የጎንደር ከተማን በትንሹ – ሙሉቀን ተስፋው

የጎንደር ከተማን ስንቶቻችን በሚገባ እናውቃታለን? የተለያዩ መረጃዎችን ስናገላብጥ ያገኘናቸው ጥንታዊ የሰፈር ስያሜ መረጃዎች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ጽሑፎች የተወሰዱት አቶ ምንውየለት ንጌሤ የተባሉ ግለሰብ ባጠናቀሩት መረጃ መሠረት ነው፤ ጽሑፉን የአገኘሁት ባሕር ዳር የዐማራ ባሕልና ቲሪዝም ቢሮ ቤተ መጽሐፍት በ2004 ወይም 2005 ዓ.ም ሳይሆን አይቀርም፡፡

1. *ጥንታዊ ናቸው የሚባሉ እና ተመዝግበው የሚታወቁ
1.1. አደናግር፡-
ይህ ስም ከፋሲል ግንብ 12 በሮች ውስጥ አንደኛው የሚጠራበት ነው፡፡ በሩ በምስራቁ የግቢው ገጽ አዛዥ ጥቁሬ እና ቀስተደመና በር በሚባሉ ሌሎች የግቢው በሮች በመካከል የሚገኝ ነው፡፡ አደናግር ተብሎ የሚታወቀው ሰፈርም የሚገኘው ከበሩ ግንባር ነው/ ነበር፡፡ አደናግር ለምን ለአካባቢው መጠሪያ ሊሆን እንደቻለ በብዙዎች የሚነገር አፈ ታሪክ የሰፈሩ ስም ከገቢው በር ስያሜ እንደተወሰደ ያረጋግጣል፡፡ የሰፈሩ ስፋት በምስረቅ እስከ አርባዕቱ እንስሳ፣ በሰሜን እስከ ደብረ ብርሀን ስላሴ፣ በደቡብ እስከ ግራ ደንበር ይደርስ እንደነበር ይነገራል፡፡ ግንቡ በሮች የተሰሩትም ሆነ የተሰየሙት በአጼ ፋሲል ዘመን በመሆኑ ሰፈሩም ስያሜውን ያገኘው ከዚያ ዘመን ጀምሮ ሊሆን ይችላል፡፡
(በዚህ በር ነገስታቱንና እቴጌዎችን ከአይንና ከጥቃት ለመከላከል፤ እንደ ነጉሶችና ነግስቶች ለብሰውና መስለው ከንጉሶችና ንግስቶች ጋር የሚወጡና የሚገቡ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነኝህ ሰዎች አሳሳቾች ወይም አደናጋሪዎች በመባል ይታወቁ ነበር፡፡ በሩም ስያሜንውን ያገኘው በእነዚህ ሰዎች እንደሆነ ይነገራል፡፡ የበሩ እንዳለ ሆኖ ሰፈሩም አደናጋሪዎች በብዛት ሰፍረውበት ስለነበር ነው ይባላል፡፡)

1.2. እርግብ በር፡-
ይህ ስ ከ12ቱ የግቢው ስሞች አንደኛው ነው፡፡ ከበሩ ፊት ለፊት ያለው ሰፈር እርግብ በር በመባል ይታወቃል፡፡ አጼ ፋሲል እርግብ ያረቡ እንደነበርና ያረቡበት የነበረ ሰፈር ከዚሁ በመሆኑ በዚህ ምክኛት ርግብ በር ተብሎ ተጠራ፡፡ የእርግብ በር ሰፈር የአባ ጃሌ ተክለ ሀይማኖት ቤተ ክርስትያን አካባቢ ጀምሮ እስከ እስከ ፒያሳ ይሸፍን እንደነበር ይገመታል፡፡ አርግብ የማርባት ልምድ ያላቸው አጼ ፋሲል ብቻ በመሆናቸው የሰፈሩ ስያሜ በእርሳቸው የንግስና ዘመን ሊሆን ይችላል፡፡ በአሁኑ ሰዐት ግን ሰፈሩ እርግ በር በሚል እነደ ጥንቱ እምብዘም አይታወቅም፡፡
1.3. እንኮየ መስክ፡-
እስከ አሁን ድረስ በከተማው ውስጥ በቀደምት ስማቸው ይታዎቃሉ ከሚባሉት ሰፈሮች እንኮየ መስክ አንደኛው ነው፡፡ ይሁኑ እንጅ መጀመሪያ በስሙ ይጠራ የነበረው አካባቢ ሁሉ በስሙ እየተጠራ አይደለም፡፡ የእንኮየ መስክ ሰፈር የሚገኘው ከፋሲል ግንብ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በቀኝ ቤትና በእጨጌ ሰፈሮች መካከል ይገኘል፡፡
ሰፈሩ ለምን እንኮየ መስክ ሊባል እንደ ቻለ የተለያዩ አፈ ታሪኮች ይነገራሉ፡፡ በብዙዎች የሚነገረው ግን ወይዘሮ እንኮየ ሰፍረውበት ስለነበረ በወይዘሮዋ ስም እንደተጠራ ይታሰባል፡፡ ወይዘሮ እንኮየ የአጼ በካፋ ሚስት፣ የእቴየ ምንትዋብ እናት ነበሩ፡፡ የሰፈሩ ስም አመጣጥ ከወይዘሮ እንኮየ አሰፋፈር ጋር ከተገናኘ ሰፈሩ በስሙ መጠራት የጀመረበት ጊዜም ከአጼ በካፋ ወይም ከቋረኛ ኢያሱ ጊዜ ጀምሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህኛው አፈ ታሪክ ሌላ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይኸውም እንከየ መስክ በሚገኝበት አካባቢ እንኮየ በር የሚባል የግንቡ በር አለ፡፡ ስለዚህ በሩ እንዴት እንኮየ በር ተብሎ ሊጠራ ቻለ ነው፡፡ ምንአልባትም በአጼ ፋሲል ዘመን በሌላ ስም ሲጠራ ቆይቶ በእንኮየ ስም ዘግይቶ በአጼ በካፋ ወይም በኢያሱ ዘመን ተቀይሮ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስያሜው ከአጼ ፋሲል ጀምሮ የነበረ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ለዚህም እንኮየ የምትባል ከአጼ ፋሲል ገረዶች መካከል ሃላፊ ሆና ትኖርበት ስለ ነበር ወይንም እንኮየ የምትባለው የንጉሱ ቅምጥ ትኖርበት ስለነበር ነው የሚሉ አሉ፡፡
1.4. ፋሲለደስ፡-
ፋሲለደስ ይባል የነበረው ሰፈር ስሙን የወሰደው አጼ ፋሲል በአሰሩትና ፋሲል መዋኛ ገንዳ ግቢ ውስጥ ይገኝ ከነበረ ቅዱስ ፋሲለደስ ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ የፋሲለደስ ሰፈርና የቤተ ክርስቲያኑ በሰሜን እስከ ቀሃ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያነ ሰበካ፣ በምዕራብና በደቡብ እስከ መጥምቁ ዮሀንስ ሰበካና በምስራቅ እስከ ሀይሌ ሜዳ ይባል የነበረውን ይሸፍን ነበር፡፡
በስሙ ይጠራበት የነበረውን ሁሉንም ባይሸፍንም በመዋኛው ገንዳ አካባቢ ፈጽሞ አልጠፋም፡፡
1.5. ዋላጅ፡-
በጎንደር ከተማ ስር ነበሩ ተብለው በቄስ ገሪማ ታፈረ (የፕ/ረ ኃይሌ ገሪማ አባት) ከተመዘገቡት ሰፈሮች አንዱ ዋላጅ ሲሆን ሰፈሩ አሁንም በዘሁ ስም ነው የሚጠራ ነው፡፡ ነገር ግን ዋልጅ የሚለው ሰፈር የጎንደር ከተማ ከመቆርቆሩ በፊትም እነደ ነበር ይነገራል፡፡ ከጎንደር ከተማ መቆርቆር በፊት እንደነበረ ቢታሰብም መቼ ጀምሮ ዋላጅ ተብሎ መጠራት እንደጀመረና የቃሉ ትርጉም በትክክል አይታዎቅም፡፡ እንደአንዳንድ አባቶች ከሆነ ዋላጅ የሚለው ቃል ለአካባቢው መታወቂያ ሊሆን የቻለው በአጼ ናኦድ ዘመን /1487-1500/ ስድስት የተወለዱ ስድስት የተወደዱ ተብለዎ ለሚታወቁ ሰዎች ርስት ጉልት ሆኖ ተሰጣቸው፡፡
ተወላጅ- ስድስቱ የተወለዱ ከንቲባ ተስፋ የሚባል የቤተ መንግስት ባለሟል ልጆች ነበሩ፡፡ አገሩ ሊሰጣቸው የቻለው የተወለዱት በቤተ መነግስት ተወላጅነታቸው የተወደዱት አባታቸው ታማኝ፣ የታፈረና የተከበረ የቤተ መንግስቱ አገልጋይ ስለነበረለአባታቸው መልካም ስራ ውለታ ነበር፡፡ ስድስቱ የተወለዱት በቤተ መንግስት ተወላጅነታቸው ከነበራቸው ክብር ጋር ባለርስት ጉቶች ስለነበሩ ከይዞታቸው በኋላ አገሩ የውላጅ አገር ተብሎ ተጠራ፡፡ጊዜ እየረዘመ ሲሄድ ግን አገሩ የውላጅ መባሉ ቀርቶ ውላጅ በኋላም ዋላጅ ወደሚል ቅላጼ ተቀየረ፡፡
ዋላጅ ከአካባቢው የመጀመሪያ ሰፋሪዎች አባት ስም ነው የሚሉም አሉ፡፡ ዋላጅ ከርከር የሚባል ወንድም ነበረው፡፡ የከርከር ልጆች የሰፈሩበት አገርም ከርከር ተብሎ ስለተጠራ የሁለቱ ወንድማማቾችና ዘሮቻቸው አገር ከርከርና ዋላጅ ተብሎ እንደተጠራ፤ በአሁኑ ወቅት ግን ከርከርና ዋላጅ የሚባሉት አካባቢዎች መጠሪያዎቻቸው ተለያይተው የሚታቁ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ናቸው፡፡
ከአካባቢው አባተች ዋለጅ ከ44ቱ ጎንደር ውስጥ እንደነበር የሚተርኩ አሉ፡፡ እንዲያውም 44ቱ ጎንደር የሚለው መጠሪያ ሊወጣ የቻለው ከ44ቱ ቤተክርስቲያኖች ስለ ነበር፤ ከ44ቱ ውስጥ ደግሞ 4ቱ የሚገኙት በዋላጅ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያኖቹም ቅዱስ አማኑኤል፣ ድባ ሀዋርያት /ድርቡሾች አቃጥለውት ኖሮ በ1951 ቤተ ክርሰቲያኑ ተሰርቶ የአቦ ታቦት ስለገባ ድባ አቦ እየተባለ ይታወቃል/፣ ምንጭርና ጊወርጊስና ቸሆን ማርያም ይባሉ እንደነር ይነገራል፡፡
በዋላጅ በአሁኑ ወቅት *ሸንበቂት የምትባል ከተማ ተመስርታበታለች፡፡ ሸምበቂት የሚለው መጠሪያ አሁን ከተማዋ ከምትገኝበት ምዕራብ አቅጣጫ ብዙ ኪሎ ሜትሮች ራቅ ብሎ በሸንበቆ ተሸፍኖ ይገኝ ከነበረና ሸንበቆች ተብሎ ከሚጠራው ዳገታማ አካባቢ የተወሰደ ነው ይባላል፡፡ ሸንበቂት ከጎንደር ከተማ ወደ ደባርቅ በሚወስደው አውራ መንገድ ዳር ከከተማው ከ9/10 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡
(*አሁን ከተማዋ ሸምበቂት ከመባሏ በፊት ፈላሻ ሜዳ በመባል ትታወቅ ነበር፡፡ ፈላሻ ሜዳ የተባለው ፈላሻዎች በብዛት ሰፍረውበት ስለነበር ነው፡፡ ፈላሻዎች ለባለርስትና ጉልት ሸክላ ብረትና ልብስ በመስራት ያገለግሉ ነበር፡፡ ከፈላሾች ጋር ቅማንቶችም ያገለግሉ እንደነበር ይነገራል፡፡)
1.6. አዘዞ፡-
*አዘዞ የሚለው መጠሪያ የጎንደር ከተማ ከመመስረቱ በፊትም እንደነበር የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ (*ስርግው፣ አማርኛ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት፣ ገጽ 90፤)፡፡ አዘዞ ለሚለው ቃል አመጣጥ ከአጼ ሲስንዮስ የመጨረሻና ከአጼ ፋሲል የመጀመሪያ አመታት ጋር አገናኝተው የሚተርኩ አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል አንደኛው **አጼ ሲስንዮስ /ከ1598/9 – 1624/ አባቶቻቸው ይከተሉት የነበረውን የኦርቶዶክስ እምነት ትተው የካቶሊክ እምነት ተከታይ ሆኑ፡፡ በካቶሊክ እምነት ከመጠመቃቸው በፊት ግን በኋላ አዘዞ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የኢየሱስ ቤተ ክርስቲያንን አስተክለው ስለነበር ሀይማኖታቸውን ከለወጡ በኋላ የካቶሊክ ስርዓተ ቅዳሴና ጥምቀት እንዲካሄድበት አደረጉ፡፡ ህዝቡም ነባሩን እምነት ትቶ በአዲሱ እንዲጠመቅ አወጁ፡፡ ይሁንጅ ካህናቱና ህዝቡ አዲሱን ሀይማኖት አንቀበልም በማለታቸው በተነሳው ጦርነት ብዙ ህዝብ አለቀ፡፡ ብዙ ካህናትና መነኮሳትም ሀይማኖታቸውን በለወጡት እጅ ተገድለው መስዋትነትን ለመቀበል ንጉሱ ወደሚገኙበት እየመጡና ንጉሱንም እያወገዙተገደሉ፡፡ አጼ ሲስንዮስ አዲሱን ሀይማኖት ህዝቡ እንዳልተቀበላቸው ሲያውቁ ዙፋናቸውን ለልጃቸው አስረከቡ፡፡ የሮም ሀይማት ትርከስ፤ የእስክንድር ሀይማት ትመለስ፤ ሲስንዮስ ይፍለስ፤ ፋሲል ይንገስ የሚል አዋጅ ተነገረ፡፡ አጼ ፋሲልም ከነገሱ በኋላ ከሸዋ የአቡነ ተክለ ሀይማኖትን ታቦት አስመጥተው በመስቀል ባርከው በወንጌል ሰብከው ብዙዎች ሰማዕትነት በወደቁበት አካባቢ ያስተክሉት ብለው አእጨጌ በትረ ጊወርጊስን ስለ አዘዙ፤ አዘዙ ከሚለው ቃል አዘዞ የሚል ቃል ወጥቶታል የሚል ነው፡፡
በሌላ በኩል ዶክተር ስርግው ሀብተ ስላሴ እንደጻፉት ከሆነ ንጉሰ ነገስቱ /አጼ ሲስንዮስ/ ደምቢያ ውስጥ ካሉት ሀገሮች መልካሙን ምድር አዘዞን መረጠ፡፡ … በቦታውም መልካምነት የአዘዞ ተክለ ሀይማኖትን ቤተ ክርስቲያን መስራት ጀመረ፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s