ወያኔን እየታገልን ዴሞክራሲያዊ ባህልንም እናዳብር!

ያሬድ በላይነህ ከብራሰልስ ቤልጀም

ወያኔን መርገምና ማሳጣትን ብቻ የፖለቲካ ግባቸው አድርገው የሚሰሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ቆም ብለው ማሰብ ይገባቸዋል።ለተግባቦት እና አብሮ ለመስራት አስቸጋሪ የሆነውን ነባር የፖለቲካ ባህላችንን ፈትሸው ህዝቡን በጋራ እንዲቆም የሚያስችል ስልት መቀየስ ይገባቸዋል።ለውጡን ከላይ ብቻ ሳይሆን ከስር የህዝቡንም ስነ ልቦና ጠጋ ብሎ በመፈተሽ ከሚመጣ ሁለንተናዊ ለውጥ ጋር ካልተጣጣመ በቀር የወያኔ መወገድ በራሱ ኢትዮጵያን በአንዴ የዴሞክራሲያዊት ሃገር አያረጋትም።

ዴሞክራሲ ባህል ነው። ባህል ደግሞ ከህዝብ ማንነትና ስነልቡና ጋር ተቆራኝቶ የሚያድግ ነገር ነው።በነጻነት ማሰብን፣ በልዩነቶች ላይ ተነጋግሮ መግባባትን ወይም ባለመግባባትም ቢሆን አብሮ ለመስራት መፍቀድን፣ የኔ ብቻ ሃሳብ፣ እቅድ፣ ፖሊሲ ብቻ ትክክል ነው ከሚል ጽንፍ የረገጠ አስተሳሰብ ወጥቶ የተለያየ ሃሳብ ካላቸው ጋር ተነጋግሮ ለመስራት መፍቀድንም ይፈልጋል ዴሞክራሲ።ለዚህም ይመስለኛል በሃገራችን ውስጥ አንባገነን ስርአት አቆጥቁጦ ለመብቀል ለም የሆነ አፈር ውሃና አየር የሚያገኘው።ዛሬ ህዝባችንን የመከራ ፍዳ እያበሉ ያሉት ገዥዎች ከኛው መሃል የወጡ እንጂ ከሰማይ የወረዱ ስላይደሉ ለውጥን ስናስብ ከስርአት ለውጥ ጋር ህዝቡንም ልናመጣ ለምንሻው ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ያለውን ሁለንተናዊ ዝግጅት ማጤን ይገባናል።

ዛሬ ላይ ህዝቡ ጋር ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲኖር የመፈለግና ለዛም ለውጥ በቁርጠኝነት እስከመስዋእትነት የመቆም ፍላጎት ቢኖርም ህዝቡን ወክለው የፖለቲካ ትግሉን እንመራለን የሚሉት የፖለቲካ ልሂቃኑ ግን ውሥጣቸውን ሊፈትሹ ይገባል።ዛሬ በየማህበራዊ ሚዲያው እንደምንሰማው የጨረባ ተስካር የሚሉትን አይነት ፖለቲካን አንግሰው እንዲተራመሱ ህዝቡ ፈቃድ አልሰጣቸውም።በኢትዮጵያ መበታተን ላይ የኛን አዲስ ሃገር እንመሰርታለን እስከሚል ጥግ እንዲሄዱ ወክለነዋል ያሉት ህዝብ ፈቃድ አልሰጣቸውም ጩኸታቸውም ሆነ ቅዠታቸው የራሳቸው ነው።ይህ አይነቱ የፖለቲካ ስካር ደግሞ ስልጣን ማግኘትን ብቻ አላማ አድርጎ የሚንደረደር የጥቂት ግለሰቦች እብደት ነው።አንዳንዶች ግን ይህን መሰሉን ግለሰባዊ የፖለቲካ ስካር ድርጅታዊ ካባ አልብሰውት መታገያ አርማ ሊያረጉት ሲሯሯጡም ታዝበናል ይሁን እንጂ ህዝቡ ለዚህም ፈቃዱን አልሰጠም።ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ እጣ በልተው በማይጠግቡ ዘራፊዎችና ነፍሰገዳዮች እጅ ላይ ወድቋል።

ህዝቡ ማንኛውም የተገፋና የተማረረ  ህዝብ እንደሚያደርገው ከፍተኛ የነጻነት ፍላጎት አለው።ድህነቱ፣ኢፍትሃዊነቱ፣ተስፋቢስነቱ ለነጻነት የሚከፈለውን ውድ ዋጋ ህይወትን መስዋእት አድርጎ እስከማቅረብ አድርሶታል ግን ይህ ድፍረቱ ብቻ ግን የሚፈልገውን ለውጥ ሊያመጣለት እንደማይችል ካለፉት የትግል ተመክሮዎቹ ያየን ይመስለኛል።ደርግ አንባገነን ነበር የተኩት በሱ መቃብር ላይ ነጻነትን እናመጣልሃለን ብለው መላው የኢትዮጵያ ህዝብን ከጎናቸው አሰልፈው ከሚኒሊክ ቤተመንግስት ሰተት ብለው ገቡ።ጠባብ የብሄር ፖለቲካን ቢያቀነቅኑም ለአንድ ብሄር ነጻነት ነው የምንታገለው ቢሉም ህዝቡ በመማረሩ ብቻ ደግፏቸው ለድል በቁ። የቋመጡለትን የስልጣን መንበር ሲያገኙ የህዝብን ውለታ ረስተው ይገሉት ፣ያስርቡት ከዛም አልፎ በኑሮ ተማሮ ልጆቹ ለስደት ቀሪውም ተስፋቢስ ለሆነ ህይወት ዳርገውት አረፉ።እነሱን ከደደቢት በረሃ ጀምሮ እስከሚኒሊክ ቤተመንግስት ደጃፍ ድረስ ተሸክሞ ለስልጣን ያበቃቸው ህዝብ ዛሬ ሙሉ ለሙሉ በጠላትነት ቆሞባቸዋል። ለውጥ ይፈልጋል ለውጡ ደግሞ ያለፈውን የሚደግም መሆን የለበትም።አንዱን ጨቋኝ በሌላው የሚተካ ለውጥ ሌላ ማቆሚያ የሌለው የመከራ ድግስ ለትውልድ ከማቆየት ውጭ ጥቅም የለውም። ስለዚህ አንባገነኖችን ከማስወገዱ ጎን ለጎን በህዝቦች መሃል የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት በልዩነቶች ላይ ተባብሮ በጋራ የመስራት ስልጡን የፖለቲካ ባህልን አብሮ ማስፈንም ያስፈልጋል።

ነባሩን ባለመተማመንና በመጠፋፋት ላይ የቆመውን ኋላ ቀር የፖለቲካ ባህላችን ላይ የለውጥ ሰይፋችንን ልናሳርፍበት ይገባል።ፖለቲከኞቻችንም ትግላቸው የመንግስት ለውጥ ከማምጣት ባለፈ ለሁለንተናዊ የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ከሆነ ራሳቸውን መፈተሽና ለውጡን ከራሳቸው ሊጀምሩት ይገባል።የጎንዮሽ ትግሉን ትተው በጋራ ለመቆም ዛሬ ህዝቡ ውስጥ ያለው የለውጥ ፍላጎት የግድ ሊላቸው ይገባል።እንደ ሃይማኖት ቀኖና ከሚያዩትና ከሚያመልኩት ከራሳቸው የፖለቲካ ፓርቲ፣ ድርጅት ወይም ተቋም ፕሮግራምና አላማ በላይ የሃገር ህልውና እና የህዝብ ዘላቂ ተስፋ ሊያሳስባቸው ይገባል።በየጊዜው እየተቀጣጠሉ የሚጠፉ የለውጥ እሳቶች የተከፈለላቸውን ዋጋ የሚመጥንና የሚታይ ለውጥን ለህዝቡ ካላመጡ በትግሉ መማረንንና ተስፋ መቁረጥን ይጋብዛሉ።ያ ደግሞ የነጻነቱን ጊዜ ማርዘምን ብቻ ሳይሆን ጭራሽም ስለነጻነት ማሰብን ትቶ በምናገባኝ የሚኖርን ተስፋ ቢስ ዜጋን ያበራክታል።

የህዝቡን ትግል የመምራት ሃላፊነት ትከሻቸው ላይ የወደቀው ሃገር በብዙ ድካም ያስተማረቻቸው የፖለቲካ ልሂቃንም ከራሳቸው ትክለ ስብእና እና የፓለቲካ ግብ በላይ ሳይማር ያስተማራቸው ህዝብ መከራ ለእውነተኛ ለውጥ እንዲቆሙ ሊያተጋቸው ይገባል።በምናገባኝና በተለያየ ምክንያት ራሳቸውን ከፖለቲካው አግለው የተቀመጡም ምሁራንም በተመሳሳዩ የዛች ሃገርን ጎስቋላ ህዝብ መከራ እንዳላዩ ሆነው መቀመጣቸው ከህሊናና ከታሪክ ተጠያቂነት አያድናቸውም። የውጭውን አለም የዴሞክራሲ እና የሰብአዊ መብት በረከት ተቋድሰው የነጻነትን ምንነት በመኖር ያዩ በውጭ የሚኖሩ በኢትዬጵያውያንም ይሄ በጨካኞች ተረግጦ ያለ ህዝባቸውን ከመከራ ለማውጣት ለሚደረገው ትግል የተሻለ አስተዋጽኦ ማበርከት ሲችሉ በምናገባኝ ጀርባ መስጠታቸው አስተዛዛቢ ነው።

ነጻነት ብዙ ዋጋ ቢያስከፍልም እውነትና ፍትህ ጉልበት ሆነውት የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣቱ አይቀርም። ዛሬ ህወሃት ህዝቡን በጎሳ ከረጢት ውስጥ ከቶ ከፋፍየዋለው ብሎ ቢያስብም የነጻነት ፍላጎቱ ግን አንድ ያደርገዋል።ወያኔ መሰረትኩት የሚለው የብሄር ፌደራሊዝም የግለሰቦች ነጻነትን እውቅና ነስቶ የቡድን ነጻነት አስከብራለሁ በሚል ባዶ ትርክት ላይ የቆመ ጸረ ዴሞክራሲ ስለሆነ እንኳን ሌሎች ብሄሮችን ሊጠቅም ቆሜለታለሁ የሚለውንም ብሄር ተጠቃሚ አላረገም። ስለዚህ የህዝቡ የነጻነት ፍላጎት ያልተገደበ እና ከዳር ዳር ያለ በመሆኑ ይህ የነጻነት ጥማት በተገቢው ለውጥ እንዲታጀብ የስርአት ለውጥ ለማድረግ ከሚደረገው ትግል ጎን ለጎን ህዝቡንም እንዲመጣ ለሚታገልለት የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ የሚሆን ትክለ ሰውነት ማላበስ ያስፈልጋል።በችግሮች ላይ በግልጽ ተወያይቶ መግባባትን አሊያም ባለመግባባትም በጋራ ግቦች ላይ አብሮ የመስራትን ባህል ከወዲሁ መገንባት ይገባል።ከፓርቲዎች ቁመና በላይ ጎልቶ የሚታይን በህዝቦች ሁለንተናዊ ስብእና ላይ የሚመሰረት የዴሞክራሲ ስርአት ባህልን ለመትከልም ነገ ሳይሆን ዛሬ ላይ ሊታሰብ ይገባል።የምእራባውያኑ ዴሞክራሲ መሰረቱ ለሰብአዊ መብት ክብር ያለው ህብረተሰብ ነው። በህግና በስርአት የሚመሩ የፍትህ ተቋማትም የስርአቱን ቀጣይነት ደግፈው ያቆሙ ዋልታዎች ናቸው።እነዚህ በሌሉበት አንባገነኖችን በማስወገድ ብቻ የሚፈለገው ለውጥ አይመጣም።

ለነጻነቱ ክብር የሚሰጥ፣ባርነትን አምርሮ የሚጠላ፣ለሰብአዊ መብት ክብር በጋራ የሚቆም ህብረተሰብ መፍጠር ባልተቻለበት ሁኔታ ብቻውን በትግል የሚመጣ ለውጥ ህዝብን ከነጻነት ክብሩ ጋር አያገናኘውም።ካለፉት ለውጦች የተማርነው እውነት ይህንኑ ነው። የንጉሱ የፊውዳል ስርአት በህዝቡ ትግል መውደቅ ተፈላጊውን ለውጥ አላመጣም ይልቁንም በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ አንባገነንን ነው የተከለው ያም ለአንድ ትውልድ እልቂትና ዛሬም ሃገራችን ለገባችበት የጥፋት ማጥ ምክንያት ሆኗል።ደርግን ታግሎ በመጣልም ሌላ የባሰ ከፋፋይና ሃገር ለማፍረስ ሌት ተቀን የሚሰራ አውዳሚ ስርአት ተፈጠረ እንጂ ትግሉ በራሱ ህዝብ የሚናፍቀውን የዴሞክራሲ ስርአት አላመጣም።ለዚህም ነው ይህንንኑ ችግር ላለመድገም ዛሬ ላይ ለውጡ የማያዳግም አገር አድን እንዲሆን ጨቋኙን ስርአት ታግሎ ከመጣል ባለፈ ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲዳብር የህዝባችንን አስተሳሰብ እና ስነልቡና በመፈተሽ ጎጂ እርስ በእርስ የመጠላለፍና የመጠፋፋት ባህላችንንም እያከምን እንሂድ የምንለው።ትግሉን እየመሩ ያሉ የፖለቲካ ልሂቃንም ከኔ በላይ ላሳር ማለታቸውን ትተው ወደውጭ ብቻ ሳይሆን ወደውስጣቸውም እንዲታገሉ ጨቋኙን ብቻ ሳይሆን ተጨቋኙንም በሞራል ልእልና ከፍ አርጎ የሚያቆም ሁለንተናዊ ሰብአዊ ልእልና ሊያጎናጽፍ የሚችል የዴሞክራሲ ባህል ባለቤት ለማድረግ እንዲታገሉ የምንሻው።

ይህ ሲሆን ብቻ የህዝብ መስዋእትነት ተገቢውን ዋጋ ያገኛል።አንባገነንነት የሚበቅልበት ለም መሬት ያጣል።ወያኔንም ተሸክሞት የሚቆም የጭቆና ቀንበርን የሚሸከም ትከሻ ይጠፋል። ከፋፍሎና ለያይቶ ሊያቆመን የሚችልበት የህልውናው መሰረት የሆነውንም ጭቆናን የሚሸከም የወረደ ስብእናና  አድርባይ ማንነት ስለሚያጣ ወደማይቀርለት የጥፋት መቃብሩ ይወርዳል።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s