ምንሊክ ሳልሳዊ – ወያኔን ማመን ከእባብ እንቁላል ርግብ መጠበቅ ማለት ነው።ወያኔን ማመን ሳይሆን በጋራ ታግሎ ማስወገድ ብቸኛ አማራጭ ነው።አንድነት የወያኔ ማርከሻ መድሃኒት ነው።
የኢትዮጵያ ትልቁ ችግርና አደጋ ከሆነው ወያኔ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የጠበቃችሁ፤ከወያኔ ሥልጣን መጋራት የፈለጋችሁ ከወያኔ የእምነት፣ የፕሬስና የሃሳብ ነጻነት የጓጓችሁ፤ ‘ከወያኔ ጋር ተስማምቶ መሥራት ይቻላል’ የምትሉ፤ እንኳን አብሮ ለመሥራት ለመወዳደር እድል የማይሰጥ ፈሪ ድርጅት መሆኑን በይፋ አረጋግጧል። ከወያኔ ጋር አንድ ነገር ብቻ ነው የሚቻለው፤ ከወያኔ በታች ሆኖ መሥራት። ጫማ እየላሱ ‘ጌታዬ፦’ ማለት። ያንን የሚመርጥ የፖለቲካ ድርጅት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደፈለገ መንቀሳቀስና መሥራት ይችላል። ጥሩ ቢሮ ይሰጠዋል።ግዙፍ ባጀት ይመደብለታል። ዓመታዊ ጉባዔውን ሼራተን መደገስ ይችላል። በየምክንያቱ ቤተመንግሥት መግባት መብቱ ይሆናል። የመገናኛ ብዙሃን ችግር አይገጥመውም። እስር፣ ዛቻና ወከባ ሕልም ሆነው ይቀሩለታል። ‘ባሪያ የተቃዋሚ ድርጅት’ እየተባለም ይወደሳል።
ወያኔ ሃብትና ሥልጣን አያጋራም። ሁሌም የበላይ ሆኖ ሌሎችን መምራትና መቆጣጠር ብቻ ነው የሚፈልገው። ሌሎቹ እሱን እንዲያጅቡት ነው እቅዱ። ለሚቀጥሉት ብዙ ዓመታትም ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ለመታየት የሚያስችለውን እርምጃ ሁሉ ከመውሰድ አይመለስም። ወያኔ ገንዘብ ያላቸውን ዓለም አቀፍ ዘራፊዎች የሚሰበስበው፣ ከትላልቅ ሃገራት የጸጥታ ድርጅቶች ጋር የሚሰራው፣ ከአለም አቀፍ አሸብር እና ወንጀለኛ ድርጅቶች ጋር በጋራ የሚንቀሳቀሰው ፣ ሰላማዊ ዜጎችን እያፈሰ በአሸባርነት የሚወነጅለው ፣ ገንዘብ እየረጨ በየመንደሩ የራሱን ሚሊዮነር የሚቀፈቅፈውና ሰራዊቱን የሚያንጸው ለሃገር ብሎ አይደለም። ለአንድ ግልጽ ዓላማ ነው፤ ሥልጣኑን ላለማጋራት፤ ሥልጣን አጠገብ ማንንም ላለማድረሰ። መታመን ያለበት እውነት ነው።በምንም ተአምር አትታለሉ፤ወያኔ በምንም ሁኔታ ሥልጣኑን አሳልፎ ለማንም አይሰጥም። ከተለያዩ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የፈለገ ዓይነት ስምምነት ቢያደርግ፣ ሥልጣኑን ያጋራል ማለት አይደለም። ቁራሽ ሥልጣን ጠብቃችሁ ከሆነ ዳግም ተሞኝታችኋል።ወያኔን ማመን ከእባብ እንቁላል ርግብ መጠበቅ ማለት ነው።ወያኔን ማመን ሳይሆን በጋራ ታግሎ ማስወገድ ብቸኛ አማራጭ ነው።አንድነት የወያኔ ማርከሻ መድሃኒት ነው።