ጻዕረ ሞትና መስፍን ወልደ ማርያም (መስፍን ወልደ ማርያም)

ጥር/ 2009

አንደኛ፣ ገና በልጅነቴ አሥር ዓመት ግድም ሲሆነኝ አንድ በድቀድቂት ከእንጦጦ ወደታች የሚወርድ ኢጣልያዊና እኔ ተጋጠምን፤ እሱ በዚያ በጥቁር ድንጋይ ኮረት በረበረበበት መንገድ ላይ ሲጓዝ ወደእንጦጦ የሚወጣ ወታደሮችን የጫነ ከባድ መኪና ቆሞ ነበር፤ በዚያ መኪና ላይ አንድ ዝንጀሮ ነበር፤ የኔ አትኩሮት በዚህ ዝንጀሮ ላይ ነበር! እንደሚመስለኝ ዝንጀሮውን እያየሁ ስሮጥ ከድቅድቂቱ ጋር ተገናኘን፤ እኔ ከስር በተረበረበው የጥቁር ድንጋይ ኮረት ላይ፣ ድቅድቂቱ ደግሞ የእኔን ራስ ጨፍልቆ!ምኒልክ ሀኪም ቤት ከስንት ቀኖች በኋላ የካቶሊክ መነኮሳት አስታማሚዎች ከነመለዮአቸው አልጋዬ አጠገብ ቆመው በትልቅ የበሽተኞች ድንኳን ውስጥ በአንዱ መደዳ ውስጥ ተኝቼ ነቃሁ፤ መድኃኔ ዓለም ማንን ልኮ የእኔን ጭንቅላት ከድንጋዩና ከድቅድቂቱ መክቶ እንዳዳነኝ አላውቅም፡፡


ሁለተኛ ከሶደሬ መውጫ ላይ በመቶ ሰባ ኪሜ የሚሽከረከር መኪና ተገልብጦ ከመኪናው በጣራው በርሬ ወጥቼ የጥቁር ድንጋይ ሰፈር በሆነበት አሸዋ ተነጥፎልኝ ሳልፈነከት በጭንቅላቴ አረፍሁና በጸጉሬ አሸዋ አፍሼ ተነሣሁ።ሦስተኛ በፓሪስ በአንድ ዓለም-አቀፍ ስብስባ ላይ የተጠናወተኝ ሕመም እስከሎንዶን ተከትሎኝ፣ ወደአዲስ አበባ ለመመለስ አንድ ወዳጄ አውሮጵላን ጣቢያ ወሰደኝ፤ እኔ ከሆቴል ከወጣሁ በኋላ ምንም የማስታውሰው ነገር የለኝም ፤ ጻዕረ ሞት እያለሳለሰ ይዞኝ በመሄድ ላይ ነበረ፤ በሦሰተኛው ቀን በሆስፒታል ውስጥ ነቃሁ፤ አሥራ ሦስት ቀን በሀኪም ቤት ስታከም ቀይቼ ወጣሁ፡፡
አራተኛ በቃሊቲ የወያኔ እስረኛ ሆኜ ጻዕረ ሞት ጎበኘኝ፤ ደበበ እሸቱ ደረሰበትና በወያኔ መልካም ፈቃድ በላንድሮቨር ወደፖሊስ ሆስፒታል ዶክ. ሰይፉ ተረከበኝ፤ ለሦስት ቀናት ያህል ረሴን አላውቅም ነበር፡፡

አምስተኛ ተወልጄ ያደግሁበት አዲስ አበባ በድንገት ላንተ አይሆንም የተባለ ይመስል ኦክሲጄን እያነሰብኝ ትንፋሽ ያጥረኝ ጀመረ፤ አዋሳ ሄጄ አንድ ወር ያህል በሰላም ቆየሁ፤ከዚያ በኋላ አገሩ ሁሉ በፉከራ፣ በጭስና በእሳት ታፈነና በአገሬ መሄጃ አጣሁና ወደህንድ መጣሁ፤ ለአሥር ቀናት ያህል ሰላም አገኘሁ፤ ከዚያ ጻዕረ ሞት ተቆጥቶ መጣ! እጄንና እግሬን ይዞኝ ታገልን! የእውነት ትግል ነበር፤ የሆቴሉን ስልክ አንሥቼ እያቃሳትሁ ወደሀኪም ቤት የሚወስደኝን መኪና (አምቡላንስ) እንዲያስመጡልኝ ጮህኩኝ! ኦክሲጀንና ሌላም ነገር እያማጉኝ በዚያ ሰውና መኪና፣ ድቅድቂት እየተጋፋ እየተዳፋ በሚሄድበት መንገድ ለረጅም ጊዜ እየተንገጫገጭሁ ተጓዝሁ፤ ነፍስ ውጪ-ነፍስ-ግቢ ክፍል አስገቡኝ፤ ጻዕረ-ሞት ተናድዶ እየዛተ ጥሎኝ ሄደ፡፡እሱም አይቀር! እኔም ማምለጫ የለኝ!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s