የችግሮቻችን መፍትሄ የሚገኘው ሁሉንም ባለድርሻ ያሳተፈ ብሄራዊ መግባባትና እርቅን መሰረት ያደረገ ሀቀኛ ድርድር ሲካሄድ ነው።

ባለፈው ሳምንት የገዥው ህወሀት/ኢህአዴግ መሪና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስቴር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ  ከተቃዋሚዎች ጋር ለመነጋገር እንደሚፈልጉ ከተናገሩ ወዲህ በሀገር ውስጥ በህጋዊነት ተመዝግበው የሚገኙ ፖለቲካ ድርጅቶች ተገናኝተው በድርድሩ አካሄድና አጀንዳ አቀራረጽ ላይ ውይይት እንዳካሄዱ በቀጣይም ተገናኝተው ለመነጋገር  እንደወሰኑ ተገልጿል።

በሀገራችን ውስጥ እጅግ እየሰፋ፣ እየተካረረና እየተወሳሰበ በመሄድ ላይ ያለውን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ሌሎችም ምስቅልቅሎች ተደማምረው አገርን እስከማፍረስ የደረሱ አደጋዎች በተጋረጡበት በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የገጠማትን ሁሉን አቀፍ ችግር ከሁሉም የአገራቸው ጉዳይ ከሚያገባቸው ኃይሎች ጋር  በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መቻል እጅግ አስፈላጊ አንደሆነ በማመን ገዥው ህወሀት/ኢህአዴግ  ከተቃዋሚው ጋር ተቀምጦ ሀቀኛ ውይይት እንዲያደርግ ድርጅታችን የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሽንጎም ይሁን ሌሎች ተቃዋሚ ድርጅቶች ደግመው ደጋግመው ሲጠሩ እንደነበር ይታወሳል።

በሀገራችን ውስጥ የሚታዩት መጠነ ሰፊ በደሎች፣ ያስከተሏቸው ብሶቶችና እነዚህ ብሶቶችም የወለዷቸው  ተቃውሞወች እጅግ ብዙ ገጽታወች ያሏቸው  ከጊዜ ወደ ጊዜም መልካቸውን እየቀያየሩ  እየሰፋና እየተወሳሰቡ በመሄድ ላይ የሚገኙ ናቸው።

ዛሬ የሚታዩት ብዙዎቹ ችግሮች በስልጣን ላይ ያለው ህወሀት/ኢህአዴግ በፖለቲካ ሥርዓቱ ቁንጮ ላይ ለብቻው ዕድሜ ልክ ለመቀመጥና ለመግዛት እንዲያመቸው ከሚያካሂደው ሰፊ የግፍ ተግባር፤ ከደነገጋቸው አፋኝና ጸረ ዲሞክራሲ ህጎች ፣ ዕለት ተዕለት ከሚያካሂደው አድልኦ፤ ሁለንተናዊና መጠነ ሰፊ የመብት ገፈፋ፣የመሬት ነጠቃ፤ የህግ የበላይነት አለመኖር፣ ከድህነት፣መስፋፋት የተነሳ በተለይ ወጣቱ ብሩህ ተስፋ ማጣት ወዘተ የሚመነጩ ናቸው።

አንዳንዶች ደግሞ ረዘም ያለ ታሪካ ያለቸው ሲሆኑ እነዚህም ችግሮች በጊዜው መፍትሄ እንዲያገኙ ስላልተደረገ ወይንም ችግሮቹን ባግባቡ ከስር መሰረቱ ለመፍታት ባመለቻሉ ሲንከባለሉ ቆይተው ቀደም ካሉ ጊዜያት የተወረሱና አሁን ያለው ሥርዓት ደግሞ ከሚገባ በላይ አጡዞ እንዲባባሱ ያደረጋቸው ናቸው።

አንዳንዶቹ ችግሮች አሁን ባለንበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ለሚመለከታቸው የተወሰኑ አካባቢዎችንና ማህበራዊ ክፍሎችን የሚመለከቱ መስለው ቢታዩም፤ ሁለመናዊ የአገሪቱን ችግሮች ነፀብራቅ በመሆናቸው ሁነኛና ዘላቂ መፍትሔ ካልተበጀላቸው፤ ወደ አገር አቀፍ ቀውስ ማደጋቸው አይቀሬ ነው። ከሚታዩት ችግሮች ውስጥ በርካቶቹ ሁለንተናዊና ሀገር አቀፍ ገጽታ ያላቸው ናቸው። አንዳንዶች በቀጥታ የፖለቲካና የሰብአዊ መብት ችግሮች ናቸው። ሌሎች ደግሞ ከእምነት/አመለካከት ነጻነት ጋር የተየያዙ ናቸው።

ባጠቃላይ ሀገራችንና ህዝባችን የተጋረጡባቸው ችግሮችና ቀውስ ዘርፈ ብዙ፣ የተወሳሰቡና መዋቅራዊም ናቸው። ኢትዮጵያውያን ሁሉ የተሳሰርንና ተጋምደን የምንኖር ስለሆነም ባንዱ የህበረተሰባችን ክፍል ላይ ወይንም ባንድ የሀገራችን አካባቢ የሚከሰት ችግር ሌሎች የሀገራችንን ማህበረሰቦችና ክፍለ ግዛቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንካቱ አይቀርም።

የተወሳሰቡት ችግሮቻችን ሁለንተናዊ መፍትሄን ይሻሉ፤ መፍትሔዎቹም ሊመጡ የሚችሉት ደግሞ ከገዢው ቡድን ብቻ ወይም ከተወሰኑ ተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊሆን ይገባል። ይህን ለማድረግ በጋራ በግልጽነትና በቅን መንፈስ መወያየትንና ለጋራ ችግሮቻችን በሰጥቶ መቀበል መንፈስ የጋራ መፍትሄ መፈለግን የግድ ይላል። ባጭሩ ሀገራችንና ወገኖቻችን ከገቡበት አስቸጋሪ ሁኔታ ወጥተው የግጭትና የቀውስ አዙሪትን ለመስበር ከተፈለገ  ሁሉም ባለድርሻወች የተሳተፉበት ብሄራዊ መግባባትና ብሄራዊ እርቅን መሰረት ያደረገ ለውጥ የግድ ይላል።

ህወሓት/ኢህአዴግ ለ25 ዓመታት ለብቻው ሁሉንም በመቆጣጣርና ሁሉንም ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችን በማፈን ለመጓዝ ሞክሯል። ነፃ የህዝብ ተቋማትን ደፍጥጦ ከአካባቢ ማህበራት ጀምሮ እስከ ፕሬዝዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ በኢህአዴግና በተለጣፊዎቹ ብቻ በመሙላት፤ አገሪቱ በማሌሊታዊ አስተሳሰብ እንድትመራ አድርጓል። ሆኖም፤ ከ25 ዓመታት በኋላ አገሪቱ የደረሰችበትን ሁኔታ በገሃድ እያየነው ነው። የተወሰኑ የልማት እንቅስቃሴዎች ለብቻቸው ምንም ማለት እንዳልሆኑ በገሃድ ታይቷል። ልማት ሁሉም ህዝብ  እጅጉን የሚፈልገውና የሚመኘው መሆኑ አያጠራጥርም። ነገ የሚተካው መንግሥትም ቢሆን አገሪቱን ሳያለማ መግዛት እንደማይቻል ይታወቃል። የህዝብን ሁለንተናዊ ፍላጎቶች ያላሟላ ልማት ለብቻው ግን የትም እንደማያደርስ ጥልቅ ግንዛቤ ያሻዋል።

በዚህ መሠረትም፤ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ የተከፈተው ውይይትም ፋይዳ ያለው እንዲሆን ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ውስብስብ ችግሮቻችንን ደረጃ በደረጃ በድፍረትና በብቃት ለመመርመርና መፍትሄ ለመፈለግ መቻል ይኖርበታል። ድርድሩ ሥልጣንን ያማከለ ከመሆን የዘለለና የዜጎችናና የአገር ጥያቄዎችን ማእከል ያደረገ መሆን ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ድርድር ታጥቦ ጭቃ ከመሆን እንዳማያልፍ ከወዲሁ ግንዛቤ ማግኘት አስፈላጊ ነው።

ባለፉት 25 አመታት በተደጋጋሚ እንደታየው ሁሉ ህወሀት/ኢህአዴግ  ከተቃዋሚዎች ጋር ለመደራደር እፈልጋለሁ የሚለው አሁንም ከገባበት ቀውስ ለማገገም፣ ጊዜ ለማግኝት የህዝቡንና የተቃዋሚውን ግፊት ለመቀነስና በመጨረሻም እንደገና አንሰራርቶ የተለመደ አግላይና የግፍ አገዛዙን ለማስቀጠል ከሆነ እጅግ ታላቅ ስህተት ውስጥ እንደሚወድቅ ከወዲሁ ሊገነዘበው ይገባል። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚወራውን ብቻ ሳይሆን የሚደረገውንም በቅርበት ይከታተላል። መብቱ ሙሉ በሙሉ እስኪከበርም ከጀመረው ትግል አይዘናጋም። ይህ እውነታ ለሁሉም ግልጽ ሊሆን ይገባል።

በኛ እምነት ውይይቱ ውጤታማ እንዲሆን ፡

  • በተለያየ ሰበብ አስባብ  ለእስር የተዳረጉትን የፖለቲካ እስረኞች ሁሉ በተለይም ደግሞ አንደ አንዱአለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ፤ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናና ኮሎኔል ደመቀን የመሳሰሉ የፖለቲካ መሪዎች፣ እንደ እስክንድር ነጋና ተመስገን ደሳለኝ፣ የመሳሰሉት ጋዜጠኞች  ወዘተ አሁኑኑ እንዲፈቱ  ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ይሆናል። ባጠቃላይ የህሊናና የፖለቲካ እሥረኞች ሁሉ አላንዳች ቅድመ ሁኔታ  ከእሥር ነጻ ሊሆኑ ይገባል።
  • መሰረታዊ የሆኑ የዴሞክራሲ መታፈንን፣ የሰብአዊ መብት መገፈፍን፣ የህግ የበላይነት መጥፋትን የመሰሉት ጉዳዮች በግልጽ ውይይት ተደርጎባቸው እነዚህን እውነታዎች ለ25 አመታት ያስቀጠለው ሁኔታ የሚወገድበትን መንገድ በጋራ መሻት የግድ ይላል፡። በግፍ የተጎዱ ሁሉ ሊካሱ የሚችሉበትን ሁኔታም ማመቻቸት ተገቢ ነው።
  • መሰረታዊ መብትን የሚገድቡና የሚጥሱ ህግጋቶችን ለምሳሌ የሲሺክ ማህበራትን፣ የፖለቲካና  የመብት ታጋይ ድርጅቶችን እንዲሁም መስል  እንቅስቃሴዎችን የሚያኮላሸውን ህግ፣ የጸረ ሽብርተኝነት ህግ፤ የሚዲያ ሕግ ወዘተ መሰረዝ አስፈላጊ ነው። ህገ መንግስቱም የሀገራችንን ህዝብ ፍላጎት በሚያንጸባርቅ መልኩ የሚሻሻልበትን ሁኔታ መመርመርና መተግበር ይኖርበታል።
  • በቅርቡ በአማራ በኦሮሞና ሌሎችም ክልሎች የተነሱትን የብዙ ወገኖቻችን ህይወት የተገበረባቸው መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች በጥሞናና በሀገራዊ ሀላፊነት መመርመር መወያየትና መፍትሄ መፈለግን የግድ ይላል፡ በነዚህ አካባቢዎች የሚካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻም ባሰቸኳይ መስቆም የግድ ነው፡
  • በህዝባችን ላይ የተጫነውን የጭንቅ ቀንበር ማስወገድ አስፈላጊ ነው። ለዚህም በመላ ሀገሪቱ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና ኮማንድ ፖስት ባሰቸኳይ ማንሳት ያስፈልጋል። ማንም ኢትዮጵያዊ  አሁንም ከየሰፈሩ እየተጎተተ የማይታሰር በወታደርና ደህንነት ሰራተኞች የማይደበደብ፣ እንደፈለጉ የማያስሩት እንደሚሆን ከቃላት ባለፈ በተጨባጭ ማሳየት አስፈላጊም አጣዳፊም ሆኖ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን አለበት።
  • በሀገሪቱ መሰረታዊ የፍትህ ሥርአት፣ የምርጫ ቦርድ፣ የምርጫ ሂደት፣ የሰራዊት እዝ፤ የደህንነት ቢሮ፤ ወዘተ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነትና የፓርቲ ተቀጽላነት ወጥተው መላ ህዝብን ሊያገለግሉ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት ማካሄድና መሰረታዊ የእርምት እርምጃም መወሰድ ይኖርበታል።
  • የጋራ ችግሮቻችንን ከስር መሰረቱ ለመፍታትና ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ፣ አግላይነትን አስወግዶ በሀገር ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ሁሉ የሚሳተፉበት ሂደትን ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል። ብሄራዊ መግባባትና እርቅ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ስብስብ ወይም ድርጅት የፈለገውን ወስኖ በሌላው ላይ የሚጭነው ወይም “ከፈለጋችሁ ተቀበሉ ካልፈለጋችሁ ተውት “ የሚባል ሳይሆን፣ ሁሉም ወገን የሂደቱም ሆነ የውጤቱ ባለቤት ሊሆኑ የሚችሉበት መሆን ይኖርበታል። ያሁኑ አካሄድም ገና ከጅምሩ ሁሉንም ባለድርሻዎች ያሳተፈ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ነው።

ሽንጎ ደግሞ ደጋግሞ እንደገለጸው ፍላጎታችን በሀገራችን ውስጥ ህገ መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ ነው። አንድነት፣ እኩልነት፣ የህግ የበላይነትና ዴሞክራሲያዊ መብትን ተግባራዊ ማድረግ ነው። ይህን በማድረግም የአመጽ፣ የጦርነት፣ የአሳሪና ታሳሪ አዙሪት፣ ቂም በቀልና ቁርሾ  እንዲያከትም ማድረግ ነው።

ህዝባችንና ሀገራችን እጅግ ብዙ ስቃይ አሳልፈዋል። ይህ ሰቃይ ሊያበቃ በሀገራችንም ላይ በቀጣይነት የሚያንዣብበው አደጋ ከስር መሰረቱ ሊወገድ ይገባዋል። ህዝባችን በማንም የማይደፈር መብትና የተከበረ ህይወት እንዲኖረው ይገባል። ሀገራችንን ይህን ሁሉ ለማከናወን የሚያስችል ታላቅ ክብሯንም ለመጎናጸፍ የሚያበቃት እምቅ ሀብት፣እውቀትና ኃይል አላት።

ይህን እምቅ ኃይል  የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ለማድረግ ግን የፖለቲካ ስርአቱን ማመቻቸት ህዝብንም የነጻነት አየር እንዲተነፍስ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ሊሆን የሚችለውም ፍርሀትን ወርውረን “ለኔ ብቻ” የሚል የግል የፖለቲካ ድርጅት ጥቅምን የማሳደድን ሩጫ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ በማድረግ ወዘተ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተጠቃሚና የሀገሩ ባለቤት የሚሆንበትን ስርአት ሰጥቶ መቀበልና፣ ይቅር ባይነትን ባካተተ ብሄራዊ መግባባትና በብሄራዊ እርቅ እውን ስናደርግ ብቻ ነው።

ድርድር የቅራኔ መፍቻ መሣሪያ ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው ህዝባችንም ሆነ ተቀዋሚ ድርጅቶች የሀገራችን ችግሮች በሰላማዊ መንገድና በውይይት እንዲፈቱ ሲጠይቁ ኖረዋል። አሁንም እየጠየቁ ነው። የድርድርን  አስፈላጊነት ሲያጣጥል ሌላ ጊዜ ደግሞ በተደጋጋሚ ለፖለቲካ ፍጆታ እንደራደር እያለ ሂደቶችን ሲያደናቅፍ የቆየው ገዢው ሕወሀት/ኢህአዴግ ነው ። ዛሬም እንደራደር ብሎ ቀርቧል። የሀገራችን ሁኔታና የህዝባችን ጥያቄ በቸልታ የሚታለፍና ለነገ የሚባል እንዳልሆነ በመገንዘብ ከላይ የዘረዘርናቸውን የህዝብ ጥያቄዎች ያካተተና ሁሉንም ወገን ያሳተፈ እውነተኛ ድርድር እንዲደረግ እያሳሰብን ሀገራችንን ከአደጋ ህዝባችንንም ከቀጣይ ስቃይ በጋራ እንታደግ እንላለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s