… እንደ ጉርድ በርሚል! – ከሥርጉተ ሥላሴ

ከሥርጉተ – ሥላሴ 27.01.2017 (ዙሪክ – ሲዊዘርላንድ።)

„ዬኃጢያት መብራት ይጠፋል፥ የእሳቱም ነበልባል ብልጭ አይልም። ብርሃን በድንኳኑ ውስጥ ይጨልማል፥ መብራቱ በላዩ ይጠፋል። የኃይሉም እርምጃ ትጠብባለች፥ ምክሩም ትጥለዋለች። እግሩ በወጥመድ ትያዛለች፥ በመረብ ላይ ይሄዳል። አሽክላ ሰኰናው ይያዛል፥ ወስፈንጠርም ይበረታበታል። በምድር ላይ የሸምቀቆ ገመድ፥ በመንገዱም ላይ ወጥመድ ለእርሱ ተሰውራለች። ድንጋጤ በኋላው ሁና ታስፈራዋለች። በስተኋላ ሆና ታባርራቸዋለች። ኃይሉ በራብ ትደክማለች፥ መቅሰፍትም እስኪሰናከል ተዘጋጅቶለታል። (መጽሐፈ እዮብ ምዕራፍ ፲፰ ከቁጥር ፭ እስከ ፲፪)

 

ጠብታ።

ትራፊ ካሰኜህ እኔ ምን ተዳዬ …

…. አሰርም ካሰኜህ እኔ ምን ተዳዬ

ጭላጭም ካሰኜህ እኔ ምን ተዳዬ ….

…. አተላም ከሆነ እኔ ምን ተዳዬ ….

ለተስፋ – ገዳዬ።

እፍታ።

በቅድሚያ እግዚአብሄርን ላመስግን። አቶ ልደቱ አያሌውን በአካል ከማላውቃቸው ዬፖለቲካ መሪዎች ውስጥ አንዱ – ስለሆኑ። ዬአቶ ኤርመያስ ለገሰን „ዬመለስ ልቃቂት“ መጽሐፍ አልገዛሁም። ስለምን? ዬሄሮድስ መለስ ዜናዊ ፎቶ ከቤቴ እንዲገባ – ባለመፍቀዴ። ወደፊትም – አልገዛውም። ይህ በደል በዛሬ ብቻ፣ እኛ እያለን ብቻ ይመስል ይሆናል። ዬሄሮድስ መለስ ጦሱን ከነዝክንትሉ ዬትግራይ ህፃናት እንዲያወራርዱት ወደፊት ሊገደዱ ይችላሉ። በሌሉበት ዬዕዳ ወለድ ከፋይ። ይህን እያሰበ ዬነገና ዬነገ ወዲያ ምጥ እያጥመነመነኝ ዬእሳቸው ፎቶ ያለበት መጸሐፍ በፈለገው ሁኔታ ሀገር ጠቀም ቢሆንም – አላስጠጋውም። አጋ ለይተን መዋለ ዕድሜያችን ሙሉ በጎሳ እንድንጨፋጨፍ ድል አድርገው ደግሰው በቀልን ዳሩትኳሉት፤ ቁርሾን መልስ፥ ቅልቅል፥ ግጥግጥ ገለመሌ እያሉ ሞሸሩት። እርቃነ  -መንፈሳቸው ያረፈበት ሁሉ ዬቋሳ ቀጠና ነው። ካለፋ በኋላ እንኳን ምን አለ ቢተውን? ሙት መንፈሳቸውን ዬደም ማወራረጃ ስንቅ ከሚያስደርጉት። በእውነቱ ዬሰኔልና ዬቹቻ ራዕይ ላንቃ – ሳንቃ ዬሚከረቸምበት ዕልት ይናፍቀኛል። ልዕልት ኢትዮጵያም ሆነ እኛም ወህ! ዬምንልበት ቀን ቢመጣ ሥሙን ማን እንበለው ይሆን? አታስጎምጅን አላችሁኝን። እንደትጥቃችን – ይወሰናል።

ይሄው ዬአፄ ዮኋንስ ዬመሰናዶ ተማሪዎች እኮ ታሪካቸው ብክል እንዳይሆን ሙግት ገጥመዋል። የዘራይ ደረስ ትንታጎች፤ ዬሃቅ ቤተኛነታቸውን በተግባራቸው – አትመዋል። ተባረኩ – ዬእኔ ጀግኖች።

… አሁን ሳር ቅጠሉ ትግራይ ሆነ እንላለን። ሄሮድስ መለስ ዜናዊ ዬቀበሩት ቧንብ ዬዘለዓለም አሳርን ነው -ለትግራይ ትውልድ ተክለው – ያለፋ። ሰው ወደደ ማለት እኮ እግዚአብሄር ወደደ ማለት እኮ ነው። ዛሬ የትግራይ ዘመንተኞች ሲነሱ ደሙ ዬማይፈላ ማን አለና? ይህን እኮ ነው ለትግራይ ህዝብ ሄሮድስ ሸልመዎት ዬሄዱት። የጸሎት መግያብያ እኮ ዬሰው መውደዱን ዬአንበሳ ግርማውን“ ስጠኝ ተብሎ ነው ዬሚጸለዬው።  ይህንን ዬዕልፍ ህይወት እኮ ነው ቅብር አድርገውት ያለፉት። ቁስ እኮ ዬሚሰበር፣ ዬሚያልቅ፣ ዬሚያረጅ  – ዬሚማርት ነው። ዬሰው መውደድ ግን ትውልድን በምርቃት ወተት ዬሚተካ ዬመንፈስ ሃብት ነው። ሄሮድስ መለስ ዜናዊ  ይህን ቀምተው ለዛሬ መጠቋቆሚያ፣ ለነገ ደግሞ መግደያ ገመድ በቦንዳ ደርድረው ነው ሽው ያሉት። በቃ ዬቅብረት ባለ ራዕዩ።ተተኪዎቻቸውም በዛው ሙቀጫ። ለእነሱ ይብላኝላቸው እንጂ ልዕልት ኢትዮዽያማ አላዛር ናት፤ እንደ ወደቀች አትቀርም – ትነሳለች። ጉርድ በርሚሎችም ዝገው ይቀራሉ። ቀድሞ ነገር ጉርድ በርሚል ሙሉ አይደለም ዬጎደለበት ነው። አፈጣጠሩም እንደ ኑሮው ነው ዬምናምንቴ – ማጠረቃቀሚያ። አታድርስ!

ሽራፊ – ጎደሎ። 

ዬሰው ልጅ ሙሉ ሁኖ ተፈጥሮ እንዴት ከወገብ በታችነት ምርጫው ይሆናል? እንዴትስ ሽርፍራፊነትን ምርጫው ያደርጋል ?

ጉርድ በርሚል ታውቃላችሁን? ጉርድ በርሚል ሁልጊዜም አገልግሎቱ ለጭላጭ – ማጠራቀሚያ፣ ለሆመጠጠ ለደረቅ ቅራሪ – ማከማቻ፤ ለአተላ ማጠራቀሚያ – ይውላል። እናላችሁ ከጠልጣላ ነፍስ ዬተጠጋ ሃሳብም ኑሮው፤ ህይወተ – ትናጋው ዬተቆራኘው ከጉርድ በርሚል ጋር ነው። ጉርድ በርሚል ውስጡን ስታዩትም ሽሁራር ዬበላው፤ ዬማረተ ነው፤ አፉም ክርክም አይደለም። እንደ ነገሩ ሸንጠርጠር ብሎ ቅርድድ ነገር ነው። በረት አፍ። ስለዚህ ግጣም ዬለውም። ቢያገኝም ሽርምጥምጥ ያለ መሰሉ ይሆንና – በትክክል ክርችም ብሎ መግጠም – አይችልም። ግጣመቢስ ነው። ሽንጥርጥር ነው። ከጋን፤ ከቸረቸራ ጋርም ግጥም ዬለውም። ጋንና እና ቸረቸራ ክብር አላቸው። ተደላድለው ዬሚቀመጡበት ሟተት ዝንጥ ብሎ በአዋቂ ይሰራላቸዋል። ሥልጡን አውራጆችም ነጠላቸውን አደግድገው ወይንም አጣፍተው፤ በክብር ጉብ ብለው ይከውናሉ – ኃላፊነታቸውን፤ በነገራችን ላይ ቸረቸራና ጋን ዬውበት ሳሎንም አላቸው፤ ብሳና እና እንዶድ ዬገላ ማታጠቢያ፤ አባሎ፤ ግራርና ወይራ ደግሞ ሳውና፤ ዬሚገርመው ዬጉርዱ በርሚልን ጩኽቱ ስለማይመቻቸው ርቆ እንዲቀመጥ፤ ወይም እዳሪ እንዲሆን ቀደም ብለው ሊጋባዎችን ያሳስባሉ። ዬወግ ገበታ ቆርቆሮና ጩኽት፤ ቆርቆሮ – ለጩኽት፤ ጩኽትም – ለቆርቆሮ ስለተፈጠሩ። አያችሁ ናፍቆቶቼ ዬሀገረ ኢትዮዽያ ልጆች ከዕቃ እንኳን ባለግርማ ሞገስ – ዬታቦት ያህል ዬሚከበከብ አለ። ጉርድ በርሚል ግን ዬጥርቅምቃሚ ማጠራቀሚያ እንደሆነ በዝገት – ስንብት። እንደከፋበት። ስለምን? በጎደሎ ቀን ስለተፈጠረ።

ጎረድ ጎረድ አርገው –  አሳዬው ላንቃህን፥

ፍርፋሪ ቢያገኝ ማዝገሚያ – ማምሻህን።

ቅራሪው ካለቀ፥ ለከብትነት መና

ጎደለው ከፍኖ –  ስንብት፥ ዬዝገት ገናና።

ዬላንቃ ሳንቃ – ሰንጣቃ።

አቶ ልደቱ አያሌው ላንቃቸው በጣም እረጅም ነው። ዬቃላቱ አሰካክም ቢሆን ዘለግለግ ያለ ነው። መካተቻው ግን ምርጫው ስለሎሌነትነው። ሎሌነቱ ደግሞ ልክ አልተሰራለትም። ግን … ግን ተዚህች ላይ አንዲት ነገር። ለምስጋና ቁልል ህትምተ – መዛግብት ቤት ዬሚያስፈልጋቸው ይመስላል ለአቶ ልደቱ አያሌው። እራሱ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በህሊናው ሳያቅለሸልሸው አይቀርም ቱባ – በቱባ፤ ነዶ – በነዶ፤ ቦንዳ – በቦንዳ ሲወርድለት፣ ምስጋናው፤ ግነቱ፤ ከንቱ ውዳሴው —- ኧረ ምኑ ቅጡ „ቀናሁባችሁም“ አለበት።

ቁልቁለት ቁልሉ – በላንቃ ተቁላሉ፥

ከንቱነት ቆመሰ ለምንትስ – ጎልጉሉ።

መጥኔ! ወንድ ሆኖ ተፈጥሮ ያልተገራ ላንቃ ተሸክሞ መሄድ፤ መኖርም አበስኩ ገበርኩ!  ዬጫማ መወልወያ ቡርሽ  በስንት ጣሙ። ዬአሁና ዬድርድር አጋፋሪነት አረቂ ከረሚሎ አሸልሞ ይሆን? ከሽልንጓ ላይ እንኳን ለጠኔ ዬሚሆን ምንትሶ ይወረወር – ይሆናል። ሞልቶ ተርፎ ምን – ታቶ። ገንፍሎ ቢባል ይሻላል – ዲታነቱ። እና „ለላንቃህ ውበት¡“ ተብሎ ጣል – ጣል ብዙም አይከብድም፤ ለነዘመኑ„ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል“ ታቅዶ ዬተከወነበት ዘመነ – ሟጠጡ – ከነቀረጢቱ።

ምድር ምጥ ላይ ሆና ቆማ ስታለቅስ፥

ሆድመራኝ ተሁኖ – አውሬን ማቀሰስ።

ጥሪት ትኩሳቱ ጡሊ  – ግዞተኛ፥

ሆነለት፥ አረፈው – ዬሴራ ድረኛ፥

ግድለቱ ዘበኛ፤ ዬሀገር ደመኛ፥

ክስለቱ – መጋኛ!

ዬሚገርመው ቁምጥ ያሉለት የአዲሱ ካቢኔ ዬሹመት ሽርጉድ ዘሏቸው ሽምጥ ሲጋልብ ውሃ እባክህን ቁሉቁሉን ትተህ ሽቅብታውንአምጣው ሆነ“  ሹታው – ክሽፈትን አተመ። ለሌላ ብሄርና ብሄረሰብ ሹመት በገፍ ታደለ።አቶ ልደቱ አያሌው ላንቃቸው እስኪላጥ ዬምላስ እስክስታውን አስነክተውት፤ ወያኔ ጉድጓዱ ዘጭ አደረጋቸው ። ወያኔ ሞኝ! ለዘብሄረ አማራ ዬአራትእግር ባለድርሻነት። አላበዱም። ዘበኝነቱንና ዬላንቃ ሊጋባነቱ ብቻ ነው ዬሚፈገው። „መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንሰኃ ግቡ“ ብሎ መንገድ ደልዳይነት ብቻ። ተዛስ? ተዛማ – አፍንጫህን ላስ ነዋ!  ቆረንጮነት። ወያኔ አስጓጎረ፣ እስኪበቃውም አንጀት ገልብጦ ጎረጎረ፤ ቄጤማዋን ነስነስ፤ ጭሷን አትጎለጎለ፤ ፈንድሻዋን እረጫ … እረጫ… ለአድባሩ አደራርጎ ካዘለዘለና ካንዘላዘለ በኋላ፥ እንደ አዘርከረከ አንቴናው ወደ ሌላው። በቃ! ለ-ልበውልቆች ምሳቸውን  – ያስታጥቃል። አብሶ አለቅላቂዎችን እንደ ጉርድ በርሚል ወገባቸውን ይሁን ወሽመጣቸውን – ጉሙድ።  ቆሽትን ለጥብስ ጀባ በል ብሎ ተንጣጣ … ጣጥ በል በማለት እፍኝ ለማትሞላ ጊዜ አሸበሸበ …. አቶ ልደቱ አያሌውም በወኔና በቁርጠኝነት ተወዛወዙ በክህደት ባንድ። ተንጣጡ … በዝረራ አደረጓቸው – ወያኔ። ድሮስ ባንዳነት ፍርፋሪ፥ ልቅምቃሚ፥ ቅርጥምጣሚ፥ ልቅላቂ ነው ትርፋ።

እያንዳንዷ ማዕልት ዬሞት መልእክተኛ

አልሰማሁም አለ አውቆ ስለተኛ።

በቁሙ መሞቱን – ይነገረው ለሱ፥

ዬባንዳ ትራፊ ለሆነው – ምላሱ።

ዬላንቃ ወበቃ ዬሆለት ምሱ፥

ማይክ ሆኖል ድግሱ – ዬግነት ትራሱ።

ዬላንቃ ባለሟል አቶ ልደቱ አያሌው ላንቃ „ቁምራ“ ዬሚሆን መስሏቸዋል። ቁምጥ ያሉለት ዬአዲሱ ካቢኔ ሹምሽር ቂጡ ዬወለቀ እንሥራ ነበር – ያደረጋችው። ትንሽ እንደ ማጎምጎም ነገር አድርጓቸው ነበር። በተለይ … በተለይ ልባቸው ጥልጥል ያለበት ነገረ ሚዲያና እሳቸው ሊተትሩት ያሰቡት ዲስኩር ዬገደል ማሚቶ ሆኖ እርፍ። „ከሞቱ አማሟቱ“ ይላል ዬጎንደር ሰው። በቁማቸው ግድል አደረጋቸው። ፍላጎታቸውም ተንከርፍፎ ቀረ። ቆሻሻ ማጠራቀሚያ፤ ወይንም ጭላጭ ነገር ሲያስፈልገው ደግሞ አቤቱ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ከላይቤት ዬሴራ ባላባት ከኤርትራዊው አቶ በረከት ስሞኦን ጎን አስቀምጦ ትወናውን – ቀጥላል። ወይን ደግሞ ከስውራን ጠቅላይ ሚ/ር ጋራ ከች ሊያደርግልን ይችላል – ዬወያኔ ሃርነት ትግራይ ባለተስፈኛውን አቶ ልደቱ አያሌውን። አቶ ልደቱ አያሌው „ምነው አምላኬ ለምን ጨከንክብኝ – ትንሽዬ ብጣቂ ዬትግሬነት ደም አክለህ ብትፈጥርልኝ? እንጥፍጣፊያውን ብትቸረኝ ምን ሠርቼህ፥ ምንስ በድዬህ ነው?“  በማለት ሳያጣውሩ አይቀሩም። አይፈረድባቸውም¡ ይህቺ ዬጋብቻ ዝምድና ከሹመኞች ጋር ሳትሆንላቸው ቀርታ ትሆን? ዬሹመኝነት ጠኔው ሞረሞራቸው – ጎለጎላቸው። „አይጣልን ያቀላል ሰው“ ትል ነበር ዬእናቴ እናት። ጥሎባቸው በላላ ገመድ መንጠላጠል ኮኮባቸው – ይመስላል። ችግሩ ገመዷ ያለችው ትናጋ ላይ ብቻ ከመሆኑ ላይ ነው። ዘንድሮም ዓመት ድገሙኝን ልባቸውን እንደ ቅል ጠልጠል ብላ ነበረች። በካራቴ – እነ አጅሬ – ተክነውበታል።

ዬዕናባው ወንዝ ሞልቶ አላሻግር አለ፤

ሰቀቀን ቀን አቶ – ቆሳስሎ መገለ።

ይሮጣል …. ይሮጣል …. ይህ ዬኢጎ አርበኛ

እንቅፋት – መጋኛ፤

ዬምንትስ – ሱሰኛ።

መሳቂያ!

መሳቂያነት በፖለቲካ ሰብዕና ከሆነ ክትመት ጎሳሚ ነው ዬሚሆነው። እንደ ሰው ሆኖ ተፈጥሮ መገዛቴ ጥሞኛልና ቀጥሉበት ማለት እንኩሮነት ነው። ጮሌነትና ለህዝብ ጥቅም መቆም መንገዳቸው እዬቅል ነው። ህልውናውን አጥቶ በሞት ዬሽረት ትግል ላይ ለሚገኝ ምንድቡና አንዲትም ዬተደፈረች ቃል ሳይኖር፥  ዬሄሮድስ መለስ ዜናዊ ዬሞት መላእክተኛ መሆን ሞት በስንት ጣሙ። ያን ያህ ቀረርቶና ፋክራ በተንሳፈፈ ግብዝ ማንነት ላይ ተኮፍሶ መተርተር፥ ትርትርነትን ብቻ ሳይሆን ከአዕምሮ ዬጎደለ ብሎን እንዳለ – ያሳጣል።

እንደ ውሻ እርጥብ ስጋ ባዩ ቁጥር ሜዳ አይብቃኝ ብሎ ዘራፍነትም ዬመንፈስ ብቃትን አጥረ ቀላልነት -ያመሳጥራል። ዬወገኖቻችን ዬግፍ እልቂታና ዬድምጽ አልባዎቹ ዬኢትዮዽያ እናቶች ያላባራ ሰቀቀን፣ ዬዕለት ተዕለት ሥጋት፤ ልጆቻቸው ወጥተው እስኪመለሱ ነፍሳቸው ተንጠልጥላ ኤሉሄ! ኤሉሄ! ማለትን አንድ ኢትዮዽያዊ ዜጋ ሃዘኑ ውስጡን ካልቦረቦረው ሃኪም ቤት ሄዶ መመርመር አለበት። ዬሆነ ነገር ትክክል ያልሆነ ነገር አለ ማለት ነው።

እኔ በተከታታይ ዬሰጡትን መግለጫ ሳዳምጠው ከወያኔ ሃርነት ትግራይ በላይ ዬሥነ – ልቦና ወይንም ዬአዕምሮ ችግር እንዳለባቸው ነው ዬገባኝ። አሁን ያን ያህል ዳንኪራ ዬሚያስመታ ምን በጎ ነገር ኖሮ ይሆን? ያን ያህል ያዙዝኝ ልቀቁኝ ብሎ ምድርን ቀውጢ ማድረግ። አሁን፣ ዛሬ፤ ይህ መራር ዘመን፣ በእውነት አለመታደል፣ መካሪ ማጣትም ነው። ከዕውነት ጋር ተፋቶ ዘመንተኛን እንደታቦት መከብከብ ዬበሽታ ነው። አሁን ላለ ዬጠቆረ ዘመን ሰው መሆን ብቻ ነው ዬሚጠይቀው። ከሰብዕና ወጥቶ ዬሰው ልጅ ዬደረሰበትን ሰቆቃ መለበጫ – ለግል ዝና ማድረግ ዬዕውነት ከሰውነት ተራ ብቻ ሳይሆን ከእንሰሳትም ተራ ያወርዳል። በልጅነት ዬተማርነው ነበር። ዬታማኝ እንሰሳን ክብር። ታማኝ ያልሆነ ሰብዕና ሰውነቱን ያጣ ማንነትን አሽኮኮ አድርጎ ዬሚኖር ግብዝ ነው። ኃላፊነት ካለታማኝነት ምድረ በዳነት ነው ዬህሊና ማሳው። „ኃይለማርያም ማሞ ዬጦሩ ገበሬ ፈረሱን እንደ ሰው አስታጠቀው ሱሪ።“ ኢትዮዽያዊ ፈረሶች ይበልጣሉ ከነ ከንቱ ውዳሴ ሹመኞች። ሽለሽል።

እናሳርገው።

ገድሎም፤ አሳዶም – ዘርፎም ዬማይበቃው ጉድጓድ ጋር ሆኖ መመፃደቅ፣ ዬልክፍት ነው። እሳት ላይ ዬተጣዱ ዕልፎች እዬተቀቀሉ ባሉበት ከድቅድቅ በከፋ ዬሰቀቀን ወቅት ከጨካኞች ጋር አብሮ ለጽዋችን መባበል አረመኔነት ነው። ሰው እንዴት እንባን እያዬ እንዴት ለሌላ ዬቅንጥ ጉዳይ አንደበቱ – ይከፈታል። መርገምት።

ኢትዮዽያዊነት ፈተናን አሸንፎ ዬተፈጠረ ሚስጢር።

መሸቢያ ጊዜ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s