በተለያዩ ኢንቨስትመንት ተሰማርተው የነበሩ ባለሃብቶች ገንዘባቸውን በማሸሽ ሥራ መጠመዳቸው ተገለጸ

 ብርሃኑ አየለ

በአሁኑ ሰዓት አገር ውስጥ በሰፈነው ስጋት ምክንያት የተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ባለሃብቶች ገንዘባቸውን ከአገር ለማውጣት የተለያዩ መንገዶችን እየተጠቀሙ እንደሆነ ለባለሃብቶቹ ቀረቤታ ያላቸው ሰዎች ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።

አገሪቱን እየገዛ ያለው ህወሃት ካለፈው መስከረም ጀምሮ ሥራ ላይ በዋለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ “ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ሠላምና መረጋጋት መልሼ ለማስፈን ችያለሁ” በማለት አዳዲስ ኢንቨስተሮች ወደ አገር ውስጥ እንዲመጡ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን በአገር ውስጥና በውጪ ሚዲያዎች በተከታታይ እየሰጠ ያለ ቢሆንም ቀደም ሲል ገንዘባቸውን አገር ውስጥ ያፈሰሱ ባለሃብቶች ስጋት ውስጥ ገብተው ገንዘባቸውን ለማውጣት እየተረባረቡ ከመሆኑ ጋር የሚቃረን መሆኑን እንኳን ለማስተዋል የቻለና መፍትሄ የሚፈልግ አለመኖሩ እንዳስገረማቸው እነዚሁ ምንጮች ይናገራሉ።

ጠቅላይ ሚንስቴር ሃይለማሪያም ደሳለኝ በተደጋጋሚ በሚዲያና በኢህአዴግ ፓርላማ ፊት ቀርበው አገር ውስጥ ተከሰተ የተባለው የጸጥታ ችግር ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር ሥር መዋሉን ከመመስከር አልፈው የኢንቨስተሮች ቁጥርም ሆነ የቱሪስቶች ፍሰት ላይ ያስከተለው ለውጥ አለመኖሩን በእርግጠኝነት መናገራቸው ይታወቃል። ሆኖም ግን ሃቁ አዳዲስ ኢንቨስተሮችን ከውጪ መሳብ ቀርቶ ቀደም ሲል የገቡትን እንኳ ለማቆየት ችግር እየተፈጠረ መሆኑን ነው ምንጮች የሚናገሩት። ባለፈው አመት ኦሮሚያ ውስጥ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰና ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም ወደ አማራ ክልል ከተዛመተ ወዲህ ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሪ እጥረት አገሪቱ ውስጥ እየተከሰተ መሆኑን ከአይ ኤም ኤፍ እና የአለም ባንክ የሚወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ። በዚህም የተነሳ የገንዘብ ግሽበት እየተከሰተ እንደሆነና 22 ብር የነበረው የአንድ ዶላር ዋጋ በ27 ብር እየተመነዘረ እንደሆነ ታውቆአል። በኢንቨስትመንት የተሰማሩ የውጪ ባለሃብቶች ከሚያገኙት ትርፍ ውስጥ ገንዘባቸውን በውጪ ምንዛሪ ለመያዝ የሚያቀርቡትን ጥያቄ ለማስተናገድ የአገሪቱ ብሄራዊ ባንክ ከአመት የበለጠ ጊዜ እየፈጀበት መምጣቱን አዲስ አበባ ውስጥ እየታተመ የሚሰራጨው አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት ህትመቱ ይፋ አድርጎአል። ከዚህ ችግር ጋር በተያያዘ ሁኔታ የዋጋ ግሽበቱ እንዳያከስራቸው የሰጉ አንዳንድ የውጪ ኢንቨስተሮች በእጃቸው ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ብሮችን መኖሪያ ቤቶችንና የከተማ ቦታዎችን በመግዛት ወደ ንብረት ለማዞር እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አዲስ ፎርቹን ዘግቦአል። ለዘገባው በዋቢነት የጠቀሰው ቱጃሩ የሲሚንቶ አምራች የሆነውን ናይጄሪያዊ አሊኮ ዳንጎቴን ነው። አሊኮ ዳንጎቴ በቅርቡ ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በማውጣት ቤቶችን እየገዛ እንደሆነና ንብረትነቱ የአቶ የማነ ገብረስላሴ የሆነና  ወደ 900 ሚሊዮን ብር ወጥቶበት ከ4 አመት በፊት የሆቴል አገልግሎት መስጠት ለጀመረ ድርጅት አንድ መቶ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መስጠቱን ፎርቹን አስነብቦአል።

ገንዘባቸውን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተጣደፉ ካሉ ባለሃብቶች በተጨማሪ በተለያየ እርከን ላይ የሚገኙ የህወሃት ባለሥልጣኖችና ግብረአበሮቻቸው በዘረፋ ያከማቹትን ገንዘብ ከተቻለ ወደ ውጪ ምንዛሪ ለውጠው ከአገር ለማሸሽ ካልሆነ ደግሞ ቋሚ የሆኑ ንብረቶችን በቅርብ ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ሥም በመግዛት ወደ ህጋዊነት ለመለወጥ ከፍተኛ የሆነ ዘመቻ ላይ እንደሚገኙ ከምንጮች ከተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሎአል። ህወሃቶች ገንዘባቸውን በውጪ ገንዘብ ለመቀየር እና ከአገር ለማሸሽ በተለያዩ የውጪ አገሮች የሚኖሩ ዘመዶቻቸውንና የጥቅም ተጋሪዎቻቸውን እንደሚጠቀሙ ይታወቃል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s