የማለዳ ወግ…ታላቋን ንግስት እቴጌ ጣይቱን እናዘከር ! – ነቢዩ ሲራክ

* ” ሴት ነኝ ፣ ጦርነት አልወድም ! ነገር ግን ሃገሬ ክብር የሚነካ ዘለፋ ከምትሸለም ጦርነትን እመርጣለሁ! ”

እትጌ ጣይቱ ብጡል ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ ይባላሉ ፣ የኢትዮጵያ ብርሃን … ሁሌም እቴጌ ጣይቱ ብጡልን ሳስታውስ በአድዋ ጦርነት ዋዜማ በውጫሌው ውል ክህደት ተቆጥተው ለጣሊያን ፋሽሽት የሰጡት ምላሽ አይዘነጋንም ፣ ይህ በወኔ የተሽቆጠቆጠ ቆራጥነት ምላሽ ንግግራቸው ፣ በኩራት የሚታወስና ከአዕምሮየ የማይጠፋ ሆኖ አብሮኝ የሚኖረው በእኔ ብቻ ሳይሆን በሚሊዮኖች ልብ ነው …!

“ … የዛሬ ሳምንት አድርገው፡፡ እኔ ሴት ነኝ፡፡ ጦርነት አልወድም፤ ነገር ግን ሀገሬ እንደዚህ ያለ ክብር የሚነካ ዘለፋ ከምትሸከም ጦርነትን እመርጣለሁ፡፡ ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ! እግሩን ለጠጠር፤ ደረቱን ለጦር አስጥቶ፤ ደሙን ለሀገሩ ፍቅር አፍስሶ፤ ለአፈሩ ክብር ለብሶ፤ እሱ ወድቆ ሀገሩን የማያቆም እዚህ ያለ እንዳይመስልህ! ሂድ! የኢትዮጵያን ሰው ባታውቀው ነው፡፡ ለሀገሩ መሞት ማለት ለሀበሻ ጌጡ ነው፡፡ ሂድ ባሻህ ግዜ ተመለስ ተሰናድተን እንጠብቅሃለን፡፡ ያንተን ወንድነትና የጣይቱን ሴትነትም ያን ጊዜ እናየዋለን ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ፡፡”

እትጌ ጣይቱ ብጡል በ1851 ዓም ተወልደው በ1918 ዓም የተለዩን ጀግና እናት ናቸው ! ስመ ጋናናዋ ንግስት እትጌ ጣይቱ የዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ባለቤት ሲሆኑ የጥቁር ህዝብ ኩራት የሆነው የአድዋ ድል ሲወሳ ስም ዝናቸው ከአጽናፍ አጽናፍ አልፋና ኦሜጋ ሲነሳ የሚኖሩ እናት ናቸው! እምዬ ምኒሊክ ስልጣኔን ለሃገራቸው ሲያስተዋውቁ እትጌ ጣይቱ ቀዳሚ ምሳሌ ነበሩ ። በሐገሪቱ እንደ ነውር ይቆጠር የነበረውን ቀሚስ ለብሰው እና ሽቶ ተቀብተው ለመጀመሪያ ጊዜ አደባባይ ወጥተውም ያውቃሉ ። አዎ እቴጌ በባህል ተቀፍድዶ የነበረውን ሃገሬ በልበ ሙሉ ያስተማሩ ልበ ሙሉ ወይዘሮ ነበሩ !

መልከ መልካሟ እትጌ ጣይቱ ብጡል ለኢትዮጵያ ሴቶች እህቶቻችን አሁን ድረሰ በታላቅ አርአያነት ይጠቀሳሉ ፣ እትጌ በወቅቱ ብቸኛ የእውቀት ምንጭ በነበረው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያንን የሐይማኖት ትምህርት በአድባራቱ የቀሰሙ ፣ የግእዝ ቁዋንቁዋ አቀላጥፈው የሚናገሩ ፣ አስተዳደር አዋቂ ፣ አስተዋይና በሙዚቃውም አለም በገና መደርደር የሚያውቁ ባለ ብሩህ አዕምሮ እመቤት እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ!

ጣይቱ የአባ ዳኘው መንግሰት እንዲረጋ ፣ በብልሃት ሕዝቡንና ባለሟሎችን በመያዝ የአስተዳደሩን ያረጋጉ በመኳንንቱና በጦሩ ዘንድ ተወዳጅ ንግስት ፣ ብልህ ሴት ነበሩ ። አፄ ምኒሊክ ስልጣን በጨበጡ ማግስት “ብርሃን ዘኢትዮጵያ ” የሚል ስራቸውን ገላጭ የንግስና ክብር ስም የተሰጣቸው ንግስት እትጌ ጣይቱ ብጡል ከባላቸው ፣ ከጦር አለቆችና ከሰራዊቱ ጋር እጅ ለጅ ሆነው ተጣጥመው ሐገር መርተዋል ። በእምዬ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ለተከናወኑት ስራዎች ሁሉ ትልቅ አሻራቸውን የጣሉት ንግስት ጣይቱ ብጡል ከሐገር ስልጣኔ እስከ መስፋፋትና ዋና ዋና ተጠቃሽ የምኒሊክ ክንውኖች ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው ።

እትጌ ፈጣሪ ነገር ሆኑ በአብራካቸው ልጅ ለማፍራት ባይታደሉም የተቸገሩትንና ያጡትን በመደገፍ ይታወቃሉ ። እትጌ በአድዋው ዘመቻ ጦሩን በማነቃቃት ከፍተኛውን ሚና መጫወታቸው በታሪክ ተደጋግሞ ተጠቅሷል ። ከድል በኋላ ሐገር ረግቶ እምየ ምኒሊክ ታመው ሲደካክሙ አስተዳደሩን በመምራት ባላቸውን በማማከር ሀገሯን በእጅ አዙር ያስተዳድሩ የነበሩ እመቤት ናቸው ! የመጨረሻ አመታት የአባ ዳኘው እምየ ምኒሊክ መዳካከም እና መታመም ሲጀመወሩ የባለቤታቸው የአፄ ምንሊክ ብቸኛ አማካሪ ሆነው አገሪቱን በእጅ አዙር አስተዳድረዋል፣ ለሃገራቸው ታምነው እምየ ምኒሌክን በክብር የሸኙ ጠንካራ ንግስት ነበሩ ፣ ጣይቱ ብጡል !

እምዬ ምኒሊክ ባረፉ ማግስት ግን በዙሪያው ያሉ መኳንንትና ሹማምንት በእትጌ ላይ አሴሩ ፣ ብዙ የክፋት ሙከራ በጦሩ ድጋፍ ባይሳካም ብርቱዋ ንግስት እትጌ ጣይቱ በንግስና ይኖሩበት ከነበረው ቤተ መንግስቱን በአሻጥር እንዲለቁ ተደረገ ። ብዙም ሳይቆይ በግዳጅ ወደ በፊቱ የእንጦጦ ቤተ መንግስታቸው ተወስደው ከማንኛውም የመንግሰት ውሳኔ ተከልክለው እስከ ህልፈታቸው እዚያው ኖሩ ነ !
በግዞት ባሉበት በእንጦጦው ቤተ መንግሰታቸው እአአ በ1918 ዓም በ67 አመታቸው በውስጠ ደዌ በሽታ ከዚህ ከንቱ አለም ተለዩ ! በቀጣይም ትውልድ ውለታቸውን እያወሳ በክብር እያዘከረ ያወድሳቸዋል !

ክብር ከሚገባው ክብር እሰጣለሁ !

ነቢዩ ሲራክ
የካቲት 18 ቀን 2009 ዓም

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s