ጎሰኝነት የአንድነትና የሀገር ጠንቅ ነው | ከፍያለው አባተ (ዶ/ር)

ከውጭም ከውስጥም በአማራው ሕዝብ ላይ ያተኮረ የጥቃት ዘመቻ ለረዥም ጊዜ ሲካሄድ መቆየቱና በደሉ አሁንም (የመንግሥትን ሥልጣን በበላይነት በሚመራው በወያኔ አቀነባባሪነት) ይበልጥ ተጠናክሮ በመቀጠሉ አንዳንድ የአማራ ልሂቃንን “እኛም እንደሌሎች የአማራ ጎሳ ፓርቲ አቋቁመን አማራውን ከጥቃት እንከላከላለን” እንዲሉ ገፋፍቷቸዋል። “እሾህን በሾህ” እንደሚባለው፤ ጎሰኝነት የተጠናወተው ወያኔ የሚፈጽምብንን በደል በአማራ ጎሰኝነት እንመክተዋለን እንደማለት ነው። ይህ አመለካከት ግን (እንደኔ አስተሳሰብ) ውስብስብ ለሆነው የሀገራችንና የአማራ ችግር መፍትሔ አይሆንም፤ አይሠራም።

የአማራ ፓርቲ የማቋቋሙን ሀሳብ በመቃወም በቅርብ ጊዜ አንዲት አጭር ጽሑፍ (በኢትዮሚዲያ ድህረ- ገጽ በኩል) አስተላልፌ ነበር። የአማራ ፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም ሽር-ጉድ በሚባልበት ባሁኑ ጊዜ ተቃውሞ ማሰማት እንደማይጥም ይሰማኛል። “እንዳልይዘው ፈጀኝ፤እንዳልተወው ልጄ ሆነብኝ” አለች ይባላል የእሳት እናት። ዝም አይባል ነገር የወገንና የሀገር ጉዳይ ነውና (ይመለከተኛል)፤ በፓርቲው ምሥረታ (ሌላው ቢቀር በቲፎዞነት እንኳን) ተባባሪ አይኮን ነገር (በኔ ግምት) መስመር/ፈር የለቀቀ፤ አቅጣጫውን የሳተ አካሄድ ነው። ስለዚህ ባይጥምም የአማራን ፓርቲ ምሥረታ በሚመለከት ይህችን የመጨረሻ ሀሳቤን ላንባቢዎች ለማካፈል ወሰንኩ።

በሀገር ግምባታ ታሪካችን ውስጥ ቀንደኛ ተሳታፊ የሆነውንና በሀገሩ (በኢትዮጵያ) ሲመካ የኖረውን የአማራ ሕዝብ በጠባብ የጎሳ ከረጢት ውስጥ መክተት፤ ሲገነባው የኖረውን የሀገር አንድነት በማላላቱና በመበተኑ ተግባር እንዲሳተፍ ማድረግ ነው። ገምብቶ ማፍረስ።

የሀገር አንድነትን መጠናከርና መላላት (ከጠናም መፈራረስ) በሚመለከት የፖለቲካ ጅኦግራፊ ምሁራን ሁለት ኃይሎች መኖራቸውን ይናገራሉ። እነዚህ ኃይሎች የስበትና (centripetal forces) የግፊት ኃይሎች (centrifugal forces) ናቸው። የስበት ኃይሎች የተባሉት የአንድን ሀገር ሕዝብ አንድነት የሚያጠናክሩ ልዩ ልዩ ኃይሎች ናቸው። የግፊት ኃይሎች የተባሉት ደግሞ ለአንድ ሀገር ሕዝብ መበታተንና ለሀገር መፍረስ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው። የስበት ኃይሎች ከግፊት ኃይሎች የበለጠ ብርቱ ከሆኑ የሀገርና የሕዝብ አንድነት እየጠነከረ ይሄዳል። የግፊት ኃይሎች ከስበት ኃይሎች ይልቅ የሚጠነክሩ ከሆኑ ግን የሀገርና የሕዝብ አንድነት እየላላ ይሄድና ሀገር እስከመፍረስ ሕዝብም እስከመበተን ሊደርስ ይችላል ይላሉ።

እነዚህ የፖለቲካ ጅኦግራፊ ምሁራን ከዚህ የሚከተሉትን አራት ዋና ዋና የስበት ኃይሎች (centripetal forces) ይሰጡናል፡ 1. የሀገር ፍቅር (nationalism) 2. አጣማሪ/አዋሀጅ ድርጅቶች (unifying institutions): ለምሳሌ፤ ትምህርት ቤቶች፤ የጦር ሠራዊት፤ ከመንግሥት ጋር የተቆራኘ ቤተክርስቲያን (state church)፤ ወ.ዘ.ተ. 3. ቀልጣፋ ድርጅቶችና የመንግሥት አስተዳደር (effective organization

and administration of government) 4. መጓጓዣና መገናኛ (systems of transportation and communication) ናቸው።

የሀገራችን ታሪክ ወደኋላ መለስ ብለን የቃኘን እንደሆነ ያለፍንበት የሀገር ግምባታ ሂደት ከሌሎች ሀገሮች ሀገር ግምባታ ሂደት ጋር ሲነጻጸር የረባ ልዩነት አይታይበትም። በእርስ በርስ ጦርነት፤ በስደት/በፍልሰት፤ በጋብቻ፤ በንግድ፤ የውጭ ጠላትን አብሮ በመመከት፤ ተፈጥሯዊና ሰው-ሰራሽ የሆኑ (ክፉም ደግም የሆኑ) ነገሮችን ለረዥም ጊዜ አብሮ በመካፈልና በመሳሰሉት የተለያዩ ክስተቶች ውስጥ በማለፍ የኢሕአዴግ መንግሥት እስከ መጣ ድረስ አንድ አሀዳዊ መንግሥት መሥርተን ኑረናል። የሀገርን ፍቅር ለማዳበር ትምህርት ቤቶች (በተለይም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች) ትልቅ ሚና ነበራቸው። በሰንደቅ ዓላማ፤ በመዝሙር፤ በዘፈንና በቀረርቶ አማካይነት ከህጻንነት ጀምረን የሀገር ፍቅር በአእምሯችን እንዲሰርጽ ይደረግ ነበር።

እናት አባት ቢሞት በሀገር ይለቀሳል ሀገር የሞተ እንደሁ በምን ይለቀሳል

እየተባለ ይገጠም ስለነበር ወጣቱ ሀገሩን ከወላጆቹ አብልጦ ይወድ ነበር። አስፈላጊም በሚሆነበት ጊዜ ለሀገሩ ለመሞት የተዘጋጀ ነበር። የጦርነት አዋጅ በታወጀ ቁጥር ሚስቴን ልጄን፤ ማቄን ጨርቄን ሳይል በየጦር ሜዳው በመሰዋት ለሀገሩ ያለውን ፍቅር በተግባር አስመስክሯል። ይህ ዓይነት ጠንካራ የሀገር ፍቅር ግን በኢትዮጵያ ምድር ሁሉ ወጥነት ነበረው ማለት አይደለም። ወጥነት እንዳይኖረው እሚያደርጉ (ባብዛኛው ከመንግሥት አቅም እጥረት የሚመነጩ) ብዙ ምክንያቶች ነበሩ። በነበራቸው አቅም ልክ ግን የመንግሥትን ሥልጣን ይዘው የነበሩት ገዥዎቻችን የሀገርን ፍቅር ለማጠንከር ብዙ ጥረት ያደርጉ ነበር። ያሁኑን አያርገውና አንድ ሰው ስራ ለመቀጠር እንኳን ለቃለ መጠይቅ ሲቀርብ “ስራ ብታገኝ ምን ታደርጋለህ?” ተብሎ ሲጠየቅ “ሀገሬን እረዳለሁ” ካለ ስራ ያገኛል ይባል ነበር።

የሠራዊቱ ስብጥር ከየጎሳው የተውጣጣ ስለነበር የሀገርንና የሕዝብን አንድነት እሚያጠናክር ነበር። የኢትዮጵያ ወጣ ገባ መሬትና ደካማው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የመንገድና የመጓጓዣ አገልግሎቱንና የጎሳዎችን ግንኙነቶች ቢገድብም፤ በመንግሥት ስራ አመዳደብ በኩል ሲታይ ግን ያንዱ አካባቢ ተወላጅ ወደሌላው አካባቢ ይመደብ ስለነበር ሕዝብን ለማስተዋወቅና የሀገርን አንድነት ለማጠናከር አስተዋጽኦ ነበረው። ይህም የሀገርን ፍቅር ለማጠናከር የመንግሥት ባለሥልጣናት ያደርጉት የነበረውን ጥረት ያመለክታል። ታዲያ ከላይ ከ1 እስከ 4 የተዘረዘሩት የስበት ኃይሎች (centripetal forces) አንድነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉት በጸጥታው፤ በአገልግሎት አሰጣጡ፤ በሀብት አደላደሉና ክፍፍሉ፤ በፍርድና ፍትሕ አሰጣጡ፤ በስራ አመዳደቡ፤ በሕዝብ ተሳትፎውና በሌሎች በሌሎችም ጭምር ሚዛናዊነቱ የተጠበቀ አሰራር እንዲሰፍን መንግሥት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ነው።

ከሁሉም የበለጠ በሀገር ግምባታው ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና በመጫወት የስበት ኃይሉን (centripetal forces) ያጠናከሩት ነገሥታቱና አገር-በቀል የሆነቺው የኢትዮጵያ ተዋሕዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ነበሩ። የነሱ (የነገሥታቱና የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን) ዓይነተኛ ተከታይ/ሠራዊት በመሆን አብሮ አገር ያቀናው ክርስቲያኑና ከሌላ ሃይማኖት ወደ ክርስትና የተለወጠው ሕዝብ ነው። ያ ሁሉ ተከታይ/ሠራዊት በየደረሰበት አማርኛ እየተናገረ፤ የክርስትና ሃይማኖትን እያመለከና እያስፋፋ፤ ሰፊ መሬትና ብዙ ጎሳዎች በውስጧ

ያካተተች አሀዳዊ ኢትዮጵያን መሠረተ። አማርኛ፤ክርስትናና ዘውድ እንደ ሦስቱ ሥላሶች እማይለያዩ አንድም ሦስትም ሆኑ። ክርስቲያን የሆነውና አማርኛ የሚናገረው ሁሉ አማራ ሁኖ ተቆጠረ። አማርኛን ያስፋፉትም ከነጋዴው በተጨማሪ ወታደሩ፤ መሳፍንቱና መኳንንቱ ነበሩ። ይህን በተመለከተ ከአጼ ሱስንዮስ ጋር ወደጎንደር የሄዱ ኦሮሞዎች፤ በነአጼ በካፋ ዘመን ጎንደር የነበሩ ኦሮሞዎች፤ የዘመነ መሳፍንት ምእራፍ ከፋች የሆኑት (ትግሬው) ሚካኤል ሥዑል ከነሠራዊታቸው፤የየጁ ኦሮሞዎች (ከታላቁ ራስ ዓሊ ጀምሮ እስከራስ ጉግሳ ወሌ ድረስ) ከነሠራዊታቸው፤ የጐጃሙ ራስ አዳል (በኋላ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት) ከነሠራዊታቸው፤ አፄ ዮሐንስ 4ኛ ከነሠራዊታቸው፤ የየራሳቸውን ቋንቋ በመጠቀም ፈንታ አማርኛን ያደባባይ (የችሎት) ቋንቋ አድርገው በመጠቀማቸው ለአማርኛ ማደግና መዳበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ባንድ (በአማርኛ) ቋንቋ በመናገርም የሕዝቦችን አንድነት፤ የሀገርን ቀጣይነት (የስበትን ኃይል) አጠናክረዋል። ከማንም የበለጠ አማርኛን ያዳበሩትና ያስፋፉትም እነዚሁ የኦሮሞና የትግሬ ባለሥልጣኖች ከነሠራዊታቸው ናቸው። አማርኛውን ያስፋፉት በእቅድ ሳይሆን ባጋጣሚ ይመስለኛል። አማርኛ (እንደ ምሥራቅ አፍሪካው ሱዋሂሊ) በአጋጣሚ ያደገና የተስፋፋ ቋንቋ ነው።

ቀደም ብየ እንደጠቀስኩት ክርስቲያን የሆነውና አማርኛ የሚናገረው ሁሉ ከዘውዱ (ከነገሥታቱና ከመሳፍንቱ) ጋር በመሰለፍ ሀገር በማስፋፋቱና አንድነትን በማጠናከሩ ተግባር ተሳትፏል። በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያን አንድነት የሚጻረሩ የውጭ ጠላቶችና (በውጭ ጠላቶች የተሰበኩ) የውስጥ ጎሰኞች በአማራው ላይ ሲያነጣጠሩ ኑረዋል።

  •   የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተስፋፋው ከላይ በጠቃቀስኳቸው በትግራይና በኦሮሞ መኳንንትና መሳፍንት አማካይነት ነው። ቤተክርስቲያን እያሰሩ፤ በብዙ መቶ ጋሻዎች የሚለካ የመተዳደሪያ መሬት ለቤተክርስቲያን እየሰጡ፤ በዘመቱበትና በተሾሙበት ቦታ ሁሉ ታቦት እየተከሉ፤ ካህን እያስወሰዱ/እያስመደቡ የክርስትናን ሃይማኖት አስፋፉ። ነገሥቱቱ ለክርስትና ሃይማኖት ብቻ ያደሉ ቢሆንም ብዙ ሕዝብ (በተለያዩ ሃይማኖቶች ስር ከሚሰባሰብ ይልቅ) በአንድ ሃይማኖት ስር እንዲሰባሰብ ማድረጋቸው ለሀገር ቀጣይነትና ለሕዝቦች አንድነት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው። የስበትን ኃይል የማጎልበት ወይም የሀገርን አንድነት የማጠናከር ስራ ነው የሰሩት።
  •   ለሀገር አንድነት ጥንካሬ ብዙ ቋንቋ ከመጠቀም ይልቅ ባንድ የጋራ ቋንቋ መግባባት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ስለዚህ አማርኛን በማስፋፋታቸውና በማዳበራቸውም ሊመሰገኑ ይገባ ነበር። ግን በመመስገን ፈንታ ተወቃሽ ሁነዋል።ክርስትና ሃይማኖት የአማራ፤ አማርኛ ቋንቋ የአማራ ስለሆኑ፤ አማራ ከሌሎቹ ጎሳዎች ልቆ ይታያል። ስለዚህ ኢትዮጵያ የአማራ የበላይነት የሰፈነባት፤ ሌሎቹ ጎሳዎች የተጨቆኑባት ሀገር ነች በማለት ምሁራን የተባሉት ኢትዮጵያዊያን የሀገር አንድነትን ወደመሸርሸር ገቡ። “የብሔሮች እኩልነት” ተብሎ በምሁራን ጐራ ሲቀነቀን የኖረው ይኸው አሁን ፍሬ አፍርቶ ኢትዮጵያ በጎሳ ክልሎች ተከፋፍላ እንዳሻሮ እንድትታመስ አደረጋት። ይህ በምሁራን ጐራ የተጀመረው ‘የብሔሮች እኩልነት’ ጥያቄ የግፊት ኃይሎችን (በታኝ ኃይሎችን) የጋበዘ ነው።የፖለቲካ ጆግራፊ ምሁራን የግፊት ኃይሎች (centrifugal forces) ብለው የሚጠሯቸው አንድነትን የሚፈታተኑትን፤የበታኝነት ሚና የሚጫወቱትን፤ ለአሀዳዊ ሀገር ቀጣይነት መሰናክልና ጋሬጣ የሚሆኑትን

የተለያዩ ሁኔታዎች ነው። ለምሳሌ፤ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ጎሳዎች ብዛት፤የተለያዩ ሃይማኖቶች ብዛት፤ ከጎሳዎች፤ ከቋንቋዎችና ከሃይማኖቶች ጋር አብረው የሚከሰቱ የባህል ልዩነቶች፤ የአገዛዝ/ያስተዳደር ብልሹነትና የመሳሰሉት ግፊት ሰጪ (በታኝ) ኃይሎች ናቸው። ያገዛዝ ብልሹነት የስበት ኃይሎች የተባሉትን ሳይቀር እሚያኮላሽ መጥፎ የግፊት (በታኝ) ኃይል ነው።

ሀገራችን ከ80 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ በርካታ ጎሳዎች የሚገኙባት ሀገር ነች። የጎሳውና የቋንቋው ብዛት የስበትን (ያንድነትን) ኃይል የሚያላላ ራሱን የቻለ ታላቅ ተግዳሮት (challenge) ነው። እነዚህ ጎሳዎች አብዛኞቹ በኢትዮጵያ ድምበር ውስጥ በመኖራቸው ብቻ ኢትዮጵያዊያን ቢሆኑም፤ በአስተዳደር ብልሹነት በኢኮኖሚውና በተለያዩ አገልግሎቶች አሰጣጥ የተረሱና ወደ ዳር የተገፉ በመሆናቸው ጥልቅ የሆነና ስር የሰደደ የሀገር ፍቅር አላቸው ለማለት አይቻልም። ስለዚህ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ኖረች አልኖረች ደንታ አይሰጣቸውም። ራሳችን እንችላለን (እንገነጠላለን) ለማለትም ጊዜ አይወስድባቸውም።

ኢትዮጵያ ብዙ የግፊት ኃይሎች የሚፈታተኗት ሀገር ነች። የሕዝቦችን ግንኙነት ገድቦ የኖረው ያገራችን ወጥ-ገብ መሬት ሳይቀር የግፊት (ግንኙነትን የማሰናከል) ኃይል አለው። ዓይነተኛ የሚባለው የግፊት ኃይል ግን የጎሳና የቋንቋ ብዛት ነው። ሀገራችን የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ልዩ ልዩ ጎሳዎች ያሏት በመሆኗ በጣም አስተዋይ፤ ሚዛናዊና አሳታፊ መንግሥት ካልኖረ በስተቀር ለመፈረካከስና ለመፍረስ የሚያስችል ጠንካራና በርካታ የግፊት ኃይል ያለባት ሀገር ናት። ይህ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ጎሰኛ መንግሥት በማጠናከር ላይ ያለው እነዚህን የግፊት (በታኝ፤አፍራሽ) ኃይሎች ነው። ይህ መንግሥት (በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲል) የሀገርን ቀጣይነትና የሕዝብን አንድነት የሚፈታተኑ ቀዳዳዎችን ሁሉ በመብራት የሚፈልግ ይመስላል። ጥቃቅን ጎሳዎችን ሁሉ እየፈለገ የጎሳ ድርጅቶችን ከማቋቋም አይቆጠብም።

ሕዝቦች በየራሳቸው የጎሳ ጐጆዎች ተኮድኩደው እንዲቀመጡ፤ ወደሌላ ጐሳ ክልል ሲሄዱ በባእድ ሀገር የሚኖሩ ያህል እንዲሳቀቁ፤ አለመግባባት በተፈጠረ ቁጥር ሂዱ/ውጡ እንዲባሉ፤ ባጠቃላይ ጎሳ ከጎሳ የጐሪጥ እንዲተያይና እንዲራራቅ የሆነው (በኔ አስተያየት) ይህ መንግሥት በጎሰኛው ወያኔ የበላይነት ስለሚመራ ብቻ አይደለም። የኢሕአዴግ የጎሳ ስብስቦች እኩል መብትና ሥልጣን ቢኖራቸውም (ወያኔ የበላይ ባይሆንም) ውክልናቸው ለየጎሳዎቻቸው ስለሆነ ከአፍራሽ ፉክክር፤ ንትርክና ብጥብጥ ነጻ አይሆኑምi። እነሱ በተነታረኩ ቁጥር እንወክለዋለን የሚሉትን ጎሳ እያስነሱ (እያሳመጹ) ጎሳን ከጎሳ የሚያጋጩ ነው የሚሆኑት። ስለዚህ ከሀገር ዜግነት ዝቅ ብለው በሃይማኖትም ሆነ በጎሳ የሚደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች አፍራሽ ፉክክርን፤ ብጥብጥን፤ የርስ በርስ ጦርነትንና በመጨረሻም ውሎ አድሮ (በሃይማኖትና በጎሳ ላይ የተመሠረተ) ፍጅትን/እልቂትን (genocide) ከማስከተል በስተቀር ሌላ ፋይዳ የላቸውም። አማራውም ጎሰኛ የአማራ ፖለቲካ-ድርጅት ቢያቋቁም (በኔ እስተያየት) የሚፈጸምበትን በደልና ጥቃት አያስቀርለትም። ጎሰኝነት በተፈጥሮው ጠብ-አጫሪ እንጂ ሰላም ፈጣሪ አይደለም። ሀገር አፍራሽ እንጂ ሀገር ገምቢ አይደለም፤ ሁኖም አያውቅም።

ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ (የጽሑፋቸውን ርዕስ ቃል በቃል አላስታውሰውም) Ethnic cleansing? genocide? is looming in Ethiopia በሚል ርዕስ በኢቲዮሚዲያ ላይ አስነብበውን ነበር። በዚያ ጽሑፋቸው በጎሰኝነት የተነሳ በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን አስፈሪ (የእልቂት) ሁኔታ ነበር ያስተላለፉት። ይህንን ጽሑፍ ካስነበቡን በኋላ ብዙ ሳይቆዩ በኢሳት ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው “አማራው የራሱን የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም አለበት” እያሉ ሲቀሰቅሱና ሲሰብኩ አየኋቸው። ስለዚህ ሻለቃ ዳዊት በመሠረቱ በጎሳ ላይ

የተመሠረተ ፓርቲን እንደማይቃወሙ ለመረዳት ቻልኩ። በትግሬ ጎሳ ላይ የተመሠረተውንም የፖለቲካ ፓርቲ (ሕወአትን = ወያኔን) ጎሳዊ አመሠራረቱን በተመለከተ ተቃውሞ እንደሌላቸው ለመታዘብ ችያለሁ። ስለዚህ ጎሰኝነትንም አይቃወሙም፤ በጎሳ መደራጀትን እየሰበኩ ጎሰኝነትን ሊቃወሙ አይችሉምና። ያለዚያ (ድፍረት አይሁንብኝ እንጂ) ሻለቃ ዳዊት የጎሰኝነትን ጠንቅ በሚገባ አልተረዱትም ማለት ነው።

እስቲ አንባቢዎቼን ሦስት አራት ያህል ጥያቄዎች ልጠይቃችሁ።

  •   የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከትግሬዎች ጋር ለረዢም ጊዜ አብሮ መኖሩን (ከራሳቸው ከወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች አንደበት) እየሰማን ነው። ወያኔ የኢትዮጵያን በትረ-መንግሥት ከጨበጠ በኋላ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆችን የማንነት ጥያቄ ምን አስነሳው? በአንድ ሀገር ውስጥና ባንድ ሕገ- መንግሥት ጥላ ስር እስከሆንን ድረስ ከወሎ ተወስዶ ወደትግራይ የተጠቃለለው መሬት (ባእድ እጅ ውስጥ እስካልገባ ድረስ) ለምን ጥያቄ አስነሳ? ወልቃይትና ጠገዴስ በጎንደር ውስጥ ተከለለ፤ በትግራይ ውስጥ ተከለለ ምን እሚያመጣው ለውጥ ቢኖር ነው ይህን ያህል የሰው ሕይወት የሚገበርበት? ድሮ እኮ ሰፊ መሬት ከአርሲ ተወስዶ ወደ ሸዋ ተጠቃልሏል። በሌሎች ክፍላተ ሀገራትም (በተለያየ ጊዜ) ብዙ መሸጋሸጐች ተደርገዋል፤ ምንም የተፈጠረ ችግር አልነበረም።
  •   በሐረር፤ በአርሲ፤ በባሌ፤ በከፋ፤ በወለጋ፤በቤኒ-ሻንጉል፤ወ.ዘ.ተ. ለረዥም ዘመናት ካካባቢው ሕዝብ ጋር ተመሳስሎ በሰላም ይኖር የነበረው አማራ፤ ወያኔ ሥልጣን ሲይዝ ለምን ተሳደደ? ለምን ተጨፈጨፈ?
  •   ላያሌ ዘመናት ከአማራው ሕዝብ ጋር አብረው በሰላም የኖሩ (ማጋነን ባይሆንብኝ የDNA ምርመራ እንኳን ቢደረግ ከአማራው ልዩነት የሚገኝባቸው የማይመስሉ) ቅማንቶች የራሳችን ክልል ይሰጠን የሚል ጥያቄ አንስተው፤ ያነሱት ጥያቄ ለብዙ ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሁኗል። ለምን?
  •   በምሥራቃዊው የሀገራችን ክፍል የኢትዮጵያ ሶማሌዎች ወደ ኦሮሞው ክልል አልፈው በመግባታቸው በኦሮሞና በሶማሌዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ብዙ የሰው ሕይዎት መጥፋቱን በቅርብ ጊዜ በዜና ማሰራጫ ሰምተናል። አንድ የኦሮሞ ባለሥልጣን በሶማሌውና በኦሮሞው መካከል ያለውን ድምበር በሚገባ ልይተው/ከልለው የሁለቱን ጎሳዎች ችግር (ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ) እፈታዋለሁ ብለው ድሬደዋ ላይ (ትራምፕኛ) ቃል ገብተዋል። በምሥራቃዊ ኢትዮጵያ ያለ ሶማሌም ሆነ ኦሮሞ ዋና መተዳደሪያው ከብት እርባታ ነው። ያካባቢውን የግጦሽ መሬት ለዘመናት በጋራ ሲጠቀምበት ኑሯል። ያሁኑን የከረረ ግጭት ምን አመጣው? ምን አስነሳው? ድምበር መከለልስ ለምን አስፈለገ?ከላይ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች መልሱ አንድና አንድ ብቻ ነው። በትረ-መንግሥቱን የጨበጠው ወያኔ ጎሰኛ ስለሆነ ብቻ ነው። (የዲፕሎማሲ አጻጻፍ ስለማልችል በነፃ አእምሮዬ የመጣልኝን እቅጩን ልናገር።) ወያኔ ለትግሬ ጎሳ የቆመ በመሆኑ በየመስኩ፡(በመሬት አደላደሉ፤በኢኮኖሚው፤በማህበራዊ ኑሮ እድገቱ፤ በሕዝብ አገልግሎት አሰጣጡ፤ በስራ አመዳደቡ፤ ወ.ዘ.ተ.) ለቆመለት ጎሳ ያደላል። የጎሳው አባላት (ትግሬዎች) ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ ባይሆኑም፤ በወያኔ መንግሥት ከሌላው ኢትዮጵያዊ የበለጠ ቀዳሚ ተጠቃሚ መሆናቸው ሊካድ አይችልም። ትግሬዎችን ሁሉ ባያጠቃልልም ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ የበለጠ ለወያኔው መንግሥት ታማኝ፤ ደጋፊና ተቆርቋሪ የሆኑትም እነሱ ናቸው። “የወያኔን መንግሥት እኩይ አሠራር ትግሬዎች እማይቃወሙት ለምንድን ነው?” እያለ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሲጠይቅ ካንዳንድ ትግሬዎችና ሌሎች ፖለቲከኞችም የሚሰጠው መልስ “ትግራይ ውስጥ ያለው አፈና ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የላቀ በመሆኑ

ነው።” የሚል ነው። ሀቁ ግን ይህ አይደለም። ሀቁ ትግሬዎች ይህንን መንግሥት እሚቃወሙበት ምክንያት ስለሌለ ነው። እሚያጎርስን እጅ አይነክሱም።

ዋናው ነጥቤ ግን አንድ ሰው ወይም ቡድን ጎሰኛ ሁኖ ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ ባንድ ዓይን ሊያይ አይችልም። የጎሰኝነት ዋና መገለጫ ጠባዩ አድላዊነት/ወገንተኝነት መሆኑን ማሳየት ነው።

የኦሮሞ ጎሳ (የፖለቲካ) ድርጅት የተደራጀው ለኦሮሞው ሕዝብ ስለሆነ ለኦሮሞው ያደላል። ማድላትም አለበት። የአፋሩ (የፖለቲካ) ድርጅት የተደራጀው የአፋርን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ስለሆነ ለአፋር ሕዝብ ያደላል። የኦጋዴን ሶማሌ (የፖለቲካ) ድርጅትም፤ የደቡብ ሕዝቦች (የፖለቲካ) ድርጅትም፤ ሌላውም የጎሳ ድርጅት ሁሉ እንደዚሁ ለየራሱ የጎሳ አባል ያደላል። አማራውም በጎሳ ቢደራጅ ከሌሎቹ የጎሳ ድርጅቶች የተለየ ሊሆን አይችልም። የተደራጀው የአማራውን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ነውና ለአማራው ያደላል። ማነኛውም ጠባብ የጎሳ የፖለቲካ ድርጅት ለተደራጀለት ጎሳ የቆመ (የሚያደላ) ነው። ያ ካልሆነ በዚያ ጎሳ ስም መደራጀቱ ምን ፋይዳ ይኖረዋል? ያድላዊ ድርጅቶች ሀገር ደግሞ ዘላቂነት ሊኖራት አይችልም። እኔ እስከማውቀው ድረስ የጎሳም ሆነ የቀለም ልዩነቶችን አቻችለው የጋራ መንግሥት (consensus government) ከመሠረቱት ከስዊትዘርላንድና ከአሜሪካ በስተቀር፤ ጎሰኝነት (በዓለም ዙሪያ በተለይ በአፍሪካ) ለሀገር እድገት፤ ለኢኮኖሚ ግምባታ፤ ለሕዝብ አንድነት ጠንቅ ሁኖ የኖረ ነው።

ሀሳቡን በመደጋገም ጽሑፉን (የነገር) ድሪቶ አደረግሁት እንጂ፤ የጎሳ ድርጅት የሀገርን ደህንነትና ቀጣይነት አደጋ ላይ ከመጣልና (ሕዝብን ከሕዝብ በማራራቅና በማናቆር) የሕዝብን አንድነት ከመሸርሸር በስተቀር ሕዝብ ሲጠቅምም፤ አገር ሲገነባም አልታየም። እስካሁን ከተከሰተው ልምድ ተነስተን የጎሳ ድርጅት ለሀገር ግምባታ ወደፊትም እንደማይጠቅም በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። ጎሰኝነት ለሀገር ግምባታና ለሕዝብ ብልጽግና የበጀበት ሀገርና አጋጣሚ አለ የሚለኝ ካለ ለመማር ዝግጁ ነኝ።

አማራው በይፋ የሚታወቅበትን ሰፊ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦ፤ ወደኋላ አፈግፍጐ ጠባብ ጎሰኛ እንዲሆን ማድረግ ፈር መልቀቅ ነው። ለሀገርም ለጎሳም እማይጠቅም የተሳሳተ አቅጣጫ መያዝ ነው። የጎሳ ታማኝነትና የዜግነት (የኢትዮጵያዊነት) ታማኝነት አብረው አይሄዱም። ቀደም ብየ እንደጠቃቀስኩት የጎሳ ድርጅት ተጠሪነቱም ታማኝነቱም ለጎሳው ብቻ ነው። ይህ በጎሳ ለሚደራጅ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይሰራል (ለትግሬም፤ ለኦሮሞም፤ ለአማራም፤ ለጋምቤላ ሕዝብም፤ ለቤኒ ሻንጉልም፤ ለሱማሌም፤ ለሐመሩም፤ ለጉጂውም፤ ወ.ዘ.ተ.)። በዚህ ባሁኑ ጎሰኛ መንግሥት የምናየው (ወደ አንድ ጎሳ ብቻ ያደላ አሰራር) እሚያረጋግጥልን ይህንኑ ሀቅ ነው። ደጋገምኩት እንጂ ወደ አንድ ወገን ብቻ ወይም ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ የሚያጋድል አሰራር እድገትን የሚያኮስስ፤ ብጥብጥን የሚጋብዝ፤ ሰላምን የሚያደፈርስና የሀገርን ቀጣይነት አደጋ ላይ የሚጥል አፍራሽ አካሄድ ነው። ባሁኑ ጊዜ በጎሳ ቡድኖች የሚገዛውን የሀገራችን ሰላም መደፍረስም ሆነ የሀገራችን ቀጣይነት ቋፍ ላይ መሆን ሁላችንም (በትካዜ) እየተከታተልን ነው።

በቅርብ ጊዜ “የጽሐፊዎች ድምጽ? መድረክ?” በተሰኘ የኢትዮጵያ ሳቴላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ፕሮግራም ላይ ርዕዮት ዓለሙ ከአንድ ኢትዮጵያዊ (ስሙን ዘነጋሁት) ጋር ቃለ መጠይቅ ስታካሂድ በዩቲዩብ እመለከት ነበር። ቃለ-መጠይቅ የሚደረግለት ግለሰብ፡ “—– እኛ በውጭ ሀገር የተማርንና የፈረንጆቹን ባህል ለማየት እድል ያገኘን ምሁራን ተገናኝተን ስለሀገራችን ሁኔታ መወያየት አለመቻላችን ያሳፍራል።” ሲል ሰማሁት። እውነቱን ነው። በሀገር ጉዳይ ላይ ተሰባስቦ መመካከር/መወያየትና መስማማት አለመቻል ያሳፍራል። ብዙ

ተምሮና የውጪውን ዓለም አይቶ ጠባብ ጎሰኛ መሆንና የጎሳ ድርጅት አራማጅ መሆን ደግሞ ይበልጥ ያሳፍራል።

አንዳንድ የኦሮሞ (የፖለቲካ) ድርጅት መሪዎች ባለፉት 40 ዓመታት የተካሄደው የኦሮሞዎች ትግል ጥሩ ውጤት አስገኝቷል፤በቁቤ እየጻፍን ነው፤ በቋንቋችን ትምህርት እየሰጠን ነው፤የራሳችን (የኦሮሞን) ክልል ራሳችን እያስተዳደርን ነው፤ወ.ዘ.ተ. እያሉ ሲናገሩ እሰማቸዋለሁ። የቁቤ ጽሑፍ በላቲን ፊደል የሚጻፍ ጽሑፍ ነው። የኦሮሞ አይደለም። ብቸኛ የሆነውን አፍሪካዊ (የአማርኛን) ፊደል ትተው የላቲንን ፊደል ተጠቃሚ መሆናቸው የሕዝብን ልዩነት ያሰፋ (የሕዝብ ለሕዝብ መቀራረብን ያላላ) ነው። ተማሪዎችን በቋንቋቸው (በኦሮሚፋ) ማስተማር ጥሩ ቢሆንም፤ ተማሪዎቹ የሀገሪቱን ኦፊሺያል የሥራ ቋንቋ ባለመማራችው ያሁኖቹ ወጣት ኦሮሞዎች ኦሮሚፋ ከማይናገረው ኢትዮጵያዊ ጋር የሀሳብ ልውውጥ ማድረግ እማይችሉ ሁነዋል። ይህም በጠባብ ጎሰኝነት እይታ ድል (በጐ ክንዋኔ) ይምሰል እንጂ፤ የሕዝብን አንድነት በማጠናከር (ልዩነትን በማጥበብ) አንጻር ሲታይ ግን የግፊትን ኃይል (በታኝነትን) ያጠናከረና አሁንም እያጠናከረ ያለ ነው። በጎሳ ላይ የተመሠረተ ያስተዳደር ክልል ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ሆን ተብሎ የተፈጠረ የአንድነት ጠንቅ ነው። የወልቃይት ጠገዴን ጥያቄ፤ የአፋርን ሕዝብ ጥያቄ፤ ያዲስ አበባን ክልል (master plan) ጥያቄ፤ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ሶማሌዎችና ኦሮሞዎችን ችግር ያጤኗል። የጎሳ ክልልንና አከላለልን በተመለከተ “ራሱን የቻለ ክልል ይገባኛል” የሚል ጎሳ ብቅ ባለ ቁጥር የሚከሰት በከርሰ ምድር ውስጥ እንደ ታመቀ እሳተ ገሞራ ፈንድቶ የሚወጣበትን ቀን የሚጠብቅ ችግር ነው። ስለዚህ እነዚህ የኦሮሞ ልሂቃን የሕዝብን አንድነትና የሀገርን ቀጣይነት በተመለከተ (የወያኔን እድል ቢያገኙ) እንደ ወያኔ ላንድ ጐሳ (ለኦሮሞ) ብቻ የሚያደሉ፤ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በሁለተኛ ደረጃ እሚመለከቱ መሆናቸው እሚያጠያይቅ አይደለም።

ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ በአፄ ዮሐንስ፤ በአፄ ምኒልክና በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ሲካሄድ የኖረው ሀገር የመገንባትና የሕዝቦችን አንድነት አጠናክሮ የማስቀጠል ስራ ብዙ ያደከመ፤ ከፍተኛ መስዋዕትነትን ያስከፈለ ነው። የሀገር ግምባታው ሂደት ብዙ መራራ (ክፉ) ገጽታ ነበረው። ምሬቱም ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሁሉ አንድ ወጥ አልነበረም። ባንዳንድ አካባቢ ምሬቱ በጣም ይጐመዝዝ ይሆናል። በሌላው አካባቢ ደግሞ ከምሬቱ ይልቅ ጣፋጭነቱ ያመዝን ይሆናል። ነገር ግን ያገር ግምባታው ሂደት ከፋም በጀም አያቶቻችንና አባቶቻችን ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የምትጠቅም/የምትበጅ አንዲት ሀገር ጥለውልን አልፈዋል። ብዙ መስዋዕትነት ከፍለው ያስረከቡንን ሀገር በጥንቃቄ ይዘን አንድነታችን አጠንክረን በጋራ ልንጠቀምባት ይገባል።

የልሂቃኑ ጐራ ዓለም የሚራመድበትን ፈለግ እየተከተለ የሀገራችን ቀጣይነትና የሕዝቦቿን አንድነት የማጠናከር አቅጣጫ ቀያሽና ፋና ወጊ መሆን ሲገባው የጎሳዎችን ልዩነቶች እያጐላና እያሰፋ በታኝ (የግፊት ኃይል) መሆን አይገባውም። አርባ ዓመታት ያህል ወደኋላ ዞር ብለን ብንመለከት የምሁራኑ ጐራ ያበረከተው ነገር ቢኖር የሀገርን ቀጣይነት የሚፈታተንና የሕዝቦችን አንድነት የሚያላላ ፖለቲካ ማቀንቀን ነው። መሆን አይገባውም።

የሀገራችንን ቀጣይነት፤ የሕዝቦቻችን አንድነት፤ እድገትና ብልጽግና ዕውን የሚሆነው ከጐሳ አመለካከት አልፈው/ወጥተው፤ ሲሆን በአሕጉር ደረጃ ያለዚያ ደግሞ በሀገር ደረጃ እሚያስቡ በሳል ኢትዮጵያዊያን ተሰባስበው በሚመሠርቱት (በሚመሠርቷቸው) (የፖለቲካ) ድርጅት(ቶች) ነው። ድጋፍ መስጠትም የሚገባን ለዚህ ዓይነቶቹ ድርጅቶች ነው።

ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ጋር ሲነጻጸሩ በጣም ጥቂት ከሆኑ ተጠቃሚዎች በስተቀር፤ ባሁኑ ጊዜ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በሚደርስበት በደል እየቆዘመ አንገቱን ደፍቶ የሚኖር ስለሆነ በኢትዮጵያዊነት ተደራጅቶ አመርቂ ለውጥ ለማምጣት አመቺ ሁኔታ አለ።

የአማራው ልሂቃንም በኢትዮጵያዊነታችን ጥብቅ እምነት አለን የሚሉ ከሆነ፤(ወደጎሳ ከረጢት ለመግባት መደራጀቱን ትተው) ከጎሳ አመለካከት ነፃ ከወጡ በሳል ኦሮሞዎች፤ ትግሬዎች፤ ጉራጌዎች፤ ወላሞዎች፤ ኑኤሮች፤ አፋሮች፤ ሲዳማዎች፤ ሐመሮች፤ ወ.ዘ.ተ. ጋር አብረው ተሰልፈው ለመደራጀት ዝግጁ መሆን ይገባቸዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብም የሚፈልገው በሰላም ባንድነት ተከባብሮ ሠርቶ፤ ፍትሕ አግኝቶ መኖርን እንጂ በጎሳ መከፋፈልን አይደለም።

በጎሰኝነት ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ድርጅት ሲቋቋም የጋምቤላው ሕዝብ ጉዳይ የሌላውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጉዳይ ይሆናል። የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ የመላ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ይሆናል። የኦሮሞ ጉዳይ የሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጉዳይ ይሆናል። “አፍንጫ ሲመታ ዐይን ያለቅሳል” እንደሚባልው፤ የጎሳን ኮፈን አውልቀን ስንጥል አንዱ ኢትዮጵያዊ ሲበደል ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይሰማዋል፤ ይጮኻል፤ ሌላ ሌላ እርምጃም ይወስዳል። የሕዝቦች አንድነትና የሀገር ቀጣይነትም የሚረጋገጠው በዚህ መልክ መጓዝ ስንችል ነው።

i ባሁኑ የኢትዮጵያ መንግሥት እውነተኛው ገዢ የትግሬ ጎሰኛ ፓርቲ ብቻ ነው። ሌሎቹ ለሽፋን የተቀመጡና ይወክሉታል የተባለው የራሳቸው ጎሳም ስለማይቀበላቸው እንደ እውነተኛ የጎሳ ፓርቲዎች አድርጌ አልቆጥራቸውም።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s