የአወዛጋቢው ት.እ.ም.ት (EFFORT) ምሥጢሮች በከፊል | ሊነበብ የሚገባው ጥብቅ መረጃ

 

በኦማን ኡሊያህ፣ ለአዲስስታንዳርድ የተጻፈ (ትርጉም)

ሁሉም አምባገነኖች የኢኮኖሚ ምዝበራ እና የበላይነታቸውን የሚያረጋግጡበት የቢዝነስ ዓይነት ወይ በግለሰቦች ሥም አሊያም በድርጅት ጭምብል ይኖራቸዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ፣ ምንም እንኳ ምዕራባዊ ወዳጆቿን ድህነትን በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እየተዋጋች እንደሆነና ዴሞክራሲዋን እያሻሻለች እንደሆነ ማሳመን ብትችልም፣ በጣም ድሃ እና ዝግ ሆነው ሀብትና ሥልጣን በጥቂት ሰዎች እጅ ከተወሰነባቸው አገሮች አንዷ መሆኗ አልቀረም፡፡ ከሁሉም በላይ የሆነው የገዢው ፓርቲ ልኂቃን ቡድን አንድ ሕዝብን መርጦ (ትግራይን) እወክላለሁ ማለቱ ደግሞ ከሌሎች አምባገነኖች ይለየዋል፡፡ በምላሹም ከሌሎች ክልሎች በተለየ ቡድኑ በትግራይ የበለጠ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ 

ይኸው የልኂቃን ስብስብ ብዙ ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያንቀሳቅስ የቢዝነስ ድርጅቶች ሰንሰለት አለው፡፡ ት.እ.ም.ት ይባላል፡፡ ት.እ.ም.ት (ትካል እግሪ ምትካል ትግራይ ወይም በእንግሊዝኛ ሥሙ ኤፈርት) በጦርነቱ ወቅት የተጎዳችውን ትግራይ መልሶ ለማቋቋም የተመሠረተ ኢንዶውመንት ነው፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ሕወሓት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያለተወዳዳሪ ሲነግሥ፣ ትእምት ደግሞ ትግራይን መልሶ በማቋቋም ሥም ትልቅ የቢዝነስ ተቋም ለመሆን በቅቷል፡፡ 

ትእምት ምንድን ነው? 

ላይ ላዩን ሲታይ ትእምት በኢንዱስትሪ፣ ባንኪንግ እና ኢንሹራንስ፣ ኢምፖርት ኤክስፖርት፣ ሚዲያ፣ ኮንስትራክሽን፣ ግብርና እና ማዕድን ማውጣት የመሰሰሉትን ሥራ የሚሠሩ ቢዝነሶችን ያቀፈ ተራ ዣንጥላ ነው፡፡

በ100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መነሻ ካፒታል ሥራውን የጀመረው ትእምት፣ አሁን ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት ሲያካብት ለ47,000 ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

የትእምት ኩባንያዎች መጀመሪያ የተመዘገቡት በሕወሓት ኃላፊዎች ሥም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እየተባሉ ነበር፡፡ በኋላ ግን የኩባንያዎቹ ባለቤቶች ድርሻቸውን ለግሰዋል ተብሎ በ1954ቱ የፍትሐብሔር ሕግ መሠረት ‹ኢንዶውመንት› ተብለው ድጋሚ ተመዘገቡ፡፡ ሆኖም፣ አሁንም የሕወሓት ሰዎች ዋና ሥራ አስኪያጆች ሆነው እያስተዳደሩት ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶቹን ለማበረታታትም በሚል ትንንሽ ድርሻ እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡

‘የመጀመሪያው ኩነኔ’: ሕወሓት ሀብቱን አንዴት አጠራቀመው? 

የትእምት ኦፊሴላዊ መግለጫ፣ የትእምት ቢዝነሶች የተመሠረቱት ሕወሓት በትግል ወቅት ያከማቸውን ሀብት ተጠቀሞ እንደሆነ ይናገራል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2008፣ የቀድሞ የሕወሓት ታጋይ አረጋዊ በርኸ፣ አምስተርዳም ለሚገኘው ቨርጀ ዩንቨርስቲ በሠራው የዶክተራል ዲግሪ ጥናቱ፣ የሕወሓት የፖለቲካ ታሪክን ሲተርክ፣ የመጀመሪያው የሕወሓት ስኬታማ ዘመቻ ‹ዘመቻ አክሱም› እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ከተማዋ የነበራት አንድ ፖሊስ ጣቢያ እና አንድ ባንክ ሲሆን፣ ሕወሓቶች ከፖሊስ ጣቢያው እስረኞችን ካስፈቱ እና መሣሪያ ከዘረፉ በኋላ፣ ወደአክሱም ባንክ ሔደው የገንዘብ ዘረፋ አድርገዋል፡፡ እንደ አረጋዊ፣ በዝርፊያው 175,000 ብር (በወቅቱ ግምት 84,000 ዶላር) ዘርፈዋል፡፡

ባንኮችን በመዝረፍ የተጀመረው የሕወሓት ሀብት የማካበት ጉዞ ቀጥሎ እጅግ አወዛጋቢ የነበረውን የእርዳታ ገንዘብ ለድርጅት ጥቅም ማዋል ላይ እንደደረሰ አረጋዊ በርኸ ይነግረናል፡፡ ሕወሓት፣ ትግል ላይ እያለ ማኅበረ ረድኤት ትግራይ (ማረት) የተባለውን የእርዳታ ድርጅት እንደ ክንፍ አቋቁሞ ነበር፡፡ አረጋዊ እንደጻፈው፣ “በጁን 1985፣ ማረት ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት በሚል አገኘ፡፡ ነገር ግን መለስ ዜናዊ ገንዘቡን እንደሚከተለው መደበው፤ 50% ለማሌሊት ምሥረታ፣ 45% ለሕወሓት ሥራ ማስኬጃ፣ እና ቀሪው 5% ደግሞ ለድርቅ ተጎጂዎች፡፡” እርግጥ ነው፣ እንደምንገምተው፣ የሕወሓት ኃላፊዎች ይህንን ክደዋል፡፡

አሁን አረናን ያቋቋመው የቀድሞው የሕወሓት ኃላፊ ገብሩ አሥራት ለምሳሌ፣ ‹ሉዓላዊነት እና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ› ባለው መጽሐፉ ላይ፣ ‹ትግል ላይ እያለን ብዙ ገንዘብ በእርዳታ እናገኝ ስለነበር፣ ገንዘቡን ለተለያዩ ተግባራት ማከፋፈል የሕወሓት ውሳኔ ነበር› በማለት የእርዳታ ገንዘብ ለፓርቲ ሥራ ውሏል ብሎ ለማለት ፈፅሞ አይቻልም ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ፣ በሕግ የሚያጠያይቁ ሀብት የማካበቻ መንገዶች፣ ፓርቲው የመንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላም መቀጠሉን የሚናገሩ አሉ፡፡ የቀድሞው የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዲኤታ፣ አዲስ ባሳተመው ሁለተኛ መጽሐፉ ‹የመለስ ልቃቂት› ላይ በትእምት አመሠራረት እና አቋቋም ላይ ብዙ አወዛጋቢ ነጥቦችን አንስቷል፡፡

በኤርምያስ 565 ገጽ መጽሐፍ ውስጥ ምዕራፍ ስድስት፣ ትእምት የገንዘብ ምንጩ ምን እንደሆነ እና እንዴት የአገሪቷን ገንዘብ ወደካዝናው እንዳዛወረ ይነግረናል፡፡ ኤርምያስ በ1986 በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ የተፈረመ ደብዳቤ ቅጂ አያይዟል፡፡ ደብዳቤው ሕወሓት በትግል ወቅት መድኃኒት ለሕዝቡ ያከፋፈልኩበት ወጪዬ ነው በሚል ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የዓመት በጀት ላይ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ (የወቅቱ ጠቅላላ በጀት 67 በመቶ) ለሕወሓት ገቢ እንዲሆን ይጠይቃል፡፡ በዚህ መንገድ ወደሕወሓት ካዝና ገቢ የተደረገው ገንዘብ 17 ሚሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ ኤርምያስ መድኃኒቱ ቀድሞውኑም ከፋርማሲ ተዘርፎ ለሕመምተኞች የተከፋፈለ መሆኑን አብሮ ያስታውሳል፡፡

ቀጣይ ኩነኔዎች እና አወዛጋቢ ሥራዎች 

የትእምት ኩባንያዎች ከግል ኩባንያነት ወደኢንዶውመንትነት መተላለፋቸውን ከላይ አንስተናል፡፡ ኢንዶውመንት ሆነው ድጋሚ ሲመዘገቡ ባለቤቶቻቸው ሀብታቸውን ለግሰዋል ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ይህም የሕዝብ ገንዘብ አልተጠቀሙም የሚለውን ሽፋን ለመስጠት የተደረገ ይመስላል፡፡ አሁን፣ ኢንዶውመንቱ ትርፉ ለግለሰቦች አይከፋፈልም በሚለው ሕግ ቢተዳደርም ለጥቂት ግለሰቦች የመክበሪያ ዕድል ሆኖላቸዋል፡፡

በ1996 በቀድሞው የሕወሓት ታጋይ የተመሠረተው የአማርኛው ሪፖርተር ጋዜጣ ትእምት ከሕዝብ ባንክ የተበደረውን እና የተሰረዘለትን ገንዘብ አወዛጋቢ ጉዳይ እየተከታተለ ይፋ አድርጓል፡፡ (የእነዚህ እትሞች ቅጂ በአዲሱ የኤርምያስ ለገሠ መጽሐፍ መዝጊያ ላይ በአባሪነት ተያይዘዋል፡፡)

እነዚህ ተከታታይ እትሞች እንዳስነበቡን፣ ትእምት 1.7 ቢሊዮን ብር ከመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይበደራል፡፡ ብድሩ ከነወለዱ 1.8 ቢሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ መጀመሪያ የንግድ ባንክ ኃላፊዎች ለትእምት ያበደርነው ገንዘብ የለም ብለው ካዱ፡፡ ነገር ግን ብድሩን ወደ ኢትዮጵያ ልማት ባንክ ማዘዋወራቸው ተደረሰበት፡፡ በመጨረሻም፣ ልማት ባንክ ብድሩን መሰብሰብ አልቻልኩም በሚል የዕዳ ስረዛ አደረገ፡፡ ኤርምያስ የትእምት ድርጅቶች መጀመሪያውንም ገንዘቡን የተበደሩት ያለምንም ማስያዥያ ነው ብሎ ያምናል፡፡ በቀጣዩ ዓመት፣ ልማት ባንክ ራሱ የ3.5 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰበት ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ያልተመለሰው የትእምት ብድር ብቸኛው ምክንያት ባይሆንም ለኪሳራው አንዱ ምክንያት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ሌላው አወዛጋቢ ጉዳይ ትእምት የቢዝነስ ሥራውን የሚያካሔድበት መንገድ ነው፡፡ ኃላፊዎቹ እንደሚሉት ለሕግ ያላቸው ታዛዥነት እና ጉቦ ለመክፈል ፈቃደኛ አለመሆናቸው ከሌሎች ጋር ዕኩል መወዳደር እስኪያቅታቸው ድረስ ለሥራቸው እንቅፋት ሆኗል፡፡ እነርሱ ይህን ይበሉ እንጂ፣ የትእምት ኩባንያዎች በጥቅሉ በመንግሥት ሠራተኞች ልዩ እንክብካቤ ነው የሚደረግላቸው፡፡ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን፣ እምብዛም ባልተለመደ ሁኔታ ታኅሣሥ 3 ቀን 2005 በልደታ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በዋለው ችሎት የተላለፈ ብይን ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ከትእምት አንዱ የሆነው እና በወ/ሮ አዜብ መስፍን የሚመራው ሜጋ የመዝናኛ ማዕከል ለቀደሙት 8 ዓመታት ሥራውን በማጭበርበር መንገድ እያካሔደ እንደነበር እና ገቢውን በማሳነስ እና ወጪውን አብዝቶ ሪፖርት በማድረግ ለመንግሥት የሚገባውን ግብር ሳይከፍል ቀርቷል ሲል በይኗል፡፡

ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ምሥጢሮች ግን አደባባይ የሚበቁት በባለድርሻዎች መካከል ግጭት ከተነሳ ብቻ ነው፡፡ በሜጋ ጉዳይ የአመራሩ አካል የነበሩት የአዜብ መስፍን እና የእቑባይ በርኸ ፀብ ምሥጢሩ እንዲወጣ ረድቷል፡፡

አሁንም ግን፣ ትእምት ምንድን ነው?

በዊኪሊክስ ሰነዶች ይፋ ከወጡ በኢትዮጵያ የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ያማሞቶ ደብዳቤዎች መካከል፣ ከቀድሞው የሕወሓት ታጋይ አቶ ስዬ አብርሃ ጋር ያደረጉት ንግግር ይገኝበታል፡፡ አቶ ስዬ ትእምት የተቋቋመበትን ምክንያት ሲያስረዳ “የአካባቢውን ሀብት ተጠቅመው ትርፍ ሊያመጡ የሚችሉ ኩባንያዎችን አጥንቶ በማቋቋም ለትግራይ የሥራ ዕድል መፍጠር ነው፡፡” ብሎ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ፣ ትእምት፣ ምንም እንኳን ጥሬ እቃውን እና ገበያውን ከትግራይ ውጪ ባሉ የኢትዮጵያ ክልሎችም የሚያገኝ ቢሆንም፣ በአብዛኛው (ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም) የሚቀጥረው ግን የትግራይ ተወላጆችን ነው፡፡

በመርሕ ደረጃ፣ ትርፉም ትግራይን መልሶ ማቋቋም አለበት፡፡ ነገር ግን ብዙ የትግራይ ተወላጆች ‹ኢንዶውመንቱ› ጥቂት የሕወሓት ልኂቃንን ለማበልፀግ ውሏል ይላሉ፡፡ የቀድሞ የትግራይ ክልል የዐሥር ዓመት ፕሬዚደንት እና የሕወሓት ታጋይ የነበሩት አቶ ገብሩ አሥራት ከላይ በጠቀስነው መጽሐፋቸው ላይ እንደተናገሩት፣ ትእምት በሕወሓት ኃላፊዎች እየተበዘበዘ ነው፡፡ አቶ ገብሩ እንዲያውም የትእምት ሀብት ተሰፍሮ በአክሲዮንም ቢሆን ለእያንዳንዱ የትግራይ ተወላጅ የሚከፋፈልበት መንገድ እንዲኖር እስከመጠቆም ደርሷል፡፡

‹ሌሎቹስ› ምን አላቸው?

አንድ የማያጠራጥር ነገር አለ፡፡ እስከ 1983 በተደረገው የ17 ዓመቱ ጦርነት ወቅት ሌሎቹም ክልሎች ጉልህ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በወቅቱ የአገሪቱ በጀት ዋና ወጪ ለወታደራዊ አለግለግሎት ነበር የሚውለው፤ ስለሆነም ሌሎቹም ክልሎች ‹ኢንዶውመንቶች› ያስፈልጓቸው ነበር፡፡

ይህንኑ በመረዳት ይመስላል፣ ሕወሓት፣ ለሌሎች እንዶውመንቶች መነሻ ካፒታል ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት፣ በኦሮሚያ ዲንሾ የነበረውና አሁን ቱምሳ የተባለው በኦሕዴድ አመራሮች እንዲመራ ሆኖ ተቋቁሟል፤ በአማራ ጥረት የተባለው በብአዴን እንዲመራ ሆኖ ተቋቁሟል፤ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ደግሞ ዎንዶ በደኢሕዴን አመራሮች እንዲመራ ሆኖ ተቋቁሟል፡፡

ስዬ አብርሃ “ሕወሓት የሀብቱን ጥቂት ክፍል ለነዚህ ለሦስቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ሰጥቷል” ሲል ተናግሯል፡፡ ይሁን እንጂ፣ እነዚህ ሦስቱ አንድላይ የሚያስተዳድሯቸው ኩባንያዎች ብዛት ከ20 በታች ነው፤ ትእምት ብቻውን የሚያስተዳድራቸው ኩባንያዎች በኦፊሴላዊ መንገድ የሚታወቁት 24 ቢሆኑም እስከ 380 እንደሚደርሱ ሌሎች ምንጮች ያሳያሉ፡፡ የኩባንያዎቹ ማንነት እና ብዛት ምሥጢራዊነት በራሱ ክፍተቱን ለመጠቀም ያለመ ይመስላል፡፡

በተቃራኒው ደሞ ሦስቱ – ኦሕዴድ፣ ብአዴን እና ደኢሕዴን ለ80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥራ ዕድል የመፍጠር ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህ እንግዲህ የሚነጻፀረው ሕወሓት እወክለዋለሁ ከሚለው ከ6 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ነው፡፡

‘Rethinking Business and Politics in Ethiopia’ በሚል ርዕስ በሳራ ቮጋን እና መስፍን ገብረሚካኤል እ.አ.አ. በ2011 የተሠራ ጥናት እንደሚያመለክተው “[የጥረት] ኩባንያዎች 2,800 ሰዎችን መቅጠር ችለዋል፡፡ ትእምት በአንፃሩ 14,000 ቋሚ እና 34,00 ጊዜያዊ ሠራተኞችን ቀጥሮ ያሠራል፡፡” የሚገርመው፣ በኢትዮጵያ በባሰ ድህነታቸው የሚታወቁት ክልሎች፣ ማለትም ሶማሊ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች የሚያቋቁማቸው ኢንዶውመንት የላቸውም፡፡ ነገር ግን የሚመሩት በኢሕአዴግ እህት የፖለቲካ ፓርቲዎች ነው፡፡

የትእምት ድርጅቶች የሆኑት እና ያልሆኑት

የትእምት ቢዝነሶችን በቀላሉ ለመረዳት የማያስችሉ ነገሮች አሉ፡፡ ሠላም ባስ አክስዮን ማኅበር ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1996 የተመሠረተው ሠላም ባስ 99.6 በመቶ የሚሆነው ባለቤትነቱ የትግራይ ልማት ማኅበር (ትልማ) ሲሆን ቀሪው በሌሎች ግለሰቦች ተይዟል፡፡ ሠላም ባስም እንደትእምት ኩባንያዎች የቦርድ አባላቱ የሕወሓት ሰዎች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ብዙ ሰዎች የትእምት ኩባንያዎችን ዘርዝሩ ሲባሉ መጀመሪያ የሚመጣላቸው የሠላም ባስ ሥም ነው፡፡ ይህ የተምታታ የባለቤትነት ጉዳይ ነው ምናልባትም ሠላም ባስን በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በተነሱ ተቃውሞዎች ላይ ተጠቂ እንዲሆኑ ያደረጋቸው፡፡

ደጀና ኢንዶውመንት ደግሞ ሌላ ምሳሌ ነው፡፡ ‹በትግራይ ልማት ለማሳለጥ› የተቋቋመው ደጀና ኢንዶውመንት የማረት ንብረት ነው፡፡ በደጀና ድረገጽ ሥር 11 ኩባንያዎች ተዘርዝረዋል፡፡  እ.ኤ.አ. በ2009 የወ/ሮ አዜብ መስፍን የትእምት ኃላፊ ሆኖ መምጣትን ተከትሎ ደጀና ኢንዶውመንት ከትምእት ጋር ተዋሃዶ ነበር፡፡ የትእምት ኩባንያዎች እርስበርስ ሼር እየተገዛዙ አንዱ ሲወድቅ ሌላኛው እንዲያነሳው ማድረግ የተለመደ አካሔዳቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ዛሬም ድረስ ስለደጀና እና ትእምት ውህደት ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በዚያ ላይ፣ የሁለቱም ድረገጾች እንዳሉ መቆየት ለተመልካች ሁለቱ ኢንዶውመንቶች የተለያዩ እንዲመስሉ ያደርጋል፡፡ የትእምት ኩባንያዎች እንደሆኑ የሚታወቁ አንዳንድ ኩባንያዎች የደጀና ናቸው ተብለው ተዘርዝረዋል፡፡

የሸገር እና የመቐለ ትንቅንቆች 

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ቢዝነስ እና ፖለቲካ መሐከል ያለውን ግንኙነት የታዘበ ተመልካች አገሪቱ በሁለት ዐብይ ትርክቶች እንደተከፈለች መረዳት አይከብደውም፡፡ እነዚህን ትርክቶች ‹የሸገር ትርክት› – በተለይ በአዲስ አበባ የሚውጠነጠነው እና፣ ‹የመቐለ ትርክት› – በተለይ በመቐለ የሚውጠነጠነው ትርክት ብዬ ከፍያቸዋለሁ፡፡

ይሁን እንጂ፣ ሁለቱም ትርክቶች እየተቦኩ ከሚጋገሩበት ማዕከል ውጪም እንደየግለሰቡ የፖለቲካ አመለካከት ከማዕከላቱ ውጪም ይገኛሉ፡፡ ‹የሸገር ትርክት› (ብዙ ተቀባይነት ያለው ትርክት) ሕወሓትን ቅቡልነት የሌለው ነገር ግን በኃይል ሥልጣን የያዘ መንግሥት አድርጎ ያየዋል፡፡ ‹የመቐለ ትርክት› ደግሞ በጥቅሉ ሕወሓትን ቅቡልነት ያለው ነገር ግን መሥመሩን በአባላቱ ሙሰኝነት በጥቂቱ የሳተ መንግሥት አድርጎ ይረዳዋል፡፡

ይህ አተረጓጎም፣ ብዙዎቹ የትግራይ ተወላጆች (በ‹መቐለ ትርክት› በመመራት) እንዲሁም ‹ሌሎች› (በ‹ሸገር ትርክት› በመመራት) እንዴት እና ለምን በሕወሓት እና ትእምት መካከል ያለውን ልዩነት እንደሚመለከቱት እንድንረዳ ያግዘናል፡፡

የትግራይ አክቲቪስቶች ትእምት ላይ ያላቸው ትችት የሚታየው በ1993 የሕወሓት መሰንጠቅ ወቅት በተባረሩት የቀድሞዎቹ የሕወሓት ኃላፊዎች ገብሩ አሥራት እና ስዬ አብርሃ አስተያየቶች ውስጥ ነው፡፡ ስዬን በዊኪሊክስ እና ገብሩን በመጽሐፉ እንዳነበብናቸው፣ ሁለቱም የሚቆጫቸው ትእምት የተቋቋመለትን ትግራይን መልሶ የማቋቋም ሕልም መርሑን ስቶ ማሳካት አለመቻሉ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ትእምት የትግራይ ሕዝብ ሀብት በመሆኑ ላይ ይስማማሉ፡፡

በተቃራኒው፣ ከትግራይ ውጪ ያሉት አክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች በኢሕአዴግ ኃላፊዎች የሚሾሩትን ትእምት እና ሌሎች ኢንዶውመንቶች የኛ አይደሉም ባይ ናቸው፡፡ የቀድሞው የኢዴፓ ሊቀመንበር፣ አቶ ልደቱ አያሌው እና በሽብርተኝነት የተፈረጀው ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ሁለቱም ትእምት የአገሪቱን ኢኮኖሚ በብቸኝነት እየበዘበዘ ያለ የፓርቲ ቢዝነስ ነው፤ ወደግል ይዞታ መዛወር አለባቸው ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ፣ ብዙ አክቲቪስቶች ዜጎች የትእምት ምርት እና አገልግሎቶችን እንዳይጠቀሙ እስከመወትወት የሚደርሱበት ጊዜ አለ፡፡

በተመሳሳይ፣ የትግራይ አክቲቪስቶች ሌሎች እንደ ማረት እና ትልማ ያሉ የክልሉ ሰብኣዊ ድርጅቶች ሳይቀሩ ሕዝባችንን ለመቆጣጠር እታች ድረስ የሚወርዱ የትግራይ ተወላጆችን ለሕወሓት ታማኝ ለማድረግ የሚውል የጭቆና መዋቅሮች ናቸው በማለት ቅሬታ ያሰማሉ፡፡ ከትግራይ ውጪ ያሉ አክትቪስቶች ደግሞ፣ እነዚህ ድርጅቶችም ልክ እንደ ትእምት ሁሉ በሌሎች ወጪ ለትግራይ ተወላጆች ያልተመጣጠነ ተጠቃሚነት ለማምጣት የተቋቋሙ ድርጅቶች ናቸው ባይ ናቸው፡፡

ከዚህ ልዩነት መደምደም የምንችለው ‹የመቐለ ትርክት› ትእምትን የትግራይ ሕዝብ ሀብት አድርጎ የሚቆጥረው ቢሆንም ለሕወሓት አመራሮች የግል ጥቅም ሲባል እየተመዘበረ ነው የሚል ቅሬታ አለው፡፡ የ‹ሸገር ትርክት› ግን ትእምት አንድ ቡድን የኢኮኖሚ የበላይነት በመፍጠር የኢትዮጵያን ሕዝብ ሀብት የሚበዘብዝበት መሣሪያ እንደሆነ ነው የሚረዳው፡፡

ቀዩ መሥመር 

ለሕወሓት እውነቱን መንገር ብዙ ግዜ አደገኛ ሆኖ ከርሟል፡፡ ስለትእምት መናገር ደግሞ የባሰውኑ አደገኛ ነገር ነው፡፡፡ አሁን በእስር ላይ የሚገኝ አንድ የአዳማ ኬላ ተቆጣጣሪ ለዚህ ጸሐፊ እንደነገረው፣ ‹የትእምት ኩባንያዎች ወደጅቡቲ ጭነው ሲሔዱ እና ሲመለሱ አይነኬ ናቸው›፡፡ በተመሳሳይ፣ ስለ ትእምት ኩባንያዎች ጥናት ማድረግ ለጋዜጠኞች እጅግ አደገኛ ነው፡፡፡ ይህም የኩባንያዎቹን ምሥጢራዊነት አጠናክሮ ያቆየዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ይህ ጽሑፍ ስለ ትእምት ሙሉ ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ስለ ትእምት እና በጥቅሉ በመንግሥት አመራሮች ስለሚደረጉ የኢኮኖሚ የበላይነት እንቅስቃሴዎች ብዙ ሊጻፍ ይችላል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s