ድርድሩ – ይገረም አለሙ

መንደርደሪያ ፤ ብዙ ግዜ አዲስ ያልሆኑ ግን እኛ አዲስ የተፈጠሩ ያህል የምንጮህባቸው ነገሮች ሲከሰቱ ብዙዎች የሚያሳዩት ነገር “የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል” ይሉ አይነት ነው፡፡ ወያኔ ሥልጣኔን ያሰነብትልኛል ብሎ እስካመነ የማይቆፍረው ጉድጓድ እንደሌለ እየታወቀ  ድርድር ጠራ ተብሎ  ተቀዋሚ ተብየዎችም ጥሪውን ተቀብሉ  ተብሎ አዲስ ተአምር የተፈጠረ ይመስል ድጋፍና ተቃውሞ በተለመደው መንገድ እየተሰማ ነው ነው፡፡ ነገር ግን ከተለመደውና መረጃም ማስረጃም ፍለጋ ከማያደክመው የፍረጃና ውንጀላ ጉዞ ወጣ ብሎ ድርድር ለምን፣  ድርድር በእነማን መካከል፣ ድርድር እንዴትና በምን ሁኔታ? ወዘተ የሚሉት ጥያቄዎች መመለስ የሚችል አስተያየት መጻፉ፣ ልምድ ማካፈሉ ነበር የሚበጀው፡፡ እኔ ይህን ለማድረግ የሚበቃ እውቀትም ልምድም የለኝም፡፡ ፍረጃና ውንጀላ ላይ በመሮጥም ሆነ ጭፍን ድጋፍ በመስጠት  ደግሞ አላምንም፣ በዚህ መካከል ሆኜ ስለ ድርድሩ የተሰማኝን  ልበል፡፡

ድረድር፣  ለድርደር ምክንያት የሆነው ጉዳይ ምንነት፣  የተደራዳሪዎቹ ማንነት፣ የድርድሩ ሂደት አንዴትነት ወዘተ ቢለያይም  ዙሪያ ጥምጥም ገለጻ ውስጥ ሳይገባ ድርድር ሰጥቶ መቀበል ነው፡፡ ትንሽ የያዘው ወይንም ምንም የሌለው የሚፈልግበት፣ ብዙ የያዘው የሚሰጥበት፡፡ በመሆኑም ያየዘውን ወዶና ፈቅዱ የሚሰጥ “ቅዱስ ፖለቲከኛ” የለምና   ያለ አስገዳጅ ሁኔታ በውዴታና በፈቃደኝነት ወደ ድርደር መድረስ አይቻልም፡፡ አሁን የሚወራለት ድርድር ይካሄዳል የሚባለው ሁሉንም ጠቅሎ በያዘውና የሚሰጠውም የማይሰጠውም በብዛት ባለው ወያኔና በየግልም በጋራም ምንም ባልያዙና ምንም የሚሰጡት ነገር በሌላቸው ተቀዋሚዎች መካከል ነው፡፡ (ይቅርታ ይደረግልኝና የድርድሩ ተካፋይ የተባሉትን ፓርቲ ብሎ ለመጥራት አንደበቴ፣ ለመጻፍ ጣቶቼ እሽ አይሉኝም፡፡ ምክንያቴ ደግሞ ለድርጅቶቹ ወይንም ለመሪዎቹ ጥላቻ ኖሮኝ ሳይሆን ፓርቲ ለመባል የማይበቁ በመሆናቸው ነው፡፡) ስለ መስጠት መቀበሉ ከማየታችን ቀደም ግን እዚህ ደረጃ እንዴትና በምን ምክንያት ተደረሰ የሚለውን ማየቱ ይበጃል፡፡

የድርድሩ ምክንያት የህዝብ እንቢተኝነት፡፡  ወያኔ የድርድር ጥሪ ያቀረበው በመላ ሀገሪቱ በተለይ ደግሞ በኦሮምያና በአማራ ክልሎች በተቀጣጠለው የህዝብ ቁጣና እንቢተኝነት በደረሰበት ድንጋጤ መሆኑን ወያኔዎችም ቢሆን የሚክዱት አይመስለኝም፡፡ በማሰር፣ በመግደል፣ በማስፈራራት አመጹን መግታት አልቻሉም፤ የሀያ አመስት አመት ብሶት ነውና ፡፡ የሚመጻደቁበትን ህገ መንግሥት ጣጥለው በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ስም ወታደራዊ አገዛዝ አሰፈኑ፤ ለወያኔ ከሥልጣን የሚብስ ነገር የለምና፡፡ ይህን ሁሉ ቢያደርጉም የህዝቡን ተቃውሞ አጥፍተው ሥልጣናቸው ሲረጋጋ አልታይ አላቸውና “ጅብን ሲወጉ በአህያ ተከልሎ ነው” እንዲሉ ተቀዋሚ ተብየዎችን ተጠቅመው የህዝቡን ተቃውሞ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ እናጠፋለን ብለው ተነሱ፡፡ ይህን ሀሰት የሚል ይኖር ይሆን? ካለ በጽሞና እንነጋገር፡፡

ወያኔን ለድርደር ያንበረከከው የህዝብ ትግል በህይወትም በአካልም አያሌ መስዋዕትነት ተከፍሎበታል፡፡ የድርድሩ አብይ ፈተና የሚመጣው እዚህ ጋር ነው፡፡ ምክንያትም ወያኔ ህዝብ መስዋዕትነት የከፈለበትን ጥያቄ መመለስ አይችልም፣ተቀዋሚ ተብየዎቹ ደግሞ ( ስም አጣሁላቸውና ተቸገርኩ) ለህዝቡ ጥያቄ መልስ የማስገኘት ፖለቲካዊ አቅም አይደለም ጥያቄውን ይዞ ለመደራደር የሞራል ብቃት የላቸውም፡፡ አረ እኔ አለሁ የሚል ካለ በጩኸትና በዘለፋ ሳይሆን በሚታይ በሚዳሰስ ማስረጃ ያሳየን፡፡

ወያኔ ለምን ይደራደራል፡ ወያኔ ተገዶም ቢሆን ለምን ወደ ድርድር መምጣት እንደፈለገ ለሁሉም ሰው ግልጽ ነውና ብዙ የሚያነጋግር አይመስለኝም፡፡ አንደኛውና የመጀመሪያው ምክንያት ከአዋጅ በፊትም ሆነ በአዋጅ መግደል ማሳሩ የህዝቡን ተቃውሞ ሊያዳፍነው ካልሆነ በስተቀር ጨርሶ ሊያጠፋው እንዳልቻለ ማየቱ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የግዜ ጉዳይ ነው አንጂ ተቃውሞው በተመሳሳይ ሁኔታ መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡  ታዲያ በየግዜው የህዝብ ቁጣ እየተነሳበት በለመደው መንገድ እየገደለ በአንድ በኩል ውግዘትና ወቀሳ እያስተናገደ ከመኖር፣በሌላ በኩል ደግሞ ከሥልጣን ሲወርድ የሚጠየቅበትን የወንጀል ክምችት እየበዛ  ከሚቀጥል የህዝብን ተቀዋሞ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ለማጥፋት ነው፡፡ ይሄ ይችላል? አሁን ከመተንበይ ግዜው አጭር ስለሆነ ጠብቆ ማየቱ ይሻላል፡፡ ሌላው በኃያላኑ መንግሥታት የገንዘብ እርዳታና ብድር እንዲሁም የዲፕሎማሲ ድጋፍ የቆመ በመሆኑ ሰላም ፈላጊ ችግርን፣ በዴሞክራሲያዊ አግባብ በሰላም የሚፈታ፣ ከተቀዋሚዎቹ ጋር የሚነጋገር መስሎ በመታየት ድጋፉን ማስቀጠል መቻል ነው፡፡ ድርድሩ ከቀጠለ ይህ እንደሚሳካለት የሚያጠራጥር አይመስለኝም፡፡ ሌላው ተቀዋሚዎችን አፍ ማስያዝ፣ ቁርጥ ያለ ዓላማ፣ እምነትና አቋም የሌላቸውን ተቀዋሚ ነን ባዮች ደግሞ (በውጪም በውስጥም ያሉ) ሲሆን በአባልነት፣ ካልሆነም በደጋፊነት ማሰልፍ መቻል የድርድሩ አንዱ ዓላማ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡

ተቀዋሚዎች ለምን ይደራደራሉ፤ የሚሰጡት የሌላቸው፣ ወያኔን ወደ ድርድር ባመጣው የህዝብ ትግል ውስጥ ጠብታ አስተዋጽኦ ያልነበራቸው፤ በተናጠል ፓርቲ ለመባል የማይበቁ፣ በጋራ፣ የጋራ የመደራደሪያ አጀንዳ ቀርጾ ለመቅረብ የሚያስችል የትግል አንድነትም ሆነ የአንድ ሀገር ልጅነት ፍቅር የሌላቸው ምን ለማትረፍ ነው ወደ ድርድሩ መድረክ ያመሩት ብሎ መጠየቁ ተገቢ ቢሆንም እንደ ስማቸው ፍላጎታቸው የበዛ እንደ ብዛታቸው መልካቸው የተዥጎረጎረ ነውና አንድ ወጥ የሆነ ምላሽ ማግኘት የዳግታል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ምላሽ መፈለግ ግድ ነውና ለመልሱ መንደርደሪያ ወይንም በር ከፋች ጥያቄ ይቅደም፡፡

የሚደራደሩት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ለማስገኘት ወይንስ የየግል ፍላጎታቸውን ለማርካት? የመጀመሪያው ከባድ የሚባል ብቻ ሳይሆን የማይሞክሩት ነው፡፡ ምክንያቱም የህዝቡ ጥያቄ የሥርዓት ለውጥ ነውና፡፡ ሁለተኛው ግን በጣም ቀላል ነው፡፡ መለስ ፍለጋውን ከቀላሉ እንጀምር፡፡

ወያኔ በፓርላማው ስራ መጀመሪያ ቀን በፕሬዝዳንቱ አንደበት ያስነገረውን “የፓርላማ ወንበር በችሮታ አንሰጣለን” የሚል መልእክት ያለው ንግግር የሚረሳ ያለ አይመስለኝም፡፡ በተነገረው መሰረት የምርጫ ህጉን በማሻሻል ( ይህን ህግ ለማሻሻል ህገ መንግሥቱን ማሻሻል ቢያስፈልግም ወያኔ ለዚህ ግድ የለውም) ፓርላማ በመገኘት ባለመገኘታቸው በወያኔ ላይ ምንም የማያመጡትን ሰዎች ወደ ፓርላማ መግቢያ በር በድርድሩ ካሳያቸው፣ በጣም ቸር ልሁን ካለ ደግሞ የተወሰኑቱ የምኒስትርነትም ባይሆን የምክትልነት ሹመት በዚህ ድርድር ማትረፍ አንደሚችሉ ካሳያቸው በወያኔ ድርጎ የሚተዳደሩ ወትሮም ከህዝብ ጋር ጉዳይ የላቸውምና “ምኞቴ ተሳካ ያሰብኩት ደረሰ” የሚለውን የጥላሁን ገሰሰን ዜፈን እያዜሙ ድርድሩ በስኬት ተጠናቀቀ፣ ኢህዴግ ለሀገርና ለህዝብ አሳቢነቱን ”

ለድረድር ከቀረቡት መካከል  ሌላው ቢቀር ቤት ኪራይ የሚከፍልልንን ደጋፊ እንዳናጣ ብለው የሚሰጉና በእምቢተኝነት የፖለቲካ ትርፍም እናገኛለን ብለው የሚያስቡ ቢገኙና በዚህ መንገድ አንደራደርም፣ ይሄን ይሄን አንቀበልም ፣በዚህ መልክ ችግሩ በዘለቄታ  አይፈታም ወዘተ ለማለት ከቻሉ ብዙም አይሆኑምና በጸረ ሰላምነት ተወግዘው፣ በድርድር አደናቃፊነት ተከሰው፣ ከዛም አልፎ የሌሎችን ተልእኮ አንግበው የመጡ የሚል ሰም ተሰጥቶአቸው አፋቸውን ለጉመው፣ እግር ከወርች ታስረው በሚኖሩበት ቢሮአቸው መመሸግ ነው፡፡

አሁን ወደ ከባዱ ጥያቄ እንመለስ፡ ህዝቡ የጠየቀው የሥርዓት ለውጥ በመጀመሪያ በአጀንዳነት ሊመዘገብ አይችልም ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል፡ ከወያኔ ባህርይ አንጻር፡፡ ምክንያት ወያኔ ሰማይ መሬቱን የሚቧጥጠው ሥልጣኑን ለማጥበቅ እንጂ ለመልቀቅ ምን አደከመው፡፡ ተደራዳሪ ተብየዎቹስ ይህ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ  መጀመሪያ ፍላጎቱ፣ ቀጥሎ ዝግጅቱ፣ ከዛስ  አጀንዳ አንዲሆን የማስገደድ የተናጠል ብቃቱ የጋራ  ህብረቱ አላቸው? ከየት መጥቶ! እናም ጉዳይ እዚሁ ላይ ያበቃል፡፡የተደራዳሪዎችም ፍላጎትና ማንነት እዚሁ ጋር ይታወቃል፡፡ “የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል ይሉ አይነቱ ጭፍን ድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ፍረጃና ውንጀላው አሁን ተገቢ የማይሆነው ለዚህ ነው፡፡

የድርድሩ የመጨረሻ ውጤት ዜሮ ነው፡  ድርደሩ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ለወያኔ  ርዳታና ብድሩ አንዳይነጥፍ፣ የዲፕሎማሲ ድጋፉ እንዳይቆም ሊያደርግለት ይችል ይሆናል፣ ችግሮችን በውይይት የሚፈታ፣ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ህገ መንግሥትን እስከ መሻሻል  ድረስ የሚሄድ፤ ለተቀዋሚዎቹ ወንበር ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ የመሳሰሉ ቅታያዎችና ማደመቂያዎች ተጨምረውበት  ገጽታ ግንባታ ለሚባለው  የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ፍጆታ ሊጠቅመው  ይችል ይሆናል፤ የትግላቸው መነሻም ሆነ መድረሻ የራስ ጥቅም ለሆኑ በተቀዋሚ ካባ ለሚንቀሳቀሱትም ትንሽ ትንሽ የሥልጣንም የገንዘብም ፍርፋሪ ሊያስገኝላቸው ይችል ይሆናል፡፡ (አሁን ከሚሰጣቸው ዳረጎት በተጨማሪ)

እንዲሁም የእነርሱ ፓርላማ መግባት የኢትዮጵያዉያን ችግር መፍትሄ ማግኘት ለሚመስላቸው ወይንም አድርገው ለሚያስቡ (ይህ ከዚህ ቀደም በተግባር ያየነው ነው)  በመጪው ምርጫ ተወዳድረው አሸንፈው ሳይሆን በችሮታ ፓርላማ የሚገቡበትን መንገድ ሊያመቻችላቸው ይችል ይሆናል፡፡ሌላም ሌላም ፤

ወያኔና ተደራዳሪዎች እንዲህ በየመጠናቸው ከድርድሩ ሊያተርፉ ይችላሉ ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ትርፍ እናገኛለን ሳይባል ሳታሰብና ሳይታቀድ አይደከምምና፡፡ የድርድሩ ምክንያት የሆነው በህይወትና በአካል መስዋዕትነት ወያኔን ወደ ድርድር ያመጣው ህዝብ ግን ጥያቄውን የሚመልስለት አይደለም ለጉዳቱ ካሳ የሚሆነው አንዳችም ነገር አያገኝም፡፡ ይሄ ነው አንግዲህ የድርድሩን ውጤት ዜሮ የሚያደርገው፡፡  እንደ እስራት ግድያውና የአስቸኳይ አዋጁ ድርድሩም  የህዝቡን ጥያቄ መመለስም ተቃውሞን ከነአካቴው ማጥፋትም አያስችልምና፡፡

በመጨረሻ፤ ለመሆኑ ድርድር ከተባለ መደረግ ያለበት ከመንግሥት ጋር ነው ወይንስ ከኢህአዴግ ጋር፡፡ ወያኔ የመንግሥትና የድርጅት ኮፍውን ሲሻው የሚቀላቅለው ሲፈልግ የሚለያየው ለእኩይ ተግባሩ መጠቀሚያ ሲል ነው፡፡ እንደውም አቶ መለስ በተካኑበት የማደናገሪያ ስልት ተከታዮቻችውንም እኛንም ሊያደናግሩ የድርጅታቸው አንዱ ችግር የድርጅትና የፓርቲ ኮፍያ ማደባለቅ አንደሆነ ነግረውን ነበር፡፡ “ፖለቲከኞቻችንስ” ኢህዴግ ማለት መንግሥት፣ መንግሥት ማለት ኢህአዴግ ነው ብለው አምነው ተቀብለው ነው ፡፡

ትክክል የሚባል ነገር ከጠፋ አመታ ተቆጠሩ እንጂ ትክክለኛው ነገር ወያኔም እንበለው ኢህአዴግ ፓርቲ ነው፤ እውነተኛ (አቅም፣ ብቃት፣ የዓላማ ጽናትና ግልጽነት ያለው ) ተቀዋሚ ቢኖር ፓርቲ ከፓርቲ ጋር መፎካከር መወዳደር እንጂ መደራደር የለም፡፡መደራደር ከመንግሥት ጋር ነው፡፡ እዚህ ጋር ኢህዴግንና መንግሥትን ምን ለያቸው የምትለው የተለመደች  ነገር አንደምትነሳ እገምታለሁ ፡፡እኔም ጥያቄ አለኝ እነርሱ የሚሉትንና የሚያደርጉትን ነው መከተል ያለብን ወይንስ ትክክል የምንለውን?

ቸር አንሰንበት

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s