ትንሽ ስለብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ – ከኮ/ል አለበል አማረ

 

በብ/ጀኔራል ተፈራ ማሞ ግለ ታሪክ ብዙ የሚነገርለት ብርቱና ጀግና የጦር ባለሙያ ነው። ብ/ጀኔራል ተፈራ ማሞን በቅርብ የማውቀውን ያክል ስለሱ ማውሳት ደጋግሜ ባስብም ተፈላጊ መረጃወችን ለማግኘት ባለመቻሌ ዘገየሁ፣ አሁን ግን ገላጭ መረጃወችን በቅርብ ለማግኘት እድሉ ያላቸውን ሰወች በማግኘቴ ስለ ጀግናችን ማንነትና በጀ/ል ሳሞራ የኑስንና ህወሃት የሚመራው ሰራዊት ንቅዘትና ብልግናን ለማሳየት የአንድን የትግሬ የጦር አዛዝ ጀኔራልን ድርጊት በማሳያነት በመውሰድ እንደሚከተለው አቅርቤዋለው።

አንባቢወቻችንን ላለማሰላቸት ጹሁፉን በሁለት ተከታታይ ክፍል አቅርበነዋል። መልካም ንባብ።

ብ/ጀ ተፈራ ማሞ ማነው?

ተፈራ ማሞ የተወለደው በላስታ እውራጃ ቡግና ወረዳ ነው። ተፈራ የድሮውን ኢህዴን ያሁኑን ብአዴን የተቀላቀለው 1976 ዓ.ም ነበር። ትግሉን ሲቀላቀል እድሜው በግምት በአስራዎቹ መጨረሻ ነበር። በወቅቱ ለምልምል ታጋዬች የሚሰጠውን መሰረታዊ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስልጠና የወሰደው ምእራብ ትግራይና ሰሜን ጎንደር ( ወልቃይት) በሚዋሰኑበት ተከዜ ወንዝ ነበር። የሰለጠነበት ጊዜ ከሃምሌ 1976 እስከ ህዳር 1977 ባሉት ወራት ነበር።

ተፈራ የአርሶ አደር ልጅ ቢሆንም በስልጠናው ሂደት የነበረው ተሳትፎ እጅግ ንቁ ነበር። ፊደል ቆጥረናል ብለው ሙህራዊ ትምክህት ያስቸግራቸው የነበሩትን በብዙ መንገድ የሚያስከነዳ ነበር። ያን ግዜ ጊዜ 6ኛ ክፍል ያጠናቀቀም ሙህራዊ ትምክህት አለብኝ እያለ ግለሂስ ያደርግ ነበር።
ዘመኑ የደርግ ኢሰፓአኮ የገነነበት ስለነበር በእለቱ የስልጠና መግቢያና ማጠቃለያ ላይ ” ኢሰፓአኮ ቀዳዳ ባኮ፣ ትግላችን ረጅምና መራራ ነው ድል ማድረጋችን የማይቀር ነው”የሚሉ መፈክሮችን በማስተጋባት የሚቀድመው ማንም አልነበረም።

ስልጠናው እንደጠናቀቀ የተመደበው ወደ ተዋጊ ሰራዊቱ ስለነበር ከወልቃይት ተነስቶ ወደ ወሎ ግንባር (ዋግ) ተነቃነቀ። በ1977 በነበረው ድርቅና ርሃብ፣ በደርግ ሰራዊት ተደጋጋሚ ወረራ ብዙዎች ተስፋ ቆርጠው ትግሉን እየጣሉ ሲሄዱ አዲስ ታጋይነቱ ሳይበግረው በአላማው ጸንቶ ያን ክፉ ጊዜ አለፈ።
ትዝ ይለኛል ህዳር 1977 የተለያየን ታህሳስ 1980 ዓ.ም በለሳና ዋግን እያዋሰነ በሚያልፈው ተከዜ ወንዝ ላይ ዳግም ተገናኘን። በወቅቱ እሱ ተመድቦ ይሰራ የነበረው ኢህዴን ውስጥ በሁሉም መመዘኛ ምርጥ የሆኑ ታጋዮች መገኛ በነበረችው ኮማንዶ ሻምበል ውስጥ ነበር። በወቅቱ ሰራዊቱ ከየነበረበት የስምሪት ግንባሮች ተከዜና አሪ ወንዞች ወደ ሚገናኙበት ቦታ የተሰባሰበው ለወራት የተሰጠውን የፖለቲካ ስልጠና ለመውሰድ ነበር።

ስልጠናው እንደተጠናቀቀም ኮረምና ማይጨው የነበረውን የደርግ ሰራዊት ለማጥቃት ተንቀሳቅሰን ከህወሃት ሰራዊት ጋር በመሆን ሁለቱንም ከተሞች ከግማሽ ቀን ባነሰ ውጊያ ተቆጣጠርን። ጊዜው ግንቦት 1980 ነበር። ማይጨው መሽጎ የነበረውን የደርግ ሰራዊት ለመደምሰስ በተደረገው ዉጊያ ግን አንድ ቁልፍ ወታደራዊ መሬት ላይ መሽጎ የነበረውን የደርግ ሰራዊት አጥቅቶ ቦታውን መቆጣጠር ከባድ ፈተና ሆነ።

ይህን ቁልፍ ቦታ የመቆጣጠር ግዳጅ የተሰጠው ለህወሃት ሰራዊት ነበር። ነገር ግን የህወሃት ሰራዊት ቦታውን መቆጣጠር አልተቻለውም። አጁሃ በሎ እየተባለ ለስአታት ቢሞከርም ከመንደፋደፍ በቀር ምንም ዉጤት አልተገኘም። በዚህ ጊዜ ነበር እነ ተፈራ ማሞ ያሉባት የኢህዴን ኮማንዶ ሻምበል ግዳጁን ተቀብላ እንድታጠቃ የታዘዘችው።

ድሮም ጀምሮ በኢህዴንና በህወሃት ሰራዊቶች መካከል ሃይለኛ ፉክክር ነበርና ግዳጁን በደስታ ተቀብላ ማጥቃቱን ጀመረች። ለማመን በሚያስቸግር ጀግንነትና ፍጥነት በቦታው የነበረውን የደርግ ወታደር ጠራርጋ ቁልፍ ወታደራዊ ቦታውን ተቆጣጠረች። የህወሃት ሰራዊት በብዛት እንጅ በጀግንነት አይበልጠንም በሚል ውስጥ ውስጡን ይብላላ የነበረው ስሜት በተግባር ታየ ተብሎም ተነገረበት።
ተፈራ ማሞ ከተራ ተዋጊነት ጀምሮ ቲም አዛዥ፣ የመቶ አዛዥ፣ የሻምበል አዛዥ፣ የሬጅሜንት ምክትልና አዛዥ፣ የክፍለጦር ምክትል እያለ ቀጥሎ ደርግ ከመውደቁ በፊት የክፍለ ጦር አዛዥ መሆን ቻለ። በሁሉም የሃላፊነት ደረጃዎች የተሰጠውን ሃላፊነት በብቃትና በጀግንነት እየተወጣ የደርግ መንግስት ወደቀ።

በሽግግር መንግስቱ ዘመንም መጀመሪያ የቴዎድሮስ ክ/ጦር ቀጥሎም ኢህአፓን ለማጥፋት ከኢህዴንና ህወሃት ተዉጣጥቶ የተደራጀው ፓራ ኮማንዶ ክ/ጦር አዛዥ ሆኖ ይሰራ ነበር። ሃገር አቀፍ የመከላከያ ሰራዊት ታህሳስ 1987 ሲደራጅም የ21ኛ ክ/ጦር አዛዥ በመሆን ለአጭር ጊዜ ሰርቱዋል።

በወቅቱ መከላከያ በከፈተው አዳሪ ት/ቤት እየተማረ 9ኛ ደርሶ እያለ ነበር የኤርትራ ወረራ መርዶ የተሰማው። ሁሉም ነገር ወደ ሰሜን ግንባር ሲባል በንፋስ ፍጥነት ወደ ባድመ ግንባር ዘመተ። በወቅቱ ወገን የነበረው የክ/ጦር ብዛት ሰባት ብቻ ስለነበር አራት ተጨማሪ ክ/ጦሮች እንዲደራጁ ሲወሰን እሱም 33ኛ (አባይ) የተባለ ክ/ጦርን እንዲያደራጅ ግዳጅ ተሰጠው።
ጊዜው እናት አገር ልትወረን ቀርቶ ልታስበን በማተገባ ታሪክ የለሽ ኤርትራ የተደፈረችበት ነበርና ሌት ተቀን ለፍቶ በብቃት መዋጋት የሚችል ክ/ጦር በወራት ውስጥ አደረሰ። የማይተዋወቁ የበታች አመራሮችን፣ ተዋጊ ወታደሮችንና የስታፍ አካላትን አሰጣጥሞ አንደ አንድ ሰው ማሰብና መንቀሳቀስ እንዲችሉ ለማድረግ የሚታለፈው ፈተና እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም።
ምንም ይክበድ አገር ነውና አደራጅቶ፣ አግባብቶ፣ አዋህዶ፣ አሰልጥኖ፣ ገንብቶ፣ ሙሉ የውጊያ ቁመና ፈጥሮ በባድመ ግንባር በተደረገው የጽሃይ ግባት ዘመቻና በተከታታይ በተካሄዱ ወሳኝ ዉጊያዎች በሙሉ ክ/ጦሩን እያዋጋ የአዛዥነት ሃላፊነቱን በብቃት ተወጥቱዋል። የሚገርመው ነገር በዚህ ውጥረት ውስጥ ሆኖ ማንም ባላደረገው ሁኔታ ትምህርቱን በርቀት ይከታተል የነበረ መሆኑ ነው።
ከ1994 ጀምሮ ደግሞ የ108ኛ ኮር ምክትል ኣዛዥ፣ ከታህሳስ 1997 ጀምሮ የሰሜን ዕዝ ኦፕሬሽናል ምክትል አዛዥ፣ ከግንቦት 2000 ጀምሮም በመከላከያ ዘመቻ ዋና መምሪያ የእቅድ ዝግጅት መምሪያ ሃላፊ ሆኖ እስከታሰረበት እለት ድረስ ይሰራ ነበር።

በጥቅሉ ተፈራ ከታገለበት እለት ጀምሮ ለእስር እስኪዳረግ ድረስ ህይወቱ ከተዋጊነትና አዋጊነት ጋር የተያያዘ ነበር።
ወደ መከላከያ ስታፍ የተዛወረው የቅንጅት ፖለቲካ በፈጠረው ቀውስ የተነሳ በሰራዊቱ የማጥራት ግምግማ ሲካሄድ ቅንጅት ነህ ተብሎ ክፉኛ ተገምግሞ ስለነበር ለክትትል እንዲያመች ተብሎ ነው ወደ መከላከያ ዘመቻ ዋና መምሪያ የተመደበው።

ተፈራ ከአቻዎቹም ሆነ ከአለቆቹ የሚለይበት አንዱ ነጥብ ትምህርት ወዳድ መሆኑ ነበር። ሁሌም አጀንዳው መማር መማር የሚል ነበር። ማንም ባላደረገው ሁኔታ በዚያ አስቸጋሪ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ምሽግ ውስጥ ሆኖ በርቀት ትምህርቱን ይከታተል የነበረውም ይህንን ጥማቱን ለመወጣት ነበር።

ጦርነት የሰውን ሞራል የሚፈትን፣ ነገን ሳይሆን ዛሬን ልኑርበት በሚል አስተሳሰብ የምትወረርበት፣ ለብዙ ጉዳቶችና በሽታዎች ዴንታ ቢስ የምትሆንበት በመሆኑ አቻዎቹና አለቆቹ በተገኘች ትርፍ ጊዜ ወደ ሽራሮና ሽሬ እየከነፉ ከወታደሩ ጋር እየተጋፉ ሲጫረቱ እሱ ግን መሃይምነትን ይዋጋ ነበር።

ሌላው ተፈራ በሁሉም ዘንድ የሚታወቅበት ስብእና ደግሞ ብሄርን መሰረት ያደረገ አድሎ ይቁም፣ የህወሃት የበላይነት መላ ይበጅለት፣ በመንግስት ስልጣኑም ሆነ በልማቱ እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት የለም ወዘተ እያለ የሚጠይቅና የሚከራከር የነበረ መሆኑ ነው። በዚህ እምነቱ የተነሳ ማንም እየተነሳ “ትምክህተኛ፣ የትምክህት ለም መሬት፣ ነፍጠኛ፣ ዘረኛ፣ ጸረ ትግሬ” ይለው ነበር።
እኔም በተሳተፍኩበት ሁለት ስብሰባዎች (በ1994 እና 1999) ትምክህተኛ፣ ዘረኛ፣ ሁሌም ራሱን የአማራ ወኪል አድርጎ የሚቆጥር ወገኛ፣ ጸረ ትግሬ፣ የትምክህት ለም መሬት፣ ትምክህት ያለበት ቦታ ሁሉ የማይታጣ፣ የቅንጅት ተስፈኛ ወዘተ ተብሎ የተገመገመበትን ሁኔታ በሚገባ አስታውሳለሁ።

እንዲያው በጥቅሉ ኦህዴድን ሲፍቁት ኦነግ ይሆናል ይባል እንደነበረው ሁሉ ተፈራን ሲነኩትም የአማራ ትምክህተኝነት ፈጦ ይወጣበታል ይባል ነበር።
በተለይ በቅንጅት ዘመን “ቅንጅት እንዴት የዕዝ አመራር መሆን ቻለ?” እያሉ የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ይናገራሉ ተብሎ በከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ሲነቀፍ ስብሰባ ላይ ቁጭ ብየ የሰማሁበት ሁኔታ በመጪው ሰላማዊ ህይወቱ ላይ አደጋ እያንዣበበበት እንዳለ እኔ ብቻ ሳልሆን የተፈራ ወዳጆች ሁሉ ጥርጥሬ ነበር።

እውነቱን ለመናገር እንዲህ አይነት አመለካከት እያለውም ቢሆን ጀነራል ሳሞራ የኑስና የትግራይ ጀኔራሎች ተፈራ የመሰለውን ፊት ለፊት ስለሚነግረን እሱ ይሻለናል በዚበሂደት ስህተቱን ያርማል በማለት በተለይም በታችኞቹ የትግራይ ከፍተኛ መኮንኖች የሚነሳበትን ግፊት ሊከላከሉለት ይሞክሩ ነበር።

በእርግጥ የአርሶ አደር ልጅ ነው እያለ መደጋገሙ የትም አይደርስም ከሚል ስሌት ይሆን እንዴ እያልን እናወራ ነበር። ለዚያም ይመስላል ተጽእኖ የመፍጠር አቅማቸው ከፍተኛ የነበሩትን በተግባርም ያስቸግሩት የነበሩትን ሜ/ጀነራል ሃይሌ ጥላሁንና ብ/ጀነራል አሳምነው ጽጌን በቅንጅትነት ወንጅሎ በጠረባ ሲዘርራቸው ተፈራ የገበሬ ልጅ ስለሆነ ሊያሻሽላል ይችላል ትንሽ እንየው በማለት ለጊዜው አቆዩት።
ከመታሰሩ ከወራት ቀደም ሲልም ለሜ/ጀነራልነት ማእረግ እንዲሾም ሃሳብ ቀርቦ የነበረ ሲሆን የመከላከያ አዛዦች ካውንስል አባላት የነበሩት ሌ/ጀነራል አበባው ታደሰና ሜ/ጀነራል አለሙ አየለ የከረረ ተቃውሞ በማቅረባቸው ሳይሾም መቅረቱ ከታማኝ ምንጭ ተረጋግጦ ነበር። የሁለቱ ጀነራሎች የተቃውሞ ነጥብ የተለመደው ትምክህተኛ ነው የሚለውና በቅንጅትነትም የተገመገመ ነው በሚል ነበር።
እነዚህ ጀነራሎች የኢህዴን ታጋዮች የነበሩ ሲሆን የራሳቸው ሰው ላይ እየቆመሩ በአቀባባይ ከበርቴነት በማገልገል የስንቱን ህይወት አጨልመው እንጀራቸውን ይወጠወጡ እንደነበር ሁሉም ያውቃቸዋል። ለሁሉም ጊዜ አለውና እነዚህ ሁለት ጀኔራሎች በሃብት ተምነሽንሸው በመባረር ባይሆንም መስራት እየቻሉ ይብቃችሁ ተብለው ወደ ነጋዴነት ተሸጋግረዋል።

በጥቅሉ ብ/ጀነራል ተፈራ ከራስ በላይ ነፋስ የሚል አመለካከት ስላልነበረው እንጅ በግሉ የደረሰበት በደል አልነበረም። የተነሳበት አላማ ትክክል ይሁን አይሁን፣ የተከተለው የትግል ስልት አዋጭ ይሁን አይሁን ሌላ ጉዳይ ሆኖ ለግል ጥቅም ሳይሸነፍ ለመታገል መወሰኑ በራሱ ትልቅ ጀግንነት ነው ።

ብ/ጀነራል ተፈራ ሲበዛ ቅን፣ ሰው አክባሪ፣ ሁሉም በእኩል አይን እንዲታይ ትልቅ ምኞት የነበረው፣ በትልልቅ ዉጊያዎች አልፎ የተገነባ ጀግንነት፣ ስብእናና ታማኝነት ባለቤት ነበር። ተፈራ በሰራዊቱም የጦሩ ገበሬ እየተባለ ነበር የሚጠራው።

የታገልነው ለእኩልነት ስለሆነ እኩል እንታይ፣ የታገልነው ስርአታዊ አድሎን ለማስወገድ ስለሆነ አድሎ ይቁም፣ የታገልነው ሁሉም ዜጋ በህግ ፊት እኩል እንዲሆን ስለሆነ የህግ የበላይነት ይስፈን፣ የታገልነው ሁሉም ህዝብ እኩል እንዲለማ ስለሆነ ፍትሃዊ የመልማት እድል ለሁሉም እኩል ይረጋገጥ፣ በመንግስትም ሆነ በመከላከያ የሚታየው የአንድ ብሄር የበላይነት ይወገድ ስላልን ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ፣ ዘረኛ፣ ጸረ ትግሬ ማለት ልክ አይደለም ወዘተ ከማለት በቀር እንደተባለው ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ፣ ዘረኛና ጸረ ትግሬ አልነበረም።
ይቀጥላል።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s