ኢትዮዽያዊነት ማለት ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን ማለት ነው። አፍሪካዊነት ማለትም ብላቴ ጌታ ሎሬት ጸጋዬ/ ገመድህን ማለት ነው

ከሥርጉተ ሥላሴ 22.02.2017 (ዙሪክ – ሲዊዘርላንድ)

„ጥበብ፡ ፈጽማ፡ የጎላች፡ ናት፡ ሥርዓቷም፡ አይልፍም፡ የሚወዷትም፡ ሰዎች፡ ፈጥነው፡ ያዋታል፡ የሚፈልጓትም፡ ሰዎች፡ ያገኙአታል። ለሚወዷት፡ ሰዎች፡ ትደርስላቸዋለች፡ አስቀድማም፡ ትገለጥላቸዋለች። በደጃፉ፡ ስትጠብቀው፡ ሁልጊዜ፡ እርሱ፡ ያገኛታል፡ ወደርስዋ፡ የሚገሠግሥ፡ ሰው፡ አይደክምም።  እርስዋን፡ ማሰብ፡ የውቀት፡ ፍፃሜ፡ ነውና። ፈጥኖ፡ ስለርሷ፡ የሚተጋ፡ ሰው፡ ያለ፡ ሃዘን፡ ይኖራል።“ (መጽሐፈ ጥበብ ምዕራፍ 6 ቁጥር 12 እስከ 16)

ይድረስ ለቅኔው ልዑል ለብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን  – ሰማይ ቤት።

አዬ … ቀን ይሄዳል – ይጓዛል። እኛን አስቀምጦ እሱ ማንአለበት ይነጉዳል፥ ይተማል፥ መጪ ይላል። ጋሼ ጸጋዬን በሥጋ ያጣንበት ወርኃ ዬካቲት። ወርኃ የካቲት የሰማዕታት መታሰቢያ … ዛሬ እስኪ ትንሽ ስለ ቅኔው ልዑል ስለብላቴ መንፈሴ ያሰኘውን ባሻው መንገድ ይል ዘንድ ወደድኩ። እንዲህና እንዲያ …

ማን እንደአንተ ጋሼ ጸጋዬ በንጽህና እና ቅድስና ኢትዮዽያን ከውስጧ ሆኖይቃኝላት። በመሆን የከበርክ – ስለእሷ እሷን ሆነህ፤ እሷን ጠጥተህ ተመገብኽ የኖርክ ሩቅ አሳቢ፤ የተበተነን መንፈስ ሰብሳቢ፤ የአፍሪካዊነት ልዑቅ – ሊቅ፤ የሰው ዘር አፍቅሮተ ትንግርትህ  – ቀንዲልነቱ የምዕተ ዓመታት ህትምት ነው ቤተመዘክር። ደጉ የቅኔው ግሥ ፤ ሩህሩሁ ሰዋሰው፤ ጌታ ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ / መድህን፤ እንደ ስምህ በምግባርህ የከበርክ የእናት ኢትዮጵያ  የውብ ቀን መርህ

መሆንን በመሆን እንዝርት ፈትለህ ለሰንደቅህ ልዕልና ነበርክ ነገረፈጅ። ባለችሎት ቢኖር፤ የመንፈሱ አቅም ያልተንኮላሼ ቢገኝ፤ ያ … ንዑድ መንፈስህ ምንኛ የኢትዮዽያዊነት የፊደል ገበታ በሆነ ነበር? አልፈህ ተርፈህ ስለ እማማ አፍሪካ የተጨነክ – የተጠበብክ የድርጊት አንበልነበርክ። ስለእያንዳንዷ ቅንጣት አመክንዮ በጉዳዬነት የያዝክ ዝልቅ ሰው ነበርክ። ትናትን ከዛሬ፤ ዛሬን ከነገ ያዋደድክ ዬጥበብ ንጡር ናሙና። አንተ፤ አንተማ ለእኔ ህዝብ ነበርክ። መቼ ቀንጣ እንደእኔ ነበርክና። በሕዝብ ውስጥ ሆነህ ስለህዝብ የኖርክ፤ የህዝብ የፍቅር አውደ ምህረት።ሞት ክፋ ሳያራራ ነጠቀን እንጂ። አንተ ራስህ እኮ ሀገር ነህ። የኢትዮዽያዊነት እንደራሴ! የአፍሪካዊነት ጭንቅላት።

የጥቁርነት ዕንቁነት በፀዳለ ትውፊት በሙሉዑ ሥነ ባህሪ ያበራህ፤ ኢትዮዽያን ያደመቅህ፤ ያስዋብክ፤ ያፈካህ የዘለዓለም ብርሃን። ውስጥህን ሳትሳሳ፤ ለእናትህ ያለተቀናቃኝ ንጹህ ልብህን የሸለምክ፤ ብሩካዊ መንፈስህን ያለ የግለኝነት ጣውንትነት ለልዕልት ኢትዮዽያ ፍቅር ያስገዛህ – ቀንዲል። እናት ሐገራችን ኢትዮዽያ ከፍ ብላ ስትታይ፤ ሞገሷ ሲጎመራ፤ ብቃቷ በአለም አደባባ ሲናኝ፤ ልጆቿ ሲወጡላት ነበር የሐሴትምንጭ። ለዚህም በምድር በኖርክባቸው ዘመንህ ሁሉ ሁለመናዋ ነበርክ። ክብሯ፤ ሞገሷ፤ ማማዋ፤ ጸዳሏ፤ ዘመኗ! ዋስ ጠበቃዋ፤ ዋቢዋ።

ትውልድ አልፎ ትውልድ መተካቱ ተፈጥሯዊ ዶግማ ቢሆንም፤ አንተን፤ ስለእናት ሀገርህ ያለህ መወድሳዊ  ያን ረቂቅ ቅዱስ መንፈስህን ግን የሚተካ አልተገኘም። ኢትዮዽዊነት እንደ ቁጥር ትምህርት በመደመርና በመቀነስ፤ ወይንም በመዳበል፤ ወይንም እንደ ተገጣጣሚ ዕቃ ተወልቆ እንደሚገጣጠም የጋራጅ ብረታ ብረት፤ ወይንም እንደ ጭቃ ተጠፍጥፎ ወይንም ተንቦልቡሎ እንደሚሰራ ጉሽጉሻ ሆነ ዕሳቤው ሁሉ።

ይህን ስልህ ግን ቅርጹ ተሸራርፎም ቢሆንም አለ – የተሰወረብን ይዘቱ ነው። የተሰወረው ዬፍጥረተ ነገሩ ንጥረ – ቅመም የግንዛቤው ጥልቀት ግልፍተኛ መሆኑን ነው። ኢትዮዽያዊነት ማሰሪያው በዛ። ምሳሩም አዬለ።በቅድመ ሁኔታ ገመድ ተተበተበ። ይለፋ አንተ ከምታውቀው ከጸዳ የዕውነት ዕሴት መነሳት ተሳነው።

ይሄውልህ የእኛ ግርማ እንዲህ የሆነበት ነገረ ምክንያቱ አሰዋወሩ ዬፍጥረተ ነገሩ ንጥረ ቅመም – የግንዛቤው ጥልቀት – ቀመሩ ሰነፍ በመሆኑ ነው። የኢትዮዽያዊነት ዕውቅናው ዜግነት መሆኑ ቀርቶ በቅድመ ሁኔታ ተገነዘ — በገጠርና በከተማ፤ በተማረና ባልተማረ፤ በሠለጠነና ባልሰለጠነ፤ ከአማርኛ ቋንቋ ተጨማሪ ቋንቋ በማወቅና ባለማወቅ፤ በተዕባትና በአንስት፤ በክት የዘውገ አባልነትና በዘወትረ፤ በአለ ዘውገኝነትና በየምነት፤ በማኒፌስቶ ማህበርተኝነትና በአልቦሾቹ … ምኑን እነግርሃለሁ በቃ ዜግነት በዚህና በዚያ ፍዳና አሳሩን ይከፍልልኃል። ቁስለቱ  – ያመግላል፤ መስፈሪያው – ያበግናል። ለዕውነት ሱባዬ ያስይዛል። የማይሰማ፤ የማይታይ የፈተና ዓይነት የለም። የኢትዮዽያዊነት አሳሩ፤ በቦንዳ፤ በደርዘን ነው። መራር ዘመን ላይ ይገኛል፤ ዓውራው ማንነት ኢትዮዽያዊነት። ስለሆነም እማም ጎዳና ላይ ስለተጣሉት ልጆቿ አምርራ – ታለቅሳለች። አብሶ ባለቤት አልቦሾቹ ይበልጡን እጅግ የበዙ ናቸው። ሰው በመጠጥና በውኃ ብቻ አይኖር ነገር …

አንተ ተፈጥሮህ አመክንዮ፤ ጉዞህ ወደ አመክንዮ። መዳረሻህም አመክንዮ። ስለምን? ሚስጢርነትህን  የመንፈስህ ብቸኛ ሚሥጢረኛ ለማድረግ ስለፈቀድክ። በአንድ ነገር ግን መጽናናት ይቻላል። ኢትዮዽያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነውና። ወደፊትም ልብ ሞልቶ ሊያናግር የሚችለው የአመክንዮ አናት ኢትዮዽያዊነት አሸናፊ ማንነት ሆኖ ቀጣይ መሆኑ ነው። የሚያቆበቁቡ ማናቸውም ሳንኮች ሁሉ ከእግሩ ሥር ይነጠፋሉ። ኢትዮዽያዊነትን ተረግጦ የህዝብን ፍቅር ያፈሰ ማንም – ምንም ኃይል የለም። ወደፊትም አይኖርም። እዚህ ላይ በትልቁ የምጋራው የሊቀ – ሊቃውንቱ የታሪክ ሙሁር የፕሮፌሰር ኃይሌ ላሪቦን „ኢትዮዽያዊነት ረቂቅ መንፈስ ነው“ ይህ አገላለጽ እኔ ሥርጉተ ሥላሴ እንደ ዶግማ ነው የምቀበለው። የቅኔው ንጉሥ ዬብላቴ ጌታ ሎሬት ጸጋዬ ገመድህን መንፈስም ቅመሙ ይሄው ነውና።

ስለምን? በውስጤ ያለውን ረቂቅ ሙቀቱን አሳምሬ ስለማውቀው። እሱን ሳስብ ብቻ ነው አጃዬ የሚሞላው። ከእሱ ጋር ለመኖር ስፈቅድ ብቻ ነው ድንጉጥ የማልሆነው። በየትኛውም ሁኔታና ቦታ ስለእሱ ስመሰክር ብቻ ነው መንፈሴ ከዕውነተኛው ሐሴት ጋር የሚገናኘው። ስለእሱ ስናገር ብቻ ነው በሰው ሀገር ብኖርም ባለሀገር መሆኔ ድፍረት የሚኖረው። በሌላ በኩል በዚህ የስደት የዝንቅ ህይወት ውስጥ ከሌላ ሀገር ዜጎች ጋር በሚኖረኝ ማናቸውም ግንኙነቶች ሁሉ ንጽጽሩ በእርጋታ ሳስተውለው ረቂቁ ማንነቴ ኢትዮዽያዊነት የሰጠኝን ዝቀሽ ዕሴት ማገናዘብ ችየበታለሁና። የመሰደዴ ዋናው ተቋሜም እራሴን የምለካበት ወቄት ማግኘቴ ነው። እማላማርረውም ለዚህ ነው እንጂ፤ ለእኔ ተፈጥሮ ውጭ ሀገር መካን አመክንዮ ነው።

ኢትዮዽያዊነት ሊገልጹት የማይችሉት የመንፈስ እጨጌ ነው። አውልቆ ለመኖር ቢታሰብ እንኳን – የሚስብ  አንዳች ብቁ ኃይል ነገር magnet አለው። እህል ውሃው የማይለቅ ጥልቅ ማንነት ነው ኢትዮዽያዊነት። ወለሉ ዲካ ዬለሽ ነው። በመገፋፋት ውስጥ መቻቻልየነገሰበት። በመሸጋሸግ ውስጥ መዋህድ የተፋቀረበት።

ኢትዮዽያዊነት ፈተናው የዘመናት ነው፤ ግን ትብትቡን ጣጥሶ አሸናፊ ይሆናል። እሱም እንደ እናቱ አላዛር ነው። ሌላው ቀርቶ ሌት ተቀን ተቀናቃኙ እያዬለ ስለእሱ በባለቤትነት የሚከወን የታቀደ ተከታታይ ተግባር ሳይኖርግን ጎልቶ፥ ፈክቶ እጅግም ጎልብቶ ብቅ ይላልታምረኛው – ኢትዮዽያዊነት። ለዚህም ነው ሊቀ ሊቃውንቱ ፕ/ ኃይሌ ላሬቦ ቃል ቢያጡለት፤ መፍቻ ትርጉም ቢያጡለት ረቂቅ መንፈስ“ያሉት። ረቂቅ መንፈሱን መቀበልም በቅድመ ሁኔታ ከወገብ በላይና በታች መሆን አይኖርበትም፥  ከመንገድ በላይና በታችም። „ሲወዱ እስከ ንፍጥ ልጋጉ“ ይላሉ ጎንደሬዎች ሲተርቱ። ከጋብቻ በኋላ በተጋቢ ቤተሰቦች ያለውን ትርምስ በቅኔ – ሲቃኙት። ጋብቻው ሁሉ በኢትዮዽያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ከሆነ የሸሪፎ ቤተኝነትን ተከልቶ መሆን ይኖርበታል።

ስለሆነም ኢትዮዽያዊነት ሞገሴ ለሚል ተቋም፤ የፖለቲካ ድርጅት፤ ወይንም ግለሰብ ማዕቀፋ ዥንጉርጉሩንም አጽድቆ ከልብ ስለልብ ሁነኝልሁንህ ማለትን ይጠይቃል። ድፍረት! ከምላስ ርጥበት ያለፈ ሁነኛ ዬማመሳከሪያ ውስጣዊ ሰነድ። ወጀብ የማይንጠው። ዬግላዊነት ቁንጥጫ የማያሸማቅቀው።

ለዛ የኢትዮዽያዊነትን መንፈስ ጥልቅነቱን ለገለጸ አንደበትም፤ ዘመን አሻጋሪ ዶግማም፤ በትረ የትውልድ ሥህንም ክብሩን ቁልቁል ማውረድ ዘመንም ታሪክም ይቅር የማይለው፤ የህሊና ዕዳ ነው። በተለይ „ኢትዮዽያ  ለዘለዓለም በክብር  ትኑር!“ አቡነ ዘበሰማያቱ ወይንም „አላህ አክብር“ ላደረገ ተቋም፤ ድርጅት ወይንም የእኔ ቢጤ ባተሌ። የእግዚአብሄር ቃል ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ „ ይላል። ለተዋህዶ አማንያን ይህን ቃለምህዳን መጋፋታም የእርግማ ጥሪት ማጠራቀም ይመስለኛል። የጻድቃን አባቶቻችን የልፋትና የድካም ዋጋ እሾህ ሆኖ ይወጋናል።

ልዕልት ሐገራችን ኢትዮዽያ በጅምላና በችርቻሮ በንግድ የገብያ ሥርዓት የተቸረቸረች ወይንም ሱቅ ተሂዶ የተሸመተች ሀገር አይደለችም።ከፈጣሪ በታች ከእሷ ልቅና እና ልዕልና በላይ ማንም፥ ምንም ዬለም። ስለሆነም በእሷ የሚመጣ ጉዳይ ሁሉ፤ ከክብሯ አገላለጽ ውጪ ያሉ ጉዳዮች ሁሉ፤ እንደ አግባብነታቸው በመንፈሷ ሥር ሊተዳደሩና በቅጡ በብልጥነት ሳይሆን በብልህነትና በጥበብ ሊመሩ ይገባል። ንጉሥ ዳዊት „ዬቤትህ  ቅናት በላይ“ ያለው ይፈጸም ዘንድ – ዶግማውን መፍቀድ ይኖርብናል። ዬቤቷ ቅናት ሊያርመጠምጠን ይገባል። ጊዜ ያልፋል፤ ዘመን ያልፋል፤ ትውልድም ያልፋል። ኢትዮዽያ ግን ፈጽሞ አታልፍም። ለዘለዓለም ትኖራለች! አልፋና ኦሜጋ ናት። ትምክኽቷ አምላኳ ነውና።

ኢቲዮዽያዊነት መሸፈኛ፤ መጠቅለያ፤ ማሸጊያ ወረቀት መሆን አይኖርበትም። የልብ ክፍል፤ የኩላሊት ክፍል፤ ቤተ – ትልቅና ትንሽ አንጀት – ዓፄው ጭንቅላት ወዘተ … ሁሉም በአንድ ላይ በተፈጥሮ ሥርአታቸው ተግባራቸውን ሲወጡ ብቻ ነው ሰውም እንደሰው፤ ትውልድም እንደትውልድ የሚቀጥለው። ስለሆነም በኢትዮዽያዊነት ውስጥም የላይ ቤት፥ የታች ቤት ሠርቶ ስብከት ለእኔ የእንቧይ ቤት ነው። በመሆንየከበረ ኢትዮዽያዊነት ነው ነፍስን ሊገዛና ሊነዳ የሚችለው። እንደ ጌታ ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን – መሆን መቻል።

ጌታ ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን ከሊቅ እስከ ደቂቅ መንፈሱ ክብር ያልሰጠበት፤ ከውስጡ ያልተመሰጠበት ከቶ አንዳችም ብሄራዊ ጉዳይ ሆነ ማህበረሰብ የለም። ለዛውም ሰውንና ዕውነትን ማዕከል በማድረግ። ዛሬ በዘመናችን በኢትዮዽያዊነት አመክንዮ ውስጥ ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ ናሙና የምለው የስሜን አሜሪካ ዬስፖርት ፌስቲባል መሰናዶና ዕሴቱን ብቻ ነው። ወጣ ገባ አይደለም። ቀጥ ባለ ግልጽና ቀጥተኛ አቋም በየዓመቱ ብሄራዊ ሰንደቅዓላማችን ከፍ እንዲል ያደርጋል። ይህ የሰንደቅ ተጋድሎ ገድል ነው ለእኔ። ተቋሙ በብሄራዊ ዓርማችን ላይ ያለው ምራቁን የዋጠ አቋም በውስጣችን ያለውን አክብሮትና ልቅና ገላጭ – የታሪካችን ቁንጮ ነው ማለት ያስችለኛል። ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ የስሜን አሜሪካው ዓመታዊ የስፖርት ዝግጅት አድዮ አበባ ነው። ለእኔ የኢትዮዽያዊነት አዝመራ ነው። ለእኔ ባለቅኔው ጸጋዬ ገመድህን ነው። ለእኔ ጀግና አብዲሳ አጋ ነው። በአጋጣሚው ያለኝን የውስጥ ፍቅር ስገልጽ ለአዘጋጆች በሐሴት ነው።

እርገት።

በል የእኔ አባታዊ ዬሥነ ጥበብ ጌታ ጋሼ ጸጋዬ ልሰናበትህ ስለእናታችን እንወዛወዝልህአለን የንፋስ ፍጥነት መለኪያው Anemometer እንዲህና እንዲያ …

ማጠናከሪያ ጹሁፍ  …

http://www.zehabesha.com/amharic/?p=39302

የውስጥ እንደራሴ – እንደ ህዝብ … – ሥርጉተ ሥላሴ

 

ኢትዮዽያዊነት ይከበር!

መሸቢያ ጊዜ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s