ድርድር ዬደራጎን ግርግር – ዬሴራ ግግር። – ከሥርጉተ ሥላሴ

ከሥርጉተ ሥላሴ 25.01.2017 (ዙሪክ ሲዊዘርላንድ።)

 „ዬምትሞቱባትን፡ ቀን፡ አስቡ፡ ነፍሳችሁ፡ ከሥጋችሁ፡ በተለየች፡ ጊዜ፡ ገንዘባችሁንም፡ ለሌላ፡ በተዋችሁ፡ ጊዜ፡ ወደማታውቁት፡ ጎዳናም፡ በሄዳችሁ፡ ጊዜ፡ የምትመጣባችሁን፡ መከራ፡ አስቧት።“

(መጽሐፈ መቃብያንም ሣልስ ምዕራፍ ፮ ቁጥር ፩)

ዬዛሬ በር።

እጅግ ዬማከብረዎት አቶ ፈቃደ ሽዋ ቀና እንዴት ሰነበቱልን። ደህና ነዎት ወይ? ባለፈው ጊዜ ኢሳት ላይ በነበረዎት ቆይታ ዬእርሰዎ ትህትና ጉዞ አደከመኝ ብዬ በኢሜለዎት መልዕክት ልኬለዎት ነበር። ዬዛሬውም እንዲሁ። እርእሱ እራሱ ዬሚገርም ነው። „አትነጋገሩ ብሎ መምከር ጥሩ ፖለቲካ አይደለም  – ፍቃደ ሸዋቀና“ ይላል።

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/71512#comments

ለመሆኑ አትናገሩ ብሎ ከልካዩ ማነው? ዬነፃነት ትግሉ እንብርት ሴሉ ዬመናገር፣ ዬመጻፍ፤ ሃሳብን በነፃነት ዬመግለጽ፣ ዬመደራጀት፣ ድርጅት ሲባል ሰዎች ዓላማቸውን ለማስፈጸም ዬሃሳብ ምክክር ዬሚያደርጉበት ዬዓላማ ማህበር ማለት ነው። ፍላጎታችን ይህ መሰለኝ ….

ይህን ያሰረው ዬወያኔ ሃርነት ትግራይ ነው፤ ወይንስ ተፎካካሪ ዬፖለቲካ ድርጅቶች ወይንስ ዬኢትዮዽያ ህዝብ? ውጪ ያለነውንም ይጨምራል። ኢትዮዽያ ሀገራችን ኢትዮዽያዊነት ደግሞ ዜግነታችን ነውና። ዬኢትዮዽያ ህዝብ ካቴናው እኮ ጉሮሮ ውስጥ ነው ያለው።ካቴናው ያለው ህሊና ውስጥ ነው። „አትናገሩ አታስቡ“ ማለት ይሄ ነው። በእዝነ ህሊናዎት እንደ          Gastroskopie ጀርመኖች ዬጨጓራ መስታውት ነው ዬሚሉት (die Magenspiegelung) ይሰቡት፤ ጉሮሮ ውስጡ ላይና ከነቃው ህሊና ውስጥ ዬብረት ካቴና ሲገጠም። Gastroskopie ከዕይታው ግብረ ምላሽ (feedback) በኋላ ይወጣል። ካቴናው ግን ዬወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶና ዬግራ ፖለቲካ መንፈስ ግራቀኙ ካላከተሙ አይፈታም።

አትናገሩም ብሎ ካቴናውን ህሊና ውስጥና ጉሮሮ ውስጥ በህግ ገጥሞ ተናገሩ ማለት አይችልም – ወያኔ። ሳይናገሩ መናገር አይቻልም። በዚህ ዘመን፤ ዘመኑን ዬማጥናት አቅሙ ቢኖረን አሁን እኮ „ደሞ ለዓይኔ ያሻኝን ባይ ማን አለኝ ከልካይ“፤ እራሱ ዬቁም እስር ላይ ነው። ወያኔ ቢችል እኮ ጸሐይን ማከፋፈል፤ ዝናብና በክልል ማደራጀት፤ ወቅታትን ከተፈጥሯቸው ባገደ ነበር። ዬሆነ ሆኖ አትዩ ፤ አታዳምጡ፤ አታንብቡ፤ ተብሎ ተጨማሪ ዬዓይን ካቴና፤ ተጨማሪ ዬጆሮ ካቴና በአፓርታይዱ ወያኔ ተመርቷል። ዬእርስዎ ቅናዊ መንገድ ዬተከተሉ ከወያኔ ጋር ዬተቀመጡ ኃይሎች ለእኔ ዬግድ ግዳ ፎቶ ወይንም ዬመንገድ ፖስተር ናቸው! ጉድጓድ ውሃ ውስጥ ዬገባ ሰው ይሰምጣል። መተንፈሻ ስለሚያጥረውም – ይሞታል። በሞት መንፈስ ላይ ይወያዩ እያሉ ነው እዬመከሩ ያሉት።

ለነገሩ „አፈርሳታ“ ዬማህበራዊ ሚዲያ አክታቢስቶች ጋር አዘጋጅቶት በነበረው ውይይትም ስለአማራ ዬዘር ጥፋት „ምን መረጃ ዕውነተኝነት አላችሁ“ ዬሚል ዕድምታ ያለው ጥያቄ አቅርበዋል። ግነት እንዳይኖር፣ ዬመረጃ ተቀባይነት እንዳይሳሳ ነው – ስጋቱ።

https://www.youtube.com/watch?v=7a4of2PdGQc

እንደ ታላቅ ዬሀገር ሃብትነተዎትና ዬትውልደ ዬሊቃውንት ዬቀለም ዋርካነተወት ቢያንስ በወያኔ መራሹ ዬስታስቲክ ጽ/ቤት ዬታመነውን 2.4 ሚሊዮን ህዝብ ህሊናዎት ላይ መቀመጥ አልቻለም። „አማራ“ መሆን ማለትና „አማራነትን“ በውስጥ ማስቀመጥ ማለት በፍጹም ሁኔታ ዬተለያዬ ነው። ጉር ያላለ ለስታ ቅቤ እንደማለት ነው  – ለእኔ። ጉር ያላለን ለስታ ቅቤ ተፈጥሯዊ ባህሪን ዱቅዱቃነቱን ዬጎንደር ሴት ታውቀዋለች።ዬሆነ ሆኖ ዬወያኔ ሃርነት ትግራይ ዬማሌሊት ማኒፌስቶ ዓላማና ግብ ጭንቅላቱ እራሱ ይህንን ጥያቄ ይመልሰዋል።  „በአማራ መቃብር ላይ ዬታላቋን ትግራይ ሪፓብሊክ እንመሰርታለን“ ይላል። ለዚህስ ዬስታስቲክ ቢሮ ይከፈትለትን?! ዬጥናትና ዬምርምር ወይንም ዬትርጉም ሥራ ከቶ ይደራጅለት ይሁን?  አማራነትን ዬእኔ ለማለት በጋብቻ፣ በአበልጅነት፣ በጉርብትና ያሉ ግንኙነቶችን ለማንነት መደለያነት አለማዋልን በአጽህኖት ይጠይቃል። ቅጂ ያለው ዬሰው ልጅ ዬለምና። አማራነት የደም ውርስ እንጂ ዬንግግር ማሟያ አይደለም! ደሙ ሲነካ መነሸጥ አለበት! ዬጥቃት ጋሻ ጃግሬ ልጅን ዬአማራ ወላጆች አይወልዱም እና። ሌላውን ለዛሬ ልተወዎው። ሲያስፈልገኝ ደግሞ እንሸራሸርበታለሁ። ዬራሴ ጌታ እኔው እራሴ ነኝና። በሽታውን ሳናውቅ ነው ዓመታት እዬተሳለቁብን ዬነጎዱት። ድፍረትም ያንሰናል ስለዕውነት።

ጉዳዩን ካነሳሁት ዘንድ „አፈርሳታ“ ቃሉ ሆነ ትርጉሙ፣ ተግባሩም ትውፊታችን ነው። ወደ ውስጣችን ለማዬት አቅም እያሸተ ስለሆነ ያስመሰግናል። እንኳንም ለዚህ አበቃን!  „አፈርሳታ“ ማለት ባህላዊ ዬወታደር ቤት ማለት ነው። ባህላዊ ዬወንጀል ምርመራ ቢሮእንደማለት።  ዝንባሌው ዬወንጀል ጥፋቶችን በባህላዊ መንገድ ፤ ባልተፃፈው ህጋችን ማውጣጣት ነው፤ አውጫጭኝ ነው። ስለሆነም ዬነፃነት ፍለጋ ጉዟችን ከወንጀልና፤ ከወንጀላዊ ቀጠናዎች ጋር ምንም ንክኪ ስሌለው መድረኩና ዓላማው በፍጹም ሁኔታ ዬማይገናኝ ነው። ፕሮግራሙ ነፍሱ ካለች ስሙን ከተግባሩ ጋር ሰያሚዎቹ ቢያገናኙት መልካም ነው እንላለን እኔና ብዕሬ።

እፍታ።

ወይ ልግጫ! ዓመት ድገሙ እያለን ነው ደግሞ ባላንባራስ እርግጫ። ዬልግጫ ዑደት ዬዕንባ ዳንሰኞች አጃቢነት ነው – ለእኔ። ለዬትኛውም ዬህይወት ዘርፍ መወያዬት ሆነ አንዱ ከሌላው ጋር መነጋገር ዬንጹህ አዬር ያህል ተፈላጊ ነው። ከግል ህይወት እስከ ሀገራዊ፣ ዓለምዓቀፋዊ ኩነቶች ድረስ መሪው ምክክር፣ ውይይት ነው። ሃይማኖታዊ ጉዳዮችም ሆነ ለኪነጥበብ ዬብልጽግና መሰረት ነው  – መወያዬት። ለፖለቲካ ተልዕኮማ ሩሁ ነው።

መወያዬት፣ መመካከር ዬመኖር ሳይንስ ናቸው። ዬአብሮነት ሲሳይ ናቸው። በቅኖች ከተቀረጹ። በግልጽነትና በቀጥተኝነት ከታወዱ። በማስተዋል ከተመሩ። በሙሉ ሀገራዊ ተቆርቋሪነት ስሜት ከተነሳሱ ስክነታቸው ህዝበ – ጠቀም ይሆናል። በስተቀር ግን እያደባ ለሚነሳ አውሬ ዬበቀል ልኳንዳ ቤት መክፈት ነው። እንደ ሰው እስከ አስር ጊዜ ስህተት በተመሳሳይ ጉዳይ ዙሪያ መስራትን ይሁን ተብሎ ቢቀበሉት እንኳን፤ በ25 ዓመት ውስጥ ተመሳሳይ ሺህ ሥህተት ውስጥ እዬዳከሩ ዬደሃውን ህዝብ አሳር ማበራከት ለእኔ ዬፖለቲካ ወንጀል ነው። ባለፈው ጊዜ ተው እዬተባሉ፤ ምርጫ ገቡ። ያው ውድ ህይወታቸውን ሌሎች ገበሩ – ምስኪኖች። እስር ቤት ዬታጎሩትም ጠያቂ ዬላቸውም።

ያን ጊዜ ከሙሁራን ዬተደመጠው ወያኔ በምርጫው ተሸንፎ ቢያጭበረብር – በዓለም ማህበረሰብ ይጋለጣል ዬሚል ነበር። ተጋልጦ ምን ዬፖለቲካ ትርፍ ተገኜ? አሁንም ይህ እዬተደመጠ ነው።

(„ትልቁ ነገር በድርድሩ መድረክ ላይ የሚቀርበው ጉዳይ ነው። ማወቅና ማረጋገጥ ያለብን በድርድር ጊዜ ተደራዳሪ ወገን ከድርድሩተጠቃሚ ለመሆን ጥረት የማድረግን ጉዳይ ነው። ተቃዋሚዎች መሰረታዊ የሚሉዋቸውን የሚታገሉላቸውንና እንዲለወጡየሚፈልጉዋቸው ጉዳዮች ላይ ማተኮርና ቢያንስ በከፊል ወይም በሙሉ መልስ የማያገኙ ከሆነ ድርድሩን ተገቢ መግለጫ አውጥተውማቋረጥ ከቻሉ የፖለቲካው ትርፍ የነሱ የሆናል። የፖለቲካ አሸናፊነቱን ተቀዳጁ ማለት ነው።“  ከአቶ ፈቃደ ሽዋ ቀና)

ለአዳዲስ ሴራዎች ዬሰው ልጅ ዬሞት ሙከራ ይካሄድ እያሉን ነው – እነ አቶ ፈቃደ ሽዋቀና – ሙሁሮቻችን። ትህትናቸውንና ዬሃሳብ ልዩነታቸውን ባከብረውም ነገረ ሥራቸው ድክም ያደርገኛል። እሳቸው ባነሷቸው ህፃጽ ሃሳቦች ትራስነትም ደግሞ አዲስ ጉግስ ተጀምሮ ከሁለት – ከሦስት መተርተር እንደተጠበቀ ሆኖ። ምን አለ ሁሌም ይድላቸው ነው ነገርዬው። አይዋ ወያኔ አራት ኪሎው ተራራ ላይ ሆኖ ዬለመደውን ዬቀጥቅጦ ግዛት ሂደቱን እረፍቱን እዬወሰደ ይቀጥላል። ፍቅር ጥሩ ቢሆንም ህዝብ ለዬዘመኑ ዬሴራ ካቴና ዬሞት መሞከሪያ ሟሟሻ ይሁን ማለት ሥም የለሽ አዟሪት ወይንም ዬሆነ ድግምት ነገረ  ነው ለእኔ – ለሥርጉተ ሥላሴ።

ዬአጓጉል ጉጉል።

ወያኔ ፍንክች አይልም። ፋሽስት ፋሽስት ነው። ፈርዖንም ፈርዖን። ደራጎንም ደራጎን። ወራሪም ወራሪ።ለአማራው ተጋድሎ ዬሰጠው መልስ ፍንጭ  „የወልቃይትን ‹‹ታሪካዊና ባሕላዊ ትግሬነት ለማረጋገጥ›› ጥናት ለሚሠሩ ተማሪዎች የተለየ በጀት መመደቡ ተሰማ፤“  ዬኔታ * ሙሉቀን ተስፋው በ23.01.2017 አስነብቦናል። ሌብነትን ህጋዊ ዕውቅና በውንብድና በማሰጠት ዬጥናትና ዬምርምር ሥራ ለማሰራት መወጠን – ለእኔ ይሄ ማለት „ለትምህርተ – ሌብነት¡“ ካሪክለም ተነድፎለታል ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ አረና ለተፈጻሚነቱ ቀኝ እጅ ለወያኔ እንደሚሆን ሳይታለም ዬተፈታ ነው።

ለአማራ ዬህልውና ተጋድሎ ምላሽ በማስገኘት ደረጃ በቁመትም በወርድም አቅሙ ዬሚመጥን ዬፖለቲካ ድርጅት ከስብስቡ ዬለም። ለለበጣ ወያኔ ሌላ ተለጣፊ ካልፈጠረ በስተቀር። ጥያቄዋን እራሱ ዬሚደፍራት አንድም ህብረ ብሄር ፓርቲ አልተፈጠረም። ስለዚህ በዚህ ዘርፍ እራሱ ዳሽ ነው።

ውይይት መፍትሄም ስኬትም ነው። ውይይት መርህም ነው ለዴሞክራሲ ጉዞ። ነገር ግን በተዘጋ በር ዬሚገኝ መፍትሄም ስኬትም አይኖረውም። ዬሰው ልጅ መጀመሪያ መተንፈስ አለበት። ኦክስጅን በሌለበት ህይወት አይቀጥልም። ንፁህ አዬር በሌለበት ሁኔታ በዬትኛው ትንፋሽ ነው አንደበት ዬሚከፈተው? ዬሰው ልጅ ቁሟ መሄዱ ብቻውን መኖሩን ሊተረጉም አይችልም። ከሁሉም በላይ ዬሥነ – ልቦና ዬበላይነት በሌለበት፤ ዬራስ መተማመን ተፈጥሮ በተሰደደበት ዬቀውስ ጊዜ፤ በምን ሁኔታ ነው ውይይት ዬሚካሄደው? ከችግር ፈጣሪው፤ ከሞት ዬማምረቻ ድርጅቱ ከወያኔ ጋር? ጨለማ ውስጥ ሆኖ ሳይተያዩ በደበሳ መናበብ ይኖራልን? ወይንስ እህል ውሃ አልባ ህይወት ይቀጥላልን? ጥያቄው እኮ ዬህልውና ነው። ማስቲካ እያላመጡ ዬማይዘነጥበት።

በአሁኑ ወቅት ዬመፍትሄ ቁልፋ ከውይይት በፊት እራሱ ወያኔ ቀድሞ ሊከውናቸው ዬሚገባ መሰረታዊ አመክንዮች አሉ። ወያኔምያውቃቸዋል ዬደንቆሮ ለቅሶ መልሶ መላልሶ“  ካልሆነ በስተቀር። መቅደም ያለባቸውን እርምጃዎች መውሰድ ያለበት ወያኔ ብቻ ነው።ዬተፎካካሪ ኃይሎች ፋይዳ በአዳራሽ ላይ መከተም አይመስለኝም መፍትሄ – አመንጩ። በተለሰነ ዬደራጎን ህሊና ግርግር መፍትሄ ለማግኘት ተስፈኛ መሆን ባይከለከልም፤ በወታደራዊ ሥር በወደቀ መንፈስ ውስጥ ሆኖ ራዕይን ለማሳካት ማሰቡ ጸሐይ ጨረቃን ተክታዬቀን ብርኃን ትሆናለች እንደ ማለት ነው።

ምክንያቱም ምግብ ለመሥራት ለምግብ መስራት ዬሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች – ያስፈልጋሉ። ይህ ካልኖረ ምግብን ለማብሰል፤ አብስሎም ለመብላት ማሰብ ማለት ነው። ማሰብ ብቻውን ደግሞ ዬራህብ ማስታገሻ ሊሆን አይችልም። ማሰብ ብቻውን ራህቡን ቢጨምር እንጂ ምግብ ሊሆን በፍጹም አይችልም። ገበሬ ለመሆን መሬትና ዬእርሻ መሳሪያ ያስፈልጋል። መምህር ክፍል ውስጥ ለማስተማር ዬትምህርት ድጋፍ መስጫ መጸሐፍት፤ ብላክቦርድ፤ ቾክ ቢኖሩ እንኳን ተማሪ ከሌለ ማስተማር ህልም ነው ዬሚሆነው። ምኞት ብቻውን ዬድል እርካብ አይሆንም። ህዝብ ሙሉ ለሙሉ አመኔታውን ለነፈገው አውሬ ዬመተንፈሻ ቧንቧ ሊሰራለት ይገባል ማለት – በሳሉን ወቅትን ካለማድመጥ ዬተቀነጨበ ጭንጋፍ ዕሳቢም ይመስለኛል። ልፍስፍስነትም ነው። ከዚያ ይልቅ ዬወያኔ ሃርነት ትግራይ ዕድሜ ያርዝምልን ብሎ ሁለት ሰባት ሱባኤ መያዙ ሳይሻል አይቀርም¡ ጠበቅ አድርጎ መስገዱንም – ቢአስነኩት¡

ህዝብ መከፋቱን ዬሚገልጽበት መንገዱ ታስሯል። ያ …  ከሥር መለቀቅ አለበት። ይህን ለመፍታት ደግሞ በህግ ዬታሰሩ መብቶችሙሉ – ለሙሉ ነፃ መውጣት ይኖርባቸዋል። በህግ ዬታሰሩ ህሊናዎች፤ ኑሮዎች፤ ዓላማዎች፤ ግቦች፤ መንፈሶች፤ ዬህልውና ንጥረ ነገሮች፤ ዬትውልድ ተስፋዎች፤ ብራናዎች፤ ብዕሮች ሙሉ – ለሙሉ ነፃ መውጣት ይኖርባቸዋል። ዬዚህ ባለ ሙሉ ሥልጣን ዬወያኔ ሃርነት ትግሬ ድርጅት ብቻ ነው። ስለዚህ ለማሟያ ካልሆነ በስተቀር፤ አዳራሽ ውስጥ ዬተቃዋሚ ኃይሎች ለመምክር መሰብሰባቸው ዬድርድር በረዷዊ ግግር ለመፍጠር ካልሆነ፤ ሊያስገኝ ዬሚችለው ዕሴት ለዛዛ እንጨት ነው። ለዘዛ እንጨት ደግሞ ወይ አነድም ወይ አነድም። ዬወያኔ ሃርነት ትግሬ ሴራ ወቅቱን ግግር በረዶ እንዲሆን ማድረግ ነው። ይህ ዬኖረበት … ተንደላቆ ዬሚዘንጥበት ዓውራ መንገዱ ነው።

ዬአሁኑ ከወትሮው ዬተለዩ – ቁምጥ ዬሚያደርጉ አጓጒ መላሾዎችን ዬጎንዮሽ መስመር መዘርጋትን አክሎ፤ በአቀራረቡ ረቀቅ ያሉ ሲናሪዎች ሊኖሩት ይችላሉ። ረቂቅ ሂደቶችን ጤናማ መሆናቸውን አገላብጦ መመርመር፣ ተገቢውን ዬክህሎት አቅም ሰጥቶ በአሸናፊነት ለመውጣት መቻልን በሚመለከት አሁን ሀገር ቤት ያለው ዬተቃዋሚ ሃይል መደገፊያ ምርኩዝ ዬሚያስፈልገው ሆኖ ነው ዬሚታዬው። ሚዲያ ላይ ወጥቶ ሃሳብን መግለጽና አሸናፊ ሃሳቦችን ቀርፆ ተፎካካሪ ፖርቲን ማሸነፍ መንገዱ ዬክረምትና ዬበጋ ያህል ልዩነት አለው፤ ወይንም ዬብስን እና ውቅያኖስን ማወዳደር ነው አሁንም ለእኔ –  ለሥርጉተ ሥላሴ።

ዬኢትዮዽያ ተቃዋሚ ኃይል ይሁን ሂደቱ እንዲቀጥል ቅንነታቸውን ዬሚለግሱ ሙሁራን ከ25 ዓመት በኋላ እንኳን ዬወያኔ ሃርነት ትግራይን አብሶ ዬአቶ በረከት ስምኦን -ን እንጦርጦስ ገጸ ባህሪ በአግባቡ ዬመተርጎም አቅም አዝጋሚ መሆኑ ለነፃነት ፍለጋ ጉዞ ዬቁርጥማት ህመም ሆኖል። አድሮ ጥጃ።“  ለዚህ እኮ ነው ህዝቡ አይቶ … አይቶ ዬጥያቄው መሪ እራሱ የሆነው። ሞቱንም፤ እስራቱንም፤ እንግልቱንም፤ ጥማቱንም ችሎ ትግሉን በትጋትና በቁርጠኝነት ዬቀጠለው። ዬህዝቡ ዬማህበራዊ ንቃተ ህሊና ከፍታ አብሶ ዬአማራ ተጋድሎ – ዬተቃዋሚ ዬፖለቲካ ድርጅቶችን በሙሉ ተመልካች አድርጓቸዋል። ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚያስችል ደረጃ ከጨዋታ ውጪ ነው ያደረጋቸው። ስለምን? ዬብሶትን ውስጥ ዬመተርጎም አቅማቸው የምች ሰለባ በመሆኑ።

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መድረክ ላይ ጎልተው ዬሚታዩት ደቡብ ህዝቦችና አረና ናቸው። ሁለቱ እንወክላቸውአለን በሚሉት ቦታ አብሶ አረና በረድ ዬፈሰሰበት ዬፖለቲካ አቋም ላይ ነው ዬሚገኘው። ሁለቱም ዬኦሮሞን ፕሮቴስት እና ዬአማራን ተጋድሎ መስዋእትነት ለቀረመት ያጠመዱት ይመስላል። ሌላው ነገረ ሰማያዊን በሚመለከት  እራስ ሳይጠና ጉተና ነው“ – ለእኔ። ገና ራሱን ለመግራት ጊዜ ያስፈልገዋል። ዬወጣት ዬተስፋ ማህደር ነበር፤ ነገር ግን ዬማይገኙ ወጣቶቹን ገብሮ፤ እያረገረገ መሆኑ እዬተደመጠ ነው። ሌሎች ያው ዬወያኔ ሃርነት ትግራይ ዬጆሮዎቹ ዓይኖች ናቸው። ከቁጥርም ዬማይገቡ። ዬወያኔ ሃርነት ትግራይ ልቡን ዬገጠመላቸው።

አጋጣሚው ጭስ መሆኑ መድረክም ይሁን ያሰባሰባቸው – አንድ ዬሚ/ር ማእረግ ካገኙ ሸብረክ ማለታቸው አይቀሬ ነው። ለሰላማዊ ትግል ጽናታቸው አዎንታዊ አስተምህሮ ቢኖረውም፤ ለስላሳና ወጣ ገብ ዬፖለቲካ አቋም ያላቸው ሊቃናት እንዳሉ ይታወቃል። አብዛኛውን ጊዜም ዬአቅም ዬመተርተሬያ ፋስነትም መሆንም አለ። ይህን ደግሞ በስማ በለው ሳይሆን በቀደሙ ሀገራዊ ዬመሰባሰብ ዬአብሮነት ጉዞ ሳንኮችን ሳያቸው ነበር።

እርገት ይሁን …

ዬግራ ፖለቲካ ዬጭቃ እሾህ ፖለቲካ ነው። መግቢያ እንጂ መውጫ ዬሌለው። በዚህ ላይ በአናሳነት ላይ ዬተገነባ ዬጎሳ ስልጣን፥ ይህም ብቻ አይደለም፥ በፍቅረ ንዋይ ልዕልና ዬመሸገ ፖለቲካ፣ እንዲሁም በአማተር ወታደራዊ ሥር ዬወደቀ ፖለቲካ ችግሮቹም ሆነ፤ ዬችግር አመንጪ መፍትሄዎቹ በንፋስ ኃይል በሚመራ ፖለቲካዊ ስሜት አሸንፎ ለመውጣት ኔቱን ዬገመዳቸው፣ ያያዛቸው ሥሮች በጥናት ላይ ዬተመሰረቱ – በተከታታይና በትጋት ዬተከወነ ዬህሊና ብቃትን ይጠይቅ ይመስለኛል። ዬፖለቲካዊ ብቃት ብልጽግናዊ መንፈስ ብልህነትን መሰነቅ – ይኖርበታል። ምራቁን ዬዋጠ – ብቃት።

በተጨማሪም ወቅትን ብቻ ሳይሆን ሊመጡ ለሚችሉ መጠራቅቆች ዬመሰናዶ ትንበያ በእጅጉ ያስፈልጋል። በደራሽ ነገሮች ላይ ሙሉ አቅም ከፈሰሰ፤ ለቀጣዩ ፈተና ዬህሊና ስንቅና ትጥቅ እጥረት ይገጥማል። አቅምም ይበተናል፣ ዬነፃነት ፍለጋ ጉዞው ተረጋግቶ መራመድም ይሳነዋል። ተሰፋ ቆራጭነት ከመጣ ፍርሰት ይገጥማል። ፍርሰቱ ደግሞ እጅ ወደ ላይን አመቻችቶ ይሸልማል።

ዛሬ ዬሚታዬው ዬፖለቲካ ትንታግ ዬአልገዛምባይነት ሙቀት ከመሪዎች ህዝቡ በእጅጉ እዬቀደመ ነው። እዬታዬ ያለውም ይሄው ነው። ዬባለቤትነት ስሜቱ ሽሚያ ላይ ዬመሆኑ ችግርም ይሄው ነው። ዬእኔ ነው ለማለት ከህዝቡ ዬበቃኝ እርምጃ በፊት ዛሬ ዬህዝቡ ዬበቃኝ ማኒፌስቶ ውስጠት ተኮር ላይ ዬቀደሙ ዬዓላማና ዬግብ ውሎች አልነበሩም። እሱ እራሱ በመከራው በቀረጸው ማኒፌስቶ ነው ዬፖለቲካ ድርጅቶች እሰጣ ገባ ላይ ዬሚገኙት። ዬዘራ ዬፍሬው ባለቤትቱን ማንም አይከለክለውም። ግን አልሆነም። ቀድሞ ነገር ይመጣል፤ ሊሆን ይችላል ተብሎ ዬሚተነበይ አመክንዮ አለመኖር፤ ዬተገኙ ትርፎችን በአቅም ግንባታ ተቀማጭ ሃብት አድርጎ ዬማስቀጠል ሆነ፤ ዬአቅም ጥሪቱን ተከታታይነት በአስተማማኝና በጥራት ሁነኛ ዬተስፋ እልፍኝ ዬማድረጉ ነገርም እንዲሁ እንዲያና እንዲህ ነው። ስለሆነም ወያኔን ያህል ጉድጓድ ድርጅት ለመቋቋም ትጥቃችነን ዬምናውቀው እኛው ነን። ለዚህም ነው ዬሴራ መተከዣ፣ ዬሴራ መረማመጃ፣ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስን ቀለብ ያደረግነው። ዬአሁኑ ጅማሮ ከእርቦ ጌጥነት በታች ያነሰ ነው። ይብቃኝ  ….

  • ዬኔታ —- ዬአማራ ወጣት አክቲቢስቶች ለእኔ መምህሮቼ ስለሆኑ ነው – ዬእኔታ ዬምላቸው። ዬዘብሄረን አማራነትን ነገር ገና ፊደል ቆጣሪ ነኝ። ሁሉ ችግር በአንድ ማዕቀፍ ይፈታል ዬሚል ሙሉ ዕምነት ነበረኝ። እውነቱ ግን አንጀዳ ያልሁኑ፤ ባለቤት ዬሌላቸውጉዳዮች እንዳሉ ተገንዝቤያለሁ። ይህ ዬውስጥነት ዬምርመራ ሂደት መጀመሩ በራሱ በእኔ ህይወት፤ አዲስ ምዕራፍ ነው። ዬረዳኝም ዬእነሱ በህይወቱ ውስጥ መኖር ጭብጡ ቀልብን ለመሸለም አቅም ያለው መሆኑ ነው።

ዬማስተዋላችን ጌታ ያድርገን ፈጣሪ። አሜን!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ። መሸቢያ ጊዜ።

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s