በሴረኞች የዐማራ ሕዝብ ተጋድሎ አይቀለበስም! – ሙሉቀን ተስፋው

ከጥር 29 ቀን 2009 ዓ/ም በሰሜን ጎንደር በምዕራብ በለሳ የሚኖሩ ዐማሮች በወያኔ መከላከያ ሠራዊት ቤታቸውና ንብረታቸው እየወደመ ይገኛል፤ የሚያሳዝነው ደግሞ ሌላው ወገናቸው ችግራቸው በሚገባ ያልታወቀ መሆኑ ነው፡፡

ከዚህ የከፋም ችግር አለ፤ የዐማራ ተጋድሎ አስተባባሪ የጎበዝ አለቆች በድብቅ ስብሰባ መጥራታቸውን ወያኔን እንቃወማለን በሚሉ ነገር ግን ደግሞ የዐማራ ሕዝብን ዐማራዊ ተጋድሎ ለቡድናቸው ወይም ለድርጅታቸው ሕልውና አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራሉ በሚባሉ ወገኖች ጠቋሚነት መሆኑ ነው፡፡

ከዐማራ ተጋድሎ አስተባባሪ የጎበዝ አለቆች ጋር በመተባበር አንድ ስብሰባ እንዲጠራ ይደረጋል፤ ብዙዎቹ የጎበዝ አለቆች ተጠራጥረው ሳይሔዱ ቀሩ፡፡ ሆኖም ሁሉም ይመጣሉ በተባለበት ሰዐት የወያኔ ወታደሮች እስከአፍንጫቸው ታጥቀው በለሳ መሸጉ፡፡ ሁሉንም ለማስቀረት ቢሞከርም በዐማራ ታጋዮች ላይ ምንም ዓይነት የሰው ሕይወት ሳይጠፋ በጀግንነትና በወኔ የወያኔን አጥር ሰብረው ሊወጡ ችለዋል፡፡ ሆኖም ከመካከል የነበረ አንድ ሰው ጠፍቷል ተብሏል፡፡

የሚያሳዝነው ግን ከቅዳሜ ዕለት ጀምሮ የበለሳ ገበሬዎች ቤትና ንብረት በግፍ እየወደመ ነው፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ መሠረት ከሃያ የማያንሱ ቤቶች በኮዛ አቦ አካባቢ በከባድ መሣሪያ ወድሟል፡፡ ከመቶ ያላነሱ ቤተሰቦችም ያለ መጠለያ ተበትነዋል፡፡ ምን ዓይነት ችግር ውስጥ እንዳሉና እንደሰነበቱ ሌላው ዐማራም አላወቀውም ገና፡፡
የዐማራ ተጋድሎን ለማኮላሸት ለወያኔ መረጃ በመስጠት የተባበሩ አካላት በዐማራነት መደራጀትን እየኮነኑ እንደገና እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ስንሰማ ደግሞ የበለጠ አዝነናል፡፡ ይህ ጉዳይ በሚገባ እየተጣራ በመሆኑ የዐማራ ተጋድሎ አስተባባሪ የጎበዝ አለቆች ትምህርት የሚወስዱበት አጋጣሚ ይሆናል፡፡

እንደማጠቃለያ ማንም ሰው (ቡድን) የፈለገውን ርዕዮተ ዓለምና አደረጃጀት ይዞ መጓዝ ይችላል፤ ሆኖም በዐማራ ሕዝብ ላይ የሚሸርቡትን ሴራ ማቆም አስፈለጊም ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው፡፡ የዐማራ ሕዝብ ትግል ላይቀለበስ ተቀጣጥሏል፡፡


የዐማራ ሕዝብ ትግል ያሸንፋል

 

Leave a comment