ቸበቸባችሁ፤ ሩሁን ሸቀጣችሁበት፤ ለውስጥ ቁስለት በሽታ ዳረጋችሁት። እህህን ተንፍሶ፤ እምን ተጎንጭቶ ውስጡ አሮና ከስሎ አምጦ እንዲኖር አስገዳችሁት፣ መሬቱን በመርዝ አቃጠላችሁት፣ ውሃውንም ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ብክል አደረጋችሁት፣ አዬሩንም ሰላሙን ቀማችሁት እና ይህ ዬሶቆቃ ቤተኛ ይሆን ዬእናንተ ዬዝርፊያ ታዳሚ ዬሚሆነውን? ጣረሞት።

ዬተማሪዎች ንቅናቄ በደሙ ያስከበረለትን ዬመሬት ላራሹን ዬባለቤትነት መብት ነጥቃችሁ በአሸባሪነት መድባችሁ ስትገድሉት፣ ስታሳድዱት፣ ስታስሩት፣ ስትደበድቡት፣ ከእርስቱ ስትነቅሉት ዓመት ይዞ እስከ ዓመት ስቃይ ስትቀልቡት ለኖራችሁት ዘርፎ አይጠግቤዎች ይሆን ቀጥልሉልኝ ብሎ ዬሚፈርምላችሁን? ጣረሞት።

እርቃን።

ያ … ማኒፌስቷችሁ ላይ „በአማራ መቃብር ላይ ዬታላቋን ትግራይን እንመሰርታልን“ ህልም መርዝ ዬትውልድ ነቀርሳ፣ ዬዘር ዕልቂት ዓዋጅ ዘ- ብሄረ አማራን ከሌላው ወገኑ ጋር እንዳይኖር ጠላትን በደርዘን ያፈራችሁለት አሳረኛ ይሆን ለባለቀኖቹ ለእናንተ ዬቀጥቅጠኝ – ዬፍለጠኝ፣ ዬተርትረኝ  ፈቃድ ሰጩ – አማራው? „ገዳይህ አማራ፣ ገዢህ አማራ“ በማለት ዲዲቲ በመነስነስ ከህልውና ውጪ ያደረጋችሁት አማራው ይሆን ዘሬን „በትጋት መንጥሩልኝ¡“ „ከእርስተ ጉልቴ እንደተነቀልኩ ልቅር“ ብሎ ከጎናችሁ ዬሚሰለፈው? ለገዳዮቹ – ለአራጆቹ – ለአገር አልቦሽ በማድረግ በፀጉረ ልውጥነት ዬተሳደደው – ዬተገደለው ከዬአካባቢው ዬተፈናቀለው ይሆን ዬዋስትናችሁ ማማ ለመሆን ዬሚቃጣው? ይህም ሳይበቃ ታስሮ ገደል ውስጥ ዬጨመራችሁት – ዬበቀል ብቅል ተረስቶ ይሆን ከእናንተ ጋር ቆሞ ለድጋሚ ለእነ ጦሮ እራሱን ዬሚያሰናዳ? ይመስለዎታልን። እርቃን።

ያ … ገመና ከታቻችሁ፤ አበልቶ – አጠጥቶ – ዬማይረካው ዬበሞቴ ዬአፈር ስሆን – ዬጉርሻችሁ – ዬጉሮሮ ማርጠቢያችሁ ዬሥራ አጥ መጠጊያችሁ – ዬወግ ዬማዕረጋችሁ – ጎረቤታችሁ አማራው ዛሬ ባድማው በእሳት ሲነድ፤ ትውፊቱ በትዕቢት ሲቃጠል፤ ሩሁ ዬባሩድ ቤተኛ ሲሆን፤ ልጆቹ ዬጸረ ሰዕብ መፈተኛ ሲሆኑ፣ ይመስላችኋል ዓይናችሁን ደግሞ ለማዬት ዬሚናፍቅ? እርቃን።

ያ … ትኩስ ከቀዝቃዛው ዬሚጭንላችሁ፤ መብራት ሆኖ፤ መብራትም ይዞ፤ ዘበኛም ሆኖ ቆሞ ዬሚያበላችሁ፤ መሬቱን ዬዘረፋችሁት፤ ማንነቱን ዬነቀላችሁት፤ ሥነ – ልቦናውን በመስቃ ዬጨቀጨቃችሁት፣ በድፈረትና በማንአለብኝነት እንዳይነሳ „አማራውን እንዳይነሳ አርቀን ቀብረነዋል“ ያላችሁት ቁሞ ሊያስተምራችሁ ዬሚችል ዬመቻቻል ዲታው አማራው ግረፋኝ፣ ዝረፋኝ፤ ጨርሱኝ፤ ዘሬን አፍልሱት ብሎ ማህተም ዬሚመታላችሁ ይመስላችኋልን? እርቃን።

ዬአገዳደላችሁን አሰቃቂነት ብርክቲ ዶር አንጅላ ሜርክል ዬጀርመን ጠቅላይ ሚኒስተር ሰቅጣጭነቱን ገልጸውላችኋል – እኮ። አዩ አቦይ ስብኃት ግፋ እስከዚህ ድረስ ባለሁለት ጭንቅላት ሃብታሟን፤ ዬአውሮፓ መንግስታት ዬጀርባ አጥንትን መራሂትን በተስተካከለ አቋም ከዕንባ ጎን እንዲቆም – አስችሏል። ይህን መንፈስ መልሶ እንደገና ለዳግም መከራ ዬሚያሰናዳ ዬአማራ እናት ከእንግዲህ –  አትውልድም።

አማራነት ማለት ቁርጥ ውሳኔ ማለት ነው። ይወቁት ቢጎምዝም አፍንጫዎት ተይዞ – ይጋቱታል። ለወዳጅም ለጠላትም ዬአማራ ልጅ ገና አሁን ነው ዬጀመረው – ስለ ውስጥ ሰላሙ ተጋድሎውን። መናጆነት ደግሞ እንዳይነሳ ተምሶ – ተቀብሯል።

አማራነት ልባምነት እንጂ ፈሪነት – አይደለም። አማራነት ክብሩን በቋሚነት ሳያስጠብቅ አያንቀላፋም። አይተኛምም። ለሚሊዮን ዓመት ዬተተኛው ከበቂ በላይ ነው። ሚሞሪ ካርዱ ሞልቷል።  ከእንግዲህ አማራ ዘበኛ አይሆንም! ከእንግዲህ አማራ ለጅምላ ጉዞ አጋፋሪነት እራሱን አያጭም! አማራነት ከእንግዲህ ለሎሌነት ደጅ አይጠናም! ዬእራሱ ጌታ እራሱ ነው! በዬትኛውም ሁኔታ ከቅንጣቷ እስከ ግዙፋ ዬፖለቲካ ውሳኔ ማእረገኑ – ለማእረጉ። አንዷን ብቸኛ በ20 ዓመት ዬማትገኘውን ጥበባዊ ልጁን ንግስት ይርጋን፣ ሺዎችን ሳተና ልጆቹን ለሰው በላ ሸልሞ ዬሚተኛ ይመስለወታልን ተጋድሎው? ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል። ተግባባን አቦይ?

አዕማዕደ – ዓሊሚራህ።

መቼም እንደ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ያለ ድርጅት ዬኢትዮዽያዊነት ሚስጢር ዐዕማድ ዬሆኑት ሥም ሲያይ ብርክ – ይይዘዋል። „እንኳንስ እኛ ብሄራዊ ሰንደቃላማችን ግመሎቻችን ያውቁታል።“ ይህ ዬሰው ልጅ መፈጠሪያ ዬልዕልት ኢትዮዽያን ፈተናን አሽንፋ ዬመፈጠሯ ሚስጢር ተርጓሚ ዬልብ ማህተም ነው። ኢትዮዽያ ገናናነቷ፣ ሥመ – ጥሩነቷ፤ ለጠላት ዬማትመች ሀገርንቷ – አሰባሳቢ ድርጅቷ ሰንደቅዓላማዋ ነው።

ይህ ብሄራዊ ዓርማ ለኮሪያ ዬጭንቅ ቀን ዬደረሰ፤ ለዚንባቢዌ ዬመከራ ቀን ጥላ ከለላ ዬሆነ፤ ለአፍሪካ ዬነፃነት ዓዋጅ ግርማ ሞገስ ዬሆነ፤ ለደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ማክተም ዬነፃነት አባት ዬኒልሰን ማንዴላን ህሊና ያበራ፤ ለነብዬ ማህመድ ልጅች ፍቅርን ዬቀለበ፤ ለዘጠኙ ቅዱሳን ቤተ ደናግል ዬሆነ አብሪ፣ ደማቅ፣ ዘመን አሻጋሪ ህይወታች ነው። ሀገርን እንደ ሀገር ያኖረ ያስቀጠለ። ዬክብሮች ሁሉ ክብር፤ ዬብርቆች ሁሉ ብርቅ። ዬሊቆች ሁሉ ሊቅ። ዬመኖር ትርጉም። ዬማሸነፍ ተቋም። በእሱ ላይ ነው ሀገርም መሬትም አለን ዬምንለው።ዬመከታ ብሩህ ቅኔ። ዬልምላሜ – ዬጀግንነት  – ዬብሩህ ተስፋ አንጎል – ብሄራዊ ሰንደቅዓላማችን። ዬህብር ህብሬ ነባቢተ – ነብስ። ፍቅር።

ለእናንተ ደግሞ ለአሻቦ መሸመቻ ከረጢት፤ ለእግራችሁ ገንባሌ፤ አቃጥላችሁ አታሟችሁን ዬምትደልቁበት ባላንጣችሁ ነው። ልክ እንደ ኢትዮዽያ ህዝብ በአሸባሪነት ዬፈረጃችሁት፣ በህግ ያሰራችሁት፤ ታሪኩና ትንግርቱ ተቀበሮ እንዲቀር ሙት በቃ ዬፈረዳችሁበት፤ „ጨርቅ¡“ ብላችሁ ያጣጣላችሁት፤ ዬናቃችሁትና ዬተሳለቃችሁበት፤ ተፎካካሪ ጥለት ሰርታችሁ በገናና ታሪኩ ላይ ቅልሞሽ ዬተጫወታችሁበት ሲሆን ዛሬ ደግሞ ተንበርክካችሁ ማረኝን ያዘወተራችሁበት፤ ዬትንፋሽ መሸመቻ መለበጫ ያደረጋችሁት ብሄራዊ ሰንደቅዓላም መንፈስ ለድጋሚ ባርነት ዬሚሰናዳ ይመስላችኋልን?

አላያችሁትም ሞትን አይፈሬው ዬጎንደር አብዮት ዬአማራ ተጋድሎ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ብሄራዊ ሰንደቁን ከፍ አድርጎ ሲያውለበልም፤ ዬተጋድሎ መርህ ስለመሆኑ ሲያውጅ፤ አላዩም አልሰሙምንም ይህን ዬአባቶቹን አደራ ዬእነ አሊምራህን ቃልኪዳን ጥሶ ዬእኛ ረድፈኛ ይሆናል ብሎ ማሰብ ጅልነት ነው። ዬአፋሩ ፖታሺዬም ሆነ ሚዲያውም መንፈሱም በትግራይ ገዝ መሆኑ ያ ጀግና ቅንና ዬብሩህ መንፈስ ባለቤት ዬሆነው በስም ብቻ ለተከለለት መቁንን አድሮ ያን ዬትውፊት አንጎልነቱን በሥጦታ ለፋሽት ወያኔ እግርብረት ያቀርባል ተብሎ አፋሩም አይታሰብም – አይጠረጠርም።  በፍጹም!  ቀን ዬሚጠብቅ ቦንብ ነው።  እኮ አቦይ ስለዬትኛው ህዝብ ዋስትና ይሆን ዬሚነግሩን?

ዬሬሳ ቤት።

ዬመኖር ትርጉም በሆነው በሐረር ዬሚደርሰው ግፍና በደል፤ ዬዘር እልቂትና ዱላ፤ ሴቶች ሳይቀሩ በገደላችሁት እሬሳ ቤት ኑሮቸው እንዲሆን በይናችሁ ደፍራችሁ፣ ደብድባችሁ፣ በዬሹሙ ቤት እስር ቤት አደራጅታችሁ በመከራ ዬቀቀላችሁት፣ ዬሰው ልጅ በህይወት እያለ ከሥጋው እሬሳ ጋር በጉድጓድ እንዲኖር ሲፈረድበት – እያዬ፣ ኑሮውን አሳሩን እዬኖረ ሀደሬው ወይንስ ሀረሬው ወይንስ ኢትዮዽያዊው ሱማሌው፤ ወይንስ አማራው ወይንስ ኦሮሞው ዬትኛው ይሆን በኢትዮዽያ ሱማሌ ዬእናንተ ጥጋብ ማበርተኛ ሊሆን ዬሚፈቅደው?

ዕንባ።

ድምጽ አልባውን ዬኢትዮዽያ ሴቶችን ዕንባ ሳስብ ዬምር – አለቅሳለሁ። ለምጽፍላቸው ድርጅቶችም ዬድምጽ አልባዎቹ ዬኢትዮዽያ ሴቶች ዬጨለማ ዘመን እያልኩ ነው። ደግሞም ትክክል ነኝ። ዬተረሱ፤ ዬተገለሉ፤ ዬተጨቆኑ፤ ግን ለማድመቂያ፤ ልጃቸውን፣ ትዳራቸውን ለፖለቲካ ሹመኞች ከትናንት እስከ ዛሬ ለግብር ዬሚያቀርቡ መብት አልቦሾች ግን ዬድርብ – ዬጥምር ግዴታ ባለሟሎች።

ሴቶች ካለፈቃዳቸው ሲደፈሩ – አባት አልባ ልጆችን ሲያሳድጉ፤ ወልደው እንዳይስሙ በመዳህኒት ስታመክኗቸው፤ ነፍሰ ጡሮችን በቢላዋ ስትዘለዝሉ፤ ዬዘር ማፍሪያ በጥርስ እንዲጎትቱ በማድረግ ዬተፈጥሮ ሰብዕናቸውን ስትፈትኑት፤ ልጅ ገድላችሁ እናትን ከሬሳ አስቀምጣችሁ ስትደበድቡ፤ መርዝ ሰጥታችሁ ጽንስ ስታስወርዱ፤ ከሥራ – ከኑሮ አፈናቅላችሁ ልጆቻቸውን ለጎዳና ስትገብሩ፤ ልጆችን በደራ ገብያ ለባዕዳን እንዳወጡ ስትሸጡ – ስትለውጡ እንደ እቃ፤ በርካቶች ሞትን ተሸክመው ዬመንገድ ጉሮሮ ለማኝ ስታደርጉ፣ በገፍ ለግርድና አረብ ሀገር በባለቤት አልቦሽነት ስትሸቅጡ፣ በሰው ሀገር ደራሽ አጥተው በስድስት ሰባት አረብ ሲደፈሩ – ሲቀቀሉ – ከፎቅ ሲወረወሩ ዬትኛዋ ዬዕንባ ማህበርተኛ ዬመከራ አጋሯ ሴት ትሆን ከጎናችሁ ቁማ ዬዋስትና ካርድ በረከት ለመቃብሯ ዬምትደራደረው? ይሄ እኮ ዬህሊና ሰው ዬመሆን ንጡር አመክንዮ ነው። ቢገባዎት። ለነገሩ „አውቆ ዬተሸሸገ“  ነው ነገርይው።

ቃጠሎ።

ዬትኛዋ እኮ ዬትኛዋ ዬሱዳን ዬሳት ራት ልጇ ዬሆነው እናት ትሆን ጋንቤላ ላይ ለእናንተ ዋስትና ዘብ ዬምትቆመው፤ ዬዕልቂት ዓውድ ዬሆነው ጋንቤላው ያን ዘግናኝ ከአራት መቶ በላይ እልቂት ወይንስ ከአራስ ቤት እያለች፥ ምጥ ቤት እያለች፤ ወይንም ከጉዳዯ ተመልሳ ስትመጣ ኑሯውም – ልጆቿም በእሳት ሲነዱ ያዬዬች ያቺ ዬኮንሶ አሳረኛዋ እናት፣ በሀገሯ ስደተኛ ሆና ከቀዬዋ ዬተሰደደችው ወይንስ መሬቱን ተነጥቆ ለትግራይ ባለሃብታና ለውጪ ቱጃር እርስተ ጉልቱን በግፍ ዬተቀማው – ዬጋንቤላ አርሶ አደር? ከቶ ዬትኛው ይሆን ዬዘራፊና ዬገዳይ ተባባሪ ድምጸኛው? ዬቱ ነው ጭካኔ ይምራኝ ዬሚል? አረመኔነት ይዳኜኝ ዬሚል? እነፈርዖን ዱላቸውን አልጠገብኩትምና አቦይ ከነዘር ምንዛራቸው ፈረሴ ይበሉኝ ዬሚለው ዬትኛው ነው? ግፈኞች።

ብትን አፈር።

ህም! እምም! በሀገሩ መሬት እዬራበው ለመኖር ያልተፈቀደለት። ከሥራ ገበታው ዬሚታገደው፤ ቤት ኪራይ ዬሚከለከለው፤ ከእድገት፤ ከሥልጠና ታግቶ በጭንቅ፤ በሥጋት ዬሚኖረው ከተሜ ይሆን ለሳጥን አሟቂነት ዬታጨውን ወይንስ ከነካቴናው ዬተቃጠለው እስረኛ ቤተሰብ ወይንስ በሌለ ቤቱ ስንቅ በማመላለስ ከነግልምጫችሁ ተሸክሞችሁ ያለው ዬእስረኛ ቤተሰብ ወይንስ ሊለምን አፍሮ እንደ ተቆለፈ ለራህብ ዬተዳረገው ሚሊዮን ወይንስ ባለቤት ጧሪና ጠዋሪ ዬሌላቸው አረጋውያን ወይንስ ወላጆቻቸውን ከሥራ አፈናቅላችሁ፣ ከመኖሪያ ቦታ ነቅላችሁ ወይንም ገድላችሁ በስጋት ሰቀቀን ዬምትገርፏቸው ዬነገ ተስፈኞች ታዳጊ ወጣት ወይንስ በገፍ እስር ቤት እያሸጋችሁ – እዬደበደባችሁ ሌሊት – ሌሊት ዬምትቀብሯቸው ወጣቶች ቤተሰብ ይሆን „ጎሽ¡ ቡቃያዬ ጨርሳችሁ ንቀሉልኝ“ ብሎ በፊውራሪነት ይሾመናል ይሸልመናል ብላችሁ? ምኞቱና ህልሙ ስንብትን ብቻ ነው። ዬነማን? ዬነ ጋሬጣ።

„ባዶ ስድስት።“

ዬአጋንንታዊ ተግባር መከወኛ የአርባ ዓመት ዬመቃብር ቤት „ባዶ ስድስት።“ ዬሲዖል ተምሳሌት ዬእሾሆች እኩይ ዬበቀል ማወራረጃ ዬፍዳ፥ ዬመከራ፤ ዬአሳር ጎለጎታ። ዬተሰወረ ዬሰው ልጅ ዬምክነት ዬጭካኔ ሸጎሬ። „ባዶ ስድስት“ ዬሳጥናኤሎች ዬቁርሾ ማወራረጃ ዬፍዳ ቀጠና። ለዚህ ከትግራይ ከወልቃይት ጠገዴ ዬተወሰዱ ዬሀገር አዛውንታት ያለቁበት ዬኦሾቲዝ ምዕራፈኛ። አዬ እነአቦይ ስብኃት – ገመነኞች።

ዬፍሬ ዘር ጠፍነት በኢሰባዊነት ዬተፈጸመበት ዬወንድ ልጅ ዬዕንባ ማዕከል። ዬትውልዱ መራራ፣ ጎምዛዛ ዬታሪክ ጥላሸት። አዎን! አለን ዬምትሉት ዬትግራይ ህዝብም በአሞሌ እያተለላችሁ፥ መጋረጃ ሰርታችሁ፥ በደሙ መነገዳችሁን ከልብ ሆኖ ዬሚያዳምጥበት ቀን ይመጣል። ዬአንድነቱን ልዑል አሉላን ሆነ በኢትዮዽያዊነቱ ዬማይደራደረው ዮኋንስም ቢሆን አጽማቸው ከመቃብሩ – ይቀሰቅሰዋል።

እኛ ከሌላው ዬኢትዮዽያ ህዝብ ጋር ሲነፃፀር አድሏዊነት፣ አለመመጣጠን አለ። ስለዚህም ትግራይ በተሻለ ተጠቅሟል ብንልም። ይህ ዬሚታይና ዬሚጨበጥ ቢሆንም – ከገዢዎቹ፤ ከቱጃሮቹ፤ ከህውኃት መስራቾችና አጋፋሪዎቹ ዬኑሮ፣ ዬቤተሰብ አያያዝ ጋር ዬሚመዛዘን ዬኑሮ ደረጃ ትግራይ አለ አንልም። ሁሉንም – እናውቃለን። እኩልነቱ በሥነ – ልቦና ዬበላይነት ብቻ ነው። በተረፈ ከወያኔ አባላትና ባለስልጣናት ጋር ሆነ ጥቅም ተጋሪ ጋር ዬኑሮ ዬደረጃ ልዩነቱ ዬሰማይና ዬምድር ነው – ዬተራው ህዝብ። በሌላ በኩል ከአነ አቦይ ዬሚተርፈው ፍርፋሪም እንደሚወረወርለት እናውቃለን። በተገኘችው ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆን መደረጉ መሸፈኛነቱ – ጉድጓድ ነው በጥልቀት ለሚያስተውለው። ሌላም ዬተመሰጠረ ዬቀጣይ እርድ ተረኛ ወይም ደቦኛ አለ። ቀጣዩ ጹሁፌ በዚህ ላይ ይሆናል። ዬነገ፣ ዬተነገ ወዲያ ያልተወለዱት ዬትግራይ ህፃናት ጉዳይ ዬቤት ሥራዬም ነውና።

ዬሆነ ሆኖ አቦይ ዬእርሰዎና ዬመሰለዎት ዬውስኪ ቅርሻ ማስተንፈሻ ዬትግራይ መሬት ከሆነ ነገ ሲመጣ እናዬዋለን። ዬቱ እንደሚበልጥበት። „ባዶ ስድስትን“ ማጽደቅ ወይንስ ማፍረስ። ከአብሮነቱ ጋር አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ብሎ መኖር ወይንስ ዬሃውዚን ድራማ እንዲደግሙ ለእነ አልጠግባይ ይለፍ መስጠት? ምርጫው ዬትግራይ ህዝብ ነው።

ባለቤት አልቦሾች ምንዱባን ቅዱስ መንፈስ።

ዬት እንዳሉ እንኮን ዬማያውቁ ዬአዕምሮ ህሙማን፣ ዓይናቸው ዬተጋረደ፣ ጆሯቸው ዬማይሰማ፥ እግር አልባዎች፣ ታዳጊ ይሁን ወጣት፤ ጎልማሳ ይሁን አረጋዊ እናንተ ውስኪ እንደ ውኃ በምትራጩባት፤ ከመኪና አይነት እስከ ቢላ ውድድር  ድረስ ጣሪያ ዬነከው ዘመኖ ኖሪዎቹ እናንተ – እነሱ ሩህ ማስቀጠያ ተስፋ ዬሌላቸው ዬጥቁር ዕጣ ሰለባዎች ንዑድ መንፈስ እርግማን ምን ያመጣ ይሆን? እናንተ ለዘር ምንዛራችሁ ዬጥሪት ሙላት ወንዝ ስትቀዝፋ እነሱ ስለቀጣዯ ሰከንድ ተስፋ ቢሶች።

ዬቀኑን ሐሩር ዬሌሊቱን ግርማ፣ ዬበጋን ወበቅ ዬክረምትን ጎርፍ ዬሚያንገላታቸው ዬአሳር እስረኞች፣ ዬትራፊ ሰልፈኞች ጎዳና አዳሪዎች፣ ሴተኛ አዳሪዎች – ዬመንገድ ታራሾች፣ ስንቱ መከራ ይዘርዘር – ይመንዘር። እሾሆች።

ከተሜው።

ከተሜውን ድሮም አትወዱትም። ቅስሙን እንደሰበራችሁት ነው። ዬሁሉ ጥቃትም ሰለባ ነው። በዘመነ ደርግ በዬኢትዮዽያ በ30.00 ብር 500 ካሬ ሜትር፤ ኋላ ላይም 250 ካሪሜትር አዲስ አበባ ላይ፣ ዬአፍሪካ መዲና ላይ ኖሪው በነፍስ ወከፍ ዬራሱ ኑሮ መመስረቻ – እንደ አቅምና ወርዱ አለኝ ዬሚለው ዬራሱ ዛኒጋባ ነበረው። ዛሬ ለካሬ ሜትር ቢጠሩትም አይሰማም። ለዛው በሊዝ ተቀፍድዶ። ይህም ሆኖ መጠለያ አልባ፤ ዬዕለት ጉርስ አልባ፤ ከፈን አልባ ማድረጋችሁ ላይበቃ እዬራበው፣ እዬጠማው፣ እዬታረዘ ለመኖር እንኳን ፈቃድ ነስታችሁ፣ ሰላሙን አውካችሁ ወጥቶ ስለመለሱ ዋስትና ነስታችሁ በስጋት ዬሽታሽቶ ታሹታላችሁ፣ ክፋዎች

ነጋዴውን ማህበረሰብ ከገብያ ውጪ አድርጋችሁ ተመጽዋች አደረጋችሁት። እናንተ አና ብላችሁ በንግዱ፤ በፖለቲካው፣ በደህንነቱ፤ በመከላከያው፤ በውጭ ግንኙነቱ እንዳሻችሁ መሬት አይብቃኝ ብላችሁ ስትፏልሉ ዬኢትዮዽያ ህዝብ ግን ለበይ ተመልካችትም አልተፈቀደለትም። ታዲያ አቦይ … ይህ ዬመከራ ቁልል እንዲቀጥል ዋስትናውን ዬትኛው ማሳ ላይ ይሆን ለመቸርፈስ ዬሚያደቡት? ቡጭቅጫቂ ህልመኝነት።

ሆዶ!

አቦይ ስብኃት ነጋ ዋስትና ሊሆኑ ይችላሉ ያሏቸው እነ ሆዶን ከሆነ ያስማማናል፡፡ እነ ሆዱ ዘመዴ ዬቀን ሰዎች ካድሬዎቻችሁ ሊሆኑ ይችላሉ። ዕሳቤያቸው ገና ጭንጋፍ ላይ ያለ ዬእንግዲህ ልጅ ነውና። ዬዛሬ ገዳዮች፤ ዬማግስት – አምካኞች። ለትውልድ ተስፋ ምንጣሮ ሆድአደሮች። እነ ሆዱ ዘመዴ ዬቀን ሰዎች ካድሬዎቻችሁ ዋስትና ሊሆኑ ይችላሉ። እነሱም ቢሆኑ ዬሞት መንገድ ላይ ዬቆም ዕብኖች። ለዛውም በገፍ ገብያ ላይ ዬተመለመለው፤ ዬእናንተው ሎሌዎች። ህሊናቸውን – ያሾለኩ። በዚህ ጨለማ ቀን ከምልዕቱ ዕንባ ጋር ለመቆም – ዬተሳናቸው። እያሉ – ዬሌሉ።

በዚህ ዬግፍና ዬጭካኔ ዘመን ከኃጣን ጋር፤ ከእኩይ ምግባር መቆም ከሃፍረት በላይ ነው። እርግጥ አብዛኞቹ ተገደው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከኃጢያት ጋር ውሎ ማደር – መኖር፤ ለገዳይ ሸማ መሆን ልጅ አያወጣም። ፈጣሪም አብዝቶ ያዝናል።  ዬዛሬ ገዳዮች፤ ዬማግስት አምካኞች መሆን ህሊናን – ይሰቀጥጣል።

ዓይነ – ጠባብነት።

ይገርማል። ከስሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ እናንተ እንዳሻችሁ ዬፈለጋችሁትን አድርጋችሁ እዬኖራችሁ – እዬፎለላችሁ፤ ዬጀርመን መንግስት ያበራባችሁን ቀይ መብራት ለማስተባበል በጠራችሁት ጉባኤ ላይ በግምት 34 በ34 ሴንቲሜትር በሆነች ሁለት ወንበር ዬተቀመጡ ዬተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ኢንጂነር ይልቃልና ኢትዮዽያዊው ማንዴላ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና መኖር ዓይነዎትን ደም አለበሰው። ፍቅራቸው ቦረቦረወት፤ መገኘታቸው አርገበገበዎት፤ ጎን ለጎን ሆነው መቀመጣቸው በእናንተው ዬካሜራ መስኮት መታዬታቸው አርመጠመጠዎት ከቶ ከእንዴት ዓይነቱ መንፈስ ይሆን ዬበቀሉት? እነሱ እኮ ለኢትዮዽያዊነት ባላባቶች ናቸው። ንገሩኝ ባይ። መቼ ይሆን ግራጫዎትና ብናኝ ትዕግስት ዬሚገናኙት? በዚህ እድሜ ብጣቂ ትእግስት እንዲህ በአደባባይ ማጣት? ይገርማል። አዛውንት እኮ ነዎት – እርሰዎ ቢያውቁት። ለባዶ ወለል ያን ያህል ዬተናጡ እነዚህ ሰዎች ህዝብ ዬመሪነት ቦታ ቢሰጣቸው ምን ሊውጥወት ይሆን? ያን ያህል በአደባባይ ዘለፋ፤ ፍጥጫና እርግጫ። ይገርማል። ኢትዮዽያ ሀገራቸው ናት! ዬእናት ኢትዮዽያ ብርቅዬ ዬማህጸኗ ሙሉ ፍሬዎች ናቸው። ዝንቅ – ቅልቅል – ዬሌለባቸው።

ክወና

አቦይ ስብኃት ነጋ …. መቼስ ጡር አይፈሬ ነዎት – ባለመስቃ። ጸጉረዎት ላይ ዬበቀለው ዬዕድሜ ጸጋነት ለሰባዕዊነት ጸር መሆነዎትን ስለሚያውቅ ብን ብሎ ለመጥፋት አስቦ ግን አያ ሆይ ዕድሜ አሻም አለው። „ከአጋም ዬተጠጋ ቁልቋል“ ሆኖበት ይሄው ሌትና ቀን ኤሉሄውን – ያስነካዋል። ምህላውን በተደሞ ለፈጣሪው ያቀርባል። ከቶ አንድዬ በቃህ ከአቦይ ስብኃት ዬተጠጋህ ዬግራጫ ጸጉር እድምተኛ ይለው ይሆን? ምነው ሥርይት በወረደለት – እንዲህ ዬአደባባይ መፈራረጃ ከሚሆን …

ዬቡግንጅ ኮሶ

ሊያገረሽ ኮስኩሶ፤

አግበስብሶ —-

ግፍ አንተርሶ

መከራ አርሶ።

ለቀበር ይሆን ተምሶ?

ነቀዝ ጠዬቀ ካስማ

ደግሞ ሊያገማ፤

ዬአድሮ ጥጃ ጉልማ።

ዬአለቅት ሙሽራ

እፋኝት ድሮ ሊያቅራራ፤

ዬምስጥ – ገራራ

ዬጃርት ዓውራ።

16.01.2017

አቦይ ስብኃት ነጋ —- ይህቺ ዬሥንኝ ቋጠሮ እርስዎን – ትመስላለች። እናም ያጣጥሟት። ዋጥ – ስልቅጥ ያድርጓት። ከውስኪዋ ጋር ከሆነችማ ሌልኛ ትሆናለች። በቃኝን፤ ትእግስትን፣ እርጋታን፣ ስክነትን – ዬትና መቼ ይሸምቷቸው ይሆን? ዬግራጫ እሮ፣ ሞሮ፤ ይብቃኝ።

ኢትዮዽያዊነት ፈተናን አሸንፎ ዬተፈጠረ ሚስጢር።

መሸቢያ ጊዜ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s