ዬኢትዮዽያ ቀን – ከሥርጉተ ሥላሴ

ከሥርጉተ – ሥላሴ  13.02.2017 (ዙሪክ – ሲዊዘርላንድ)

„ፍርድና ልቅሶ በሚደረግበት ቀን፥ እግዚአብሄር በሚመጣበት ቀንና ቊርጥ ፍርድ በሚፈረድበት ቀን ፥የእግዚአብሄርን ህግ የዘነጉ ሰዎች በሚቆሙበት ቦታ ይቆማሉ።“
(መጽሐፈ መቃብያን ካልዕ ምዕራፍ ፲፭ ቁጥር ፫ )

… ፊቱ ውሃ ሲሄድበት ዬከረመ ይመስላል። የዕንባው ወራጅ ቁልል ኮረብታን ገንብቷል። ብልዘቱ እንደ መልካም ነገር ከሩቅ ያሳጣል። ክርክም ባልተሠራለት የአንገቱ ወለል ላይ ውስጡን እያነቃና … እያደራጀ በሰቀ-ደረቱ ላይ ለሽ ያለው ዬእንባ ኖራ፥ ዬመከፋት ቀለም ቀቢነቱ በቡዙ ውስጡን በቅኔ ቅንነት ይተረጉማል። የወጣት ሰአሊ ነው። የብራናው ሰሌዳም ገፁ፥ ሜሮኑም የዐይኑ ጨው ነው። ከቃጠሎውም ዬተነሳ የቁስለቱ በስጋት የተገነዘ ፍዳ ደረቱ ላይ ዬእሳተ ጎመራ ቀለ ሰርቶ፥ ጎጆውን በእልህና ወኔ ቀልሷል። ውስጡ በመከራና በአሳር ፍሞ አክስሎታል። ቀረብ ብሎ ከውስጥነት ካላዩት ተክለ ቁመናውን ሆነ የገጹን ላሂ በውስጥ ቃጠሎው ምሬት የተነሳ እሱ መሆኑን መለየት ፈጽሞ አይቻልም።

ከእማ ዬተጠጋ ቀን ሁልጊዜም እንዳለቀሰ ነው። ዕጣው ከእርሷ ጋር እንደ ጠነዘለ። ያልፍልኛል ብላ ባለመችበት ሰዓት፣ ወቅትና ዘመን ሁሉ ለቅሶ – ይደገስላታል። ለምሾዋ ማጫ – ይመታባታል። እሷ ማዲያት – በማድያት መሆኗ ውስጧን ሲሟጥጠው ዋይታ ይለፍ ተሰጥቶት ይታወጅባታል። ቀን ዬቀናቱን ታጣፊ አልጋነት ልተወው ቢል እንኳን፥ እረፍት ሰጪ ከቶ ዬላትም። ውጋቷ እንዲያጥድፋት ይታከል፥ ይታከል፥ እያለ … ተጠቋቋሚው ሁሉ ያለባት የፋሽስት አሳር ላይበቃ፤ ሌላውም ፋታ አልቦሽ በተደራቢነት ይወግራታል – ይሰልቃታል፤ ያልፍልኛል ስትል ይቀማታል፥ አረመኔ ሲያሯሩጣት መጠጊያ ስትሻ ዋሻ ያለችውም ዘንበል ቀና እያለ – ያለዛታል። ሸማዋ እንኳን ተቀናቃኝን ደጅ እንዲጠና ዱብ … ዱብ እዬተባለለት ነው … ህም!

እምም! ደግሞ ዬሚገርመው እሷው ለቻለችው፥ እሷው ለተሸከመችው፤ እሷው ለተጫነችው „አታልቅሺ ይሏታል“ያልተያዘ ግልግል ያውቃል“  እንደሚባለው። ስለምን አታነባ? አርማ – ኮትኩታ – ዬአዘራችው ቡቃያ ዬተባይ ቀለብ ሲሆን፥ እኮ! ስለምን እንባዋን አትለቀው? ዬማግስት መጋኛ ሲገን፤ ግን እኮ! ስለምን እሪአትል? እሸቷ ሲነቃቀል፥ እኮ! ስለምን አታምርር? እንዲህ ጨለማ ሲውጣት፤ እኮ! ስለምን – ዋይተኛ አትሁን? ህሊናዋ ዬፍም ረድፈኛ ሲሆን፥ እኮ! ስለምን ኡኡ አትል? ተስፋዋ ዬምድጃ፤ የረመጥ ቤተኛ ሲሆን ሲያንስ …. ነዲዱ ጎጆዋን አመድ ዱቂት ሲያደርገው፤ በጢስ ታፍና ስታምጥ፤ ልጇቿ በታቀደ ቃጠሎ እንደ በግ፥ እንደ ሰንጋ ሥጋ የእሳት መፈተኛ ሲሆኑ ጨርቋን ጥላ አለማበዷም እሷ ሆና ነው። የፈረደባት፤ ጠላቶቿን ጡት አጥብታ አሳድጋ በነጋ በጠባ ሲኮንኗት፤ ሲያጣጥሏት ልጠው ሲጠብሷት ይውላሉ  – ያድራሉ፤ ይሄው ያምሷታል፥ ይቆሏታል ይፈጯታል። እየጠሏት – ይግጧታል፤ እየናቋት – ቁርጥም አድርገው ይበሏታል፤ አናውቅሽም ተብላ ይሞሸሩባታል። የወላድ መካን ዬሆነች – ባተሌ ። እያገላበጡ ሀገር በቀል ፋሽስቶች – አነደዷት። ሲዘነጥሏት ለአፋቸው ሞግድ አልሠራለትም። የህዳር ዝናቦች። እያዬ እዬሰማ እግዜሩም ዝም አለ።

„ዬደላው“ አሉ። ሲመሽም ሲነገም ለባቴሌዋ ያው ነው፤ ዜሮ ሲደመር ዜሮ ያው ዜሮ። ከዜሮ ላይም ዜሮ ሲቀነስ ያው ዜሮ። ዜሮ ሲባዛ በዜሮም ያው አምሳያው ነው። አሽሙሩ መረረኝ ስትል መስቃው፥ መስቃው ወቃኝ ስትል ውርዴቱ፤ ውርዴቱ ተከመረብኝ ስትል ግልምጫና ልግጫው ፈረደባት በእፋኝት የድንጋይ ሽበት፤ እሷ በመኖሯ ፈጥራ „ምጥ ለእናቷ“ ሆኖ ፈጠርንሽ ይሏታል። ጠላቷን መክታ ለወግ ለማዕረግ ስላበቃች፤ ጠላትሽን ቅስሙን ሰብረሽ ማባረርሽ እንግዳ ወዳጅ አለመሆንሽን ተፈላስመንበታል ይሏታል፤ እንቁላል ተሽጦ በተሸመነው የሐረግ ዝርግ። መንኰራኲራቸው ባነዳነት፤ ትዕቢተኝነታቸው ልሳነ ፍግ ነውና።

… ያልፋል ስትል እንደ መጫኛ ዬሚያፋ፤ ይሆናል ስትል እንደ ህልም ብን … ትን … ትርትር ዬሚል፤ ደረስኩ ስትል እንደ ጉም ሽንት ዬኋልዮሽ – ዬሚያሰኘው፤ ስለቱ መረረኝ ስትል – ገጀሞው፤ ገጀሞውም ፋታ ነሳኝ ስትል – መዶሻው፤ መዶሻውን እህል ውሃውን ያሳጥርልኝ ብላ ስታጣውር እሳት ዬላሰ – ፋስ፤ ፋሱን ተገላገልኩ ስትል – ባሩድ፤ ባሩዱ አላተረፈኝም ብላ ልታመልጥ ጉሩቦ ከጉሩቦ ከፈርኦን ጋር ስትገጥም በመርዝ — ህም! እና እሷ ያላለቀሰች ማን ያልቅስ? እሷ ያላማጠች ማን ያምጥ? እሷ ማቅ ያለበሰች ማን ይልበስ? እሷ  ለፈጣሪዋ በእንባ ያላመለከተች ማን? እኮ ማን? ቀኗ እራሱ ስቅስቅ ብሎ አብሯት ከውስጧ መከፋት ጋር ይታደማል። በምህላ በበገና፤ በሱባኤ በክራር ይታደማል። ከስግድቱ ብዛት ጉልበቱ ሌላ ሸከር ያለ ተደራቢ ሞረድ ቆዳ አብቅሏል።

እሷማ ሁልጊዜም ዒላማ ናት! በቅላ እንዳትታይ ወፍበላ ዬሰፈረባት፤ ዬተስፋ ቀን ጠኔ ዬሚያጥመነምናት፤ ስለምጧ ቀን ተንበርክካ ዬምትማስን  – አሳረኛ። ሀገር በቀል ሪህ መቅኖዋን ምጥጥ አድርጎ ያለባት፥ በደረቁ ዬላጫት፤ በአለሎ – ዬሚደቁሳት፤ በመዳመጫ ያሻውን ያህል ዬሚድጣት ከቀኗ ጋር ያሻታል – በሽታሽቶ። ተወልጄ ነኝ ይላታል። ድንቄም¡ አሰር ውሃ፤

በ20 ዓመት ቀና ዬምትል ባተሌ ከኖረች ዬእሷማ ስፍር ቁጥር በሌለው መጋኛ – ትጣደፋለች። እንደ አንስት በባለደምነት ዬተፈረጀባት ሐገር እንደ ኢትዮዽያ እንደ ሌለ ሰማዕቱ ዬኢትዮዽያ ቀን እንባውን ተግ አድርጎ፤ ዘለግ ባለ ቃና ዬፍዳዋን መጫኛነት ይመሰክርላታል።

እሱ እቴ ዬዋዛ! ዬኢትዮዽያ ቀን ዕውነት እኮ ነው ትንፋሹ። አቅም ያላቸው ሴቶች እንደ ባለደም መታዬታቸው አልበቃ ብሉ ዬመከራ ሙከራ ቤት መሆናቸው ዕንባማው ዬኢትዮዽያ ቀን ከሁሉ በላይ – ያብሰለስለዋል። ሁሉ እያላቸው መተንፈሻቸው ታስሮ መረማመጃ መሆኑ ውስጡን – ይፈጀዋል።

እሱ ግን ዕንባማው የኢትዮጵያ ቀን እግዚአብሄር ዬተመሰገነ ይሁን እንጂ፤ ቅርባቸው ለመሆን – ቆርጧል። እነ አቤቶ አውሎውን ካላኩበት። ለነገሩ ዬእነሱ ነገር ምን ገና „አቡጊዳ ሳይደርሱ“  ይለቅማል በወጥመድ – አቤቶ ፈርኦናዊው ማኒፌስቶ፤ እቴ አምጡልኝማ ዬዛሬውን ዘመን ዬአርበኝነት ውሎ፤ ማነ ነው ዬሚሉት አያ? እ … መጣልኝ ሴት ብሎገሪስት፤ ሴት አክቲቢስት፥ አዎን እነሱንም ሳጥናኤል ልቅምቅም አድርጎ  – ከርቸሌ።

ህም፤ አንስት ያልተፈራ ማን ይፈራ? መቼስ አንስት ብቅ ስትል ዬሳጥናኤል ሰይፋ ጨንገር ተነስቶበት ልቡ ጥፍት እስኪል ድረስ ያስነካዋል። እንቱን -ን፤ ዛሩን ከሰጠሰጠ በኋላ፤ ያቺ በ20 ይሁን በ30 ዓመት ብቅ ዬምትል ዬምንቴ ትሁን ዬትዋቡ፤ ዬጣይቱ ትሁን ዬዘውዲቱ ብቻ ምንአለፋችሁ መረብ ዘርግቶ አደኑን ያጣድፈዋል። መቼስ ሴት ቀና ካለች ያክለፈልፈዋል – ስላችሁ። ይጐማጃል – ቅስሟን እንክትክት ለማደረግ። ስጋ ያዬ ጅብ ነው ዬሚሆነው። ጉምጅታም – አራዊት

ወይ ፍዳ! ተሰጦዬን በብራና ላወራርድ ዬሚል ዬብዕር ጠብታን ብራና ላይ መሰስ ሲያደርገው – ቀለም ፈራሹ ዬፈርኦን ሰይፌ ጨንገር ክላሽን ያህል ፈርቶ ከርሸሌ ቀኑ ይሆናል፤ እስቲ ባለችኝ እንኮን ከእንባሽ ጎን ልቁም፤ አጋርሽም ልሁን፤ ባይሆን ዛሬ ዬዓንችው ዓይን ፍሰት ተግ ይበልልሽ፤ ተረኛ እኔ ልሁን ብሎ ሲሰለፍ „መሀይም ብሎ ፖለቲከኛ¡ መሀይም ብሎ ዬሐገር ተቆርቋሪ¡ ተብሎ ቀን ያሰለፈችው ትንታግ ከማህበረ ዬነፃነት አርበኝነት በፎርፌ፤ እሺ! እነኛ ያልተማሩ ከተባሉ፤ በቀለም በሰል ካሉት ሲባል ደግሞ ዬዓላማ ማህበራቸውን ዬቀራኒዎ ቀን። ዬኢትዮዽያ ቀን ውጋቱ ብዙ ነው። ለዚህ ነው ዬእማምዬ ዝናቧ እራሱ ዕንባ ዬሆነው። መሬቷም ልማቱ በዕንባ መስኖ። ልማታዊ – ቅብጥርሶ – ምንትሶ – ገለመሌ – ወለሜሌ የሚሉት እኮ ወስፋት ታስሮ ለ“ቁምራ“ አንጀት ለማትደርሰው የቆረባ ማስታገሻ ቁራሽ እኮ ነው። ለእሷም ሰዓት እላፊ ታውጆባታል አሉ። ምን መሽቶ ሲቲነጋ ዓዋጅ ነው ሲረቅ ውሎ የሚታድረው። አንቀጡ ቢዘረጋጋ አምላካችሁ አለ ምድሪቱን ባለበሳት።

አዎና የምድር ስጋጃ አንቀጥ በሰለጠነው የጫካ ተመክሮ። የአንቀጥ ገመድ፤ የአንቀጥ መረብ፤ የአንቀጥ ትሬኮላታ ኧረ ምኑ ተጨውቶ፤ የእነ እንቶፎቶ ስልቻ የቃሬዛ ስንብቻ፤  የአንቀጥ ካቴና። ትንፋሻቸው መስንበቻዋ እኮ የነጋሪት ጋዜጣ – በጋሬጣ።

ስደት እያገላበጠ እንደ ዶሮቄት ዬሚቆላው ዬኢትዮዽያ ቀን ተዚህም ዬት ሲቀርላት፤ ሥደቱ ቋያ፤ ዬፈርዖን ጀሌ ቋያ፤ ነገ ስለአንቺ ቀን ቆርጠናል፤ ታጥቀናል ዬሚለውም ባለችው መብት ለሌላው በገደብ፤ በደንበር፤ በወገን፤ በአድሎ፤ በአጋ፤ በደረጃ፤ በከፍና ዝቅ ተሰቅዞ ስደቱ ላይበቃው በግራ ቀኝ በውከባ ወበቅ ሲገረፍ … ዬኢትዮዽያ ቀን ዓይኑን ብቻ ሳይሆን አብራክንም ያዝና በላይም በታችም በምጥ ዬታጀበ ዕንባውን በጣምራ ሲለቀው ላዬ ምናኔ በስንት ጣሙ ያሰኛል። ለዚህ እኮነው የቅኔው ግሥ ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን የወንድ ልጅ ዕንባው ሆድነቱን የተቃኘው።

አልቃሻው ዬኢትዮዽያ ቀን መፍትሄ ዬሚባል መላዕክን ይመኛል፥ ይናፍቃል፥ ሽው ይለዋል፥ ይርበዋል ግን ይቻለው ይሆን? ህልም ፈቺ ከተገኘ? ውሸታም ያልሆነ ወይንም ያልሆነች። አደባባይን ውስጡ ያደረገ ወይንም ያደረገች ፥ ዬጓሮ ጉዞን ዬተጸዬፈ ወይንም የተጠዬፈች። ዕውን ተናፋቂው ዴሞክራሲ ጋር መምከር ዬቻለ ወይንም የቻለች።

ጨለማን ገፎ በጠኃይ የሚያንቆጠቁጥ፤ ብሩክ፤ ወይንም ደግሞ ወዘተረፈውን ካቴና እንኩትኩቱን ያወጣች ብርክት ምህረትን ከሸበላው ብሩህ ተስፋ ጋር ታኮመኩሙን ይሆን? … እስቲ ይርዳቸው አንድዬ እንደ – ዬመንገዳቸው ጠላታቸውን ሰብሮ የልብ – ለልብ የሚያደርስ ቀን ያምጣ። ከእቱ ከእናቱ የተጠጋውም ዓጤው ቀኖ ከዕንባው ጋር ፍቺ የሚመጣለት ንዑድ መላዕክ ይዘዝለት። አሜን!

መከራን የሚረታ፥ ፍቅራዊነትን የሚያንሰራፋ፥ በቀልን በምህረት አቅም ድል የሚያደርግ፥ የዕውነተኛ የተስፋ ቀን ፈጣሪ ይስጠን። አሜን!

ለአላዛሯ ኢትዮዽያ አዲስ ቀን ፈጣሪ አምላካችን መርቆ ይስጥልን። አሜን!

መሸቢያ ጊዜ፥ እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s