ለባንዳዎች ፕሮፓጋንዳ ምላሽ አለን በአሥራ አንደኛው ሰአት ላሉት – ለይገረም አለሙ

ካለፉት 50 እና 60 ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ የባንዳዎች መለዋወጫና መሰበጣጠሪያ መናኅሪያ ሆናለች። በኢትዮጵያችን ማንም ትውልድ በዚህ መሰል ውጣ ውረድ አላለፈም። የባንዳዎችን ቅብብሎሽ የለመደ ትውልድ ጀግና ሊያፈራ አልቻለም። የትናንቷ ኢትዮጵያ የዛሬይቷና የነገይቷ ኢትዮጵያ መሠረት ናት። ለናሙና የምናያቸውም ጀግኖቻችን የኢትዮጵያ ልባስ ናቸው። በእኛ እምነት ዛሬ ኢትዮጵያ የምንላት አገር በትናንቷ ኢትዮጵያ መስራቾችና ጽናትና አላማ በሐቀኞች ልጆቿዋ ትከሻ ላይ የቆመች ናት።

ጀግንነትና ጀግናን እያጣጣልን ባንዳን ማሞከሻት ባህል በማድረጋችን ለአገር ክብርና ሰማዕትነት የቆሙትን ወገኖች እንደፈራለን፣ እንተቻለን። በዚህ የተነሳ አገር ሻጮችን የአገር ክብር ለሚያዋርዱ ሰለባ ሆነናል። ኢትዮጵያችን ከምንም በላይ የበለጠ ሃብትዋና ኩራትዋ የዘመናት ጀግንነትና የተከፈለው መሰዋዕትነት መሆኑን ትውልዱ እንዲረዳው የዘመናችን ጀግኖች አቅፈን ባለመያዛችን ምክንያት በክህደት ባህር እየሰመጥን ነው። እውነትና በእውነቱና በሐቀኛ ቅርፁና መልኩ ተሟጋች በመጥፋቱ የዛሬው የእብደት ዘመን ላይ ደርሰናል።

 

መቼም “ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ” እንደሚባለው ለኢትዮጵያዊነት ትግል ግንባራቸውን ሰጥተው ከወያኔ ጋር ተፋጠው መራራውን ፅዋ የቀመሱትን ስናነሳ የሚገባ ክብራቸውን በመንፈግ ከሆነ፣ የምንሰጠው ትችት በሕዝብ ሕሊና ይመዘናል። እነዚህ የክፉ ቀን ልጆች የምንላቸውን ከወያኔ ጋር በተደረገ ግብግብ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱ ኢትዮጵያዊነት ድምፁን ከፍ አድርጎ የሚያሰማው ምስክርነት ነው። ዝምታችንን ሰብረን ለእውነት ከቆምን እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች ወደ ትግሉ ሜዳ ሊፈሱ ይችላሉ። በቅጥፈት ፐሮፓጋንዳ ግን ስብዕናቸውን የምንነካ ከሆነ ታጋይ አናገኝም።

 

ሰሞኑን ዶ/ር ታየ ወልደሰማያት በመጨረሻው 11ኛ ሰዓት በመድረክ ብቅ አለ በሚል ፅሑፍ ከአንድ ግለሰብ የተጻፈውን ፅሑፍ ለንባብ በቅቷል። በዚህ አጋጣሚ ፀሐፊውን ሌሎች ከዜሮ ሰዓት የጀመሩት ምን ፈጸሙ? የት ደረሱ? የሚለውን ጥያቄ እንድመልሱ እንጋብዛቸዋለን። ዶ/ር ታየን ጥላሸት መቀባት በዲያስፖራው አናት ላይ ቁጢጥ ካለው የክህደት ደቀመዛሙርቶች ጋር መቧደን አይሆንም ወይ? ፀሐፊው የዶ/ር ታየ ወደትግሉ መድረክ ብቅ ማለት ያስደነገጣቸው ይመስላል።

 

እኞ ግን ዶ/ር ታየን ታላቅ ተጋድሎአቸውና ራዕያቸውን እስከወዲያኛው ዘመን በታላቅ አክብሮት ጋር የምንጠቅሰው ነው። በጐ ጐኑ ለትውልድ ቅብብሎሽ የሚወሳ ነው። የወያኔን የካንጋሮን ፍርድ ቤት በፊት ለፊት የወነጀሉ፣ በወያኔ ካድሬ ዳኞች አልዳኝም የሚል ቃል ያሰሙ፣ በተጨማሪም የግፍና የበቀል እርምጃ ለሚንገላቱ ወገኖች የሞራል ልዕልናን ያጐናፀፉ ናቸው። በሲቪክ ድርጅት ተቋም ኢዲሞክራሲ አገዛዝን በትግል ለመፈተን ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል። ድፍረትን አስተምረው ትውልድን ለመታደግ በከፈሉት መሰዋዕትነት በጐ ምግባራቸውን ይህ ትውልድ እንዲያነሳ ሞራላዊ ግዴታ አለበት።

 

ተጋድሏቸውን ለማደብዘዝ የሚደረገው ጥረት በዲያስፖራው የተደበቁትን ከሃዲዎች ማንነት ተሃድሶ ለመስጠት የሚደረግ ጥረት ለመሆኑ በግልፅ ያሳያል።

በቅርቡ የዶ/ር ታየን በፖለቲካ መድረክ ብቅ ማለት አስመልክቶ በሜዲያ የተለቀቀው ፅሑፍ አስተዛዛቢ ነው። ዶ/ሩን ለመመዘን የተሞከረበት የፕሮፓጋንዳ ፅሑፍ ታማኝነት ይጐለዋል። ለነጻነት ትግሉ ቆራጥ ታጋይዎች ሳይሆን የሚያስፈለጉት የቆሸሸ ታሪክ ያላቸው የዛሬይቱንም ሆነ የነገይቷን ኢትዮጵያን መከራዎች ከማባባስ ያለፈ ፋይዳ የሌላቸውን የሚመርጥ ይመስላል።

 

የወያኔ አገልጋይ የነበሩ በያዙት ሴራ የኢትዮጵያዊነትን የወደፊት ተስፋ ለማሳጣት ለቅጥፈታቸው ሰለባ የሚያደርጋቸው የሞራል ብቃታቸው የተሟላላቸውንና የዓላማ ጽናት ያላቸውን ሰዎች ነው። ባንዳዎች ውሸት እንዲነግስ ይሰራሉ፣ የፈጠራ ታሪክ ተአማኒነት እንዲያገኝ ብዙ ይጥራሉ። ዛሬ ቢያንስ በዲያስፖራው በቅጥፈት ተቀባይነት ተንሰራፍቶ ያለው፣ ባንዳዎች ሳይታክታቸው የውሸት ባህሪያቸው በአደባባይ ለማውጣት በመድፈራቸው ነው። ከወያኔ ባልተናነሰ ሁኔታ የፈጠራ ድርሳንን የሙጥኝ ያለው ባንዳዎች የሚጓዙበትን የጥፋት ጎዳና በጋራ ባህሪ አድርጎ የያዘው የዲያስፖራው ጀሌ የተሰጠውን ሐሰት በብብቱ አቅፎ የሚያሞቅ ለመሆኑ ለትዝብት እያየነው ነው።

 

የዘመኑ ባንዳዎች ከወያኔ ጋር በአንድ አልጋ ሲተኙ በነበረበት ወቅት እንደነ ዶ/ር ታየ ወልደሰማያት ያለና ብርቅየ የኢትዮጵያ ልጅ እውነተኛ የሰላማዊ ትግል የወያኔን የመጨቆኛ አውታር ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ አርበኝነትን ምን እንደሆነ በአርአያነት ያስተማሩ፣ ያስተባበሩ፣የመሩ ለመሆናቸው ታሪክ ይመሰክራል።ዛሬ በተቃዋሚ ስም በአመራር፣ በሜድያ በሌላም ስም በአናቱ ቁጢጥ ያሉት ሁሉ ከወያኔ ጋር እጅና ጓንቲ ሆነው ሲያገለግሉ በነበረበት ወቅት በግንባር ቀደምትነት ነፍሳቸውን ይማርና ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስና በኢንጅነር ሐይሉ ሻውል ዛሬ በሕይወት ባሉት ዶ/ር ታየ ላይ አድማ ሲያካሂዱ እንደነበር ይህ ትውልድ ያየውን ይመሰክራል። ትውልዱ ጨርሶ ተጠርጎ ሳያልፍ ይህን ሐቅ አስተባብሎ ባንዳዎችን በመሾምና በመሸለም የክፉ ቀን አለኝታ የሆኑትን የቁርጥ ቀን ልጆች ስያሜ መስጠት የምፀት ምፀት ነው። ዘመኑ የባንዳ ዘመን ለመሆኑ ከወያኔ ጉያ እየተፈለፈሉ ዛሬ በሕዝብ ፊት ለመቆም የደፈሩ ብዙዎች ናቸው።

 

በኢትዮጵያኖች ለህሊናው፣ ለህዝብና ለሃገሩ የሚቆረቆር፣ የእውነት ተሟጋችና የሞራል ልዕልና የተቀዳጁ ከምንላቸው በኩራዝ ተፈልገው ከሚገኙት አንዱ ዶ/ር ታየ ናቸው። ከደቂቅ እስከ ምሁር የግል ጥቅም አሳዳጅና አፋሽ አጐንባሽ በመሆን በወያኔ ጫማ ሲወሸቅ ለሃገር ቤዛ በመሆን ከወገን ጋር መራብን፣ መታሰርን፣ መንገላታትን በተግባር ያሳዩ፣ በወያኔ እስር ቤት እግራቸው በብረት ሰንሰለት ተይዞ በወያኔ የበቀል እርምጃ በአስከፊ የሞት ፅዋ አፋፍ ላይ እንዳሉ እያወቁ የጠላትን ጫማ ከመላስና ያላመኑበትን ተናግሮ ምህረት ከመጠየቅ ይልቅ በድፍረት ሞትን ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ወይንም ግንባራቸውን ለጥይት መስጠት የመረጡ ጀግና ናቸው። በዘመናችን በፍርሃት ተሸመድምደው ራሳቸው በጥፍራቸው ውስጥ ለመደበቅ ለሚዳዳቸው የዶ/ር ታየ ስም ፈውስ ሊሆንላቸው እንደሚችል ስንገልጽ እውነት ላይ በመቆም ነው።

 

የእኝህን ጀግና ሰው ተምሳሌነት ለታሪክ ከተከናወኑ አንድ እውነታ ጋር አያይዘን እንመልከት። እ.ኢ.አ በ1953 ዓ.ም የታህሳስ ግርግር ተብሎ የሚጠራው አንድ ታላቅ ኢትዮጵያዊ የሞራል ልዕልና ከትውልድና ከሃገር ጥቅም ጋር በማያያዝ የሰጡት ምስክርነት በአስረጅነት ማቅረቡ ለእውነት መሟገትና የሞራል ልዕልና ዋጋው ምን እንደሆነ ስለሚያስረዳ እዚህ ላይ እጠቅሰዋለው። እኝህ ግለሰብ አቶ ሽፈራው ደሳለኝ ይባላሉ። በ1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጊዜ በንጉሡ ላይ ለተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ድጋፍ ሰጥተዋል ተብለው በመንግሥት ተይዘው ከድሬደዋ ወደ አዲስ አበባ ከተላኩት አንዱ ሲሆኑ በፍርድ ገምድል ዳኞች ፊት ቀርበው እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፣ ጥቅሱ የተገኘው “ህሣሥ ግርግር መዘዙ” ከተሰኘው በብርሃን አስረስ የተደረሰ መፅሐፍ ላይ ነው።

 

አቶ ሽፈራው ከድሬድዋ ወደ አዲስ አበባ ተልከው ለፖሊስ ቃላቸውን ሰጥተው ፍርድ ቤት ቀረቡ። የዕምነት ክህደት ቃል ሲጠየቁ ዳኛው ሰርተሃል ሰለተባለው ወንጀል ጥፋተኛ ነህ፣ አይደለህም? ይላቸዋል “የቱን ወንጀል” ሲሉ አቶ ሽፈራው ዳኛውን ይጠይቃሉ። ዳኛው አቶ ሽፈራው ሰርተዋል የተባለውን የወንጀል ቃል ሊናገሩት አልወደዱም፣ አልደፈሩምና “አንተ የሰራሃውን” ብለው ጠየቁ። አቶ ሽፈራው ”እስቲ“ ወንጀል የተባለው ይነበብልኝ? ብለው አጥብቀው ይጠይቃሉ። ይህን ጊዜ ዳኛው ሳይወዱ “ይህ ጣሳ” (ንጉሡን) መሆኑ ነው፡ እግዚአብሔር ገላግለን፣አወረድልን ማለትህን። ለዚህ ጥፋተኛ ነህ አይደለህም ይሏቸዋል። “የለም ተስተካክሎ ይጻፍልኝና የእምነት ክህደቴን ልናገር” ይላሉ። ዳኛውም የለም በዚህ ላይ ጥፋተኛ ነኝ በል፣ ይሏቸዋል። “ትክክለኛ ቃሌ ይፃፍና ነው እንጂ እንዲሁ ጥፋተኛ ነኝ” አይደለሁም፣ አልልም ብለው ይመልሳሉ። “እሺ ምን ተብሎ ይሰተካከል ሲሏቸው” ይህን የበሰበሰ የተጠረማመሰ አሮጌ ጣሳ እግዚአብሔር ገላገለን ነው ያልኩት ሲሉ ዳኞቹ የተባለውን አልሰማንም ለማለት ራሳቸውን ጠረፔዛ ስር አግብተው ተደበቁ።

 

የእኝህ ጀግና ኢትዮጵያዊ ቃል ስር ለሰደደው አደርባይነት እና የሞራል ክስረት ፈዋሽ ነው። ዶ/ር ታየ የሞራል ልዕልና የተቀዳጁ ለመሆናቸው ልክ እንደ አቶ ሽፈራው ደሳለኝ ባመኑበት መቆምን ያስተማሩ ናቸው። እንደብለሃት ወይንም እንደብልጥነት ተደርጐ በሚወሰደው የአደርባይነት ስልት አልተመላለሱበትም። እዚህ ላይ የአቶ ሽፈራውን ጉዳይ ለንፅፅር ያቀረብነው ክብርንና ማንነትን ከውልደት ጋር የሚገኝ ለጥቂት ሰዎች የሚሰጥ ፀጋ መሆኑን ለማሳየት ነው።

 

ሰው ሞቶ ስላላለቀ ዶ/ር ታየ ላይ ተቃውሞ የምትሰነዝሩ ባንዳዎች ተሟጦ ወደአለቀው ሕሊናችሁ ተመለሱ። ስለዛሬው 10 ዓመት ስናወራ እንጠንቀቅ። የቅንጅት ዓለም አቀፍ አመራር እና የቅንጅት ዓለም አቀፍ ምክር ቤት ስንገመግም ማን የራስን ቡድናዊ የበላይነት ለማንገስ በተደረገ ሴራ ስለቅራኔው አመጣጥ እና ያስከተለውን ችግር፣ የከፋ መዘዝ እንዲሁም ለችግሩ መባባስ በአሉታዊ ገፅታው አደገኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ግለሰቦች እነማን እንደሆኑ ይታወቃል። ዛሬ በግንቦት 7 ውስጥ ያሉትና ተንጠባጥበው በየፌርማታው የወረዱት ሁሉ ቀጥተኛ ተጠያቂዎች ናቸው። የሐሰት መረጃ እያቀረበና በቅንጅት መሃል ልዩነት እንዳለ በማስወራት በህብረተሰቡ ውስጥ እጅግ አደገኛ ውዥንብሮችን በመንዛት የቅንጅት አመራር ግለሰቦችን ስም እያነሳ ክፍፍል በመፍጠር ትግሉን አለንበት ደረጃ ያደረሰው የነአንዳርጋቸው ፅጌ ቡድን እንደነበር ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው።

 

በዓለም ዙሪያ በአንድ መንፈስ የተደራጀውን እጅግ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ የመቻቻል፣ የፍቅር የአንድነት እምነትና ተነሳሽነትን ያጨለመው ይሄው ቡድን ነው። ግለሰቦች ለግል ስልጣንና ዝናቸውን ሲሉ የወሰዱት አስነዋሪ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ምክንያት በቡድናዊ የገመድ ጉተታ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸው ነበር። የቀድሞውን የቅንጅት ዓለም አቀፍ አመራር መፈራረስ ስንገመግም በዶ/ር ታየ ላይ የአመልካች ጣታችንን ስንጠቁም የቀሩት ጣቶች ጉዳዩ ወደሚመለከታቸው እንደሚጠቁም አንዘንጋ። በዚህ ወቅት የቅንጅት ዓለም አቀፍ አመራር ቅራኔዎችን ለመፍታት የተፈተነበት ወቅት በመሆኑ ድርጅቱ የቀፋቸው የአመራር አባላት ዕድሜ፣ ብስለትና ተመክሮ ተቀናጅቶ መፍትሔ ያመጣሉ፣ ያረጋጋሉ ሲባል በሰዎች የዕድሜ ገደብ ሊለካ የማይችል አሳፋሪ የሞራል ዝቅጠት ተነክረው እንደነበር ማስገንዘቡ የግምገማው አንዱ ዋንኛ እንደነበር ከወዲሁ እናስረግጣለን።

 

ዶ/ር ታየ በዚህ የድርጅት ቡድናዊ ገመድ ጉተታ ውስጥ አላለፉበትም። ለፖለቲካው ሽፍጥ በዋና ተጠያቂነት የምንጠቅሰው ቡድን ዛሬ በግንቦት 7 መሽጓል። ይህ ቡድን ነው በስም ማጥፋት ዘመቻ ውድ የኢትዮጵያ ልጆችን ከትግሉ ሜዳ እንዲወጡ ያደረገው። የአፍራሽ ተልዕኰ ያላቸው ነውጠኞች ባካሄዱት እኩይ ተግባር ብዙ ሰዎችን አጥተናል። በአሁኑ ወቅት ዶ/ር ታየ ወልደሰማያት ወደትግሉ ተቀላቀሉ ማለት፣ የፈራውን ከማጀገን፣ ትውልዳዊ ግዴታን ከመወጣት የተበላሸውን የኢትዮጵያን ገድል በፅናት ከማቆም፣ ታጋዮች ወደትግሉ መድረክ እንዲጐርፉ ከማድረግና የፋኖ ዜማ ከማሰማት የዘለለ ዓላማ ስለሌለው ሁላችንንም ደስ ሊለን ይገባል። http://ethiopatriots.com/sound/LeBandawochMelash20170115EA.mp3

ኢትዮጵያ አንድነት ራዲዮ ስዊድን ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s